በደም ሕይወትን ማዳን—እንዴት?
“እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና . . . ቃሉንም [የአምላክን ቃል] ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”—ዘዳግም 30:19, 20.
1. እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሕይወት ባላቸው አክብሮት የተለዩ የሆኑት እንዴት ነው?
ብዙ ሰዎች ሕይወትን እንደሚያከብሩ ይናገራሉ። ለዚህም እንደ ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት የሞት ቅጣት ስለመፍረድ፣ ስለ ማስወረድ፣ ወይም ስለ አደን ያላቸውን አመለካከት ነው። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሕይወት ያላቸውን አክብሮት የሚያሳዩበት አንድ ልዩ መንገድ አለ። መዝሙር 36:9፦ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ [ከአምላክ] ዘንድ ነውና” ይላል። ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ በመሆኑ ክርስቲያኖች እርሱ ስለ ደመ ሕይወት ያለውን አመለካከት ይከተላሉ።
2, 3. ደምን በተመለከተ አምላክን በጉዳዩ ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ሥራ 17:25, 28)
2 ሕይወታችን የተመካው በመላው አካላችን ውስጥ ኦክሲጅን ይዞ በሚዘዋወረው፣ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን በሚያስወግደው፣ ከአየር ጠባይ መለዋወጥ ጋር ሰውነታችን እንዲለማመድና በሽታን ለመዋጋት በሚረዳን በደም ላይ ነው። ሕይወታችንን የሰጠን አምላክ የሕይወት ምሰሶ የሆነውን ደም ተብሎ የሚጠራ አስደናቂ ፈሳሽ የሠራና የሰጠን ነው። ይህም የሰው ሕይወት ከአደጋ ተጠብቆ እንዲኖር ያለውን የማያቋርጥ ፍላጎት ያንጸባርቃል።—ዘፍጥረት 45:5፤ ዘዳግም 28:66፤ 30:15, 16
3 ክርስቲያኖችም ሆኑ በአጠቃላይ ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን፦ ‘ደም ሕይወቴን ሊያድን የሚችለው ባለው ተፈጥሮአዊ ሥራ ብቻ ነው ወይስ ደም ሕይወትን ይበልጥ ጥልቅ በሆነ መንገድ ሊያድን ይችላል?’ አብዛኞቹ ሰዎች በሕይወትና በተለመደው የደም ሥራ መካከል ያለውን ግንኙነት ቢረዱም ከዚህ የሚበልጥ ነገርም አለ። ሁሉም የክርስቲያን፣ የእስላምና የአይሁድ የሥነ ምግባር ትምህርት ስለ ሕይወትና ስለ ደም ያለውን አቋም በገለጸው ሕይወት ሰጪ ላይ ያተኮረ ነው። አዎን ፈጣሪያችን ስለ ደም የሚናገረው ብዙ ነገር አለው።
አምላክ ስለ ደም ያለው ጥብቅ አቋም
4. በሰው ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ ላይ አምላክ ስለ ደም ምን ብሎ ነበር?
4 ደም በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ400 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል። ይሖዋ ከሰጣቸው ጥንታዊ ትዕዛዛት ውስጥ አንዱ፦ “ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ . . . ነገር ግን ደሙ ሕይወቱ ያለበትን ሥጋ አትብሉ” ይላል። ቀጥሎም፦ “ደመ ሕይወታችሁን በእርግጥ እጠይቃለሁ” ይላል። (ዘፍጥረት 9:3-5 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ይሖዋ ይህንን የተናገረው የሰብዓዊው ቤተሰብ ሁሉ አባት ለሆነው ለኖኅ ነው። በዚህም ምክንያት ፈጣሪ ደምን ለሕይወት የቆመ ነገር አድርጎ እንደሚመለከተው ሁሉም የሰው ዘር እንዲያውቀው አድርጓል። እንግዲያውስ አምላክን እንደ ሕይወት ሰጪ አድርጎ የሚመለከት ሰው ሁሉ ደመ ሕይወትን በመጠቀም ረገድ አምላክ ጥብቅ አቋም እንዳለው መገንዘብ ይኖርበታል።
5. እስራኤላውያን ደም የማይወስዱበት ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?
