የጥናት ርዕስ 11
ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
‘አምላክ ጽናትን ይሰጣል።’—ሮም 15:5
መዝሙር 94 ለአምላክ ቃል አመስጋኝ መሆን
ማስተዋወቂያa
1. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ዓይነት ፈተና ሊያጋጥማቸው ይችላል?
ከባድ ፈተና አጋጥሞሃል? ምናልባት በጉባኤህ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ስሜትህን ጎድቶት ይሆናል። (ያዕ. 3:2) ወይም ደግሞ ይሖዋን በማገልገልህ ምክንያት የሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ የሚማሩ ልጆች ያሾፉብህ ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) አሊያም ደግሞ ቤተሰቦችህ በስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ወይም ስለ እምነትህ እንዳትመሠክር ሊከለክሉህ እየሞከሩ ይሆናል። (ማቴ. 10:35, 36) የገጠመህ ፈተና በጣም ከባድ ከሆነብህ ይሖዋን ማገልገልህን ለማቆም ትፈተን ይሆናል። ሆኖም ያጋጠመህ ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጥበብና ፈተናውን በጽናት ለመቋቋም የሚረዳ ብርታት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
2. በሮም 15:4 መሠረት የአምላክን ቃል ማንበብ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
2 ይሖዋ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ከባድ ፈተናዎችን የተቋቋሙት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ዝርዝር ሐሳቦችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ለእኛ ትምህርት እንዲሆን አስቦ ነው። ይሖዋ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት በሮም 15:4 ላይ የነገረን ይህንን ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዘገባዎች ማንበባችን መጽናኛና ተስፋ ሊሰጠን ይችላል። ሆኖም የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ብቻውን በቂ አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናነበው ነገር አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው እና ልባችንን እንዲነካው መፍቀድ ይኖርብናል። ያጋጠመንን ፈተና ለመወጣት የሚረዳ መመሪያ ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ እንችላለን? የሚከተሉትን አራት እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን፦ (1) መጸለይ፣ (2) በዓይነ ሕሊና መሣል፣ (3) ማሰላሰል እና (4) በተግባር ማዋል። እነዚህን አራት እርምጃዎች መውሰድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመረምራለን።b ከዚያም ንጉሥ ዳዊት እና ሐዋርያው ጳውሎስ ካጋጠማቸው ነገር ትምህርት ለማግኘት እነዚህን አራት እርምጃዎች መውሰድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
3. የመጽሐፍ ቅዱስን ንባብህን ከመጀመርህ በፊት ምን ማድረግ አለብህ? ለምንስ?
3 (1) መጸለይ። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ከመጀመርህ በፊት ከምታነበው ነገር ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ለምሳሌ አንድን ችግር ለመወጣት የሚረዳ ምክር ማግኘት ከፈለግህ በዚህ ረገድ የሚረዱህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቃሉ ውስጥ ለማግኘት እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ ያዕ. 1:5
4. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሕያው እንዲሆንልህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
4 (2) በዓይነ ሕሊና መሣል። ይሖዋ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናችን የመሣል አስደናቂ ችሎታ ሰጥቶናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሕያው እንዲሆንልህ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣልና ራስህን በዋናው ባለታሪክ ቦታ ለማስቀመጥ ጥረት አድርግ። ባለታሪኩ ያየው ነገር እንዲታይህና የተሰማው ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ ሞክር።
5. ማሰላሰል ምንድን ነው? ማሰላሰል የምንችለውስ እንዴት ነው?
5 (3) ማሰላሰል። ማሰላሰል ማለት ስላነበብከው ነገርና ዘገባው ለአንተ ስለያዘው ትምህርት በጥልቀት ማሰብ ማለት ነው። ማሰላሰልህ ነጥቦቹን ለማያያዝና ርዕሰ ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳት ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ ምግብ ለማብሰል የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን ሰብስቦ ጠረጴዛ ላይ ከማስቀመጥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ማሰላሰል ደግሞ እነዚህን ጥሬ ዕቃዎች ተጠቅሞ ጣፋጭ ምግብ እንደማብሰል ነው። ለማሰላሰል እንዲረዳህ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መሞከር ትችላለህ፦ ‘በዘገባው ላይ የተጠቀሰው ዋነኛው ባለታሪክ ችግሩን ለመፍታት ምን እርምጃ ወስዷል? ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው? ከዘገባው ያገኘሁትን ትምህርት ያጋጠመኝን ችግር ለመቋቋም ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’
6. የተማርነውን ነገር በተግባር ማዋል ያለብን ለምንድን ነው?
