ምዕራፍ አሥራ አንድ
መሲሑ የሚመጣበት ጊዜ ታወቀ
1. ይሖዋ ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ የማይል አምላክ በመሆኑ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
ይሖዋ፣ ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ አይልም። ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ወራትና ዘመናት ሁሉ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ናቸው። (ሥራ 1:7) በእነዚህ ወራትና ዘመናት ውስጥ እንዲፈጸሙ የወሰናቸው ነገሮች ያላንዳች ጥርጥር ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ እንጂ በፍጹም አይከሽፉም።
2, 3. ዳንኤል ያተኮረው በየትኛው ትንቢት ላይ ነው? በወቅቱስ ባቢሎንን ያስተዳድር የነበረው የትኛው ገዥ ነው?
2 ነቢዩ ዳንኤል ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ያጠና ስለ ነበር ይሖዋ አንዳንድ ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ ለመወሰንና ለማስፈጸም እንደሚችል እምነት ነበረው። በተለይ የዳንኤልን ትኩረት ይበልጥ የሳቡት ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት የተነገሩት ትንቢቶች ናቸው። ኤርምያስ ቅድስቲቱ ከተማ ለምን ያህል ጊዜ ባድማ ሆና እንደምትቆይ የሚገልጸውን የአምላክ ራእይ መዝግቦ ስለነበር ዳንኤል ይህን ትንቢት በጥንቃቄ መርምሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፣ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፣ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፣ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ።”—ዳንኤል 9:1, 2፤ ኤርምያስ 25:11
3 በወቅቱ “በከለዳውያን መንግሥት ላይ” ገዥ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስ ነበር። ቀደም ሲል ዳንኤል በግድግዳው ላይ የታየውን ጽሕፈት ፍቺ ሲገልጽ የተናገረው ትንቢት ቅጽበታዊ ፍጻሜውን አግኝቶ ነበር። የባቢሎናውያን ግዛት ጠፍቶ የነበረ ሲሆን በ539 ከዘአበ “ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጥቷል።”—ዳንኤል 5:24-28, 30, 31
ዳንኤል ይሖዋን በትሕትና ተማጸነ
4. (ሀ) አምላክ ነፃ እንዲያወጣቸው ምን ማድረግ ይፈለግባቸው ነበር? (ለ) ዳንኤል ወደ ይሖዋ የቀረበው እንዴት ነበር?
4 ዳንኤል የኢየሩሳሌም የ70 ዓመት ባድማነት የሚያበቃበት ጊዜ እንደተቃረበ ተገንዝቦ ነበር። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ራሱ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ። ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፣ [ተናዘዝሁም]።” (ዳንኤል 9:3, 4) አምላክ በምሕረት ዓይኑ አይቶ ነፃ እንዲያወጣቸው ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ማሳየት ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 26:31-46፤ 1 ነገሥት 8:46-53) እምነትና የተዋረደ መንፈስ ማሳየት እንዲሁም ወደ ምርኮና ባርነት ካደረሷቸው ኃጢአቶች ሙሉ በሙሉ ንስሐ መግባት ነበረባቸው። በመሆኑም ዳንኤል በኃጢአተኛው ሕዝቡ ስም ወደ አምላክ ቀርቧል። እንዴት? በጾም፣ በሐዘን እንዲሁም የንስሐና የልብ ቅንነት መግለጫ የሆነውን ማቅ በመልበስ ነው።
5. ዳንኤል አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ የሚሆንበት ምን ምክንያት ነበረው?
5 የኤርምያስ ትንቢት፣ ብዙም ሳይቆይ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ይሁዳ እንደሚመለሱ ስለሚጠቁም ለዳንኤል ተስፋ ሆኖት ነበር። (ኤርምያስ 25:12፤ 29:10) ፋርስን እያስተዳደረ የነበረው ቂሮስ የሚባል ንጉሥ ስለነበር ዳንኤል የተገፉትና የተጨቆኑት አይሁዳውያን እፎይ የሚሉበት ጊዜ መቅረቡን እርግጠኛ እንደነበር አያጠራጥርም። አይሁዳውያን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ይገነቡ ዘንድ በቂሮስ አማካኝነት ነፃ እንደሚወጡ ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሮ አልነበረምን? (ኢሳይያስ 44:28–45:3) ይሁን እንጂ ይህ ነገር እንዴት እንደሚፈጸም ዳንኤል የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በመሆኑም ይሖዋን መማጸኑን ቀጠለ።
6. ዳንኤል በጸሎቱ ምን ነገር አምኖ መቀበሉን አሳይቷል?
6 ዳንኤል ያተኮረው በአምላክ ምሕረትና ፍቅራዊ ደግነት ላይ ነበር። አይሁዳውያን በማመፃቸው፣ የይሖዋን ትእዛዝ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸውና ለነቢያቱ ጀርባቸውን በመስጠታቸው ኃጢአት እንደሠሩ በትሕትና አምኗል። ‘በበደላቸው ምክንያት አምላክ እነርሱን መበተኑ’ ተገቢ ነበር። ዳንኤል እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “ጌታ ሆይ፣ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። በእርሱ ላይ ምንም እንኳ ያመፅን ብንሆን፣ በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን ባኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንኳ ባንሰማ፣ ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው። እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፣ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን።”—ዳንኤል 9:5-11፤ ዘጸአት 19:5-8፤ 24:3, 7, 8
7. ይሖዋ አይሁዳውያን በምርኮ እንዲሄዱ መፍቀዱ ተገቢ ነው ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው?
