‘ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት’
“ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን?”—ማርቆስ 11:17
1. አዳምና ሔዋን በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ነበራቸው?
አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ከሰማያዊ አባታቸው ጋር የተቀራረበ ዝምድና ነበራቸው። ይሖዋ አምላክ በቀጥታ ከእነርሱ ጋር በመነጋገር ለሰው ዘር ያለውን አስደናቂ ዓላማ ገልጾላቸዋል። ብዙውን ጊዜ ዕፁብ ድንቅ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ይሖዋን ለማወደስ ይገፋፉ እንደነበር አያጠራጥርም። አዳምና ሔዋን ወደፊት የሰብዓዊው ቤተሰብ ወላጆች በመሆን የሚያከናውኑትን ተግባር በተመለከተ መመሪያ ለማግኘት በገነቲቷ መኖሪያቸው ውስጥ በየትኛውም ቦታ ሆነው አምላክን ሊያነጋግሩት ይችሉ ነበር። እነርሱ በቤተ መቅደስ ውስጥ የክህነት አገልግሎት የሚያቀርብ ካህን አያስፈልጋቸውም ነበር።—ዘፍጥረት 1:28
2. አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ምን ለውጥ ተከሰተ?
2 አንድ ዓመፀኛ መልአክ ለሔዋን “እንደ እግዚአብሔር” ትሆኛለሽ ብሎ በመናገር በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ማመፅ የተሻለ ሕይወት ያስገኝልኛል ብላ እንድታስብ በማድረግ ሲያታልላት ሁኔታው ተለወጠ። ሔዋን ውሸቱን በማመኗ አምላክ እንዳይበሉ ከከለከላቸው ዛፍ ፍሬ በላች። ከዚያም ሰይጣን ባልዋን ለመፈተን በራሷ በሔዋን ተጠቀመ። የሚያሳዝነው አዳም ኃጢአተኛ ሚስቱን በመስማት ከአምላክ ወዳጅነት ይልቅ የእርሷ ዝምድና እንደሚበልጥበት አሳየ። (ዘፍጥረት 3:4-7) በተዘዋዋሪ መንገድ አዳምና ሔዋን ሰይጣን አምላካቸው እንዲሆን መረጡ።—ከ2 ቆሮንቶስ 4:4 ጋር አወዳድር።
3. የአዳምና ሔዋን ዓመፅ ያስከተላቸው አስከፊ ውጤቶች ምንድን ናቸው?
3 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲህ በማድረጋቸው ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ውድ ዝምድና ብቻ ሳይሆን በምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጥተዋል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ኃጢአተኛ ሥጋቸው ቀስ በቀስ እየደከመ ሄዶ በመጨረሻ ሞቱ። ዘሮቻቸውም ይህን የኃጢአተኛነት ሁኔታ ወርሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደዚሁም . . . ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ይገልጻል።—ሮሜ 5:12
4. አምላክ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ምን ተስፋ ዘርግቷል?
