የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መጋቢት 2020
ከመጋቢት 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 22–23
“አምላክ አብርሃምን ፈተነው”
(ዘፍጥረት 22:1, 2) ከዚህ በኋላ እውነተኛው አምላክ አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” ሲል ጠራው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ። 2 ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።”
አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ አምላክ የጠየቀው ለምንድን ነው?
አምላክ ለአብርሃም የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት፦ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ . . . የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።” (ዘፍጥረት 22:2) ይሖዋ ስለ ይስሐቅ ሲናገር “የምትወደውን . . . ልጅህን” ማለቱን ልብ በል። አብርሃም ይስሐቅን ምን ያህል እንደሚወደው ይሖዋ ያውቅ ነበር። አምላክ፣ እሱ ራሱም ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚሰማው ያውቃል። ይሖዋ ኢየሱስን በጣም የሚወደው ከመሆኑ የተነሳ ከሰማይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የምወድህ ልጄ” እና “የምወደው ልጄ” ብሏል።—ማርቆስ 1:11፤ 9:7
ይሖዋ ለአብርሃም ጥያቄውን ያቀረበበት መንገድ “የጠየቀው ነገር ምን ያህል ከባድ መሥዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑን እንደተገነዘበ” የሚያሳይ እንደሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ተናግረዋል። አምላክ ያቀረበው ጥያቄ አብርሃምን በጥልቅ እንዲያዝን አድርጎት ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን፤ በተመሳሳይም ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት በሚመለከትበት ወቅት የተሰማው ጥልቅ ሐዘን እኛ ልናስበው ከምንችለው በላይ ነው። የልጁ ሞት ይሖዋ ከዚያ በፊት ካጋጠመውም ሆነ ከዚያ በኋላ ሊያጋጥመው ከሚችል ከማንኛውም ሁኔታ የከፋ ሐዘን እንዳስከተለበት ጥርጥር የለውም።
ይሖዋ፣ አብርሃምን የጠየቀውን ነገር ስናስበው ቢዘገንነንም አምላክ ይህ ታማኝ ሰው ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እንዳልፈቀደ ማስታወሳችን ጥበብ ነው። አምላክ፣ ይስሐቅ እንዲሞት ባለመፍቀድ አንድ ወላጅ ሊደርስበት የሚችለው ከሁሉ የከፋ ሐዘን አብርሃም ላይ እንዳይደርስ አድርጓል። ያም ሆኖ ይሖዋ ‘ለገዛ ልጁ ሳይሳሳ ለእኛ አሳልፎ ሰጥቶታል።’ (ሮም 8:32) አምላክ እንዲህ ያለ ከባድ ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይህን ያደረገው “ሕይወት ማግኘት እንድንችል” ሲል ነው። (1 ዮሐንስ 4:9) አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ታላቅ መሥዋዕት ነው! ታዲያ ይህ እኛም በምላሹ እሱን እንድንወደው ሊያነሳሳን አይገባም?
(ዘፍጥረት 22:9-12) በመጨረሻም እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን ረበረበበት። ልጁን ይስሐቅንም እጁንና እግሩን አስሮ በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ አጋደመው። 10 ከዚያም አብርሃም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላውን አነሳ። 11 ሆኖም የይሖዋ መልአክ ከሰማይ ጠርቶት “አብርሃም፣ አብርሃም!” አለው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ። 12 መልአኩም እንዲህ አለው፦ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት፤ ምንም ነገር አታድርግበት፤ ምክንያቱም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ።”
(ዘፍጥረት 22:15-18) የይሖዋም መልአክ ከሰማይ ለሁለተኛ ጊዜ አብርሃምን ጠራው፤ 16 እንዲህም አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በራሴ እምላለሁ፤ ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለመስጠት ስላልሳሳህ 17 በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ በእርግጥ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶቹን በር ይወርሳል። 18 ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’”
አምላክን በመታዘዝ በመሐላ ከገባው ቃል ተጠቃሚ ሁኑ
6 ይሖዋ አምላክም ኃጢአተኞች ለሆኑት የሰው ልጆች ጥቅም ሲል “በሕያውነቴ እምላለሁ! ይላል ልዑል እግዚአብሔር” እንደሚለው ያሉ አገላለጾችን በመጠቀም መሐላ ገብቷል። (ሕዝ. 17:16) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ ከ40 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ጊዜያት በመሐላ ቃል እንደገባ ይገልጻል። በዚህ ረገድ በሰፊው የሚታወቀው ምሳሌ አምላክ ከአብርሃም ጋር በነበረው ግንኙነት የገባው መሐላ ሳይሆን አይቀርም። በርካታ ዓመታት ባስቆጠረ ጊዜ ውስጥ ይሖዋ ለአብርሃም የተለያዩ የቃል ኪዳን ተስፋዎች የሰጠው ሲሆን ተስፋዎቹ ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ አስቀድሞ የተነገረለት ዘር በልጁ በይስሐቅ በኩል ከአብርሃም እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። (ዘፍ. 12:1-3, 7፤ 13:14-17፤ 15:5, 18፤ 21:12) ይሁንና ይሖዋ፣ አብርሃም የሚወደውን ልጁን እንዲሠዋ ባዘዘው ጊዜ በአብርሃም ፊት ከባድ ፈተና ተደቀነ። አብርሃም ምንም ሳያመነታ ታዘዘ፤ የአምላክ መልአክ ባያስቆመው ኖሮ ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ምንም አልቀረውም ነበር። በዚህ ጊዜ አምላክ የሚከተለውን መሐላ ገባለት፦ “በራሴ ማልሁ . . . አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና፣ በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”—ዘፍ. 22:1-3, 9-12, 15-18
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 22:5) በዚህ ጊዜ አብርሃም አገልጋዮቹን “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው።
ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል
13 አብርሃም አብረውት ከተጓዙት አገልጋዮቹ ከመለየቱ በፊት “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” ብሏቸዋል። (ዘፍ. 22:5) አብርሃም ምን ማለቱ ነበር? ይስሐቅን መሥዋዕት ሊያደርገው እንደሆነ እያወቀ ከይስሐቅ ጋር እንደሚመለስ ለአገልጋዮቹ ሲናገር እየዋሸ ነበር? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም ምን አስቦ እንደነበር ለማወቅ ይረዳናል። (ዕብራውያን 11:19ን አንብብ።) አብርሃም “አምላክ [ይስሐቅን] ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።” አዎ፣ አብርሃም በትንሣኤ ያምን ነበር። እሱም ሆነ ሣራ በስተርጅናቸው ልጅ መውለድ እንዲችሉ ይሖዋ እንደረዳቸው ያውቃል። (ዕብ. 11:11, 12, 18) አብርሃም በይሖዋ ዘንድ የማይቻል ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል። በመሆኑም በዚያ ፈታኝ ወቅት የሚፈጠረው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ የሚወደውን ልጁን መልሶ እንደሚያገኘው እርግጠኛ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት በይስሐቅ በኩል ነው። በእርግጥም አብርሃም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም!
