ከይሖዋ ድርጅት ጋር በታማኝነት ማገልገል
“ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ።”—2 ሳሙኤል 22:26 NW
1, 2. ሁላችንም በጉባኤ ውስጥ ልናያቸው የምንችላቸው አንዳንድ ታማኝነትን የሚያሳዩ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
ምሽቱ እየገፋ ሄዷል፣ ሆኖም አንድ ሽማግሌ ቁጭ ብሎ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የሚያቀርበውን ንግግር ይዘጋጃል። ዝግጅቱን አቁሞ ትንሽ ቢዝናና ደስ ይለው ነበር፤ ነገር ግን የመንጋውን ልብ የሚነኩና የሚያበረታቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችንና ምሳሌዎችን መፈለጉን ቀጥሏል። ስብሰባው በሚደረግበት ምሽት ላይ ደግሞ በዚያው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ድካም የተጫጫናቸው ባልና ሚስት ምሽቱን በቤታቸው ቢያሳልፉ ደስ ባላቸው ነበር፤ ሆኖም እንደምንም ድካማቸውን ተቋቁመው ልጆቻቸውን አዘገጃጅተው ወደ ስብሰባው ይሄዳሉ። ስብሰባው እንዳለቀ ጥቂት ክርስቲያኖች ሰብሰብ ብለው ሽማግሌው ስላቀረበው ክፍል ይወያያሉ። በዚህ መሀል አንዲት እህት ይህ ወንድም ራሱ አንድ ቀን ስሜቷን ጎድቶት እንደነበር ለመናገር ተፈትና ነበር፤ ነገር ግን ከጠቀሳቸው ነጥቦች መካከል አንዱን አንስታ በአንድናቆት ትናገራለች። እነዚህን ነገሮች የሚያዛምዳቸው ምን እንደሆነ አስተውለሃልን?
2 ታማኝነት ነው። ሽማግሌው የአምላክን መንጋ ለማገልገል በታማኝነት ይሠራል፤ እነዚያ ወላጆች በታማኝነት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ፤ ያቺ እህት በታማኝነት ሽማግሌዎችን ትደግፋለች። (ዕብራውያን 10:24, 25፤ 13:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:2) አዎን፣ የአምላክ ሕዝቦች በሁሉም የኑሮ ዘርፎች ከይሖዋ ድርጅት ጋር በታማኝነት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ እናስተውላለን።
3. ለይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ያለንን ታማኝነት መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ ከላይ ሆኖ ይህን ብልሹ ዓለም ሲመለከተው ቅንጣት ታክል እንኳ ታማኝነት አያገኝበትም። (ሚክያስ 7:2 NW) ሕዝቦቹ የሚያሳዩትን ታማኝነት ሲመለከት ልቡ ምንኛ በደስታ ይሞላል! አዎን፣ እናንተ የምታሳዩት ታማኝነት ደስ ያሰኘዋል። ይሁን እንጂ ይህ ታማኝነት የመጀመሪያውን ዓመፀኛ ሰይጣንን ያስቆጣዋል፤ ሐሰተኛ መሆኑንም ያረጋግጣል። (ምሳሌ 27:11፤ ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን ለይሖዋና ለድርጅቱ ያላችሁን ታማኝነት ለመሸርሸር እንደሚሞክር አትዘንጉ። ሰይጣን ይህን ለማድረግ የሚጠቀምባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት። ከዚህ ጥናት እስከ መጨረሻ ድረስ ታማኝ ሆነን መቆየት የምንችልበትም መንገድ የበለጠ ማስተዋልም እንችል ይሆናል።—2 ቆሮንቶስ 2:11
በሌሎች አለፍጽምና ላይ ማተኮር ታማኝነታችንን ሊሸረሽረው ይችላል
4. (ሀ) በኃላፊነት ቦታ ላይ ስላሉት ወንድሞች አሉታዊ አስተሳሰብ ማሳደር ቀላል የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቆሬ ለይሖዋ ድርጅት የነበረውን ታማኝነት ያጎደለው እንዴት ነው?