4 ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ከቅዱሱ ፈጣሪያቸው ጋር ለማስታረቅ አንድ ነገር ያስፈልግ ነበር። አምላክ በአዳምና ሔዋን ላይ ብያኔውን ባሳለፈበት ወቅት የሰውን ዘር የሰይጣን ዓመፅ ካስከተላቸው ውጤቶች የሚያድን አንድ “ዘር” እንደሚመጣ ቃል በመግባት ለመጪዎቹ ልጆቻቸው ተስፋ ሰጠ። (ዘፍጥረት 3:15) ከጊዜ በኋላም አምላክ የበረከት ምንጭ የሆነው ዘር በአብርሃም በኩል እንደሚመጣ ተናገረ። (ዘፍጥረት 22:18) አምላክ ይህን ፍቅራዊ ዓላማ በአእምሮው በመያዝ የአብርሃም ዝርያ የሆኑት እስራኤላውያን የእርሱ ምርጥ ሕዝብ እንዲሆኑ ለይቷቸዋል።
5. አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ስለገባው የሕግ ቃል ኪዳን ዝርዝር የማወቅ ጉጉት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
5 እስራኤላውያን በ1513 ከዘአበ ከአምላክ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና በመመሥረት ሕግጋቱን ለመታዘዝ ተስማሙ። የሕጉ ቃል ኪዳን የተስፋውን ዘር የሚጠቁም በመሆኑ በዛሬው ጊዜ አምላክን ለማምለክ የሚፈልጉ ሁሉ ስለዚህ ቃል ኪዳን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ሊኖራቸው ይገባል። ጳውሎስ ‘ሊመጣ ላለው በጎ ነገር ጥላ’ እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብራውያን 10:1) ጳውሎስ ይህን ሲል በተንቀሳቃሽ የመገናኛ ድንኳን ወይም የአምልኮ ድንኳን ውስጥ የነበሩ የእስራኤል ካህናት ስለሚያቀርቡት አገልግሎት መናገሩ ነበር። የመገናኛው ድንኳን ‘የይሖዋ ቤተ መቅደስ’ ወይም ‘የይሖዋ ቤት’ ተብሎ ይጠራ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:9, 24) በይሖዋ ምድራዊ ቤት ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ቅዱስ አገልግሎት ስንመረምር ዛሬ ያሉ ኃጢአተኛ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሊታረቁ ስለሚችሉበት የምሕረት ዝግጅት ይበልጥ በተሟላ መልኩ ልንረዳ እንችላለን።
ቅድስተ ቅዱሳን
6. በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የነበረው ነገር ምንድን ነው? የአምላክን መገኘት የሚወክለው ነገር ምን ነበር?
6 መጽሐፍ ቅዱስ “ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም” ይላል። (ሥራ 7:48) ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ በሚጠራው በውስጠኛ ክፍል ደመና መታየቱ አምላክ በምድራዊ ቤቱ መገኘቱን የሚያመለክት ነበር። (ዘሌዋውያን 16:2) ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው በደመናው ውስጥ ያለው ደማቅ ብርሃን ቅድስተ ቅዱሳኑን በሙሉ ወገግ አድርጎ ያበራው ነበር። ይህ ደመና አምላክ ለእስራኤል የሰጣቸው ጥቂት ትእዛዛት የተቀረጹባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ከያዘው ‘የምሥክሩ ታቦት’ ተብሎ ከሚጠራው ቅዱስ ሣጥን በላይ ያርፍ ነበር። በታቦቱ ክዳን ላይ በአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸውን መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚያመለክቱ ክንፋቸውን የዘረጉ ሁለት የወርቅ ኪሩቦች ነበሩ። ብርሃን የሚሰጠው ተዓምራዊ ደመና የሚገኘው ከታቦቱ ክዳን በላይ በኪሩቦች መካከል ነበር። (ዘጸአት 25:22) ይህም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕያዋን ኪሩቦች በሚሸከሙት ሰማያዊ ሰረገላ ላይ መቀመጡን የሚያመለክት ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:18) ይህም ‘በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ’ በማለት ንጉሥ ሕዝቅያስ የጸለየበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል።—ኢሳይያስ 37:16
ቅድስት
7. ቅድስት ተብሎ በሚጠራው ክፍል ውስጥ ምን ነገሮች ነበሩ?
