የአምላክን ቃል መውደድ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
“[ጥበብን] ውደዳት፣ ትጠብቅህማለች። . . . ብታቅፋትም ታከብርሃለች።”—ምሳሌ 4:6, 8
1. የአምላክን ቃል ከልብ መውደድ ምን ነገርን ይጨምራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ለአንድ ክርስቲያን የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ እንዲሁ ማንበብ ብቻውን ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዳለን አያሳይም። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን ነገሮች የሚያደርግ ቢሆንስ? ይህ ሰው የመዝሙር 119 ጸሐፊ ለአምላክ ቃል የነበረው ዓይነት ፍቅር እንደሌለው ግልጽ ነው። ለአምላክ ቃል የነበረው ፍቅር መዝሙራዊውን በቃሉ ውስጥ ከሰፈረው ብቃት ጋር ተስማምቶ እንዲኖር አነሳስቶታል።—መዝሙር 119:97, 101, 105
2. በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጥበብ ምን ጥቅሞች አሉት?
2 ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ዘወትር አስተሳሰብንና አኗኗርን እያስተካከሉ መቀጠልን ይጠይቃል። እንዲህ ያለውን ጎዳና መከተል ጥበብ ሲሆን ይህም የአምላክን ቃል በማጥናት ያገኙትን እውቀትና ማስተዋል በተግባር ማዋል ማለት ነው። “[ጥበብን] ውደዳት ትጠብቅህማለች። ከፍ ከፍ አድርጋት፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ብታቅፋትም ታከብርሃለች። ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፣ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትሃለች።” (ምሳሌ 4:6, 8, 9) የአምላክን ቃል እንድንወድና በዚያ እንድንመራ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ማበረታቻ ነው! ጥበቃ ማግኘት፣ ከፍ ከፍ መደረግና መከበር የማይፈልግ ማን አለ?
ከዘላቂ ጉዳት ጥበቃ ማግኘት
3. ክርስቲያኖች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? የሚጠበቁትስ ከማን ነው?
3 አንድ ሰው የአምላክን ቃል በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል የሚያገኘው ጥበብ ጥበቃ የሚሆንለት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከሰይጣን ዲያብሎስ ይጠበቃል። ኢየሱስ ተከታዮቹ ከክፉው ከሰይጣን ይድኑ ዘንድ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:13) በተለይ ዛሬ በጸሎታችን ይህን ልመና ማቅረባችን አንገብጋቢ ሆኗል። ሰይጣንና አጋንንቱ ከ1914 በኋላ ከሰማይ ከተጣሉ ወዲህ ሰይጣን ‘የቀረው ጊዜ ጥቂት መሆኑን በማወቁ በጣም ተቆጥቷል።’ (ራእይ 12:9, 10, 12) በዚህ ባለቀ ሰዓት ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁት የኢየሱስም ምስክር ባላቸው’ ሰዎች ላይ በከፈተው ውጊያ ስላልተሳካለት እርር ድብን ብሎ መሆን አለበት።—ራእይ 12:17
4. ክርስቲያኖች ከሰይጣን ተጽእኖዎችና ወጥመዶች የሚጠበቁት እንዴት ነው?
4 ሰይጣን በቁጣ ተነሳስቶ በእነዚህ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ችግር መፍጠሩን እንዲሁም ከባድ ስደት መቆስቆሱን ወይም በሥራቸው ላይ ሌሎች እንቅፋቶች መፍጠሩን ቀጥሏል። በተጨማሪም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ከማተኮር ይልቅ ዓለማዊ እውቅና ማግኘትን እንዲናፍቁ፣ መዝናኛን እንዲያፈቅሩ፣ ቁሳዊ ሃብት ወደ ማከማቸት ዘወር እንዲሉ እንዲሁም ተድላን እንዲያሳድዱ ለማድረግ ይፈልጋል። የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ለሰይጣን ተጽዕኖ እንዳይሸነፉ ወይም በወጥመዶቹ እንዳይያዙ የሚጠብቃቸው ምንድን ነው? እርግጥ ነው፣ ጸሎት፣ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትና ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በማይቀረው የእርሱ ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደር የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩትን ማሳሰቢያዎች ከማወቅና እነዚህንም ማሳሰቢያዎች ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህን ማሳሰቢያዎች የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ስናነብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ፣ መሰል አማኞች የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ስንከተል ወይም ደግሞ የአምላክ መንፈስ በሚያስታውሰን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በጸሎት ስናሰላስል ነው።—ኢሳይያስ 30:21፤ ዮሐንስ 14:26፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
5. በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጥበብ ጥበቃ የሚሆንልን በምን መንገዶች ነው?
