ይሖዋ ታጋሽ አምላክ ነው
“እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነት . . . ነው።”—ዘጸአት 34:6, 7
1, 2. (ሀ) በጥንት ጊዜ ከይሖዋ ትዕግሥት እነማን ተጠቅመዋል? (ለ) “ትዕግሥት” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች፣ ከሙሴ ጋር በምድረ በዳ የተጓዙት እስራኤላውያንና ኢየሱስ ምድር ሳለ የነበሩት አይሁዳውያን ይኖሩበት የነበረው ሁኔታ የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ከይሖዋ የትዕግሥት ባሕርይ ጥቅም አግኝተዋል። እንዲያውም ለአንዳንዶች መዳን ምክንያት ሆኗል። የይሖዋ ትዕግሥት ለእኛም መዳናችን ሊሆን ይችላል።
2 ትዕግሥት ምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ ያሳየው መቼ ነው? ለምንስ? “ትዕግሥት” የሚለው ቃል “በደል ወይም የሚያስቆጣ ነገር ሲፈጸም በትዕግሥት መቻል፣ የሻከረው ግንኙነት ሊሻሻል አይችልም ብሎ ተስፋ አለመቁረጥ” ተብሎ ተተርጉሟል። ስለዚህ ይህ ባሕርይ የሚንጸባረቀው በዓላማ ነው። በተለይ መጥፎ ሁኔታ እንዲፈጠር ላደረገው ግለሰብ ደህንነት የሚያስብ ነው። እንዲህ ሲባል ግን ትዕግሥት ስህተትን ችላ ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። ትዕግሥት ማሳየት ያስፈለገበት ዓላማ ሲፈጸም ወይም ሁኔታውን ከዚያ በላይ ለመታገሥ የሚያበቃ ተጨማሪ ምክንያት በማይኖርበት ጊዜ ትዕግሥት ማሳየት ያበቃል።
3. ይሖዋ ትዕግሥት የሚያሳይበት ዓላማ ምንድን ነው? የሚታገሠው እስከ ምን ድረስ ነው?
3 ሰዎች ትዕግሥት የማሳየት ችሎታ ያላቸው ቢሆንም እንኳ ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ይሖዋ ነው። በይሖዋና በሰብዓዊ ፍጥረታቱ መካከል ያለው ዝምድና በኃጢአት ምክንያት ተበላሽቶ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ ፈጣሪያችን ትዕግሥት ሲያሳይና ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማሻሻል ይችሉ ዘንድ ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል። (2 ጴጥሮስ 3:9፤ 1 ዮሐንስ 4:10) ይሁን እንጂ ትዕግሥት እንዲያሳይ የተነሳሳበት ዓላማ ግቡን ሲመታ አምላክ ሆን ብለው ኃጢአት በሚሠሩ ሰዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ይህን የነገሮች ሥርዓት ያጠፋዋል።—2 ጴጥሮስ 3:7
ከአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት ጋር ይስማማል
4. (ሀ) ትዕግሥት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንዴት ተብሎ ተገልጿል? (በተጨማሪም የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ነቢዩ ናሆም ይሖዋን የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ ስለ ይሖዋ ትዕግሥት ምን ያሳያል?
4 በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ትዕግሥት የሚለው ሐሳብ በቀጥታ ሲተረጎሙ “የአፍንጫ ርዝማኔ” የሚል ትርጉም ባላቸው ሁለት ቃላት የተገለጸ ሲሆን በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ “ለቁጣ የዘገየ” ተብሎ ተተርጉሟል።a ነቢዩ ናሆም አምላክ ስላሳየው ትዕግሥት ሲገልጽ “እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ በኃይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም” በማለት ተናግሯል። (ናሆም 1:3) ስለዚህ የይሖዋ ትዕግሥት የድክመት ምልክት ተደርጎ መታየት የማይገባው ከመሆኑም በላይ ገደብ እንዳለው ማስታወስ ያስፈልጋል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ኃይል ያለው ሆኖ ሳለ ለቁጣ የዘገየ መሆኑ ትዕግሥት የሚያሳየው በዓላማ እንደሆነ ያመለክታል። ይሖዋ ለመቅጣት ሥልጣን ያለው ቢሆንም እንኳ መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲያገኝ ሲል ፈጥኖ እርምጃ ከመውሰድ ይቆጠባል። (ሕዝቅኤል 18:31, 32) ስለዚህ የይሖዋ ትዕግሥት የፍቅሩ መግለጫ ሲሆን በኃይሉ አጠቃቀም ረገድም ጥበበኛ መሆኑን ያሳያል።
5. የይሖዋ ትዕግሥት ከፍትሑ ጋር የሚጣጣም የሆነው በምን መንገድ ነው?