7 የመገናኛው ድንኳን ሁለተኛው ክፍል ቅድስት ተብሎ ይጠራ ነበር። በዚህ ክፍል ውስጥ ከመግቢያው በስተግራ በኩል ሰባት ጡት ያለው ውብ መቅረዝና በስተቀኝ ደግሞ የገጸ ኅብስት ገበታው ይገኝ ነበር። ከፊት ለፊት የዕጣኑ ጣፋጭ ሽታ የሚያርግበት መሠዊያ ነበር። መሠዊያው የተቀመጠው ቅድስት ተብሎ የሚጠራውን ክፍል ከቅድስተ ቅዱሳን ከሚለየው መጋረጃ ፊት ነበር።
8. ካህናት በቅድስቱ ውስጥ ዘወትር ያከናውኗቸው የነበሩት ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
8 በየዕለቱ ጠዋትና ማታ አንድ ካህን ወደ መገናኛው ድንኳን እየገባ በዕጣኑ መሠዊያው ላይ ዕጣን ማጤስ ነበረበት። (ዘጸአት 30:7, 8) ጠዋት ዕጣን በሚጨስበት ወቅት ከወርቅ በተሠራው መቅረዝ ላይ የሚገኙት ሰባት መብራቶች ዘይት ይሞሉ ነበር። መብራቶቹ ማታ ለቅድስቱ እንዲያበሩ ይለኮሳሉ። አንድ ካህን በእያንዳንዱ ሰንበት በገጸ ኅብስት ገበታው ላይ 12 ትኩስ ኅብስቶች ማኖር ነበረበት።—ዘሌዋውያን 24:4-8
አደባባዩ
9. በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያለው ውኃ ለምን የሚያገለግል ነበር? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 ከዚህም በተጨማሪ የመገናኛው ድንኳን በጨርቅ አጥር የተከለለ አደባባይ ነበረው። በዚህ አደባባይ ውስጥ ካህናቱ ወደ ቅድስት ከመግባታቸው በፊት እጃቸውንና እግራቸውን የሚታጠቡበት ትልቅ ሰን ነበር። እንዲሁም በአደባባዩ በሚገኘው መሠዊያ ላይ መሥዋዕቶችን ከማቅረባቸው በፊት መታጠብ ነበረባቸው። (ዘጸአት 30:18-21) ይህ የንጽሕና ብቃት በአሁኑ ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የሚያቀርቡት አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለጉ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ መጣር እንዳለባቸው ጠንካራ ማሳሰቢያ ይሆንላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ከጊዜ በኋላ ለመሠዊያው እሳት የሚሆን እንጨትና መታጠቢያው ሰን ውስጥ የሚጨመረውን ውኃ የሚያቀርቡት እስራኤላውያን ያልሆኑ የቤተ መቅደስ ባሪያዎች ነበሩ።—ኢያሱ 9:27
10. በመሠዊያው ላይ የሚቀርቡት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ነበሩ?
10 በእያንዳንዱ ዕለት ጠዋትና ማታ አንድ የመሥዋዕት ጠቦት ከእህልና ከመጠጥ ቁርባን ጋር በመሠዊያው ይቃጠል ነበር። (ዘጸአት 29:38-41) ሌሎች መሥዋዕቶች የሚቀርቡባቸውም ለየት ያሉ ጊዜያት ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ግለሰብ በግሉ ለፈጸመው ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 5:5, 6) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አንድ እስራኤላዊ በውዴታው የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር፤ ካህናቱና መሥዋዕቱን ያቀረበው ሰው ከዚህ መሥዋዕት የተወሰነውን ክፍል ይበላሉ። ይህም ኃጢአተኛ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላም ሊኖራቸውና በምሳሌያዊ አነጋገር ከእርሱ ጋር አንድ ማዕድ ሊካፈሉ እንደሚችሉ ያመለክታል። ሌላው ቀርቶ አንድ መጻተኛ እንኳ የይሖዋ አምላኪ መሆንና በራሱ ፈቃደኛነት በቤቱም መሥዋዕት የማቅረብ መብት ማግኘት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ተገቢውን አክብሮት ለማሳየት ካህናቱ የሚቀበሉት ምርጥ የሆኑትን መሥዋዕቶች ብቻ ነበር። የእህሉ ቁርባን የላመ ዱቄት መሆን የነበረበት ሲሆን የእንስሳት መሥዋዕቶቹ ደግሞ እንከን የለሽ መሆን ነበረባቸው።—ዘሌዋውያን 2:1፤ 22:18-20፤ ሚልክያስ 1:6-8