7 እስራኤላውያን አምላክን አለመታዘዛቸው ወይም ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ሳይጠብቁ መቅረታቸው ምን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል አምላክ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 26:31-33፤ ዘዳግም 28:15፤ 31:17) ዳንኤል ይህ የአምላክ እርምጃ ትክክል መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ በሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም። በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኃጢአታችንም እንመለስ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም። ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገሩን ጠብቆ በእኛ ላይ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ እኛም ቃሉን አልሰማንምና።”—ዳንኤል 9:12-14
8. ዳንኤል ለይሖዋ ያቀረበው ምልጃ ምንን መሠረት ያደረገ ነበር?
8 ዳንኤል ሕዝቡ ስላደረገው ነገር ሰበብ ለመደርደር አልሞከረም። “ኃጢአትን ሠርተናል፣ ክፋትንም አድርገናል” ብሎ ሲናገር በግዞት መወሰዳቸው የተገባ መሆኑን ያለ ምንም ማንገራገር መቀበሉ ነበር። (ዳንኤል 9:15) ዳንኤል ያሳሰበው ከመከራ መገላገሉ አልነበረም። ያቀረበው ልመና መሠረት ያደረገው የይሖዋን መከበርና ከፍ ከፍ ማለት ነው። አምላክ የአይሁዳውያኑን በደል ይቅር በማለትና ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለስ በኤርምያስ በኩል የገባውን ቃል የሚፈጽም ከመሆኑም ሌላ ታላቅ ስሙ እንዲቀደስ ያደርጋል። ዳንኤል እንዲህ ሲል ለምኗል:- “ጌታ ሆይ፣ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቁጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ።”—ዳንኤል 9:16
9. (ሀ) ዳንኤል ጸሎቱን የደመደመው ምን ልመና በማቅረብ ነው? (ለ) ዳንኤልን ያሳሰበው ነገር ምን ነበር? ለአምላክ ስም እንደሚጨነቅ ያሳየው እንዴት ነው?
9 ዳንኤል የሚያቀርበውን ልባዊ ጸሎት በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “አሁንም፣ አምላካችን ሆይ፣ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ፣ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። አምላኬ ሆይ፣ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት። አቤቱ፣ ስማ፤ አቤቱ፣ ይቅር በል፤ አቤቱ፣ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፣ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።” (ዳንኤል 9:17-19) አምላክ ይቅር ባይ ሳይሆን ቀርቶ ሕዝቦቹን ከግዞት ነፃ ባያወጣቸውና ቅድስቲቱ ከተማው ኢየሩሳሌምም ባድማ ሆና እንድትቀር ቢያደርግ ኖሮ ብሔራት የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩት ነበርን? ይሖዋ የባቢሎን አማልክትን በኃይል እንደማይተካከል አድርገው ሊያስቡ አይችሉም ነበርን? አዎን፣ የይሖዋ ስም ይነቀፍ ነበር። ዳንኤልንም ያስጨነቀው ይህ ነው። ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ 19 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን 18ቱ የተጠቀሱት በዚህ ጸሎቱ ውስጥ ነው!
ገብርኤል ከተፍ አለ
10. (ሀ) ወደ ዳንኤል የተላከው ማን ነው? ለምንስ? (ለ) ዳንኤል ገብርኤልን እንደ ‘ሰው’ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው?
10 ዳንኤል ገና እየጸለየ ሳለ ገብርኤል ከተፍ ብሎ እንዲህ አለው:- “ዳንኤል ሆይ፣ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። አንተ እጅግ የተወደድህ ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ትእዛዝ ወጥቷል፣ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፣ ራእዩንም አስተውል።” ይሁን እንጂ ዳንኤል ‘ገብርኤልን እንደ ሰው’ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው? (ዳንኤል 9:20-23) ዳንኤል ቀደም ሲል ስለ አውራው ፍየልና አውራው በግ ያየውን ራእይ በሚመለከት ማስተዋል ለማግኘት በጠየቀ ጊዜ “የሰው ምስያ [“ሰው የሚመስል፣” የ1980 ትርጉም]” በፊቱ ቆሞ ተመልክቷል። ይህ ለዳንኤል ማስተዋል እንዲሰጥ የተላከው መልአኩ ገብርኤል ነበር። (ዳንኤል 8:15-17) አሁንም በተመሳሳይ ዳንኤል ጸሎት ካቀረበ በኋላ ይህ መልአክ በሰው አምሳያ መጥቶ አጠገቡ እንዳለ ሰው ሆኖ አነጋግሮታል።
11, 12. (ሀ) በባቢሎን የይሖዋ ቤተ መቅደስም ሆነ መሠዊያ ባይኖርም ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በሕጉ ይፈለግባቸው ስለ ነበረው ቁርባን ያስቡ እንደነበር ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል ‘እጅግ የተወደደ ሰው’ የተባለው ለምንድን ነው?
