ዘካርያስ ካያቸው ራእዮች ምን ትምህርት እናገኛለን?
“ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።”—ዘካ. 1:3
1-3. (ሀ) ዘካርያስ ትንቢት መናገር በጀመረበት ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር? (ለ) ይሖዋ እስራኤላውያንን ‘ወደ እሱ እንዲመለሱ’ የጠየቃቸው ለምን ነበር?
የሚበር ጥቅልል፣ በመስፈሪያ ውስጥ ያለች አንዲት ሴትና የራዛ ዓይነት ክንፎች ያላቸው በነፋስ መካከል የሚወነጨፉ ሁለት ሴቶች። የዘካርያስ መጽሐፍ እንደነዚህ ያሉ አስደናቂ ራእዮችን ይዟል። (ዘካ. 5:1, 7-9) ለመሆኑ ይሖዋ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ያሉ ራእዮችን እንዲያይ ያደረገው ለምንድን ነው? በወቅቱ እስራኤላውያን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር? በዛሬው ጊዜ የምንኖረው የአምላክ አገልጋዮችስ ዘካርያስ ካያቸው ራእዮች ምን ትምህርት እናገኛለን?
2 በ537 ዓ.ዓ. የይሖዋ ሕዝቦች በጣም ተደስተው ነበር። ለ70 ዓመታት ያህል በግዞት ከቆዩ በኋላ ከባቢሎን ነፃ የወጡት በዚህ ዓመት ነው። በመሆኑም በኢየሩሳሌም እውነተኛውን አምልኮ መልሰው ለማቋቋም በከፍተኛ ቅንዓት ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በ536 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ መሠረት ተጣለ። መሠረቱ በተጣለበት ወቅት “ሕዝቡ ድምፁ ከሩቅ እስኪሰማ ድረስ ከፍ ባለ ድምፅ ይጮኽ [ነበር]።” (ዕዝራ 3:10-13) ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የግንባታ ሥራው ተቃውሞ አጋጠመው። ሕዝቡ በወቅቱ በተፈጠሩት በርካታ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተነሳ ተስፋ ስለቆረጠ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ትቶ የራሱን መኖሪያ ቤት ወደማደራጀትና እርሻውን ወደማልማት ዞር አለ። በዚህም ምክንያት መሠረቱ ከተጣለ 16 ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ ካለበት ንቅንቅ አላለም። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች በግል ጉዳዮቻቸው መጠመዳቸውን ትተው ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ያስፈልጋቸው ነበር። ይሖዋ ሕዝቦቹ ወደ እሱ ተመልሰው እንደቀድሞው በድፍረትና በሙሉ ልብ እንዲያመልኩት ይፈልግ ነበር።
3 አምላክ ሕዝቡ መጀመሪያውኑም ከባቢሎን ነፃ የወጣበትን ምክንያት ለማስታወስ ሲል በ520 ዓ.ዓ. ዘካርያስን ነቢይ አድርጎ ላከው። “ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም ያለው ዘካርያስ የሚለው ስም በራሱ ሕዝቡ አንድ አስፈላጊ እውነት እንዲገነዘብ ሳያደርግ አልቀረም። እስራኤላውያን ይሖዋ እነሱን ለማዳን የወሰደውን እርምጃ ቢዘነጉም ይሖዋ ግን ሕዝቡን አልረሳም። (ዘካርያስ 1:3, 4ን አንብብ።) በመሆኑም በፍቅር ተነሳስቶ፣ ንጹሑን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ እንደሚረዳቸው አረጋገጠላቸው፤ በሌላ በኩል ግን በተከፋፈለ ልብ የሚቀርብ አምልኮን ጨርሶ እንደማይታገስ በመግለጽ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ይሖዋ ለዘካርያስ በገለጠለት ስድስተኛና ሰባተኛ ራእይ አማካኝነት ሕዝቡን ለተግባር ያነሳሳው እንዴት እንደሆነና እኛም ከዚህ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።
መስረቅ የሚያስከትለው መለኮታዊ ቅጣት
4. ዘካርያስ በስድስተኛው ራእዩ ላይ ምን ተመልክቷል? ጥቅልሉ በሁለቱም በኩል የተጻፈበት መሆኑ ምን ይጠቁማል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል 1 ተመልከት።)
4 ዘካርያስ ምዕራፍ 5 የሚጀምረው ስለ አንድ ለየት ያለ ራእይ በመናገር ነው። (ዘካርያስ 5:1, 2ን አንብብ።) ዘካርያስ በራእዩ ላይ ዘጠኝ ሜትር ገደማ ርዝመትና 4.5 ሜትር ገደማ ስፋት ያለው አንድ የተተረተረ ጥቅልል በሰማይ ላይ ሲበር አየ! ጥቅልሉ በላዩ ላይ የፍርድ መልእክት ተጽፎበታል። መልእክቱ የተጻፈው በሁለቱም በኩል ማለትም በጥቅልሉ ፊትና ኋላ ላይ ነው። (ዘካ. 5:3) ይህም መልእክቱ ከባድና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ይጠቁማል፤ ምክንያቱም በአብዛኛው በጥቅልል ላይ የሚጻፈው በአንድ በኩል ብቻ ነው።
5, 6. ይሖዋ ለማንኛውም ዓይነት የስርቆት ድርጊት ምን አመለካከት አለው?