11. (ሀ) በእንስሳት መሥዋዕቱ ደም ምን ይደረግ ነበር? ይህስ ምን የሚያመለክት ነበር? (ለ) አምላክ ለሰዎችና ለእንስሳት ደም ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
11 የእነዚህ መሥዋዕቶች ደም በመሠዊያው ላይ ይቀርብ ነበር። ይህም የእስራኤል ብሔር ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ደሙን አፍስሶ ኃጢአታቸውን ለዘለቄታው የሚያስተሰርይና ከሞት የሚያድናቸው ተቤዥ እንደሚያስፈልጋቸው ያስታውሳቸው ነበር። (ሮሜ 7:24, 25፤ ገላትያ 3:24፤ ከዕብራውያን 10:3 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ደም ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ መዋሉ እስራኤላውያን ደም ሕይወትን እንደሚወክልና ሕይወትም የአምላክ እንደሆነ እንዲያስታውሱ የሚያደርጋቸው ነበር። አምላክ መቼውንም ቢሆን ሰዎች ደምን በማናቸውም ሌላ መንገድ እንዲጠቀሙበት ፈቅዶ አያውቅም።—ዘፍጥረት 9:4፤ ዘሌዋውያን 17:10-12፤ ሥራ 15:28, 29
የስርየት ቀን
12, 13. (ሀ) የስርየት ቀን ምን ነበር? (ለ) ሊቀ ካህናቱ ደሙን ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ምን ማድረግ ነበረበት?
12 በዓመት አንድ ጊዜ የስርየት ቀን ተብሎ በሚጠራው ዕለት ይሖዋን የሚያመልኩ መጻተኞችን ጨምሮ መላው የእስራኤል ብሔር ከማንኛውም ዓይነት ሥራ ነጻ መሆንና መጾም ነበረበት። (ዘሌዋውያን 16:29, 30) በዚህ ታላቅ ቀን ብሔሩ ለቀጣዩ አንድ ዓመት ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ዝምድና ለማግኘት እንዲችል ለመጪው ነገር ጥላ በሚሆን መንገድ ከኃጢአቱ ይነጻ ነበር። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን በመመልከት ጎላ ብለው የሚታዩትን አንዳንዶቹን ገጽታዎች እንመርምር።
13 ሊቀ ካህናቱ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ ነው። በተጠራቀመው ውኃ ከታጠበ በኋላ ለመሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ያርዳል። የወይፈኑ ደም በሳህን ይቀመጣል፤ ይህም የሌዊ የካህናት ነገድ የኃጢአት ስርየት እንዲያገኝ ለየት ባለ መንገድ ጥቅም ላይ ይውላል። (ዘሌዋውያን 16:4, 6, 11) ይሁን እንጂ አምላክ የእነዚህን ልዩ መሥዋዕቶች ደም እንዲቀበል ሊቀ ካህናቱ በመሥዋዕቱ ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ሊያደርገው የሚገባ ነገር ነበር። መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን ይይዝና (በጭልፋ ላይ ሳይሆን አይቀርም) ከመሠዊያው ላይ በጥናው ፍም ይወስዳል። ከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ይገባና ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ ያመራል። በዝግታ በመጋረጃው በኩል ዞሮ ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይቆማል። ከዚያ ከሌሎች ሰዎች ዕይታ ውጭ ሆኖ ዕጣኑን በእሳቱ ፍም ላይ ሲያደርግ ቅድስተ ቅዱሳኑ ጣፋጭ ሽታ ባለው የጢስ ደመና ይሞላል።—ዘሌዋውያን 16:12, 13
14. ሊቀ ካህናቱ የሁለት የተለያዩ እንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚኖርበት ለምንድን ነበር?
