በዛሬው ጊዜ ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል ትክክለኛ መሠረት
በ1866 የተወለዱት ታሪክ ጸሐፊና የማኅበራዊ ጉዳዮች አጥኚ ኤች ጂ ዌልስ በ20ኛው መቶ ዘመን አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል። ሳይንሳዊ እድገት ታላቅ የደስታ ጊዜን እንደሚያመጣ ያላቸውን የጸና እምነት በጽሑፎቻቸው አብራርተዋል። በመሆኑም ኮሊየርስ ኢንሳይክሎፔድያ፣ ዌልስ ሐሳባቸውን በሰዎች ዘንድ በስፋት ለማሳወቅ ያለማቋረጥ ሲሠሩ “ገደብ የለሽ ብሩህ አመለካከት” እንደነበራቸው በማስታወስ ዘግቧል። ይሁን እንጂ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ የነበራቸው ብሩህ አመለካከት መጨለሙን ጭምር ገልጿል።
ዌልስ “ሳይንስ መልካም ነገሮችን ብቻ ሳይሆን መጥፎ ነገሮችንም እንደሚሠራ ሲገነዘቡ እምነታቸው ከዳቸውና አፍራሽ አመለካከት ወደ መያዝ አዘነበሉ” ሲል ቻምበርስ ባዮግራፊካል ዲክሽነሪ ተናግሯል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
የዌልስ እምነትና ብሩህ አመለካከት የተመሠረተው በሰው ልጅ የሥራ ስኬት ላይ ብቻ ነበር። የሰው ልጅ ያለመውን ፍጹም ሁኔታ ማምጣት እንደማይችል ሲገነዘቡ ፊታቸውን ሊያዞሩበት የሚችሉት ምንም ነገር አልነበራቸውም። ተስፋ በመቁረጣቸው ወዲያውኑ አፍራሽ አመለካከት አደረባቸው።
ዛሬ ብዙ ሰዎች በዚሁ ምክንያት ተመሳሳይ የሆነ ተሞክሮ ይገጥማቸዋል። በወጣትነታቸው ዘመን በብሩህ አመለካከት ሲፈነድቁ የነበሩ ሁሉ እየጎለመሱ ሲሄዱ ግን በአፍራሽ አመለካከት ጨለማ ውስጥ ይወድቃሉ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ወጣቶች የተለመደ የሚባለውን የሕይወት መንገድ በመተው አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም፣ ልቅ በሆነ ወሲባዊ ድርጊት እንዲሁም በሌሎች አጥፊ የአኗኗር ዘይቤዎች ይጠመዳሉ። መፍትሔው ምንድን ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተወሰዱ የሚከተሉትን ምሳሌዎች መርምርና ስላለፈው፣ ስለ አሁኑና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችለው መሠረት ምን እንደሆነ ተመልከት።
አብርሃም ብሩህ አመለካከት በመያዙ ተክሷል
በ1943 ከዘአበ አብርሃም ካራንን ለቅቆ ኤፍራጥስ ወንዝን በማቋረጥ ከነዓን ምድር ገባ። አብርሃም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን እንዴት ያለ ግሩም የሆነ ምሳሌ ትቷል!—ሮሜ 4:11
የአብርሃም የሞተው ወንድሙ ልጅ ሎጥና ቤተሰቡ ከአብርሃም ጋር ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ምድሪቱን ረሃብ በመታት ጊዜ ሁለቱ ቤተሰቦች ወደ ግብጽ ተጉዘው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይም አንድ ላይ ተመልሰዋል። በዚህን ጊዜ ሁለቱም ማለትም አብርሃምና ሎጥ ብዙ ንብረት እንዲሁም የርቢ እንስሳት ነበራቸው። በእረኞቻቸው መካከል ጥል በተነሣ ጊዜ አብርሃም ቅድሚያውን በመውሰድ እንዲህ አለ:- “እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።”—ዘፍጥረት 13:8, 9