5 አምላክ ሕጉን ለእስራኤል በሚሰጥበት ጊዜ ደምን እንደገና ጠቅሶታል። በአይሁድ ታናክ ትርጉም መሠረት ዘሌዋውያን 17:10, 11 እንዲህ ይነበባል፦ “ከእስራኤል ቤት ውስጥ ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች መካከል ማንም ሰው ደም ቢወስድ ደም በሚወስደው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ከዘመዶቹም መካከል እቆርጠዋለሁ፤ ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት በደም ውስጥ ነው።” ይህ ሕግ በጤንነት አንጻር ጥቅሞች ቢኖሩትም ጉዳዩ ሌሎች ነገሮችን የሚጨምር ነው። እሥራኤላውያን ደምን እንደ ልዩ ነገር አድርገው በመመልከት ሕይወታቸው በአምላክ ላይ የተመካ መሆኑን ያሳዩ ነበር። (ዘዳግም 30:19, 20) አዎን ደም ከመብላት የሚርቁበት ዋነኛው ምክንያት ጤንነትን የሚጎዳ ስለሆነ ሳይሆን ደም ለአምላክ ልዩ ትርጉም ያለው በመሆኑ ነው።
6. ኢየሱስ አምላክ ስለ ደም ያለውን አቋም እንደደገፈ እርግጠኛ ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
6 የክርስትና እምነት ሰብዓዊውን ሕይወት በደም በማዳኑ ጉዳይ ላይ ምን አቋም አለው? ኢየሱስ አባቱ ስለ ደም አጠቃቀም የተናገረውን ያውቅ ነበር። ኢየሱስ “ኃጢአትን አላደረገም፣ በከንፈሮቹም ተንኮል አልተገኘም።” ይህም ሕጉን፤ ስለ ደም የተሰጠውን ሕግም ጭምር፤ አሟልቶ ጠብቆአል ማለት ነው። (1 ጴጥሮስ 2:22) በዚህም መንገድ ለተከታዮቹ ምሳሌ ትቶላቸዋል፤ ይኸውም ለደምና ለሕይወት አክብሮት የማሳየት ምሳሌ ነው።
7, 8. አምላክ ስለ ደም ያወጣው ሕግ ለክርስቲያኖች እንደሚሠራ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?
7 ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን የአስተዳደር አካል ስብሰባ አድርጎ ክርስቲያኖች ሁሉንም የእስራኤል ሕጎች መጠበቅ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ሲወስን ምን እንደተፈጸመ ታሪክ ያሳየናል። እነርሱም በመለኮታዊ ኃይል እየተመሩ ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ እንደማይገደዱ ነገር ግን “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም (ደሙ ካልፈሰሰ ሥጋ)፣ ከዝሙትም” መራቃቸው ‘አስፈላጊ’ እንደሆነ ተናገሩ። (ሥራ 15:22-29) በዚህም መንገድ ከደም መራቁ ከዝሙትና ከከባድ የሥነ ምግባር ኃጢአት የመራቅን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ግልጽ አደረጉ።a
8 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መለኮታዊውን ዕገዳ ያከብሩ ነበር። እንግሊዛዊው ምሁር ጆሴፍ ቤንሰን በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ አሉ፦ “ይህ ለኖኅና ለወደፊት ዝርያዎቹ የተሰጠውና ለእስራኤላውያን የተደገመው ደምን በመብላት ላይ የተደረገ ዕገዳ . . . በፍጹም አልተሰረዘም። እንዲያውም በተቃራኒው በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሥራ ምዕራፍ 15 ላይ ይበልጥ ተረጋግጧል። በዚህም መንገድ የዘላለም ግዴታ ሆኗል።” ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረው ነገር በኖኅ ዘመን ወይም በሐዋርያት ዘመን ጥቅም ላይ ያልዋሉትን ደምን ከሰው ወደ ሰው እንደማዘዋወር ያሉ ዘመናዊ የሕክምና ዘዴዎችን ይከለክላልን?
ደምን መድኃኒት ውስጥ መጨመሩ ወይም እንደ መድኃኒት መጠቀሙ
9. ክርስቲያኖች ከነበራቸው አቋም በመጻረር በጥንት ዘመን ደም ለመድሃኒትነት ያገለግል የነበረው እንዴት ነው?