6 (4) በተግባር ማዋል። ኢየሱስ የተማረውን ነገር በተግባር የማያውል ሰው፣ ቤቱን በአሸዋ ላይ ከሠራ ሰው ጋር እንደሚመሳሰል ተናግሯል። ይህ ሰው ቤቱን ለመገንባት ተግቶ ቢሠራም ልፋቱ ከንቱ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጎርፍ ሲጎርፍና ነፋስ ሲነፍስ ቤቱ ይደረመሳል። (ማቴ. 7:24-27) እኛም በተመሳሳይ ብንጸልይም፣ በዓይነ ሕሊናችን ብንሥልም እንዲሁም ብናሰላስልም ከዘገባው ያገኘነውን ትምህርት በተግባር እስካላዋልን ድረስ ጥረታችን ከንቱ ነው። ፈተና ወይም ስደት ሲያጋጥመን ለመጽናት የሚያስችል ጠንካራ እምነት አይኖረንም። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና እና የተማርነውን ነገር በተግባር ስናውል የተሻለ ውሳኔ እናደርጋለን፣ ውስጣዊ ሰላም ይኖረናል እንዲሁም እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። (ኢሳ. 48:17, 18) ከዚህ በመቀጠል እስካሁን ያየናቸውን አራት እርምጃዎች ተጠቅመን፣ ንጉሥ ዳዊት በአንድ ወቅት ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።
ከንጉሥ ዳዊት ምን እንማራለን?
7. የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንመለከታለን?
7 ጓደኛህ ወይም የቤተሰብህ አባል በሆነ መንገድ ጎድቶሃል? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ስለ ንጉሥ ዳዊት እና ስለ ልጁ ስለ አቢሴሎም የሚገልጸውን ታሪክ መመርመርህ ሊጠቅምህ ይችላል። አቢሴሎም አባቱን በመክዳት ንግሥናውን ሊነጥቀው ሞክሮ ነበር።—2 ሳሙ. 15:5-14, 31፤ 18:6-14
8. የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?
8 (1) መጸለይ። ዘገባውን በአእምሮህ ይዘህ፣ የደረሰብህ በደል ምን ስሜት እንደፈጠረብህ ለይሖዋ ንገረው። (መዝ. 6:6-9) ስሜትህን ግልጥልጥ አድርገህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከዚያም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።
9. ስለ ዳዊት እና ስለ አቢሴሎም የሚገልጸውን ዘገባ በአጭሩ ተርክ።
9 (2) በዓይነ ሕሊና መሣል። በዚህ ዘገባ ላይ ስለተጠቀሱት ክንውኖች አስብ፤ እንዲሁም ይህ በዳዊት ላይ ምን አስከትሎ ሊሆን እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ሣል። የዳዊት ልጅ አቢሴሎም የሕዝቡን ልብ ለመስረቅ ለበርካታ ዓመታት ሲሞክር ቆይቷል። (2 ሳሙ. 15:7) አቢሴሎም አመቺ ጊዜ እንዳገኘ ሲሰማው ሕዝቡ እንደ ንጉሣቸው አድርገው እንዲቀበሉት ለማዘጋጀት በመላው እስራኤል ሰላዮችን አሰማራ። አልፎ ተርፎም ከዳዊት የቅርብ ወዳጆችና አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌልን በዓመፁ እንዲተባበር አሳመነው። ከዚያም አቢሴሎም፣ ንጉሥ መሆኑን አወጀ፤ እንዲሁም ዳዊትን ለመያዝና ለመግደል ሞከረ፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ዳዊት በጠና በታመመበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (መዝ. 41:1-9) ዳዊት የተጠነሰሰውን ሴራ ሲያውቅ ከኢየሩሳሌም ሸሸ። በኋላም የአቢሴሎም ሠራዊት ከዳዊት ታማኝ ወታደሮች ጋር ተዋጋ። በውጊያው ዓማፂያኑ የተሸነፉ ሲሆን የዳዊት ልጅ አቢሴሎምም ተገደለ።
10. ንጉሥ ዳዊት ለደረሰበት መከራ ምን ምላሽ ሊሰጥ ይችል ነበር?