አብርሃም በዕድሜ ታላቅ እንደመሆኑ መጠን የፈለገውን ሊያደርግ ይችል ነበር፤ እንዲሁም ሎጥ ለአጎቱ ከነበረው አክብሮት የተነሣ የአብርሃምን ምርጫ ሊቀበል ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ “[ሎጥ] ዓይኑን አነሣ፣ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ። ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ።” ይህን የመሰለ ምርጫ ካደረገ በኋላ ሎጥ ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው። ይሁን እንጂ አብርሃምስ?—ዘፍጥረት 13:10, 11
አብርሃም የሞኝነት እርምጃ በመውሰድ የቤተሰቡን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣሉ ነበርን? አልነበረም። የአብርሃም አዎንታዊ አመለካከትና የለጋስነት መንፈሱ ትልቅ ጥቅም አስገኝቶለታል። ይሖዋ ለአብርሃም እንዲህ አለው:- “ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና።”—ዘፍጥረት 13:14, 15
አብርሃም ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል ትክክለኛ መሠረት ነበረው። ‘የምድር ነገዶችም ሁሉ [በአብርሃም] ራሳቸውን የሚባርኩበት’ አንድ ታላቅ ብሔር ከአብርሃም እንደሚወጣ አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነበር። (ዘፍጥረት 12:2-4, 7) “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ” ስለምናውቅ እኛም ጭምር ሙሉ ትምክህት የምናሳድርበት ምክንያት አለን።—ሮሜ 8:28
ብሩህ አመለካከት የነበራቸው ሁለት ሰላዮች
ከ400 ዓመታት በኋላ የእስራኤል ብሔር “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር” ወደ ከነዓን ለመግባት በደፍ ላይ ነበር። (ዘጸአት 3:8፤ ዘዳግም 6:3) ሙሴ 12 አለቆችን በመምረጥ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉና ስለሚሄዱበት መንገድ እንዲሁም ስለሚገቡባቸው ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩ’ ተልእኮ ሰጣቸው። (ዘዳግም 1:22፤ ዘኁልቁ 13:2) አሥራ ሁለቱም ሰላዮች ስለ ምድሪቱ ብልጽግና የሰጡት መግለጫ አንድ ዓይነት ነበር። ይሁን እንጂ አሥሩ ሰላዮች በሕዝቡ ልብ ውስጥ ፍርሃትን ያሳደረ አፍራሽ አመለካከትን የያዘ ዘገባ አቀረቡ።—ዘኁልቁ 13:31-33
በሌላ በኩል ግን ኢያሱና ካሌብ ለሕዝቡ ብሩህ አመለካከትን የሚያንጸባርቅ መልእክት አቀረቡ፤ እንዲሁም ፍርሃታቸውን ለማስወገድ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። እነርሱ የነበራቸው አመለካከትና ያቀረቡት ዘገባ ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም ችሎታ እንዳለውና ወደ ተስፋይቱ ምድር መልሶ እንደሚያስገባቸው ሙሉ ትምክህት እንደነበራቸው ያሳየ ቢሆንም ሕዝቡን ግን ለማሳመን አልቻሉም። እንዲያውም “ማኅበሩ ሁሉ . . . በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ።”—ዘኁልቁ 13:30፤ 14:6-10
