ልንሸሻቸው የሚገቡ ነገሮች
“እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?” —ማቴ. 3:7 የ1954 ትርጉም
1. ከመሸሽ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
‘ሽሹ’ የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንዶች ዮሴፍ የተባለው መልከ መልካም ወጣት፣ የጲጢፋራ ሚስት ከእሷ ጋር እንዲተኛ በጠየቀችው ጊዜ መሸሹን ያስታውሱ ይሆናል። (ዘፍ. 39:7-12) ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመስማት በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከኢየሩሳሌም የሸሹትን ክርስቲያኖች ያስቡ ይሆናል፤ ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ . . . በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማ ያሉትም ከዚያ ይውጡ።”—ሉቃስ 21:20, 21
2, 3. (ሀ) መጥምቁ ዮሐንስ በሃይማኖታዊ መሪዎቹ ላይ የሰነዘረው ነቀፋ ትርጉሙ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ፣ ዮሐንስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያጠናከረው እንዴት ነበር?
2 ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ላይ ሰዎቹ ቃል በቃል መሸሽ ነበረባቸው። በዛሬው ጊዜም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ ሁኔታ በአስቸኳይ መሸሽ አለባቸው። መጥምቁ ዮሐንስ ‘መሸሽ’ የሚለውን ቃል የተጠቀመበት በዚህ መንገድ ነበር። ወደ ዮሐንስ ከመጡት ሰዎች መካከል፣ ራሳቸውን የሚያመጻድቁት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው አይሰማቸውም ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ይጠመቁ የነበሩትን ሰዎች ይንቋቸው ነበር። ዮሐንስ፣ እነዚህን ግብዝ መሪዎች እንዲህ በማለት በድፍረት አጋልጧቸዋል:- “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ።”—ማቴ. 3:7, 8 የ1954 ትርጉም
3 ዮሐንስ እዚህ ላይ የተናገረው ቃል በቃል ስለ መሸሽ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የፍርድና የቁጣ ቀን እንደሚመጣ መግለጹ ነበር፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ከዚያ ቀን ማምለጥ ከፈለጉ ንስሐ መግባታቸውን የሚያሳይ ፍሬ ማፍራት እንደሚኖርባቸው አስጠንቅቋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ነፍስ ለማጥፋት መፈለጋቸው አባታቸው ዲያብሎስ መሆኑን እንደሚጠቁም በመናገር በድፍረት አውግዟቸዋል። (ዮሐ. 8:44) ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “የእፉኝት ልጆች” ብሎ በመጥራት ቀደም ሲል ዮሐንስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያጠናከረው ሲሆን “ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ?” በማለት ጠይቋቸዋል። (ማቴ. 23:33) ኢየሱስ እዚህ ላይ “ገሃነም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
4. ኢየሱስ “ገሃነም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
4 ገሃነም፣ ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ የሚገኝ ሸለቆ ሲሆን በዚያም ቆሻሻ እንዲሁም የሞቱ እንስሳት ይቃጠሉ ነበር። ኢየሱስ፣ ገሃነም የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ዘላለማዊ ሞትን ለማመልከት ነው። (ገጽ 27ን ተመልከት።) ኢየሱስ ከገሃነም ፍርድ ስለማምለጥ ያቀረበው ጥያቄ፣ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በቡድን ደረጃ የዘላለም ጥፋት የሚገባቸው መሆኑን ያመለክታል።—ማቴ. 5:22, 29
5. ዮሐንስና ኢየሱስ የሰጡት ማስጠንቀቂያ እንደተፈጸመ ታሪክ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
5 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ኢየሱስንና ተከታዮቹን በማሳደድ ተጨማሪ ኃጢአት ፈጽመዋል። ዮሐንስና ኢየሱስ እንዳስጠነቀቁት ከጊዜ በኋላ የአምላክ የቁጣ ቀን መጣ። በዚያ ወቅት ‘የመጣው ቍጣ’ በአንድ አካባቢ ማለትም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሕዝቡ ቃል በቃል መሸሽ ይችል ነበር። ይህ ቁጣ የመጣው በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በሮማውያን ሠራዊት በተደመሰሱበት ወቅት ነበር። በዚያን ጊዜ የደረሰው “መከራ” ኢየሩሳሌም ከዚያ ቀደም ካጋጠማት መከራ ሁሉ የከፋ ነበር። ብዙዎች ተገድለዋል እንዲሁም በምርኮ ተወስደዋል። ይህ ሁኔታ በርካታ ስመ ክርስቲያኖችና ሌሎች ሃይማኖቶች ከዚህ የከፋ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው ይጠቁማል።—ማቴ. 24:21
ከሚመጣው ቁጣ መሸሽ
6. በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ተከስቶ ነበር?
