መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን በተመለከተ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ፣ የሚቆጣውን ሰውም ሆነ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች እንደሚጎዳ ይናገራል። (ምሳሌ 29:22) መቆጣት ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስ አዘውትረው ‘በቁጣ የሚገነፍሉ’ ሰዎች መዳን እንደማያገኙ ይናገራል። (ገላትያ 5:19-21) መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን መቆጣጠር እንድንችል የሚረዱ መመሪያዎችን ይዟል።
መቆጣት ሁልጊዜ ስህተት ነው?
አይደለም። መቆጣት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኝ ሰው የሆነው ነህምያ አብረውት አምላክን የሚያመልኩ አንዳንድ ወገኖቹ ጭቆና እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲሰማ ‘በጣም ተናድዶ’ ነበር።
አምላክም የሚቆጣባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ በጥንት ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹ፣ እሱን ብቻ ለማምለክ የገቡትን ቃል አጥፈው የሐሰት አማልክትን ማምለክ በጀመሩበት ወቅት ‘የይሖዋ ቁጣ በእነሱ ላይ ነድዶ’ ነበር። (መሳፍንት 2:13, 14) ይሁን እንጂ፣ ቁጣ ከይሖዋ አምላክ ዋነኛ ባሕርያት አንዱ አይደለም። ይሖዋ የሚቆጣው ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ቁጣው መቼም ቢሆን ከቁጥጥሩ ውጭ አይደለም።—ዘፀአት 34:6፤ ኢሳይያስ 48:9
መቆጣት ተገቢ የማይሆነው መቼ ነው?
አንድ ሰው ቁጣው ከቁጥጥሩ ውጭ ከሆነ ወይም የተቆጣው ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ከሆነ መቆጣቱ ስህተት ነው፤ ደግሞም ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ቁጣ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ነው። ለምሳሌ ያህል፦
ቃየን፣ አምላክ መሥዋዕቱን ባልተቀበለበት ወቅት ‘በጣም ተናድዶ’ ነበር። ቃየን ቁጣው ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን በመፍቀዱ ወንድሙን እስከ መግደል ደርሷል።—ዘፍጥረት 4:3-8
ነቢዩ ዮናስ፣ አምላክ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት ባሳየበት ወቅት ‘እጅግ ተቆጥቶ’ ነበር። አምላክ፣ ዮናስ “እንዲህ [መቆጣቱ] ተገቢ” እንዳልሆነና ንስሐ ለገቡት ኃጢአተኞች ሊያዝንላቸው ይገባ እንደነበር በመንገር ዮናስን አርሞታል።—ዮናስ 3:10 እስከ 4:1, 4, 11a
እነዚህ ምሳሌዎች ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች “ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም” እንደማያደርግ ያሳያሉ።—ያዕቆብ 1:20
ቁጣህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ የሚያስከትለውን ጉዳት አስብ። አንዳንድ ሰዎች ቁጣቸውን መግለጽ የጥንካሬ ምልክት እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ቁጣውን መቆጣጠር የማይችል ሰው ትልቅ ድክመት አለው። “ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ቅጥር እንደሌላት የፈረሰች ከተማ ነው።” (ምሳሌ 25:28፤ 29:11) በሌላ በኩል ደግሞ ቁጣችንን የመቆጣጠር ችሎታ ካዳበርን እውነተኛ ጥንካሬና ማስተዋል እንዳለን እናሳያለን። (ምሳሌ 14:29) መጽሐፍ ቅዱስ “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ከኃያል ሰው . . . ይሻላል” ይላል።—ምሳሌ 16:32
በኋላ የምትቆጭበትን ነገር ከማድረግህ በፊት ቁጣህን ተቆጣጠር። መዝሙር 37:8 “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤ ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ” ይላል። በምንቆጣበት ወቅት ‘ክፉ ነገር ከመሥራት’ ይልቅ ቁጣችንን ለመቆጣጠር መምረጥ እንደምንችል ልብ በል። ኤፌሶን 4:26 “ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ” ይላል።
እየተናደድክ እንደሆነ ሲሰማህ የሚቻል ከሆነ ከዚያ አካባቢ ዞር በል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ መጫር ግድብን ከመሸንቆር ተለይቶ አይታይም፤ ስለዚህ ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 17:14) ከሌሎች ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ጉዳዩን ቶሎ መፍታታችን የጥበብ እርምጃ ቢሆንም ስለ ጉዳዩ በሰከነ መንፈስ መነጋገር እንድችል መጀመሪያ ጊዜ ወስደን መረጋጋት ሊያስፈልገን ይችላል።
ሙሉ መረጃ ይኑርህ። ምሳሌ 19:11 “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል” ይላል። አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረሳችን በፊት ስለ ጉዳዩ ሙሉ መረጃ ለማግኘት መሞከራችን የጥበብ እርምጃ ነው። ስለ አንድ ጉዳይ ሁሉንም ነገር መስማታችን ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ከመቆጣት ይጠብቀናል።—ያዕቆብ 1:19
የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ጸልይ። ጸሎት “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” ለማግኘት ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 4:7) በተጨማሪም ጸሎት የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት ከምንችልባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ነው፤ የአምላክ መንፈስ ደግሞ እንደ ሰላም፣ ትዕግሥትና ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል።—ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23
ጓደኞችህን በጥንቃቄ ምረጥ። አብዛኞቻችን ጓደኞቻችንን የመምሰል ዝንባሌ አለን። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) መጽሐፍ ቅዱስ “ከግልፍተኛ ሰው ጋር አትግጠም፤ በቀላሉ ቱግ ከሚል ሰውም ጋር አትቀራረብ” የሚል ምክር መስጠቱ በእርግጥም ተገቢ ነው። ለምን? ጥቅሱ “አለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ለራስህም ወጥመድ ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 22:24, 25
a ዮናስ እርማቱን በመቀበል የተሰማውን ቁጣ ማሸነፍ እንደቻለ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም በስሙ የተጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲጽፍ አምላክ ተጠቅሞበታል።