ሙሴ ሕዝቡ በይሖዋ እንዲታመኑ ቢያሳስባቸውም ለመስማት አሻፈረን አሉ። አፍራሽ የሆነውን አመለካከታቸውን የሙጥኝ በማለታቸው ጠቅላላው ብሔር ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራተተ። ከአሥራ ሁለቱ ሰላዮች ውስጥ ብሩህ አመለካከት በመያዛቸው የተካሱት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ። መሠረታዊው ችግር ምን ነበር? ሕዝቡ በራሳቸው ጥበብ መመራታቸው ያስከተለው የእምነት ማጣት ነበር።—ዘኁልቁ 14:26-30፤ ዕብራውያን 3:7-12
ዮናስ ያሳየው ማወላወል
ዮናስ የኖረው በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ዮናስ በዳግማዊ ኢዮርብዓም የንግሥና ዘመን አካባቢ ለአሥሩ የእስራኤል ነገዶች መንግሥት የይሖዋ የታመነ ነቢይ ሆኖ አገልግሎ ነበር። ሆኖም ወደ ነነዌ በመሄድ ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቅ ሲነገረው ተልእኮውን አልቀበልም አለ። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደተናገረው ዮናስ “መኮብለሉ እንደሚሻለው በማሰብ” ወደ ኢዮጴ ሄዷል። በዚያም ወደ ተርሴስ (ዘመናዊቷ ስፔይን ሳትሆን አትቀርም) በምትሄድ መርከብ ላይ ተሳፈረ። (ዮናስ 1:1-3) ዮናስ ለዚህ የሥራ ምድብ ይህን የመሰለ አፍራሽ አመለካከት ሊይዝ የቻለው ለምን እንደሆነ በዮናስ 4:2 ላይ ተብራርቷል።
ከጊዜ በኋላ ዮናስ የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ቢስማማም የነነዌ ሰዎች ንስሐ በመግባታቸው ተበሳጨ። ስለዚህ ዮናስ ተጠልሎባት የነበረችን አንዲት የቅል ተክል እንድትጠወልግና እንድትሞት በማድረግ ርኅራኄ የማሳየትን አስፈላጊነት በተመለከተ ይሖዋ ግሩም በሆነ መንገድ አስተምሮታል። (ዮናስ 4:1-8) ዮናስ ከሞተችው ተክል ይልቅ ‘ቀኛቸውንና ግራቸውን ለማይለዩት’ በነነዌ ለሚኖሩት 120,000 ሰዎች ሊያዝንላቸው ይገባ ነበር።—ዮናስ 4:11
ከዮናስ ተሞክሮ ምን ለመማር እንችላለን? ቅዱስ አገልግሎት ለአፍራሽ አመለካከት ቦታ የለውም። የይሖዋን አመራር ካስተዋልንና በሙሉ ትምክህት ከተከተልን ይሳካልናል።—ምሳሌ 3:5, 6
በመከራ ውስጥ ብሩህ አመለካከት መያዝ
ንጉሥ ዳዊት “በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ፤ ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 37:1 የ1980 ትርጉም) ዛሬ ግፍና ጠማማነት በዙሪያችን ተስፋፍቶ ስለሚገኝ ይህ ምክር ጠቃሚ መሆኑ የተረጋገጠ ነው።—መክብብ 8:11
በኃጢአተኞች ባንቀናም እንኳ ንጹሐን ሰዎች በክፉዎች እጅ ሲሰቃዩ ስንመለከት ወይም እኛ ራሳችን ግፍ ሲፈጸምብን በጣም እንበሳጫለን። እንዲያውም እነዚህን የመሳሰሉ ገጠመኞች ከባድ ሐዘን ላይ ሊጥሉን ወይም አፍራሽ አመለካከት እንድናዳብር ሊያደርጉን ይችላሉ። እንዲህ በሚሰማን ጊዜ ምን ማድረግ አለብን? በመጀመሪያ ደረጃ ክፉዎች ፈጽሞ የበቀል እርምጃ አይወሰድብንም ብለው በማሰብ ሊዝናኑ እንደማይችሉ መዘንጋት አይገባንም። መዝሙር 37 ቁጥር 2 “[ክፉዎች] እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።
በተጨማሪም ጥሩ የሆነውን ማድረጋችንን መቀጠል፣ ብሩህ አመለካከት ይዘን መቆየትና ይሖዋን መጠባበቅ እንችላለን። መዝሙራዊው ቀጥሎ እንደተናገረው “ከክፉ ሽሽ፣ መልካምንም አድርግ ለዘላለምም ትኖራለህ። እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና፣ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና።”—መዝሙር 37:27, 28
እውነተኛው ብሩህ አመለካከት ይሰፍናል!