5 የይሖዋ ትዕግሥት ከፍትሑና ከጽድቁ ጋርም ይጣጣማል። “እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም [“ለቁጣ የዘገየ፣” NW ]፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” እንደሆነ ለሙሴ ተገልጦለታል። (ዘጸአት 34:6) ከዓመታት በኋላ ሙሴ “መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሕ፣” NW ] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” በማለት ይሖዋን በማወደስ ዘምሯል። (ዘዳግም 32:4) አዎን፣ የይሖዋ ምሕረት፣ ትዕግሥት፣ ፍትሕና ቅንነት እርስ በርስ ተጣጥመው የሚንጸባረቁ ባሕርያት ናቸው።
ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በፊት ያሳየው ትዕግሥት
6. ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ዝርያዎች ያሳየው የሚደነቅ ትዕግሥት ምንድን ነው?
6 አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ የፈጸሙት ዓመፅ አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያቸው ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ውድ ዝምድና ለዘለቄታው እንዲያጡ አድርጓቸዋል። (ዘፍጥረት 3:8-13, 23, 24) ይህም ኃጢአትን፣ አለፍጽምናንና ሞትን በወረሱት ዘሮቻቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። (ሮሜ 5:17-19) ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ኃጢአት የሠሩት ሆን ብለው ቢሆንም ይሖዋ ልጆች እንዲወልዱ ፈቀደላቸው። ከጊዜ በኋላ የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች ከእርሱ ጋር እርቅ መፍጠር ይችሉ ዘንድ በፍቅሩ ተነሳስቶ ዝግጅት አደረገ። (ዮሐንስ 3:16, 36) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቊጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፣ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን።”—ሮሜ 5:8-10
7. ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በፊት ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው? ከጥፋት ውኃው በፊት የነበረው ትውልድ መጥፋት ይገባው የነበረው ለምንድን ነው?
7 የይሖዋ ትዕግሥት በኖኅ ዘመን ታይቷል። ከጥፋት ውኃው በፊት አንድ መቶ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ ቀደም ብሎ “እግዚአብሔርም ምድርን አየ፣ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።” (ዘፍጥረት 6:12) ሆኖም ይሖዋ ለአንድ ለተወሰነ ጊዜ ለሰው ዘር ትዕግሥት አሳይቷል። እርሱም “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፣ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ” በማለት ተናገረ። (ዘፍጥረት 6:3) እነዚህ 120 ዓመታት ታማኙ ኖኅ ልጆች ወልዶ ለማሳደግ፣ አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት መርከብ ለመሥራትና በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ከሚመጣው የጥፋት ውኃ እንዲድኑ ለማስጠንቀቅ አስችለውታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፣ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:20) እርግጥ ነው ከራሱ ከኖኅ ቤተሰቦች በስተቀር የኖኅን ስብከት ‘ያስተዋለ’ ሰው አልነበረም። (ማቴዎስ 24:38, 39 NW ) ሆኖም ይሖዋ፣ ኖኅ መርከብ እንዲሠራና ምናልባትም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ‘የጽድቅ ሰባኪ ሆኖ እንዲያገለግል’ በማድረግ በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ከክፉ ሥራቸው ንሥሐ እንዲገቡና እርሱን ማገልገል እንዲጀምሩ ለማድረግ በቂ ጊዜ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5፤ ዕብራውያን 11:7) በዚያን ወቅት የነበረው ክፉ ትውልድ እንዲጠፋ መደረጉ በእርግጥ ተገቢ ነበር።
ለእስራኤላውያን ያሳየው ትዕግሥት ምሳሌ ይሆናል
8. ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?