(ዘፍጥረት 22:12) መልአኩም እንዲህ አለው፦ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት፤ ምንም ነገር አታድርግበት፤ ምክንያቱም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ።”
it-1 853 አን. 5-6
አስቀድሞ ማወቅ፣ አስቀድሞ መወሰን
የወደፊቱን የማወቅ ችሎታን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ መጠቀም። ‘አምላክ የወደፊቱን የማወቅ ችሎታውን በማንኛውም ጊዜ ይጠቀምበታል’ ከሚለው አመለካከት የተለየ ሌላ አመለካከት አለ። ይህም ‘አምላክ ይህን ችሎታውን የሚጠቀምበት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው’ የሚለው ሲሆን ይህ አመለካከት አምላክ ካወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶችና በቃሉ ውስጥ ስለ ራሱ ከገለጻቸው ነገሮች ጋር መስማማት ይኖርበታል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አምላክ የወደፊቱን የማወቅ ችሎታውን በማንኛውም ጊዜ እንደሚጠቀምበት ሳይሆን በወቅቱ ያለውን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ በዚያ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ።
ለምሳሌ ዘፍጥረት 11፡5-8 ላይ አምላክ ትኩረቱን ወደ ምድር በማድረግ በባቤል የነበረውን ሁኔታ እንደቃኘና ከዚያ በኋላ ፕሮጀክታቸውን ለማጨናገፍ ምን መደረግ እንዳለበት እንደወሰነ ይገልጻል። በሰዶምና በገሞራ ክፋት ከተስፋፋ በኋላ ይሖዋ ጉዳዩን ለማጣራት (በመላእክቱ አማካኝነት) እንዳሰበ ለአብርሃም ገልጾለታል፤ እንዲህ ብሎታል፦ “ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ። ነገሩ እንደዚያ ካልሆነም ማወቅ እችላለሁ።” (ዘፍ 18:20-22፤ 19:1) በተጨማሪም አምላክ ‘ከአብርሃም ጋር እንደተዋወቀ’ ተናግሯል፤ እንዲሁም ይሖዋ፣ አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ እንደደረሰ ከተመለከተ በኋላ “አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ” ብሏል።—ዘፍ 18:19፤ 22:11, 12፤ ከነህ 9:7, 8 እና ከገላ 4:9 ጋር አወዳድር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
it-1 604 አን. 5
ጻድቅ ሆኖ መቆጠር
አብርሃም የኖረው ክርስቶስ ከመሞቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም ጻድቅ ተደርጎ ሊቆጠር የቻለው እንዴት ነው?
በተመሳሳይም ከሥራ ጋር የተጣመረው የአብርሃም እምነት ‘ጽድቅ ሆኖ ተቆጥሮለታል።’ (ሮም 4:20-22) ይህ ሲባል ግን አብርሃምም ሆነ በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ ሌሎች ታማኝ ሰዎች ፍጹም ወይም ምንም ኃጢአት የሌለባቸው ነበሩ ማለት አይደለም። ሆኖም አምላክ ‘ዘሩን’ አስመልክቶ በሰጠው የተስፋ ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው ስላሳዩና የአምላክን ትእዛዛት ለመጠበቅ ጥረት ስላደረጉ ከቀረው የሰው ዘር ዓለም በተለየ ጻድቅ እንደሆኑና በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም እንዳላቸው ተደርገው ሊቆጠሩ ችለዋል። (ዘፍ 3:15፤ መዝ 119:2, 3) አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ከእሱ ከራቀው የሰው ዘር ጋር በማነጻጸር ምንም በደል እንደሌለባቸው አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (መዝ 32:1, 2፤ ኤፌ 2:12) እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም ጠንካራ እምነት በማሳየታቸው አምላክ ፍጹም የሆነውን የጽድቅ መሥፈርቱን መጣስ ሳያስፈልገው ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረትና እነሱን መባረክ ችሏል። (መዝ 36:10) ያም ሆኖ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ከኃጢአት መዋጀት እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበው ነበር፤ ደግሞም አምላክ ይህን የሚያደርግበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።—መዝ 49:7-9፤ ዕብ 9:26
ከመጋቢት 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 24
“ለይስሐቅ የምትሆን ሚስት”
(ዘፍጥረት 24:2-4) አብርሃም ንብረቱን በሙሉ የሚያስተዳድርለትንና በቤቱ ውስጥ ካሉት አገልጋዮች ሁሉ አንጋፋ የሆነውን አገልጋዩን እንዲህ አለው፦ “እባክህ እጅህን ከጭኔ ሥር አድርግ፤ 3 በመካከላቸው ከምኖረው ከከነአናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳታመጣለት የሰማይና የምድር አምላክ በሆነው በይሖዋ አስምልሃለሁ። 4 ከዚህ ይልቅ ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት አምጣለት።”
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
አብርሃም በከነአን ከሚኖሩ ሴቶች መካከል ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዳይመርጥ ኤልዔዘርን በመሐላ ቃል አስገብቶታል። ለምን? ምክንያቱም ከነአናውያን ለይሖዋ አምላክ አክብሮት የላቸውም፤ እሱንም አያመልኩም። ይሖዋ፣ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሚፈጽሙት ክፉ ድርጊት የተነሳ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እነሱን የመቅጣት ዓላማ አለው፤ አብርሃም ደግሞ ይህን ያውቃል። አብርሃም የሚወደው ልጁ ይስሐቅ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ቁርኝት እንዲፈጥርም ሆነ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አኗኗራቸውን እንዲከተል አልፈለገም። ከዚህም በተጨማሪ፣ አምላክ ተስፋ ከሰጣቸው ነገሮች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ይስሐቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተገንዝቧል።—ዘፍጥረት 15:16፤ 17:19፤ 24:2-4
