“በራስህ ማስተዋል አትደገፍ”
“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ።”—ምሳሌ 3:5
1, 2. (ሀ) ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? (ለ) የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ወይም ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ሲያጋጥሙን አሊያም ፈተናዎችን ለመቋቋም በምናደርገው ትግል መታመን ያለብን በማን ነው? ለምንስ?
ሲንትያa የምትሠራበት ድርጅት የንግድ እንቅስቃሴውን በመቀነሱ የተወሰኑ ሠራተኞች ከሥራ ተባረዋል። በመሆኑም ሲንትያ ነገ ተመሳሳይ ዕጣ ይደርስብኛል የሚል ስጋት አድሮባታል። ከሥራ ብትባረር ምን ይውጣታል? ወርኃዊ ወጪዎቿንስ እንዴት መሸፈን ትችላለች? ፓሚላ የተባለች አንዲት እህት ደግሞ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውራ ማገልገል ትፈልጋለች፤ ታዲያ ይህን ማድረግ ይኖርባት ይሆን? ሳሙኤል የተባለን አንድ ወጣት ያስጨነቀው ነገር ደግሞ ለየት ያለ ነው። ይህ ወጣት በልጅነቱ የብልግና ምስሎችን ይመለከት ነበር። አሁን በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ወደ ቀድሞ ልማዱ የመመለስ ከባድ ፈተና አጋጥሞታል። ታዲያ የብልግና ምስሎችን እንዲመለከት የሚገፋፋውን ስሜት መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው?
2 የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ወይም ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ሲያጋጥሙህ አሊያም ፈተናዎችን ለመቋቋም በምታደርገው ትግል የምትታመነው በማን ነው? ሙሉ በሙሉ በራስህ ማስተዋል ትደገፋለህ? ወይስ “የከበደህን ነገር” በይሖዋ ላይ ትጥላለህ? (መዝ. 55:22) መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው” ይላል። (መዝ. 34:15) በመሆኑም በፍጹም ልባችን በይሖዋ መታመናችንና በራሳችን ማስተዋል አለመደገፋችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ምሳሌ 3:5
3. (ሀ) በፍጹም ልብ በይሖዋ መታመን ምንን ይጨምራል? (ለ) አንዳንዶች በራሳቸው ማስተዋል የሚታመኑት ለምን ሊሆን ይችላል?
3 በፍጹም ልብ በይሖዋ መታመን ነገሮችን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማለትም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ማድረግን ይጨምራል። ለዚህ ቁልፍ የሆነው ነገር የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ያለማቋረጥ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ነው። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን ለብዙዎች ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሊን የተባለች አንዲት ክርስቲያን “በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ለመማር ያልተቋረጠ ትግል ማድረግ ጠይቆብኛል” በማለት በግልጽ ተናግራለች። በይሖዋ መታመን አስቸጋሪ የሆነባት ለምንድን ነው? ሊን እንዲህ ብላለች፦ “ከአባቴ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረንም። እናቴም ብትሆን ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ፍላጎቴን ለማሟላት ያን ያህል ጥረት አታደርግም ነበር። በዚህም የተነሳ ገና በልጅነቴ የራሴን ሕይወት መምራት ጀመርኩ።” ሊን ያደገችበት መንገድ በማንም ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳትታመን አድርጓታል። በተጨማሪም አንድ ሰው ያለው ችሎታና ያገኘው ስኬት በራሱ እንዲተማመን ሊያደርጉት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ሽማግሌ ባለው ተሞክሮ የሚመካ ከሆነ በቅድሚያ አምላክን በጸሎት ሳይጠይቅ ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን ሊነሳሳ ይችላል።
4. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
4 ይሖዋ ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ልባዊ ጥረት እንድናደርግና ማንኛውንም ነገር ስናደርግ የእሱን ፈቃድ ከግምት ውስጥ እንድናስገባ ይፈልጋል። ታዲያ የሚያስጨንቀንን ነገር በእሱ ላይ መጣልንና አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመወጣት የበኩላችንን ጥረት ማድረግን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ የምንችለው እንዴት ነው? ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል? ፈተናዎችን ለመቋቋም ትግል በምናደርግበት ጊዜ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቅዱስ ጹሑፋዊ ምሳሌዎችን በመመርመር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን።
የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን
5, 6. ሕዝቅያስ፣ የአሦር ንጉሥ ለሰነዘረበት ዛቻ ምን ምላሽ ሰጠ?