9 ደምን ለመድኃኒትነት መጠቀሙ በፍጹም አዲስ ነገር አይደለም። በሪይ ታናሂል የተጻፈው ሥጋና ደም የተባለው መጽሐፍ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት በግብጽና በሌሎች ቦታዎች “ደም ለቁምጥና በሽታ ከሁሉ የላቀ መድኃኒት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር” ሲሉ ጠቅሰዋል። ሮማውያንም የሚጥል በሽታ የሰውን ደም በመውሰድ ሊፈወስ እንደሚችል ያምኑ ነበር። ተርቱልያን ስለዚህ ደምን ‘በሕክምና’ የመጠቀም ዘዴ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “ስታዲየም መሰል በሆነ ትርዒት ማሳያ ውስጥ የክፉ ወንጀለኞችን ትኩስ ደም ተስገብግበው የሚጠጡትን ተመልከቷቸው . . . ከሚጥል በሽታ ለመዳን ይወስዱታል።” ይህ ሁኔታ ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ቀጥሎ የተገለጸውን አቋም በከፍተኛ ደረጃ ይፃረራል፦ “በምግባችን ውስጥ የእንስሳት ደም እንኳ አይገባም . . . ክርስቲያኖችን በምታሰቃዩበት ጊዜ ደም የተቀላቀለባቸው ምግቦችን ታቀርቡላቸዋላችሁ። በእርግጥ ይህን ማድረጉ ለእነርሱ ሕግ ማፍረስ መሆኑን ታምናላችሁ።” እዚህ ላይ ያለውን መልዕክት ልብ በለው፦ የጥንት ክርስቲያኖች ሕይወትን የሚወክለውን ደም ከመውሰድ ይልቅ ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኞች ነበሩ።—ከ2 ሳሙኤል 23:15-17 ጋር አወዳድር
10, 11. አምላክ ስለ ደም ያለው የአቋም ደረጃ የሌላን ሰው ደም መውሰድን ይከለክላል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
10 እርግጥ በዚያን ጊዜ የአንድ ሰው ደም ለሌላው አይሰጥም ነበር፤ ምክንያቱም ደምን በደም ሥር የመስጠት የላቦራቶሪ ሙከራዎች የተደረጉት ወደ 16ኛው መቶ ዘመን አካባቢ ብቻ ነው። ሆኖም በ17ኛው መቶ ዘመን በኮፐንሃገን ዩንቨርሲቲ የሰው አካል ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ ሰው እንደሚከተለው በማለት ተቃውሞአቸውን ገልጸው ነበር፦ ‘የሰውን ደም ውስጣዊ በሽታዎችን ለማከም የሚጠቀሙበት ሁሉ ደምን ያለ አግባብ የሚጠቀሙበትና ከባድ ኃጢአት የሚሠሩ ይመስለኛል። የሰውን ሥጋ የሚበሉ ተወግዘዋል። ጉሮሮአቸውን በሰው ደም የሚያቆሽሹትንስ ለምን አንጸየፋቸውም? የደም ሥር ቀዶ በአፍም ሆነ በደም ማስተላለፊያ መሣሪያዎች ደም መስጠትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ይህንን አሠራር የጀመሩት ሰዎች መለኮታዊው ያሸብራቸዋል።’
11 አዎን ባለፉት መቶ ዘመናት ውስጥም እንኳ ቢሆን ሰዎች ደምን በደም ሥርም ይሁን በአፍ መውሰዳቸውን የአምላክ ሕግ እንደሚከለክል ይገባቸው ነበር። ይህንን ማወቁ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የወሰዱትን ከአምላክ አቋም ጋር የሚስማማ አቋም ለመገንዘብ ሊረዳቸው ይችላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወትን ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው አድርገው የሚመለከቱና የሕክምና እርዳታን የሚያደንቁ ቢሆኑም እንኳ ሕይወትን ከአምላክ እንደ ተሰጠ ስጦታ አድርገው ያከብሩታል። ስለዚህም ደም በመውሰድ ሕይወትን ለማቆየት አይሞክሩም።—1 ሳሙኤል 25:29
በሕክምና ሲሠራበት ሕይወት አድን ነውን?
12. ማሰብ የሚችሉ ሰዎች የሰውን ደም ስለ መውሰድ ምን ብለው ቢያስቡ ምክንያታዊ ነገር ነው?
12 ለብዙ ዓመታት ባለሞያዎች ደም ሕይወትን ያድናል ብለው ሲናገሩ ቆይተዋል። ዶክተሮች ብዙ ደም የፈሰሰበት ሰው ደም ተሰጥቶት እንደተሻለው ይናገሩ ይሆናል። ስለዚህ ሰዎች ‘ክርስቲያኖች የያዙት አቋም በሕክምናው አንፃር ሲታይ ምን ያህል ጥበብ ያለበት ወይም የጎደለው ነውን?’ ብለው ይጠይቃሉ። ማሰብ የሚችል ሰው ማንኛውንም ዓይነት ከበድ ያለ ሕክምና ለመቀበል ከመወሰኑ በፊት ሊገኙ የሚችሉትን ጥቅሞችም ሆነ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን አደጋዎች ለማወቅ ይሞክራል። ደም ስለመውሰድ ምን ሊባል ይቻላል? ደም መውሰድ በብዙ አደጋዎች የተሞላ መሆኑ ሐቅ ነው። ሞትንም ሊያመጣ ይችላል።
13, 14. (ሀ) የሌላውን ደም መውሰዱ አደገኛ ሆኖ የተገኘባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) ደም ሊያስከትለው የሚችለውን የጤንነት አደጋ በጳጳሱ ላይ ከደረሰው ሁኔታ እንዴት ለማየት ይቻላል?
