የጥናት ርዕስ 14
አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ እየፈጸምክ ነው?
“ምሥራቹን መስበክህን ቀጥል እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።”—2 ጢሞ. 4:5 ግርጌ
መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ
የትምህርቱ ዓላማa
1. ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ምን ማድረግ ይፈልጋሉ? ለምንስ? (ሽፋኑን ተመልከት።)
ክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” በማለት አዟቸዋል። (ማቴ. 28:19) ሁሉም ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች፣ የተሰጣቸውን ይህን የአገልግሎት ተልእኮ ‘በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይፈልጋሉ። (2 ጢሞ. 4:5) ምክንያቱም ይህ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ልናከናውነው ከምንችለው ከየትኛውም ሥራ ይበልጥ አስፈላጊ፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና አጣዳፊ ነው። ሆኖም የምንፈልገውን ያህል ጊዜ ለአገልግሎቱ መስጠት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል።
2. አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ተፈታታኝ እንዲሆንብን የሚያደርጉት የትኞቹ ነገሮች ናቸው?
2 ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚሻሙብን ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ስንል በቀን ውስጥ ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅብን ይሆናል። ከዚህም ሌላ ተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነት ሊኖርብን አሊያም ከሕመም፣ ከመንፈስ ጭንቀት ወይም የዕድሜ መግፋት ከሚያስከትላቸው ችግሮች ጋር እየታገልን ሊሆን ይችላል። ታዲያ እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቁመን አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?
3. በማቴዎስ 13:23 ላይ ከሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ምን እንገነዘባለን?
3 ያለንበት ሁኔታ ለይሖዋ አገልግሎት የምናውለውን ጊዜ የሚገድብብን ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ኢየሱስ ሁላችንም የመንግሥቱን ፍሬ በእኩል መጠን ማፍራት እንደማንችል ያውቃል። (ማቴዎስ 13:23ን አንብብ።) ይሖዋ ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በእሱ አገልግሎት የምናከናውነውን ማንኛውንም ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብ. 6:10-12) በሌላ በኩል ደግሞ ሁኔታችን በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ተሳትፎ ለማድረግ እንደሚፈቅድልን ይሰማን ይሆናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ለአገልግሎታችን ቅድሚያ መስጠት፣ ኑሯችንን ቀላል ማድረግ እንዲሁም የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በቅድሚያ ግን ‘አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ሲባል ምን ማለት ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መልስ እንመርምር።
4. አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ሲባል ምን ማለት ነው?
4 በአጭር አነጋገር፣ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ሲባል በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም ይህ በአገልግሎት ከምናሳልፈው ጊዜ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ይሖዋ አገልግሎቱን ለማከናወን ለተነሳሳንበትም ምክንያት ትኩረት ይሰጣል። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንንb በሙሉ ነፍሳችን የምናከናውነው፣ ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ ነው። (ማር. 12:30, 31፤ ቆላ. 3:23) አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ሲባል ሁለንተናችንን ለእሱ መስጠት ማለት ነው፤ ይህም አቅማችን እስከፈቀደው ድረስ ኃይላችንንና ጉልበታችንን ለእሱ አገልግሎት ማዋልን ይጠይቃል። ለተሰጠን ውድ የስብከት ሥራ አድናቆት ካለን ምሥራቹን በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ጥረት እናደርጋለን።
5-6. አንድ ሰው፣ ጊዜው የተጣበበ ቢሆንም ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
5 እስቲ ጊታር መጫወት የሚወድን አንድ ወጣት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ወጣት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጊታር መጫወት ያስደስተዋል። ከጊዜ በኋላ፣ በአካባቢው በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ጊታር እንዲጫወት ተቀጠረ። ሆኖም የሚያገኘው ገቢ ወጪውን ለመሸፈን በቂ አልሆነም። በመሆኑም ከሰኞ እስከ ዓርብ በአንድ መደብር ውስጥ ገንዘብ ተቀባይ ሆኖ መሥራት ጀመረ። አብዛኛውን ጊዜውን የሚይዘው ይህ ሥራ ቢሆንም ልቡ ያለው ሙዚቃው ላይ ነው። ስለዚህ ችሎታውን አሻሽሎ ሙሉ በሙሉ በዚህ ሥራ ላይ ለመሰማራት ይጓጓል። እስከዚያው ድረስ ግን ለአጭር ጊዜም ቢሆን፣ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ጊታር ለመጫወት ይሞክራል።
6 አንተም በተመሳሳይ፣ የምትፈልገውን ያህል ጊዜ በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ አትችል ይሆናል። ሆኖም ይህ የምትወደው ሥራ ነው። በመሆኑም ችሎታህን በማሻሻል የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ምሥራቹን ለመስበክ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለህ። ይሁንና ጊዜህን የሚሻሙብህ ብዙ ነገሮች ከመኖራቸው አንጻር ‘ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
ለአገልግሎትህ ቅድሚያ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?
