የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት መቀበል ማለት የእኛን ፍጹም ታዛዥነት የሚጠይቅ ነገር ነው? በአንድ ወቅት ታማኝ የነበረ ሰው ሁልጊዜም በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል? ለእውነተኛው አምላክ “እንደ ልቡ” የሚሆንለት ምን ዓይነት ሰው ነው? (1 ሳሙኤል 13:14) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጠናል።
ሁለተኛ ሳሙኤልን የጻፉት ጋድና ናታን ሲሆኑ እነዚህ ሁለት ነቢያት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ከነበረው ከዳዊት ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራቸው።a መጽሐፉ ተጽፎ የተጠናቀቀው በ1040 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ይኸውም ለ40 ዓመታት በቆየው የዳዊት የንግሥና ዘመን መገባደጃ አካባቢ ሲሆን በይበልጥ የሚያተኩረውም በዳዊትና እርሱ ከይሖዋ ጋር በነበረው ዝምድና ላይ ነው። አስደሳች የሆነው ይህ ትረካ በጦርነት ሲታመስ የኖረ ብሔር በአንድ ጀግና ንጉሥ የሚተዳደር አንድነት ያለውና የበለጸገ አገር ለመሆን እንዴት እንደበቃ ያወሳል። ይህ ማራኪ ዘገባ ጥልቅ ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀባቸውን ትረካዎች ይዟል።
“ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ”
ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ሞት በሰማበት ወቅት ያደረገው ነገር ለእነርሱም ሆነ ለይሖዋ ያለውን ስሜት በግልጽ አሳይቷል። ወደ ኬብሮን ከመጣ በኋላ በይሁዳ ነገድ ላይ ቀብተው አነገሡት። የሳኦል ልጅ የሆነው ኢያቡስቴ ደግሞ በቀሪው የእስራኤል ብሔር ላይ ነገሠ። ዳዊትም “ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ” በመሄድ ከሰባት ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ በጠቅላላው የእስራኤል ብሔር ላይ ንጉሥ ሆነ።—2 ሳሙኤል 5:10
ዳዊት ኢየሩሳሌምን ከኢያቡሳውያን እጅ በመማረክ የመንግሥቱ ዋና ከተማ አደረጋት። የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ አደጋ ቢያስከትልም ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገው ጥረት በመሳካቱ ዳዊት ደስታውን በጭፈራ ገልጿል። ይሖዋም ከዳዊት ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደረገ። አምላክ ከዳዊት ጋር ስለነበር ጠላቶቹን ድል ለመንሳትም ችሏል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:18—ኢዮአብና ሁለቱ ወንድሞቹ የጽሩያ ሦስት ልጆች ተብለው በእናታቸው ስም የተጠሩት ለምንድን ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የዘር ሐረግ የሚቆጠረው በአባት በኩል ነበር። የጽሩያ ባል ሞቶ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እርሱን ማካተት ተገቢ ያልሆነበት ምክንያት ይኖር ይሆናል። አሊያም ጽሩያ የተጠቀሰችው የዳዊት እህት (ወይም ግማሽ እህት) ስለሆነች ሊሆን ይችላል። (1 ዜና መዋዕል 2:15, 16) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእነዚህ ሦስት ወንድማማቾች አባት ተጠቅሶ የሚገኝበት ቦታ የተቀበረው በቤተልሔም መሆኑን የሚገልጸው ብቻ ነው።—2 ሳሙኤል 2:32
5:1, 2—ዳዊት በእስራኤል ላይ የነገሰው ኢያቡስቴ ከተገደለ በኋላ ምን ያህል ቆይቶ ነው? ኢያቡስቴ ለሁለት ዓመት የቆየ ንግሥናውን የጀመረው ንጉሥ ሳኦል ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ይኸውም ዳዊት በኬብሮን በነገሰበት ወቅት አካባቢ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል። ዳዊት መቀመጫውን ኬብሮን ላይ አድርጎ ይሁዳን የገዛው ለሰባት ዓመት ተኩል ያህል ነው። ከዚያም በአጠቃላይ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንደሆነ ምንም ያህል ሳይቆይ ዋና ከተማውን ወደ ኢየሩሳሌም አዛወረ። ስለዚህ ከኢያቡስቴ ሞት በኋላ ዳዊት በጠቅላላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ከመሆኑ በፊት አምስት ዓመታት ያህል አልፈዋል ማለት ነው።—2 ሳሙኤል 2:3, 4, 8-11፤ 5:4, 5