5 ዘካርያስ 5:3, 4ን አንብብ። ሁሉም የሰው ዘር በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ቢሆንም ስሙን የተሸከሙት ሕዝቦቹ ደግሞ ይበልጥ ተጠያቂ ናቸው። አምላክን የሚወዱ ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ስርቆት ‘የአምላካቸውን ስም እንደሚያሰድብ’ ይገነዘባሉ። (ምሳሌ 30:8, 9) አንዳንዶች አንድ ሰው በቂ ምክንያት እስካለው ድረስ ቢሰርቅ ምንም ችግር እንደሌለው ሊያስቡ ይችላሉ፤ ይሁንና አንድ ሰው ለስርቆት የተነሳሳበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህን ድርጊት መፈጸሙ የስግብግብነት ፍላጎቱን ከአምላክ እንደሚያስበልጥና ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ቦታ እንደሚሰጥ ያሳያል። በተጨማሪም የአምላክን ሕግ አቅልሎ እንደሚመለከትና ለይሖዋም ሆነ ለስሙ አክብሮት እንደሌለው ይጠቁማል።
6 ዘካርያስ 5:3, 4 ‘እርግማኑ ወደ ሌባው ቤት ይገባል፤ በዚያም ቤት ውስጥ ይቀመጣል፤ ቤቱንም ይበላዋል’ እንደሚል ልብ በል። የይሖዋን የቅጣት ፍርድ አጥር በማጠር ወይም በር በመቆለፍ መከላከል አይቻልም። ይሖዋ በሕዝቡ መካከል የተፈጸመውን የትኛውንም የተደበቀ ኃጢአት ያጋልጣል። ግለሰቡ የስርቆት ድርጊቱን ከባለሥልጣናት፣ ከአሠሪዎቹ፣ ከሽማግሌዎች ወይም ከወላጆቹ ሊደብቅ ይችል ይሆናል፤ ማንኛውንም ዓይነት ስርቆት ገሃድ እንደሚያወጣ ቃል ከገባው አምላክ ግን ምንም ነገር መደበቅ አይቻልም። (ዕብ. 4:13) በእርግጥም “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች መካከል መሆን በጣም አስደሳች ነው!—ዕብ. 13:18
7. በሚበረው ጥቅልል ላይ ከሰፈረው እርግማን ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ስርቆት ይጠላል። እኛም ይሖዋ ካወጣቸው የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ትልቅ ክብር እንደሆነ ስለሚሰማን በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ከሚያመጣ ከማንኛውም ድርጊት እንርቃለን። ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ሆን ብለው የይሖዋን ሕጎች በሚጥሱ ሰዎች ላይ ከሚመጣው የቅጣት ፍርድ እንድንተርፍ ያስችለናል።
የገባነውን ቃል “በየቀኑ” ጠብቀን መመላለስ
8-10. (ሀ) መሐላ ምንድን ነው? (ለ) ንጉሥ ሴዴቅያስ የትኛውን መሐላ ሳይጠብቅ ቀርቷል?