ታዲያ ስለ ወደፊቱ ተስፋችን ምን ለማለት ይቻላል? የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው የዮሐንስ ራእይ “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር” ይነግረናል። ከእነዚህም መካከል ጦርነትን የሚያመለክተው ቀዩ ፈረስ ‘ሰላምን ከምድር እንደሚወስድ’ ተገልጿል።—ራእይ 1:1፤ 6:4
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በብሪታንያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ይህ ጦርነት ለመጨረሻ ጊዜ የሚደረግ ከፍተኛ ጦርነት ይሆናል የሚል ብሩህ አመለካከት ነበራቸው። በ1916 ብሪታንያዊው ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ዴቪድ ሎይድ ጆርጅ እውነታውን ለመሸሽ አልፈለጉም ነበር። እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ጦርነት፣ ልክ እንደሚቀጥለው ጦርነት፣ ጦርነትን ለማስቆም የሚደረግ ጦርነት ነው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሰውየው ትክክል ነበሩ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይበልጥ አውዳሚ የሆኑ መሣሪያዎችን የማምረቱን ፍጥነት ከመጨመር ሌላ ምንም ለውጥ አላመጣም ነበር። ከ50 ዓመታት በኋላም እንኳ ቢሆን ጦርነት የሚያከትምበት ጊዜ በቅርቡ የሚመጣ አይመስልም።
በዚያው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ረሃብን፣ ተላላፊ በሽታንና ሞትን ስለሚያመለክቱ ሌሎች ፈረሰኞችም እናነባለን። (ራእይ 6:5-8) እነዚህም ቢሆኑ ስለ ጊዜው የተሰጡ ተጨማሪ ምልክቶች ናቸው።—ማቴዎስ 24:3-8
እነዚህ ነገሮች አፍራሽ አመለካከት እንድንይዝ ምክንያት ሊሆኑን ይገባልን? በፍጹም አይገባም፤ ምክንያቱም ራእዩ በዚህ ላይ ሲያክል “አምባላይ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፣ አክሊልም ተሰጠው፣ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት” በማለት ይገልጻል። (ራእይ 6:2) እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድ ሰላምንና አንድነትን ለማስፈን በመጋለብ ላይ መሆኑን እንመለከታለን።a
ኢየሱስ ክርስቶስ ዕጩ ንጉሥ ሆኖ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ስለዚያች መንግሥት እንዲጸልዩ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል። ምናልባት አንተም “አባታችን ሆይ” የተባለውን ወይም የጌታን ጸሎት ተምረህ ይሆናል። በዚህ ጸሎት ላይ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣና በሰማይ ላይ የሆነው ፈቃዱ በምድር ላይም እንዲፈጸም እንጸልያለን።—ማቴዎስ 6:9-13
ይሖዋ አሁን ያለውን የነገሮች ሥርዓት ለመጠገን ከመሞከር ይልቅ በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ያስወግደዋል። በምትኩ ይላል ይሖዋ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።” በሰማያዊቷ መንግሥታዊ መስተዳድር ሥር ምድር ሰላምና ደስታ የሰፈነባት የሰው ልጆች መኖሪያ ትሆናለች። በዚያን ጊዜ ሕይወትና ሥራ የማያቋርጥ የደስታ ምንጭ ይሆናሉ። ይሖዋ “በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና” ብሏል። (ኢሳይያስ 65:17-22) የወደፊት ተስፋህን መሬት ጠብ በማይለው በዚህ ተስፋ ላይ መሠረት ካደረግህ አሁንም ሆነ ለዘላለም ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ትችላለህ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለዚህ ራእይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 16ን እባክህ ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤች ጂ ዌልስ
[ምንጭ]
Corbis-Bettmann