4 አንድ ወንድም ኃላፊነት ካለው የሚሠራቸው ስህተቶች ይበልጥ ግልጽ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። ‘በገዛ ዓይናችን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ሳናስተውል በሌላው ወንድማችን ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ’ መልቀም እንዴት ቀላል ነው! (ማቴዎስ 7:1-5) ይሁንና ሌሎች ስለፈጸሙት ስህተት ማውጠንጠን ታማኝነት ማጉደልን ሊያስከትል ይችላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በቆሬና በዳዊት መካከል የነበረውን ልዩነት እንመልከት። ቆሬ ብዙ ኃላፊነት የነበረው ሰው ሲሆን ለብዙ ዓመታትም በታማኝነት ሳያገለግል አልቀረም፤ ይሁንና ከፍተኛ የሥልጣን ጥማት አደረበት። በአጎቱ ልጆች በሙሴና በአሮን ሥልጣን ደስ አልተሰኘም። ሙሴ በምድር ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ትሑት የነበረ ቢሆንም ቆሬ እርሱን በክፉ ዓይን መመልከት ጀምሮ ነበር። ሙሴ አንዳንድ ነገሮችን ሲሳሳት ሊያየው እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሙሴ ስህተት ስለፈጸመ ቆሬ ለይሖዋ ድርጅት ያለውን ታማኝነት ማጉደል አለበት ማለት አልነበረም። ቆሬ ከጉባኤው መካከል እንዲጠፋ ተደርጓል።—ዘኁልቁ 12:3፤ 16:11, 31-33
5. ዳዊት በሳኦል ላይ ለማመፅ ተፈትኖ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
5 በአንጻሩ ደግሞ ዳዊት በንጉሥ ሳኦል ሥር ሆኖ ያገለግል ነበር። በአንድ ወቅት ጥሩ ንጉሥ የነበረው ሳኦል ክፉ ሰው ሆነ። ዳዊት፣ ቅንዓት ያቃጠለው ሳኦል የሚሰነዝርበትን ጥቃት ለመወጣት እምነትና ጽናት ብሎም ብልህነት አስፈልጎት ነበር። ሆኖም ዳዊት መበቀል የሚችልበትን አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ ይሖዋ በቀባው ሰው ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም ‘በይሖዋ ፊት የማይታሰብ ነገር’ እንደሆነ ተናግሯል።—1 ሳሙኤል 26:11
6. በሽማግሌዎች ላይ ድክመትና ስህተት ብናገኝም እንኳ ፈጽሞ ምን ልናደርግ አይገባም?
6 በመካከላችን ቀዳሚ ሆነው ከሚያገለግሉት ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ የተሳሳተ ውሳኔ እንዳደረጉ ቢሰማን፣ ሸካራ ቃላት ቢናገሩ፣ ወይም አድሎ እንዳሳዩ ቢሰማን ስለ እነርሱ በማማረር በጉባኤ ውስጥ የነቀፋ መንፈስ እንዲዛመት እናደርጋለንን? ተቃውሟችንን ለማሳየት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንርቃለንን? እንዲህ እንደማናደርግ የታወቀ ነው! ሌሎች የሚሠሩት ስህተት ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለንን ታማኝነት እንድናጎድል ምክንያት እንዲሆነን ባለመፍቀድ የዳዊትን ምሳሌ እንከተል!—መዝሙር 119:165
7. በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘ ተስፋፍተው የነበሩት ብልሹ ድርጊቶች ምንድን ናቸው? ስለዚህስ ጉዳይ ኢየሱስ ምን ተሰምቶት ነበር?
7 በታማኝነት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በትንቢትም የይሖዋ ‘ታማኝ’ ተብሎ ተገልጿል። (መዝሙር 16:10 NW) በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ብልሹ ለሆነ ተግባር መዋሉ ታማኝነትን ፈታኝ አድርጎት መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ የሊቀ ካህናቱ ሥራና መሥዋዕቶቹ የእርሱን አገልግሎትና መሥዋዕታዊ ሞት እንደሚያመለክቱ ያውቅ ስለ ነበር ሕዝቡ ከእነዚህ ነገሮች መማራቸው የግድ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ቤተ መቅደሱን “የወንበዶች ዋሻ” እንዳደረጉት ሲመለከት በጽድቅ ቁጣ ተሞልቶ ነበር። አምላክ በሰጠው ሥልጣን በመጠቀም ሁለት ጊዜ ቤተ መቅደሱን የማጽዳት እርምጃ ወስዷል።a—ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:15-17
