የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ፈጣሪያችን ለሆነው ለይሖዋ አምላክ የቀረቡ በርካታ ውዳሴዎችን ለያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ተስማሚ የሆነው መጠሪያ ምንድን ነው? መጽሐፉ መዝሙር ወይም ምስጋና ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ይህ ረጅም መጽሐፍ የአምላክን ግሩም ባሕርያትና ታላላቅ ሥራዎች የሚያወሱ እንዲሁም በርካታ ትንቢቶችን ያካተቱና በሚስብ መንገድ የተቀናበሩ መዝሙሮችን የያዘ መጽሐፍ ነው። አብዛኞቹ መዝሙሮች ጸሐፊዎቹ መከራ ሲደርስባቸው ምን እንደተሰማቸው የሚገልጹ ናቸው። በእነዚህ መዝሙሮች ውስጥ የሚገኙት አገላለጾች ከነቢዩ ሙሴ ዘመን አንስቶ አይሁዳውያን ከባቢሎን እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ ባሉት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ የኖሩ ሰዎች የነበሯቸውን ስሜቶች የሚያሳዩ ናቸው። ጸሐፊዎቹ ሙሴ፣ ንጉሥ ዳዊትና ሌሎች ሰዎች ናቸው። የመዝሙርን መጽሐፍ አሁን ባለው መልኩ ያቀናበረው ካህኑ ዕዝራ ነው።
ከጥንት ጀምሮ የመዝሙር መጽሐፍ በአምስት የተለያዩ የመዝሙራት ስብስቦች ወይም መጽሐፎች የተከፋፈለ ሲሆን እነርሱም:- (1) መዝሙር 1-41፣ (2) መዝሙር 42-72፣ (3) መዝሙር 73-89፣ (4) መዝሙር 90-106 እና (5) መዝሙር 107-150 ናቸው። ይህ ርዕስ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ያተኩራል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት መዝሙሮች መካከል ከሦስቱ በስተቀር ሁሉንም የጻፈው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ነው። የመዝሙር 1, 10 እና 33 አቀናባሪ ማን እንደሆነ አይታወቅም።
“እግዚአብሔር ዐለቴ” ነው
የመጀመሪያው መዝሙር የይሖዋን ሕግ የሚወድ ሰው ደስተኛ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ሁለተኛው መዝሙር በቀጥታ ስለ መንግሥቱ ይናገራል።a በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙት መዝሙሮች በአብዛኛው ለአምላክ የቀረቡ ልመናዎችን የያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 3 እስከ 5, 7, 12, 13 እና 17 ዘማሪው አምላክ ከጠላት እንዲያድነው ያቀረባቸው ልመናዎች ናቸው። ሰው ከይሖዋ ታላቅነት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የማይባል ኢምንት መሆኑን መዝሙር 8 ያጎላል።
ዳዊት፣ ይሖዋ የሕዝቡ ጠባቂ እንደሆነ በመግለጽ “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 18:2) በመዝሙር 19 ላይ ይሖዋ ውዳሴ የሚገባው ፈጣሪና ሕግ አውጪ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን መዝሙር 20 ደግሞ አዳኝ መሆኑን እንዲሁም መዝሙር 21 የተቀባውን ንጉሥ የሚያድን እንደሆነ ይናገራል። በመዝሙር 23 ላይ ይሖዋ እንደ ታላቅ እረኛ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን 24ኛው መዝሙር ደግሞ የላቀ ክብር የተቀዳጀ ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:1, 2—ብሔራት የሚያውጠነጥኑት “ከንቱ ነገር” ምንድን ነው? “ከንቱ ነገር” የተባለው ሰብዓዊ መንግሥታት ሥልጣናቸውን ለማራዘም ሁልጊዜ የሚያውጠነጥኑት ሐሳብ ነው። ዓላማቸው ስለማይሳካ ከንቱ ተብሏል። ደግሞስ ሰዎች “በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ” ተነስተው ሊሳካላቸው ይችላል?
