የጥናት ርዕስ 28
የአምላክ መንግሥት ተቋቁሟል!
“የዓለም መንግሥት የጌታችንና የእሱ መሲሕ መንግሥት ሆነ።”—ራእይ 11:15
መዝሙር 22 በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!
ማስተዋወቂያa
1. ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ለምንስ?
የዓለምን ሁኔታ ስትመለከቱ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከባድ ይሆንባችኋል? ቤተሰቦች እየፈራረሱ ነው። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሰዎች ዓመፀኛ፣ ራስ ወዳድና ቁጡ ሆነዋል። ብዙዎች በባለሥልጣናት ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል። ሆኖም እነዚህ ነገሮች በዓለም ላይ መታየታቸው እምነታችንን ያጠናክርልናል። ለምን? ምክንያቱም የሰዎቹ ምግባር ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” የሚናገረው አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) የትኛውም ሐቀኛ ሰው ይህ ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ሊክድ አይችልም። ይህ ትንቢት መፈጸሙ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ ያረጋግጣል። ሆኖም ይህ ትንቢት ስለ መንግሥቱ ከሚናገሩት በርካታ ትንቢቶች አንዱ ብቻ ነው። ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙ ሌሎች ትንቢቶችን መመርመራችን እምነታችንን ያጠናክርልናል።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ለምንስ? (በሽፋኑ ሥዕል ላይ ሐሳብ ስጥ።)
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ (1) መንግሥቱ የተቋቋመው መቼ እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳንን ትንቢት፣ (2) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መግዛት እንደጀመረ ለማስተዋል የሚረዱንን ትንቢቶች እንዲሁም (3) የአምላክ መንግሥት ጠላቶች የሚጠፉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ትንቢቶችን እንመረምራለን። እነዚህ ትንቢቶች እንደ ተገጣጣሚ ሥዕል ናቸው፤ አንድ ላይ ሆነው ሲታዩ በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ የት ቦታ ላይ እንደምንገኝ ግልጽ ምስል ይሰጡናል።
መንግሥቱ መቼ እንደተቋቋመ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
3. በዳንኤል 7:13, 14 ላይ የሚገኘው ትንቢት የአምላክን መንግሥት ንጉሥ በተመለከተ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
3 በዳንኤል 7:13, 14 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ገዢ ለመሆን ከማንም የተሻለ ብቃት እንዳለው ያረጋግጥልናል። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በደስታ ‘ያገለግሉታል’፤ እንዲሁም እሱን የሚተካ ሌላ ገዢ አይኖርም። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ሌላ ትንቢት ደግሞ ኢየሱስ መንግሥቱን የሚቀበለው “ሰባት ዘመናት” ተብሎ በተጠራው ጊዜ ማብቂያ ላይ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ አስደሳች ክንውን መቼ እንደተከሰተ ማወቅ ይቻላል?
4. ዳንኤል 4:10-17 ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነበትን ዓመት የሚጠቁመን እንዴት እንደሆነ አብራራ። (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
4 ዳንኤል 4:10-17ን አንብብ። ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2,520 ዓመታትን ያመለክታሉ። ይህ ጊዜ የጀመረው በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የይሖዋ ዙፋን ላይ የመጨረሻውን ንጉሥ ባስወገዱበት ወቅት ነው። ያበቃው ደግሞ በ1914 ዓ.ም. ይሖዋ “ሕጋዊ መብት” ያለውን ኢየሱስን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ዙፋን ላይ ባስቀመጠበት ወቅት ነው።b—ሕዝ. 21:25-27
5. ስለ ‘ሰባቱ ዘመናት’ ከሚገልጸው ትንቢት ምን ጥቅም እናገኛለን?
5 ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው? ስለ ‘ሰባቱ ዘመናት’ የሚገልጸውን ትንቢት መረዳታችን ይሖዋ የገባውን ቃል ልክ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ይሖዋ መንግሥቱ የሚቋቋምበትን ቀን እንደቆረጠ ሁሉ ሌሎቹ ትንቢቶች በሙሉ በእሱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲፈጸሙ ያደርጋል። አዎ፣ የይሖዋ ቀን “አይዘገይም!”—ዕን. 2:3
ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እየገዛ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?