(ዘፍጥረት 24:11-15) ከከተማዋ ውጭ ባለ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብም ግመሎቹን አንበረከከ። ጊዜውም ወደ ማምሻው አካባቢ ነበር፤ ይህ ጊዜ ደግሞ ሴቶች ውኃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነው። 12 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይሖዋ፣ እባክህ በዚህ ዕለት ጉዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃምም ታማኝ ፍቅርህን አሳየው። 13 ይኸው እኔ እዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሴቶች ልጆች ውኃ ለመቅዳት እየመጡ ነው። 14 እንግዲህ ‘እባክሽ፣ ውኃ እንድጠጣ እንስራሽን አውርጂልኝ’ ስላት ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ የምትለኝ ወጣት ለአገልጋይህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ እንዲህ ካደረግክልኝ ለጌታዬ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኸው አውቃለሁ።” 15 እሱም ገና ንግግሩን ሳይጨርስ የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ባቱኤል የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ሚልካ የወለደችው ነው።
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
ኤልዔዘር፣ በእንግድነት ለተቀበሉት ሰዎች ካራን አቅራቢያ ያለው የውኃው ጉድጓድ ጋ ሲደርስ ለይሖዋ አምላክ መጸለዩን ነገራቸው። ይህም ይስሐቅ የሚያገባትን ወጣት ይሖዋ እንዲመርጥ የጠየቀ ያህል ነበር። እንዴት? ኤልዔዘር፣ አምላክ የይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የሚፈልጋት ወጣት ወደ ውኃው ጉድጓድ እንድትመጣ ጠየቀ። ውኃ አጠጪኝ ሲላት ኤልዔዘርን ብቻ ሳይሆን ግመሎቹንም ጭምር ውኃ ለማጠጣት ፈቃደኛ ልትሆን ይገባል። (ዘፍጥረት 24:12-14) ታዲያ ወደዚያ መጥታ ልክ እንደጠየቀው ያደረገችው ማን ናት? ርብቃ ነች! ኤልዔዘር ለቤተሰቧ ሁኔታውን ሲተርክ ወሬው ወደ ጆሮዋ ጥልቅ ቢል ምን ሊሰማት እንደሚችል ገምት!
(ዘፍጥረት 24:58) ርብቃን ጠርተውም “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽ?” አሏት። እሷም “አዎ፣ እሄዳለሁ” አለች።
(ዘፍጥረት 24:67) ከዚያም ይስሐቅ ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ። በዚህ መንገድ ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት፤ እሱም ወደዳት፤ ከእናቱም ሞት ተጽናና።
wp16.3 14 አን. 6-7
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ኤልዔዘር “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ?” በማለት ለአብርሃም ይህንኑ ጉዳይ አንስቶለት ነበር። በዚህ ጊዜ አብርሃም “እንዲህ ካደረግክ ከመሐላህ ነፃ ትሆናለህ” የሚል መልስ ሰጠው። (ዘፍጥረት 24:39, 41) በባቱኤልም ቤት ቢሆን የልጅቷ ምርጫ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኤልዔዘር ተልዕኮው በመሳካቱ እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ በማግስቱ ርብቃን ይዞ ወዲያውኑ ወደ ከነአን መመለስ ይችል እንደሆነ ጠየቃቸው። ቤተሰቦቿ ግን ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለአሥር ቀናት ከእነሱ ጋር እንድትቆይ ፈልገው ነበር። በመጨረሻም “ልጅቷን እንጥራና እንጠይቃት” በማለት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ተስማሙ።—ዘፍጥረት 24:57
ርብቃ በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ውሳኔ የምታደርግበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። መልሷ ምን ይሆን? አባቷና ወንድሟ ማዘናቸውን ሰበብ በማድረግ ወደማታውቀው አገር መሄዱ እንዲቀርባት ትማጸናቸው ይሆን? ወይስ ይሖዋ እያሳካው እንደሆነ በግልጽ በሚታየው ክንውን ውስጥ ድርሻ ያላት መሆኑን እንደ መብት ትቆጥረዋለች? ለቀረበላት ጥያቄ የሰጠችው መልስ በሕይወቷ ውስጥ ስላጋጠማት ስለዚህ ድንገተኛ፣ ምናልባትም አስደንጋጭ የሆነ ለውጥ ምን እንደተሰማት ያሳያል። ምንም ሳታቅማማ “አዎ፣ እሄዳለሁ” አለች።—ዘፍጥረት 24:58
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 24:19, 20) ለእሱ ሰጥታው ከጠጣ በኋላ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውኃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው። 20 በእንስራዋ ውስጥ የነበረውን ውኃም በፍጥነት ገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ ከዚያም በሩጫ እየተመላለሰች ከጉድጓዱ ውኃ ትቀዳ ጀመር፤ ለግመሎቹም ሁሉ ቀዳች።
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
አንድ ቀን አመሻሹ ላይ እንስራዋን ውኃ ከሞላች በኋላ አንድ አረጋዊ ወደ እሷ እየሮጠ መጥቶ “እባክሽ ከእንስራሽ ውኃ ልጎንጭ” አላት። ሰውየው ቀላል ነገር ነው የጠየቃት፤ ያውም በአክብሮት! ርብቃ፣ ሰውየው ብዙ መንገድ ተጉዞ እንደመጣ መረዳት ችላለች። በመሆኑም እንስራዋን በፍጥነት ከትከሻዋ ላይ አውርዳ እንዲያው ፉት እንዲል ሳይሆን እስኪረካ ድረስ የሚጠጣው ቀዝቀዝ ያለ ንጹሕ ውኃ ሰጠችው። እዚያው አካባቢ በርከክ ያሉ አሥር ግመሎች እንዳሉት ሆኖም እነሱ የሚጠጡት ውኃ ገንዳው ውስጥ አለመሞላቱን አየች። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ዓይኖቹ በትኩረት እንደሚከታተሏት ገብቷታል፤ በመሆኑም አቅሟ በሚፈቅደው መጠን ሰውየውን ልትረዳው ፈልጋለች። ከዚያም “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውኃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው።—ዘፍጥረት 24:17-19