2:7—‘የእግዚአብሔር ሕግ’ የተባለው ምንድን ነው? ይሖዋ ከሚወደው ልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን ነው።—ሉቃስ 22:28, 29 NW
2:12—ብሔራት ‘ልጁን የሚስሙት’ በምን መንገድ ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን መሳም የወዳጅነትና የታማኝነት መግለጫ ነበር። አንድ ሰው እንግዶች ቤቱ ሲመጡ መደሰቱን በመሳም ይገልጽ ነበር። የምድር ነገሥታት ልጁን እንዲስሙት ማለትም መሲሐዊ ንጉሥ መሆኑን እንዲቀበሉ ታዘዋል።
3:0—በመዝሙሩ አናት ላይ የሚገኘው መግለጫ—በአንዳንዶቹ መዝሙሮች አናት ላይ የሚገኘው መግለጫ ምን ጠቀሜታ አለው? በመዝሙሮቹ አናት ላይ የሚገኘው መግለጫ አንዳንድ ጊዜ የጸሐፊውን ስም የሚገልጽ ሲሆን በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በመዝሙር 3 መግቢያ ላይ እንደሚታየው መዝሙሩ በተጻፈበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ይጠቅሳል። በመዝሙሮቹ አናት ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ መግለጫዎች አንድ መዝሙር በየትኛው ወቅት እንደሚዘመር ወይም ዓላማው ምን እንደሆነ ያብራራሉ (መዝሙር 4 እና 5)፤ እንዲሁም የሙዚቃውን ቅንብር በተመለከተ መመሪያ ይሰጣሉ (መዝሙር 6)።
3:2—“ሴላ” ምንድን ነው? ይህ ቃል የሚያመለክተው በድምፅ ብቻ በሚዜምበት ወቅትም ሆነ በሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ በሚዘመርበት ጊዜ ለማሰላሰል ሲባል ቆም የሚባልበትን ቦታ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። በመዝሙሩ መሃል ቆም የሚባልበት ምክንያት የመዝሙሩን ሐሳብ ወይም ስሜት ይበልጥ ለማጉላት ነበር። በመሆኑም ለሕዝብ በምናነብበት ወቅት ይህን ቃል መጥራቱ አስፈላጊ አይደለም።
11:3—የተናዱት መሠረቶች የትኞቹ ናቸው? ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ መሠረት የሆኑት ነገሮች ማለትም ሕግ፣ ሥርዓትና ፍትሕ ናቸው። ሆኖም ይህ መሠረት ከተናጋ ማኅበራዊው ሥርዓት ለውድቀት ይዳረጋል፤ እንዲሁም ፍትሕ አይኖርም። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ሥር “ጻድቅ” የሆነ ሰው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን አለበት።—መዝሙር 11:4-7
21:3—“የንጹሕ ወርቅ ዘውድ” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? ይህ አባባል ቃል በቃል ዘውድን የሚያመለክት ይሁን ወይም ዳዊት ባገኛቸው በርካታ ድሎች የተነሳ የሚኖረውን ተጨማሪ ክብር የሚያሳይ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ በግልጽ አልሠፈረም። ሆኖም ይህ ጥቅስ ኢየሱስ በ1914 ከይሖዋ የተቀበለውን የንግሥና ዘውድ የሚያሳይ ትንቢታዊ አገላለጽ ነው። ዘውዱ ከወርቅ መሠራቱ ግዛቱ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ያሳያል።
22:1, 2—ዳዊት ይሖዋ እንደተወው የተሰማው ለምን ሊሆን ይችላል? ዳዊት ከጠላቶቹ በሚደርስበት ጥቃት በጣም ተጨንቆ ስለነበረ ‘ልቡ እንደ ሰም በውስጡ የቀለጠ’ ያህል ነበር። (መዝሙር 22:14) በዚህም ምክንያት ይሖዋ የተወው መስሎት ይሆናል። ኢየሱስም በተሰቀለበት ጊዜ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር። (ማቴዎስ 27:46) ዳዊት በደረሰበት አስከፊ ሁኔታ የተሰማውን ስሜት በእነዚህ ቃላት ገልጿል። ሆኖም በመዝሙር 22:16-21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎት ዳዊት በአምላክ ላይ የነበረውን እምነት እንዳላጣ በግልጽ ያሳያል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:1:- ይሖዋን ከማይወዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መፍጠር ፈጽሞ አይገባም።—1 ቆሮንቶስ 15:33
1:2:- ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ሳናስብ አንድም ቀን እንዲያልፍ መፍቀድ የለብንም።—ማቴዎስ 4:4
4:4:- በምንናደድበት ጊዜ፣ የኋላ ኋላ የምንቆጭበትን ነገር እንዳንናገር ምላሳችንን መግታት የጥበብ እርምጃ ነው።—ኤፌሶን 4:26
4:5:- የምናቀርበው መንፈሳዊ መሥዋዕት ‘የጽድቅ መሥዋዕት’ ሊሆን የሚችለው ከትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት የመነጨ ሲሆንና ምግባራችን ከይሖዋ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ ሲሆን ብቻ ነው።
6:5:- በሕይወት የመኖራችን ዋና ዓላማ ይሖዋን ማወደስ ነው።—መዝሙር 115:17
9:12:- ይሖዋ የደም ዕዳ ያለባቸውን ይቀጣል፤ “የጭቍኖችንም ጩኸት” አይዘነጋም።
15:2, 3፤ 24:3-5:- እውነተኛ አምላኪዎች እውነትን መናገር እንዲሁም በሐሰት ከመማልና ስም ከማጥፋት መቆጠብ አለባቸው።
15:4:- ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ መሐላ እስካልፈጸምን ድረስ በጣም ከባድ ቢሆንም እንኳ ቃላችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
15:5:- የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን በገንዘብ አጠቃቀማችን ረገድ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል።
17:14, 15:- ‘የዚህ ዓለም ሰዎች’ በኑሯቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ ቤተሰብ ለመመሥረትና ለልጆቻቸው የሚያወርሱት ነገር ለማከማቸት ይሯሯጣሉ። ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ትኩረት የሰጠው በአምላክ ዘንድ መልካም ስም አትርፎ ‘ፊቱን ለማየት’ ወይም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ነበር። ዳዊት ‘ሲነቃ’ ወይም ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎችና ማረጋገጫዎች ሲገነዘብ ‘ክብሩን አይቶ ይረካል፤’ ይህም ማለት ይሖዋ ከእሱ ጋር እንዳለ ስለሚያውቅ ይደሰታል። እኛስ እንደ ዳዊት ልባችንን በመንፈሳዊ ሀብት ላይ ማድረግ አይኖርብንም?