10 ቀጥሎ ደግሞ ዳዊት ይሄ ሁሉ ነገር ሲደርስበት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ሣል። ዳዊት አቢሴሎምን ይወደው፣ አኪጦፌልንም ያምነው ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሁለቱም ሰዎች ከዱት። ስሜቱን በጥልቅ መጉዳታቸው ሳያንስ ሊገድሉት ሞክረዋል። ይህ ሁኔታ ዳዊት፣ ሌሎቹ ወዳጆቹም ከአቢሴሎም ጋር እንደተባበሩ በማሰብ በእነሱ ላይ እምነት እንዲያጣ ሊያደርገው ይችል ነበር። አሊያም ደግሞ የራሱን ሕይወት ብቻ ለማትረፍ በማሰብ ብቻውን አገር ጥሎ ለመሸሽ ሊወስን ይችል ነበር። ወይም ደግሞ ተስፋ ቆርጦ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ሊተወው ይችል ነበር። ዳዊት ግን እነዚህን ነገሮች አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ይህን ከባድ ሁኔታ ተቋቁሞ አልፏል። ይህን ለማድረግ የረዳው ምንድን ነው?
11. ዳዊት ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት ምን አድርጓል?
11 (3) ማሰላሰል። ከዚህ ዘገባ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማግኘት ትችላለህ? “ዳዊት ችግሩን ለመፍታት ምን እርምጃ ወስዷል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሞክር። ዳዊት በሁኔታው ተሸብሮ በችኮላ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ አላደረገም። ወይም ደግሞ በፍርሃት ከመዋጡ የተነሳ ውሳኔ ለማድረግ አላመነታም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮአል። የወዳጆቹንም እርዳታ ጠይቋል። በተጨማሪም ከውሳኔው ጋር የሚስማማ እርምጃ ወዲያውኑ ወስዷል። ዳዊት ስሜቱ በጥልቅ ቢጎዳም ተጠራጣሪ አልሆነም ወይም በምሬት አልተዋጠም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ መተማመኑን ቀጥሏል፤ በወዳጆቹም ላይ እምነት አላጣም።
12. ይሖዋ ዳዊትን የረዳው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ዳዊትን የረዳው እንዴት ነው? ጊዜ ወስደህ ምርምር ብታደርግ ይሖዋ ዳዊት ያጋጠመውን ፈተና በጽናት እንዲወጣ ብርታት እንደሰጠው ትገነዘባለህ። (መዝ. 3:1-8፤ አናት ላይ ያለው መግለጫ) ይሖዋ፣ ዳዊት ያደረጋቸውን ውሳኔዎች ባርኮለታል። በተጨማሪም የዳዊት ታማኝ ወዳጆች ንጉሣቸውን ለመጠበቅ ሲዋጉ ይሖዋ ረድቷቸዋል።
13. አንድ ሰው ከባድ በደል ቢያደርስብህ የዳዊትን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 18:15-17)
13 (4) በተግባር ማዋል። ‘የዳዊትን ምሳሌ መከተል የምችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ችግሩን ለመፍታት ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ይኖርብሃል። ኢየሱስ በማቴዎስ 18 ላይ የጠቀሳቸውን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ፤ አሊያም ደግሞ በምክሩ ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች አንተ ካጋጠመህ ሁኔታ አንጻር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ። (ማቴዎስ 18:15-17ን አንብብ።) ሆኖም ስሜታዊ ሆነህ በችኮላ ውሳኔ ማድረግ የለብህም። ይሖዋ እንድትረጋጋ እንዲረዳህና ችግሩን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው። በተጨማሪም በወዳጆችህ ላይ ያለህ እምነት አይጥፋ። ከዚህ ይልቅ የሚሰጡህን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን። (ምሳሌ 17:17) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚሰጥህን ምክር በተግባር አውል።—ምሳሌ 3:5, 6
ከጳውሎስ ምን እንማራለን?
14. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 1:12-16 እና 4:6-11, 17-22 ላይ ያለው ሐሳብ ሊያበረታታህ የሚችለው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው?