8:2—ሞዓባውያን ከእስራኤላውያን ጋር ከተዋጉ በኋላ ምን ያህል ሰዎች ተገድለውባቸዋል? ብዛታቸው ከቁጥር ይልቅ በመለኪያ ተገልጾ እናገኘዋለን። ዳዊት ሞዓባውያንን መሬት ላይ በተርታ እንዲተኙ ያደረጋቸው ይመስላል። ቀጥሎም የሰልፉን ርዝመት በገመድ ለካው። በገመድ ከለካቸውም ሁለት እጅ ወይም ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ሲገድል አንድ እጅ ማለትም አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ግን በሕይወት ይተው ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:1፤ 5:19, 23፦ ዳዊት በኬብሮን ለመኖር ከመነሳቱም ሆነ ከጠላቶቹ ጋር ውጊያ ከመግጠሙ በፊት ይሖዋን ይጠይቅ ነበር። እኛም ብንሆን መንፈሳዊነታችንን ሊነካ የሚችል ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት መጣር አለብን።
3:26-30፦ ብቀላ ውጤቱ አሳዛኝ ነው።—ሮሜ 12:17-19
3:31-34፤ 4:9-12፦ ዳዊት በቀለኛ እንዲሁም ቂመኛ ባለመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።
5:12፦ ይሖዋ እርሱ በመረጠው መንገድ እንደሚያስተምረንና ከእርሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ሁኔታዎችን እንዳመቻቸልን በፍጹም መዘንጋት የለብንም።
6:1-7፦ ዳዊት ታቦቱን በሠረገላ ለማምጣት ሙከራ ያደረገው በቅን ልቦና ተነሳስቶ ቢሆንም ድርጊቱ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ችግር አስከትሏል። (ዘፀአት 25:13, 14፤ ዘኁልቁ 4:15, 19፤ 7:7-9) ዖዛም ቢሆን እጁን ዘርግቶ ታቦቱን መያዙ በቅንነት የሚደረጉ ነገሮችም እንኳ የአምላክን መመሪያዎች እንደማይለውጡት ያሳያል።
6:8, 9፦ ዳዊት ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ በመጀመሪያ ላይ የተከፋ ቢሆንም ከዚያ ግን ፍርሃት አድሮበታል፤ ምናልባትም ለደረሰው መከራ ይሖዋን ተወቃሽ አድርጎ ሊሆን ይችላል። እኛም ብንሆን የአምላክን ትእዛዛት ችላ በማለት ለሚደርሱብን ችግሮች እርሱን ተወቃሽ ላለማድረግ ልንጠነቀቅ ይገባል።
7:18, 22, 23, 26፦ ዳዊትን በትሕትናው፣ በሙሉ ልብ ይሖዋን በማምለኩ እንዲሁም የአምላክን ስም ለማወደስ ባለው ፍላጎት ልንኮርጀው ይገባል።
8:2፦ ከ400 ዓመታት በፊት የተነገረ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘኍልቊ 24:17) የይሖዋ ቃል ሁልጊዜም ይፈጸማል።
9:1, 6, 7፦ ዳዊት ቃሉን ጠብቋል። እኛም ቃላችንን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
ይሖዋ ራሱ በቀባው ላይ ክፉ ነገር አስነሣበት
ይሖዋ ዳዊትን “እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ” ካለው በኋላ አክሎም “ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል” አለው። (2 ሳሙኤል 12:11) ዳዊት ይህ የፍርድ መልእክት የተላለፈበት ለምን ነበር? ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት በመሥራቱ ነበር። ንስሐ በመግባቱ ምሕረት ቢያገኝም ኃጢአቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ ግን ማምለጥ አልቻለም።
በመጀመሪያ ደረጃ ቤርሳቤህ የወለደችው ልጅ ሞተ። ቀጥሎም ድንግል የነበረችው የዳዊት ልጅ ትዕማር የአባቷ ልጅ በሆነው በአምኖን ተደፈረች። በዚህም ምክንያት ወንድሟ አቤሴሎም በብቀላ ተነሳስቶ አምኖንን ገደለው። አቤሴሎም በአባቱ ላይ በማሴር በኬብሮን ንጉሥ መሆኑን አዋጅ አስነገረ። ዳዊትም ኢየሩሳሌምን ትቶ ለመሸሽ ተገዶ ነበር። አቤሴሎም ቤት እንዲጠብቁ ከቀሩት የዳዊት አሥር ቁባቶች ጋር ተኛ። ዳዊት ወደ ንግሥናው ለመመለስ የቻለው አቤሴሎም ከተገደለ በኋላ ነበር። ብንያማዊው ሳቤዔም ቢሆን በዳዊት ላይ ዓመጽ የቀሰቀሰ ሲሆን በመጨረሻም ሳቤዔ በመገደሉ ዓመጹ ሊደመደም ችሏል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