8. (ሀ) ኢየሱስ ለቤተ መቅደሱ ዝግጅት ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋን ንጹሕ ከሆነው ድርጅቱ ጋር ተባብረን ማገልገላችንን እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ያም ሆኖ ኢየሱስ የቤተ መቅደሱን ዝግጅት በታማኝነት ደግፏል። ከልጅነቱ አንስቶ በቤተ መቅደስ በሚደረጉት ክብረ በዓሎች ላይ ይገኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጊዜም አስተምሮበታል። የቤተ መቅደስ ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ያልነበረበት ቢሆንም ከፍሏል። (ማቴዎስ 17:24-27) ድኻዋ መበለት በቤተ መቅደሱ የገንዘብ ማስቀመጫ ዕቃ ውስጥ “ትዳርዋን ሁሉ” በመጣልዋ ኢየሱስ አመስግኗታል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በዚህ ቤተ መቅደስ መጠቀሙን አቁሟል። ይሁን እንጂ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ኢየሱስ ለዚህ ቤተ መቅደስ ታማኝ ነበረ። (ማርቆስ 12:41-44፤ ማቴዎስ 23:38) ዛሬ ያለው የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ከአይሁድ ሥርዓትም ሆነ በዚያ ከነበረው ቤተ መቅደስ እጅግ የላቀ ነው። ፍጹም አለመሆኑ የማይካድ ነገር ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ማስተካከያዎች የሚደረጉትም ለዚህ ነው። ሆኖም በብልሹ ምግባር የጎደፈ አይደለም፤ ይሖዋም ቢሆን በሌላ አይተካውም። በዚህ ድርጅት ውስጥ የምናየው አለፍጽምና እንድንመረር ወይም የተቺነትና አሉታዊ አስተሳሰብ እንድንይዝ እንዲያደርገን ፈጽሞ ልንፈቅድለት አይገባም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ታማኝነት እንኮርጅ።—1 ጴጥሮስ 2:21
የራሳችን አለፍጽምና
9, 10. (ሀ) የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት በአለፍጽምናችን ተጠቅሞ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚያደርገን እንዴት ነው? (ለ) አንድ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ምን ማድረግ ይገባዋል?
9 ሰይጣን የራሳችንን አለፍጽምና በመጠቀምም ታማኝነታችንን እንድናጎድል ለማድረግ ይሞክራል። የእርሱ የነገሮች ሥርዓት በይሖዋ ዓይን መጥፎ የሆነውን ነገር እንድንሠራ በድካማችን ይፈትነናል። የሚያሳዝነው በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በጾታ ብልግና ይወድቃሉ። አንዳንዶች የሥነ ምግባር ብልግና እየፈጸሙም የታመኑ ክርስቲያኖች መስለው እንዲታዩ የሚያደርጋቸውን ሁለት ዓይነት ኑሮ በመኖር በኃጢአት ድርጊታቸው ይቀጥላሉ። አንዲት ወጣት ይህን ርዕሰ ጉዳይ በሚመለከት “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው የንቁ! መጽሔት ዓምድ ሥር ስለወጡት ርዕሶች ስትገልጽ “በእነዚህ ርዕሶች ላይ የሚወጡት የእኔ የሕይወት ታሪኮች ናቸው” ስትል ጽፋለች። ይሖዋን ከማይወዱ ወጣቶች ጋር በምሥጢር ወዳጅነት አበጅታ ነበር። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ሕይወቴ ከንቱ ሆነ፣ የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸሜ ምክንያት በጉባኤ ተግሳጽ ተሰጠኝ። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ተበላሸ፤ በወላጆቼና በሽማግሌዎች ዘንድ የነበረኝ አመኔታ ጠፋ።”b
10 ይህች ወጣት ከሽማግሌዎች እርዳታ በማግኘቷ እንደገና ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል በቅታለች። ይሁንና የሚያሳዝነው ብዙዎች የከፉ ችግሮች ይገጥሟቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ወደ መንጋው ሳይመለሱ ጠፍተው ይቀራሉ። ታማኝ ሆኖ የዚህን ክፉ ዓለም ፈተናዎች መቋቋሙ ምንኛ የተሻለ ነው! ዓለማዊ ጓደኝነትንና ወራዳ መዝናኛዎችን በሚመለከት በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ማስጠንቀቂያዎች ተከተሉ። መቼውንም ቢሆን ታማኝነታችሁን ለሚያጎድል ድርጊት እጃችሁን አትስጡ። ብትሸነፉ እንኳ ያልሆናችሁትን መስላችሁ ለመገኘት አትሞክሩ። (መዝሙር 26:4 NW) ከዚህ ይልቅ እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ክርስቲያን ወላጆችና ሽማግሌዎች ሁልጊዜ እናንተን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።—ያዕቆብ 5:14
11. ራሳችንን ምንም ዋጋ እንደሌለው መጥፎ ሰው አድርገን መመልከታችን ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው? አመለካከታችንንስ ለማረም የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሊረዳን ይችላል?
