የጥናት ርዕስ 11
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟችሁም መጽናት ትችላላችሁ
“በአቋምህ ጸንተሃል፤ ስለ ስሜም ስትል ብዙ ችግሮችን ተቋቁመሃል።”—ራእይ 2:3
ዓላማ
ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በይሖዋ አገልግሎት መጽናት እንችላለን።
1. የይሖዋ ድርጅት ክፍል በመሆናችን የትኞቹን በረከቶች አግኝተናል?
በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ድርጅት ክፍል መሆናችን በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው። በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድም እንኳ ይሖዋ ግሩም ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ አንድነት ያለው መንፈሳዊ ቤተሰብ ሰጥቶናል። (መዝ. 133:1) አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን ይረዳናል። (ኤፌ. 5:33–6:1) በተጨማሪም ውስጣዊ ሰላም ለማጣጣም የሚያስችል ጥበብና ማስተዋል ይሰጠናል።
2. ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?
2 ይሁንና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በሌሎች አለፍጽምና ምክንያት ቅር ልንሰኝ እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ያለብን ድክመት ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል፤ በተለይም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ስህተት የምንሠራ ከሆነ መጽናት ሊከብደን ይችላል። (1) የእምነት አጋራችን ስሜታችንን ሲጎዳን፣ (2) የትዳር ጓደኛችን ቅር ሲያሰኘን እንዲሁም (3) በሠራነው ስህተት የተነሳ ቅስማችን ሲሰበር በይሖዋ አገልግሎት መጽናት ይኖርብናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ እነዚህ ሁኔታዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከአንድ ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ የምናገኘውን ትምህርት እንመለከታለን።
የእምነት አጋሮቻችሁ ቅር ቢያሰኟችሁም ጽኑ
3. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
3 ተፈታታኙ ነገር። አንዳንድ የእምነት አጋሮቻችን ባሕርያቸው ያበሳጨን ይሆናል። ሌሎች ደግሞ እንደጠበቅናቸው ሆነው ላይገኙ ወይም አሳቢነት የጎደለው ነገር ሊያደርጉብን ይችላሉ። አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። በእነዚህ ነገሮች የተነሳ አንዳንዶች፣ ይህ በእርግጥ የይሖዋ ድርጅት መሆኑን መጠራጠር ሊጀምሩ ይችላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር “እጅ ለእጅ ተያይዘው” አምላክን ማገልገላቸውን ከመቀጠል ይልቅ ካበሳጯቸው ሰዎች ሊርቁ ወይም ከናካቴው ከስብሰባዎች ሊቀሩ ይችላሉ። (ሶፎ. 3:9) ታዲያ ይህ የጥበብ እርምጃ ነው? ተመሳሳይ ችግር ካጋጠመው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።
4. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል?
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ፍጹማን እንዳልሆኑ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ከጉባኤው ጋር ለመቀላቀል ጥረት ማድረግ በጀመረበት ወቅት ወንድሞች አላመኑትም ነበር። (ሥራ 9:26) ከጊዜ በኋላም አንዳንዶች ስለ እሱ መጥፎ ነገር በመናገር ስሙን አጥፍተዋል። (2 ቆሮ. 10:10) ጳውሎስ፣ ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም ሌሎችን ሊያሰናክል የሚችል መጥፎ ውሳኔ ሲያደርግ ተመልክቷል። (ገላ. 2:11, 12) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ከቅርብ ጓደኞቹ አንዱ የሆነው ማርቆስ እንደጠበቀው ሆኖ ሳይገኝ በመቅረቱ በጣም አዝኗል። (ሥራ 15:37, 38) ጳውሎስ በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ፣ ቅር ካሰኙት ወንድሞች ለመራቅ ሊወስን ይችል ነበር። ያም ቢሆን ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ጸንቷል። ታዲያ ጳውሎስን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው?
5. ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ ተስፋ እንዳይቆርጥባቸው የረዳው ምንድን ነው? (ቆላስይስ 3:13, 14) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
5 ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን ይወዳቸው ነበር። ጳውሎስ ለሌሎች ያለው ፍቅር በድክመቶቻቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። በተጨማሪም ጳውሎስ ፍቅር ያለው መሆኑ በቆላስይስ 3:13, 14 ላይ የጻፈውን ሐሳብ በሥራ ላይ እንዲያውል ረድቶታል። (ጥቅሱን አንብብ።) ከማርቆስ ጋር በተያያዘ ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ጳውሎስ በመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ማርቆስ ትቶት ቢሄድም በእሱ ተበሳጭቶ አልቆየም። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በቆላስይስ ላለው ጉባኤ ፍቅራዊ ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ማርቆስ ጥሩ የሥራ ባልደረባው እንደሆነና “የብርታት ምንጭ” እንደሆነለት ገልጿል። (ቆላ. 4:10, 11) እንዲያውም ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ማርቆስ መጥቶ እንዲረዳው ጠይቋል። (2 ጢሞ. 4:11) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ በወንድሞቹ ላይ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። እኛስ ከጳውሎስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
6-7. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ ለእነሱ ፍቅር በማሳየት መጽናት የምንችለው እንዴት ነው? (1 ዮሐንስ 4:7)
6 የምናገኘው ትምህርት። ይሖዋ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር በማሳየት እንድንጸና ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 4:7ን አንብብ።) አንድ ወንድማችን አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሳያሳይ ከቀረ፣ ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ቢፈልግም እንኳ ሳያስበው ስሜታችንን እንደጎዳው ልናስብ እንችላለን። (ምሳሌ 12:18) አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ ይወዳቸዋል። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ተስፋ አይቆርጥብንም፤ ወይም ቂም አይዝብንም። (መዝ. 103:9) ይቅር ባይ የሆነውን አባታችንን መምሰላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ኤፌ. 4:32–5:1
7 ከዚህም ሌላ፣ ወደ መጨረሻው እየተቃረብን ስንሄድ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቀራርበን መኖር እንደሚያስፈልገን ማስታወስ ይኖርብናል። የሚደርስብን ስደት እየጨመረ እንደሚመጣ መጠበቅ እንችላለን። ምናልባትም በእምነታችን ምክንያት እንታሰር ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያስፈልጉናል። (ምሳሌ 17:17) በስፔን የሚኖር ጆሴፍa የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ምን እንዳጋጠመው እስቲ እንመልከት። እሱና ሌሎች ወንድሞች በገለልተኝነት አቋማቸው የተነሳ አንድ ላይ ታስረው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ውስጥ ሁልጊዜ አብረን ስለሆንን በእምነት አጋሮቻችን የመበሳጨታችን አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። እርስ በርስ መቻቻልና በነፃ ይቅር መባባል ነበረብን። ይህም አንድነት እንዲኖረንና ጥበቃ እንድናገኝ አስችሎናል። ምክንያቱም በዙሪያችን ይሖዋን የማያገለግሉ ብዙ እስረኞች ነበሩ። በአንድ ወቅት ጉዳት ስለደረሰብኝ እጄ በጀሶ ታስሮ ነበር፤ በመሆኑም የተለያዩ ነገሮችን በራሴ ማድረግ አልችልም ነበር። ሆኖም አንድ ወንድም ልብሴን በማጠብና በሌሎች መንገዶች ይንከባከበኝ ነበር። በጣም በሚያስፈልገኝ ጊዜ የወንድሞቼን እውነተኛ ፍቅር ማጣጣም ችያለሁ።” በእርግጥም በመካከላችን ያሉትን ችግሮች ከአሁኑ ለመፍታት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን።
የትዳር ጓደኛችሁ ቅር ቢያሰኛችሁም ጽኑ
8. ባለትዳሮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
8 ተፈታታኙ ነገር። በሁሉም ትዳሮች ውስጥ ችግር መፈጠሩ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:28) ለምን? ምክንያቱም በትዳር የሚጣመሩት ፍጽምና የጎደላቸው ሁለት ሰዎች ናቸው፤ ሁለቱም ባሕርያቸው እንዲሁም የሚወዱትና የሚጠሉት ነገር የተለያየ ነው። ባልና ሚስቱ የተለያየ ባሕል ወይም አስተዳደግ ይኖራቸው ይሆናል። ከመጋባታቸው በፊት ተደብቀው የነበሩ አንዳንድ ባሕርያት ውሎ አድሮ ብቅ ማለት ሊጀምሩ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች በባለትዳሮቹ መካከል ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ባለትዳሮቹ በችግሩ ውስጥ የሁለቱም እጅ እንዳለበት አምነው ከመቀበልና ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትዳር አጋራቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይጀምሩ ይሆናል። ይባስ ብሎም ብቸኛው መፍትሔ መለያየት ወይም መፋታት እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና መፍትሔው ትዳሩን ማፍረስ ነው?b በጣም አስቸጋሪ የትዳር ሕይወት ቢኖራትም እንኳ ከጸናች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ምን እንደምንማር እንመልከት።
9. አቢጋኤል ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟታል?