14:7—“መብራቴን” የሚለው ቃል ምን ለመግለጽ የገባ አባባል ነው? መብራት የሚለው ቃል በሕይወት ያለውን ልጅዋን ያመለክታል።
19:29—ዳዊት ለሜምፊቦስቴ ንግግር በዚህ መንገድ ምላሽ የሰጠው ለምንድን ነበር? ዳዊት የሜምፊቦስቴን ምላሽ በሰማበት ወቅት የሲባን ቃላት እንዳለ አምኖ መቀበሉ ስሕተት እንደነበር ተገንዝቦ መሆን አለበት። (2 ሳሙኤል 16:1-4፤ 19:24-28) ይህ ደግሞ ዳዊትን ስላናደደው ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ነገር መስማት አልፈለገም።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
11:2-15፦ የዳዊት ድክመቶች በግልጽ መጻፋቸው መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ለመጻፉ ማስረጃ ይሆናል።
11:16-27፦ አንድ ከበድ ያለ ኃጢአት ብንሠራ እንደ ዳዊት ለመደበቅ መሞከር የለብንም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአታችንን ለይሖዋ መናዘዝና ከጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።—ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:13-16
12:1-14፦ ናታን በጉባኤ ውስጥ ላሉ የተሾሙ ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ሽማግሌዎች ኃጢአተኞች የስሕተት አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ መርዳት ይኖርባቸዋል። ይህንንም ኃላፊነታቸውን በጥበብ ሊወጡት ይገባል።
12:15-23፦ ዳዊት እየደረሰበት ስላለው ነገር ትክክለኛ አመለካከት መያዙ ለገጠመው መከራ ተገቢ የሆነ ምላሽ እንዲሰጥ ረድቶታል።
15:12፤ 16:15, 21, 23፦ በጥሩ ምክር ሰጭነቱ ታዋቂ የነበረው አኪጦፌል ኩሩና ክብር ፈላጊ በመሆኑ አቤሴሎም እንደሚነግሥ ሲሰማው ክህደት ሊፈጽም ችሏል። ትሕትናና ታማኝነት ያልታከለበት እውቀት ብቻውን ወጥመድ ነው።
19:24, 30፦ ሜምፊቦስቴ የዳዊትን ፍቅራዊ ደግነት ከልቡ አድንቋል። ሲባን አስመልክቶ ንጉሡ የሰጠውን ውሳኔ ያለምንም ማንገራገር ተቀብሏል። እኛም በተመሳሳይ ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለን አድናቆት ወደ ታዛዥነት ሊመራን ይገባል።
20:21, 22፦ የአንድ ሰው ጥበብ በብዙዎች ላይ የተደቀነውን አደጋ ሊያስቀር ይችላል።—መክብብ 9:14, 15
“በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ”
ሳኦል ገባዖናውያንን መግደሉ በደም ዕዳ ተጠያቂ ስላደረገው ለሦስት ዓመት ያህል እስራኤላውያን በረሃብ እንዲጠቁ ምክንያት ሆኗል። (ኢያሱ 9:15) ገባዖናውያን ይህን የደም ዕዳ ለመበቀል የሳኦልን ሰባት ልጆች በስቅላት ለመግደል ጠየቁ። ዳዊትም የሳኦልን ልጆች ለገባዖናውያን አሳልፎ በመስጠቱ ተቋርጦ የነበረው ዝናብ መዝነብ ጀመረ። አራት ግዙፍ ፍልስጥኤማውያን “በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።”—2 ሳሙኤል 21:22
ዳዊት ተገቢ ያልሆነ የሕዝብ ቆጠራ በማድረግ ከባድ ኃጢአት ሠራ። ኃጢአቱን ከመናዘዙም በተጨማሪ ‘በእግዚአብሔር እጅ መውደቅን’ መርጧል። (2 ሳሙኤል 24:14) በዚህም ምክንያት 70,000 ሰዎች በቸነፈር ሞቱ። ከዚያም ዳዊት የይሖዋን መመሪያ በመከተሉ መቅሰፍቱ ሊቆም ችሏል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
21:9, 10—ሪጽፋ በገባዖናውያን የተገደሉትን የራሷን ሁለት ልጆችና አምስቱን የሳኦልን የልጅ ልጆች ሬሳ በንቃት የጠበቀችው ለምን ያህል ጊዜ ነበር? ሰባቱም የተሰቀሉት “በመከሩ ወራት የመጀመሪያ ቀኖች” ማለትም በመጋቢት ወይም በሚያዝያ ወር ላይ ሲሆን ሬሳቸውንም በኮረብታ ላይ ሰቀሉት። ሪጽፋ ሰባቱንም ሬሳዎች የይሖዋ ቁጣ እስከተመለሰበት ድረስና ድርቁ እስካበቃበት ድረስ ሌት ተቀን ጠብቃለች። የአጨዳው ጊዜ እስከሚጠናቀቅበት እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ኃይለኛ ዝናብ ይጥላል ተብሎ አይጠበቅም። ስለሆነም ሪጽፋ ለአምስት ወይም ለስድስት ወራት በትጋት ጠብቃ ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ ዳዊት የሰዎቹን አጥንት ወስዶ ቀበረ።
