ምዕራፍ 10
ጋብቻ—ከአምላክ የተገኘ ስጦታ
“በሦስት የተገመደ ገመድ . . . ቶሎ አይበጠስም።”—መክብብ 4:12
1, 2. (ሀ) አዲስ ተጋቢዎች ምን ዓይነት ትዳር እንዲኖራቸው ይመኛሉ? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ላይ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
ደስተኛ የሆኑ ሙሽሮችን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሙሽሮቹ የትዳር ሕይወታቸውን ለመጀመር ጓጉተዋል፤ የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ሆኖ ይታያቸዋል። ትዳራቸው አስደሳችና ዘላቂ እንደሚሆንም ተስፋ ያደርጋሉ።
2 የሚያሳዝነው ግን ጥሩ አጀማመር ያላቸው በርካታ ትዳሮች በዚያው አይዘልቁም። ባልና ሚስት፣ ትዳራቸው ዘላቂና አስደሳች እንዲሆን የአምላክ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ አንጻር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት፦ ትዳር የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው? ትዳር ለመመሥረት ካሰብክ ጥሩ የትዳር ጓደኛ መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? ጥሩ የትዳር አጋር መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? ትዳር ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለውስ እንዴት ነው?—ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።
ትዳር ልመሥርት?
3. አንድ ሰው ደስተኛ ለመሆን የግድ ማግባት አለበት? አብራራ።
3 አንዳንዶች፣ ያላገባ ሰው ደስተኛ መሆን እንደማይችል ይሰማቸዋል። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል አይደለም። ኢየሱስ፣ ሳያገቡ መኖር ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:10-12) ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን አለማግባት አንዳንድ ጥቅሞች እንዳሉት ጠቁሟል። (1 ቆሮንቶስ 7:32-38) እርግጥ ትዳር መመሥረትን በተመለከተ ውሳኔውን ማድረግ ያለብህ አንተ ራስህ ነህ። ጓደኞችህና የቤተሰብህ አባላት ወይም ማኅበረሰቡ በዚህ ረገድ ጫና እንዲያደርጉብህ አትፍቀድ።
4. ጥሩ ትዳር የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጋብቻ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነና የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዳሉ ይናገራል። ይሖዋ የመጀመሪያው ሰው የሆነውን አዳምን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ሰውየው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም። ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ።” (ዘፍጥረት 2:18) ይሖዋ፣ ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ሚስት እንድትሆነው ለአዳም ሰጠው፤ የመጀመሪያው ሰብዓዊ ቤተሰብ የተመሠረተው በዚህ መንገድ ነበር። ጋብቻ፣ ልጆች ያለስጋት የሚያድጉበት ሁኔታ እንዲኖር ያደርጋል። ይሁን እንጂ ጋብቻ የሚመሠረተው ልጆች ለመውለድ ብቻ አይደለም።—መዝሙር 127:3፤ ኤፌሶን 6:1-4
5, 6. ትዳር ‘በሦስት እንደተገመደ ገመድ’ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
5 ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ ምክንያቱም ሁለት ሆነው የሚያከናውኑት ሥራ ጥሩ ውጤት ያስገኝላቸዋል። አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና። ይሁንና ደግፎ የሚያነሳው ሰው በሌለበት አንዱ ቢወድቅ እንዴት ይሆናል? . . . በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።”—መክብብ 4:9-12
6 ጥሩ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት ከማንም ይበልጥ የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ይሆናሉ፤ እርስ በርስ ይረዳዳሉ፣ አንዳቸው ሌላውን ያጽናናሉ እንዲሁም ከጉዳት ይጠብቃሉ። ባልና ሚስት የሚዋደዱ ከሆነ ጠንካራ ትዳር ይኖራቸዋል፤ ትዳራቸው ይበልጥ የሚጠናከረው ግን ሁለቱም ይሖዋን የሚያመልኩ ከሆነ ነው። እንዲህ ያለው ትዳር ‘በሦስት እንደተገመደ ገመድ’ ይሆናል። በሁለት ከተገመደ ገመድ ይልቅ በሦስት የተገመደ ገመድ ጠንካራ እንደሆነ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አንድ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ይሖዋ እንዲኖር ሲያደርጉ ጥምረታቸው ጠንካራ ይሆናል።
7, 8. ጳውሎስ ትዳር መመሥረትን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?
