የጥናት ርዕስ 20
የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል
“ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።”—መዝ. 62:8
መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር
ማስተዋወቂያa
1. ይሖዋ አገልጋዮቹ ምን እንዲያደርጉ ጋብዟቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
ማጽናኛና መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከማን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ እናውቀዋለን። ወደ ይሖዋ አምላክ በጸሎት መቅረብ እንችላለን። ይሖዋ ይህን እንድናደርግ ጋብዞናል። ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:17) በነፃነት በመጸለይ ስለ የትኛውም የሕይወታችን ዘርፍ መመሪያ ልንጠይቀው እንችላለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ ለጋስ አምላክ ስለሆነ ስንት ጊዜ መጸለይ እንደምንችል ገደብ አላስቀመጠም።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 የጸሎት መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ሆኖም ብዙ ሥራ ስላለብን ለጸሎት የሚሆን ጊዜ እናጣ ይሆናል። በተጨማሪም የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። ደስ የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ማበረታቻና መመሪያ እናገኛለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ የኢየሱስን ታሪክ በመመርመር ለጸሎት ጊዜ መመደብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ፣ አምስት አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማካተት የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።
ኢየሱስ ለጸሎት ጊዜ መድቧል
3. ኢየሱስ ስለ ጸሎት ምን ያውቅ ነበር?
3 ኢየሱስ፣ ይሖዋ ጸሎትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ያውቃል። ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት አባቱ የታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ጸሎት ሲመልስ ተመልክቷል። ለምሳሌ ይሖዋ ሐና፣ ዳዊት፣ ኤልያስና ሌሎች ያቀረቡትን ልባዊ ጸሎት ሲመልስ ኢየሱስ ከአባቱ ጎን ነበር። (1 ሳሙ. 1:10, 11, 20፤ 1 ነገ. 19:4-6፤ መዝ. 32:5) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አዘውትረው እንዲጸልዩና ጸሎታቸው እንደሚመለስ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያስተማራቸው ለዚህ ነው።—ማቴ. 7:7-11
4. ከኢየሱስ ጸሎቶች ምን እንማራለን?
4 ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ባቀረባቸው ጸሎቶች አማካኝነት ለደቀ መዛሙርቱ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ብዙ ጊዜ ጸልዮአል። ሥራ ስለሚበዛበት እንዲሁም ብዙዎች ወደ እሱ ይመጡ ስለነበር ለጸሎት የሚሆን ጊዜ መመደብ ነበረበት። (ማር. 6:31, 45, 46) ብቻውን የሚጸልይበት ጊዜ ለማግኘት ሲል በማለዳ ይነሳ ነበር። (ማር. 1:35) እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ከባድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12, 13) በተጨማሪም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በምድራዊ አገልግሎቱ ከተሰጡት ኃላፊነቶች በጣም ከባዱን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጸልዮአል።—ማቴ. 26:39, 42, 44
5. በጸሎት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
5 ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብን ለጸሎት ጊዜ መመደብ እንዳለብን የኢየሱስ ታሪክ ያስተምረናል። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ለጸሎት የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ስንል በማለዳ መነሳት ወይም ትንሽ ማምሸት ሊኖርብን ይችላል። እንዲህ ስናደርግ፣ ይሖዋ ለሰጠን ውድ ስጦታ አመስጋኝ መሆናችንን እናሳያለን። ሊን የተባለች አንዲት እህት ስለ ጸሎት መብት መጀመሪያ በተማረችበት ወቅት ልቧ ምን ያህል እንደተነካ ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን በማንኛውም ሰዓት ላነጋግረው እንደምችል ስማር እሱን እንደ ቅርብ ጓደኛዬ መመልከት ጀመርኩ፤ የጸሎቴን ይዘት ለማሻሻልም ተነሳሳሁ።” ብዙዎቻችን እንደዚህ እንደሚሰማን ምንም ጥያቄ የለውም። እንግዲያው በጸሎታችን ውስጥ ልናካትታቸው የምንችላቸውን አምስት ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች እንመልከት።
አምስት የጸሎት ርዕሰ ጉዳዮች
6. በራእይ 4:10, 11 መሠረት ይሖዋ ምን ሊቀበል ይገባዋል?