8 በሚበረው ጥቅልል ላይ የተጻፈው ቀጣዩ መልእክት ‘በአምላክ ስም በሐሰት ለሚምሉ ሰዎች’ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። (ዘካ. 5:4) መሐላ፣ አንድ ሰው የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን አስረግጦ ለመግለጽ ሲል የሚናገረውን ነገር ወይም አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሚገባውን ቃል ያመለክታል።
9 በይሖዋ ስም መማል በጣም ከባድ ነገር ነው። በኢየሩሳሌም በነገሠው የመጨረሻው ንጉሥ ላይ የደረሰው ሁኔታ ይህን ያሳያል። ሴዴቅያስ ለባቢሎን ንጉሥ በታማኝነት እንደሚገዛ በይሖዋ ስም ምሎ የነበረ ቢሆንም መሐላውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ የሚል ፍርድ አስተላልፎበታል፦ “በሕያውነቴ እምላለሁ . . . [ሴዴቅያስ] ንጉሥ አድርጎ የሾመው ንጉሥ በሚኖርበት ቦታ ይኸውም በባቢሎን ይሞታል፤ ይህ ሰው መሐላውን አቃሎበታል፤ ቃል ኪዳኑንም አፍርሶበታል።”—ሕዝ. 17:16
10 ንጉሥ ሴዴቅያስ መሐላውን የፈጸመው በአምላክ ስም በመማል ነበር፤ ይሖዋም ይህን መሐላውን እንዲፈጽም ይጠብቅበት ነበር። (2 ዜና 36:13) እሱ ግን ከባቢሎን ቀንበር ነፃ መውጣት ስለፈለገ መሐላውን በማፍረስ የግብፅን እርዳታ ጠየቀ፤ ሆኖም ያደረገው ሙከራ ከንቱ ነበር።—ሕዝ. 17:11-15, 17, 18
11, 12. (ሀ) ከገባናቸው ቃሎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የትኛው ነው? (ለ) ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንደምንኖር በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ እኛም ቃል በምንገባበት ጊዜ የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ የገባነውን ቃል አክብዶ ይመለከተዋል። በመሆኑም የእሱን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን ቃላችንን መጠበቅ አለብን። (መዝ. 76:11) ከገባናቸው ቃሎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ደግሞ ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነው ቃል እንደሆነ የታወቀ ነው። ራስን መወሰን፣ አንድ ሰው ይሖዋን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማገልገል የሚገባው ከባድ ቃለ መሐላ ነው።
12 ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንደምንኖር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከባድም ሆነ ቀላል ፈተና ሲያጋጥመን የምንወስደው እርምጃ “በየቀኑ” ይሖዋን ለማወደስ የገባነውን ቃል አክብደን እንደምንመለከት የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። (መዝ. 61:8) ለምሳሌ ያህል፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት አንድ ሰው ሊያሽኮረምምህ በሚሞክርበት ጊዜ ቆራጥ አቋም በመውሰድ ‘የይሖዋን መንገድ እንደምትወድ’ ታሳያለህ? (ምሳሌ 23:26) አሊያም ደግሞ የምትኖረው ይሖዋን በማያመልክ ቤተሰብ ውስጥ ነው እንበል። ከቤተሰብህ መካከል የይሖዋን መመሪያዎች ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርግ ማንም ሰው ባይኖርም ክርስቲያናዊ አቋምህን ጠብቀህ ለመኖር እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ትጠይቀዋለህ? በሰማይ ወዳለው አፍቃሪ አባትህ በየቀኑ በመጸለይ ፍቅር ስላሳየህና በእሱ አገዛዝ ሥር እንድትሆን ስላስቻለህ ታመሰግነዋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ ትመድባለህ? እስቲ አስበው፤ ራስህን በወሰንክበት ወቅት እነዚህን ነገሮች እንደምታደርግ ቃል ገብተህ የለም? በመሆኑም ይህ የታዛዥነት ጉዳይ ነው። በይሖዋ አምልኮ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግህ እሱን እንደምትወደውና ራስህን ለእሱ የወሰንከው ከልብህ እንደሆነ ያሳያል። ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ እንዲሁ በዘልማድ የሚደረግ ሳይሆን መላ ሕይወታችንን የሚነካ ጉዳይ ነው። ደግሞም የገባነውን ቃል በመጠበቃችን የምንጠቀመው እኛው ራሳችን ነን፤ ምክንያቱም ታማኝ መሆናችን አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል።—ዘዳ. 10:12, 13
13. ዘካርያስ ካየው ስድስተኛ ራእይ ምን እንማራለን?
