ይሖዋን መሸሸጊያህ አድርገው
“ይሖዋ ሆይ፣ አንተን መሸሸጊያዬ አደረግሁህ።”—መዝሙር 31:1 አዓት
1. መዝሙር 31 ይሖዋ መሸሸጊያ ለማዘጋጀት ባለው ችሎታ ላይ ሊኖረን የሚችለውን ትምክህት የሚገልጸው እንዴት ነው?
አእምሮውና ሰውነቱ ቢዝልም በይሖዋ ላይ ተደግፎ ስለቆመ ሰው ጥሩ ጣዕም ባለው ዜማ የሚዘመር አንድ መዝሙር ነበር። የዚያ ቅዱስ መዝሙር ግጥሞች እምነት ድል ያደርጋል ይላሉ። ተዘርግተው በሚጠብቁት ሁሉን በሚችለው አምላክ ክንዶች ውስጥ ይህ ሰው ያለ እረፍት ከሚያሳድዱት ሰዎች መሸሸጊያ አገኘ። “አቤቱ፣ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር፤ በጽድቅህም አድነኝ” በማለት መዝሙሩ ይቀጥላል።—መዝሙር 31:1
2.(ሀ) ይሖዋን እንደ መከላከያ ኃይላችን አድርገን እምነታችንን በእርሱ ላይ ልንጥል የምንችለው በየትኞቹ ሁለት ምሰሶዎች መሠረት ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው?
2 መዝሙራዊው ከሁሉ የሚበልጥ አንድ መሸሸጊያ አለው። ሌሎች ነገሮች ሁሉ አጠራጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሖዋ መሸሸጊያውና የመከላከያ ኃይሉ የመሆኑ ሐቅ ግን አላጠራጠረውም። ትምክህቱ በሁለት አስተማማኝ ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነበር። አንደኛው እምነቱ ሲሆን ይሖዋ እንዲህ ያለ እምነት ያለውን ሰው እንዲያፍር አያደርገውም፤ ሁለተኛው ደግሞ አገልጋዮቹን ለዘለቄታው እንደማይተዋቸው የሚያረጋግጠው የይሖዋ ጽድቅ ነው። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን የሚያሳፍር አምላክ አይደለም፤ የገባውን ቃል አያፈርስም። ከዚህ ይልቅ እርሱ የእውነት አምላክና ከልባቸው ለሚተማመኑበት ሰዎች ዋጋቸውን የሚከፍል አምላክ ነው። ስለሆነም እንዲህ ያለው እምነት በመጨረሻው ተገቢውን ዋጋ ያስገኛል! ከመከራ የምንገላገልበት ጊዜ ይመጣል።—መዝሙር 31:5, 6
3. መዝሙራዊው ይሖዋን ከፍ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
3 ሙዚቃውን ከፍና ዝቅ አድርጎ በመቃኘት በኀዘንና በወዮታ ትካዜ ውስጥ ከገባ በኋላ እንደገና በልበ ሙሉነት ስሜት እንዲሞላ የሚያደርግ ዜማ ማውጣቱ ለመዝሙራዊው ውስጣዊ ብርታት አስገኝቶለታል። ይሖዋን ስለ ታማኝ ፍቅሩ ከፍ አድርጎ ያመሰግነዋል። “በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን [ፍቅራዊ ደግነቱን አዓት] በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን” በማለት ይዘምራል።—መዝሙር 31:21
መንግሥቱን የሚያውጅ ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት
4, 5. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋን እያወደሰ ያለው ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት ምንድን ነው? ባለፈው የአገልግሎት ዓመትስ ይህንን ያደረጉት እንዴት ነው? (በገጽ 12–15 ላይ ያለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።) (ለ) የመንግሥቱን አዋጅ ነጋሪዎች የመዘምራን ቡድን ለመተባበር በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተጨማሪ ግለሰቦች እንዳሉ የመታሰቢያው በዓል የተሰብሳቢዎች ብዛት የሚጠቁመው እንዴት ነው? (ሠንጠረዡን ተመልከት።) (ሐ) በጉባኤህ ውስጥ የመዘምራኑን ቡድን ለመተባበር ዝግጁ የሆነው ሠራዊት የትኛው ነው?