14 ከዚህ በኋላ አምላክ ለመጪው ነገር ጥላ በሚሆን መንገድ ምሕረት ለማሳየትም ሆነ የሥርየት ልመናውን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል። በዚህ ምክንያት የታቦቱ ክዳን “የምሕረት መቀመጫ” ወይም “የስርየት መክደኛ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዕብራውያን 9:5 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ሊቀ ካህኑ ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወጥቶ የወይፈኑን ደም ይይዝና ተመልሶ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል። በሕጉ ውስጥ እንደታዘዘው ጣቱን በደሙ ውስጥ እየነከረ ከታቦቱ መክደኛ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። (ዘሌዋውያን 16:14) ከዚያም ወደ አደባባዩ ይመለስና ‘ለሕዝቡ’ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን ፍየል ያርዳል። ከፍየሉ ደም ጥቂት ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት በወይፈኑ ደም እንዳደረገው እንዲሁ ያደርጋል። (ዘሌዋውያን 16:15) በስርየት ቀን ሌሎች ዓቢይ አገልግሎቶችም ይከናወኑ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሊቀ ካህናቱ በሁለተኛው ፍየል ራስ ላይ እጁን ጭኖ “የእስራኤልን ልጆች በደል” መናዘዝ ነበረበት። ከዚያ በኋላ የሕዝቡን ኃጢአት በምሳሌያዊ መንገድ እንዲሸከም ከነሕይወቱ ወደ በረሃ ተወስዶ ይለቀቃል። በዚህ መንገድ በየዓመቱ “ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ” ስርየት ይደረጋል።—ዘሌዋውያን 16:16, 21, 22, 33
15. (ሀ) የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከመገናኛው ድንኳን ጋር ተመሳሳይ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደስ ይከናወን ስለ ነበረው አገልግሎት የዕብራውያን መጽሐፍ ምን ይላል?
15 እስራኤላውያን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ሆነው ባሳለፏቸው የመጀመሪያዎቹ 486 ዓመታት ውስጥ ተንቀሳቃሹ የመገናኛ ድንኳን አምላካቸውን ይሖዋን የሚያመልኩበት ቦታ ሆኖላቸው ነበር። ከዚያም እስራኤላዊው ሰሎሞን በቋሚነት የሚያገለግል አንድ ሕንፃ የመሥራት መብት አገኘ። ይህ ቤተ መቅደስ ከመገናኛው ድንኳን ይበልጥ ሰፊና ያማረ ቢሆንም የንድፉ ምንጭ መለኮታዊ በመሆኑ ከቀድሞው ጋር አንድ ዓይነት ሥርዓት የተከተለ ነበር። እንደ መገናኛው ድንኳን ሁሉ ‘ሰው ሳይሆን ይሖዋ ራሱ ለተከለው’ ታላቅና ይበልጥ ውጤታማ ለሆነው የአምልኮ ዝግጅት ጥላ ነበር።—ዕብራውያን 8:2, 5፤ 9:9, 11
የመጀመሪያውና ሁለተኛው ቤተ መቅደስ
16. (ሀ) ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለአምላክ አገልግሎት በሚወስንበት ጊዜ ያቀረበው ፍቅራዊ ልመና ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የሰሎሞንን ጸሎት እንደተቀበለ ያሳየው እንዴት ነበር?
16 ሰሎሞን የመጀመሪያውን ክብራማ ቤተ መቅደስ ለአምላክ አገልግሎት እንዲወሰን ባደረገበት ጊዜ በመንፈስ አነሳሽነት የሚከተለውን ልመና አቅርቦ ነበር፦ “ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ . . . ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፣ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፣ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፣ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፣ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።” (2 ዜና መዋዕል 6:32, 33) ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን ያቀረበውን ጸሎት እንደ ተቀበለው አምላክ በግልጽ አሳይቷል። እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ የነበረውን የእንስሳ መሥዋዕት ከመብላቱም በላይ የይሖዋ ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው።—2 ዜና መዋዕል 7:1-3
17. ሰሎሞን የሠራው ቤተ መቅደስ ከጊዜ በኋላ ምን ደረሰበት? ለምንስ?