8 ይሖዋ እስራኤልን ከ120 እጅግ ለሚበልጥ ዓመት ታግሦአል። የአምላክ ምርጥ ሕዝብ ሆነው በቆዩባቸው ከ1, 500 በሚበልጡ ዓመታት የአምላክን ትዕግሥት ያልተፈታተኑበት ወቅት የለም ለማለት ይቻላል። ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር በማለት ለአዳኛቸው ከፍተኛ ንቀት አሳይተዋል። (ዘጸአት 32:4፤ መዝሙር 106:21) ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ይሖዋ በምድረ በዳ በተአምር ይሰጣቸው በነበረው ምግብ ላይ አንጎራጎሩ፣ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ፣ ይሖዋን አማረሩ እንዲሁም ከአረማውያን ጋር ዝሙት ፈጸሙ፣ አልፎ ተርፎም በበኣል አምልኮ እስከመካፈል ደረሱ። (ዘኁልቊ 11:4-6፤ 14:2-4፤ 21:5፤ 25:1-3፤ 1 ቆሮንቶስ 10:6-11) ይሖዋ ሕዝቡን ጠራርጎ ሊያጠፋቸው ይችል የነበረ ቢሆንም እንኳ እንደዚያ ከማድረግ በመታቀብ ትዕግሥት አሳይቷቸዋል።—ዘኁልቊ 14:11-21
9. ይሖዋ በመሳፍንትና በነገሥታት ዘመን ታጋሽ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
9 በመሳፍንት ዘመን እስራኤላውያን በተደጋጋሚ በጣዖት አምልኮ ወድቀዋል። እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። ይሁን እንጂ ንስሐ ገብተው ለእርዳታ በሚጮሁበት ጊዜ ትዕግሥት በማሳየት መሳፍንትን አዳኝ አድርጎ ያስነሳላቸው ነበር። (መሳፍንት 2:17, 18) እስራኤላውያን በነገሥታት ይተዳደሩ በነበረበት ረዥም ዘመን ለይሖዋ የጸና አቋም ይዘው የገዙት ጥቂት ነገሥታት ብቻ ነበሩ። ታማኝ በሆኑት ነገሥታት ዘመንም እንኳ ሳይቀር ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ጋር ይቀላቅሉ ነበር። ይሖዋ ነቢያትን በማስነሳት ክህደታቸውን ባጋለጠበት ጊዜ ሕዝቡ በተደጋጋሚ ብልሹ ካህናትንና ሐሰተኛ ነቢያትን ማዳመጥ ይመርጡ ነበር። (ኤርምያስ 5:31፤ 25:4-7) እንዲያውም እስራኤላውያን የይሖዋን ታማኝ ነቢያት ከማሳደድም አልፈው አንዳንዶቹን ገድለዋል። (2 ዜና መዋዕል 24:20, 21፤ ሥራ 7:51, 52) እንዲህም ሆኖ ይሖዋ ትዕግሥት ከማሳየት አልተቆጠበም።—2 ዜና መዋዕል 36:15
ይሖዋ ትዕግሥቱ አላለቀም
10. የይሖዋ ትዕግሥት ገደቡ ላይ ደርሶ የነበረው መቼ ነው?
10 ሆኖም የአምላክ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው ከታሪክ መረዳት ይቻላል። በ740 ከዘአበ አሦራውያን የአሥሩን ነገዶች የእስራኤል መንግሥት እንዲገለብጡና ሕዝቡን አግዘው እንዲወስዱ አድርጓል። (2 ነገሥት 17:5, 6) በቀጣዩ መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ደግሞ ባቢሎናውያን የሁለቱን ነገዶች የይሁዳ መንግሥት እንዲወርሩና ኢየሩሳሌምን ከነቤተ መቅደሷ እንዲያጠፏት ፈቅዷል።—2 ዜና መዋዕል 36:16-19
11. ይሖዋ የፍርድ እርምጃ ከወሰደ በኋላም እንኳ ትዕግሥት ማሳየቱን የቀጠለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ፍርዱን ካስፈጸመ በኋላም እንኳ ትዕግሥት ማሳየቱን አላቆመም። ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ምርጥ ሕዝቦቹ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ትንቢት ተናገረ። እንዲህ አለ:- “ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፣ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፣ . . . ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፣ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።”—ኤርምያስ 29:10, 14
12. የአይሁድ ቀሪዎች ወደ ይሁዳ መመለስ ከመሲሑ መምጣት ጋር በተያያዘ ጥሩ አጋጣሚ የሆነው እንዴት ነው?