ርብቃ ለአሥሩ ግመሎች ውኃ ለመስጠት ሐሳብ ያቀረበችው ጠጥተው እስኪረኩ ድረስ እንጂ እንዲቃመሱ ያህል ብቻ አለመሆኑን ልብ በል። ውኃ የጠማው አንድ ግመል ከ95 ሊትር በላይ ውኃ ሊጠጣ ይችላል! አሥሩም ግመሎች በጣም ጠምቷቸው ከነበረ ርብቃ ብዙ ሰዓት የሚፈጅ አድካሚ ሥራ ይጠብቃታል ማለት ነው። የተፈጸመውን ሁኔታ ስናስብ ግመሎቹ በጣም ተጠምተው ነበር ለማለት አያስደፍርም። ይሁንና ርብቃ ግመሎቹን ለማጠጣት ሐሳብ ስታቀርብ ይህን ታውቅ ነበር? በጭራሽ። ለአካባቢው ባይተዋር ለሆነው ለዚህ አረጋዊ ሰው፣ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት ስትል ጉልበቷን ሳትቆጥብ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኝነቱም ሆነ ጉጉቱ ነበራት። እሱም በሐሳቧ ተስማማ። ከዚያም እንስራዋን ለመሙላት እየተመላለሰች ገንዳው ውስጥ ውኃ ደጋግማ ስትገለብጥ በመገረም ይመለከታት ነበር።—ዘፍጥረት 24:20, 21
wp16.3 13 ግርጌ
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
ርብቃ ውኃ ልትቀዳ የሄደችው አመሻሽ ላይ ነበር። ዘገባው የውኃው ጉድጓድ ጋ ብዙ ሰዓት እንዳሳለፈች ምንም ፍንጭ አይሰጥም። በተጨማሪም ሥራውን ጨርሳ ስትመጣ ቤተሰቦቿ ተኝተው እንደጠበቋት ወይም የተላከችበትን ጉዳይ ለመፈጸም በጣም በመዘግየቷ እሷን ፍለጋ የመጣ ሰው መኖሩን አይጠቁምም።
(ዘፍጥረት 24:65) አገልጋዩንም “ከእኛ ጋር ለመገናኘት ሜዳውን አቋርጦ የሚመጣው ያ ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም “ጌታዬ ነው” አላት። በመሆኑም ዓይነ ርግቧን ወስዳ ራሷን ሸፈነች።
“አዎ፣ እሄዳለሁ”
በመጨረሻ፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የጠቀስነው ቀን ደረሰ። በሰልፍ የሚሄዱት ግመሎች ኔጌብን እያቋረጡ ባሉበትና ጀንበሯ መጥለቅ በጀመረችበት ሰዓት ርብቃ አንድ ሰው መስኩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ አየች። ሰውየው የሆነ ነገር እያሰላሰለ ያለ ይመስላል። ዘገባው “ከግመሉ ላይ በፍጥነት ወረደች” ይላል፤ ምናልባትም ግመሉ በርከክ እስኪል ደረስ አልጠበቀች ይሆናል፤ ከዚያም ወደዚህ አገር ያመጣትን ሰው “ከእኛ ጋር ለመገናኘት ሜዳውን አቋርጦ የሚመጣው ያ ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። ግለሰቡ ይስሐቅ መሆኑን ስታውቅ ፊቷን ሸፈነች። (ዘፍጥረት 24:62-65) ለምን? እንዲህ ማድረጓ ወደፊት ባሏ ለሚሆነው ሰው ያላትን አክብሮት የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ተገዢነት ጊዜ ያለፈበት ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ወንዶችም ሆንን ሴቶች ርብቃ ካሳየችው ትሕትና ትምህርት መቅሰም እንችላለን፤ ምክንያቱም ከእኛ መካከል ይህ ግሩም ባሕርይ የስብዕናው ክፍል እንዲሆን የማይፈልግ ማን አለ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከመጋቢት 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 25–26
“ኤሳው የብኩርና መብቱን ሸጠ”
(ዘፍጥረት 25:27, 28) ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ ኤሳው ውጭ መዋል የሚወድ የተዋጣለት አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን አብዛኛውን ጊዜውን በድንኳን የሚያሳልፍ ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር። 28 ይስሐቅ ኤሳውን ይወደው ነበር፤ ምክንያቱም እያደነ ያበላው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።
it-1 1242
ያዕቆብ
በአባቱ ዘንድ ተወዳጅ ከነበረው እንዲሁም አንድ ቦታ አርፎ የማይቀመጥ፣ ቀዥቃዣና ከቦታ ቦታ የሚንከራተት አዳኝ ከሆነው ከኤሳው በተቃራኒ ያዕቆብ የተረጋጋ ሕይወት የሚመራና “ጊዜውን በድንኳን የሚያሳልፍ ነቀፋ የሌለበት [በዕብራይስጥ ታም]” ሰው እንደሆነ ተገልጿል፤ ያዕቆብ የቤት ውስጥ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ እምነት የሚጣልበት ሲሆን በተለይ በእናቱ ዘንድ ተወዳጅ ነበር። (ዘፍ 25:27, 28) ታም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በሌሎች ቦታዎች ላይ፣ በአምላክ ዘንድ ሞገስ ያገኙ ሰዎችን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ደም የተጠሙ ሰዎች ነቀፋ የሌለበትን ሰው ሁሉ” እንደሚጠሉ ይሖዋ ግን “[ነቀፋ የሌለበት] ሰው የወደፊት ሕይወት ሰላማዊ ይሆናል” የሚል ዋስትና እንደሰጠ ይገልጻል። (ምሳሌ 29:10 ግርጌ፤ መዝ 37:37) በተጨማሪም ንጹሕ አቋም ጠባቂ መሆኑን ያስመሠከረው ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው” እንደሆነ ይናገራል።—ኢዮብ 1:1, 8 ግርጌ፤ 2:3 ግርጌ
(ዘፍጥረት 25:29, 30) አንድ ቀን ኤሳው ውጭ ውሎ በጣም ደክሞት ሲመጣ ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ነበር። 30 በመሆኑም ኤሳው ያዕቆብን “ቶሎ በል እባክህ፣ በጣም ስለደከመኝ ከዚያ ከቀዩ ወጥ የተወሰነ ስጠኝ!” አለው። ስሙ ኤዶም የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው።
(ዘፍጥረት 25:31-34) በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን ሽጥልኝ!” አለው። 32 ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው። 33 ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት። 34 ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።
አድናቆታችንን መግለጽ ያለብን ለምንድን ነው?