6 ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶች ከሃዲዎች በመሆን ለራሳቸው ተከታዮችን አፍርተው ነበር። (ሥራ 20:29, 30) የኢየሱስ ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ወቅት እንዲህ ያለውን ክህደት ‘ይከላከሉ’ የነበረ ቢሆንም እነሱ ከሞቱ በኋላ በሐሰተኛ ክርስትና ውስጥ በርካታ ኑፋቄዎች ተፈጠሩ። በዛሬው ጊዜም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እርስ በርስ የሚቃረኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት አስቀድሞ የተናገረ ሲሆን በቡድን ደረጃ “የዐመፅ ሰው” እንዲሁም “ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ ሰው” በማለት ጠርቷቸዋል፤ ከዚህም በላይ ይህን የዐመፅ ሰው ‘ጌታ ኢየሱስ እንደሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ እንደሚያጠፋው’ ተገልጿል።—2 ተሰ. 2:3, 6-8
7. “የዐመፅ ሰው” የሚለው መግለጫ ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
7 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ትምህርቶችን፣ በዓላትንና አኗኗርን በማስፋፋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሳታቸው ዓመፀኞች ናቸው። ኢየሱስ እንዳወገዛቸው የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ‘ለጥፋት የተመደበው የዐመፅ ሰው’ ክፍል የሆኑ የሐሰት ሃይማኖት መሪዎችም የትንሣኤ ተስፋ የሌለው ጥፋት ይጠብቃቸዋል። (2 ተሰ. 1:6-9) ይሁን እንጂ በሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም ሆነ በሌሎች የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች የተታለሉ ሰዎችስ ምን ይጠብቃቸዋል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጠፋች በኋላ የተከናወኑትን ነገሮች እንመልከት።
“ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ”
8, 9. (ሀ) ኤርምያስ በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው ለነበሩት አይሁዳውያን ምን ትንቢታዊ መልእክት ተናግሮ ነበር? (ለ) ባቢሎን፣ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ከሆነች በኋላ ሕዝቡ በምን ዓይነት ሁኔታ መሸሽ ይችሉ ነበር?
8 ነቢዩ ኤርምያስ፣ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተፈጸመውን የኢየሩሳሌም ጥፋት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች በግዞት እንደሚወሰዱና ‘ከሰባ ዓመት’ በኋላ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ገልጾ ነበር። (ኤር. 29:4, 10) ኤርምያስ፣ ተማርከው ወደ ባቢሎን የተወሰዱት አይሁዳውያን በዚያ ባለው የሐሰት ሃይማኖት እንዳይበከሉ በማስጠንቀቅ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት ነግሯቸዋል። ሕዝቡ ይህን መልእክት ሰምተው ተግባራዊ ካደረጉ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ንጹሑን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ዝግጁ ይሆናሉ። ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎንን ድል ካደረጓት ብዙም ሳይቆይ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው መመለስ ቻሉ። የፋርሱ ንጉሥ ዳግማዊ ቂሮስ፣ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ አዋጅ አስነገረ።—ዕዝራ 1:1-4
9 በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ወደ አገራቸው ተመለሱ። (ዕዝራ 2:64-67) ይህንንም በማድረግ ኤርምያስ በትንቢቱ ላይ በሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ወደ ሌላ ቦታ ሸሽተዋል። (ኤርምያስ 51:6, 45, 50ን አንብብ።) ሆኖም ረጅሙን መንገድ ተጉዘው ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ለመመለስ ሁኔታቸው የፈቀደላቸው ሁሉም አይሁዳውያን አልነበሩም። እንደ አረጋዊው ነቢዩ ዳንኤል ያሉት በባቢሎን የቀሩ አይሁዳውያን፣ በኢየሩሳሌም የሚካሄደውን ንጹሕ አምልኮ በሙሉ ልብ ከደገፉና ከባቢሎናውያን የሐሰት አምልኮ ከራቁ የአምላክን በረከት ማግኘት ይችሉ ነበር።
10. “ታላቂቱ ባቢሎን” ለየትኞቹ “ርኩሰቶች” ተጠያቂ ናት?