5 የአምላክን ቃል የሚወዱ ሰዎች በሌላ መልኩም ጥበቃ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል አደገኛ ዕፆችን አላግባብ መጠቀም፣ ትንባሆ ማጨስና የፆታ ብልግናን የመሰሉ ነገሮች ከሚያስከትሉት የስሜት ስቃይና ሕመም ይጠበቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) ሐሜት ወይም ደግነት የጎደለው ንግግር በመናገር ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲሻክር አይፈቅዱም። (ኤፌሶን 4:31) የዓለም ጥበብ ውጤት የሆኑ አታላይ ፍልስፍናዎችን በመከታተል በጥርጣሬ ወጥመድ ውስጥም አይወድቁም። (1 ቆሮንቶስ 3:19) ለአምላክ ቃል ያላቸው ፍቅር ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድናና የዘላለም ሕይወት ተስፋቸውን ከሚያሳጡ ነገሮች ይጠብቃቸዋል። ‘ራሳቸውንም ሆነ የሚሰሟቸውንም ሰዎች እንደሚያድኑ’ ስለሚያውቁ ጎረቤቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ድንቅ ተስፋዎች ላይ እምነት እንዲያሳድሩ በመርዳቱ ሥራ ራሳቸውን ያስጠምዳሉ።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
6. በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጥበብ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሳይቀር ጥበቃ ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?
6 እርግጥ ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ ‘ጊዜና አጋጣሚ’ ከሚያመጣው ነገር ነፃ የሆነ ማንም ሰው የለም። (መክብብ 9:11) ከመካከላችን አንዳንዶች የተፈጥሮ አደጋ፣ ከባድ ሕመምና ድንገተኛ አደጋ ሊደርስባቸው ወይም ያለ እድሜያቸው ሊቀጩ ይችላሉ። ይህ ግን ጥበቃ አላገኘንም ማለት አይደለም። አንድ ሰው የአምላክን ቃል ከልቡ የሚወድ ከሆነ የሚደርስበት ማንኛውም ዓይነት መከራ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትልበት አይችልም። ደግሞም ወደፊት ሊደርስ ስለሚችለው ነገር ከልክ በላይ መጨነቅ አያስፈልገንም። በበኩላችን አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ካደረግን በኋላ የተቀረውን ለይሖዋ መተዉ የተሻለ ነው። ዛሬ ያለው ያልተረጋጋ ሕይወት ደስታችንን እንዲነጥቅብን መፍቀድ አይኖርብንም። (ማቴዎስ 6:33, 34፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የትንሣኤ ተስፋ መፈጸሙና አምላክ ‘ሁሉን አዲስ’ ሲያደርግ የተሻለ ሕይወት መምጣቱ እንደማይቀር ሁልጊዜ አስታውስ።—ራእይ 21:5፤ ዮሐንስ 11:25
‘መልካም’ አፈር መሆናችሁን አሳዩ
7. ኢየሱስ እርሱን ለመስማት ለመጡት ሰዎች ምን ምሳሌ ነገራቸው?
7 ለአምላክ ቃል ትክክለኛ አመለካከት የመያዝ አስፈላጊነት ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ውስጥ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ኢየሱስ በፍልስጤም ምድር ምሥራቹን ያውጅ በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎች እርሱን ለመስማት ተሰበሰቡ። (ሉቃስ 8:1, 4) ይሁን እንጂ ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበራቸው ሁሉም አልነበሩም። ብዙዎቹ እርሱን ለመስማት የመጡት ተዓምራት ለማየት ፈልገው ወይም ደግሞ በጣም አስገራሚ የነበረው የማስተማር ችሎታው ስላስደሰታቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢየሱስ ለተሰበሰበው ሕዝብ አንድ ምሳሌ ተናገረ:- “ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፣ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፣ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፣ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።”—ሉቃስ 8:5-8
8. በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተገለጸው ዘር ምንድን ነው?
8 ለምሥራቹ የሚሰጠው ምላሽ እንደ ሰሚው የልብ ሁኔታ ሊለያይ እንደሚችል ከኢየሱስ ምሳሌ ለመረዳት ይቻላል። ይህ የተዘራው ዘር “የእግዚአብሔር ቃል” ነው። (ሉቃስ 8:11) ወይም ስለዚሁ ምሳሌ የሚገልጸው ሌላው ዘገባ እንደሚለው ዘሩ ‘የመንግሥት ቃል’ ነው። (ማቴዎስ 13:19) የአምላክ ቃል ዋና ጭብጥ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥና ስሙን ለማስቀደስ የሚጠቀምበት ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለት ሰማያዊ መንግሥት ስለሆነ ኢየሱስ ሁለቱንም አባባል መጠቀሙ ያስኬዳል። (ማቴዎስ 6:9, 10) በሌላ አባባል ዘሩ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የምሥራቹ መልእክት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያውን ዘሪ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ዘሩን ሲዘሩ የመንግሥቱን መልእክት ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። የሚያገኙት ምላሽ ምን ይመስላል?