9 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። አቢጋኤል የናባል ሚስት ነበረች። ናባል ኃይለኛና ምግባረ ብልሹ ሰው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ሳሙ. 25:3) እንዲህ ካለ ሰው ጋር መኖር ለአቢጋኤል በጣም ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥያቄ የለውም። አቢጋኤል ከዚህ ትዳር መገላገል የምትችልበት ቀላል መንገድ ይኖር ይሆን? ወደፊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተሾመው ዳዊት፣ ናባል እሱንና ሰዎቹን ስለሰደባቸው ሊገድለው በመጣ ጊዜ አቢጋኤል እንዲህ ያለ አጋጣሚ አግኝታ ነበር። (1 ሳሙ. 25:9-13) አቢጋኤል በዳዊት ዕቅድ ውስጥ ጣልቃ ሳትገባ መሸሽ ትችል ነበር። ያም ቢሆን እርምጃ ወሰደች፤ ዳዊት ናባልን እንዳይገድለው አሳመነችው። (1 ሳሙ. 25:23-27) አቢጋኤል እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሳት ምን ሊሆን ይችላል?
10. አቢጋኤል የትዳር ሕይወቷ አስቸጋሪ ቢሆንም እንድትጸና ያነሳሳት ምን ሊሆን ይችላል?
10 አቢጋኤል ይሖዋን ትወደው ነበር፤ እንዲሁም እሱ ለትዳር ላወጣው መሥፈርት አክብሮት ነበራት። አምላክ የመጀመሪያውን ትዳር ባቋቋመበት ወቅት አዳምንና ሔዋንን ምን እንዳላቸው እንደምታውቅ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዘፍ. 2:24) አቢጋኤል፣ ይሖዋ ትዳርን ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከተው ታውቅ ነበር። አቢጋኤል አምላክን ማስደሰት ትፈልግ ነበር፤ ይህም ባለቤቷን ጨምሮ ቤተሰቧን በሙሉ ለመታደግ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ እንድታደርግ አነሳስቷታል። ዳዊት ናባልን እንዳይገድለው ለማድረግ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። በተጨማሪም ላልሠራችው ጥፋት ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ነበረች። በእርግጥም ይህችን ደፋርና የሌሎችን ፍላጎት የምታስቀድም ሴት ይሖዋ ይወዳት እንደነበረ ግልጽ ነው። ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከአቢጋኤል ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
11. (ሀ) ይሖዋ ከባለትዳሮች ምን ይጠብቃል? (ኤፌሶን 5:33) (ለ) ካርመን ትዳሯን ለመታደግ ጥረት ካደረገችበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝታችኋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 የምናገኘው ትምህርት። ይሖዋ፣ ባለትዳሮች የትዳር አጋራቸው አብሮ ለመኖር አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ የጋብቻን ዝግጅት አክብረው እንዲኖሩ ይፈልጋል። አምላክ፣ ባለትዳሮች ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርና አክብሮት ለማሳየት ጥረት ሲያደርጉ ሲመለከት በጣም እንደሚደሰት ምንም ጥያቄ የለውም። (ኤፌሶን 5:33ን አንብብ።) የካርመንን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ካርመን ትዳር ከመሠረተች ከስድስት ዓመት ገደማ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ በኋላም ተጠመቀች። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ በዚህ አልተደሰተም። ለይሖዋ በምሰጠው ጊዜ መቅናት ጀመረ። ይሰድበኝ እንዲሁም ጥሎኝ እንደሚሄድ ይዝት ነበር።” ያም ቢሆን ካርመን በትዳሯ ጸንታለች። በፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተ የትዳር ሕይወት ለመምራት ለ50 ዓመት ያህል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ይበልጥ አስተዋይ መሆን እንዲሁም ባለቤቴን በዘዴ ማነጋገር የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ። ትዳር በይሖዋ ዓይን ቅዱስ እንደሆነ ስላወቅኩ ትዳሬን ለመጠበቅ የቻልኩትን ሁሉ ጥረት አድርጌያለሁ። በትዳሬ ተስፋ ያልቆረጥኩት ይሖዋን ስለምወደው ነው።”c እናንተም በትዳራችሁ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ይሖዋ እንደሚደግፋችሁና ለመጽናት እንደሚረዳችሁ መተማመን ትችላላችሁ።
በሠራችሁት ስህተት የተነሳ ቅስማችሁ ቢሰበርም ጽኑ
12. ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ምን ሊሰማን ይችላል?