19:1-6:- መናገርም ሆነ ማመዛዘን የማይችሉ ግዑዛን ፍጥረታት ለይሖዋ ክብር የሚሰጡ ከሆነ የማሰብ፣ የመናገርና የማምለክ ችሎታ ያለን ሰዎችማ ይበልጥ ልናከብረው አይገባም?—ራእይ 4:11
19:7-11:- ይሖዋ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ሁሉ ለእኛ እንዴት ጠቃሚ ናቸው!
19:12, 13:- ከስህተትና ከድፍረት ኃጢአት መራቅ አለብን።
19:14:- ለተግባራችን ብቻ ሳይሆን ለምንናገረውና ለምናስበው ነገርም ትኩረት መስጠት ይገባናል።
“ስለ ጭንቀቴ [“ጽኑ አቋሜ፣” NW] ደግፈህ ይዘኸኛል”
ዳዊት ጽኑ አቋሙን ጠብቆ ለመኖር ያለው ልባዊ ፍላጎትና ያደረገው ቁርጥ ውሳኔ በመዝሙር 25 እና 26 ላይ ተገልጿል! “እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት [“በጽኑ አቋሜ፣” NW] እጓዛለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 26:11) ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት ሲጸልይ “ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሣ፣ ዝም ባልሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ተበላሹ” ብሏል። (መዝሙር 32:3) ዳዊት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ለሚገኙ ሰዎች “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል።—መዝሙር 34:15
በመዝሙር 37 ላይ የሚገኘው ምክር ለእስራኤላውያንም ሆነ “በመጨረሻው ዘመን” ለምንገኘው ለእኛ በጣም ጠቃሚ ነው! (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በመዝሙር 40:7, 8 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል:- “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።” መዝሙር 41 ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ በነበሩት አስጨናቂ ዓመታት ይሖዋ እንዲረዳው ያቀረበውን ልመና የያዘ ነው። ዳዊት “ስለ ጭንቀቴ [“ጽኑ አቋሜ፣” NW] ደግፈህ ይዘኸኛል” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 41:12
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
26:6—እንደ ዳዊት በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የእግዚአብሔርን መሠዊያ መዞር’ የምንችለው እንዴት ነው? መሠዊያው የይሖዋን ፈቃድ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለመዋጀት ያቀረበውን መሥዋዕት መቀበሉን ያመለክታል። (ዕብራውያን 8:5፤ 10:5-10) የይሖዋን መሠዊያ መዞር የምንችለው በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን ነው።
29:3-9—የይሖዋ ድምፅ ፍርሃት እንዲያድርብን ከሚያደርግ ነጎድጓድ ጋር ተመሳስሎ የተገለጸው ምንን ለማመልከት ነው? በአጭር አገላለጽ፣ የይሖዋን ታላቅ ኃይል ለማመልከት ነው!