9. (ሀ) በመንገድ ዳር (ለ) በአለት ላይ (ሐ) በእሾሀማ መሬት ላይ የሚወድቀው ዘር ምን ያመለክታል?
9 ኢየሱስ አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር እንደሚወድቅና እንደሚረጋገጥ ገልጿል። ይህም የመንግሥቱ ዘር በልባቸው ውስጥ ሥር እንዳይሰድ በብዙ ነገር የተጠላለፉ ሰዎችን ያመለክታል። ለአምላክ ቃል ፍቅር ከማዳበራቸው በፊት “ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።” (ሉቃስ 8:12) አንዳንዱ ዘር ደግሞ አለት ላይ ይወድቃል። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ደስ ብሏቸው የሚቀበሉትንና ነገር ግን ቃሉ ልባቸውን እንዲነካ የማይፈቅዱለትን ሰዎች ያመለክታል። ተቃውሞ ሲገጥማቸው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ማዋሉ ከባድ እንደሆነ ሲሰማቸው ሥር ስለሌላቸው ‘ይክዳሉ።’ (ሉቃስ 8:13) ከዚያ ደግሞ ቃሉን የሚሰሙ ነገር ግን በዚህ ሕይወት ‘አሳብና የባለ ጠግነት ምቾት’ የሚዋጡ ሰዎች አሉ። በመጨረሻም በእሾህ እንደተያዘ ተክል ሙሉ በሙሉ “ይታነቃሉ።”—ሉቃስ 8:14
10, 11. (ሀ) በመልካም አፈር የተመሰሉት እነማን ናቸው? (ለ) የአምላክን ቃል በልባችን ‘ለመጠበቅ’ ምን ማድረግ ይገባናል?
10 በመጨረሻ ደግሞ በመልካም መሬት ላይ የሚወድቀው ዘር አለ። ይህ መልእክቱን “በመልካምና በበጎ ልብ” የሚቀበሉትን ሰዎች ያመለክታል። ሁላችንም በእነዚህ ሰዎች መካከል እንደምንገኝ አድርገን እንደምናስብ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ወሳኙ አምላክ ለእኛ ያለው አመለካከት ይሆናል። (ምሳሌ 17:3፤ 1 ቆሮንቶስ 4:4, 5) የአምላክ ቃል እንደሚገልጽልን ‘መልካምና በጎ ልብ’ ያለን መሆኑን የምናረጋግጠው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ወይም አምላክ ይህንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት እስከሚያጠፋበት ጊዜ ድረስ በምናደርገው ነገር ይሆናል። ለመንግሥቱ መልእክት የሰጠነው የመጀመሪያ ምላሽ ጥሩ መሆኑ መልካም ነው። ይሁን እንጂ መልካምና በጎ ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክን ቃል ተቀብለው ‘ይጠብቁታል፤ በመጽናትም ፍሬ ያፈራሉ።’—ሉቃስ 8:15
11 የአምላክን ቃል በልባችን ለመጠበቅ የሚያስችለን ብቸኛው መንገድ በግልም ሆነ ከእምነት ወንድሞቻችን ጋር በጋራ ቃሉን ማንበብና ማጥናታችን ነው። ይህም የኢየሱስን እውነተኛ ተከታዮች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟላ በተሾመው ክፍል በኩል የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠቀምን ይጨምራል። (ማቴዎስ 24:45-47) በዚህ መንገድ የአምላክን ቃል በልባቸው የሚጠብቁ ሰዎች በፍቅር ተገፋፍተው ‘በመጽናት ፍሬ ያፈራሉ።’
12. በጽናት ልናፈራው የሚገባን ፍሬ ምንድን ነው?
12 መልካም የሆነው መሬት የሚያፈራው ፍሬ ምንድን ነው? ወደ ዕፅዋቱ ዓለም የመጣን እንደሆነ አንድ ዘር በቅሎ ተመሳሳይ ዘር የሚያፈራ ተክል ይሆናል። ይህም ዘር ተጨማሪ ፍሬ እንዲያፈራ ሊዘራ ይችላል። በተመሳሳይም መልካምና በጎ ልብ ባላቸው ሰዎች ውስጥ የቃሉ ዘር ያድግና እነርሱም በተራቸው ዘሩን በሌሎች ሰዎች ልብ ውስጥ ለመዝራት ብቁ እስከመሆን ድረስ ለመንፈሳዊ እድገት ያነሳሳቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ዘሩን የመዝራት ሥራቸው ጽናት የሚጠይቅ ነው። ኢየሱስ ዘር መዝራቱ ምን ያህል ጽናት እንደሚጠይቅ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:13, 14
‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ ማፍራት’
13. ጳውሎስ ፍሬን ከአምላክ ቃል እውቀት ጋር አጣምሮ የሚገልጽ ምን ጸሎት አቅርቧል?