11 ገብርኤል የመጣው ‘በማታ መሥዋዕት ጊዜ ነው።’ የይሖዋ መሠዊያ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ጋር አብሮ ጠፍቷል። አይሁዳውያኑም አረማዊ በሆኑት ባቢሎናውያን ዘንድ በግዞት ላይ ናቸው። በመሆኑም በባቢሎን ያሉት አይሁዳውያን ለአምላክ መሥዋዕት አያቀርቡም ነበር። ይሁን እንጂ በባቢሎን ያሉት ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በሙሴ ሕግ ለመሥዋዕት በተመደቡት ጊዜያት ይሖዋን ማወደሳቸውና መለመናቸው ተገቢ ነበር። ዳንኤል ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ ሰው እንደመሆኑ መጠን ‘እጅግ የተወደደ’ ተብሏል። ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው ይሖዋ በእርሱ ተደስቶ ነበር። ገብርኤልም በፍጥነት የተላከው ዳንኤል በእምነት ላቀረበው ጸሎት መልስ ይሰጥ ዘንድ ነው።—መዝሙር 65:2
12 ዳንኤል ወደ ይሖዋ መጸለይ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል በሆነበት ጊዜም እንኳ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላክ መጸለዩን አልተወም ነበር። (ዳንኤል 6:10, 11) በይሖዋ ፊት እጅግ የተወደደ ሆኖ መገኘቱ ምንም አያስገርምም! ከጸሎትም በተጨማሪ ዳንኤል በአምላክ ቃል ላይ የሚያደርገው ማሰላሰል የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለይቶ እንዲያውቅ አስችሎታል። ዳንኤል በጸሎት ከመጽናቱም ሌላ ጸሎቱ መልስ እንዲያገኝ ወደ ይሖዋ እንዴት መቅረብ እንዳለበትም ያውቅ ነበር። የአምላክን ጽድቅ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዳንኤል 9:7, 14, 16) ጠላቶቹ ምንም ስህተት ሊያገኙበት ባይችሉም እንኳ ዳንኤል በአምላክ ዓይን ኃጢአተኛ መሆኑን በመገንዘብ ተናዝዟል።—ዳንኤል 6:4፤ ሮሜ 3:23
ኃጢአትን ወደ ፍጻሜ ለማምጣት የተቀጠረ “ሰባ ሳምንት”
13, 14. (ሀ) ገብርኤል ለዳንኤል የገለጸለት በጣም አስፈላጊ መረጃ ምንድን ነው? (ለ) ‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ የምን ያህል ጊዜ ርዝማኔ አላቸው? እንዴትስ እናውቃለን?
13 በጸሎት ይተጋ የነበረው ዳንኤል ያገኘው መልስ እንዴት የሚያስገርም ነው! ይሖዋ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ከማረጋገጥም አልፎ ከዚያ ይበልጥ ትርጉም ስላለው ክንውን ይኸውም አስቀድሞ በትንቢት ስለተነገረው የመሲሑ መምጣት እንዲያስተውል ረድቶታል። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ ኢሳይያስ 9:6, 7) ገብርኤል ለዳንኤል እንዲህ ብሎታል:- “ዓመፃን ይጨርስ [“መተላለፍን ያስቀር” NW]፣ ኃጢአትንም ይፈጽም [“ወደ ፍጻሜው ያመጣ፣” NW]፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምንም ጽድቅ ያገባ፣ ራእይንና ትንቢትን [“ነቢይን፣” NW] ያትም፣ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ [“ሳምንት፣” NW] ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።”—ዳንኤል 9:24, 25
14 ይህ በእርግጥም ምሥራች ነበር! ኢየሩሳሌም እንደገና መገንባቷና አምልኮው በአዲሱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ተመልሶ መቋቋሙ እንዳለ ሆኖ ‘አለቃው መሲሕም’ በተቀጠረው ጊዜ ሊመጣ ነው። ይህ ሁሉ የሚከናወነው ‘በሰባ ሳምንታት’ ውስጥ ነው። ገብርኤል ስለ ቀናት ስላልተናገረ እነዚህ እያንዳንዳቸው ሰባት ቀናት ያሏቸውን ሳምንታት ማለትም 490 ቀናት ወይም አንድ ሙሉ አንድ ሦስተኛ ዓመትን ብቻ የሚያመለክቱ አይደሉም። አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው የኢየሩሳሌም ‘ከጎዳናና ከቅጥር ጋር’ ዳግም መገንባት ከዚያ የበለጠ ጊዜ ወስዷል። እነዚህ ሳምንታት የዓመታት ሳምንታት ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሠሩ በርካታ ትርጉሞች እያንዳንዱ ሳምንት ሰባት ዓመታትን ያቀፈ መሆኑን ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል የአይሁዳውያን ጽሑፎች ማኅበር ያዘጋጀው ታናክ—ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ የተባለው ትርጉም በዳንኤል 9:24 ግርጌ ማስታወሻ ላይ “ሰባ የዓመታት ሳምንቶች” ብሎ አስቀምጦታል። አን አሜሪካን ትራንስሌሽን ደግሞ “በሕዝባችሁና በቅድስት ከተማችሁ ላይ ሰባ የዓመታት ሳምንታት ተቀጥረዋል” ይላል። የሞፋትና የሮዘርሃም ትርጉሞችም በተመሳሳይ መልኩ አስቀምጠውታል።
15. ‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ በየትኞቹ ሦስት ክፍሎች ተከፋፍለዋል? የሚጀምሩትስ መቼ ነው?