13 ዘካርያስ ያየው ስድስተኛ ራእይ ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ከማንኛውም ዓይነት ስርቆት መራቅ እንዲሁም በሐሰት ከመማል መቆጠብ እንዳለባቸው እንድ ንገነዘብ ረድቶናል። በተጨማሪም ይህ ራእይ እስራኤ ላውያን በተደጋጋሚ ስህተት ቢሠሩም ይሖዋ እንዳልተዋቸው ያሳያል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ተከበው መኖራቸው ምን ያህል ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው እንደሚችል ተረድቶላቸው ነበር። ከዚህም ሌላ ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ እንደተወልንና እኛም እንዲሁ እንድናደርግ እንደሚረዳን ያስገነዝበናል። ይሖዋ እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ደግሞ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስደሳች ተስፋ በመስጠት ነው፤ በቅርቡ ክፋትን ሁሉ ከምድር ላይ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ የሚገልጽ ተስፋ ሰጥቶናል። ዘካርያስ ያየው ቀጣዩ ራእይ ይህ አስደሳች ተስፋ እንደሚፈጸም ያረጋግጣል።
ክፋትን ‘በተገቢው ቦታዋ ላይ ማስቀመጥ’
14, 15. (ሀ) ዘካርያስ በሰባተኛው ራእይ ላይ ምን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል 2 ተመልከት።) (ለ) በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ ያለችው ሴት ምን ታመለክታለች? በመስፈሪያው ውስጥ እንድትቀመጥና እንዲዘጋባት የተደረገውስ ለምንድን ነው?
14 ዘካርያስ የሚበረውን ጥቅልል ካየ በኋላ መልአኩ “ቀና ብለህ . . . ተመልከት” አለው። ይሖዋ በሰባተኛው ራእይ ላይ ለዘካርያስ ምን ይገልጥለት ይሆን? ዘካርያስ በራእዩ ላይ “ኢፍ” ተብሎ የሚጠራ መስፈሪያ ሲወጣ አየ። (ዘካርያስ 5:5-8ን አንብብ።) ይህ መካከለኛ መጠን ያለው መስፈሪያ ‘ከእርሳስ የተሠራ ክብ መክደኛ’ አለው። መክደኛው ሲነሳ ዘካርያስ በመስፈሪያው ውስጥ “አንዲት ሴት ተቀምጣ” አየ። መልአኩ ይህች ሴት “ክፋትን” እንደምታመለክት ገለጸ። ዘካርያስ ይህች ሴት ከመስፈሪያው ለመውጣት ስትጣጣር ሲያይ ምን ያህል ሊደነግጥ እንደሚችል እስቲ አስበው! ከዚያም መልአኩ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ሴቲቱን መልሶ መስፈሪያው ውስጥ ከጣላት በኋላ ከባዱን መክደኛ በመስፈሪያው አፍ ላይ ገጠመው። የዚህ ራእይ ትርጉም ምንድን ነው?
15 ይህ ራእይ እንደሚያሳየው ይሖዋ በሕዝቡ መካከል የሚፈጸምን ማንኛውንም ክፋት በቸልታ አያልፍም። ከዚህ ይልቅ በቁጥጥር ሥር እንዲውልና በፍጥነት እንዲወገድ ያደርጋል። (1 ቆሮ. 5:13) መልአኩ ከእርሳስ የተሠራውን መክደኛ በመስፈሪያው አፍ ላይ መግጠሙ ይህን ያረጋግጥልናል።
16. (ሀ) በመቀጠል ዘካርያስ የኢፍ መስፈሪያው ምን ሲሆን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል 3 ተመልከት።) (ለ) ክንፍ ያላቸው ሁለት ሴቶች የኢፍ መስፈሪያውን ወዴት ወሰዱት?