13 በቅርቡ ዶክተር ኤል ቲ ጉድናፍ እና ዶክተር ጄ ኤም ሻክ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፦ “ደምን ከበሽታ ነፃ ማድረግን እስካወቅንበት ድረስ የደም አቅርቦቱ አስተማማኝ እንደሆነ የሕክምና ማኅበረሰቡ ካወቀ ቆየት ብሏል። ሆኖም የሌላውን ደም መስጠቱ ምን ጊዜም አደጋ አለው። የአንዱን ደም ለሌላው መስጠት ከሚያስከትላቸው በተደጋጋሚ ከታዩት ችግሮች አንዱ ነን ኤ፣ ነን ቢ ሄፐታይቲስ (ኤ ወይም ቢ ያልሆነ ሄፐታይተስ) የተባለው የጉበት በሽታ መሆኑን ቀጥሏል። ሌሎቹ ሊመጡ የሚችሉ በሽታዎች ሄፐታይቲስ ቢ፣ አሎኢሚዩናይዜሽን፣ ሰውነት የሌላን ደም አልቀበልም ማለት፣ የሰውነት በሽታን የመከላከል ችሎታ ማዳከምና በደም ውስጥ ከመጠን በላይ የብረት መብዛት ናቸው።” ከእነዚህ ከባድ አደጋዎች ውስጥ አንዱን ብቻ ለምሳሌ ያህል በመውሰድ ዘገባው ጨምሮ እንዲህ ይላል፦ “[በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ] 40,000 የሚያክሉ ሰዎች በየዓመቱ ኤ ወይም ቢ ያልሆነ ሄፐታይተስ በሽታ ይከሰትባቸዋል። ከእነዚህም መካከል 10 ከመቶ የሚሆኑት የጉበት ማበጥ ወይም ሄፓቶማ [የጉበት ካንሰር] ይይዛቸዋል።”—ዘ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ፣ ሰኔ 1990
14 የሌላውን ደም መውሰዱ በሽታ የማስተላለፉ አደጋ እንዳለው በስፋት እየታወቀ ሲመጣ ሰዎች ስለ ደም ስለ መውሰድ ያላቸውን አመለካከት እንደገና በመመርመር ላይ ናቸው። ለምሳሌም ያህል ጳጳሱ በ1981 በጥይት ከተመቱ በኋላ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ተደርጎላቸው ወጡ። ከዚያ ቆየት ብሎ እንደገና ወደ ሆስፒታል በመመለስ እዚያ ሁለት ወር መቆየት አስፈለጋቸው። ሁኔታቸውም በጣም አሳሳቢ ስለነበር ሊሠሩ እንደማይችሉ ተደርገው ጡረታ መውጣት ያስፈለጋቸው መስለው ነበር። ለምን? ተሰጥቷቸው ከነበረው ደም የቫይረስ ኢንፌክሽን ይዟቸው ስለነበር ነው። አንዳንዶች ‘ለጳጳሱ የተሰጠው ደም አስተማማኝ ካልሆነ ለእኛ ለተራዎቹ ሰዎች የሚሰጠው ደም እንዴት ሊሆን ነው?’ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ።
15, 16. ደሙ በሽታ እንዳለበትና እንደሌለበት ተመርምሮ ያለፈ ቢሆንም እንኳ ደም መውሰዱ አስተማማኝ የማይሆነው ለምንድን ነው?