15 መልአኩ በተናገረው መሠረት ‘ሰባው ሳምንታት’ በሦስት ወቅቶች ይከፈላሉ:- (1) ‘ሰባት ሳምንታት፣’ (2) ‘ስድሳ ሁለት ሳምንታት’ እንዲሁም (3) አንድ ሳምንት። ይህም 49 ዓመት፣ 434 ዓመት እንዲሁም 7 ዓመት በድምሩ 490 ዓመት ይሆናል ማለት ነው። የሚያስገርመው ዘ ሪቫይዝድ ኢንግሊሽ ባይብል እንዲህ ይላል:- “በሕዝብህና በቅዱስ ከተማችሁ ላይ ሰባ ጊዜ ሰባት ዓመት ተቀጥሮባችኋል።” አይሁዳውያኑ ለ70 ዓመታት በባቢሎን ካሳለፉት የግዞተኝነትና የመከራ ዘመን በኋላ ለ490 ዓመታት ወይም ለ7 ጊዜ 70 ዓመታት ያህል በአምላክ ፊት ለየት ያለ ሞገስ ያገኛሉ። ይህ ጊዜ የሚጀምረው “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት” አንስቶ ነው። ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ ጀመሩ
16. ቂሮስ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ እንደተገለጸው አይሁዳውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው የመለሳቸው ለምን ነበር?
16 ‘ከሰባዎቹ ሳምንታት’ መጀመሪያ ጋር በተያያዘ መጤን የሚገባቸው ሦስት ጉልህ ክንውኖች አሉ። የመጀመሪያው በ537 ከዘአበ ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ያወጣበት ጊዜ ነበር። እንዲህ እናነባለን:- “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል:- የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፣ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤ በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።” (ዕዝራ 1:2-4) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የዚህ ድንጋጌ ዋነኛ ዓላማ “የእግዚአብሔር ቤት” ማለትም ቤተ መቅደሱ በቀድሞው ቦታ ላይ እንደገና እንዲሠራ ማድረግ ነው።
17. ለዕዝራ የተሰጠው ደብዳቤ ወደ ኢየሩሳሌም ስለተመለሰበት ምክንያት ምን ይላል?
17 ሁለተኛው ክንውን ደግሞ በፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ (የቀዳማዊ ዜርሰስ ልጅ አርጤክስስ ሎንጊማነስ) ሰባተኛ የግዛት ዘመን የተፈጸመው ነው። በዚህ ወቅት ጸሐፊው ዕዝራ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም አራት ወር የፈጀ ጉዞ አድርጓል። ከንጉሡ ልዩ ደብዳቤ አስጽፎ የነበረ ቢሆንም ኢየሩሳሌም እንድትገነባ ፈቃድ የሚሰጥ አልነበረም። ይልቁንም የዕዝራ ተልእኮ ‘በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔር ቤት ማሳመር’ ነበር። ደብዳቤው ስለ ወርቅ፣ ብር፣ ንዋየ ቅድሳት እንዲሁም በመቅደስ የሚደረገውን አምልኮ ለመደገፍ የስንዴ፣ የወይን፣ የዘይት እንዲሁም የጨው መዋጮ ስለ ማድረግና በዚህ ሥራ የሚሳተፉ ሰዎችም ከቀረጥ ነፃ ስለ መሆናቸው የሚጠቅሰውም ለዚህ ነው።—ዕዝራ 7:6-27
18. ነህምያን የረበሸው ዜና ምን ነበር? ንጉሥ አርጤክስስ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?
18 ሦስተኛው ክንውን ደግሞ ከ13 ዓመታት በኋላ በፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ 20ኛ ዓመት ላይ የተፈጸመው ነው። በዚህ ጊዜ ነህምያ “በሱሳ ግንብ” የወይን ጠጅ አሳላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር። ከባቢሎን የተመለሱት ቀሪዎች ኢየሩሳሌምን በተወሰነ መጠን መልሰው ገንብተዋት ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር ተስተካክሏል ማለት አልነበረም። ነህምያ ‘የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደፈረሰና በሮችዋም በእሳት እንደተቃጠሉ’ ሰማ። በዚህ ወሬ እጅግ ከመረበሹ የተነሳ ልቡ በሐዘን ተዋጠ። ነህምያ ያሳዘነው ነገር ምን እንደሆነ ሲጠየቅ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ፤ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፣ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን” ሲል መልስ ሰጥቷል።—ነህምያ 1:1-3፤ 2:1-3
19. (ሀ) ነህምያ በንጉሥ አርጤክስስ ጥያቄ ሲቀርብለት መጀመሪያ ያደረገው ምን ነበር? (ለ) ነህምያ ምን ጠየቀ? በጉዳዩ የይሖዋ እጅ እንደነበረበትስ የገለጸው እንዴት ነው?