4 ዛሬ የመዝሙራዊው ቃሎች እንደገና ሕያው ሆነዋል። ለይሖዋ የሚቀርቡት የምስጋና መዝሙሮች በማንኛውም ክፉ ተቃዋሚ፣ በማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ ወይም በማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊታፈን አይችልም። በእውነትም የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ለሕዝቦቹ በጣም አስደናቂ ሆኖላቸዋል። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥራቸው 4,709,889 ላይ የደረሰ እጅግ ብዙ መዘምራን በ231 አገሮች የአምላክን መንግሥት መልእክት ዘምረዋል። በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው የይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት የማያሳፍር አስተማማኝ መሸሸጊያ ነው። ባለፈው ዓመት በ73,070 ጉባኤዎች የሚገኙት እነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በጠቅላላ 1,057,341,972 ሰዓት በወንጌላዊነት ሥራ ላይ አሳልፈዋል። ከዚህም የተነሣ 296,004 ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለማመልከት በውኃ ተጠምቀዋል። ባለፈው ነሐሴ በዩክሬይን አገር በኪየቭ ከተማ በተደረገው መለኮታዊ ትምህርት የወረዳ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ነገር አይተዋል። በይሖዋ ምስክሮች ታሪክ ውስጥ አንድ ታሪካዊ ክንውን ተመልክተዋል። ከአሁን በፊት ታይቶ የማይታወቅ መጠን ያለው የእውነተኛ ክርስቲያኖች የውኃ ጥምቀት አስመዝግበዋል። በኢሳይያስ 54:2, 3 ላይ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው የአምላክ ሕዝቦች ታይቶ የማይታወቅ የቁጥር ጭማሪ እያገኙ ነው።
5 ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ለመሆን የሚፈልጉ ተጨማሪ ሰዎች ከመዘምራኑ ቡድን ጋር ለመደባለቅ ተራቸውን እየጠበቁ ነው። ባለፈው ዓመት በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ በጠቅላላው 11,865,765 ሰዎች ተገኝተዋል። በዚህ የአገልግሎት ዓመት ብዙዎቹ ከበር ወደ በር በመሄድ የመንግሥቱን መዝሙር ለመዘመር ብቁዎች እንደሚሆኑ ተስፋ እናደርጋለን። ከፊት ለፊታችን የምንጠብቀው እንዲህ ያለው ውጤት የእውነት ጠላት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን እንዴት ያቃጥለው ይሆን!—ራእይ 12:12, 17
6, 7. አንድ ለእውነት ፍላጎት ያሳየ ሰው በይሖዋ እርዳታ ከአጋንንት ሥቃይ እንዴት እንደተላቀቀ አስረዳ።
6 ሰይጣን ሌሎች በዚያ ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት ውስጥ ተገኝተው ድምፃቸውን እንዳያሰሙ ለመከልከል ይሞክራል። ለምሳሌ በታይላንድ የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በአጋንንት የሚሠቃዩ ሆነው አግኝተዋቸዋል። ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ግን በይሖዋ እርዳታ ከዚህ ሥቃይ ተላቅቀዋል። አንድ ሰው ከጉጉት የተነሣ ጠንቋይ ቤት ከሄደ በኋላ ለአሥር ዓመታት ያህል በአጋንንት ኃይል ተይዞ ከረመ። በአንድ ቄስ እርዳታ ከአጋንንቱ ለመላቀቅ ሞክሮ ምንም ለውጥ አላየም። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ የይሖዋ ምስክር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረለትና ከአጋንንት ተጽእኖ ሊላቀቅ የሚችልበትን ብቸኛ መፍትሔ ማለትም ትክክለኛ የእውነት እውቀት ማግኘት፣ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ማድረግና በጸሎት ወደ እርሱ ምልጃ ማቅረብን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስተማረው።—1 ቆሮንቶስ 2:5፤ ኤፌሶን 4:6, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
7 ይህንን ውይይት ካደረጉ በኋላ በዚያው ሌሊት ሰውዬው በሕልሙ የሞተው አባቱ እንደ ቀድሞው ከመናፍስት ጋር መገናኘት አለብህ በማለት ሲያስፈራራው ተመለከተ። ቤተሰቡ መጎዳት ጀመረ። የያዘውን መንገድ ለመለወጥ ፈቃደኛ ባለመሆን ሰውዬው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱን ቀጠለ፤ በስብሰባም መገኘት ጀመረ። ከእነዚህ የጥናት ፕሮግራሞች በአንዱ አቅኚው ወንድም አንዳንድ ጊዜ ከመዳፋቸው ለመላቀቅ የሚሞክሩ ሰዎች ለመናፍስታዊ ድርጊት ሲገለገሉባቸው የነበሩ አንዳንድ ዕቃዎች ካሉ አጋንንቱ ጥቃት እንዲያደርሱ የሚያስችል መንገድ እንደሚከፍቱላቸው አስረዳው። ሰውዬው ለመልካም ዕድል ይረዳል ብሎ ያስቀመጠው ዘይት እንደነበረው ትዝ አለው። ሊጥለው እንደሚገባው አሁን ተረዳ። እሱን ከጣለ በኋላ ክፉ መናፍስት አላስቸገሩትም። (ከኤፌሶን 6:13ና ከያዕቆብ 4:7, 8 ጋር አወዳድር።) እርሱና ሚስቱ በጥናታቸው ጥሩ እድገት እያደረጉና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለማግኘት አዘውትረው በስብሰባ ላይ እየተገኙ ነው።
8, 9. አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ያሸነፏቸው ሌሎች እንቅፋቶች ምንድን ናቸው?
8 ሌሎች እንቅፋቶችም የምሥራቹ ድምፅ እንዳይሰማ ለማድረግ ይሞክራሉ። በጋና በደረሰው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት የተነሣ ሠራተኞች ከሥራ ይባረሩ ነበር። ኑሮ በጣም ስለ ተወደደ ለኑሮ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ማግኘት ከፍተኛ ችግር ነበር። የይሖዋ ሕዝቦች ይህንን ችግር እንዴት ተቋቋሙት? በራሳቸው ሳይሆን በይሖዋ በመመካት ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ቀን አንድ ሰው በቅርንጫፍ ቢሮው የእንግዳ መቀበያ ጠረጴዛ ላይ አንድ የታሸገ ፖስታ ትቶ ሄደ። በፖስታው ውስጥ 1,000 ብር ወይም አነስተኛ የሚባለው የአንድ ሰው የሦስት ወር ደሞዝ የሚያክል ገንዘብ ነበረበት። ፖስታው ስሙን ካልጠቀሰ ከአንድ ሰው የተላከ ስጦታ ነበር። በገንዘቡ መጠቅለያ ላይ ግን “ከሥራ ወጥቼ ነበር። ነገር ግን ይሖዋ ሌላ ሥራ ሰጠኝ። ለእርሱና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ የማቀርበው ምስጋና በጣም ታላቅ ነው። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱን ምሥራች ስብከት ሥራ ለመደገፍ አነስተኛ መዋጮ ማድረጌ ነው” የሚል ጽሕፈት ነበረበት።—ከ2 ቆሮንቶስ 9:11 ጋር አወዳድር።
