ጥበቃ የሚያደርጉልን ሠረገሎችና አክሊል
“የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ብትሰሙ ይህ ይሆናል።”—ዘካ. 6:15
1, 2. ዘካርያስ ሰባተኛውን ራእይ ካየ በኋላ ባሉት ጊዜያት አይሁዳውያኑ የነበሩበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ዘካርያስ ሰባተኛውን ራእይ ካየ በኋላ ብዙ ነገር ሳያሳስበው አልቀረም። ይሖዋ ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎችን በፈጸሙት ክፉ ድርጊት የተነሳ እንደሚቀጣቸው ዋስትና ሰጥቶ ነበር። ይሖዋ የገባው ይህ ቃል ዘካርያስን አበረታቶት መሆን አለበት። ሆኖም ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ሰዎቹ አሁንም ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ማድረጋቸውንና ሌሎች ክፉ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አላቆሙም። በኢየሩሳሌም የሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታም ገና ብዙ ይቀረዋል። ለመሆኑ አይሁዳውያኑ ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ እንዲህ በፍጥነት እርግፍ አድርገው የተዉት ለምን ይሆን? ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት የግል ጉዳያቸውን ለማከናወን ብለው ነበር?
2 ዘካርያስ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን እምነት የነበራቸው ሰዎች እንደሆኑ ያውቃል። የተደላደለ ኑሯቸውንና ንግዳቸውን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት እነዚህ ወንዶችና ሴቶች “እውነተኛው አምላክ መንፈሳቸውን ያነሳሳው ሰዎች” ናቸው። (ዕዝራ 1:2, 3, 5) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢየሩሳሌምን አይተዋት አያውቁም፤ ሆኖም የኖሩበትን አካባቢ ትተው ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱን ሥራ ከፍ አድርገው ባይመለከቱት ኖሮ 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ያለውን አስቸጋሪ ጉዞ ለማድረግ አይነሱም ነበር።
3, 4. ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን ምን እንቅፋቶች አጋጥመዋቸዋል?
3 እስቲ የእነዚህ አይሁዳውያን ጉዞ ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በጉዟቸው ላይ ስለ አዲሱ መኖሪያቸው ብዙ አስበው መሆን አለበት። ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት ምን ያህል ውብ ከተማ እንደነበረች ሰምተዋል። ምክንያቱም በመካከላቸው የነበሩት አረጋውያን የቀድሞውን ቤተ መቅደስ ክብር የማየት አጋጣሚ አግኝተዋል። (ዕዝራ 3:12) አንተም ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረህ እየተጓዝክ ቢሆን አዲሷን መኖሪያህን ኢየሩሳሌምን ከሩቅ ስታያት ምን ይሰማህ ነበር? የፈራረሱ ቤቶች አረም በቅሎባቸው፣ የመጠበቂያ ማማዎቿ ተንደውና በሮቿ ወላልቀው ስታይ ታዝን ነበር? የኢየሩሳሌምን የፈራረሱ ግንቦች፣ ግዙፍና ድርብ ከሆነው የባቢሎን ግንብ ጋር ታወዳድር ነበር? ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን በዚያ ባዩት ሁኔታ ተስፋ አልቆረጡም። ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም ባደረጉት ረጅም ጉዞ ላይ የይሖዋን የማዳን እጅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተዋል። ኢየሩሳሌም እንደደረሱ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር የቀድሞው ቤተ መቅደስ በነበረበት ቦታ ላይ መሠዊያ መሥራት ነው፤ ከዚያም በየዕለቱ ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ። (ዕዝራ 3:1, 2) አይሁዳውያኑ መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ቅንዓት ሲታይ ምንም ነገር የሚያስቆማቸው አይመስልም ነበር።
4 እነዚህ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን ከመገንባት በተጨማሪ ከተሞቻቸውንም መልሰው መገንባት ነበረባቸው። ከዚህም ሌላ የሚኖሩበትን ቤት መሥራት፣ እርሻቸውን ማልማት እንዲሁም ቤተሰባቸውን መመገብ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዕዝራ 2:70) ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ሥራ በጣም ከባድ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ ብዙም ሳይቆይ ከባድ ተቃውሞ አጋጠማቸው። መጀመሪያ ላይ በአቋማቸው የጸኑ ቢሆንም ለ15 ዓመታት በዘለቀው ስደት ምክንያት ቀስ በቀስ ተስፋ እየቆረጡ ሄዱ። (ዕዝራ 4:1-4) በ522 ዓ.ዓ. የፋርስ ንጉሥ በኢየሩሳሌም በሚከናወነው የግንባታ ሥራ ላይ እገዳ ሲጥል ደግሞ ሁኔታው ጨርሶ ያበቃለት ይመስል ነበር። ከተማዋ ዳግመኛ የመገንባት ተስፋ ያላት አይመስልም ነበር።—ዕዝራ 4:21-24
5. ይሖዋ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የገጠማቸውን ሕዝቦቹን ለመርዳት ምን አደረገ?