24:1—ዳዊት ሰዎቹን መቁጠሩ እንደ ከባድ ኃጢአት የተቆጠረበት ለምንድን ነው? ሰውን መቁጠር በራሱ በሕጉ ውስጥ አልተከለከለም። (ዘኁልቁ 1:1-3፤ 26:1-4) መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ቆጠራውን ለማድረግ የተነሳሳበትን ዓላማ አይገልጽም። ይሁንና 1 ዜና መዋዕል 21:1 ይህን እንዲያደርግ ሰይጣን እንዳነሳሳው ይነግረናል። ያም ሆነ ይህ የዳዊት የጦር አዛዥ የሆነው ኢዮአብ ዳዊት ሕዝቡን ለመቁጠር መወሰኑ ስሕተት መሆኑን በመረዳት እንደዚያ እንዳያደርግ ምክር ሰጥቶት ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
22:2-51፦ ይሖዋ እውነተኛና ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት የሚገባ አምላክ መሆኑን የዳዊት መዝሙር ግሩም አድርጎ ገልጾታል!
23:15-17፦ ዳዊት አምላክ ስለ ደምና ስለ ሕይወት ላወጣው ሕግ ጥልቅ አክብሮት ስለነበረው በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ይህን ሕግ የሚያስጥስ የሚመስል ነገር በገጠመው ወቅት ድርጊቱን ከመፈጸም ተቆጥቧል። እኛም ብንሆን ሁሉንም የአምላክ ሕጎች በመጠበቅ ረገድ የእርሱ ዓይነት ዝንባሌ ልንኮተኩት ይገባናል።
24:10፦ ዳዊት ሕሊናው ንስሐ እንዲገባ አድርጎታል። የእኛስ ሕሊና በዚህ ረገድ ንቁ ነው?
24:14፦ ዳዊት ከሰው ይልቅ ይሖዋ በጣም መሐሪ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። እኛስ እንዲህ ያለ እምነት አለን?
24:17፦ ዳዊት እርሱ በሠራው ኃጢአት መላው የእስራኤል ሕዝብ ሲሠቃይ በተመለከተበት ወቅት በጣም አዝኗል። ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛም በጉባኤው ላይ ነቀፌታ አምጥቶ ከነበር የጸጸት ስሜት ሊሰማው ይገባል።
የአምላክን ልብ ማስደሰት ከአቅማችን በላይ አይደለም
ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ ‘ለይሖዋ እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው’ መሆኑን አሳይቷል። (1 ሳሙኤል 13:14) ዳዊት አንድም ጊዜ ቢሆን በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ላይ ጥርጣሬ አድሮበት አያውቅም፤ በተጨማሪም ከአምላክ አገዛዝ ርቆ በራሱ ለመመራት አልፈለገም። ዳዊት በተሳሳተባቸው ጊዜያት ሁሉ ኃጢአት መሥራቱን አምኗል፣ እርማት ተቀብሏል እንዲሁም መንገዱን አስተካክሏል። ዳዊት ታማኝም ነበር። በተለይ ስሕተት ከሠራን እንደ እርሱ መሆን አዋቂነት አይደለም?
የዳዊት የሕይወት ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየው የይሖዋን ሉዓላዊነት መቀበል ማለት እርሱ መልካምና ክፉ የሆኑ ነገሮችን አስመልክቶ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መቀበልን እንዲሁም በታማኝነት ከእነርሱ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ጥረት ማድረግን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ ከአቅማችን በላይ አይደለም። ከሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ለተማርነው ነገር ምንኛ አመስጋኝ መሆን ይኖርብናል! በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው መልእክት በእውነትም ሕያውና የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ መጽሐፍ በሳሙኤል ስም ቢጠራም እርሱ አልጻፈውም፣ በስሙ የተጠራበትም ምክንያት የአንደኛና የሁለተኛ ሳሙኤል መጻሕፍት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅልል ውስጥ አንድ ላይ ይገኙ ስለነበር ነው። ይሁን እንጂ የአንደኛ ሳሙኤልን መጽሐፍ አብዛኛውን ክፍል የጻፈው ሳሙኤል ነው።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ንጉሥ አድርጎ የሾመው ማን እንደሆነ ማወቁ ትሑት እንዲሆን ረድቶታል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ”
ቤርሳቤህ
ትዕማር
አምኖን