9 ለይሖዋ የምስጋና መዝሙር ከሚያቀርበው ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት ጋር የሚቀላቀሉትን በስብሰባ መገኘቱ እንዲሠለጥኑ ይረዳቸዋል። (ከመዝሙር 22:22 ጋር አወዳድር።) በደቡባዊው የሆንዱራስ ክፍል ኤል ሆርዳን የተባለ አንድ ጉባኤ አለ። ይህን አነስተኛ ቡድን ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? በስብሰባዎች ለመገኘት የሚያሳዩት ታማኝነት ነው። ከጉባኤው 19 አስፋፊዎች መካከል 12ቱ በየሳምንቱ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ትልቅ ወንዝ መሻገር አለባቸው። በበጋ ወራት በወንዙ ውስጥ ያሉትን ድንጋዮች እየረገጡ ስለሚያልፉ ወንዙን ማቋረጥ አስቸጋሪ አይደለም። ይሁን እንጂ በዝናብ ወራት ሁኔታዎቹ ይለወጣሉ። በቀላሉ ይሻገሩት የነበረው ውኃ አሁን በመንገዱ ላይ የሚያገኘውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ የሚሄድ ኃይለኛ ጎርፍ ይሆናል። ይህንን እንቅፋት ለማሸነፍ ወንድሞችና እኅቶች ጥሩ ዋናተኛ መሆን አለባቸው። ወንዙን ከማቋረጣቸው በፊት ለስብሰባ የሚጠቀሙባቸውን ልብሶች በሳፋ ላይ ያስቀምጡና በላስቲክ ከረጢት ይጠቀልሉታል። ጠንካራው ዋናተኛ ሳፋውን እንደ ምልክት አድርጎ ይጠቀምበትና ቡድኑን ይመራል። በደኅና ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ ሰውነታቸውን ያደርቁና ልብሳቸውን ለባብሰው ደስ ብሏቸውና ንጹሕ ሆነው ወደ መንግሥት አዳራሹ ይደርሳሉ።—መዝሙር 40:9
ልንኖርበት የምንችል ትልቅ ምሽግ
10. በአስጨናቂ ወቅት ወደ ይሖዋ ፊታችንን መለስ ልናደርግ የምንችለው ለምንድን ነው?
10 በአጋንንት ጥቃትም ይሁን በሌላ ምክንያት ተጨንቀህ ከሆነ ይሖዋ መሸሸጊያ ሊሆንልህ ይችላል። በጸሎት ተማጸነው። ሕዝቦቹ እያቃሰቱ እንኳ የሚያሰሙትን የደከመ ድምፅ በትኩረት ከልብ ያዳምጣል። መዝሙራዊው ይህ እውነት መሆኑን ስለተረዳ እንደዚህ ብሎ ጻፈ፦ “ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፣ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ። አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም። አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ።”—መዝሙር 31:2–4
11. ይሖዋ የሚያዘጋጀው ምሽግ ጊዜያዊ ያልሆነበትን ምክንያት አስረዳ።
11 ይሖዋ ጊዜያዊ መጠለያ ሳይሆን ተረጋግተን ልንኖርበት የምንችልበትን የማይደፈር ምሽግ ያዘጋጅልናል። አመራሩና የሚሰጠው መመሪያ ሕዝቦቹን ለችግር ዳርጓቸው አያውቅም። መለኮታዊው ኃይል ሰይጣንና ተከታዮቹ የሚያዘጋጁአቸውን የተንኮል ዘዴዎች ሁሉ ያከሽፋቸዋል። (ኤፌሶን 6:10, 11) በሙሉ ልባችን በይሖዋ ከተማመንን ከሰይጣን ወጥመዶች እንድንሸሽ ይረዳናል። (2 ጴጥሮስ 2:9) ባለፉት አራት ዓመታት 35 አገሮች ለይሖዋ ምስክሮች ሥራ በራቸውን ከፍተዋል። በተጨማሪም ማኅበራዊ፣ አኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ለምሥራቹ ስብከት እንቅፋት በሆኑባቸው የዓለም ክፍሎች ወጥተው በነፃነት ይበልጥ መሥራት ወደሚቻልባቸው ቦታዎች የተዛወሩ አንዳንድ በግ መሰል ሰዎች አሉ። እንደዚህ ካሉት ቦታዎች አንዷ ጃፓን ናት።
12. በጃፓን የሚኖር አንድ አቅኚ ይሖዋን መሸሸጊያው ያደረገው እንዴት ነው?