19 ስለ ነህምያ የሚናገረው ዘገባ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ንጉሡም:- ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። ንጉሡንም:- ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፣ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፣ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት።” አርጤክስስ በሐሳቡ ተደሰተ። ነህምያ ቀጥሎ ያቀረበውንም ጥያቄ ተቀበለው:- “ንጉሡ ደስ ቢለው፣ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ [በኤፍራጥስ] ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፣ ለከተማውም ቅጥር፣ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት።” ነህምያ በጉዳዩ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ሲገልጽ “ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ” ሲል ተናግሯል።—ነህምያ 2:4-8
20. (ሀ) ‘ኢየሩሳሌምን ስለ መጠገንና መሥራት’ የወጣው ትእዛዝ ተግባራዊ የሆነው መቼ ነው? (ለ) ‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ የጀመሩት መቼ ነው? ያበቁትስ? (ሐ) ‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ የጀመሩበትና ያበቁበት ጊዜ ትክክል መሆኑን የሚጠቁሙት የትኞቹ ማስረጃዎች ናቸው?
20 ፈቃድ የተሰጠው በኒሳን ወር ማለትም በአርጤክስስ 20ኛ የግዛት ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ቢሆንም ‘ኢየሩሳሌምን የመጠገንና የመሥራት ትእዛዙ’ ተግባራዊ የሆነው ከወራት በኋላ ነበር። ይህም የሆነው ነህምያ ኢየሩሳሌም ደርሶ የመልሶ ግንባታውን ሥራ ሲጀምር ነው። ዕዝራ ኢየሩሳሌም ለመድረስ አራት ወር ፈጅቶበት ነበር። ሱሳ ግን የምትገኘው ከባቢሎን በስተ ምሥራቅ 322 ኪሎ ሜትር ርቃ ስለ ነበር ለኢየሩሳሌም የበለጠ ሩቅ ነበረች። እንግዲያው ነህምያ ኢየሩሳሌም የደረሰው በአርጤክስስ 20ኛ ዓመት ሊያበቃ ሲቃረብ ወይም በ455 ከዘአበ ነው ለማለት ይቻላል። እነዚያ በትንቢት የተነገሩት ‘ሰባ ሳምንታት’ ወይም 490 ዓመታት የሚጀምሩት በዚህ ጊዜ ሲሆን በ36 እዘአ መገባደጃ ላይ ያበቃሉ።—በገጽ 197 ላይ የሚገኘውን “የአርጤክስስ የግዛት ዘመን የጀመረው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
‘አለቃው መሲሕ’ ተገለጠ
21. (ሀ) በመጀመሪያዎቹ ‘ሰባት ሳምንታት’ ውስጥ ምን ነገር መከናወን ነበረበት? በወቅቱስ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ነበሩ? (ለ) መሲሑ መገለጥ የነበረበት በየትኛው ዓመት ነው? የሉቃስ ወንጌል በዚያ ጊዜ ምን ነገር እንደተከናወነ ይገልጻል?
21 ኢየሩሳሌም መልሳ እስክትገነባ ድረስ ምን ያህል ዓመታት አልፈዋል? አይሁዳውያኑ በነበረባቸው የውስጥ ችግር እንዲሁም ከሰማርያ ሰዎችና ከሌሎቹ ይደርስባቸው ከነበረው ተቃውሞ የተነሣ የከተማዋ መልሶ ግንባታ “በጭንቀት ዘመን” እንደሚሆን ተነግሯል። ሥራው በ406 ከዘአበ ላይ ማለትም ‘በሰባቱ ሳምንታት’ ወይም በ49 ዓመታት ውስጥ የሚፈለገውን ያህል ተከናውኖ እንደነበር መረዳት ይቻላል። (ዳንኤል 9:25) ከዚህ በኋላ የ62 ሳምንት ወይም የ434 ዓመታት ክፍለ ጊዜው ይቀጥላል። ይህ ጊዜ ሲፈጸም ለረጅም ጊዜ የተጠበቀው መሲሕ ይመጣል። ከ455 ከዘአበ ተነሥተን 483 ዓመታት (49 ሲደመር 434) ስንቆጥር 29 እዘአ ላይ እንደርሳለን። በዚህ ጊዜ የተፈጸመው ነገር ምን ነበር? ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ እንዲህ ይለናል:- “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፣ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፣ . . . ሳ[ለ] . . . “የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። . . . የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መሲሑን ‘ይጠብቁ’ ነበር።—ሉቃስ 3:1-3, 15
22. ኢየሱስ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ የሆነው መቼና በምን መልኩ ነበር?