15 አንድ ሰው ‘ታዲያ በደም ውስጥ በሽታ መኖሩን ለይተው ማወቅ አይችሉምን?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። እስቲ እንደ ምሳሌ አድርገን ሄፐታይቲስ ቢ የተባለውን ለይቶ ለማወቅ የተደረገውን ምርመራ እንመልከት። ፔሸንት ኬር (የካቲት 28, 1990) እንዲህ ሲል አመልክቷል፦ “ደም ከተሰጠ በኋላ የሚከሰተው የሄፐታይቲስ ወይም የጉበት በሽታ ደምን ከዚህ በሽታ ነፃ ማድረግ ከተቻለ በኋላ ቀንሷል፤ ቢሆንም ከ5-10 ከመቶ የሚሆኑ ደም ከተወሰደ በኋላ የተፈጠሩ የሄፐታይተስ ችግሮች አሁንም በሄፐታይቲስ ቢ ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው።”
16 ይህ ዓይነት ምርመራ ሊሳሳት እንደሚችል የሚያሳየው ሌላው በደም የሚተላለፍ በሽታ ኤድስ ነው። እንደ ወረርሽን የሚዛመተው ኤድስ የተበከለ ደም ለሚያስከትለው አደጋ ሰዎችን አንቅቶአቸዋል። እርግጥ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በደም ውስጥ የቫይረሱን መኖር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ምርመራዎች አሉ። ይሁን እንጂ ደም እንደዚህ ያለ የማጣሪያ ምርመራ የሚደረግበት በሁሉም ቦታ አይደለም። በተጨማሪም ሰዊሀለ ኤድስ በአሁኑ ጊዜ ባሉት የምርመራ ዘዴዎች ሳይገኝባቸው ለብዙ ዓመታት በደማቸው ውስጥ የኤድስን ቫይረስ ተሸክመው ሊቆዩ ይችላሉ። ስለዚህ በሽተኞች ተመርምሮ ካለፈ ደም ኤድስ ሊይዛቸው ይችላል፤ ደግሞም ኤድስ ይዟቸዋል!
17. ደም መውሰድ ወዲያውኑ በግልጽ የማይታይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችለው እንዴት ነው?
17 ዶክተር ጉድናፍ እና ዶክተር ሻክ የሌላውን ደም መውሰድ ‘የሰውነትን በሽታን የመከላከል ኃይል ያዳክማል’ ሲሉም ጠቅሰዋል። አዎን የሰጪውና የወሳጁ ሰው ደም ተመሳሳይ መሆኑ የተረጋገጠው ደም እንኳ ሳይቀር አንድ ሰው በሽታን ለመከላከል ያለውን የተፈጥሮ ኃይል ሊጎዳውና ለካንሰርና ለሞት በር የሚከፍት ሊሆን ይችላል። አንድ የካናዳ የራስና የአንገት ካንሰር በሽተኞች ጥናት ‘አንድን ዓይነት ተዛማች ዕባጭ ለማስወገድ ደም የተሰጣቸው ሰዎች ከዚያን ጊዜ በኋላ የአካላቸው በሽታን የመከላከል ኃይል በኃይል ቀንሶባቸዋል።’ (ዘ ሜዲካል ፖስት፣ ሐምሌ 10, 1990) በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩንቨርሲቲ የሚገኙ ዶክተሮች የሚከተለውን ዘገባ አቅርበዋል፦ “የማንቁርት ካንሰር በቀዶ ጥገና ከወጣ በኋላ እንደገና የማገርሸቱ አጋጣሚ ደም ላልወሰዱት 14 ከመቶ ሲሆን ደም ለወሰዱት ደግሞ 65 ከመቶ ነው። አፍ፣ ጉሮሮ፣ አፍንጫና ሳይነስ ላይ ለሚወጣው ካንሰር በሽታው እንደገና የማገርሸቱ አጋጣሚ በአማካይ ደም ላልወሰዱት 31 ከመቶ ሲሆን ደም ለወሰዱት ደግሞ 71 ከመቶ ነው።” (አናልስ ኦቭ ኦክቶሎጂ፣ ራይኖሎጂ፣ ኤንድ ላሪኖሎጂ፣ መጋቢት 1989) ሰውነት በሽታን ለመከላከል የነበረው ኃይል መዳከሙ በቀዶ ጥገና ጊዜ ደም የሚሰጣቸው ሰዎች ኢንፌክሽን ሊፈጠርባቸው የሚኖረው አጋጣሚ የበለጠ መሆኑን ያረጋግጣል።—በገጽ 10 ላይ ያለውን ሳጥን ተመልከት።
በደም ፈንታ ሌሎች አማራጮች አሉን?
18. (ሀ) የአንዱን ደም ለሌላው መስጠቱ የሚኖረው አደጋ ሐኪሞችን ወደ ምን ዘወር እንዲሉ እያደረጋቸው ነው? (ለ) ከሐኪሞችህ ጋር በደም ፋንታ ስላሉት አማራጮች የት ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ልታካፍላቸው ትችላለህ?