16 በመቀጠልም ዘካርያስ የራዛ ዓይነት ጠንካራ ክንፎች ያሏቸው ሁለት ሴቶች ተመለከተ። (ዘካርያስ 5:9-11ን አንብብ።) እነዚህ ሴቶች በመስፈሪያው ውስጥ ካለችው ሴት ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ! በጠንካራ ክንፎቻቸው ተወንጭፈው በመምጣት “ክፋትን” የያዘውን መስፈሪያ ወደ ላይ አነሱት። መስፈሪያውን ወዴት ይወስዱት ይሆን? መስፈሪያውን ወስደው ‘በሰናኦር ምድር’ ማለትም በባቢሎን አስቀመጡት። ለመሆኑ እነዚህ ሴቶች መስፈሪያውን ወደ ባቢሎን የወሰዱት ለምንድን ነው?
17, 18. (ሀ) ሰናኦር “ክፋትን” ለማስቀመጥ ‘ተገቢ ቦታ’ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ክፋትን በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
17 በዘካርያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ሰናኦር ክፋትን ለማስቀመጥ ተገቢ ቦታ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግታቸውም። ዘካርያስም ሆነ በዘመኑ የነበሩት ሌሎች አይሁዳውያን ባቢሎን ክፋት የነገሠባት ቦታ እንደሆነች በገዛ ዓይናቸው ተመልክተዋል። በሥነ ምግባር ባዘቀጠችውና በጣዖት አምልኮ በተሞላችው በዚህች ከተማ ውስጥ ያደጉት እነዚህ አይሁዳውያን በዙሪያቸው ያለው አረማዊ ሥርዓት ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው በየቀኑ ትግል ማድረግ ነበረባቸው። ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ ከክፋት እንደሚጠብቅ ዋስትና የሚሰጠው ይህ ራእይ በእርግጥም ትልቅ እፎይታ አምጥቶላቸው መሆን አለበት!
18 በተጨማሪም ይህ ራእይ አይሁዳውያኑ፣ የሚያቀርቡት አምልኮ ከክፋት የጸዳ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝቧቸዋል። ክፋት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሰርጎ እንዲገባና በመካከላቸው እንዲኖር እንደማይፈቀድለት ደግሞም ሊፈቀድለት እንደማይገባ ግልጽ ነው። ጥበቃና ፍቅራዊ እንክብካቤ በምናገኝበት እንዲሁም ንጹሕ በሆነው የአምላክ ድርጅት ውስጥ የታቀፍን እንደመሆናችን መጠን ይህ ንጽሕና ተጠብቆ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለብን። ታዲያ የይሖዋ ድርጅት ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን የማድረግ ተነሳሽነት አለን? በመንፈሳዊ ገነታችን ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ክፋት ቦታ የለውም።
ይሖዋን የሚያስከብር ንጹሕ ሕዝብ
19. ዘካርያስ ካያቸው አስደናቂ ራእዮች ምን ትምህርት እናገኛለን?
19 ዘካርያስ ያየው ስድስተኛውና ሰባተኛው ራእይ ሐቀኝነት በጎደለው አካሄዳቸው ለሚቀጥሉ ሰዎች ይሖዋ መጥፎ ድርጊትን ችላ ብሎ እንደማያልፍ የሚያስገነዝብ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ይሖዋን በንጹሕ ልቦና የሚያመልኩ አገልጋዮቹ ደግሞ ለክፋት ከፍተኛ ጥላቻ ሊኖራቸው ይገባል። ዘካርያስ ያያቸው ራእዮች ይሖዋ የሰጠንን ፍቅራዊ ማረጋገጫም ይዘዋል። የአምላክ ሞገስና ጥበቃ ያለን ሰዎች ለመሆን ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ሞትን ከሚያስከትለው እርግማን ማምለጥ እንችላለን። በተጨማሪም የይሖዋን በረከት እናገኛለን። በክፋት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆነን ለመኖር የምናደርገው ትግል ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይደለም። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ እንደሚሳካልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! ይሁንና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ እውነተኛው አምልኮ ድል እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ታላቁ መከራ እየቀረበ ሲሄድ ይሖዋ ድርጅቱን እንደሚጠብቅ ምን ዋስትና አለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።