6. (ሀ) ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ በሰማይ ላይ መግዛት መጀመሩን የሚያሳየው የሚታይ ማስረጃ ምንድን ነው? (ለ) በራእይ 6:2-8 ላይ የሚገኘው ትንቢት ይህን ማስረጃ የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ማብቂያ አካባቢ አንድ ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ በዚህ ትንቢት ላይ፣ ተከታዮቹ እሱ በሰማይ ላይ መግዛት መጀመሩን ለማወቅ የሚረዷቸውን በዓለም ላይ የሚታዩ አንዳንድ ክንውኖች ጠቅሷል። በትንቢቱ ላይ ስለ ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር ነውጥና ሌሎች ነገሮች ተናግሯል። በተጨማሪም “በተለያየ ስፍራ” ቸነፈሮች ማለትም በሽታዎች እንደሚከሰቱ ተናግሯል፤ በቅርቡ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። እነዚህ ክንውኖች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የክርስቶስን መገኘት የሚያሳየው ምልክት ክፍል ናቸው። (ማቴ. 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:7, 10, 11) ኢየሱስ ከሞተና ወደ ሰማይ ከሄደ 60 ዓመታት ካለፉ በኋላ ለሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህ ክንውኖች እንደሚከሰቱ የሚያሳይ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጠው። (ራእይ 6:2-8ን አንብብ።) ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ላይ ከነገሠበት ጊዜ አንስቶ እነዚህ ክንውኖች በሙሉ ተፈጽመዋል።
7. ኢየሱስ መግዛት መጀመሩ በምድር ላይ ወዮታ ያስከተለው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ሲጀምር የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው ለምንድን ነው? ራእይ 6:2 ወሳኝ መረጃ ይሰጠናል፤ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ አክሊሉን እንደተቀበለ የመጀመሪያ ተልዕኮው ጦርነት ማወጅ ነበር። በማን ላይ? በዲያብሎስ እና በአጋንንቱ ላይ። በራእይ ምዕራፍ 12 መሠረት ሰይጣን በጦርነቱ ተሸነፈ፤ እሱና አጋንንቱም ወደ ምድር ተወረወሩ። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ንዴቱን በሰው ልጆች ላይ መወጣት ጀመረ፤ ይህም ‘በምድር ላይ ወዮታ’ አስከትሏል።—ራእይ 12:7-12
8. ስለ መንግሥቱ የሚናገሩት ትንቢቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ማየታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
8 እነዚህ ትንቢቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው? በዓለም ላይ የሚታዩ ክንውኖችና በሰዎች ባሕርይ ላይ የሚታየው ለውጥ ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን ለማስተዋል ይረዳናል። በመሆኑም ሰዎች ራስ ወዳድና ጨካኝ መሆናቸውን ስናይ ከመበሳጨት ይልቅ ምግባራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ እናስታውሳለን። አዎ፣ መንግሥቱ ተቋቁሟል! (መዝ. 37:1) ደግሞም ወደ አርማጌዶን በተቃረብን መጠን በዓለም ላይ የሚታየው መከራ እየተባባሰ እንደሚሄድ እንጠብቃለን። (ማር. 13:8፤ 2 ጢሞ. 3:13) በእርግጥም አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን፣ ዓለማችን ትርምስምሱ የወጣው ለምን እንደሆነ እንድናውቅ ስለረዳን በጣም እናመሰግነዋለን።
የአምላክ መንግሥት ጠላቶች የሚጠፉት እንዴት ነው?
9. በዳንኤል 2:28, 31-35 ላይ የሚገኘው ትንቢት የመጨረሻውን የዓለም ኃያል መንግሥት የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?