11 የሚያሳዝነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች አድናቆት እንደሌላቸው አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤሳው ይሖዋን በሚወድና በሚያከብር ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ቢሆንም ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት አልነበረውም። (ዕብራውያን 12:16ን አንብብ።) ኤሳው አመስጋኝ እንዳልሆነ ያሳየው እንዴት ነው? አንድ ጊዜ ለሚበላው ቀይ ወጥ ሲል የብኩርና መብቱን ለታናሽ ወንድሙ ለያዕቆብ ሸጧል። (ዘፍ. 25:30-34) በኋላ ላይ ኤሳው በውሳኔው በጣም ተጸጽቷል። ሆኖም ለነበረው ነገር አድናቆት እንደሌለው ስላሳየ ‘የብኩርና መብቴ ተወሰደብኝ’ ብሎ ማማረር አይችልም ነበር።
it-1 835
የበኩር ልጅ፣ በኩር
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የበኩር ልጅ በቤተሰቡ ውስጥ የተከበረ ቦታ የነበረው ሲሆን ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነት የሚረከበው እሱ ነበር። ከአባቱ ንብረት ላይ ሁለት እጥፍ ውርስ ያገኝ ነበር። (ዘዳ 21:17) የዮሴፍ ወንድሞች ከዮሴፍ ጋር በማዕድ በተቀመጡ ጊዜ ሮቤል እንደ ብኩርና መብቱ ቀዳሚውን ቦታ አግኝቷል። (ዘፍ 43:33) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን በተወለዱበት ቅደም ተከተል በመዘርዘር በኩር የሆነውን ልጅ መጀመሪያ ላይ የማይጠቅስበት ጊዜ አለ። በአብዛኛው መጀመሪያ ላይ የሚጠቀሰው ይበልጥ የሚታወቀው ወይም ታማኝ የሆነው ልጅ ነው።—ዘፍ 6:10፤ 1ዜና 1:28፤ ከዘፍ 11:26, 32 እና 12:4 ጋር አወዳድር፤ የብኩርና መብት፤ ውርስ የሚለውን ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 25:31-34) በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን ሽጥልኝ!” አለው። 32 ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው። 33 ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት። 34 ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።
(ዕብራውያን 12:16) በተጨማሪም በመካከላችሁ ሴሰኛ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አሁን ደግሞ ዕብራውያን 12:16ን መለስ ብለን እንመልከት፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በመካከላችሁ ሴሰኛ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።” እዚህ ጥቅስ ላይ ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ ስለተካተቱ ሰዎች አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖችን “ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ [እንዲጓዙ]” እየመከራቸው ነበር። እንዲህ ካደረጉ ‘የአምላክን ጸጋ አያጡም’፤ በተቃራኒው ግን የፆታ ብልግና ከፈጸሙ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊደርስባቸው ይችላል። (ዕብ. 12:12-16) ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ ኤሳው ሆኑ ማለት ነው። ኤሳው ‘ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት ሳያሳይ’ የቀረ ሲሆን ቃል በቃል ሥጋዊ ሰው ሆኗል።
ኤሳው የኖረው በጥንት ዘመን ስለሆነ ምናልባትም ቤተሰቡን ወክሎ አልፎ አልፎ መሥዋዕት የማቅረብ መብት ሳያገኝ አልቀረም። (ዘፍ. 8:20, 21፤ 12:7, 8፤ ኢዮብ 1:4, 5) ይሁን እንጂ ኤሳው ሥጋዊ አመለካከት የነበረው ሰው በመሆኑ፣ ብኩርናው የሚያስገኝለትን መብቶች በሙሉ በምስር ወጥ ለውጧል። ምናልባትም በአብርሃም ዘሮች ላይ እንደሚመጣ በትንቢት የተነገረው መከራ እንዳይደርስበት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 15:13) በተጨማሪም ኤሳው ሁለት አረማዊ ሴቶችን ማግባቱ ሥጋዊ ሰው ማለትም ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት የሌለው ሰው መሆኑን ያሳያል፤ ኤሳው ያደረገው ውሳኔ ወላጆቹንም ቢሆን አሳዝኗል። (ዘፍ. 26:34, 35) በእርግጥም ኤሳው፣ እውነተኛውን አምላክ የምታመልክ ሴት ለማግባት ጥረት ካደረገው ከያዕቆብ ምንኛ የተለየ ነበር!—ዘፍ. 28:6, 7፤ 29:10-12, 18
(ዘፍጥረት 26:7) የዚያ አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት “እህቴ ናት” ይላቸው ነበር። “የዚህ አገር ሰዎች በርብቃ የተነሳ ሊገድሉኝ ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ “ሚስቴ ናት” ለማለት ፈርቶ ነበር፤ ምክንያቱም ርብቃ ቆንጆ ነበረች።
it-2 245 አን. 6
ውሸት
በተንኮል ተነሳስቶ የሚነገር ውሸት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ይህ ሲባል ግን ለማይመለከታቸው ሰዎች እውነቱን የመናገር ግዴታ አለብን ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ። አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።” (ማቴ 7:6) እሱ ራሱም ቢሆን ሳያስፈልግ ለችግር ሊዳርጉ የሚችሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡለት ሙሉ መረጃ ወይም ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት የተቆጠበው ለዚህ ነበር። (ማቴ 15:1-6፤ 21:23-27፤ ዮሐ 7:3-10) በተመሳሳይም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ረዓብና ኤልሳዕ ይሖዋን ለማያመልኩ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸው ወይም ሙሉ በሙሉ እውነቱን ላለመናገር መወሰናቸው ከዚህ አንጻር ሊታይ ይገባል።—ዘፍ 12:10-19፤ ምዕ 20፤ 26:1-10፤ ኢያሱ 2:1-6፤ ያዕ 2:25፤ 2ነገ 6:11-23
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከመጋቢት 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 27–28
“ያዕቆብ የሚገባውን በረከት አገኘ”