22 ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ዮሐንስ አልነበረም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በ29 እዘአ በናዝሬት በተጠመቀ ጊዜ ያየውን ነገር በሚመለከት ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፣ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ:- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” (ዮሐንስ 1:32-34) ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ቅቡዕ ማለትም መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኗል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ የዮሐንስ ደቀ መዝሙር የሆነው እንድርያስ ከተቀባው ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ለስምዖን ጴጥሮስ “መሢሕን አግኝተናል” ብሎታል። (ዮሐንስ 1:42) በዚህ መንገድ ‘አለቃው መሲሕ’ በተነገረለት ጊዜ ማለትም በ69 ሳምንታቱ ፍጻሜ ላይ ተገኝቷል!
የመጨረሻው ሳምንት ክንውኖች
23. ‘አለቃው መሲሕ’ መሞት የነበረበት ለምንድን ነው? ይህስ የሚሆነው መቼ ነበር?
23 በ70ኛው ሳምንት ላይ መከናወን የነበረበት ነገር ምንድን ነው? ገብርኤል ‘ሰባ ሳምንት’ የተቀጠረው “መተላለፍን ያስቀር፣ ኃጢአትንም ወደ ፍጻሜው ያመጣ፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምንም ጽድቅ ያገባ፣ ራእይንና ነቢይን ያትም፣ ቅዱሰ ቅዱሳንንም ይቀባ ዘንድ” ነው ሲል ተናግሯል። ይህን ሁሉ ለማከናወን ‘አለቃው መሢሕ’ መሞት ነበረበት። መቼ? ገብርኤል እንዲህ ብሏል:- “ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፣ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ . . . እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቁርባኑን ያስቀራል።” (ዳንኤል 9:26ሀ [NW], 27ሀ) ወሳኝ የሆነው ጊዜ፤ ‘የሣምንቱ እኩሌታ’ ነው። ይህም የመጨረሻው የዓመታት ሳምንት አጋማሽ ነው።
24, 25. (ሀ) በትንቢት በተነገረው መሠረት ክርስቶስ የሞተው መቼ ነው? የእርሱ ሞትና ትንሣኤስ ምን ነገር ወደ ፍጻሜው እንዲመጣ አድርጓል? (ለ) የኢየሱስ ሞት ምን ነገር አከናውኗል?
24 የኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝባዊ አገልግሎት የጀመረው በ29 እዘአ መገባደጃ ላይ ሲሆን ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቀጥሏል። በትንቢት በተነገረው መሠረት ክርስቶስ በ33 እዘአ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ‘በተገደለ’ ጊዜ ሰብዓዊ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 53:8፤ ማቴዎስ 20:28) ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ የሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት ዋጋ በሰማይ ለአምላክ ካቀረበ በኋላ የእንስሳ መሥዋዕትና ቁርባን የማቅረቡ አስፈላጊነት ቀርቷል። የአይሁድ ካህናት በ70 እዘአ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እስከ ጠፋበት ጊዜ ድረስ የእንስሳ መሥዋዕት ያቀርቡ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቶቹ መሥዋዕቶች በአምላክ ፊት ተቀባይነት አጡ። ዳግመኛ መቅረብ በማያስፈልገው የተሻለ መሥዋዕት ተተኩ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ክርስቶስ] ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም . . .፣ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና።”—ዕብራውያን 10:12, 14
25 ኃጢአትና ሞት የሰውን ልጅ ፍዳ ማስቆጠራቸውን ቢቀጥሉም ኢየሱስ በመሞትና ሰማያዊ ሕይወት አግኝቶ ከሞት በመነሳት ትንቢቱ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል። ‘መተላለፍን አስቀርቷል፣ ኃጢአትን ወደ ፍጻሜው አምጥቷል፣ በደልንም አስተሰርዮአል፣ ጽድቅንም አግብቷል።’ አምላክ፣ አይሁዳውያን ኃጢአተኞች መሆናቸውን ያጋለጠውንና የኮነናቸውን ሕግ አስወግዶት ነበር። (ሮሜ 5:12, 19, 20፤ ገላትያ 3:13, 19፤ ኤፌሶን 2:14, 15፤ ቆላስይስ 2:13, 14) ከዚህ በኋላ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች በደላቸው ሊሰረዝላቸውና ቅጣታቸውም ሊቀር ይችላል። እምነት ለሚያሳዩ ሰዎች በመሲሑ የማስተሠርያ መሥዋዕት አማካኝነት ከአምላክ ጋር መታረቅ የሚችሉበት መንገድ ተከፍቶላቸው ነበር። ‘በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት’ ለማግኘት ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ሮሜ 3:21-26፤ 6:22, 23፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
26. (ሀ) የሕጉ ቃል ኪዳን ተወግዶ የነበረ ቢሆንም ‘ለአንድ ሳምንት የጸናው ቃል ኪዳን’ የትኛው ነው? (ለ) በሰባኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ ምን ነገር ተከናውኗል?