11 አለፍጽምናችን በሌላም መንገድ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል። ታማኝነታቸውን የሚያጎድፍ ድርጊት የፈጸሙ አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠው ይሖዋን ለማስደሰት መጣጣራቸውን ያቆማሉ። ዳዊት ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ እንደነበር አስታውሱ። ይሁንና ዳዊት ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንኳ ይሖዋ የታመነ አገልጋይ እንደሆነ አድርጎ አስታውሶታል። (ዕብራውያን 11:32፤ 12:1) ለምን? ምክንያቱም ይሖዋን ለማስደሰት ከመጣጣር ወደኋላ አላለም። ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፣ ይነሣማል” ይላል። በሚታገለን የሥጋ ድካም ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ እንኳ በጥቃቅን ኃጢአቶች ብንወድቅ ‘መነሣታችንን’ ከቀጠልን ማለትም ከልባችን ንስሐ ገብተን የታማኝነት አገልግሎታችንን ከቀጠልን በይሖዋ ዓይን እንደ ጻድቅ ልንቆጠር እንችል ይሆናል።—ከ2 ቆሮንቶስ 2:7 ጋር አወዳድር።
በረቀቀ መንገድ ታማኝነታችሁን ከሚያጎድፉ ነገሮች ራሳችሁን ጠብቁ!
12. ግትር አቋምና ሕግ አጥባቂነት ፈሪሳውያንን ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ወደመፈጸም የመራቸው እንዴት ነው?
12 በረቀቀ መንገድ ታማኝነታችንን የሚያጎድፍ ነገር ሊገጥመን ይችላል። እንዲያውም ታማኝነት መስሎ ሊታየን ይችላል! ለምሳሌ ያህል በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ራሳቸውን በጣም ከፍተኛ የታማኝነት ደረጃ ያላቸው ሰዎች አድርገው ገምተው ይሆናል።c ሆኖም ግትሮችና ጭፍን አምባገነኖች በመሆናቸው ታማኝ በመሆንና በግትርነት ሰው ሠራሽ ሕጎችን የሙጥኝ በማለት መካከል ያለውን ልዩነት ሳያስተውሉ ቀርተዋል። (ከመክብብ 7:16 ጋር አወዳድር።) ከዚህ አንጻር ሲታዩ ሊያገለግሉት ይገባቸው ለነበረው ሕዝብ፣ እናስተምረዋለን ለሚሉት ለሕጉ መንፈስና ለይሖዋ ጭምር ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በፍቅር ላይ ለተመሠረተው ሕግ መንፈስ ታማኝ ነበር። መሲሑን አስመልክተው ከተነገሩት ትንቢቶች ጋር በመስማማት ሌሎችን አንጿል፣ አበረታቷል።—ኢሳይያስ 42:3፤ 50:4፤ 61:1, 2
13. (ሀ) ክርስቲያን ወላጆች ታማኝነት የጎደላቸው ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሳጽ በሚሰጡበት ጊዜ ከልክ በላይ ሸካራ፣ ተቺ ወይም አሉታዊ መሆን የማይገባቸው ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተወው አርዓያ በተወሰነ መጠን ሥልጣን ያላቸውን ክርስቲያኖች በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። ለምሳሌ ያህል ታማኝ ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሳጽ መስጠት እንዳለባቸው ያውቃሉ። (ምሳሌ 13:24) ሆኖም በቁጣ ገንፍለው ወይም የነቀፋ ውርጅብኝ በማዝነብ በሚሰጡት ተግሳጽ ልጆቻቸውን እንዳያበሳጯቸው ይጠነቀቃሉ። ወላጆቻቸውን ፈጽሞ ማስደሰት እንደማይቻል የሚሰማቸው ወይም አምልኳቸው አሉታዊና ስህተት ፈላጊዎች ከማድረግ ሌላ ለወላጆቻቸው ምንም እንዳልፈየደላቸው የሚሰማቸው ልጆች ልባቸው ሊዝልና በመጨረሻም ከእውነተኛው እምነት እንዲርቁ ሊያደርጋቸው ይችላል።—ቆላስይስ 3:21
14. ክርስቲያን እረኞች ለሚያገለግሉት መንጋ ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ሊሆን ይችላል?