12 ጃፓን ከውጭ አገሮች እየመጡ በጊዜያዊነት የሚሠሩ እንግዶች በብዛት ስላሉባት በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ብዙ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። ይህ የውጭ አገር ሰዎች የሚኖሩበት መስክ ምን ያህል ፍሬያማ እንደሆነ በአንድ የጃፓን ጉባኤ የሚሰበሰብ ወንድም ያጋጠመው ተሞክሮ ያስረዳል። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዶ ለማገልገል ፈለገ። ይሁን እንጂ በነበረበት ቦታ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራ ነበር። ከጓደኞቹ አንዱ እየቀለደ “የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ የምትሄድ ከሆነ እዚያ 20 ጥናቶች መምራት ይኖርብሃል” አለው። የአገልግሎት ምድቡን ተቀበለና ወደ ሂሮሽማ ሄደ። ከአራት ወር በኋላ የነበረው አንድ ጥናት ብቻ ነበር። አንድ ቀን የፖርቱጋል ቋንቋ ብቻ የሚችል አንድ ብራዚልያዊ ሰው አነጋገረ። ወንድም ከሰውዬው ጋር መነጋገር ስላልቻለ የፖርቱጋል ቋንቋ ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ ገዛ። አንዳንድ ቀላል የመግባቢያ አነጋገሮችን ካጠና በኋላ እንደገና ሰውዬውን አነጋገረው። ወንድም በፖርቱጋል ቋንቋ ሰላምታ ሲሰጠው ሰውዬው በጣም ተገረመና እየሳቀ ቤቱን ከፍቶ ወደ ውስጥ እንዲገባ ጠየቀው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ወንድም 22 ጥናቶች ይመራ ጀመር። ከእነዚህም ውስጥ 14ቱ በፖርቱጋል፣ 6ቱ በስፓንኛ 2ቱ ደግሞ በጃፓንኛ የሚመሩ ናቸው።
በልበ ሙሉነት መስበክ
13. ማንም ሰው እኛን በማሳፈር ይሖዋን እንድናገለግል ለማስገደድ መሞከር የማይገባው ለምንድን ነው?
13 የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋ መታመኛቸው እንደሆነ ሙሉ በሙሉ በማመን የመንግሥቱን መዝሙር በልበ ሙሉነት ይዘምራሉ። (መዝሙር 31:14) ይሖዋ ቃሉን ስለሚያከብርና ስለማያዋርዳቸው አያፍሩም። (መዝሙር 31:17) ዲያብሎስና አጋንንታዊ ጭፍራው ያፍራሉ። የይሖዋ ሕዝቦች ከሐፍረት ነፃ የሆነ መልእክት እንዲሰብኩ ስለተላኩ በስብከቱ የሚሳተፉት ሌሎች ሰዎች እያሳፈሩ ስለ ገፋፏቸው አይደለም። ይሖዋ ወይም ልጁ ሕዝቦቹ ይሖዋን እንዲያመልኩ የሚያነሣሷቸው በዚህ መንገድ አይደለም። ሰዎች ጥሩ የልብ ሁኔታ ሲኖራቸው ማለትም ልባቸው በእምነትና ለይሖዋ ጥሩነትና ፍቅራዊ ደግነት ባላቸው አድናቆት ሲሞላ አፋቸው እንዲናገር ይገፋፋል። (ሉቃስ 6:45) በዚህም ምክንያት በተለይ የሰዓት ሪፖርታችን የምንችለውን ያህል የሠራንበትን የሚያሳይ ከሆነ በየወሩ በአገልግሎት የምናሳልፈው ሰዓት ምንም ያህል ቢሆን ጥሩና የማያሳፍር ይሆንልናል። የመበለቲቱ ስጦታ በኢየሱስና በአባቱ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተደናቂነት አግኝቶ አልነበረምን?—ሉቃስ 21:1–4
14. ስለ አቅኚነት ሥራ ምን ሐሳብ ለመስጠት ትችላለህ? (ሠንጠረዡን ተመልከት።)
14 አቅኚ በመሆን ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የሚያገለግሉት አስፋፊዎች ቁጥራቸው እያደገ መጥቷል። ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ ባስመዘገበው ወር ላይ ቁጥራቸው 890,231 ደርሶ ነበር። ያለፈው ዓመት እድገት በዚያው ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ቁጥሩ ከ1,000,000 ይበልጥ ነበር። የሚቀጥለው ተሞክሮ በናይጄርያ የምትገኝ አንዲት እኅት እንዴት የዘወትር አቅኚ ለመሆን እንደበቃች ያሳያል። እኅት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመጨረስ በተቃረብኩበት ወቅት በይሖዋ ምስክሮች የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለተካፈሉት ተማሪዎች ምግብ ለማብሰል በተደረገው ዝግጅት ለመርዳት ሄድኩ። በዚያም ከሴት አያቴ በዕድሜ የሚበልጡ ሁለት እኅቶች አገኘሁ። በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የመጡ አቅኚዎች መሆናቸውን ሳውቅ ‘እነዚህ ሁለት እኅቶች አቅኚ መሆን ከቻሉ እኔ የማልችልበት ምክንያት ምንድን ነው?’ ብዬ ለራሴ አሰብኩ። ስለዚህ ትምህርቴን እንደጨረስኩ እኔም የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።”
15. መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት ሌሎች ሰዎች ይሖዋን መሸሸጊያቸው እንዲያደርጉት መንገድ የሚከፍትላቸው እንዴት ነው?