(ዘፍጥረት 27:6-10) ርብቃም ልጇን ያዕቆብን እንዲህ አለችው፦ “አባትህ ወንድምህን ኤሳውን እንዲህ ሲለው ሰምቻለሁ፦ 7 ‘እስቲ አደን አድነህ አምጣልኝና ጣፋጭ ምግብ ሥራልኝ። እኔም ሳልሞት በይሖዋ ፊት እንድባርክህ ልብላ።’ 8 እንግዲህ ልጄ፣ አሁን የምልህን በጥሞና አዳምጥ፤ የማዝህንም አድርግ። 9 አባትህ የሚወደው ዓይነት ጣፋጭ ምግብ እንዳዘጋጅለት እባክህ ወደ መንጋው ሂድና ፍርጥም ያሉ ሁለት የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ። 10 ከዚያም ከመሞቱ በፊት እንዲባርክህ ምግቡን ለአባትህ ታቀርብለትና ይበላል።”
ርብቃ—ፈሪሃ አምላክ ያላት የተግባር ሴት
ዔሳው ለያዕቆብ መገዛት እንዳለበት ይስሐቅ ያውቅ እንደሆነና እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። የሆነ ሆኖ ርብቃም ሆነች ያዕቆብ በረከቱ የሚገባው ለእርሱ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ይስሐቅ እንስሳ አድኖ ምግብ ሠርቶ ካመጣለት እንደሚባርከው ለዔሳው ሲነግረው ርብቃ ስትሰማ ጊዜ ሳታጠፋ አንድ ነገር ለማድረግ ተነሳች። ከወጣትነቷ ጀምሮ የምትታወቅበት ቆራጥነትና ቅንዓት አሁንም አልተለያትም ነበር። ያዕቆብን ሁለት የፍየል ጠቦቶች እንዲያመጣላት ‘አዘዘችው’ [የ1954 ትርጉም]። ባሏ የሚወደውን ምግብ ልታዘጋጅለትና ያዕቆብ በረከቱን ለማግኘት ዔሳውን መስሎ ወደ ይስሐቅ እንዲገባ አስባ ነበር። ያዕቆብ ሐሳቧን ተቃወመ። አባቱ እንዳታለሉት ሲያውቅ እንዳይረግመው ፈርቶ ነበር። ቢሆንም ርብቃ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም” በማለት አደፋፈረችው። ከዚያም ምግቡን አዘጋጀችና ያዕቆብን ከዔሳው ጋር አመሳስላ ወደ ባሏ ላከችው።—ዘፍጥረት 27:1-17
ርብቃ እንደዚህ ያደረገችው ለምን እንደሆነ በታሪኩ ላይ አልተጠቀሰም። ብዙዎች በዚህ ድርጊቷ ይኮንኗታል። ሆኖም ይህ ተግባሯ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተወገዘ ከመሆኑም በላይ ይስሐቅም በረከቱን የወሰደው ያዕቆብ መሆኑን ሲያውቅ አልኮነናትም። እንዲያውም ያዕቆብን ጨምሮ ባርኮታል። (ዘፍጥረት 27:29፤ 28:3, 4) ርብቃ ይሖዋ ልጆቿን አስመልክቶ የተናገረውን ታውቃለች። ስለሆነም እንዲህ ያደረገችው ያዕቆብ ለእርሱ የሚገባውን በረከት እንዲያገኝ ብላ ነበር። ይህም ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንደሆነ አያጠራጥርም።—ሮሜ 9:6-13
(ዘፍጥረት 27:18, 19) እሱም ወደ አባቱ ገብቶ “አባቴ ሆይ!” አለው። እሱም መልሶ “አቤት! ለመሆኑ አንተ ማነህ ልጄ?” አለው። 19 ያዕቆብም አባቱን “እኔ የበኩር ልጅህ ኤሳው ነኝ። ልክ እንዳልከኝ አድርጌአለሁ። እንድትባርከኝ እባክህ ቀና ብለህ ተቀመጥና አድኜ ካመጣሁት ብላ” አለው።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ የተከሰተው በድንገት እንደሆነ ቢገልጽም ርብቃና ያዕቆብ እንዲህ ያደረጉበትን ምክንያት በዝርዝር አይነግረንም። የአምላክ ቃል ርብቃና ያዕቆብ ያደረጉትን ነገር የሚደግፍም ሆነ የሚያወግዝ ሐሳብ አልያዘም፤ በመሆኑም ይህ ዘገባ ለውሸትና ለማጭበርበር ሰበብ አይሆንም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁኔታው የበለጠ ለማወቅ የሚያስችለን ሐሳብ ይዟል።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዘገባው የአባቱን ምርቃት የማግኘት መብት የነበረው ያዕቆብ እንጂ ዔሳው እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ያዕቆብ፣ ለመብቱ አድናቆት ካልነበረው መንትያ ወንድሙ ብኩርናውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ገዝቶት ነበር፤ ዔሳው ረሃቡን ለማስታገስ ሲል ብኩርናውን በምግብ በመሸጡ ‘ብኩርናውን አቃሎታል።’ (ዘፍጥረት 25:29-34) በመሆኑም ያዕቆብ የአባቱን ምርቃት ለመቀበል ባለመብት ነበር።
(ዘፍጥረት 27:27-29) ስለዚህ ወደ እሱ ቀረበና ሳመው፤ ይስሐቅም የልጁን ልብስ ጠረን አሸተተ። ከዚያም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦ “አቤት፣ የልጄ ጠረን ይሖዋ እንደባረከው መስክ መዓዛ ነው። 28 እውነተኛው አምላክ የሰማያትን ጠል፣ የምድርን ለም አፈር እንዲሁም የተትረፈረፈ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ ይስጥህ። 29 ሕዝቦች ያገልግሉህ፤ ብሔራትም ይስገዱልህ። የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤ የእናትህም ወንዶች ልጆች ይስገዱልህ። የሚረግሙህ ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚባርኩህም ሁሉ የተባረኩ ይሁኑ።”
it-1 341 አን. 6
በረከት
በጥንት ዘመን በነበረው በቤተሰብ ራሶች የሚመራ ማኅበረሰብ ውስጥ አባቶች በአብዛኛው መሞቻቸው ሲቃረብ ልጆቻቸውን የመባረክ ልማድ ነበራቸው። ይህ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠርና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። በዚህ ልማድ መሠረት ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የበኩር ልጁ ኤሳው ስለመሰለው የባረከው ሲሆን ከወንድሙ ከኤሳው የበለጠ ሞገስና ብልጽግና እንዲያገኝ መርቆታል። ይስሐቅ በዚህ ወቅት ዓይኑ ታውሮና ዕድሜው ገፍቶ ስለነበር በበረከቱ ላይ የጠቀሳቸውን ነገሮች እንዲፈጽምለት ይሖዋን ተማጽኖ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍ 27:1-4, 23-29፤ 28:1, 6፤ ዕብ 11:20፤ 12:16, 17) ከጊዜ በኋላ ይስሐቅ የያዕቆብን ትክክለኛ ማንነት እያወቀም በበረከቱ ላይ የጠቀሳቸውን ነገሮች ድጋሚ የተናገረ ከመሆኑም በላይ ከበረከቱ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ መረጃዎችን ሰጥቷል። (ዘፍ 28:1-4) ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት በመጀመሪያ ሁለቱን የዮሴፍ ወንድ ልጆች በኋላም የራሱን ወንዶች ልጆች ባርኳል። (ዘፍ 48:9, 20፤ 49:1-28፤ ዕብ 11:21) ሙሴም ከመሞቱ በፊት መላውን የእስራኤል ብሔር ባርኳል። (ዘዳ 33:1) ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ሁሉ ላይ እንደታየው በረከቶቹ በሙሉ ትንቢታዊ ይዘት ነበራቸው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች፣ እየባረከ ያለው ሰው እየተባረከ ባለው ሰው ራስ ላይ እጁን ይጭን ነበር።—ዘፍ 48:13, 14
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 27:46–28:2) ከዚያ በኋላ ርብቃ ይስሐቅን እንዲህ ትለው ጀመር፦ “በሄት ሴቶች ልጆች የተነሳ ሕይወቴን ጠልቻለሁ። ያዕቆብም በዚህ አገር የሚገኙትን እንደነዚህ ያሉትን የሄት ሴቶች ልጆች የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለእኔ ምን ያደርግልኛል?”