26 በመሆኑም ይሖዋ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት በ33 እዘአ የሕጉን ቃል ኪዳን አስወግዶታል። ታዲያ መሲሑ “ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ” ያደርጋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? የአብርሃምን ቃል ኪዳን በማጽናቱ ነው። ሰባኛው ሳምንት እስኪጠናቀቅ ድረስ አምላክ የዚህን ቃል ኪዳን በረከት ለዕብራውያኑ የአብርሃም ዝርያዎች ዘርግቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ‘በሰባው ሳምንት’ ማብቂያ ላይ ማለትም በ36 እዘአ ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምልኮ ፍቅር ለነበረው ለኢጣሊያዊው ቆርኔሌዎስና ለቤተሰቦቹ እንዲሁም ለሌሎች አሕዛብ ሰብኳል። ከዚያ ዕለት አንስቶ ምሥራቹ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ መታወጅ ጀምሯል።—ሥራ 3:25, 26፤ 10:1-48፤ ገላትያ 3:8, 9, 14
27. የተቀባው ‘ቅድስተ ቅዱሳን’ ምንድን ነው? እንዴትስ?
27 በተጨማሪም ትንቢቱ ‘ቅድስተ ቅዱሳኑ’ እንደሚቀባ ተናግሯል። ይህ የሚያመለክተው በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ወይም ውስጠኛ ክፍል መቀባቱን አይደለም። እዚህ ላይ ‘ቅድስተ ቅዱሳን’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የአምላክን ሰማያዊ መቅደስ ነው። በዚያም ኢየሱስ የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ለአባቱ አቅርቧል። ኢየሱስ በ29 እዘአ መጠመቁ በምድራዊው መገናኛ ድንኳን በኋላም ቤተ መቅደስ ውስጥ በነበረው ቅድስተ ቅዱሳን የሚወከለው ሰማያዊ ማለትም መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲቀባ ወይም ለሥራ የተለየ እንዲሆን አድርጓል።—ዕብራውያን 9:11, 12
አምላክ ማረጋገጫ የሰጠበት ትንቢት
28. ‘ራእይንና ነቢይን ማተሙ’ ምን ትርጉም አለው?
28 መልአኩ ገብርኤል የተናገረው መሲሐዊ ትንቢት ‘ራእይንና ነቢይን ስለ ማተምም’ ይገልጻል። ይህም ማለት መሲሑ በመሥዋዕቱ፣ በትንሣኤውና በሰማይ በመገኘቱ እንዲሁም በ70ኛው ሳምንት በተከናወኑት ነገሮች አማካኝነት እንደሚፈጽማቸው የተነገሩትን ጨምሮ መሲሑን የሚመለከቱት ሁሉም ትንቢቶች መለኮታዊ ማረጋገጫ እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ ታትመዋል፣ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ፣ አመኔታም የሚጣልባቸው ይሆናሉ ማለት ነው። ራእይው መታተሙ ለመሲሑ ብቻ የተወሰነ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ፍጻሜውን የሚያገኘው በመሲሑና አምላክ በእርሱ አማካኝነት በሚያከናውነው ሥራ ይሆናል። የራእይውን ትክክለኛ ማብራሪያም ማግኘት የምንችለው በትንቢት ከተነገረለት መሲሕ ብቻ ይሆናል። ታትሟልና ሌላ ትርጉሙን ሊፈታልን የሚችል አይኖርም።
29. ተመልሳ የተገነባችው ኢየሩሳሌም ምን ይጠብቃት ነበር? ከምን የተነሣ?
29 ገብርኤል ኢየሩሳሌም መልሳ እንደምትገነባ ተንብዮ ነበር። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እንደገና የተገነባችው ከተማና ቤተ መቅደሷ እንደሚፈርሱ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፣ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። . . . በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቆረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።” (ዳንኤል 9:26ለ, 27ለ) ይህ ጥፋት የሚፈጸመው ‘ከሰባው ሳምንት’ በኋላ ቢሆንም ክርስቶስን አንቀበልም ብለው በገደሉበት የመጨረሻ “ሳምንት” የተከናወኑት ነገሮች ያስከተሉት መዘዝ ነው።—ማቴዎስ 23:37, 38
30. የታሪክ መዛግብት እንደሚያረጋግጡት ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ የማይለው አምላክ የተናገረው ቃል ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
30 የታሪክ መዛግብት እንደሚያረጋግጡት የሶርያው ገዥ ሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮማ ሠራዊት በ66 እዘአ ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር። አይሁዳውያን ለመከላከል ቢሞክሩም የሮማ ኃይሎች የጣዖት አርማዎቻቸውን ወይም ምልክቶቻቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት በስተ ሰሜን ያለውን የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ማፍረስ ጀመሩ። በዚያ ስፍራ መቆማቸው ከፍተኛ ውድመት ሊያስክትል የሚችል “ርኵሰት” አድርጓቸዋል። (ማቴዎስ 24:15, 16) በ70 እዘአ ግን ሮማውያን በጄኔራል ቲቶ እየተመሩ እንደ “ጎርፍ” በመምጣት ከተማዋንና ቤተ መቅደሷን አወደሙ። ይህ በአምላክ የተወሰነ በሌላ አባባል “የተቆረጠ” ነገር ስለ ነበር ምንም ነገር ሊገታቸው አልቻለም። ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ የማይለው ይሖዋ በድጋሚ ቃሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል!
ምን አስተውለሃል?