15 ሁሉም አስፋፊዎች አቅኚ ለመሆን ባይችሉም መመስከር ግን ይችላሉ። በቤልጅየም አንዲት የ82 ዓመት እኅት ሥጋ ለመግዛት ሄዱ። የሉካንዳ ነጋዴው ሚስት በቅርቡ በተፈጠሩት የፖለቲካ ውጣ ውረዶች በጣም መረበሿን ተመለከቱ። ስለዚህ እኅት ለገዙት ዕቃ ገንዘብ ሲከፍሉ “የይሖዋ ምስክሮች ምን ብለው ያምናሉ?” የተባለውን ትራክት በገንዘቡ መሀል አድርገው አብረው ሰጧት። እኅት በሌላ ቀን ወደ ሥጋ ቤቱ ተመልሰው ሲመጡ የሉካንዳ ነጋዴው ሚስት ምንም ጊዜ ሳታጠፋ ወዲያውኑ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ሊነሣ ስለመቻሉ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ጠየቀች። እኅት እውነተኛ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ልታገኝ የምትችለው እንዴት ነው? የተባለውን መጽሐፍ አመጡላት። ከጥቂት ቀኖች በኋላ አረጋዊቷ እኅት ወደ ሥጋ ቤቱ ጎራ ሲሉ የሉካንዳ ነጋዴው ሚስት ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዛ ቀረበች። እኅት ሴትዮዋ በጣም ስላሳዘነቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ሐሳብ አቀረቡላት፤ ሴትዮዋም ተስማማች። አሁን የሉካንዳ ነጋዴው ሚስት ለመጠመቅ ትፈልጋለች። የሉካንዳው ባለቤትስ ምን አቋም ወስዶ ይሆን? ትራክቱን ካነበበ በኋላ አሁን መጽሐፍ ቅዱስ እያጠና ነው።
‘ውድ ሀብት የሆነ መልካምነት’
16. ይሖዋ ለሕዝቦቹ የመልካምነትን ውድ ሀብት ያዘጋጀላቸው እንዴት ነው?
16 በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ይሖዋ እርሱን መሸሸጊያቸው ላደረጉ ሁሉ “አስገራሚ ፍቅራዊ ደግነት አላደረገምን?” አፍቃሪና ተንከባካቢ እንደሆነ አባት ይሖዋ ለምድራዊ ልጆቹ የመልካምነትን ውድ ሀብት አትረፍርፎላቸዋል። ልክ መዝሙራዊው እንዳለው በተመልካቾች ሁሉ ፊት ደስታን አዝንቦላቸዋል። “በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፣ ቸርነትህ እንደምን በዛች!”—መዝሙር 31:19, 21
17-19. በጋና አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ጋብቻቸውን በሕግ በማስመዝገባቸው ምን መልካም ውጤት ተገኝቷል?