10 በዛሬው ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከጥንቷ ባቢሎን በመነጩ የተለያዩ የሐሰት ሃይማኖት ገጽታዎች ይካፈላሉ። (ዘፍ. 11:6-9) እነዚህ ሃይማኖቶች በቡድን ደረጃ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት” ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 17:5) የሐሰት ሃይማኖት ለረጅም ዘመናት የዚህን ዓለም የፖለቲካ ገዥዎች ሲደግፍ ቆይቷል። የሐሰት ሃይማኖት ተጠያቂ ከሆነባቸው “ርኩሰቶች” መካከል በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ‘በምድር ላይ እንዲገደሉ’ ምክንያት የሆኑት በርካታ ጦርነቶች ይገኙበታል። (ራእይ 18:24) ከዚህም በላይ ቀሳውስቱ ሕፃናትን ማስነወራቸውና ሌሎች የጾታ ብልግናዎችን መፈጸማቸው እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናቱ ባለ ሥልጣናት ጉዳዩን በቸልታ ማለፋቸው በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ከሚፈጸሙት ሌሎች “ርኩሰቶች” መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ታዲያ ይሖዋ አምላክ በቅርቡ የሐሰት ሃይማኖትን ከምድር ገጽ የሚያጠፋ መሆኑ ምን ያስገርማል?—ራእይ 18:8
11. ታላቂቱ ባቢሎን እስክትጠፋ ድረስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን የማድረግ ግዴታ አለባቸው?
11 የሐሰት ሃይማኖት እንደሚጠፋ የሚያውቁት እውነተኛ ክርስቲያኖች የታላቂቱ ባቢሎንን አባላት የማስጠንቀቅ ግዴታ አለባቸው። ይህንን ከሚያደርጉባቸው መንገዶች አንዱ ኢየሱስ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ እንዲያዘጋጅ በሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚቀርቡትን መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ማሰራጨት ነው። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም) ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ካሳዩ የአምላክን ቃል እንዲያጠኑ ዝግጅት ይደረጋል። እነዚህ ሰዎች “ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ” የሚለውን ትእዛዝ ተግባራዊ የማድረግን አስፈላጊነት ጊዜው ከማለቁ በፊት እንደሚገነዘቡ ተስፋ እናደርጋለን።—ራእይ 18:4
ከጣዖት አምልኮ ሽሹ
12. አምላክ የምስልንና የጣዖትን አምልኮ እንዴት ይመለከተዋል?
12 በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የሚፈጸመው ሌላው ርኩሰት ደግሞ የምስሎችና የጣዖታት አምልኮ ነው። አምላክ እነዚህን ነገሮች “አስጸያፊ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ዘዳ. 29:17) አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ከጣዖት አምልኮ መራቅ አለባቸው፤ እንዲህ በማድረግ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም” ከሚለው የአምላክ ሐሳብ ጋር እንደሚስማሙ ያሳያሉ።—ኢሳ. 42:8
13. ከየትኞቹ ስውር የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች መሸሽ አለብን?