14 በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መንጋው የሚገጥመውን ችግርና አደጋ በትኩረት ይከታተላሉ። ታማኝ እረኞች እንደመሆናቸው መጠን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በመጀመሪያ እውነታውን በትክክል ካረጋገጡ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስና በማኅበሩ ጽሑፎች ላይ በመመርኮዝ ምክር ይሰጣሉ። (መዝሙር 119:105፤ ምሳሌ 18:13) በተጨማሪም በጎቹ፣ በመንፈሳዊ ያንጹናል ይመግቡናል ብለውም እንደሚታመኑባቸው ያውቃሉ። በመሆኑም የመልካሙን እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ለመኮረጅ ይጣጣራሉ። በመንቀፍ ሳይሆን በማነጽ እንዲሁም እምነታቸውን በማጠናከር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከሳምንት ሳምንት በጎቹን በታማኝነት ያገለግላሉ።—ማቴዎስ 20:28፤ ኤፌሶን 4:11, 12፤ ዕብራውያን 13:20, 21
15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንዶች ያለቦታው ታማኝነት ያሳዩት እንዴት ነበር?
15 ሌላው በረቀቀ መንገድ ታማኝነታችንን የሚያጎድፈው ነገር ያለቦታው ታማኝነት ማሳየት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ዓይነት እውነተኛ ታማኝነት ለይሖዋ አምላክ ካለን ታማኝነት አስበልጠን የምናየው ሌላ ምንም ነገር እንዲኖር አይፈቅድልንም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን የሙሴን ሕግና የአይሁድን የነገሮች ሥርዓት ሙጭጭ አድርገው ይዘው አንለቅም ብለው ነበር። ሆኖም ይሖዋ በረከቱን ከዓመፀኛው ብሔር ወስዶ ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን ብሔር የሚሰጥበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የተገኙትና ከዚህ በጣም ወሳኝ ለውጥ ጋር ራሳቸውን ያስማሙት በአንፃራዊ ሁኔታ በጣም ጥቂት ነበሩ። በክርስቲያኖች መካከል እንኳ ሳይቀር ስለ አይሁድ እምነት የሚከራከሩ አንዳንዶች በክርስቶስ ፍጻሜውን ባገኘው የሙሴ ሕግ ውስጥ ወዳሉት ‘ደካማና የሚናቁ የመጀመሪያ ትምህርቶች’ ካልተመለስን ብለው ይሟገቱ ነበር።—ገላትያ 4:9፤ 5:6-12፤ ፊልጵስዩስ 3:2, 3
16. ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ማስተካከያዎች ሲደረጉ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
16 ከዚህ በተቃራኒ በአሁኑ ዘመን ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ለውጥ በተደረጉባቸው ጊዜያት ሁሉ ታማኝ መሆናቸውን አሳይተዋል። የእውነት ብርሃን እየደመቀ በሄደ ቁጥር ማስተካከያዎች ይደረጋሉ። (ምሳሌ 4:18) በቅርቡ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በማቴዎስ 24:34 ላይ ስለተገለጸው “ትውልድ” ስለሚለው ቃል ያለን ግንዛቤና በማቴዎስ ምዕራፍ 25:31-46 ላይ የተጠቀሱት “በጎች” እና “ፍየሎች” ፍርድ ስለሚያገኙበት ጊዜ እንዲሁም ስለ አንዳንድ ዓይነት የሲቪል አገልግሎቶች ያለንን አመለካከት እንድናጠራ ረድቶናል። (ማቴዎስ 24:45) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በግትርነት ስለ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ቀደም ሲል የነበረውን ሐሳብ ሙጭጭ አድርገው ቢቀሩና መሻሻል ለማድረግ እምቢተኞች ቢሆኑ ኖሮ አንዳንድ ከሃዲዎች ደስ እንደሚላቸው ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም እንዲህ ያለ ነገር አልታየም። ለምን? የይሖዋ ሕዝቦች ታማኞች ናቸው።
17. የምንወዳቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ታማኝነታችንን ሊፈትኑት የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ያለቦታው ታማኝነት ማሳየት በግለሰብ ደረጃም ሊነካን ይችላል። የቅርብ ወዳጃችን ወይም ደግሞ አንድ የቤተሰባችን አባል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚቃረን ጎዳና ለመከተል በሚመርጥበት ጊዜ በሁለት ወገን ታማኝነት ለማሳየት በመጣር አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባን ይሰማን ይሆናል። ለቤተሰባችን አባላት የታማኝነት ስሜት ማሳየታችን የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር ያለንን ትስስር ለይሖዋ ካለን ታማኝነት ማስበለጥ አይገባንም! (ከ1 ሳሙኤል 23:16-18 ጋር አወዳድር።) ኃጢአት የፈጸሙት ሰዎች የሠሩትን ከባድ ኃጢአት እንዲደብቁ አንረዳቸውም፤ እንዲሁም ‘በየዋህነት መንፈስ ሊያቀኗቸው’ የሚጥሩትን ሽማግሌዎች በመቃወም ከእነርሱ ጎን አንወግንም። (ገላትያ 6:1) እንዲህ ማድረግ ለይሖዋ፣ ለድርጅቱ እና ለምንወዳቸውም ሰዎች ታማኝ አለመሆን ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ተግሳጽ እንዳያገኝ መከላከል የይሖዋን የፍቅር መግለጫ እንዳያገኝ ከማገድ ተለይቶ አይታይም። (ዕብራውያን 12:5-7) “የወዳጅ ማቁሰል የታመነ” እንደሆነ አትርሱ። (ምሳሌ 27:6) በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ቀጥተኛና ፍቅራዊ ምክር ኃጢአት የፈጸመውን ወዳጃችንን ስሜት ሊያቆስል ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ለወደፊቱ ሕይወት አድን ሊሆንለት ይችላል!