9 ዳንኤል 2:28, 31-35ን አንብብ። በዛሬው ጊዜ ይሄኛው ትንቢትም ሲፈጸም እያየን ነው። የናቡከደነጾር ሕልም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ማለትም ክርስቶስ መግዛት ከጀመረ በኋላ የሚፈጸመውን ነገር የሚያሳይ ነው። ከኢየሱስ ምድራዊ ጠላቶች መካከል ‘ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት የምስሉ እግሮች’ የተወከለው መንግሥት ይገኝበታል፤ ይህ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት በአሁኑ ወቅት በመግዛት ላይ ነው። ወደ ሕልውና የመጣው በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኅብረት በመመሥረት የአንግሎ አሜሪካን ጥምር ኃይል በፈጠሩበት ጊዜ ነው። ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየው ምስል፣ ይህንን የዓለም ኃያል መንግሥት ከእሱ በፊት ከተነሱት ሌሎች መንግሥታት የተለየ የሚያደርጉትን ቢያንስ ሁለት ነገሮች ይጠቁማል።
10. (ሀ) የዳንኤል ትንቢት የአንግሎ አሜሪካን ጥምረት በትክክል ገልጾታል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ከየትኛው አደጋ መጠንቀቅ ይኖርብናል? (“ከሸክላው ተጠንቀቁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
10 በመጀመሪያ፣ በራእዩ ላይ ከተጠቀሱት ከሌሎቹ የዓለም ኃያል መንግሥታት በተለየ መልኩ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት የተወከለው እንደ ወርቅ ወይም ብር ባለ ንጹሕ ንጥረ ነገር ሳይሆን በብረትና በሸክላ ቅልቅል ነው። ሸክላው ‘የሰውን ዘር’ ማለትም ተራውን ሕዝብ ያመለክታል። (ዳን. 2:43 ግርጌ) በዛሬው ጊዜ በግልጽ እንደሚታየው ሕዝቡ በምርጫ፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ፣ በተቃውሞ ሰልፍ እንዲሁም በሠራተኞች ማኅበራት አማካኝነት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት ፖሊሲዎቹን ለማስፈጸም ያለውን ኃይል ያዳክመዋል።
11. የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት እየገዛ መሆኑ የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን እንደሆነ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
11 ሁለተኛ፣ በግዙፉ ምስል እግሮች የተወከለው አንግሎ አሜሪካ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ከእሱ በኋላ የሚነሳ ሌላ የዓለም ኃያል መንግሥት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን እሱንም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን ሌሎች መንግሥታት በሙሉ ያደቃቸዋል።c—ራእይ 16:13, 14, 16፤ 19:19, 20
12. የዳንኤል ትንቢት ማጽናኛና ማበረታቻ የሚሰጥ ምን ተጨማሪ ማስረጃ ይዟል?
12 ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው? የዳንኤል ትንቢት የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን እንደሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጠናል። ከ2,500 ዓመታት በፊት ዳንኤል ከባቢሎን በኋላ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አራት ሌሎች የዓለም ኃያላን መንግሥታት እንደሚነሱ ተንብዮ ነበር። በተጨማሪም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ከእነዚህ መንግሥታት የመጨረሻው እንደሚሆን ገልጿል። ይህም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ እንደሚደመስስና ምድርን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ተስፋ ይሰጠናል፤ ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው!—ዳን. 2:44
13. በራእይ 17:9-12 ላይ የተጠቀሰው “ስምንተኛ ንጉሥ” እና “አሥር ነገሥታት” ምን ያመለክታሉ? ይህ ትንቢት የተፈጸመውስ እንዴት ነው?
13 ራእይ 17:9-12ን አንብብ። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ያስከተለው ውድመት ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገር ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል። የዓለም መሪዎች በዓለም ላይ ሰላም ለማስፈን ፈልገው ነበር። በመሆኑም ጥር 1920 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን አቋቋሙ፤ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጥቅምት 1945 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተተክቷል። ይህ ድርጅት “ስምንተኛ ንጉሥ” ተብሎ ተጠርቷል። ሆኖም ድርጅቱ የዓለም ኃያል መንግሥት አይደለም። ሥልጣኑና የሚያሳድረው ተጽዕኖ የተመካው በሚደግፉት የፖለቲካ ኃይሎች ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን የፖለቲካ ኃይሎች “አሥር ነገሥታት” በማለት ይጠራቸዋል።
14-15. (ሀ) በራእይ 17:3-5 ላይ ያለው ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚገልጸው ራእይ የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) በርካታ የሐሰት ሃይማኖት ደጋፊዎች ምን እያደረጉ ነው?
