የጥናት ርዕስ 12
ፍቅር ጥላቻን ለመቋቋም ይረዳናል
“እነዚህን ነገሮች የማዛችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው። ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ።”—ዮሐ. 15:17, 18
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
ማስተዋወቂያa
1. በማቴዎስ 24:9 መሠረት ዓለም ቢጠላን ልንገረም የማይገባው ለምንድን ነው?
ይሖዋ የፈጠረን ለሌሎች ፍቅር እንድናሳይና የመወደድ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። ስለዚህ ሌሎች ሲጠሉን ስሜታችን ይጎዳል፤ ምናልባትም ፍርሃት ሊያድርብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጆርጂና የምትባል በአውሮፓ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ይሖዋን በማገልገሌ የተነሳ እናቴ ትጠላኝ ጀመር። እንደማልፈለግና ጥሩ ሰው እንዳልሆንኩ ተሰማኝ።”b ዳኒሎ የተባለ ወንድምም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ምክንያት ወታደሮች ሲደበድቡኝ፣ ሲሰድቡኝና ሲያስፈራሩኝ ፍርሃት አደረብኝ፤ እንደተዋረድኩም ተሰማኝ።” እንዲህ ያለ ጥላቻ ሲደርስብን ስሜታችን እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። ሆኖም ዓለም የሚጠላን መሆኑ አያስገርመንም። ኢየሱስ ሰዎች እንደሚጠሉን በትንቢት ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:9ን አንብብ።
2-3. ዓለም የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠላቸው ለምንድን ነው?
2 ዓለም የኢየሱስን ተከታዮች ይጠላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ‘የዓለም ክፍል አይደለንም።’ (ዮሐ. 15:17-19) በመሆኑም መንግሥታትን ብናከብርም ለእነሱም ሆነ እነሱን ለሚወክሉ ምልክቶች አምልኮ አከል ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለንም። የምናመልከው ይሖዋን ብቻ ነው። የሰው ዘርን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ መሆኑን እንደምንቀበል እናሳያለን፤ ሰይጣንና የእሱ ‘ዘር’ ግን አምላክ እንዲህ ያለ መብት ያለው መሆኑን አጥብቀው ይቃወማሉ። (ዘፍ. 3:1-5, 15) የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን እንዲሁም ይህ መንግሥት በቅርቡ ተቃዋሚዎቹን በሙሉ እንደሚያደቅ እንሰብካለን። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 19:19-21) ይህ መልእክት ለየዋሆች ምሥራች ቢሆንም ለክፉዎች ግን መጥፎ ዜና ነው።—መዝ. 37:10, 11
3 በዓለም እንድንጠላ የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች የምንመራ መሆኑ ነው። በእነዚህ መሥፈርቶችና ዓለም በሚከተለው ያዘቀጠ የሥነ ምግባር መሥፈርት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት እንዲነሳሳ ያደረጉትን አስጸያፊ የብልግና ድርጊቶች በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በይፋ ይደግፋሉ። (ይሁዳ 7) ከእንደነዚህ ዓይነት ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በመከተላችን ብዙ ሰዎች ያፌዙብናል እንዲሁም ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለን ይናገራሉ።—1 ጴጥ. 4:3, 4
4. ሰዎች ሲጠሉን የትኞቹ ባሕርያት ይረዱናል?
4 የሰዎችን ጥላቻና ስድብ ለመቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው? ይህን ለማድረግ የሚያስችለን ይሖዋ እንደሚረዳን ያለን ጠንካራ እምነት ነው። እምነታችን እንደ ጋሻ በመሆን “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል ይረዳናል። (ኤፌ. 6:16) ሆኖም የሚያስፈልገን እምነት ብቻ አይደለም። ፍቅርም ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ፍቅር “በቀላሉ አይበሳጭም።” የሚጎዱ ነገሮችን ሁሉ ችሎ ያልፋል እንዲሁም በጽናት ይቋቋማል። (1 ቆሮ. 13:4-7, 13) ለይሖዋና ለእምነት ባልንጀሮቻችን ሌላው ቀርቶ ለጠላቶቻችን እንኳ ያለን ፍቅር ጥላቻን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጥላቻን ለመቋቋም ይረዳናል
5. ኢየሱስ ለአባቱ ያለው ፍቅር ብርታት የሰጠው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ በጠላቶቹ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ታማኝ ተከታዮቹን “እኔ አብን [ስለምወደው] አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ ለይሖዋ ያለው ፍቅር ከፊቱ የሚጠብቁትን ፈተናዎች ለመቋቋም ብርታት ሰጥቶታል። እኛም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ብርታት ይሰጠናል።
6. በሮም 5:3-5 መሠረት የይሖዋ አገልጋዮች ዓለም ሲጠላቸው ምን ይሰማቸዋል?