5 ይሖዋ ሕዝቡ በዚያ ወቅት ምን እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። አምላክ ለዘካርያስ በገለጠለት የመጨረሻ ራእይ አማካኝነት ለአይሁዳውያኑ ያለውን ፍቅር እንዲሁም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ላከናወኑት ነገር ያለውን አድናቆት ገልጿል፤ በተጨማሪም ሕዝቦቹ ወደ ሥራው ከተመለሱ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ከቤተ መቅደሱ ዳግመኛ መገንባት ጋር በተያያዘም የሚከተለውን ቃል ገብቷል፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ብትሰሙ ይህ ይሆናል።”—ዘካ. 6:15
ፈረሰኛ የመላእክት ሠራዊት
6. (ሀ) ዘካርያስ በስምንተኛው ራእይ መጀመሪያ ላይ ምን ተመልክቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ፈረሶቹ የተለያየ ቀለም ያላቸው ለምንድን ነው?
6 ዘካርያስ ያየው ስምንተኛውና የመጨረሻው ራእይ ከዚያ በፊት ካያቸው ራእዮች ሁሉ ይበልጥ እምነት የሚያጠናክር ነው ማለት ይቻላል። (ዘካርያስ 6:1-3ን አንብብ።) እስቲ ራእዩን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦ “አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራሮች መካከል” ገስግሰው እየወጡ ነው፤ ሠረገሎቹ የጦር ሠረገሎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ‘ተራሮቹ የመዳብ ተራሮች’ ናቸው። ሠረገሎቹን የሚጎትቱት ፈረሶች የተለያየ ቀለም አላቸው። ይህም የሠረገሎቹን ጋላቢዎች በቀላሉ ለመለየት ያስችላል። ዘካርያስ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” ሲል ጠየቀ። (ዘካ. 6:4) እኛም የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም ይህ ራእይ እኛንም ይመለከታል።
ይሖዋ ዛሬም ሕዝቦቹን ለመጠበቅና ለማጠናከር መላእክቱን ይጠቀማል
7, 8. (ሀ) ሁለቱ ተራሮች ምን ይወክላሉ? (ለ) ተራሮቹ የመዳብ ተራሮች መሆናቸው ምን ያመለክታል?
7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራሮች መንግሥታትን ወይም አገዛዝን ሊያመለክቱ ይችላሉ። ዘካርያስ በራእዩ ላይ ያያቸው ተራሮች በዳንኤል ትንቢት ላይ ከተጠቀሱት ሁለት ተራሮች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። አንደኛው ተራራ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊና ዘላለማዊ አገዛዝ ያመለክታል። ሌላኛው ተራራ ደግሞ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛበትን መሲሐዊ መንግሥት ያመለክታል። (ዳን. 2:35, 45) ኢየሱስ በ1914 የጸደይ ወራት ላይ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ ሁለቱም ተራሮች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም በማድረግ ረገድ ልዩ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
8 ተራሮቹ የመዳብ ተራሮች መሆናቸው ምን ያመለክታል? ልክ እንደ ወርቅ ሁሉ መዳብም ውድ ዋጋ ያለው ማዕድን ነው። ይሖዋ ይህ የሚያብረቀርቅ መልክ ያለው ማዕድን ከማደሪያ ድንኳኑ፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ግንባታ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ እንዲውል መመሪያ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀ. 27:1-3፤ 1 ነገ. 7:13-16) በእርግጥም ሁለቱ ምሳሌያዊ ተራሮች የመዳብ ተራሮች መሆናቸው የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ አገዛዝና መሲሐዊው መንግሥት ያላቸውን ላቅ ያለ ደረጃ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። እነዚህ ሁለት መንግሥታት መላው የሰው ዘር ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖርና የተትረፈረፉ በረከቶችን እንዲያጭድ ያደርጋሉ።
9. ሠረገሎቹና ጋላቢዎቻቸው እነማንን ይወክላሉ? የተሰጣቸው ተልእኮስ ምንድን ነው?