12 በግዞት ከነበሩት መካከል ቀሪዎች ወደ ይሁዳ ተመልሰው ኢየሩሳሌም ውስጥ ዳግመኛ በተሠራው ቤተ መቅደስ የይሖዋ አምልኮ እንደገና እንዲያንሰራራ አደረጉ። በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ እነዚህ ቀሪዎች ማነቃቂያና ብልጽግና እንደሚያመጣ “ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል” ይሆናሉ። “በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ” ደፋሮችና ጠንካሮች ይሆናሉ። (ሚክያስ 5:7, 8) ይህ የኋለኛው መግለጫ አይሁዳውያን በመቃብያን ቤተሰብ አመራር ሥር ሆነው ጠላቶቻቸውን ከተስፋይቱ ምድር ባባረሩበትና ረክሶ የነበረውን ቤተ መቅደስ ለአምላክ እንዲወሰን ባደረጉበት በመቃብያን ዘመን ተፈጽሞ ሊሆን ይችላል። ሌሎች የታመኑ ቀሪዎች መሲሕ ሆኖ የሚገለጠውን የአምላክ ልጅ መቀበል ይችሉ ዘንድ ምድሪቱና ቤተ መቅደሱ በዚህ መንገድ ተጠብቀው ቆይተዋል።—ዳንኤል 9:25፤ ሉቃስ 1:13-17, 67-79፤ 3:15, 21, 22
13. አይሁዳውያን ልጁን ከገደሉ በኋላ እንኳ ይሖዋ ትዕግሥቱን ያሳያቸው እንዴት ነው?
13 አይሁዳውያን ልጁን ከገደሉ በኋላም እንኳ ይሖዋ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር ክፍል የመሆንን ልዩ አጋጣሚ ክፍት አድርጎ በመጠበቅ ከሦስት ዓመት ተኩል ለሚበልጡ ተጨማሪ ዓመታት ትዕግሥቱን አሳይቷቸዋል። (ዳንኤል 9:27)b ከ36 እዘአ በፊትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት አንዳንድ አይሁዳውያን ይህን ጥሪ በመቀበል ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ እንደገለጸው “በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች” ሆነዋል።—ሮሜ 11:5
14. (ሀ) በ36 እዘአ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር ክፍል የመሆን መብት የተዘረጋላቸው እነማን ናቸው? (ለ) ይሖዋ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላትን የሚመርጥበትን መንገድ በማስመልከት ጳውሎስ የተሰማውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?
14 በ36 እዘአ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር ክፍል የመሆን መብት ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁድ ላልሆኑና ወደ ይሁዲነት ላልተለወጡ ሰዎች ተሰጠ። ለዚህ ጥሪ ምላሽ የሚሰጥ ማንኛውም ሰው ይገባናል ከማንለው የይሖዋ ደግነትና ትዕግሥት ተጠቃሚ ይሆናል። (ገላትያ 3:26-29፤ ኤፌሶን 2:4-7) ጳውሎስ መንፈሳዊ እስራኤልን እንዲያሟሉ ለተጠሩት ሰዎች መሰብሰብ ምክንያት ከሆነው የይሖዋ ምሕረት አዘል ትዕግሥት በስተጀርባ ስላለው ጥበብና ዓላማ የተሰማውን ጥልቅ አድናቆት ሲገልጽ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” በማለት ተናግሯል።—ሮሜ 11:25, 26, 33፤ ገላትያ 6:15, 16
ለስሙ ሲል ይታገሣል
15. አምላክ ትዕግሥት የሚያሳይበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? በጊዜ ሂደት እልባት ማግኘት የሚኖርበት አከራካሪ ጉዳይ የትኛው ነው?