14 ራእይ 17:3-5ን አንብብ። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት አንዲት አመንዝራ በራእይ ተመልክቶ ነበር፤ “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ የተጠራችው ይህች አመንዝራ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች። ይህ ራእይ የተፈጸመው እንዴት ነው? የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ለረጅም ዘመናት ከዓለም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሲሠሩና ሲደግፏቸው ቆይተዋል። ይሁንና ይሖዋ በቅርቡ ሐሳቡን በእነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ልብ ውስጥ በማኖር “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ” ያደርጋል። ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ማለትም ‘አሥሩ ነገሥታት’ በሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ላይ በመነሳት ያጠፏቸዋል።—ራእይ 17:1, 2, 16, 17
15 ታላቂቱ ባቢሎን መጥፊያዋ እንደቀረበ እንዴት እናውቃለን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ነገር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ለጥንቷ የባቢሎን ከተማ በተወሰነ መጠን ጥበቃ ያደርግላት ነበር። የራእይ መጽሐፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን የታላቂቱ ባቢሎን ደጋፊዎች ጥበቃ ከሚያደርጉ “ውኃዎች” ጋር አመሳስሏቸዋል። (ራእይ 17:15) ሆኖም የራእይ መጽሐፍ ውኃዎቹ ‘እንደሚደርቁም’ ይናገራል፤ ይህም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ብዙዎቹን ደጋፊዎቻቸውን እንደሚያጡ ያመለክታል። (ራእይ 16:12) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ሲፈጸም እየተመለከትን ነው፤ ብዙዎች የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በመተው ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ወደ ሌሎች ምንጮች ዘወር ማለት ጀምረዋል።
16. ስለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መነሳትና ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት የሚገልጹትን ትንቢቶች መረዳታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
16 እነዚህ ትንቢቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መነሳትና የሐሰት ሃይማኖት ደጋፊዎች መመናመን የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጠናል። ባቢሎንን የሚደግፏት ምሳሌያዊ ውኃዎች እየደረቁ ቢሆንም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ጥፋት የሚመጣው ከተለየ አቅጣጫ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ ‘አሥሩ ነገሥታት’ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚደግፉት የፖለቲካ ኃይሎች “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ” የእሱን ሐሳብ በልባቸው ያኖራል። እነዚህ ብሔራት የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጠፉት በድንገት ነው። ይህም ዓለምን የሚያናውጥ አስደንጋጭ ክስተት ይሆናል።d (ራእይ 18:8-10) የታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት በመላው ዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣና አንዳንድ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። ያም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች በዚያ ወቅት ለመደሰት የሚያበቋቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች ይኖሯቸዋል። አንደኛ፣ ለረጅም ዘመን የይሖዋ አምላክ ጠላት ሆና የኖረችው ታላቂቱ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ተደምስሳለች፤ ሁለተኛ፣ ከዚህ ክፉ ሥርዓት የምንገላገልበት ጊዜ ቅርብ ነው!—ሉቃስ 21:28
የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ጠብቁ
17-18. (ሀ) እምነታችንን ማጠናከራችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
17 ዳንኤል ‘እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ተንብዮ ነበር። በእርግጥም በዝቷል! ስለምንኖርበት ዘመን የሚናገሩ ትንቢቶችን በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤ አግኝተናል። (ዳን. 12:4, 9, 10) እነዚህ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው ለይሖዋ እና በመንፈስ መሪነት ላስጻፈው ቃሉ ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል። (ኢሳ. 46:10፤ 55:11) እንግዲያው ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት በማጥናት እንዲሁም ሌሎችም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት እምነታችሁን ማጠናከራችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑበትን ይጠብቃቸዋል፤ ‘ዘላቂ ሰላምም’ ይሰጣቸዋል።—ኢሳ. 26:3
18 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ከመጨረሻው ዘመንና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በተያያዙ ትንቢቶች ላይ እናተኩራለን። እነዚህ ትንቢቶች ስለ መጨረሻው ዘመን ከሚናገሩት ሌሎች ትንቢቶች ጋር የሚዛመዱት እንዴት እንደሆነ እንማራለን። በመግዛት ላይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ታማኝ ተከታዮቹን እየመራቸው እንዳለ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እናያለን።
መዝሙር 61 እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!
a የምንኖረው በታሪክ ውስጥ በጣም አስደናቂ በሆነ ዘመን ላይ ነው። በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ እንደተተነበየው የአምላክ መንግሥት ተቋቁሟል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመረምራለን፤ ይህም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር እንዲሁም አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ነገሮች በእርጋታና በልበ ሙሉነት ለመጋፈጥ ይረዳናል።
b ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 32 ነጥብ 4 ተመልከት፤ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት ጀምሯል የሚለውን ቪዲዮ ከjw.org ላይ ተመልከት።
c ስለ ዳንኤል ትንቢት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሰኔ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-19ን ተመልከት።
d በቅርቡ ስለሚከሰቱት ክንውኖች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 21 ተመልከት።