7-8. ኢየሱስ ለአገልግሎት የነበረውን አመለካከት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ለአገልግሎት የነበረው አመለካከት ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበኩ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። (ዮሐ. 4:34, 35) በተቻለው መጠን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ሲል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ከቤት ወደ ቤትም ሆነ ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ቦታዎች ይሰብክ ነበር። የኢየሱስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ ነበር።
8 እኛም ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ በመከተል በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለሰዎች ምሥራቹን የምንሰብክበት አጋጣሚ እንፈልጋለን። በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመካፈል ስንል የራሳችንን ምቾት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። (ማር. 6:31-34፤ 1 ጴጥ. 2:21) በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ልዩ አቅኚ፣ የዘወትር አቅኚ ወይም ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ። ሌሎች ደግሞ አዲስ ቋንቋ ለመማር ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ለማገልገል የሚያስችላቸውን እርምጃ ወስደዋል። ሆኖም አብዛኛው የወንጌላዊነት ሥራ የሚከናወነው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ በሚጥሩ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነው። ሁኔታችን ምንም ሆነ ምን፣ ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ሁላችንም “ደስተኛው አምላክ [የገለጸውን] ክብራማ ምሥራች” ስናውጅ ለእሱ በምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት እንድንደሰት ይፈልጋል።—1 ጢሞ. 1:11፤ ዘዳ. 30:11
9. (ሀ) ጳውሎስ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት የነበረበት ቢሆንም ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ ይሰጥ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የሐዋርያት ሥራ 28:16, 30, 31 ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ስለነበረው አመለካከት ምን ይጠቁመናል?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በቆሮንቶስ ሳለ፣ ወጪውን ለመሸፈን ገንዘብ ስላስፈለገው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ድንኳን ለመሥራት ተገዶ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ ድንኳን መስፋትን እንደ ዋነኛ ሥራው አድርጎ አልተመለከተውም። በዚህ ሙያ የተሰማራው ራሱን በመደገፍ በቆሮንቶስ ለነበሩ ሰዎች ምሥራቹን “ያለዋጋ” ለመስበክ ማለትም በእነሱ ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል ነው። (2 ቆሮ. 11:7) ጳውሎስ የተወሰነ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ያስፈለገው ቢሆንም ለአገልግሎቱ ምንጊዜም ቅድሚያ ይሰጥ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በየሰንበቱ ይሰብክ ነበር። ያለበት ሁኔታ ሲስተካከል ግን በስብከቱ ሥራ ላይ ይበልጥ ማተኮር ችሏል። ጳውሎስ “ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ [በመጠመድ] ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ መሆኑን እያስረዳ ለአይሁዳውያን ይመሠክር ነበር።” (ሥራ 18:3-5፤ 2 ቆሮ. 11:9) ከጊዜ በኋላም በሮም ውስጥ ለሁለት ዓመት ያህል የቁም እስረኛ ሳለ፣ ደብዳቤዎችን ይጽፍ እንዲሁም ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች ይመሠክር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:16, 30, 31ን አንብብ።) ጳውሎስ ለአገልግሎቱ የሚሰጠውን ትኩረት ምንም ነገር እንዳይከፋፍልበት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። “ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 4:1) እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ቢኖርብንም በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠት እንችላለን።
10-11. በጤና እክል ምክንያት የአቅም ገደብ ቢኖርብንም አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?