6 ይሖዋን ማወደስ። ሐዋርያው ዮሐንስ 24 ሽማግሌዎች በሰማይ ይሖዋን ሲያመልኩ የሚያሳይ አስደናቂ ራእይ ተመልክቷል። ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች አምላክ “ግርማ፣ ክብርና ኃይል” ሊቀበል እንደሚገባው በመግለጽ አወድሰውታል። (ራእይ 4:10, 11ን አንብብ።) ታማኝ መላእክትም ይሖዋን ለማወደስና ለማክበር የሚያነሳሳ ስፍር ቁጥር የሌለው ምክንያት አላቸው። በሰማይ ከእሱ ጋር ስለሚኖሩ በሚገባ ያውቁታል። ከሚሠራው ነገር ባሕርያቱን ማስተዋል ይችላሉ። ይሖዋ የሚያከናውናቸውን ነገሮች ሲመለከቱ እሱን ለማወደስ ይነሳሳሉ።—ኢዮብ 38:4-7
7. ይሖዋን ስለ ምን ጉዳይ ልናወድሰው እንችላለን?
7 እኛም በጸሎታችን ላይ ይሖዋን እንድንወደውና እንድናከብረው የሚያደርጉንን ምክንያቶች በመጥቀስ ልናወድሰው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና ስታጠና አንተን ይበልጥ የሚማርኩህን የይሖዋ ባሕርያት ለማግኘት ሞክር። (ኢዮብ 37:23፤ ሮም 11:33) ከዚያም ስለ እነዚህ ባሕርያት ምን እንደሚሰማህ ለይሖዋ ንገረው። በተጨማሪም ይሖዋን ለእኛም ሆነ ለመንፈሳዊ ቤተሰባችን ላደረገው ነገር ልናወድሰው እንችላለን። ምንጊዜም ይንከባከበናል፤ እንዲሁም ጥበቃ ያደርግልናል።—1 ሳሙ. 1:27፤ 2:1, 2
8. ይሖዋን እንድናመሰግን ከሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? (1 ተሰሎንቄ 5:18)
8 ይሖዋን ማመስገን። ይሖዋን በጸሎት የምናመሰግንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። (1 ተሰሎንቄ 5:18ን አንብብ።) ስላገኘነው ስለ ማንኛውም መልካም ነገር ልናመሰግነው እንችላለን፤ ደግሞም የመልካም ስጦታ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። (ያዕ. 1:17) ለምሳሌ ምድራችን ስላላት ውበት እንዲሁም በተፈጥሮ ላይ ስለሚታየው ጥበብ ይሖዋን ልናመሰግነው እንችላለን። በተጨማሪም ስለ ሕይወታችን፣ ስለ ቤተሰቦቻችን፣ ስለ ወዳጆቻችን እና ስለ ተስፋችን ልናመሰግነው እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ከእሱ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት ውድ መብት ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባል።
9. ይሖዋ ላደረገልን ነገር አድናቆት ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?
9 በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሱንን ምክንያቶች ለማሰብ ለየት ያለ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። የምንኖረው ምስጋና ቢስ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩት ማግኘት በሚፈልጉት ነገር ላይ እንጂ ላሏቸው ነገሮች አመስጋኝነታቸውን ማሳየት በሚችሉበት መንገድ ላይ አይደለም። እንዲህ ያለው አመለካከት ከተጋባብን ጸሎታችን ልመና ብቻ ያካተተ ይሆንብናል። ይህ እንዲያጋጥመን ካልፈለግን ይሖዋ ላደረገልን ነገር በሙሉ አድናቆት ማዳበራችንን እና ማመስገናችንን መቀጠል አለብን።—ሉቃስ 6:45
10. አንዲት እህት አመስጋኝ መሆኗ ለመጽናት የረዳት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 አመስጋኝነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይረዳናል። በጥር 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን የክዮንግ ሱክን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ክዮንግ ሱክ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሰ የሳንባ ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። እንዲህ ብላለች፦ “የጤንነቴን ሁኔታ መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር፤ ሁሉን ነገር እንዳጣሁ የተሰማኝ ሲሆን በፍርሃት ተዋጥኩ።” ታዲያ ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው? በየዕለቱ ከመተኛቷ በፊት በቤቷ ጣሪያ ላይ ወጥታ በዚያ ቀን ያገኘቻቸውን አምስት ነገሮች በመጥቀስ ይሖዋን ጮክ ብላ እንደምታመሰግነው ተናግራለች። እንዲህ ማድረጓ አረጋግቷታል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ያላትን ፍቅር ለመግለጽ አነሳስቷታል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ከባድ ፈተናዎችን መቋቋም እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ተመልክታለች፤ በተጨማሪም የምናገኛቸው በረከቶች በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ይበልጥ ብዙ እንደሆኑ ተገንዝባለች። እኛም ፈተና ውስጥ ብንሆንም እንደ ክዮንግ ሱክ ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። ምስጋናችንን በጸሎት መግለጻችን ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋምና ስሜታችንን ለማረጋጋት ይረዳናል።
11. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ድፍረት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
11 አገልግሎታችንን ስናከናውን ድፍረት እንዲሰጠን ይሖዋን መጠየቅ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ እሱ ምሥክርነት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሷቸዋል። (ሥራ 1:8፤ ሉቃስ 24:46-48) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ሐዋርያው ጴጥሮስንና ዮሐንስን በሳንሄድሪን ፊት አቅርበው መስበካቸውን እንዲያቆሙ አዘዟቸው፤ አልፎ ተርፎም አስፈራሯቸው። (ሥራ 4:18, 21) ታዲያ ጴጥሮስና ዮሐንስ ምን አደረጉ?