12 ተፈታታኙ ነገር። ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን በራሳችን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስም ኃጢአት ‘ልባችንን ሊሰብረውና ሊደቁሰው’ እንደሚችል ይናገራል። (መዝ. 51:17) ሮበርት የተባለ አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ለበርካታ ዓመታት ጠንክሮ ሲሠራ ቆይቷል። ሆኖም ከባድ ኃጢአት ፈጸመ፤ በዚህም የተነሳ ይሖዋን እንደከዳው ተሰማው። እንዲህ ብሏል፦ “ሕሊናዬ የድንጋይ ናዳ አወረደብኝ። ውስጤን አመመኝ። ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ፈጽሞ ጸሎቴን እንደማይሰማ ተሰምቶኝ ነበር። ‘እንዲህ አሳፍሬውማ እንዴት ይሰማኛል?’ ብዬ አስቤ ነበር።” እኛም ለኃጢአት እጅ ከሰጠን፣ የተደቆሰው ልባችን ይሖዋ ተስፋ እንደቆረጠብን ስለሚሰማው በራሳችን ተስፋ ለመቁረጥ ልንፈተን እንችላለን። (መዝ. 38:4) እናንተም እንደዚህ ተሰምቷችሁ የሚያውቅ ከሆነ፣ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምም እንኳ በይሖዋ አገልግሎት ከጸና አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ልብ በሉ።
13. ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን ከባድ ኃጢአት ፈጸመ? ከዚያ በፊትስ የትኞቹን ስህተቶች ሠርቷል?
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ሐዋርያው ጴጥሮስ በተከታታይ ስህተቶችን ሠርቶ ነበር፤ በመጨረሻም ከባድ ኃጢአት ፈጸመ። በመጀመሪያ፣ ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ ተማምኗል፤ ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስን ቢክዱት እንኳ እሱ ታማኝ እንደሚሆን በመግለጽ ጉራውን ነዛ። (ማር. 14:27-29) ከዚያም በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በነበሩበት ወቅት ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ነቅቶ መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። (ማር. 14:32, 37-41) በኋላም ኢየሱስን ጠላቶቹ ሲይዙት ጴጥሮስ ጥሎት ሸሸ። (ማር. 14:50) በመጨረሻም ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ኢየሱስን ካደው፤ ይባስ ብሎም ‘አላውቀውም’ ብሎ ማለ። (ማር. 14:66-71) ጴጥሮስ የኃጢአቱን ክብደት ሲገነዘብ ምን ተሰማው? በጥፋተኝነት ስሜት ስለተዋጠ ምርር ብሎ አለቀሰ። (ማር. 14:72) ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ወዳጁ ኢየሱስ ሲገደል ጴጥሮስ ምንኛ ቅስሙ ተሰብሮ ይሆን! የከንቱነት ስሜት ተሰምቶት መሆን አለበት።
14. ጴጥሮስን በይሖዋ አገልግሎት እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
14 ጴጥሮስን በይሖዋ አገልግሎት እንዲጸና የረዱት የተለያዩ ነገሮች አሉ። ራሱን አላገለለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ መንፈሳዊ ወንድሞቹ ሄዷል፤ እነሱም እንዳጽናኑት ምንም ጥያቄ የለውም። (ሉቃስ 24:33) በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገልጦለታል፤ ይህን ያደረገው ሊያበረታታው ስለፈለገ መሆን አለበት። (ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮ. 15:5) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን በኃጢአቱ የተነሳ ከመውቀስ ይልቅ ተጨማሪ ኃላፊነት እንደሚቀበል ነገረው። (ዮሐ. 21:15-17) ጴጥሮስ ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ገብቶታል፤ ሆኖም በራሱ ተስፋ አልቆረጠም። ለምን? ጌታው ኢየሱስ ተስፋ እንዳልቆረጠበት እርግጠኛ ስለነበረ ነው። ደግሞም የጴጥሮስ መንፈሳዊ ወንድሞች እሱን መደገፋቸውን ቀጥለዋል። እኛስ ከጴጥሮስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