17 ስለዚህ ዓለማዊ ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሐቀኞች ለመሆናቸው የዓይን ምስክሮች ናቸው። በሚያሳዩት የሐቀኝነት ጠባይም ይገረማሉ። ለምሳሌ ያህል በጋና የ96 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አንድ ሰው የጋብቻ ምዝገባ ወደሚፈጸምበት መሥሪያ ቤት ሄደው ለ70 ዓመት የቆየው ባሕላዊ ጋብቻቸው በሕግ እንዲመዘገብ ጠየቁ። የጋብቻ ምዝገባ ክፍል ኃላፊው ማመን ስላቃተው “በእርግጥ ይህን ማድረግ ይፈልጋሉን? በዚህ ዕድሜዎ!” በማለት ጠየቃቸው።
18 አዛውንቱ “ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ለመሆን እፈልጋለሁ። የዓለም ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ከሁሉም በሚበልጠው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለመካፈል እፈልጋለሁ። ይህ ሥራ ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል። የይሖዋ ምስክሮች ጋብቻን በሕግ ማስመዝገብን የሚጨምረውን የመንግሥትን ሕግ በሙሉ ይታዘዛሉ። ስለዚህ እባክህ በሕጋዊ መዝገብ ላይ ጋብቻዬን መዝግብልኝ” በማለት አብራሩለት። የምዝገባ ክፍል ኃላፊው አፉን ይዞ ምዝገባውን አከናወነላቸው። አዛውንቱ አሁን በሕግ የተመዘገበ ጋብቻ ስላገኙ ደስ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።—ከሮሜ 12:2 ጋር አወዳድር።
19 ይህ ከሆነ በኋላ የጋብቻ ምዝገባ ክፍል ኃላፊው የሰማቸውን ነገሮች እየመላለሰ ያስብባቸው ጀመር። “የይሖዋ ምስክሮች . . . ከሁሉ የሚበልጠው ሥራ . . . የዓለም ፍጻሜ . . . የአምላክ መንግሥት . . . የዘላለም ሕይወት።” የ96ቱ ዓመት አዛውንት እነዚህ ነገሮች ሁሉ ምን ትርጉም እንዳላቸው ግራ ስለገባው ጉዳዩን ይበልጥ ለመመርመርና ለማወቅ ምስክሮቹን ለማግኘት ቆርጦ ተነሣ። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ተስማምቶ ፈጣን እድገት አደረገ። ዛሬ ይህ የጋብቻ ምዝገባ ክፍል ኃላፊ የተጠመቀ ምስክር ነው። ከዚህ እንደምንረዳው ሌሎች ጥቃቅን ናቸው ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች እንኳ ሳይቀር ይሖዋን ስንታዘዝ ለእኛም ሆነ ጠባያችንን ለሚመለከቱ የዓይን ምስክሮች በቃላት ሊገለጽ የማይችል መልካም ነገር እናገኛለን።—ከ1 ጴጥሮስ 2:12 ጋር አወዳድር።
20. በማያንማር የአንዲት ወጣት እኅት ሐቀኝነት ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት ያስቻለው እንዴት ነው?
20 እውነት ሐቀኛ ሰዎች እንዲሆኑ አድርጎ የቀረጻቸው በዕድሜ ከፍ ያሉ ሰዎች በዚህ ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በማያንማር ሐቀኛ የሆነች አንዲት ወጣት እኅት አለች። እኅት 10 ልጆች ካሉት በኑሮ ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ የመጣች ናት። ጡረተኛ አባትዋ የዘወትር አቅኚ ነው። አንድ ቀን እኅት ትምህርት ቤቷ ውስጥ አንድ የአልማዝ ቀለበት አገኘችና ወዲያውኑ ለአስተማሪዋ ሰጠቻት። በሚቀጥለው ቀን ተማሪዎቹ ሲሰበሰቡ አስተማሪዋ የአልማዝ ቀለበቱ እንዴት እንደተገኘና ለባለቤቷ እንዴት እንደተመለሰ ለተማሪዎቹ ነገረቻቸው። ከዚያም ሌሎች ተማሪዎች ቢሆኑ ኖሮ ለራሳቸው ሊያስቀሩት ይችሉ እንደነበረ በማሰብ ወጣቷን እኅት በተማሪዎቹ ሁሉ ፊት እንድትቆምና ለምን ይህን እንዳደረገች ምክንያቱን እንድታስረዳ ጠየቀቻት። እኅት የይሖዋ ምስክር እንደሆነችና አምላኳ መስረቅንም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንደማይወድ አስረዳች። ይህን ስትናገር ጠቅላላው የትምህርት ቤቱ አባላት ይሰሙ ስለነበር ይህ ሁኔታ ለወጣቷ እኅታችን ለአስተማሪዎቿና ለተማሪዎቹ በሙሉ የመመስከር አጋጣሚ አስገኝቶላታል።
21. ወጣቶች በይሖዋ ላይ ሲታመኑ ጠባያቸው ይሖዋን እንዴት ያስከብረዋል?