13 ሐዋርያው ጳውሎስም ፍሬ የማፍራትን አስፈላጊነት የገለጸ ሲሆን ይህንንም ከአምላክ ቃል ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። የእምነት ወንድሞቹ ‘[የአምላክ] የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ [ሞልቶባቸው]፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈሩ በነገር ሁሉ ደስ ሊያሰኙ ለጌታ እንደሚገባ’ ይመላለሱ ዘንድ ጸልዮአል።—ቆላስይስ 1:9, 10፤ ፊልጵስዩስ 1:9-11
14-16. ከጳውሎስ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች ምን ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ?
14 በዚህ መንገድ ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት የመጨረሻው ደረጃ እንዳልሆነ ጠቁሟል። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ቃል ያለን ፍቅር ‘በበጎ ሥራ ሁሉ መልካም ፍሬ እያፈራን’ በመቀጠል ‘ለይሖዋ እንደሚገባ’ እንድንመላለስ ያነሳሳናል። ይህ በጎ ሥራ ምንድን ነው? በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ለሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮች የተሰጣቸው ጉልህ ሥራ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ነው። (ማርቆስ 13:10) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች ይህን ሥራ ዘወትር በገንዘብ ለመደገፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን እንደሚወድድ’ ስለሚያውቁ ይህን መብት በማግኘታቸው ደስ ይላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) የሚያደርጉት መዋጮ ከአንድ መቶ የሚበልጡትን የቤቴል ቢሮዎች ወጪ ለመሸፈን ይውላል። በእነዚህ ቦታዎች የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ይደራጃል እንዲሁም በአንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይታተማል። በተጨማሪም መዋጮአቸው የትላልቅ ክርስቲያናዊ የአውራጃ ስብሰባዎችን እንዲሁም ወደ ሌላ ቦታ የሚላኩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ ሚስዮናውያንንና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ወጪ ለመሸፈን ይውላል።
15 የንጹሕ አምልኮ ማዕከሎችን መገንባትና መንከባከብም ሌላ መልካም ሥራ ነው። የይሖዋ አምላኪዎች ለአምላክ ቃል ያላቸው ፍቅር የመንግሥት አዳራሾችና ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቸል አለመባላቸውን እንዲከታተሉ ያነሳሳቸዋል። (ከነህምያ 10:39 ጋር አወዳድር።) በእነዚህ ሕንጻዎች ላይ የአምላክ ስም ተጽፎ ስለሚታይ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ንጹሕና ማራኪ መሆናቸው እንዲሁም እንደነዚህ ባሉት አዳራሾች ውስጥ ለአምልኮ የሚሰበሰቡትም ሰዎች አኗኗር ከነቀፋ የጸዳ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:3) አንዳንድ ክርስቲያኖች የበለጠ ለመሥራት ሁኔታቸው ስለሚፈቅድላቸው ለአምላክ ቃል ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው በድህነት ወይም በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት ተጨማሪ እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው የዓለም ክፍሎች ረጅም ርቀት በመጓዝ በአዳዲስ የአምልኮ ቦታዎች ግንባታ ይካፈላሉ።—2 ቆሮንቶስ 8:14
16 በተጨማሪም ‘በበጎ ሥራ ሁሉ መልካም ፍሬ ማፍራት’ የቤተሰብ ኃላፊነቶችን መወጣትንና ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችን አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል። ለአምላክ ቃል ያለን ፍቅር ‘በእምነት የሚዛመዱን’ ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ እንድንሆንና ‘ለገዛ ቤተ ሰዎቻችን ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንድናሳይ’ ይገፋፋናል። (ገላትያ 6:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8 NW) በዚህ ረገድ የታመሙትን መጠየቅና ሐዘን የደረሰባቸውን ማጽናናት በጎ ሥራ ነው። ፈታኝ የሆነ የሕክምና ሁኔታ የገጠማቸውን ግለሰቦች በመርዳት በኩል ሽማግሌዎችና የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች የሚያከናውኑት ሥራ ምንኛ የሚደነቅ ነው! (ሥራ 15:28, 29) ከዚህም ሌላ በየጊዜው ብዙ አደጋዎች የሚደርሱ ሲሆን አንዳንዶቹ የተፈጥሮ ሌሎቹ ደግሞ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ በሚያገኙት መንፈስ በመታገዝ ለእምነት ወንድሞቻቸው እንዲሁም በተፈጥሮና በሌሎች አደጋዎች ሰለባ ለሆኑ ሌሎች ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ በማቅረብ በብዙ የዓለም ክፍሎች መልካም ስም ለማትረፍ በቅተዋል። እነዚህ ሁሉ ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች የሚያንጸባርቋቸው መልካም ፍሬዎች ናቸው።
ወደፊት የምናገኘው ታላቅ ጥቅም
17, 18. (ሀ) የሚዘራው የመንግሥት ዘር ምን ዓይነት ውጤቶችን በማስገኘት ላይ ነው? (ለ) የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች በቅርቡ ዓለምን የሚያናውጥ ምን ነገር ሲከናወን ያያሉ?