• የኢየሩሳሌም የ70 ዓመት ባድማነት ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ ዳንኤል ለይሖዋ ያቀረበው ልመና ምን ነበር?
• ‘የሰባው ሳምንታት’ ርዝማኔ ምን ያህል ነው? የጀመረውና ያበቃውስ መቼ ነው?
• ‘አለቃው መሲሕ’ የተገለጠው መቼ ነው? ‘የተገደለውስ’ በየትኛው ወሳኝ ወቅት ላይ ነው?
• ‘ከብዙዎች ጋር ለአንድ ሳምንት የጸናው’ ቃል ኪዳን የትኛው ነው?
• ‘ከሰባዎቹ ሳምንታት’ በኋላ ምን ነገር ተፈጽሟል?
[በገጽ 197 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የአርጤክስስ የግዛት ዘመን የጀመረው መቼ ነው?
የፋርሱ ንጉሥ የአርጤክስስ የግዛት ዘመን የጀመረበትን ዓመት በሚመለከት በታሪክ ጸሐፊዎች መካከል ልዩነት ይታያል። አንዳንዶች አባቱ ዜርሰስ መግዛት የጀመረው በ486 ከዘአበ ስለሆነና በ21ኛው የግዛቱ ዓመት ስለሞተ አርጤክስስ ወደ ሥልጣን የወጣው በ465 ከዘአበ ነው ይላሉ። ነገር ግን አርጤክስስ ወደ ዙፋን የወጣው በ475 ከዘአበ እንደሆነና የመጀመሪያው የግዛት ዘመኑም 474 ከዘአበ እንደነበር የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ።
በጥንቷ የፋርስ መዲና በፐርሰፐሊስ ተቆፍረው የተገኙ የተቀረጹ ጽሑፎችና ምስሎች ዜርሰስና አባቱ ቀዳማዊ ዳርዮስ አብረው ይገዙ እንደነበር ይጠቁማሉ። አብረው የገዙት ለአሥር ዓመት ቢሆንና ዳርዮስ በ486 ከዘአበ ከሞተ በኋላ ዜርሰስ ለ11 ዓመት ብቻውን ቢገዛ የአርጤክስስ የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት 474 ከዘአበ ሊሆን ይችላል።
ሁለተኛው ማስረጃ ደግሞ በ480 ከዘአበ የዜርሰስን ኃይሎች ድል ካደረገው ከአቴናዊው ጄኔራል ቴሚስቶክልስ ጋር የተያያዘ ነው። ከጊዜ በኋላ በግሪካውያኑ ዘንድ ጥላቻን በማትረፉ አገር በመክዳት ወንጀል ይከሰሳል። ቴሚስቶክልስ ሸሽቶ በፋርስ ቤተ መንግሥት ጥገኝነት ሲጠይቅ እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውታል። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ቱሳይዳይደስ እንዳለው ከሆነ ይህ የሆነው አርጤክስስ ‘ገና ዙፋኑን እንደጨበጠ’ ነበር። እንደ ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዲዶረስ ሲከለስ አባባል ቴሚስቶክልስ የሞተው በ471 ከዘአበ ነው። ቴሚስቶክልስ ንጉሥ አርጤክስስ ፊት ከመቅረቡ በፊት የፋርስን ቋንቋ የሚማርበት አንድ ዓመት እንዲፈቀድለት ጠይቆ ስለነበር ወደ ትንሿ እስያ የመጣው ግፋ ቢል በ473 ከዘአበ መሆን ይኖርበታል። በጄሮም የተዘጋጀው የዩሴቢየስ ዜና ታሪክም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። አርጤክስስ ‘ሥልጣን ላይ የወጣው’ ቴሚስቶክልስ በ473 ከዘአበ ወደ ትንሿ እስያ ከመድረሱ ‘ትንሽ ቀደም ብሎ’ ስለነበር ጀርመናዊው ምሁር ኧርነስት ሄስተንበርክ፣ ክሪስቶሎጂ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት በተባለው የጽሑፍ ሥራቸው ላይ እንደገለጹት ሌሎች ምንጮች እንደሚሉት ሁሉ የአርጤክስስ ግዛት የጀመረው በ474 ከዘአበ ነው በሚለው ሐሳብ ተስማምተዋል። በመጨመርም “የአርጤክስስ ግዛት 20 ዓመት የሚሞላው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ455 ላይ ነው” ብለዋል።
[ሥዕል]
የቴሚስቶክልስ ምስል
[በገጽ 188 እና 189 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
“ሰባ ሳምንት”
455 ከዘአበ 406 ከዘአበ 29 እዘአ 33 እዘአ 36 እዘአ
‘ኢየሩሳሌምን ኢየሩሳሌም ዳግም መሲሑ መሲሑ ‘የሰባው ሳምንታት’
ለመጠገን ትእዛዝ የተገነባችበት ጊዜ የተገለጠበት ጊዜ የሞተበት ጊዜ ፍጻሜ
የወጣበት ጊዜ’
7 ሳምንታት 62 ሳምንታት 1 ሳምንት
49 ዓመታት 434 ዓመታት 7 ዓመታት
[በገጽ 180 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 193 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]