17 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን ለይሖዋ የነበራቸውን ጤናማ ፍርሃት አጡ። ከጊዜ በኋላ ደም በማፍሰስ፣ በጣዖት አምልኮ፣ በምንዝር፣ ከቅርብ ዘመዶች ጋር የጾታ ብልግና በመፈጸም እንዲሁም ወላጆች የሌላቸውን ልጆች፣ ባልቴቶችንና መጻተኞችን በማንገላታት ታላቁን ስሙን አረከሱ። (ሕዝቅኤል 22:2, 3, 7, 11, 12, 26, 29) በዚህም ምክንያት አምላክ በ607 ከዘአበ የባቢሎናውያን ሠራዊት ቤተ መቅደሱን እንዲያጠፉ በማድረግ የቅጣት ፍርዱን አስፈጸመ። በሕይወት የተረፉት እስራኤላውያንም በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።
18. የይሖዋን አምልኮ በሙሉ ልባቸው ለሚደግፉ እስራኤላውያን ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ሲሠራ ምን መብት ተከፍቶላቸው ነበር?
18 ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከ70 ዓመታት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና የመገንባት መብት አገኙ። የሚያስገርመው በዚህ በሁለተኛው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ በቂ ካህናትና ሌዋውያን አልነበሩም። ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያን ካልሆኑ የቤተ መቅደስ ባሪያዎች ልጆች የተወለዱት ናታኒሞች በአምላክ ቤት ውስጥ የማገልገል ትልቅ መብት ተሰጣቸው። ሆኖም ፈጽሞ ከካህናትና ሌዋውያን ጋር የሚተካከሉ አልነበሩም።—ዕዝራ 7:24፤ 8:17, 20
19. አምላክ ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቶ ነበር? እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነበር?
19 በመጀመሪያ አካባቢ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ከቀድሞው ጋር ሲወዳደር የተናቀ መስሎ ይታይ ነበር። (ሐጌ 2:3) ሆኖም ይሖዋ “አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፣ . . . ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል” የሚል ተስፋ ሰጠ። (ሐጌ 2:7, 9) በትንቢቱ ፍጻሜ መሠረት ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ከመጀመሪያው የበለጠ ክብር አግኝቷል። ከመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ዕድሜ በ164 ዓመታት የሚበልጥ ሲሆን ከሌሎች ብዙ አገሮች የተውጣጡ ብዙ አምላኪዎች ወደ አደባባዮቹ ጎርፈዋል። (ከሥራ 2:5-11 ጋር አወዳድር።) የሁለተኛው ቤተ መቅደስ እድሳት የተጀመረው በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ሲሆን በዚህ ወቅት አደባባዮቹ እንዲሰፉ ተደርገዋል። ቤተ መቅደሱ የተሠራው ከመሬት በጣም ከፍ ብሎ በተገነባ የድንጋይ መሠረት ላይ ከመሆኑም ሌላ ዙሪያው ውብ በሆኑ አምዶች የተከበበ በመሆኑ ሰሎሞን ከሠራው የመጀመሪያ ቤተ መቅደስ የማይተናነስ ግርማ ነበረው። ከውጭ በኩል ይሖዋን ለማምለክ ከተለያዩ ብሔራት ለሚመጡ ሰዎች የተዘጋጀ ትልቅ አደባባይ ነበረው። ይህን የአሕዛብ አደባባይና ለእስራኤላውያን ብቻ የሚፈቀደውን ውስጠኛውን አደባባይ የሚለይ የግንብ ግድግዳ ነበር።
20. (ሀ) እንደገና የተገነባው ቤተ መቅደስ ምን የላቀ ክብር አግኝቷል? (ለ) አይሁዳውያን ለቤተ መቅደሱ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? ኢየሱስስ ለዚህ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?