28 በመሆኑም ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ ባረከውና እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ። 2 በጳዳንአራም ወደሚገኘው ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድና ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዷን አግባ።
ከትዳር ጓደኛህ ጋር በግልጽ ለመነጋገር የሚረዱ ነጥቦች
ታዲያ ይስሐቅና ርብቃ በግልጽ የመነጋገር ልማድ ነበራቸው? ዔሳው የተባለው ልጃቸው ኬጢያውያን የሆኑ ሁለት ሴቶችን ካገባ በኋላ በቤተሰቡ ውስጥ ከባድ ችግር ተከሰተ። ርብቃ ይስሐቅን “‘ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም [ታናሹ ልጃቸው] . . . ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ’ አለችው።” (ዘፍጥረት 26:34፤ 27:46) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ርብቃ የሚያሳስባትን ሁሉ አንድም ሳይቀር በግልጽ ነግራዋለች።
ይስሐቅ የዔሳው መንትያ ለሆነው ለያዕቆብ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳያገባ ነገረው። (ዘፍጥረት 28:1, 2) ርብቃ መልእክቷን አስተላልፋለች። እነዚህ ባልና ሚስት አሳሳቢ ስለነበረው የቤተሰብ ጉዳይ በግልጽ በመነጋገር ረገድ በዛሬ ጊዜ ላለነው ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛሞች በአንድ ጉዳይ ላይ ባይስማሙ ምን ማድረግ ይችላሉ?
(ዘፍጥረት 28:12, 13) እሱም ሕልም አለመ፤ በሕልሙም በምድር ላይ የተተከለ ደረጃ አየ፤ የደረጃውም ጫፍ እስከ ሰማያት ይደርስ ነበር፤ በላዩም ላይ የአምላክ መላእክት ይወጡና ይወርዱ ነበር። 13 ከደረጃውም በላይ ይሖዋ ነበር፤ እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክና የይስሐቅ አምላክ ይሖዋ ነኝ። የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
28:12, 13—ያዕቆብ ስለ “መሰላል” የተመለከተው ሕልም ትርጉሙ ምንድን ነው? በድንጋይ ከተሠራ ደረጃ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው ይህ “መሰላል” በምድርና በሰማይ መካከል የሐሳብ ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል። የአምላክ መላእክት በመሰላሉ ላይ ይወጡና ይወርዱ የነበረ መሆኑ መላእክት በይሖዋና ሞገሱን በሚያገኙ ሰዎች መካከል አንዳንድ ጠቃሚ አገልግሎቶችን እንደሚያከናውኑ ያሳያል።—ዮሐንስ 1:51
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከመጋቢት 30–ሚያዝያ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 29–30
“ያዕቆብ ሚስት አገባ”
(ዘፍጥረት 29:18-20) ያዕቆብ ራሔልን ይወዳት ስለነበር “ለታናሿ ልጅህ ለራሔል ስል ሰባት ዓመት ላገለግልህ ፈቃደኛ ነኝ” አለው። 19 ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20 ያዕቆብም ለራሔል ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ይሁንና ራሔልን ይወዳት ስለነበር ሰባቱ ዓመታት ለእሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበሩ።
ያዕቆብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት ነበረው
አንድ ወንድ ሚስት ሲያጭ ለሙሽሪቷ ቤተሰብ ጥሎሽ መስጠት ይጠበቅበት ነበር። ከጊዜ በኋላ የወጣው የሙሴ ሕግ ድንግል ልጃገረድን አባብሎ የደረሰባት ሰው 50 የብር ሰቅል ለአባቷ እንዲከፍል ይደነግግ ነበር። ጎርደን ዌንሃም የተባሉ ምሑር ይህ ገንዘብ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሎሽ” እንደነበረና አብዛኞቹ የጥሎሽ ክፍያዎች ግን “ከዚህ በጣም አነስተኛ” እንደነበሩ ያምናሉ። (ዘዳግም 22:28, 29) ያዕቆብ ገንዘብ መክፈል አይችልም ነበር። ስለዚህ ለላባ ያቀረበው ክፍያ የሰባት ዓመት አገልግሎት ነበር። ጎርደን ዌንሃም አክለው “በጥንት ባቢሎናውያን ዘመን ተራ ሠራተኞች በወር የሚከፈላቸው ደመወዝ ከግማሽ እስከ አንድ ሰቅል ብር ስለነበር (በሰባት ዓመት ውስጥ ከ42 እስከ 84 ሰቅል ማለት ነው) ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ለላባ ያቀረበለት ጥሎሽ ከፍተኛ ነበር” ብለዋል። ላባም ሐሳቡን የተቀበለው ሳያንገራግር ነበር።—ዘፍጥረት 29:19
(ዘፍጥረት 29:21-26) ከዚያም ያዕቆብ ላባን “እንግዲህ የተባባልነው ጊዜ ስላበቃ ሚስቴን ስጠኝ፤ ከእሷም ጋር ልተኛ” አለው። 22 ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠራ፤ ግብዣም አደረገ። 23 ሆኖም ሲመሽ ላባ ልጁን ሊያን ወስዶ ከእሷ ጋር እንዲተኛ ለያዕቆብ ሰጠው። 24 በተጨማሪም ላባ የእሱ አገልጋይ የሆነችውን ዚልጳን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለሊያ ሰጣት። 25 በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ሊያ መሆኗን አወቀ! በመሆኑም ያዕቆብ ላባን “ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ለራሔል ስል አልነበረም? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?” አለው። 26 ላባም እንዲህ አለው፦ “በአካባቢያችን በኩሯ እያለች ታናሺቱን መዳር የተለመደ አይደለም።
‘የእስራኤልን ቤት የሠሩት’ እህትማማቾች ጭንቀት