9 አሁን ደግሞ ትኩረታችንን ወደ ሠረገሎቹ እንመልስ። እነዚህ ሠረገሎችና ጋላቢዎቻቸው ምን ይወክላሉ? ሠረገሎቹና ጋላቢዎቻቸው የሚወክሉት መላእክትን ሲሆን እነዚህ መላእክት በቡድን በቡድን የተደራጁ ሳይሆኑ አይቀሩም። (ዘካርያስ 6:5-8ን አንብብ።) መላእክቱ ልዩ ተልእኮ ተቀብለው ‘ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት’ እየወጡ ነው። ለመሆኑ የተሰጣቸው ተልእኮ ምንድን ነው? ሠረገሎቹና ጋላቢዎቻቸው ተልእኳቸውን የሚፈጽሙበት የተወሰነ ክልል ተሰጥቷቸዋል። ተልእኳቸው የይሖዋን ሕዝቦች ከጥቃት በተለይም ‘የሰሜን ምድር’ ማለትም ባቢሎን ከሚሰነዝርባቸው ጥቃት መጠበቅ ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹ ዳግመኛ በባቢሎን ቀንበር ሥር እንዳይገቡ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። በዘካርያስ ዘመን የነበሩት ቤተ መቅደሱን የሚገነቡ አይሁዳውያን ይህን በማወቃቸው በጣም ተጽናንተው መሆን አለበት! ጠላቶቻችን ሥራውን ያስቆሙናል ብለው መስጋት አያስፈልጋቸውም ነበር።
10. የአምላክ ሕዝቦች ስለ ሠረገሎቹና ስለ ጋላቢዎቻቸው የሚናገረውን የዘካርያስ ትንቢት መመርመራቸው ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል?
10 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በዘካርያስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ሕዝቦቹን ለመጠበቅና ለማጠናከር መላእክቱን ይጠቀማል። (ሚል. 3:6፤ ዕብ. 1:7, 14) ጠላቶች እውነተኛው አምልኮ እንዳይስፋፋ ተቃውሞ ያልሰነዘሩበት ጊዜ የለም፤ ያም ሆኖ መንፈሳዊ እስራኤል በ1919 በምሳሌያዊ ሁኔታ ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እውነተኛው አምልኮ እድገት ማድረጉንና መስፋፋቱን ቀጥሏል። (ራእይ 18:4) የመላእክት ጥበቃ ስላለን የይሖዋ ድርጅት ዳግመኛ በመንፈሳዊ የባርነት ቀንበር ውስጥ ይገባል ብለን መስጋት አያስፈልገንም። (መዝ. 34:7) ከዚህ ይልቅ በዓለም ዙሪያ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ መበልጸጋቸውን እንደሚቀጥሉ ልንተማመን እንችላለን። የዘካርያስን ራእይ መመርመራችን በሁለቱ ተራሮች ከለላ ሥር እስካለን ድረስ ምንም የሚያሰጋን ነገር እንደሌለ እርግጠኞች እንድንሆን ያስችለናል።
11. በቅርቡ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ሊያስፈራን የማይገባው ለምንድን ነው?
11 በቅርቡ የሰይጣን ዓለም ፖለቲካዊ ኃይሎች የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ግንባር ይፈጥራሉ። (ሕዝ. 38:2, 10-12፤ ዳን. 11:40, 44, 45፤ ራእይ 19:19) የሕዝቅኤል ትንቢት እነዚህ ኃይሎች በፈረሶች ላይ ተቀምጠው ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በመሆን የአምላክን ሕዝቦች ለማጥቃት በቁጣ እንደሚመጡ ይናገራል። (ሕዝ. 38:15, 16)a ታዲያ ይህ ሊያስፈራን ይገባል? በፍጹም! ፈረሰኛ የመላእክት ሠራዊት ከጎናችን እንዳለ እናውቃለን። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ባለው በዚያ ወሳኝ ወቅት የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ኃያላን መላእክት፣ አንድ ላይ በመሆን ለአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙትን ሁሉ ያጠፋሉ። (2 ተሰ. 1:7, 8) ያ ዕለት እንዴት ያለ ልዩ ቀን ይሆናል! ለመሆኑ በሰማይ ያለውን የይሖዋ ሠራዊት የሚመራው ማን ነው?