18 አንዳንዶች ‘ደም መውሰድ ከፍተኛ አደጋ አለው፤ ግን ሌሎች አማራጮች ይኖራሉን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እኛ ከፍተኛ ጥራት ያለውን ውጤታማ የሆነ የሕክምና ዘዴ እንፈልጋለን። ታዲያ ከባድ የጤና ችግሮችን ያለ ደም ትክክለኛና ውጤታማ በሆኑ መንገዶች ማስወገድ የሚቻልባቸው ዘዴዎች አሉን? አዎን አሉ። ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን (ሰኔ 7, 1990) እንዲህ ሲል ዘግቦ ነበር፦ “ሐኪሞች [ኤድስ] እና ደም በመስጠት የሚፈጠሩ ሌሎች ኢንፌክሽኖች የሚያስከትሏቸውን አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ስለተገነዘቡ በደም መስጠት ምክንያት የሚመጡትን አደጋዎችና ጥቅሞች እንደገና በመመርመር ወደ ሌሎች አማራጮች ዘወር እያሉ ነው፤ ከእነዚህ አማራጮች አንዱ ደም መስጠቱን ጭራሹኑ መተው ይገኝበታል።”b
19. ደም አልወስድም ብለህ የተሳካ ሕክምና ለማግኘት እንደምትችል እርግጠኛ ለመሆን የምትችለው ለምንድን ነው?
19 የይሖዋ ምስክሮች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሌላውን ደም መውሰድን ሲቃወሙ ቆይተዋል። ይህን ያደረጉበትም ዋነኛ ምክንያት በጤና ላይ ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ሳይሆን አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ለመታዘዝ ሲሉ ነው። (ሥራ 15:28, 29) ሆኖም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ዶክተሮች የይሖዋ ምስክሮች ለሆኑ በሽተኞች ደምና ደም የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ሳይሰጡ የተሳካ ሕክምና አድርገውላቸዋል። ለዚህ ምሳሌ ሊሆኑ ከሚችሉትና በሕክምና ጽሑፎች ላይ ከወጡት ውስጥ አንዱ የቀዶ ጥገና ማኅደር በተባለው መጽሔት ላይ (ኅዳር 1990) የወጣው የሌላ ሰው ልብ እንዲተካላቸው ኅሊናቸው በፈቀደላቸው የይሖዋ ምስክር የሆኑ በሽተኞች ላይ ያለ ደም ስለተደረገ ቀዶ ጥገና አብራርቷል። ዘገባው እንዲህ አለ፦ “ለ25 ዓመታት በይሖዋ ምስክሮች ላይ በተደረገ የልብ ቀዶ ጥገና የተገኘው ልምድ ያለ ደም ውጤቶች የተሳካ የልብ መተካት ቀዶ ጥገና ወደ ማድረግ ወደሚቻልበት ደረጃ ደርሶ ተደምድሟል። . . . በዚህ ዓይነቱ ቀዶ ጥገና ምክንያት ሞት አላጋጠመም። ቀደም ሲል ተደርገው የነበሩ የክትትል ጥናቶች እነዚህ በሽተኞች ከፍተኛ ለሆነ ባዕድ አካልን የመቃወም ችግር ብዙም የማይጋለጡ መሆናቸውን አሳይተዋል።”
ከሁሉ በላይ ውድ የሆነው ደም
20, 21. ክርስቲያኖች “ደም መጥፎ መድሃኒት ነው” የሚለው ዝንባሌ እንዳያድርባቸው መጠንቀቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
20 ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ልብን የሚመረምር ጥያቄ አለ። ‘ደም ላለመውሰድ ውሳኔ ካደረግሁ ይህን ያደረግሁት ለምንድንነው? ራሴን ሳላታልል ዋነኛው መሠረታዊ ምክንያቴ ምንድን ነው?’
21 ደም ከመውሰድ ጋር ለተያያዙ ብዙ አደጋዎች የማያጋልጡ ውጤታማ የሆኑ የደም አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰናል። እንደ ሄፐታይቲስ ወይም ኤድስ ያሉ አደጋዎች ብዙ ሰዎችን ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ምክንያቶች ደም አንወስድም እንዲሉ ገፋፍተዋቸዋል። አንዳንዶች በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍ ባለ ድምጽ ተቃውሞአቸውን ያሳያሉ፤ ልክ “ደም መጥፎ መድሃኒት ነው” የሚል መፈክር ይዘው ሰልፍ እንደሚያደርጉ ያህል ነው። አንድ ክርስቲያን ወደዚህ ሰልፍ ተስቦ ሊገባ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ጉዞ መጨረሻው ሞት ነው። እንዴት?
