ዘፍጥረት
30 ራሔል ለያዕቆብ ምንም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእህቷ ቀናች፤ ያዕቆብንም “ልጆች ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” ትለው ጀመር። 2 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ራሔልን በጣም ተቆጥቶ “እኔ፣ እንዳትወልጂ ያደረገሽን* አምላክ መሰልኩሽ እንዴ?” አላት። 3 እሷም በዚህ ጊዜ “ባሪያዬ ባላ+ ይችውልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና* እኔም በእሷ አማካኝነት ልጆች እንዳገኝ ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጽም” አለችው። 4 በዚህ መሠረት አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጸመ።+ 5 ባላም ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 6 ራሔልም “አምላክ ዳኛ ሆነልኝ፤ ቃሌንም ሰማ። በመሆኑም ወንድ ልጅ ሰጠኝ” አለች። በዚህም የተነሳ ስሙን ዳን*+ አለችው። 7 የራሔል አገልጋይ ባላ በድጋሚ ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 8 ራሔልም “ከእህቴ ጋር ብርቱ ትግል ገጠምኩ፤ አሸናፊም ሆንኩ!” አለች። በመሆኑም ስሙን ንፍታሌም*+ አለችው።
9 ሊያ ልጅ መውለድ እንዳቆመች ስትረዳ አገልጋይዋን ዚልጳን ለያዕቆብ ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው።+ 10 የሊያም አገልጋይ ዚልጳ ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 11 ከዚያም ሊያ “ምንኛ መታደል ነው!” አለች። በመሆኑም ስሙን ጋድ*+ አለችው። 12 ከዚያ በኋላ የሊያ አገልጋይ ዚልጳ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 13 ከዚያም ሊያ “ምንኛ ደስተኛ ነኝ! በእርግጥም ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛ ይሉኛል”+ አለች። በመሆኑም ስሙን አሴር*+ አለችው።
14 የስንዴ መከር በሚሰበሰብበት ወቅት ሮቤል+ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ከሜዳውም ላይ ፍሬ* ለቀመ። ለእናቱ ለሊያም አመጣላት። ከዚያም ራሔል ሊያን “እባክሽ፣ ልጅሽ ካመጣው ፍሬ የተወሰነ ስጪኝ” አለቻት። 15 በዚህ ጊዜ ሊያ “ባሌን የወሰድሽብኝ አነሰሽና+ አሁን ደግሞ ልጄ ያመጣውን ፍሬ መውሰድ ትፈልጊያለሽ?” አለቻት። በመሆኑም ራሔል “እሺ፣ ልጅሽ ባመጣው ፍሬ ፋንታ ዛሬ ማታ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።
16 ያዕቆብ የዚያን ቀን ምሽት ከእርሻ ሲመለስ ሊያ ወጥታ ተቀበለችውና “ልጄ ባመጣው ፍሬ ስለተከራየሁህ ዛሬ የምትተኛው ከእኔ ጋር ነው” አለችው። ስለሆነም በዚያ ሌሊት ከእሷ ጋር አደረ። 17 አምላክም ሊያን ሰማት፤ መልስም ሰጣት፤ እሷም ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ አምስተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 18 ሊያም “አገልጋዬን ለባሌ ስለሰጠሁ አምላክ ደሞዜን* ከፈለኝ” አለች። በመሆኑም ስሙን ይሳኮር*+ አለችው። 19 ሊያም በድጋሚ ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ስድስተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት።+ 20 ሊያም “አምላክ አድሎኛል፤ አዎ፣ መልካም ስጦታ ሰጥቶኛል። ለባሌ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለወለድኩለት+ ከእንግዲህ ይታገሠኛል”+ አለች። በመሆኑም ስሙን ዛብሎን*+ አለችው። 21 ከዚያ በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ዲና+ አለቻት።
22 በመጨረሻም አምላክ ራሔልን አሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ መፀነስ እንድትችል በማድረግ* ጸሎቷን መለሰላት።+ 23 እሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ከዚያም “አምላክ ነቀፋዬን አስወገደልኝ!”+ አለች። 24 በመሆኑም “ይሖዋ ሌላ ወንድ ልጅ ጨመረልኝ” በማለት ስሙን ዮሴፍ*+ አለችው።