ይሖዋ ካህኑን ንጉሥ አድርጎ ሾመው
12, 13. (ሀ) ዘካርያስ ቀጥሎ ምን እንዲያደርግ ተነገረው? (ለ) ቀንበጥ ተብሎ የተጠራው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያመለክት እንዴት እናውቃለን?
12 ዘካርያስ ስምንቱን ራእዮች ያየው ብቻውን ነበር። አሁን ግን ሌሎችም ሊያዩ የሚችሉትና የአምላክን ቤተ መቅደስ የሚገነቡትን ሰዎች የሚያበረታታ ትንቢታዊ ትርጉም ያለው አንድ ነገር ሊያደርግ ነው። (ዘካርያስ 6:9-12ን አንብብ።) ዘካርያስ በቅርቡ ከባቢሎን ከተመለሱት ከሄልዳይ፣ ከጦቢያህና ከየዳያህ ብርና ወርቅ ወስዶ “ታላቅ አክሊል” እንዲሠራ ተነገረው። (ዘካ. 6:11 ግርጌ) ዘካርያስ አክሊሉን እንዲያደርግ የተነገረው ከይሁዳ ነገድ በተወለደውና የዳዊት ዘር በሆነው በገዢው በዘሩባቤል ራስ ላይ ነው? አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘካርያስ አክሊሉን ያደረገው በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ራስ ነው፤ ይህን የተመለከቱ ሰዎች ሳይገረሙ አልቀሩም።
13 በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ራስ ላይ አክሊል መደረጉ ኢያሱ ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ የሚጠቁም ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም ኢያሱ የተወለደው በዳዊት የንግሥና መስመር ስላልሆነ ንጉሥ ለመሆን ብቃቱን አያሟላም። በመሆኑም በኢያሱ ራስ ላይ አክሊል መደረጉ ወደፊት ለሚመጣው ዘላለማዊ ንጉሥና ካህን ትንቢታዊ ጥላ ነው። ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ሊቀ ካህናት ቀንበጥ ተብሎ ይጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ ቀንበጥ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።—ኢሳ. 11:1፤ ማቴ. 2:23 ግርጌ
14. ንጉሥና ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ምን ሥራ ያከናውናል?
14 በሰማይ ያለውን የይሖዋን ሠራዊት የሚመራው፣ ንጉሥም ሊቀ ካህናትም የሆነው ኢየሱስ ነው። የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩት በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ቢሆንም ኢየሱስ በቡድን ደረጃ ጥበቃ ስለሚያደርግላቸው ያለስጋት መኖር ይችላሉ። (ኤር. 23:5, 6) በቅርቡ ደግሞ ክርስቶስ ግንባር ቀደም ሆኖ መንግሥታትን ድል በማድረግ የአምላክን ሉዓላዊነት እንደሚደግፍ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሕዝቦች ይታደጋል። (ራእይ 17:12-14፤ 19:11, 14, 15) ይሁንና ቀንበጥ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ አንድ ትልቅ ሥራ አለ።
ቤተ መቅደሱን ይገነባል
15, 16. (ሀ) በዘመናችን ምን የመልሶ ማቋቋምና የማጥራት ሥራ ተከናውኗል? ይህን ሥራ ያከናወነውስ ማን ነው? (ለ) የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲያበቃ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?
15 ኢየሱስ ንጉሥና ሊቀ ካህናት በመሆን ከሚያከናውነው ሥራ በተጨማሪ “የይሖዋን ቤተ መቅደስ [የመገንባት]” ተልእኮ ተሰጥቶታል። (ዘካርያስ 6:13ን አንብብ።) በዘመናችን ኢየሱስ የሚያከናውነው የግንባታ ሥራ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችን ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ማውጣትንና የክርስቲያን ጉባኤን መልሶ ማቋቋምን ይጨምራል፤ ይህ ሥራ የተከናወነው በ1919 ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተል “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። (ማቴ. 24:45) ከዚህም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ እንዲችሉ ለመርዳት ሲል እነሱን የማጥራት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።—ሚል. 3:1-3
16 በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ኢየሱስና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙት 144,000 ነገሥታትና ካህናት ታማኝ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ ይረዷቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላ ከክፋት በጸዳችው ምድር ላይ የሚቀሩት፣ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ብቻ ይሆናሉ። በመጨረሻም እውነተኛውን አምልኮ መልሶ የማቋቋሙ ሥራ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል!