17 የመንግሥቱ ዘር መዘራት ለሰው ዘር ታላላቅ ጥቅሞች ማምጣቱን ይቀጥላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ከ300,000 የሚበልጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በልባቸው ውስጥ ሥር እንዲሰድ በመፍቀድ ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት እያሳዩ ነው። እነዚህ ሰዎች ከፊታቸው እንዴት ያለ ክብራማ ጊዜ ይጠብቃቸዋል!
18 የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሁሉ በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ስሙን ለማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ያውቃሉ። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ‘ታላቂቱ ባቢሎን’ ትጠፋለች። (ራእይ 18:2, 8) ከአምላክ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ፈቃደኛ የማይሆኑት ሁሉ በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ይገደላሉ። (መዝሙር 2:9-11፤ ዳንኤል 2:44) ከዚያም የአምላክ መንግሥት ከወንጀል፣ ከጦርነትና ከሌሎች አደጋዎች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይገላግለናል። በዚያን ወቅት በስቃይ፣ በሕመምና በሞት ምክንያት ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው አይኖርም።—ራእይ 21:3, 4
19, 20. የአምላክን ቃል ከልባቸው የሚያፈቅሩ ሰዎች ምን ክብራማ የሆነ ጊዜ ይጠብቃቸዋል?
19 በዚያ ጊዜ ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ታላላቅ በጎ ሥራዎችን ያከናውናሉ! ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች ምድርን ወደ ገነትነት የመለወጡን አስደሳች ሥራ ይያያዙታል። በአሁኑ ጊዜ በመቃብር ያሉትና በአምላክ ዝክር ውስጥ የተቀመጡት የትንሣኤ ተስፋ ያላቸው ሙታን ሲነሱ ለመቀበል የሚያስፈልገውን ዝግጅት የማድረግ ልዩ መብት ያገኛሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) በዚያ ጊዜ ልዑሉ ጌታ ይሖዋ ከፍ ያለ ክብር በተቀዳጀው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለመላው የምድር ነዋሪ ፍጹም የሆነ መመሪያ ይሰጣል። ለአዲሱ ዓለም የሚያገለግሉ የይሖዋን መመሪያዎች የያዙ ‘መጻሕፍት ይከፈታሉ።’—ራእይ 20:12
20 ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የተሟላው የታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ‘ከክርስቶስ ጋር ለመንገሥ’ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመውረስ ይነሳሉ። (ሮሜ 8:17) ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው በምድር የሚኖሩ የሰው ልጆች በሙሉ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የአእምሮና የአካል ፍጽምናን ይላበሳሉ። የመጨረሻውን ፈተና የታመኑ ሆነው ካለፉ በኋላ የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳሉ። (ሮሜ 8:21፤ ራእይ 20:1-3, 7-10) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! በእውነትም ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ለቃሉ ጊዜ የማይሽረው ፍቅር ካሳየንና በአምላካዊ ጥበብ ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን አሁን ጥበቃ ይሆንልናል። ወደፊት ደግሞ ‘አቅፈነዋልና ያከብረናል።’—ምሳሌ 4:6, 8
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ለአምላክ ቃል ያለን ፍቅር ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
◻ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተገለጸው ዘር ምንድን ነው? የተዘራውስ እንዴት ነው?
◻ ‘መልካም መሬት’ መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?
◻ የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች ምን ጥቅም እናገኛለን ብለው ሊጠባበቁ ይችላሉ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ዘር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የምሥራች መልእክት ያመለክታል
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች የታላቁን ዘሪ ምሳሌ ይኮርጃሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአርማጌዶን ተራፊዎች በምድር ፍሬ ይረካሉ