ታማኝነት ስደትን ይቋቋማል
18, 19. (ሀ) አክዓብ፣ ናቡቴ ምን እንዲያደርግለት ፈልጎ ነበር? ናቡቴ እምቢ ያለውስ ለምንድን ነው? (ለ) ናቡቴ ለታማኝነቱ ሲል ይህን ያክል ዋጋ መክፈሉ ተገቢ ነበርን? አብራራ።
18 አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን በታማኝነታችን ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት ቀጥተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል በናቡቴ ላይ የደረሰበትን ሁኔታ ተመልከት። ንጉሥ አክዓብ የወይን ቦታውን እንዲሸጥ ባስጨነቀው ጊዜ “የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ” ሲል መለሰለት። (1 ነገሥት 20:3) ናቡቴ ይህን ሲል ታማኝ መሆኑ እንጂ እምቢተኛ መሆኑ አልነበረም። የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ርስታቸውን ለዘለቄታው መሸጥ እንደሌለባቸው ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:23-28) አክዓብ በሚስቱ በኤልዛቤል አማካኝነት ብዙዎቹን የይሖዋን ነቢያት አስገድሎ ስለነበር ናቡቴ ይህ ጨካኝ ንጉሥ ሊያስገድለው እንደሚችል ያውቅ ነበር! ይሁን እንጂ ናቡቴ ጽኑ አቋም ወሰደ።—1 ነገሥት 18:4
19 ታማኝነት አንዳንድ ጊዜ መሥዋዕትነት ይጠይቃል። ኤልዛቤል ‘ምናምንቴ ሰዎችን’ ሰብስባ ናቡቴ ባልፈጸመው ወንጀል እንዲከሰስ አደረገች። በዚህም ምክንያት እርሱና ልጆቹ በሙሉ ተገደሉ። (1 ነገሥት 20:7-16፤ 2 ነገሥት 9:26) ይህ ናቡቴ ያሳየው ታማኝነት የተሳሳተ እንደነበር ያረጋግጣልን? አያረጋግጥም! በአሁኑ ጊዜ ናቡቴ በይሖዋ የማስታወሻ ማኅደር ‘ሕያው’ ሆነው ከሚገኙት ብዙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዱ በመሆን እስከ ትንሣኤ ድረስ በሰላም አንቀላፍቶ ይገኛል።—ሉቃስ 20:38፤ ሥራ 24:15
20. ተስፋ ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
20 ይህ የትንሣኤ ተስፋ ዛሬ ላሉት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ማስተማመኛ ይሆናቸዋል። በዚህ ዓለም ውስጥ ታማኝ መሆን ትልቅ መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅብን እናውቃለን። ኢየሱስ ክርስቶስ በታማኝነት ለመቆም ሲል ሕይወቱን ከፍሏል፤ ተከታዮቹም የሚጠብቃቸው ነገር ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:20) ከፊቱ ያለው ተስፋ እንዲጸና እንደረዳው ሁሉ ተስፋችን እንድንጸና ይረዳናል። (ዕብራውያን 12:2) በመሆኑም ምንም ዓይነት ስደት ቢገጥመን ታማኞች መሆን እንችላለን።
21. ይሖዋ ለታማኞቹ ምን ዋስትና ሰጥቷል?