12. በሐዋርያት ሥራ 4:29, 31 መሠረት ደቀ መዛሙርቱ ምን አደረጉ?
12 ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሃይማኖት መሪዎቹ ማስፈራሪያ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጡ፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።” (ሥራ 4:19, 20) ጴጥሮስና ዮሐንስ ከተለቀቁ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ በይሖዋ ፈቃድ ላይ ያተኮረ ጸሎት አቀረቡ። “[ባሪያዎችህ] ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው” ብለው ጸለዩ። ይሖዋ ለዚህ ልባዊ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል።—የሐዋርያት ሥራ 4:29, 31ን አንብብ።
13. ከጂን ህዮክ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 የመንግሥት ባለሥልጣናት መስበካችንን እንድናቆም ቢያዙንም መስበካችንን በመቀጠል የደቀ መዛሙርቱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። በገለልተኝነት አቋሙ የተነሳ ታስሮ የነበረ ጂን ህዮክ የተባለ ወንድም የተወውን ምሳሌ እንመልከት። እስር ቤት በነበረበት ወቅት ብቻቸውን የታሰሩ አንዳንድ እስረኞችን እንዲከታተል ተመድቦ ነበር። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከሥራው ጋር ተያያዥነት ስለሌለው ስለ ማንኛውም ጉዳይ እነሱን ማነጋገር አይፈቀድለትም ነበር። ጂን ህዮክ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመስበክ የሚያስችል ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ ጸለየ። (ሥራ 5:29) እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ድፍረትና ጥበብ በመስጠት ጸሎቴን መልሶልኛል። ለበርካታ እስረኞች እዚያው በራቸው ላይ አምስት ደቂቃ የሚፈጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እመራ ነበር። ከዚያም ማታ ላይ ደብዳቤ ጽፌ በማግስቱ ለእስረኞቹ እሰጣቸዋለሁ።” እኛም ይሖዋ አገልግሎታችንን ለመፈጸም እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን። እንደ ጂን ህዮክ፣ ይሖዋ ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ እንችላለን።
14. ችግር ሲያጋጥመን ምን ሊረዳን ይችላል? (መዝሙር 37:3, 5)
14 የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም እንዲረዳን ይሖዋን መጠየቅ። ብዙዎቻችን አካላዊ ሕመም፣ ስሜታዊ ቀውስ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት፣ የቤተሰብ ችግር፣ ስደት ወይም ሌላ ዓይነት ፈተና ያጋጥመናል። እንደ ጦርነትና ወረርሽኝ ያሉት ነገሮች ደግሞ የሚያጋጥመንን ችግር መቋቋም ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋሉ። እንግዲያው በይሖዋ ፊት ልብህን አፍስስ። ለአንድ የቅርብ ጓደኛህ እንደምታደርገው፣ የሚሰማህን ነገር ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። ይሖዋ “ለአንተ ሲል እርምጃ” እንደሚወስድ እርግጠኛ ሁን።—መዝሙር 37:3, 5ን አንብብ።
15. ጸሎት ‘መከራን በጽናት ለመቋቋም’ የሚረዳን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
15 ሳንታክት መጸለያችን ‘መከራን በጽናት ለመቋቋም’ ይረዳናል። (ሮም 12:12) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መከራ ያውቃል፤ “እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል።” (መዝ. 145:18, 19) በአቅኚነት የምታገለግለው የ29 ዓመቷ ክርስቲ ይህ እውነት መሆኑን ተመልክታለች። በድንገት ከባድ የጤና እክል አጋጠማት። በዚህም የተነሳ በከፍተኛ ጭንቀት ተዋጠች። በኋላ ደግሞ ክርስቲ፣ እናቷ የማይድን በሽታ እንዳለባት አወቀች። ክርስቲ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እያንዳንዱን ቀን ለማለፍ የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠኝ አጥብቄ እጸልይ ነበር። በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና የግል ጥናት በማድረግ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዤ ለመቀጠል ሞከርኩ።