20 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቤተ መቅደስ አደባባዮች ቆሞ በማስተማሩ ይህ ሁለተኛ ቤተ መቅደስ የላቀ ክብር አግኝቷል። ሆኖም አይሁዳውያን በጥቅሉ እንደ መጀመሪያው ቤተ መቅደስ ሁሉ የአምላክ ቤት ባለ አደራዎች እንዲሆኑ ለተሰጣቸው መብት ትክክለኛ አመለካከት አልነበራቸውም። እንዲያውም በአሕዛብ አደባባይ መካከል ነጋዴዎች ንግዳቸውን እንዲያጧጥፉ ፈቅደውላቸው ነበር። ከዚህም በላይ በኢየሩሳሌም በኩል ዕቃ ተሸክመው የሚሄዱ ሰዎችም በቤተ መቅደሱ አቋርጠው እንዲያልፉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ አራት ቀናት ቀደም ብሎ ቤተ መቅደሱን እነዚህን ከመሰሉ መንፈሳዊ ያልሆኑ ተግባሮች ካጸዳ በኋላ “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” ብሏል።—ማርቆስ 11:15-17
አምላክ ምድራዊ ቤቱን ለዘላለም ትቶታል
21. የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ኢየሱስ የጠቆመው ነገር ምንድን ነው?
21 ኢየሱስ የአምላክን ንጹሕ አምልኮ ለመጠበቅ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዱ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሊገድሉት ቆርጠው ተነሱ። (ማርቆስ 11:18) ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚገደል ስላወቀ ለአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:37, 38) በዚህ መንገድ በምድራዊው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሚቀርበው አምልኮ በአምላክ ፊት ተቀባይነት የሚያጣባት ጊዜ በጣም እንደቀረበ አመልክቷል። “ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት” መሆኑ ያከትማል። ደቀ መዛሙርቱ ዕፁብ ድንቅ ስለ ነበረው የቤተ መቅደስ ሕንፃ ባነሡለት ጊዜ ኢየሱስ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? . . . ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።”—ማቴዎስ 24:1, 2
22. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ የተናገራቸው ቃላት የተፈጸሙት እንዴት ነበር? (ለ) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በምድራዊ ከተማ ላይ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ምንን ይጠባባቁ ነበር?
22 ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እዘአ የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ባጠፋ ጊዜ የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ በእርግጥም አምላክ ለመጪው ነገር ጥላ ሆኖ ያገለገለውን ቤቱን እንደተወ የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነበር። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሌላ ቤተ መቅደስ እንዲሚገነባ ፈጽሞ አልተነበየም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህችን ምድራዊ ከተማ በተመለከተ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፣ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን” ብሏል። (ዕብራውያን 13:14) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ‘የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም’ ማለትም ከተማ መሰል የሆነችው የአምላክ መንግሥት ክፍል ለመሆን ተጠባብቀዋል። (ዕብራውያን 12:22) በዚህ መንገድ የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ በምድር ላይ የሚገኝን አንድ ቤተ መቅደስ ማዕከል ያደረገ መሆኑ አከተመ። በሚቀጥለው ርዕስ ሥር አምላክ እርሱን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ያቋቋመውን ታላቅ ዝግጅት እንመለከታለን።—ዮሐንስ 4:21, 24
የክለሣ ጥያቄዎች
◻ አዳምና ሔዋን ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ምን ዓይነት ዝምድና አጡ?
◻ ስለ መገናኛው ድንኳን ገጽታዎች ለማወቅ ጉጉት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ ከሚከናወኑት ነገሮች ምን እንማራለን?
◻ አምላክ የገዛ ቤተ መቅደሱ እንዲጠፋ የፈቀደው ለምንድን ነበር?
[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሄሮድስ እንደገና የሠራው ቤተ መቅደስ
1. ቅድስተ ቅዱሳን
2. ቅድስት
3. የሚቃጠል መሥዋዕት ማሳረጊያ
4. ኩሬ
5. የካህናት ሸንጎ
6. የእስራኤል ሸንጎ
7. የሴቶች ሸንጎ