7 ሁለት ሰዎች ከተጋቡ በኋላ፣ ተፈጥሯዊ የሆነውን የፆታ ፍላጎታቸውን ማርካት ይችላሉ። (ምሳሌ 5:18) ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሚያገባው የፆታ ፍላጎቱን ለማርካት ብቻ ከሆነ የትዳር ጓደኛውን በጥበብ ላይመርጥ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው ማግባት ያለበት “አፍላ የጉርምስና ዕድሜን [ካለፈ]” በኋላ እንደሆነ የሚናገረው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዕድሜ ላይ የፆታ ስሜት ይበልጥ ያይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) በመሆኑም ይህ ስሜት እስኪረጋጋ ድረስ ትዳር አለመመሥረቱ የተሻለ ነው። አንድ ሰው ይህን ዕድሜ ካለፈ በኋላ ይበልጥ ተረጋግቶ ማሰብና የተሻለ ውሳኔ ማድረግ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 7:9፤ ያዕቆብ 1:15
8 ለማግባት እያሰብክ ከሆነ ስለ ትዳር እውነታውን ያገናዘበ አመለካከት መያዝ እንዲሁም በየትኛውም ትዳር ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መገንዘብ ይኖርብሃል። ጳውሎስ “የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) በጣም ጥሩ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት እንኳ በትዳራቸው ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። እንግዲያው ለማግባት ከወሰንክ የትዳር ጓደኛህን በጥበብ መምረጥ ይኖርብሃል።
ማንን ላግባ?
9, 10. ይሖዋን የማያገለግል ሰው ካገባን ምን ያጋጥመናል?
9 የትዳር ጓደኛ ምርጫን በተመለከተ ልብ ልንለው የሚገባ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አለ፤ ይህም “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” የሚለው ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ገበሬዎች እንስሳትን ጠምደው የሚያርሱበትን መንገድ በአእምሮው ይዞ ነው። አንድ ገበሬ በመጠንም ሆነ በጉልበት ጨርሶ የማይመጣጠኑ ሁለት እንስሳትን አንድ ላይ ጠምዶ አያርስም። እንዲህ ቢያደርግ ሁለቱም እንስሳት ይጎዳሉ። ከጋብቻ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ይሖዋን የሚያገለግል ሌላው ግን ይሖዋን የማያገለግል ከሆነ በትዳራቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “በጌታ ብቻ” እንድናገባ ይመክራል።—1 ቆሮንቶስ 7:39
10 አንዳንድ ክርስቲያኖች ብቻቸውን ሆነው ከሚቀሩ ይልቅ ይሖዋን የማያገለግል ሰው ማግባት እንደሚሻል ተሰምቷቸዋል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ችላ ማለት ብዙውን ጊዜ መከራና ሐዘን ያስከትላል። የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን እሱን ማገልገል በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ የምንሰጠው ነገር ነው። በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠውን ነገር ከትዳር አጋርህ ጋር ማድረግ አለመቻል ምን ያህል አሳዛኝ እንደሚሆን አስበው። ብዙዎች ይሖዋን የማይወድና የማያገለግል ሰው ከማግባት ይልቅ ሳያገቡ ለመኖር መርጠዋል።—መዝሙር 32:8ን አንብብ።
11. ተስማሚ የትዳር ጓደኛ መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?
11 ይህ ሲባል ግን ይሖዋን የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ለማግባት እያሰብክ ከሆነ፣ ከልብ የምትወዳትና ከአንተ ጋር የሚጣጣም ባሕርይ ያላት ሴት ምረጥ። የአንተ ዓይነት ግብ ያላት እንዲሁም አምላክን ለማገልገል ቅድሚያ የምትሰጥ ሴት እስክታገኝ ድረስ በትዕግሥት ጠብቅ። ታማኙ ባሪያ ትዳርን በተመለከተ በጽሑፎቻችን ላይ ያወጣቸውን ጠቃሚ ምክሮች ጊዜ ወስደህ አንብብ እንዲሁም አሰላስልባቸው።—መዝሙር 119:105ን አንብብ።
12. አብርሃም ለልጁ ሚስት እንደመረጠ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
12 በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ መምረጣቸው የተለመደ ነገር ነው። በእነዚህ ባሕሎች ውስጥ ወላጆች ለልጃቸው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ የሚሆነውን ሰው የመምረጥ ብቃት እንዳላቸው ይታመናል። በጥንት ዘመንም እንዲህ ዓይነት ልማድ ነበር። የአንተም ወላጆች ይህን ልማድ የሚከተሉ ከሆነ ለየትኞቹ ባሕርያት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት ሲመርጥ ትኩረት ያደረገው፣ ልጅቷ ለይሖዋ ባላት ፍቅር ላይ እንጂ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላት ቦታ ወይም በሀብቷ ላይ አይደለም።—ዘፍጥረት 24:3, 67፤ ተጨማሪ ሐሳብ 25ን ተመልከት።
ለትዳር መዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?