13 የአምላክ ቃል ስውር ስለሆኑ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶችም ይገልጻል። ለአብነት ያህል፣ መጎምጀትን “አምልኮተ ጣዖት” በማለት ጠርቶታል። (ቈላ. 3:5) መጎምጀት ሲባል የተከለከለ ነገርን ለምሳሌ የሌላ ሰው ንብረትን መመኘት ማለት ነው። (ዘፀ. 20:17) ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው መልአክ፣ እንደ ልዑል አምላክ የመሆንና የመመለክ ምኞት ነበረው። (ሉቃስ 4:5-7) እንዲህ ያለው ምኞት በይሖዋ ላይ እንዲያምጽ ያደረገው ከመሆኑም በላይ ሔዋንን በማታለል አምላክ የከለከላትን ነገር እንድትመኝ አድርጓታል። አዳምም ቢሆን ከሚስቱ ጋር ለመሆን ያለው የራስ ወዳድነት ፍላጎት አፍቃሪ የሆነውን ሰማያዊ አባቱን ከመታዘዝ እንዲበልጥበት በመፍቀዱ በጣዖት አምልኮ ተካፍሏል ማለት ይቻላል። ከዚህ በተቃራኒ ከአምላክ የቁጣ ቀን ለመሸሽ የሚፈልጉ ሁሉ ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንዲሁም ከመጎምጀት መራቅ ይኖርባቸዋል።
“ከዝሙት ሽሹ”
14-16. (ሀ) ዮሴፍ በሥነ ምግባር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ርኩስ የሆኑ የጾታ ስሜቶች ካሉን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሐ) ከዝሙት ለመሸሽ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 አንደኛ ቆሮንቶስ 6:18ን አንብብ። ዮሴፍ፣ የጲጢፋራ ሚስት ልታሳስተው በሞከረችበት ወቅት ቃል በቃል ሸሽቷል። ይህ ወጣት ላላገቡም ሆነ ትዳር ላላቸው ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! ዮሴፍ፣ አምላክ ስለ ጾታ ብልግና ያለውን አመለካከት የሚጠቁሙ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ክንውኖችን በማስታወስ ሕሊናውን አሠልጥኖት እንደነበር በግልጽ ለመመልከት ይቻላል። እኛም “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን ትእዛዝ ለመፈጸም ከፈለግን የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ሰው የጾታ ስሜት እንዲኖረን ሊያደርጉ ከሚችሉ ነገሮች እንርቃለን። “ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም:- ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል” የሚል ምክር ተሰጥቶናል።—ቈላ. 3:5, 6
15 “የእግዚአብሔር ቍጣ . . . ይመጣል” የሚለውን ሐሳብ ልብ በል። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ተገቢ ያልሆኑ የጾታ ምኞቶች አሏቸው፤ ለእነዚህ ምኞቶቻቸውም ይሸነፋሉ። በመሆኑም ክርስቲያኖች ርኩስ የሆኑ የጾታ ምኞቶች እንዳይቆጣጠሩን የአምላክን እርዳታና ቅዱስ መንፈሱን ለማግኘት መጸለይ አለብን። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ምሥራቹን ለሰዎች መስበክ ‘በመንፈስ እንድንኖር’ ይረዳናል። እንዲህ ካደረግን ደግሞ ‘የሥጋን ምኞት ከመፈጸም’ እንርቃለን።—ገላ. 5:16
16 የብልግና ምስሎችን የምንመለከት ከሆነ “በመንፈስ ኑሩ” የሚለውን መመሪያ እየተከተልን እንዳልሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲሁም እያንዳንዱ ክርስቲያን የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ከማንበብ፣ ከማየትና ከማዳመጥ መራቅ ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ቅዱስ የሆነው የአምላክ ሕዝብ’ ስለ እነዚህ ነገሮች በመቀለድም ሆነ በማውራት መደሰት የለበትም። (ኤፌ. 5:3, 4) ከእነዚህ ነገሮች የምንርቅ ከሆነ አፍቃሪ የሆነው አባታችን፣ ከሚያመጣው ቁጣ ለማምለጥና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደምንፈልግ ማወቅ ይችላል።
‘ከገንዘብ ፍቅር’ ሽሹ
17, 18. ‘ከገንዘብ ፍቅር’ መሸሽ ያለብን ለምንድን ነው?