15. ይሖዋ ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች እንድንሆን ይፈልጋል? (መዝሙር 86:5፤ ሮም 8:38, 39) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 የምናገኘው ትምህርት። ይሖዋ እሱ እንደሚወደንና ይቅር እንደሚለን እንድንተማመን ይፈልጋል። (መዝሙር 86:5፤ ሮም 8:38, 39ን አንብብ።) ኃጢአት ስንሠራ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ይህም የሚጠበቅና ተገቢ የሆነ ስሜት ነው። ይሁንና ይሖዋ ሊወደን ወይም ይቅር ሊለን እንደማይችል ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “በኃጢአት የወደቅኩት ፈተናውን ለመቋቋም በራሴ ጥንካሬ ስለተማመንኩ ነው።” ሮበርት ሽማግሌዎችን ማነጋገር እንዳለበት ተገነዘበ። እንዲህ ብሏል፦ “ልክ ይህን እርምጃ እንደወሰድኩ በሽማግሌዎች አማካኝነት የይሖዋን ፍቅራዊ እርዳታ ማጣጣም ቻልኩ። ሽማግሌዎቹ ተስፋ አልቆረጡብኝም። ይሖዋ እንዳልተወኝ እንድተማመን ረዱኝ።” እኛም ከኃጢአታችን ንስሐ ከገባን፣ እርዳታ ከጠየቅን እንዲሁም ስህተታችንን ላለመድገም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋ በጥልቅ እንደሚወደንና ይቅር እንደሚለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ዮሐ. 1:8, 9) ይህን ማመናችን፣ ስህተት ስንሠራ ወይም ስንወድቅ በራሳችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።
16. በይሖዋ አገልግሎት ለመጽናት የቆረጥከው ለምንድን ነው?
16 ይሖዋ በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በይሖዋ እርዳታ መጽናት እንችላለን። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማዳበር እንዲሁም ቅር ቢያሰኙንም እንኳ እነሱን ይቅር ማለት እንችላለን። በትዳራችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለአምላክ ያለንን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ለዝግጅቶቹ ያለንን አክብሮት ማሳየት እንችላለን። ኃጢአት ከሠራን ደግሞ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፣ እሱ እንደሚወደንና ይቅር እንደሚለን መተማመን እንዲሁም በእሱ አገልግሎት ወደፊት መግፋት እንችላለን። “ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን” ካልተውን የተትረፈረፈ በረከት እንደምናጭድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ገላ. 6:9
የሚከተሉት ነገሮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ አገልግሎት መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቅር ሲያሰኘን
የትዳር አጋራችን ቅር ሲያሰኘን
በሠራነው ስህተት የተነሳ ቅስማችን ሲሰበር
መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b የአምላክ ቃል፣ ባለትዳሮች ተለያይተው እንዲኖሩ አያበረታታም፤ በተጨማሪም ተለያይተው የሚኖሩ ባለትዳሮች ሌላ ሰው ለማግባት ነፃነት እንደሌላቸው በግልጽ ይናገራል። ይሁንና አንዳንድ ክርስቲያኖች በትዳራቸው ውስጥ ባጋጠማቸው ከባድ ችግር የተነሳ ለመለያየት ወስነዋል። ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ተጨማሪ ሐሳብ 4 ላይ የሚገኘውን “ከትዳር ጓደኛ መለያየት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ተጨማሪ ምሳሌ ለማየት አሳሳች በሆነ ሰላም አትታለሉ!—ዴረል እና ዴብራ ፍሬዚንገር የተባለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።