10 ከቤት ወደ ቤት የምናከናውነው አገልግሎት በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት ከተገደበ በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል እንችላለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንጌላውያን፣ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ይሰብኩ ነበር። በየትኛውም አጋጣሚ ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ‘ለሚያገኟቸው ሰዎች’ እውነትን ይናገሩ ነበር። (ሥራ 17:17፤ 20:20) ብዙ መራመድ የሚከብደን ከሆነ፣ ሰው በሚበዛበት ቦታ ተቀምጠን ለአላፊ አግዳሚው መስበክ እንችል ይሆናል። አሊያም መደበኛ ባልሆነ መንገድ፣ በደብዳቤ ወይም በስልክ መመሥከር እንችላለን። ከባድ የአቅም ገደብ ያለባቸው በርካታ አስፋፊዎች በእነዚህ ተጨማሪ የአገልግሎት ዘርፎች በመካፈል ከፍተኛ ደስታና እርካታ ማግኘት ችለዋል።
11 የጤና እክል ቢኖርብህም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ትችላለህ። እስቲ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በድጋሚ እንመልከት። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ብሏል። (ፊልጵ. 4:13) ጳውሎስ ከሚስዮናዊ ጉዞዎቹ በአንዱ ላይ የጤና እክል ባጋጠመው ጊዜ ይህ ኃይል አስፈልጎት ነበር። በገላትያ ላሉ ክርስቲያኖች “ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናንተ ምሥራቹን ለመስበክ አጋጣሚ ያገኘሁት በመታመሜ የተነሳ [ነበር]” ብሏቸዋል። (ገላ. 4:13) አንተም ያለብህ የጤና እክል ለሐኪሞች፣ ለነርሶችና ለሚንከባከቡህ ሰዎች ምሥራቹን የምትሰብክበት አጋጣሚ ሊከፍትልህ ይችላል። እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ቦታ ስለሚውሉ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አያገኟቸውም።
ኑሮህን ቀላል ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
12. ዓይናችን “በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ” እንዲሆን ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?
12 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ [ወይም “ቀላል፣” ግርጌ] ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል።” (ማቴ. 6:22) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ትኩረታችንን ከሚከፋፍሉ ነገሮች በመራቅ ኑሯችንን ቀላል አሊያም በአንድ ግብ ወይም ዓላማ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ እንዳለብን መናገሩ ነበር። ኢየሱስ ራሱ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ ላይ በማድረግ ምሳሌ ትቶልናል፤ ደቀ መዛሙርቱንም ትኩረታቸው ምንጊዜም በአገልግሎታቸውና በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲሆን አስተምሯቸዋል። እኛም ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ በመፈለግ’ ሕይወታችን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር የምናደርግ ከሆነ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን።—ማቴ. 6:33
13. በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ ለማተኮር ምን ሊረዳን ይችላል?
13 በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ኑሯችንን ቀላል ማድረግ ነው፤ ይህም ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ለመርዳት የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ እንድናገኝ ይረዳናል።c ለምሳሌ በሳምንቱ ውስጥ ለአገልግሎት የምናውለው ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንድንችል ሰብዓዊ ሥራ በምንሠራበት ሰዓት ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንችል ይሆን? ረዘም ያለ ጊዜ ከሚወስዱብን መዝናኛዎች ላይ የተወሰነ ጊዜ መቀነስ እንችል ይሆን?
14. አንድ ባልና ሚስት ለአገልግሎታቸው ተጨማሪ ጊዜና ትኩረት ለመስጠት ሲሉ ምን ማስተካከያ አድርገዋል?
14 ኤልያስ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ባለቤቱ ያደረጉት ይህንኑ ነው። ኤልያስ እንዲህ ብሏል፦ “ወዲያውኑ አቅኚ መሆን ባንችል እንኳ በስብከቱ ሥራ ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ እንዳለብን ተሰምቶን ነበር። በመሆኑም በአገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ የሚረዱንን ቀለል ያሉ እርምጃዎች ወሰድን። ለምሳሌ ወጪያችንን ቀነስን፣ ለመዝናኛ እናውል በነበረው ሰፊ ጊዜ ላይ ማስተካከያ አደረግን እንዲሁም አሠሪዎቻችን የሥራ ሰዓታችንን እንዲቀንሱልን ጠየቅን። በውጤቱም በምሽት አገልግሎት መካፈል፣ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት፣ አልፎ ተርፎም በሳምንቱ መካከል በወር ሁለቴ አገልግሎት መውጣት ችለናል። በዚህ በጣም ደስተኞች ነን!”