17 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ክርስቲያን ባሪያዎች ሊመሩባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ ከእነዚህ ባሪያዎች አንዳንዶቹ፣ ጌቶቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ቁሳዊ ጥቅም እንደሚያገኙ ጠብቀው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ በክርስቲያን ወንድሞቻቸው ተጠቅመው የግል ጥቅም ለማግኘት ሞክረው ይሆናል። ጳውሎስ “መንፈሳዊው ነገር [ቁሳዊ] ትርፍ ማግኛ” እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግሯል። እንዲህ ላለው አመለካከት መንስኤው “የገንዘብ ፍቅር” ሊሆን ይችላል፤ የገንዘብ ፍቅር፣ ሀብታም ድሃ ሳይል በማንኛውም ሰው ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል።—1 ጢሞ. 6:1, 2, 5, 9, 10
18 “የገንዘብ ፍቅር” ስለነበራቸው ወይም ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ መሠረታዊ ያልሆኑ ነገሮችን ስለወደዱ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና ያጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ማስታወስ ትችላለህ? (ኢያሱ 7:11, 21፤ 2 ነገ. 5:20, 25-27) ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን እንዲህ በማለት መክሮታል:- “የአምላክ ሰው ሆይ፣ አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ። ከዚህ ይልቅ ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን ተከታተል።” (1 ጢሞ. 6:11 NW) ከሚመጣው የቁጣ ቀን ለመትረፍ የሚፈለጉ ሁሉ ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።
“ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ”
19. ወጣቶች በሙሉ ምን ያስፈልጋቸዋል?
19 ምሳሌ 22:15ን አንብብ። በወጣቶች ልብ ውስጥ ያለው ሞኝነት በቀላሉ ወደ ጥፋት ሊመራቸው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ ይህንን ለመቋቋም ይረዳል። እምነታቸውን የማይጋሯቸው ወላጆች ያሏቸው በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘትና በሥራ ለማዋል ይጥራሉ። ሌሎች ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከሚሰጧቸው ጥበብ ያዘለ ምክር ይጠቀማሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር የሚሰጠን ማንም ይሁን ማን፣ ይህንን ምክር መታዘዛችን አሁንም ሆነ ወደፊት ደስታ ያስገኝልናል።—ዕብ. 12:8-11
20. ወጣቶች ከክፉ ምኞቶች ለመሸሽ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ከየት ማግኘት ይችላሉ?
20 ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 2:20-22ን አንብብ። በርካታ ወጣቶች ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽ ባለማግኘታቸው የሞኝነት ጎዳናዎችን ተከትለዋል፤ ከእነዚህ ጎዳናዎች መካከል የውድድር መንፈስ፣ መጎምጀት፣ ዝሙት፣ የገንዘብ ፍቅርና ተድላን ማሳደድ ይገኙበታል። እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንድንሸሸው የሚመክረንን ‘የወጣትነት ክፉ ምኞት’ ያንጸባርቃሉ። አንድ ክርስቲያን ወጣት ከዚህ ዓይነቱ ምኞት ለመሸሽ ከየትኛውም አቅጣጫ ከሚመጡ ጎጂ ተጽዕኖዎች መራቅ ይኖርበታል። በተለይ ደግሞ “በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር” በመሆን አምላካዊ ባሕርያትን ለመከታተል ጥረት እንዲያደርግ የሚያበረታታውን መለኮታዊ ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።
21. ኢየሱስ ክርስቶስ በበጎች ለተመሰሉት ተከታዮቹ ምን ቃል ገብቶላቸዋል?
21 ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች፣ ሊያሳስቱን የሚሞክሩ ሰዎችን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አለመሆናችን ‘እንግዳ ከሆነው ድምፅ ከሚሸሹት’ በግ መሰል የኢየሱስ ተከታዮች መካከል መሆን እንደምንፈልግ ያሳያል። (ዮሐ. 10:5) ከአምላክ የቁጣ ቀን ለማምለጥ ግን ጎጂ ከሆኑ ነገሮች ከመሸሽ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። በጎ የሆኑ ባሕርያትንም ማፍራት ይኖርብናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ሰባቱን እንመለከታለን። ኢየሱስ “እኔ [ለበጎቼ] የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም” በማለት ቃል ስለገባልን ስለ እነዚህ ባሕርያት ይበልጥ ለማወቅ የሚያነሳሳን ጥሩ ምክንያት አለን።—ዮሐ. 10:28
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ ለሃይማኖት መሪዎቹ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር?
• በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፊታቸው ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ተደቅኖባቸዋል?
• ከየትኞቹ ስውር የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች መሸሽ ይኖርብናል?
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘ሽሹ’ የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?