14 ከቤተሰብህ አባላት ተቃውሞ እየደረሰብህ ነው? ወይም ደግሞ የምትኖረው በይሖዋ ሕዝቦች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በተጣለበት አሊያም ሥራችን ጨርሶ በታገደበት አገር ውስጥ ነው? ከሆነ 2 ጢሞቴዎስ 1:12-16ን እና 4:6-11, 17-22ን ማንበብህ ሊያበረታታህ ይችላል።c ጳውሎስ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፈው እስር ቤት ሆኖ ነው።
15. ይሖዋን ምን ልትጠይቀው ትችላለህ?
15 (1) መጸለይ። እነዚህን ጥቅሶች ማንበብ ከመጀመርህ በፊት፣ ስላጋጠመህ ችግርና ችግሩ ስለፈጠረብህ ስሜት ለይሖዋ ንገረው። ስሜትህን ግልጥልጥ አድርገህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከዚያም ጳውሎስ ስለደረሰበት ፈተና ከሚገልጸው ታሪክ ውስጥ፣ አንተ ያጋጠመህን ፈተና ለመቋቋም የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።
16. ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታ በአጭሩ ግለጽ።
16 (2) በዓይነ ሕሊና መሣል። ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ጳውሎስ ሮም ባለ እስር ቤት ውስጥ ታስሯል። እርግጥ ጳውሎስ እስር ቤት ሲገባ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ በዚህ ወቅት ግን እንደሚገደል ያውቃል። በዚያ ላይ አንዳንድ ወዳጆቹ ትተውት ሄደዋል፤ እንዲሁም ሰውነቱ ዝሏል።—2 ጢሞ. 1:15
17. ጳውሎስ ላጋጠመው ፈተና ምን ምላሽ ሊሰጥ ይችል ነበር?
17 ጳውሎስ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ውሳኔዎች በማሰብ ‘ቀናተኛ ክርስቲያን ባልሆን ኖሮ አልታሰርም ነበር’ ብሎ ሊቆጭ ይችል ነበር። ትተውት በሄዱት በእስያ አውራጃ የነበሩ ሰዎች ምክንያት ምሬት ሊያድርበት ይችል ነበር፤ ወይም ደግሞ ሌሎች ወዳጆቹን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ሊጀምር ይችል ነበር። ጳውሎስ ግን እነዚህን ነገሮች አላደረገም። ታዲያ ጳውሎስ በጓደኞቹ ላይ ያለውን እምነት እንዲሁም ይሖዋ እንደሚባርከው ያለውን ተስፋ ሳያጣ መቀጠል የቻለው እንዴት ነው?
18. ጳውሎስ ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ ምን አድርጓል?
18 (3) ማሰላሰል። “ጳውሎስ ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ ምን አድርጓል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሞክር። ጳውሎስ ከሞት ጋር ቢፋጠጥም አንገብጋቢው ጉዳይ ይሖዋን ማስከበር እንደሆነ አልዘነጋም። እንዲሁም ሌሎችን ማበረታታት ስለሚችልባቸው መንገዶች ማሰቡን ቀጥሏል። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ አዘውትሮ በመጸለይ በእሱ እንደሚታመን አሳይቷል። (2 ጢሞ. 1:3) ትተውት በሄዱት ሰዎች ላይ ከልክ በላይ ከማተኮር ይልቅ በተለያዩ መንገዶች በታማኝነት ለደገፉት ወዳጆቹ ያለውን ጥልቅ የአድናቆት ስሜት ገልጿል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ የአምላክን ቃል ማጥናቱን ቀጥሏል። (2 ጢሞ. 3:16, 17፤ 4:13) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚወዱት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። እነሱ አልተዉትም፤ በታማኝነት ላከናወነው አገልግሎት ብድራቱን ይከፍሉታል።
19. ይሖዋ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ክርስቲያን በመሆኑ ስደት እንደሚደርስበት ይሖዋ አስቀድሞ ነግሮት ነበር። (ሥራ 21:11-13) ታዲያ ይሖዋ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው? ይሖዋ ጸሎቱን የመለሰለት ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ኃይል ሰጥቶታል። (2 ጢሞ. 4:17) ጳውሎስ ብዙ የለፋለትን ሽልማት እንደሚያገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ የጳውሎስን ታማኝ ወዳጆች በተለያዩ መንገዶች ጳውሎስን እንዲረዱት አነሳስቷቸዋል።
20. ሮም 8:38, 39 እንደሚጠቁመው ጳውሎስ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
20 (4) በተግባር ማዋል። ‘የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በእምነታችን ምክንያት ስደት እንደሚደርስብን መጠበቅ ይኖርብናል። (ማር. 10:29, 30) በፈተና ውስጥ ታማኝነታችንን መጠበቅ እንድንችል፣ አዘውትረን በመጸለይ በይሖዋ እንደምንተማመን ማሳየት እንዲሁም ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር አለብን። ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ለይሖዋ ክብር ማምጣት እንደሆነም ምንጊዜም ማስታወስ አለብን። ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወንና ከይሖዋ ፍቅር ማንም ሊለየን እንደማይችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 8:38, 39ን አንብብ፤ ዕብ. 13:5, 6
ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች መማር
21. ዓያ እና ሄክተር ያጋጠማቸውን ፈተና ለመወጣት የረዳቸው ምንድን ነው?