13-15. (ሀ) አንድ ወንድ ጥሩ ባል ለመሆን ዝግጅት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንዲት ሴት ጥሩ ሚስት ለመሆን ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
13 ትዳር ለመመሥረት እያሰብክ ከሆነ ‘ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ ነኝ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለትዳር ዝግጁ እንደሆንክ ይሰማህ ይሆናል፤ ለማንኛውም ግን፣ ለትዳር ዝግጁ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እስቲ እንመርምር። ይህን ማድረጋችን ከዚህ ቀደም ያላሰብካቸውን ነገሮች ለማስተዋል ይረዳህ ይሆናል።
14 መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችና ሚስቶች በቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ድርሻ እንዳላቸው ይናገራል። በመሆኑም ወንዶችና ሴቶች ለትዳር ዝግጅት የሚያደርጉበት መንገድ የተለያየ ነው። አንድ ወንድ ትዳር ለመመሥረት እያሰበ ከሆነ ‘የቤተሰብ ራስ ለመሆን ዝግጁ ነኝ?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያስፈልገዋል። አንድ ባል የባለቤቱንና የልጆቹን ቁሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት እንዲያሟላ ይሖዋ ይጠብቅበታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ ባል ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ቅድሚያውን ወስዶ ቤተሰቡን መምራት ይኖርበታል። ቤተሰቡን የማይንከባከብ ባል “እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እንግዲያው ለማግባት የምታስብ ከሆነ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችል አስብበት፦ “በደጅ ያለህን ሥራ አሰናዳ፤ በእርሻም ላይ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አዘጋጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤትህን ሥራ።” በሌላ አባባል ትዳር ከመመሥረትህ በፊት፣ ይሖዋ ከባሎች የሚጠብቀውን ብቃት የምታሟላ መሆንህን ቆም ብለህ ልታስብበት ይገባል።—ምሳሌ 24:27
15 ለማግባት የምታስብ ሴትም ‘ሚስት እና እናት መሆን የሚያስከትሏቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ዝግጁ ነኝ?’ ብላ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ጥሩ ሚስት ባሏንና ልጆቿን መንከባከብ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ይጠቅሳል። (ምሳሌ 31:10-31) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የሚያስቡት፣ ከትዳር አጋራቸው ስለሚያገኙት ነገር ብቻ ነው። ይሖዋ ግን እንድናስብ የሚፈልገው እኛ ለትዳር ጓደኛችን ማድረግ ስለምንችለው ነገር ነው።
16, 17. ለማግባት እያሰብክ ከሆነ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ ማሰላሰል ይኖርብሃል?
16 ትዳር ከመመሥረታችሁ በፊት ይሖዋ ለባሎችም ሆነ ለሚስቶች የሰጠውን መመሪያ አስቡበት። ባል የቤተሰቡ ራስ ነው ሲባል በቤተሰቡ ላይ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጥቃት ማድረስ ይችላል ማለት አይደለም። ጥሩ የቤተሰብ ራስ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል፤ ኢየሱስ በሥሩ ያሉትን ሰዎች ምንጊዜም የሚይዘው በፍቅርና በደግነት ነው። (ኤፌሶን 5:23) በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት የባሏን ውሳኔዎች መደገፍና ከእሱ ጋር መተባበር ምን ማለት እንደሆነ ልታስብበት ይገባል። (ሮም 7:2) ፍጹም ላልሆነ ሰው በደስታ መገዛት ትችል እንደሆነ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። ይህን ማድረግ እንደማትችል ከተሰማት ሳታገባ መቆየቷ የተሻለ ሊሆን ይችላል።
17 ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከራሳቸው ይልቅ የትዳር ጓደኛቸው ደስታ ሊያሳስባቸው ይገባል። (ፊልጵስዩስ 2:4ን አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።” (ኤፌሶን 5:21-33) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች መወደድና መከበር እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። ትዳር የተሳካ እንዲሆን ግን ወንዱ ይበልጥ የሚፈልገው የሚስቱን አክብሮት ሲሆን ሴቷ ደግሞ ከምንም በላይ የባሏን ፍቅር ማግኘት ትፈልጋለች።
18. አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጠናኑበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?
18 አንድ ወንድና አንዲት ሴት እርስ በርስ በደንብ ለመተዋወቅ የሚጠናኑበት ጊዜ አስደሳች እንደሚሆን የታወቀ ነው። የወደፊት ሕይወታቸውን አብረው ማሳለፍ ይፈልጉ እንደሆነ መወሰን እንዲችሉ በሚጠናኑበት ጊዜ ግልጽና ሐቀኛ መሆን ይኖርባቸዋል። በዚህ ወቅት አንዳቸው ለሌላው ሐሳባቸውን እንዴት እንደሚገልጹ መማር እንዲሁም አንዳቸው የሌላውን ውስጣዊ ማንነት ለማስተዋል ጥረት ማድረግ አለባቸው። የሚጠናኑት ሰዎች ይበልጥ እየተቀራረቡ ሲሄዱ አካላዊ የፍቅር መግለጫዎችን ለመጠቀም ሊፈተኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከመጋባታቸው በፊት ስሜታቸውን ከሚገልጹበት መንገድ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ይህም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም ይጠብቃቸዋል። አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር ካላቸው ራሳቸውን ይገዛሉ፤ በተጨማሪም እርስ በርስም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚያበላሽ ነገር ከመፈጸም ይቆጠባሉ።—1 ተሰሎንቄ 4:6
ትዳሬ ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
19, 20. ክርስቲያኖች ለትዳር ምን አመለካከት አላቸው?