6 በታሪክ ዘመናት ሁሉ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ስደትን ለመቋቋም ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያት የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስበካቸውን እንዲያቆሙ ቢያዝዛቸውም ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው እንዲታዘዙ’ ያነሳሳቸው ለእሱ ያላቸው ፍቅር ነው። (ሥራ 5:29፤ 1 ዮሐ. 5:3) በዛሬው ጊዜ፣ ጨካኝና ኃያል በሆኑ መንግሥታት ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንም ሁኔታውን በጽናት እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው እንዲህ ያለው ጽኑ ፍቅር ነው። ዓለም ሲጠላን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እንደሰታለን።—ሥራ 5:41፤ ሮም 5:3-5ን አንብብ።
7. የቤተሰባችን አባላት ሲቃወሙን ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል?
7 ብዙውን ጊዜ ለመቋቋም በጣም ከባድ የሚሆንብን ከቤተሰባችን አባላት የሚደርስብን ተቃውሞ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስንጀምር አንዳንዶቹ የቤተሰባችን አባላት እንደተታለልን ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ አእምሯችንን እንደሳትን ያስቡ ይሆናል። (ከማርቆስ 3:21 ጋር አወዳድር።) ይባስ ብሎም ከባድ ስደት ያደርሱብን ይሆናል። እንዲህ ያለው ተቃውሞ ሊያስገርመን አይገባም። ምክንያቱም ኢየሱስ “የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 10:36) እርግጥ ነው፣ ዘመዶቻችን ምንም አደረጉብን ምን እንደ ጠላቶቻችን አንቆጥራቸውም። እንዲያውም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሲያድግ ለሰዎች ያለን ፍቅርም ይጨምራል። (ማቴ. 22:37-39) ሆኖም ሰዎችን ለማስደሰት ስንል የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጽሞ አንጥስም።
8-9. አንዲት እህት የደረሰባትን ከባድ ተቃውሞ እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው?
8 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጆርጂና እናቷ ከባድ ተቃውሞ ብታደርስባትም ሁኔታውን በጽናት መቋቋም ችላለች። ጆርጂና እንዲህ ብላለች፦ “እኔና እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርነው አብረን ነው። ከስድስት ወር በኋላ፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደምፈልግ ስነግራት ግን እናቴ ትቃወመኝ ጀመር። በኋላ ሲገባኝ እናቴ ከከሃዲዎች ጋር መነጋገር ጀምራ ነበር፤ ከእኔ ጋር ስትነጋገርም እነሱ የሚያነሷቸውን ነጥቦች ትጠቅስልኝ ነበር። በተጨማሪም ትሰድበኝ፣ ፀጉሬን ትነጨኝ፣ ታንቀኝ እንዲሁም ጽሑፎቼን ትጥልብኝ ነበር። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ተጠመቅሁ። እናቴ ይሖዋን ማገልገሌን እንዳቆም ለማድረግ ስትል ለአስቸጋሪ ወጣቶች ወደተዘጋጀ ተቋም አስገባችኝ፤ እዚያ ከነበሩት ወጣቶች አንዳንዶቹ የዕፅ ሱሰኞችና ወንጀለኞች ነበሩ። ሊወደንና ሊንከባከበን ከሚገባ ሰው እንዲህ ያለ ተቃውሞ ሲሰነዘርብን ለመቋቋም በጣም ከባድ ነው።”
9 ታዲያ ጆርጂና ሁኔታውን መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ እኔን መቃወም በጀመረችበት ቀን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ልክ አንብቤ መጨረሴ ነበር። በመሆኑም እውነትን እንዳገኘሁ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበርኩ፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ በጣም እንደቀረብኩ ተሰምቶኝ ነበር። ወደ እሱ አዘውትሬ እጸልይ ነበር፤ እሱም ጸሎቴን ሰምቶኛል። በተቋሙ ውስጥ በምኖርበት ወቅት አንዲት እህት ቤቷ ትጋብዘኝ ነበር፤ እዚያም መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እናጠናለን። በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች የሰጡኝ ማበረታቻም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በጣም ረድቶኛል። ቤተሰባቸው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል። የሚቃወመን ማንም ይሁን ማን፣ ይሖዋ ከተቃዋሚዎቻችን ይበልጥ ኃያል እንደሆነ በራሴ ሕይወት አይቻለሁ።”
10. አምላካችን ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን መተማመን እንችላለን?