25 ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ “ወደ ስፍራዬና ወደ ምድሬ እንድመለስ አሰናብተኝ።+ 26 ለእነሱ ስል ያገለገልኩህን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ ምን ያህል እንዳገለገልኩህ በሚገባ ታውቃለህ።”+ 27 ከዚያም ላባ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ይሖዋ እየባረከኝ ያለው በአንተ የተነሳ መሆኑን በንግርት* ተረድቻለሁ” አለው። 28 ከዚያም “ደሞዝህን አሳውቀኝና እሰጥሃለሁ”+ አለው። 29 በመሆኑም ያዕቆብ እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዳገለገልኩህና መንጋህም ምን ያህል እየበዛልህ እንዳለ ታውቃለህ፤+ 30 እኔ ከመምጣቴ በፊት የነበረህ ነገር ጥቂት እንደሆነና እኔ ከመጣሁ በኋላ ግን ከብቶችህ በጣም እየበዙ እንደሄዱ፣ ይሖዋም እንደባረከህ ታውቃለህ። ታዲያ ለራሴ ቤት አንድ ነገር የማደርገው መቼ ነው?”+
31 ከዚያም ላባ “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው። ያዕቆብም እንዲህ አለ፦ “እኔ ምንም ነገር እንድትሰጠኝ አልፈልግም! የምጠይቅህን አንድ ነገር ብቻ የምታደርግልኝ ከሆነ መንጋህን መጠበቄንና መንከባከቤን እቀጥላለሁ።+ 32 ዛሬ በመንጎችህ ሁሉ መካከል እዘዋወራለሁ። አንተም ከመንጋው መካከል ጠቃጠቆ ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን በጎች ሁሉ፣ ከጠቦቶቹም መካከል ጥቁር ቡናማ የሆኑትን በጎች ሁሉ እንዲሁም ዥጉርጉር የሆኑትንና ጠቃጠቆ ያለባቸውን እንስት ፍየሎች ሁሉ ለይ። ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነቶቹ የእኔ ደሞዝ ይሆናሉ።+ 33 ወደፊት ደሞዜን ለመመልከት በምትመጣበት ጊዜ ጽድቄ* ስለ እኔ ይናገራል፤ ከእንስት ፍየሎቹ መካከል ጠቃጠቆ የሌለበትና ዥጉርጉር ያልሆነ እንዲሁም ከጠቦቶቹ መካከል ጥቁር ቡናማ ያልሆነ በእኔ ዘንድ ከተገኘ ያ የተሰረቀ እንደሆነ ይቆጠራል።”
34 በዚህ ጊዜ ላባ “ይሄማ ጥሩ ነው! እንዳልከው ይሁን” አለው።+ 35 ከዚያም በዚያኑ ቀን ሽንትር ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን ተባዕት ፍየሎች ሁሉ፣ ጠቃጠቆ ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን እንስት ፍየሎች ሁሉ፣ ነጭ የሚባል ነገር ያለበትን ሁሉ እንዲሁም ከጠቦቶቹ መካከል ጥቁር ቡናማ የሆኑትን ሁሉ ለየ፤ እነዚህንም ወንዶች ልጆቹ እንዲጠብቋቸው ሰጣቸው። 36 ከዚህ በኋላ በእሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ያህል ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ይጠብቅ ጀመር።
37 ከዚያም ያዕቆብ ከሊብነህ፣* ከአልሞንድና ከአርሞን* ዛፎች ላይ የተቆረጡ እርጥብ በትሮችን ወሰደ፤ በመቀጠልም በትሮቹን አለፍ አለፍ ብሎ በመላጥና ነጩ እንዲታይ በማድረግ ዥጉርጉር እንዲሆኑ አደረገ። 38 ከዚያም የላጣቸውን በትሮች ወስዶ መንጎቹ ውኃ ለመጠጣት ሲመጡ እንዲያዩአቸው በመንጎቹ ፊት ለፊት በቦዮቹ ማለትም ውኃ በሚጠጡባቸው ገንዳዎች ውስጥ አስቀመጣቸው፤ ይህን ያደረገውም መንጎቹ ውኃ ለመጠጣት ሲመጡ በበትሮቹ ፊት ለስሪያ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው።
39 ስለዚህ መንጎቹ በበትሮቹ ፊት ለስሪያ ይነሳሱ ነበር፤ መንጎቹም ሽንትርና ጠቃጠቆ ያለባቸውን እንዲሁም ዥጉርጉር የሆኑ ግልገሎችን ይወልዱ ነበር። 40 ከዚያም ያዕቆብ ጠቦቶቹን ለየ፤ ከዚያም መንጎቹ በላባ መንጎች መካከል ወዳሉት ሽንትር ወዳለባቸውና ጥቁር ቡናማ ወደሆኑት ሁሉ እንዲመለከቱ አደረገ። ከዚያም የራሱን መንጎች ለየ፤ ከላባ መንጎች ጋር አልቀላቀላቸውም። 41 ያዕቆብም ብርቱ የሆኑት እንስሳት ለስሪያ በተነሳሱ ቁጥር በትሮቹን በመንጎቹ ፊት ለፊት ገንዳዎቹ ውስጥ ያስቀምጣቸው ነበር፤ እንዲህ የሚያደርገው መንጎቹ በበትሮቹ አማካኝነት ለስሪያ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነበር። 42 እንስሶቹ ደካማ ሲሆኑ ግን በትሮቹን ገንዳዎቹ ውስጥ አያስቀምጥም ነበር። ስለሆነም ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ ብርቱ ብርቱዎቹ ግን ለያዕቆብ ሆኑ።+
43 በዚህ መንገድ ይህ ሰው እጅግ ባለጸጋ እየሆነ ሄደ፤ የብዙ መንጎች፣ የወንድና የሴት አገልጋዮች፣ የግመሎች እንዲሁም የአህዮች ባለቤት ሆነ።+