33:6—ከይሖዋ አፍ የሚወጣው “እስትንፋስ” ምንድን ነው? ይህ እስትንፋስ አምላክ ግዑዙን ሰማይ ለመፍጠር የተጠቀመበትን ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 1:1, 2) በአፉም እስትንፋስ ተብሎ መጠራቱ እንደ ኃይለኛ እስትንፋስ ሩቅ ድረስ ተልኮ የተፈለገውን ነገር ሊያከናውን እንደሚችል ያሳያል።
35:19—ዳዊት ጠላቶቹ በዐይናቸው እንዳይጣቀሱበት ሲለምን ምን ማለቱ ነበር? ጠላቶቹ በዐይናቸው መጣቀሳቸው በዳዊት ላይ የጠነሰሱት የክፋት ሤራ በመሳካቱ እንደተደሰቱ የሚያሳይ ሲሆን ዳዊትም የጸለየው ይህ እንዳይሆን ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
26:4:- ጥበበኞች በመሆን በኢንተርኔት ቻት ሩም ማንነታቸውን ደብቀው ከሚያናግሩን ግብዞች፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ስውር ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ወዳጅ መስለው ከሚቀርቡን ሰዎች እንዲሁም አታላይ ከሆኑ ከሃዲዎችና በጉባኤ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሕይወት ከሚመሩ ክርስቲያኖች ጋር ጓደኝነት ከመመሥረት መራቅ አለብን።
26:7, 12፤ 35:18፤ 40:9:- በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሕዝብ ፊት ይሖዋን ማወደስ አለብን።
26:8፤ 27:4:- ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ያስደስተናል?
26:11:- ዳዊት ጽኑ አቋሙን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ ከተናገረ በኋላ ይሖዋ እንዲያድነውም ጠይቋል። እኛም በተመሳሳይ ፍጹም ባንሆንም እንኳ ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።
29:10:- ይሖዋ “በጐርፍ” ላይ እንደተቀመጠ የተገለጸው በሁሉም ነገር ላይ ኃይል ያለው አምላክ መሆኑን ለማሳየት ነው።
30:5:- የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር እንጂ ቁጣ አይደለም።
32:9:- ይሖዋ በልጓም ካልተገሩ ወይም ካልተመቱ በስተቀር እንደማይታዘዙት እንደ ፈረስና በቅሎ እንድንሆን አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ ፈቃዱን ተገንዝበን በራሳችን ተነሳሽነት እንድንታዘዘው ይፈልጋል።
33:17-19:- የሰው ሥርዓት ምንም ያህል ኃይል ቢኖረው መዳን ሊያመጣ አይችልም። ተስፋ ማድረግ ያለብን በይሖዋና በመንግሥቱ ላይ ነው።
34:10:- በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት ለሚያስቀድሙ ሰዎች እንዴት ያሉ የሚያበረታቱ ቃላት ናቸው!
39:1, 2:- ክፉ ሰዎች፣ የእምነት ወንድሞቻችንን ለመጉዳት በማሰብ ጥያቄ ሲያቀርቡልን ‘ልጓም በአፋችን በማስገባት’ ዝም ማለት ከሁሉ የተሻለ የጥበብ መንገድ ነው።
40:1, 2:- ይሖዋን ተስፋ ማድረግ “ከሚውጥ ጒድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ” የመውጣትን ያህል የመንፈስ ጭንቀትን እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል።
40:5, 12:- ባገኘናቸው ‘ስፍር ቍጥር’ የሌላቸው በረከቶች ላይ የምናተኩር ከሆነ የግል ድክመቶቻችን ወይም የሚደርሱብን ችግሮች ምንም ያህል ቢበዙ ከአቅማችን በላይ አይሆኑብንም።
‘እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን’
የመጀመሪያዎቹ 41 መዝሙራት ምንኛ የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ ናቸው! አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጥንም ይሁን በሕሊና ወቀሳ እየተሠቃየን፣ የአምላክ ቃል ኃይል ስላለው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ያጠናክረናል እንዲሁም ያበረታናል። (ዕብራውያን 4:12) እነዚህ መዝሙሮች ለሕይወታችን አስተማማኝ መመሪያ ይሆኑናል። ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ይሖዋ እንደማይተወን በተደጋጋሚ ጊዜያት ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን፤ አሜን፤ አሜን።” (መዝሙር 41:13) በእነዚህ መዝሙሮች ላይ ያደረግነው ውይይት ይሖዋን ለመባረክ ወይም ለማወደስ አላነሳሳንም?
[የግርጌ ማስታወሻ]
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መናገርም ሆነ ማመዛዘን የማይችሉ ግዑዛን ፍጥረታት ለይሖዋ ክብር የሚሰጡ ከሆነ እኛ ሰዎችማ ይበልጥ ልናከብረው አይገባም?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመጀመሪያዎቹ 41 መዝሙራት አብዛኞቹን ያቀናበረው ዳዊት ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን እንደ ታላቅ እረኛ አድርጎ የሚገልጸው የትኛው መዝሙር እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ሳናስብ አንድም ቀን እንዲያልፍ መፍቀድ የለብንም
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ኮከቦች:- Courtesy United States Naval Observatory
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ኮከቦች፣ ገጽ 18 እና 19:- Courtesy United States Naval Observatory
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ኮከቦች:- Courtesy United States Naval Observatory