21 በቤልጅየም አንድ አስተማሪ በአንድ ክፍል ውስጥ ሲያስተምር የይሖዋ ምስክሮችን አመስግኖ ተናገረ። ከተማሪዎቹ የአንዷን ወጣት እኅት ጠባይ ልብ ብሎ ይከታተል ነበር። እርሱም “አሁን ስለ ይሖዋ ምስክሮች ለየት ያለ አመለካከት መያዝ ጀምሬአለሁ። ከነበረኝ ጥላቻ የተነሣ ክፉ ሰዎች እንደሆኑ አድርጌ አስብ ነበር። መሠረታዊ ሥርዓቶቻቸውን እንዲጥሱ እስካልተጠየቁ ድረስ በጣም ደግ ሰዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ” በማለት ተናገረ። በየዓመቱ ብልጫ ያገኘ ተማሪ ከአስተማሪዎቹ ሽልማት ይሰጠዋል። በሥነ ምግባር ትምህርትም ብልጫ ላሳዩ ሽልማት ይሰጥ ነበር። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት እስከ ሦስተኛ ድረስ ለወጡት ጎበዝ ተማሪዎች ይህ አስተማሪ ሽልማት የሰጠው ለይሖዋ ምስክሮች ልጆች ነበር። የማይናወጥ እምነታቸው በይሖዋ ላይ የሆነ ሁሉ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ነገር ያጋጥማቸዋል።—መዝሙር 31:23
22. የመዝሙር 31 የድል አድራጊነት መደምደሚያ ምንድን ነው? በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመዝጊያ ቀኖችስ ይሖዋ እንዴት ይረዳናል?
22 መዝሙር 31 በድል አድራጊነት ስሜት ሲደመደም “ይሖዋን የምትጠባበቁ ሁላችሁ፣ በርቱ ልባችሁም ይጥና” ይላል። (መዝሙር 31:24 አዓት) ስለዚህ የሰይጣንን ዓለም የመደምደሚያ ቀኖች ስንጠባበቅ ይሖዋ እኛን ከመተው ይልቅ ወደ እኛ በጣም ይቀርባል፤ ኃይሉንም በእኛ ውስጥ ያኖራል። ይሖዋ የታመነ ነው። ቃሉንም አይለውጥም። እርሱ መሸሸጊያችን ነው። እርሱ አምባችን ነው።—ምሳሌ 18:10
ታስታውሳለህን?
◻ በልበ ሙሉነት ይሖዋን መሸሸጊያችን ልናደርገው የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት የመንግሥቱን ውዳሴ በድፍረት እየዘመረ መሆኑን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
◻ የሰይጣን ወጥመድ የይሖዋን ሕዝቦች ሊያጠምዳቸው እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ እርሱን መሸሸጊያቸው ላደረጉት ሁሉ ይሖዋ ያዘጋጀላቸው ውድ ሀብት ምንድን ነው?
[በገጽ 12-15 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የይሖዋ ምሥክሮች የ1993 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(See bound volume)
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋን መሸሸጊያቸው ያደረጉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች 4,709,889 የሚያህሉ ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት ሆነዋል!
1. ሴኔጋል
2. ብራዚል
3. ቺሊ
4. ቦሊቪያ