የመስበክና የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?
15-16. በ1 ጢሞቴዎስ 4:13, 15 መሠረት የወንጌላዊነት ችሎታችንን እያሻሻልን መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? (“አገልግሎቴን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚረዱኝ ግቦች” የሚለውንም ሣጥን ተመልከት።)
15 አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችልበት ሌላው መንገድ በስብከቱ ሥራ ችሎታችንን ማሻሻል ነው። በአንዳንድ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች እውቀታቸውንና ችሎታቸውን ለማሻሻል ቀጣይ የሆነ ትምህርትና ሥልጠና እንዲወስዱ ይጠበቅባቸዋል። ከመንግሥቱ ሰባኪዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችልበትን መንገድ በቀጣይነት መማር ይኖርብናል።—ምሳሌ 1:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13, 15ን አንብብ።
16 ታዲያ የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው? በየሳምንቱ በምናደርገው የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ ለምናገኛቸው መመሪያዎች ትኩረት በመስጠት ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ከመስክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ችሎታችንን ደረጃ በደረጃ እንድናሳድግ የሚረዳ ጠቃሚ ሥልጠና እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ መንበሩ ክፍል ላቀረቡ ተማሪዎች ምክር ሲሰጥ እኛም በአገልግሎታችን ማሻሻያ ልናደርግ የምንችልባቸውን ነጥቦች እንማራለን። በቀጣዩ ጊዜ ምሥራቹን ስንሰብክ እነዚህን ነጥቦች ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን። የመስክ አገልግሎት ቡድናችን የበላይ ተመልካች እንዲረዳን መጠየቃችን አሊያም ከእሱ ወይም ልምድ ካለው ሌላ አስፋፊ፣ አቅኚ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር አብረን ማገልገላችን ይረዳናል። እያንዳንዱን የማስተማሪያ መሣሪያ በመጠቀም ረገድ ችሎታችንን እያሳደግን ስንሄድ የመስበክና የማስተማር ሥራው ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል።
17. አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ስትፈጽም ምን በረከቶች ታገኛለህ?
17 ይሖዋ ከእሱ ጋር ‘አብረን እንድንሠራ’ የጋበዘን መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (1 ቆሮ. 3:9) “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች [ለይተህ] በማወቅ” በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ ‘ይሖዋን በደስታ ማገልገል’ ትችላለህ። (ፊልጵ. 1:10፤ መዝ. 100:2) ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ወይም የአቅም ገደብ ቢኖርብህ የአምላክ አገልጋይ ስለሆንክ እሱ አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችልህን ኃይል እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ሁን! (2 ቆሮ. 4:1, 7፤ 6:4) ያለህበት ሁኔታ በስብከቱ ሥራ ሰፊ ጊዜ እንድታሳልፍ ፈቀደልህም አልፈቀደልህ አገልግሎትህን በሙሉ ነፍስ እስካከናወንክ ድረስ ‘እጅግ የምትደሰትበት ነገር’ ታገኛለህ። (ገላ. 6:4) አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ስትፈጽም ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር እንዳለህ ታሳያለህ። “ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ።”—1 ጢሞ. 4:16
መዝሙር 58 ሰላም ወዳዶችን መፈለግ
a ሁላችንም የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ ተሰጥቶናል። ይህ ርዕስ፣ በግለሰብ ደረጃ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም እንኳ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በስብከቱ ሥራችን ይበልጥ ውጤታማና ደስተኛ መሆን የምንችልበትን መንገድ እንማራለን።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ፣ ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን የመገንባቱንና የመጠገኑን ሥራ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራን ያካትታል።—2 ቆሮ. 5:18, 19፤ 8:4
c በሐምሌ 2016 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10 ላይ በሚገኘው “ኑሯችሁን ማቅለል የምትችሉት እንዴት ነው?” በሚለው ሣጥን ሥር የተጠቀሱትን ሰባት ነጥቦች ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ የተመላልሶ መጠየቅ ክፍል ስታቀርብ። ከዚያም የስብሰባው ሊቀ መንበር ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ማስተማር በተባለው ብሮሹር ላይ ማስታወሻ ስትይዝ። በኋላም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አገልግሎት ወጥታ፣ በስብሰባው ላይ የተማረችውን ነገር ተግባራዊ ስታደርግ።