በግንባታ ሥራው ተካፈሉ
17. በመቀጠል ይሖዋ ለአይሁዳውያኑ ምን ማረጋገጫ ሰጣቸው? ይህስ በእነሱ ላይ ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል?
17 የዘካርያስ መልእክት በዘመኑ በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ምን ስሜት አሳድሮባቸው ይሆን? ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውና ሥራውን የሚያስቆመው ምንም ነገር እንደማይኖር ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ቤተ መቅደሱ እንደሚገነባ የሰጣቸው ይህ ዋስትና የዛለው ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ አድርጎ መሆን አለበት። ይሁንና ጥቂት የሆኑት አይሁዳውያን ይህን ከባድ ሥራ ዳር ማድረስ የሚችሉት እንዴት ነው? ዘካርያስ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ በውስጣቸው ሊፈጠር የሚችለውን ማንኛውንም ፍርሃት ወይም ጥርጣሬ የሚያስወግድ ነበር። እንደ ሄልዳይ፣ ጦቢያህና የዳያህ ያሉ ታማኝ ሰዎች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች ‘በይሖዋ ቤተ መቅደስ የግንባታ ሥራ እንደሚካፈሉ’ አምላክ ተናግሯል። (ዘካርያስ 6:15ን አንብብ።) አይሁዳውያኑ አምላክ እንደሚረዳቸው በመተማመን ወዲያውኑ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን እገዳው ቢኖርም ግንባታውን ማከናወናቸውን ቀጠሉ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የተራራ ያህል ግዙፍ የነበረው እንቅፋት ማለትም በግንባታ ሥራው ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ አደረገ፤ በመሆኑም በ515 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተጠናቀቀ። (ዕዝራ 6:22፤ ዘካ. 4:6, 7) ይሁንና ይሖዋ የገባው ቃል በዘመናችን ከዚህ እጅግ የላቀ ፍጻሜ ያገኛል።
18. ዘካርያስ 6:15 በዘመናችን ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
18 በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን እየተሰለፉ ሲሆን ያሏቸውን “ውድ ነገሮች” ማለትም ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ለታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ድጋፍ እያደረጉ ነው። (ምሳሌ 3:9) ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት ለመደገፍ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ዘካርያስ አክሊሉን የሠራው ሄልዳይ፣ ጦቢያህና የዳያህ ባመጡት ነገር ተጠቅሞ እንደሆነ እናስታውስ። አክሊሉም እነዚህ ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ላደረጉት አስተዋጽኦ “መታሰቢያ” ወይም “ማስታወሻ” ሆኖ አገልግሏል። (ዘካ. 6:14 ግርጌ) በተመሳሳይም ይሖዋ እኛ የምናከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለእሱ የምናሳየውን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም። (ዕብ. 6:10) ከዚህ ይልቅ ለዘላለም በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ ይኖራል።
19. ዘካርያስ ያያቸው ራእዮች ምን እንድናደርግ ሊያነሳሱን ይገባል?
19 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የይሖዋ በረከት እንዳልተለየንና በክርስቶስ አመራር ሥር እንደሆንን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው። የታቀፍነው አስተማማኝ፣ የይሖዋ ጥበቃ ባለውና ዘላለማዊ በሆነ ድርጅት ውስጥ ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዘው የይሖዋ ዓላማ “ይሆናል” ወይም ይፈጸማል። በመሆኑም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለንን ቦታ በአድናቆት እንመልከት፤ እንዲሁም ‘የአምላካችንን የይሖዋን ቃል እንስማ።’ ይህም የንጉሣችንንና የሊቀ ካህናታችንን እንዲሁም የሠረገሎቹን ጋላቢዎች ጥበቃ ያስገኝልናል። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይህ ሥርዓት ሊደመደም በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥም ሆነ ለዘላለም፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በግንቦት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 29-30 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።