ልያ ያዕቆብን ለማታለል አስባ ነበር? ወይስ ይህን ያደረገችው አባቷን መታዘዝ ግድ ሆኖባት ነው? በዚህ ጊዜ ራሔል የት ነበረች? ምን እየተደረገ እንዳለ ታውቅ ነበር? ከሆነስ ምን ተሰምቷት ይሆን? ግትር የሆነው አባቷ የሰጣትን ትእዛዝ መጣስ ትችል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የለም። ራሔልና ልያ ስለ ጉዳዩ የነበራቸው ስሜት ምንም ይሁን ምን ይህ የተንኮል ድርጊት ያዕቆብን በጣም አናዶታል። ያዕቆብ በጉዳዩ አለመስማማቱን የገለጸው ለላባ እንጂ ለልጆቹ አልነበረም፤ “ያገለገልኹህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። ላባ ምን ምላሽ ሰጠ? “ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና፣ ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን” አለው። (ዘፍጥረት 29:25-27) ላባ፣ በዚህ መንገድ ያዕቆብን በማታለል ሁለት ሴቶች እንዲያገባ ያደረገው ሲሆን ይህም ከፍተኛ ቅናት አስከትሏል።
it-2 341 አን. 3
ጋብቻ
አከባበር። በእስራኤል ውስጥ መደበኛ የሆነ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ባይኖርም ጋብቻ በጣም አስደሳች በሆነ መንገድ ይከበር ነበር። በሠርጉ ቀን ሙሽራዋ በራሷ ቤት የምታከናውናቸው ሰፊ ዝግጅቶች አሉ። በመጀመሪያ ገላዋን ታጥባ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ትቀባለች። (ከሩት 3:3 እና ከሕዝ 23:40 ጋር አወዳድር) አንዳንድ ጊዜ በሴት አገልጋዮቿ እየታገዘች ጌጠኛ መቀነቷን ትታጠቃለች፤ እንዲሁም ነጭ ልብሷን ትለብሳለች። የገንዘብ አቅሟ በሚፈቅደው መጠን በመቀነቷና በልብሷ ላይ የሚያምር ጥልፍ ይጠለፍበታል። (ኤር 2:32፤ ራእይ 19:7, 8፤ መዝ 45:13, 14) እንደ አቅሟ በተለያዩ ጌጣጌጦች ትዋባለች (ኢሳ 49:18፤ 61:10፤ ራእይ 21:2)፤ ከዚያም ከራሷ አንስቶ እስከ እግሯ ድረስ በሚደርስ ስስ ጨርቅ ትሸፈናለች። (ኢሳ 3:19, 23) ላባ ያዕቆብን በቀላሉ ሊያታልለው የቻለውና ያዕቆብ፣ ላባ የሰጠው ራሔልን ሳይሆን ሊያን እንደሆነ ያላወቀው በዚህ ምክንያት ነው። (ዘፍ 29:23, 25) ርብቃ ይስሐቅን ለማግኘት ስትቃረብ ፊቷን በዓይነ ርግብ ሸፍናለች። (ዘፍ 24:65) ይህም ሙሽሪት ለሙሽራው ሥልጣን እንደምትገዛ ያሳያል።—1ቆሮ 11:5, 10
(ዘፍጥረት 29:27, 28) ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸር። ከዚያም ለምታገለግለኝ ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ሌላኛዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።” 28 ያዕቆብም እንደተባለው አደረገ፤ ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸረ። ከዚያም ላባ ልጁን ራሔልን ሚስት እንድትሆነው ሰጠው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 30:3) እሷም በዚህ ጊዜ “ባሪያዬ ባላ ይችውልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም በእሷ አማካኝነት ልጆች እንዳገኝ ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጽም” አለችው።
it-1 50
ማደጎ
ራሔልና ሊያ አገልጋዮቻቸው ከያዕቆብ የወለዷቸውን ልጆች ‘በጉልበቶቻቸው ላይ እንደተወለዱላቸው ልጆች’ ማለትም ልክ እንደ ራሳቸው ልጆች አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። (ዘፍ 30:3-8, 12, 13, 24 ግርጌ) ከያዕቆብ ሕጋዊ ሚስቶች በቀጥታ እንደተወለዱት ልጆች ሁሉ እነዚህ ልጆችም ውርስ ይሰጣቸው ነበር። እነዚህ ልጆች ከአባትየው የተወለዱ ስለሆኑና አገልጋዮቹም የሚስቶቹ ማለትም የራሔልና የሊያ ንብረቶች ስለነበሩ ራሔልና ሊያ እነዚህን ልጆች እንደ ራሳቸው ልጆች አድርገው የመቁጠር መብት ነበራቸው።
(ዘፍጥረት 30:14, 15) የስንዴ መከር በሚሰበሰብበት ወቅት ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ፤ ከሜዳውም ላይ ፍሬ ለቀመ። ለእናቱ ለሊያም አመጣላት። ከዚያም ራሔል ሊያን “እባክሽ፣ ልጅሽ ካመጣው ፍሬ የተወሰነ ስጪኝ” አለቻት። 15 በዚህ ጊዜ ሊያ “ባሌን የወሰድሽብኝ አነሰሽና አሁን ደግሞ ልጄ ያመጣውን ፍሬ መውሰድ ትፈልጊያለሽ?” አለቻት። በመሆኑም ራሔል “እሺ፣ ልጅሽ ባመጣው ፍሬ ፋንታ ዛሬ ማታ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
30:14, 15—ራሔል ከባሏ ጋር በማደር ለመጸነስ የነበራትን አጋጣሚ በእንኮይ የለወጠችው ለምን ነበር? በጥንት ጊዜ እንኮይ ለሥቃይ ማስታገሻነትና ድንገተኛ የጡንቻ መኮማተርን ለመከላከል ወይም ለማስታገስ ተብሎ በመድኃኒትነት ይወሰድ ነበር። በተጨማሪም ይህ ፍሬ የጾታ ፍላጎትን ያነሳሳል እንዲሁም የመጸነስ አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታመን ነበር። (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 7:13) ራሔል ከባልዋ ጋር ለማደር የነበራትን አጋጣሚ በእንኮይ ለመለወጥ የተነሳሳችበትን ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ባይገልጽልንም እንኮዩ እንድትጸንስ አስችሏት በመካንነቷ ከሚደርስባት ነቀፋ ለመገላገል አስባ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ማኅፀንዋን የከፈተላት’ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነበር።—ዘፍጥረት 30:22-24
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