22. ስለ ሕይወትና ስለ ሞት የትኛውን እውነተኛ የሆነ አስተሳሰብ መያዝ ይኖርብናል? (መክብብ 7:2)
22 ጥሩ ሕክምና ይሰጣሉ፣ በጣም ጥሩ ናቸው በሚባሉት ሆስፒታሎችም እንኳ ቢሆን በአንድ ነጥብ ላይ ሰዎች እንደሚሞቱ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። ደም ተሰጥቷቸውም ይሁን ሳይሰጣቸው ሰዎች ይሞታሉ። ይህን ስንል ለሞት አደጋ መጋለጡ ጥሩ ነው ባዮች አያደርገንም። ያለውን እውነታ መቀበል ማለት ነው። ሞት በዛሬው ጊዜ ያለ የማይቀር የኑሮ እውነታ ነው። አምላክ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ ቸል የሚሉ ሰዎች ደም የሚያስከትለው ጉዳት ወዲያውኑ ወይም ዘግይቶ ይደርስባቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች በተወሰደው ደም ምክንያት ይሞታሉ። ሆኖም ሁላችንም መገንዘብ እንደሚኖርብን ደም ወስደው ከሞት የተረፉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት አላገኙም፤ ስለዚህ ደም ሕይወታቸውን ለዘላለም የሚያድንላቸው ሆኖ አልተገኘም። በሌላው በኩል ግን በሃይማኖት አለዚያም በሕክምና ምክንያት ወይም በሁለቱም ምክንያቶች ደም አንወስድም የሚሉና አማራጭ ሕክምናዎችን የሚቀበሉ አብዛኞቹ ሰዎች ከሕክምና አንጻር ሲታይ ጤንነታቸው ተመልሶላቸዋል። በዚህ መንገድ ዕድሜያቸውን ለብዙ ዓመታት ያራዝሙ ይሆናል—ግን ለዘላለም አላራዘሙትም።
23. አምላክ ስለ ደም ያወጣቸው ሕጎች ኃጢአተኞችና ቤዛ የሚያስፈልገን ከመሆናችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?
23 ዛሬ በሕይወት የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸውና ቀስ በቀስ ወደ ሞት የሚጓዙ መሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም ወደሚገልጸው ማዕከላዊ ነጥብ ይመራናል። ሁሉም የሰው ልጆች ደም መብላት እንደሌለባቸው አምላክ ነግሯቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ሕይወትን የሚወክል ስለሆነ ነው። (ዘፍጥረት 9:3-6) በሕጉ ውስጥ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች የመሆናቸውን ሐቅ የሚያረጋግጡ ሕጎችን ሰጥቶ ነበር። እስራኤላውያን ኃጢአታቸው መሸፈን የሚያስፈልገው መሆኑን ለማሳየት የእንስሳት መስዋዕቶችን ማቅረብ እንደሚችሉ ነግሯቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 4:4-7, 13-18, 22-30) ዛሬ ከእኛ የሚጠይቀው ነገር ይህ ባይሆንም ይህ ሕግ አሁንም ትርጉም ያለው ነው። አምላክ ሁሉንም አማኞች ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ለማድረግ አንድ መስዋዕት ይኸውም ቤዛ አዘጋጅቷል። (ማቴዎስ 20:28) አምላክ ስለ ደም ያለው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን የሚያስፈልገን ለዚህ ነው።
24. (ሀ) ደምን በተመለከተ በጤንነት ላይ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ዋነኛ ነጥብ አድርጎ መውሰዱ ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ደም አጠቃቀም ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት ሊወስን የሚገባው ምንድን ነው?
24 ደም በጤና ላይ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች እንደ ዋነኛ ነገር አድርጎ በዚያ ላይ ማተኮሩ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ትኩረት የሰጠው ለዚህ አልነበረም። እስራኤላውያን የአሳማዎችን ወይም የጥንብ አንሳ እንሰሳትን ሥጋ ባለመብላታቸው የጤንነት ጥቅሞችን ያገኙ እንደነበረው ሁሉ ደም ባለመውሰዳቸውም አንዳንድ የጤንነት ጥቅሞችን አግኝተው ይሆናል። (ዘዳግም 12:15, 16፤ 14:7, 8, 11, 12) ሆኖም አምላክ ለኖኅ ሥጋ እንዲበላ ፈቃድ በሰጠው ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ሥጋ እንዳይበላ እንዳልከለከለው አስታውስ። ይሁን እንጂ ሰዎች ደም መብላት እንደሌለባቸው ትእዛዝ ሰጥቶታል። አምላክ ትኩረቱን ያደረገው ሊያጋጥሙ በሚችሉ የጤንነት አደጋዎች ላይ አልነበረም። ስለ ደም ድንጋጌ እንዲያወጣ ያደረገው ዋነኛው ነጥብ ይህ አልነበረም። አምላኪዎቹ ደምን በመውሰድ ሕይወታቸውን ለማቆየት ፈቃደኛ የማይሆኑበት ዋነኛው ምክንያት ጤንነትን የሚጎዳ ስለሆነ ሳይሆን ይህን ማድረጉ ቅዱስ ስላልሆነ ነው። ደም ለመውሰድ ፈቃደኞች የማይሆኑት ደም በበሽታ የተበከለ ስለሆነ ሳይሆን ክቡር ነገር በመሆኑ ነው። ይቅርታ ለማግኘት ይችሉ የነበሩት በመስዋዕታዊ ደም ብቻ ነበር።
25. ደም ለዘለቄታው ሕይወትን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው?