10 ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም ነገር “በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል” ጽፏል። (ሮም 8:38, 39) ለተወሰነ ጊዜ ያህል መከራ ሊደርስብን ቢችልም ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ሆኖ ያጽናናናል እንዲሁም ያበረታታናል። በተጨማሪም የጆርጂና ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይሖዋ ውድ በሆነው መንፈሳዊ ቤተሰባችን አማካኝነት ይረዳናል።
ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ጥላቻን ለመቋቋም ይረዳናል
11. ኢየሱስ በዮሐንስ 15:12, 13 ላይ እንደገለጸው ደቀ መዛሙርቱ ፍቅር ማሳየታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
11 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አሳስቧቸዋል። (ዮሐንስ 15:12, 13ን አንብብ።) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማዳበራቸው አንድነታቸውን ለመጠበቅና የዓለምን ጥላቻ ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ያውቅ ነበር። በተሰሎንቄ የነበረውን ጉባኤ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጉባኤው ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የጉባኤው አባላት ስደት ይደርስባቸው ነበር። ሆኖም በዚያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች፣ በሚያሳዩት ጽናትና ፍቅር ምሳሌ ሆነዋል። (1 ተሰ. 1:3, 6, 7) ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች “ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ” ፍቅር ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል። (1 ተሰ. 4:9, 10) ፍቅር የተጨነቁትን ለማጽናናትና ደካሞችን ለመደገፍ ያነሳሳቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) እነዚህ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ምክር በተግባር አውለዋል። በመሆኑም ጳውሎስ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በጻፈላቸው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ “ሁላችሁም እርስ በርስ የምታሳዩት ፍቅር እየጨመረ [መጥቷል]” ሊላቸው ችሏል። (2 ተሰ. 1:3-5) ፍቅራቸው መከራንና ስደትን ለመቋቋም ረድቷቸዋል።
12. በአንድ አገር የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች በጦርነት ወቅት አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?
12 ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የዳኒሎን እና የባለቤቱን ተሞክሮ እንመልከት። የሚኖሩበት ከተማ በጦርነት ቢታመስም በስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን፣ አቅማቸው በፈቀደ መጠን መስበካቸውን እንዲሁም ያላቸውን ምግብ ለወንድሞችና ለእህቶች ማካፈላቸውን ቀጥለው ነበር። አንድ ቀን መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ዳኒሎ ቤት መጡ። ዳኒሎ እንዲህ ብሏል፦ “እምነቴን እንድክድ ሊያስገድዱኝ ሞከሩ። ፈቃደኛ አለመሆኔን ስገልጽላቸው ደበደቡኝ፤ እንዲሁም ሽጉጥ ከደገኑብኝ በኋላ ከአናቴ በላይ በመተኮስ ሊያስፈራሩኝ ሞከሩ። ከዚያም ተመልሰው እንደሚመጡና ባለቤቴን እንደሚደፍሯት ዝተውብኝ ሄዱ። ሆኖም ወንድሞች በፍጥነት ባቡር አሳፍረው ወደ ሌላ ከተማ ላኩን። እነዚያ ውድ ወንድሞቻችን ያሳዩንን ፍቅር መቼም ቢሆን አልረሳውም። በሄድንበት ከተማ ያሉት ወንድሞችም ምግብ ሰጡን እንዲሁም ሥራና ቤት እንዳገኝ ረዱኝ። በመሆኑም ከጦርነት ቀጠና ሸሽተው ለሚመጡ ወንድሞች እኛም መጠለያ መስጠት ቻልን።” እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች ክርስቲያናዊ ፍቅር ጥላቻን ለመቋቋም እንደሚረዳን ያሳያሉ።