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “የጨለማውን ጊዜ ለማለፍ የረዳኝ ጸሎት ነው። ይሖዋ ምንጊዜም አብሮኝ እንዳለ እርግጠኛ ነበርኩ፤ ይህን ማወቄ በእጅጉ አጽናንቶኛል። እርግጥ ነው፣ ያለብኝ የጤና ችግር ወዲያውኑ መፍትሔ አላገኘም። ሆኖም ይሖዋ ውስጣዊ ሰላምና የተረጋጋ ልብ በመስጠት ጸሎቴን መልሶልኛል።” እንግዲያው “ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” እንደሚያውቅ ፈጽሞ አንርሳ።—2 ጴጥ. 2:9
16. ፈተናን ለማሸነፍ የይሖዋ እርዳታ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
16 ፈተናን ለማሸነፍ እንዲረዳን ይሖዋን መጠየቅ። ፍጹማን ስላልሆንን መጥፎ ነገር ላለማድረግ ሁልጊዜ መታገል ያስፈልገናል። ሰይጣን ደግሞ ይህን ትግል ይበልጥ ለማክበድ ይጥራል። አስተሳሰባችንን ለመመረዝ የሚሞክርበት አንዱ መንገድ ወራዳ መዝናኛ በመጠቀም ነው። እንዲህ ያለው መዝናኛ አእምሯችን በርኩስ ሐሳቦች እንዲሞላ ያደርጋል፤ እነዚህ ሐሳቦች ደግሞ ውስጣዊ ማንነታችንን ሊያበላሹትና ወደ ከባድ ኃጢአት ሊመሩን ይችላሉ።—ማር. 7:21-23፤ ያዕ. 1:14, 15
17. ፈተናን ለማሸነፍ ካቀረብነው ልመና ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 መጥፎ ነገር እንድናደርግ የሚደርስብንን ፈተና ለመወጣት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ውስጥ “ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” የሚለውን ልመና አካቷል። (ማቴ. 6:13) ይሖዋ ሊረዳን ይፈልጋል፤ ሆኖም እርዳታውን ልንጠይቅ ይገባል። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃም መውሰድ አለብን። የሰይጣን ሥርዓት ለሚያስፋፋቸው የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ያለንን ተጋላጭነት ለመቀነስ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። (መዝ. 97:10) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት አእምሯችንን በጤናማ ሐሳቦች መሙላት እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንና በአገልግሎት መካፈላችንም አስተሳሰባችንን ለመጠበቅ ይረዳናል። ይሖዋም ልንሸከም ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ቃል ገብቶልናል።—1 ቆሮ. 10:12, 13
18. ከጸሎት ጋር በተያያዘ ሁላችንም ምን ማድረግ አለብን?
18 በእነዚህ ተፈታታኝ የመጨረሻ ቀናት ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ ሁላችንም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በትጋት መጸለይ ይኖርብናል። ልባዊ ጸሎት ለማቅረብ በየዕለቱ ጊዜ መድብ። ይሖዋ ወደ እሱ በመጸለይ ‘ልባችንን በፊቱ እንድናፈስ’ ይፈልጋል። (መዝ. 62:8) ይሖዋን አወድሰው፤ እንዲሁም ላደረገልህ ነገር ሁሉ አመስግነው። በአገልግሎት ደፋር ለመሆን እንዲረዳህ ጠይቀው። የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለመወጣትና ማንኛውንም ፈተና ለማሸነፍ እንዲረዳህ ለምነው። ማንም ሰው ወይም ማንኛውም ነገር ወደ ይሖዋ አዘውትረህ ከመጸለይ እንዲያግድህ አትፍቀድ። ይሁንና ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው? ይህን ወሳኝ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመልሳለን።
መዝሙር 42 የአምላክ አገልጋይ ጸሎት
a ጸሎታችን ለቅርብ ጓደኛችን እንደምንጽፈው ከልብ የመነጨ ደብዳቤ እንዲሆን እንፈልጋለን። ያም ቢሆን ለጸሎት የሚሆን ጊዜ ማግኘት ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። በተጨማሪም ‘ስለ ምን ልጸልይ?’ የሚለው ጉዳይ ሊያሳስበን ይችላል። ይህ ርዕስ እነዚህን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ያብራራል።