25 ይህ ሁኔታ ለእኛም ቢሆን ያው ነው። በኤፌሶን 1:7 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በውድ ልጁም [በክርስቶስ] እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፣ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን።” አምላክ የአንድን ሰው ኃጢአት ይቅር ካለና ያንንም ሰው እንደ ጻድቅ አድርጎ ከተመለከተው ይህ ሰው የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለው። ስለዚህ የኢየሱስ ቤዛዊ ደም ለዘለቄታው እንዲያውም ለዘላለም ሕይወትን ለማዳን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ድንጋጌው “ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ” በማለት ይደመደማል። (ሥራ 15:29) እዚህ ላይ “ጤና ይስጣችሁ” የሚለው አባባል ‘ከደም ወይም ከዝሙት ከራቃችሁ የተሻለ ጤንነት ይኖራችኋል’ የሚል ተስፋ ያዘለ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ደህና ሁኑ’ ከሚለው ጋር የሚመሳሰል የደብዳቤ መዝጊያ ነው።
b ደም በመስጠት ፈንታ መጠቀም የሚቻሉ ውጤታማ የሆኑ ብዙ አማራጮች ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? በተባለው በ1990 በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር በታተመ ብሮሹር ውስጥ ተዘርዝሮ ይገኛል።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የይሖዋ ምስክሮች ደም ለመውሰድ እምቢ የሚሉበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም ያለው አቋም ከሕክምና አንጻር ሲታይ ምክንያተቢስ እንዳልሆነ የትኛው ማስረጃ ያረጋግጣል?
◻ ቤዛው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም ከሚገልጸው ሕግ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
◻ ደም ሕይወትን ለዘለቄታው ሊያድን የሚችልበት ብቸኛ መንገድ ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሰው ደም መውሰድና ኢንፌክሽን
ደም መውሰድ አንድን በሽተኛ ለኢንፌክሽን ጥቃት ይበልጥ የሚያጋልጠው ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ሰፊ ጥናት ካደረጉ በኋላ ዶክተር ኒል ብላምበርግ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “[ስለ ጉዳዩ] ከተደረጉት 12 የክሊኒክ ጥናቶች ውስጥ 10ሩ ደም መውሰዱ በአደገኛ ሁኔታ ለከፍተኛ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን አደጋ እንደሚያጋልጥ አሳይተዋል። . . . በተጨማሪም ቀዶ ጥገናው ከመደረጉ ረዘም ካለ ጊዜ በፊት የሌላውን ደም መውሰድ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደም በመውሰድ ሳቢያ የመጣ ሰውነት በሽታን የመከላከል ኃይሉ መዳከሙ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በሽተኛውን ኢንፌክሽንን ለመቋቋም ያለውን ኃይል ሊነካበት ይችላል። . . . እነዚህ መረጃዎች ሌሎች ሁኔታዎችንም እንዲሸፍኑ ሰፋ ማለት ከቻሉና ትክክለኝነታቸው ከተረጋገጠ ደም ከተሰጠ በኋላ ከሚከሰቱት የጤንነት ችግሮች ውስጥ ከቀዶ ጥገና በኋላ የሚፈጠር አጣዳፊ የኢንፌክሽን በሽታ ነው ለማለት የሚቻል ይመስላል።”—ደም መስጠት፣ የሕክምና መድኃኒትና አስተያየቶች የተባለው መጽሔት ጥቅምት 1, 1990
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመነጽር ብዙ ጊዜ ጎልተው የሚታዩ ቀይ የደም ሴሎች። “እያንዳንዱ ማይክሮሊትር (0.00003 አውንስ) ደም ከ4 ሚልዮን እስከ 6 ሚልዮን ቀይ የደም ሴሎችን ይይዛል።”—“ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ”
[ምንጭ]
Kunkel-CNRI/PHOTOTAKE NYC