21 ዛሬ በታማኝነታችን ላይ ይህን የመሰለ ቀጥተኛ ጥቃት የሚሰነዘርብን ጥቂቶች እንደሆን አይካድም። ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ተጨማሪ ስደቶችን መቋቋም ያስፈልጋቸው ይሆናል። የዚያን ጊዜ ታማኝነታችንን እንደምንጠብቅ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ዛሬ ታማኝነታችንን በመጠበቅ ነው። ይሖዋ ስለ መንግሥቱ የመስበክና የማስተማር ታላቅ ተልእኮ ሰጥቶናል። ይህን በጣም ወሳኝ የሆነ ሥራ በታማኝነት ማከናወናችንን እንቀጥል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ሰብዓዊ አለፍጽምናዎች ለይሖዋ ድርጅት ያለንን ታማኝነት እንዲሸረሽረው የማንፈቅድ ከሆነና ያለቦታው ታማኝነት ማሳየትን የመሳሰሉ የረቀቁ የታማኝነት ፈተናዎችን ከተቋቋምን ከዚያም የከፋ የታማኝነት ፈተና ቢገጥመን ለመቋቋም ይበልጥ የተዘጋጀን እንሆናለን። ምንም ይምጣ ምን ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ታማኝ ሆኖ እንደሚገኝ ሁልጊዜ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (2 ሳሙኤል 22:26) አዎን፣ ይሖዋ ታማኞቹን ይጠብቃል!—መዝሙር 97:10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኢየሱስ ለትርፍ የሚደረገውን ሩጫ ለማስቆም ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት የቤተ መቅደሱ ቀረጥ መከፈል የነበረበት የተወሰነ ዓይነት ባለው የጥንት የአይሁዳውያን ሣንቲም ብቻ ነበር። በመሆኑም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡ ብዙ ጎብኚዎች ቀረጡን መክፈል ይችሉ ዘንድ ገንዘባቸውን መለወጥ ያስፈልጋቸው ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ የተወሰነ መጠን ያለው ክፍያ እንዲጠይቁ ፈቃድ ስለነበራቸው ብዙ ገንዘብ ያገኙ ነበረ።
b ንቁ! ሚያዝያ—ሰኔ 1994፣ ሐምሌ—መስከረም 1994 እንዲሁም የጥር 22, 1994 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔቶችን ተመልከት።
c የግሪካውያንን ተጽዕኖ ለመግታት ተብሎ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ከተቋቋመው የሔሲዲም ቡድን ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ሔሲዲም የተባለው ቡድን ስሙን ያገኘው “ታማኞች” ወይም “ለሃይማኖታቸው ያደሩ” የሚል ትርጉም ካለው ቼሲዲም ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። ምናልባትም ስለ ይሖዋ “ታማኞች” የሚናገሩት ጥቅሶች በአንድ የተለየ መንገድ ስለ እነርሱ እንደሚጠቅሱ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 50:5 NW) እነርሱም ሆኑ ከእነርሱ በኋላ የተነሡት ፈሪሳውያን ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ አክራሪ የሕጉ ፊደላት ጠበቆች ነበሩ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የሌሎች አለፍጽምና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ወደመፈጸም እንዳይመራን ልንጠነቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ የራሳችን አለፍጽምና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ወደመፈጸም ሊመራን የሚችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ ያለቦታው ታማኝነት እንድናሳይ የሚገጥመንን ፈተና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
◻ በስደት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን ምንድን ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቤቴል ውስጥ በታማኝነት ማገልገል
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” (1 ቆሮንቶስ 14:40) ጳውሎስ አንድ ጉባኤ በአግባቡ እንዲሠራ ካስፈለገ “ሥርዓት” ሊኖር እንደሚገባና መደራጀት እንደሚያስፈልግ ተረድቶ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ሽማግሌዎች የጉባኤ አባላትን በየመጽሐፍ ጥናት ቡድን መመደብን፣ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ማዘጋጀትን፣ የአገልግሎት ክልሎች መሸፈናቸውን መቆጣጠርንና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በሚመለከት ጠቃሚ ውሳኔዎችን ማድረግ ይፈለግባቸዋል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች አንዳንድ ጊዜ ታማኝነትን የሚፈትኑ ሊሆኑ ይችላሉ። በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተሰጡ ትእዛዛት አይደሉም፤ የእያንዳንዱን ግለሰብ ምርጫም አያሟሉም።
አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለተደረጉት ጠቃሚ ዝግጅቶች ታማኝ ሆኖ መገኘት ፈታኝ ይሆንብሃልን? ከሆነ ከቤቴል ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ታገኝ ይሆናል። ቤቴል የሚለው ስም “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን 104 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎችና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በዚህ ስያሜ ይጠራሉ። በቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትና የሚሠሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች እነዚህ ቦታዎች ለይሖዋ ያላቸውን ጥልቅ አክብሮትና ፍርሃት የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ ከእያንዳንዳቸው ታማኝነትን ይጠይቃል።
ብዙውን ጊዜ ወደ ቤቴል የሚመጡ ጎብኚዎች ስለሚያዩት ሥርዓታማነትና ንጽሕና ይናገራሉ። ሠራተኞቹ የተደራጁና ደስተኞች ናቸው፤ ንግግራቸውና ጠባያቸው እንዲሁም አለባበሳቸውና የሰውነት አያያዛቸው የጎለመሰና በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ክርስቲያናዊ ሕሊና እንዳላቸው የሚያንጸባርቅ ነው። ሁሉም የቤቴል ቤተሰብ አባላት በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን የአቋም ደረጃዎች በታማኝነት ይደግፋሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የአስተዳደር አካሉ በአንድነት አብሮ መኖር የተባለ (የእንግሊዝኛ) ቡክሌት አዘጋጅቶላቸዋል፤ ይህ ቡክሌት እንዲህ ያለው ትልቅ ቤተሰብ በአንድነት ሥራውን በሚገባ ማከናወን እንዲችል የሚረዱ ጠቃሚ ሥርዓቶችን ይዟል። (መዝሙር 133:1) ለምሳሌ ያህል የክፍል አያያዝን፣ ምግብን፣ ንጽሕናን፣ ልብስን እንዲሁም አጋጌጥንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ይዳስሳል። የቤቴል ቤተሰብ አባላት የግል ምርጫቸው ከዚህ የተለየ ሊሆን ቢችልም እንኳ እነዚህን ሥርዓቶች በታማኝነት ይደግፋሉ፤ አጥብቀውም ይከተላሉ። ይህንን መመሪያ ድርቅ ያለ ሕግ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትም፤ ይልቁንም አንድነትንና ስምምነትን ለማስፈን ሲባል እንደተዘጋጀ ጠቃሚ መመሪያ አድርገው ያዩታል። የበላይ ተመልካቾችም እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የአሠራር ሥርዓቶች በታማኝነት የሚደግፉ ሲሆን የቤቴል ቤተሰብ በቅዱስ አገልግሎቱ መቀጠል ይችል ዘንድ እነዚህን መመሪያዎች ቤተሰቡን ለማነጽና ለማበረታታት አዎንታዊ በሆነ መንገድ ይጠቀሙባቸዋል።
እነዚህ የፋብሪካ፣ የቢሮና የመኖሪያ ሕንፃዎች ታላቁን የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ወይም ቤት አያመለክቱም። የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚያመለክተው ለንጹሕ አምልኮ የተደረገውን ዝግጅት ነው። (ሚክያስ 4:1) በመሆኑም በምድር ላይ በሚገኝ በማንኛውም ዓይነት ግንባታ አይወከልም።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ታማኝ ሰውና ሕግ አጥባቂ ሰው
በ1916 ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ “በታማኝ ሰውና በሕግ አጥባቂ ሰው መካከል ያለው ልዩነት በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊታይ ይችላል” ሲል አስፍሮ ነበር። እንዲህ ሲል አብራርቷል:- “ሕግ አጥባቂ ሰው የተነገረውን ይሠራል፣ ምንም ዓይነት ሕግ አይጥስም፤ በጽሑፍ የሠፈረውንና ሊነበብ የሚችለውን ነገር ሁሉ ያምናል። ታማኝ ሰውም ይህን ሁሉ ያደርጋል፤ ይሁንና . . . ከዚህም ይበልጥ ሙሉ በሙሉ በሥራው የተጠመደ ራሱን ከቆመለት ዓላማ ጋር የሚያስተካክል ሰው እንደሆነ እምነት ይጣልበታል።” ከዚያም ይኸው ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ብሏል:- “ታማኝ ሰው መሆን ለሕግ ከመታዘዝ በእጅጉ የሚበልጥ ነገር ነው። . . . ታማኝ ሰው ለሕግ ከሚታዘዝ ሰው የሚለየው በሙሉ ልቡና ሐሳቡ የሚያገለግል በመሆኑ ሲሆን . . . ሆነ ብሎ ኃጢአት አይሠራም፣ ማድረግ ያለበትንም አያጓድልም፣ ለቸልተኛነትም ቦታ አይሰጥም።”