21 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ብርታት ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ በጃፓን የምትኖር ዓያ የተባለች አቅኚ፣ የዮናስ ታሪክ በአደባባይ ምሥክርነት ከመካፈል ጋር በተያያዘ የነበራትን ፍርሃት ለማሸነፍ እንደረዳት ተናግራለች። ይሖዋን የማያገለግሉ ወላጆች ያሉት ሄክተር የተባለ በኢንዶኔዥያ የሚኖር ወጣትም የሩት ምሳሌ ስለ ይሖዋ ለመማርና እሱን ለማገልገል እንዳነሳሳው ገልጿል።
22. ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማዎች ወይም “በእምነታቸው ምሰሏቸው” ከተባለው ዓምድ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
22 ብርታት የሚሰጡህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በድርጅታችን የተዘጋጁ ቪዲዮዎችና ድራማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች እንዲሁም “በእምነታቸው ምሰሏቸው” የተባለው ዓምድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሕያው እንዲሆኑልን ይረዱናል።d ምርምር ተደርጎባቸው የተዘጋጁትን እነዚህን ታሪኮች መመልከት፣ ማዳመጥ ወይም ማንበብ ከመጀመርህ በፊት አንተን የሚጠቅሙ ነጥቦችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ራስህን በዋናው ባለታሪክ ቦታ በማስቀመጥ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። እነዚህ ውድ የአምላክ አገልጋዮች ምን እርምጃ እንደወሰዱ እንዲሁም ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። ከዚያም ያገኘኸውን ትምህርት ከአንተ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተግባር አውለው። ይሖዋን ላደረገልህ እርዳታ አመስግነው። በተጨማሪም ሌሎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በመፈለግ ይሖዋ ላደረገልህ እርዳታ ያለህን አድናቆት አሳይ።
23. በኢሳይያስ 41:10, 13 መሠረት ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል?
23 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሕይወት ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑብን ሊሰማን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:1) ሆኖም መጨነቅ ወይም መፍራት አይኖርብንም። ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ በደንብ ያውቃል። በምንወድቅበት ጊዜ፣ ኃያል በሆነው ቀኝ እጁ አጥብቆ እንደሚይዘን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳይያስ 41:10, 13ን አንብብ።) እንግዲያው ይሖዋ እንደሚደግፈን ሙሉ በሙሉ በመተማመን ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታት ማግኘትና የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና መወጣት እንችላለን።
መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው
a ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸውና ማንኛውንም ፈተና እንዲቋቋሙ እንደሚረዳቸው የሚያሳዩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ተጨማሪ ጥቅም ማግኘት በሚያስችል መንገድ የግል ጥናት ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
b በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረበው ዘዴ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያስችል አንድ ዘዴ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሌሎች ዘዴዎች የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ፤ “መጽሐፍ ቅዱስ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መረዳት” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።
c በጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት እነዚህ ጥቅሶች መነበብ የለባቸውም።
d jw.org ላይ “በእምነታቸው ምሰሏቸው—በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች” የሚለውን ተመልከት። (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > በአምላክ ማመን በሚለው ሥር ይገኛል።)