15 ይሖዋ ትዕግሥት የሚያሳየው ለምንድን ነው? በአንደኛ ደረጃ ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ ለማድረግና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ነው። (1 ሳሙኤል 12:20-22) ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል ነው ወይስ አይደለም በሚል ሰይጣን ያስነሳው ጥያቄ በሁሉም ፍጥረታት ፊት በአጥጋቢ ሁኔታ እልባት ማግኘት ይችል ዘንድ ጊዜ ያስፈልግ ነበር። (ኢዮብ 1:9-11፤ 42:2, 5, 6) በዚህም የተነሳ ሕዝቦቹ በግብፅ ጭቆና ይደርስባቸው በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለፈርዖን “ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ” ብሎታል።—ዘጸአት 9:16
16. (ሀ) የይሖዋ ትዕግሥት ለስሙ የሚሆን ሕዝብ ለማዘጋጀት መንገድ የከፈተው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ስም የሚቀደሰውና ሉዓላዊነቱ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ቅዱስ ስሙን በማስከበር ረገድ ትዕግሥቱ የሚጫወተውን ሚና በሚያብራራበት ጊዜ ይሖዋ ለፈርዖን የተናገራቸውን ቃላት ጠቅሶ ተናግሯል። ከዚያም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጻፈ:- “ነገር ግን እግዚአብሔር ቊጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፣ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፣ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ፣ እንዴት ነው? የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፣ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ:- ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ . . . እጠራለሁ።” (ሮሜ 9:17, 22-25) ይሖዋ ትዕግሥት ማሳየቱ ከአሕዛብ “ለስሙ የሚሆንን ወገን” እንዲወስድ አስችሎታል። (ሥራ 15:14) እነዚህ “ቅዱሳን ሕዝብ” በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነው ይሖዋ ታላቅ ስሙን ለማስቀደስና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ የሚጠቀምበትን መንግሥት ይወርሳሉ።—ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14, 27፤ ራእይ 4:9-11፤ 5:9, 10
የይሖዋ ትዕግሥት መዳንን ያስገኛል
17, 18. (ሀ) ባሳየው ትዕግሥት ምክንያት ሳይታወቀን ይሖዋን ልንወቅሰው የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ላሳየው ትዕግሥት ምን ዓይነት አመለካከት እንድናዳብር ማበረታቻ ተሰጥቶናል?
17 የሰው ዘር ኃጢአት ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ይሖዋ ታጋሽ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። ከጥፋት ውኃው በፊት ያሳየው ትዕግሥት ተገቢ ማስጠንቀቂያ ለመስጠትና መዳን የሚቻልበትን መርከብ ለመገንባት በቂ ጊዜ አስገኝቷል። ይሁን እንጂ ትዕግሥቱ ገደቡ ላይ በደረሰ ጊዜ የጥፋት ውኃው መጥቷል። በተመሳሳይም ዛሬ ይሖዋ ታላቅ ትዕግሥት እያሳየ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች ይህ ከገመቱት በላይ እንደረዘመ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን አይገባም። እንዲህ ማድረግ ትዕግሥት በማሳየቱ አምላክን እንደመውቀስ ይቆጠራል። ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን?” በማለት ጠይቋል።—ሮሜ 2:4
18 ማናችንም ብንሆን በፊቱ ለመዳን የሚያበቃንን ሞገስ ለማግኘት የአምላክ ትዕግሥት የሚያስፈልገን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” በማለት መክሮናል። (ፊልጵስዩስ 2:12) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”—2 ጴጥሮስ 3:9
19. ይሖዋ ካሳየው ትዕግሥት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
19 ስለዚህ ይሖዋ ነገሮችን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ ትዕግሥት ከማጣት ይልቅ “የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ” በማለት ጴጥሮስ አክሎ የሰጠውን ምክር እንከተል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው የእነማን መዳን ነው? የእኛና ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ መስማት የሚኖርባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች መዳን ነው። (2 ጴጥሮስ 3:15፤ ማቴዎስ 24:14) ይህም ይሖዋ ትዕግሥተኛ በመሆን ያሳየውን ደግነት እንድናደንቅ ይረዳናል እንዲሁም እኛም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ትዕግሥተኞች እንድንሆን ያንቀሳቅሰናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “አፍንጫን” ለማመልከት የሚሠራበት (አፍ የሚለው) የዕብራይስጥ ቃል ብዙውን ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ቁጣን ለማመልከት ያገለግላል። ይህም በጣም የተቆጣ ሰው በኃይል ስለሚተነፍስ ወይም ስለሚደነፋ ነው።
b ስለዚህ ትንቢት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙትን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 191-4ን ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• “ትዕግሥት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ትርጉም አለው?
• ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ከባቢሎን ግዞት በኋላና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ትዕግሥቱን ያሳየው እንዴት ነው?
• ይሖዋ ትዕግሥት የሚያሳይባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
• የይሖዋን ትዕግሥት እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጥፋት ውኃ በፊት ይሖዋ ያሳየው ትዕግሥት ሰዎች ንስሐ መግባት እንዲችሉ በቂ ጊዜ ሰጥቷቸዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባቢሎን ከወደቀች በኋላ አይሁዳውያን ከይሖዋ ትዕግሥት ጥቅም አግኝተዋል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያንም ሆኑ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ይሖዋ ካሳየው ትዕግሥት ጥቅም አግኝተዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የይሖዋን ትዕግሥት በአግባቡ ይጠቀሙበታል