ለጠላቶቻችን ያለን ፍቅር ጥላቻን ለመቋቋም ይረዳናል
13. ሰዎች ቢጠሉንም ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 5:44, 45) ይሁንና እንዲህ ማድረግ ቀላል ነው? በፍጹም! ሆኖም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ጠላቶቻችንን መውደድ እንችላለን። የአምላክ መንፈስ የሚያፈራው ፍሬ ፍቅርን እንዲሁም ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን ያካትታል። (ገላ. 5:22, 23) እነዚህ ባሕርያት ጥላቻን ለመቋቋም ይረዱናል። ብዙ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክር የሆነው የትዳር ጓደኛቸው፣ ልጃቸው ወይም ጎረቤታቸው እነዚህን ግሩም ባሕርያት በማሳየቱ የተነሳ አመለካከታቸውን ቀይረዋል። እንዲያውም ብዙ ተቃዋሚዎች ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆነዋል። ስለዚህ የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ ብቻ የሚጠሉህን ሰዎች መውደድ ከከበደህ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። (ሉቃስ 11:13) እንዲሁም አምላክን መታዘዝ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለው አካሄድ እንደሆነ ሙሉ እምነት ይኑርህ።—ምሳሌ 3:5-7
14-15. ያስሚን ባለቤቷ ከባድ ተቃውሞ ቢያደርስባትም ፍቅር ማሳየቷን ለመቀጠል ሮም 12:17-21 የረዳት እንዴት ነው?
14 በመካከለኛው ምሥራቅ የምትኖረውን የያስሚንን ምሳሌ እንመለከት። ያስሚን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ስትወስን ባለቤቷ እንደተታለለች ስለተሰማው አምላክን ማገልገሏን ሊያስቆማት ሞከረ። ይሰድባት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ዘመዶቿን እንዲሁም የሃይማኖት መሪና ጠንቋይ በመላክ እንዲያስፈራሯትና ቤተሰቧን እያፈረሰች እንዳለ እንዲነግሯት አደረገ። ይባስ ብሎም ባለቤቷ፣ ወንድሞች በጉባኤ ስብሰባ ላይ እያሉ ሄዶ ሰደባቸው! ያስሚን ባለቤቷ በሚያደርስባት በደል ምክንያት ብዙ ጊዜ ታለቅስ ነበር።
15 ሆኖም ያስሚን ስብሰባ ስትሄድ መንፈሳዊ ቤተሰቦቿ ያጽናኗት እንዲሁም ያበረታቷት ነበር። ሽማግሌዎቹም በሮም 12:17-21 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ እንድታደርግ አበረታቷት። (ጥቅሱን አንብብ።) ያስሚን እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የቻልኩትን ሁሉ አደረግኩ። ባለቤቴ ሊያበሳጨኝ በማሰብ ኩሽና ውስጥ ቆሻሻ ሲጥል አጸዳው ነበር። ሲሰድበኝ በገርነት ምላሽ እሰጠው ነበር። ሲታመምም ተንከባክቤዋለሁ።”
16-17. ከያስሚን ምሳሌ ምን እንማራለን?
16 ያስሚን ለባለቤቷ ፍቅር በማሳየቷ ተክሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ምንጊዜም እውነት እንደምናገር ስላስተዋለ በእኔ ላይ ይበልጥ እምነት መጣል ጀመረ። ስለ ሃይማኖት ስንነጋገር በአክብሮት ያዳምጠኝ ጀመር፤ እንዲሁም ቤት ውስጥ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን ለማድረግ ተስማማ። አሁን፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ ያበረታታኛል። የቤተሰብ ሕይወታችን በእጅጉ ተሻሽሏል፤ ቤታችን ሰላም የሰፈነበት ሆኗል። ባለቤቴ እውነትን ተቀብሎ ከእኔ ጋር ይሖዋን ማገልገል እንደሚጀምር ተስፋ አደርጋለሁ።”
17 የያስሚን ተሞክሮ ‘ፍቅር ሁሉን ችሎ እንደሚያልፍ፣ ሁሉን ተስፋ እንደሚያደርግና ሁሉን ነገር በጽናት እንደሚቋቋም’ ያሳያል። (1 ቆሮ. 13:4, 7) ጥላቻ ኃይል እንዳለውና ጎጂ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም የፍቅር ኃይል በእጅጉ ይበልጣል። ፍቅር የሰዎችን ልብ ይገዛል። እንዲሁም የይሖዋን ልብ ያስደስታል። ይሁንና ተቃዋሚዎች እኛን መጥላታቸውን ባያቆሙም ደስተኞች መሆን እንችላለን። እንዴት?