19 በርካታ መጻሕፍትና ፊልሞች የሚደመደሙት ባለታሪኮቹ ድል ባለ አስደሳች የሠርግ ሥነ ሥርዓት ሲጋቡ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሠርግ የትዳር መጀመሪያ ብቻ ነው። የይሖዋ ዓላማ ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ነው።—ዘፍጥረት 2:24
20 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ትዳርን እንደ ዘላቂ ጥምረት አድርገው አይመለከቱትም። መጋባትም ሆነ መፋታት ለእነሱ ቀላል ነገር ነው። አንዳንዶች በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው መፍትሔው ጋብቻውን ማፍረስ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም በሦስት ስለተገመደ ጠንካራ ገመድ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እናስታውስ። እንዲህ ያለው ገመድ በጣም ቢወጠርም አይበጠስም። እኛም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ትዳራችን ዘላቂ ይሆናል። ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል።—ማቴዎስ 19:6
21. ባልና ሚስት በፍቅር ለመኖር ምን ሊረዳቸው ይችላል?
21 ሁላችንም የየራሳችን ጠንካራና ደካማ ጎን አለን። በሌሎች በተለይም በትዳር ጓደኛችን ድክመቶች ላይ ማተኮር ቀላል ነው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ግን ደስታችንን እናጣለን። በሌላ በኩል ደግሞ በትዳር ጓደኛችን ጥሩ ባሕርያት ላይ ካተኮርን አስደሳች ትዳር ይኖረናል። ሆኖም ፍጽምና በሚጎድለው የትዳር ጓደኛችን መልካም ጎን ላይ ማተኮር የሚቻል ነገር ነው? አዎ! ይሖዋ ፍጹማን እንዳልሆንን ቢያውቅም የሚያተኩረው በጥሩ ጎናችን ላይ ነው። እንዲህ ባያደርግ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ እናስብ! መዝሙራዊው “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” ብሏል። (መዝሙር 130:3) ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በትዳር ጓደኛቸው መልካም ባሕርያት ላይ በማተኮር እንዲሁም ይቅር ባይ በመሆን የይሖዋን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።—ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።
22, 23. አብርሃምና ሣራ ለባለትዳሮች ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል?
22 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ትዳራችሁ እየተጠናከረ ይሄዳል። አብርሃምና ሣራ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ አስደሳች ትዳር ነበራቸው። ይሖዋ ለአብርሃም የትውልድ ከተማውን ዑርን ለቆ እንዲወጣ ሲነግረው ሣራ ከ60 ዓመት በላይ ሳይሆናት አይቀርም። በዚህ ወቅት ምቹ የሆነ ቤቷን ትታ በድንኳን ውስጥ መኖር ምን ያህል ሊከብዳት እንደሚችል አስበው። ሣራ ግን ለባሏ ጥሩ አጋርና ጓደኛ የነበረች ሲሆን በጥልቅ ታከብረውም ነበር። በመሆኑም የአብርሃምን ውሳኔዎች ደግፋለች፤ ውሳኔዎቹ የተሳኩ እንዲሆኑም ረድታዋለች።—ዘፍጥረት 18:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:6
23 እርግጥ ነው፣ አንድ ባልና ሚስት ጥሩ ትዳር አላቸው ሲባል በመካከላቸው ጨርሶ የሐሳብ ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም። በአንድ ወቅት አብርሃም የሣራን ሐሳብ መቀበል ከብዶት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ “የምትልህን ስማ” ብሎታል። አብርሃም እንደታዘዘው ያደረገ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። (ዘፍጥረት 21:9-13) ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ባትስማሙ ተስፋ አትቁረጡ። ዋናው ቁም ነገር፣ የማትስማሙበት ነገር በሚያጋጥማችሁ ጊዜም እንኳ አንዳችሁ ሌላውን በፍቅርና በአክብሮት መያዛችሁ ነው።
24. ትዳራችን ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
24 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ደስተኛ ባለትዳሮች ይገኛሉ። አንተም ለማግባት እያሰብክ ከሆነ የትዳር ጓደኛ መምረጥ፣ በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች አንዱ መሆኑን አስታውስ። ትዳር በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነገር ስለሆነ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግክ የትዳር ጓደኛህን በጥበብ መምረጥ፣ ለትዳር ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም ይሖዋን የሚያስከብር ጠንካራና በፍቅር የተሞላ ትዳር መመሥረት ትችላለህ።