5 መጽሐፍ ቅዱስ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስን አስመልክቶ “ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ” ይላል። አዎ፣ ‘ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ታምኗል።’ (2 ነገ. 18:5, 6) የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የጦር መሪውን ጨምሮ ተወካዮቹን ከታላቅ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በላከ ጊዜ ሕዝቅያስ ምን አደረገ? ኃያሉ የአሦር ሠራዊት ቀደም ሲል በርካታ የተመሸጉ የይሁዳ ከተሞችን በቁጥጥሩ ሥር አውሏል፤ አሁን ደግሞ ዓይኑን በኢየሩሳሌም ላይ ጥሏል። ሕዝቅያስ ወደ ይሖዋ ቤት በመሄድ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ “አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ፣ ከእጁ አድነን።”—2 ነገ. 19:14-19
6 ሕዝቅያስ ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። እንዲያውም ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ከመሄዱ በፊት ሕዝቡ ለሰናክሬም ዛቻ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳይሰጥ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። በተጨማሪም ሕዝቅያስ ምክር ለማግኘት ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ መልእክተኞችን ልኮ ነበር። (2 ነገ. 18:36፤ 19:1, 2) ሕዝቅያስ ማድረግ የሚችለውን ትክክለኛ እርምጃ ወስዷል። በዚህ ወቅት፣ ከግብፅ ወይም ከሌሎች ጎረቤት አገሮች እርዳታ በመጠየቅ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የማይስማማ መፍትሔ ለማግኘት አልሞከረም። ሕዝቅያስ በራሱ ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በይሖዋ ታምኗል። የይሖዋ መልአክ 185,000 የአሦር ወታደሮችን በገደለ ጊዜ ሰናክሬም ሸሽቶ ወደ ነነዌ ተመለሰ።—2 ነገ. 19:35, 36
7. ሐና እና ዮናስ ካቀረቡት ጸሎት ምን የሚያጽናና ሐሳብ ማግኘት እንችላለን?
7 የሌዋዊው የሕልቃና ሚስት ሐና፣ ልጅ መውለድ ባለመቻሏ ምክንያት በተጨነቀች ጊዜ በይሖዋ ታምና ነበር። (1 ሳሙ. 1:9-11, 18) ነቢዩ ዮናስ ከትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ የወጣው የሚከተለውን ጸሎት ካቀረበ በኋላ ነው፦ “ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከመቃብሩም ጥልቅ ርዳታን ፈልጌ ተጣራሁ፤ አንተም ጩኸቴን ሰማህ።” (ዮናስ 2:1, 2, 10) ያለንበት ሁኔታ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ይሖዋ እንዲረዳን “ልመና” ማቅረብ እንደምንችል ማወቃችን በጣም የሚያጽናና ነው!—መዝሙር 55:1, 16ን አንብብ።
8, 9. ሕዝቅያስ፣ ሐና እና ዮናስ በሚጸልዩበት ጊዜ የትኞቹ ጉዳዮች እንዳሳሰቧቸው ገልጸዋል? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
8 ሕዝቅያስ፣ ሐና እና ዮናስ የተዉት ምሳሌ የሚያስጨንቅ ነገር አጋጥሞን በምንጸልይበት ጊዜ መርሳት የሌለብንን ነገር በተመለከተም ግሩም ትምህርት ይሰጠናል። ሦስቱም፣ አስቸጋሪ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ ስሜታዊ ሥቃይ ደርሶባቸው ነበር። ያም ሆኖ ካቀረቡት ጸሎት መረዳት እንደምንችለው ያሳሰባቸው የራሳቸው ሁኔታ ወይም ከችግራቸው መገላገላቸው ብቻ አልነበረም። ከምንም በላይ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የአምላክ ስም፣ የእሱ አምልኮና ፈቃዱን የመፈጸሙ ጉዳይ ነበር። ሕዝቅያስ በይሖዋ ስም ላይ ይሰነዘር በነበረው ነቀፋ እጅግ አዝኖ ነበር። እንዲሁም ሐና በጣም የጓጓችለትን ልጅ፣ ሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን እንዲያገለግል ለመስጠት ቃል ገብታለች። ዮናስም ቢሆን “የተሳልሁትንም እሰጣለሁ” በማለት ተናግሯል።—ዮናስ 2:9