ሰዎች ቢጠሉንም መደሰት
18. ሰዎች ሲጠሉን የምንደሰተው ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ ‘ሰዎች በሚጠሏችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ’ ብሏል። (ሉቃስ 6:22) እርግጥ ሰዎች እንዲጠሉን አንፈልግም። ሰማዕታት የመሆን ምኞትም የለንም። ታዲያ ሰዎች ሲጠሉን የምንደሰተው ለምንድን ነው? ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት። አንደኛ፣ በታማኝነት ስንጸና የአምላክን ሞገስ እናገኛለን። (1 ጴጥ. 4:13, 14) ሁለተኛ፣ እምነታችን ተፈትኖ ይጠራል እንዲሁም ይጠናከራል። (1 ጴጥ. 1:7) ሦስተኛ፣ ውድ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ሽልማት እናገኛለን።—ሮም 2:6, 7
19. ሐዋርያቱ ከተገረፉ በኋላ የተደሰቱት ለምንድን ነው?
19 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያቱ እሱ የተናገረለትን ደስታ ማጣጣም ችለዋል። ሐዋርያቱ ከተገረፉና መስበካቸውን እንዲያቆሙ ከታዘዙ በኋላ ደስ ብሏቸዋል። ለምን? የተደሰቱት “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ነው። (ሥራ 5:40-42) ለጌታቸው ያላቸው ፍቅር ለጠላቶቻቸው ካላቸው ፍርሃት ይበልጥ ነበር። ይህን ፍቅራቸውንም ምሥራቹን “ያለማሰለስ” በመስበክ አሳይተዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንድሞቻችንም ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋ ሥራቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳ እርግጠኞች ናቸው።—ዕብ. 6:10
20. በቀጣዩ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
20 ይህ ሥርዓት እስከቀጠለ ድረስ ዓለም እኛን መጥላቱን አያቆምም። (ዮሐ. 15:19) ሆኖም መፍራት አይኖርብንም። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይሖዋ ታማኞቹን ‘ያጠነክራቸዋል እንዲሁም ይጠብቃቸዋል።’ (2 ተሰ. 3:3) እንግዲያው ይሖዋን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻችንን እንኳ መውደዳችንን እንቀጥል። ይህን ምክር ስንከተል አንድነታችን ይጠበቃል፣ ምንጊዜም በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንሆናለን፣ ለይሖዋ ክብር እናመጣለን እንዲሁም ፍቅር ከጥላቻ ይበልጥ ኃይል እንዳለው እናረጋግጣለን።
መዝሙር 106 ፍቅርን ማዳበር
a ለይሖዋ፣ ለእምነት ባልንጀሮቻችን፣ ሌላው ቀርቶ ለጠላቶቻችን እንኳ ያለን ፍቅር የዚህን ዓለም ጥላቻ እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ኢየሱስ ሌሎች ሲጠሉን ደስተኞች መሆን እንደምንችል የተናገረው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።
b ስሞቹ ተቀይረዋል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ወታደሮች ዳኒሎን ካስፈራሩት በኋላ ወንድሞች እሱንና ባለቤቱን ወደ ሌላ ቦታ ላኳቸው፤ በሄዱበት ቦታ ያሉ ወንድሞችም ጥሩ አድርገው ተቀበሏቸው።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ያስሚን ባለቤቷ ሲቃወማት ሽማግሌዎች ጥሩ ምክር ሰጧት። እሷም ጥሩ ሚስት ለመሆን ጥረት አደረገች፤ እንዲሁም ባለቤቷ ሲታመም ተንከባከበችው።