9 ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመገላገል ስንጸልይ ውስጣዊ ዝንባሌያችን ምን እንደሆነ መመርመራችን የጥበብ አካሄድ ነው። በዋነኝነት የሚያሳስበን ከችግሩ መገላገላችን ነው? ወይስ ይሖዋንና የእሱን ዓላማ ግምት ውስጥ እናስገባለን? የሚደርሱብን ችግሮች ሳናውቀው በራሳችን ጉዳይ ብቻ እንድንዋጥ ሊያደርጉንና መንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳናተኩር በቀላሉ ሊጋርዱን ይችላሉ። አምላክ እንዲረዳን ስንጸልይ ስለ ይሖዋ ማለትም ስለ ስሙ መቀደስ እና ስለ ሉዓላዊነቱ መረጋገጥ መጥቀሳችንን መዘንጋት የለብንም። እንዲህ ማድረጋችን እኛ የጠበቅነው ዓይነት ምላሽ ባናገኝም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። አምላክ ጸሎታችንን የሚመልስልን ሁኔታውን ተቋቁመን እንድንኖር የሚያስችል ኃይል በመስጠት ሊሆን ይችላል።—ኢሳይያስ 40:29ን እና ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።
ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ሲያጋጥሙን
10, 11. ኢዮሳፍጥ ምን መወሰን እንዳለበት ግራ በገባው ጊዜ ምን አደረገ?
10 በሕይወትህ ውስጥ ውሳኔ የሚያሻው ከባድ ነገር ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? ምናልባትም የምትፈልገውን ውሳኔ ካደረግህ በኋላ ይሖዋ ይህን ውሳኔህን እንዲያሳካልህ ትጸልይ ይሆን? የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮሳፍጥ የሞዓባውያንና የአሞናውያን ጥምር ጦር ሊወጋው ሲመጣ ምን እንዳደረገ እንመልከት። የይሁዳ መንግሥት ይህን ጦር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አልነበረውም። ታዲያ ኢዮሳፍጥ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን?
11 መጽሐፍ ቅዱስ “ኢዮሣፍጥም እጅግ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወሰነ” ይላል። በተጨማሪም በይሁዳ ሁሉ ጾም አወጀ፤ እንዲሁም “የእግዚአብሔ[ር]ን ርዳታ” ለመጠየቅ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰበሰበ። ከዚያም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ ፊት ቆሞ ጸለየ። ኢዮሳፍጥ ያቀረበው ልመና በከፊል እንዲህ ይላል፦ “አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።” እውነተኛው አምላክ የኢዮሳፍጥን ጸሎት በመስማት ሕዝቡን ተአምራዊ በሆነ መንገድ አዳነ። (2 ዜና 20:3-12, 17) እኛስ፣ ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ሲያጋጥሙን በተለይ ደግሞ መንፈሳዊነታችንን የሚነኩ በሚሆኑበት ጊዜ በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በይሖዋ መታመን አይኖርብንም?
12, 13. ውሳኔ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ንጉሥ ዳዊት ምን ምሳሌ ትቷል?
12 በቀላሉ እልባት ልንሰጠው እንደምንችል የሚሰማን አንድ ችግር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ምናልባት ካለን ልምድ በመነሳት በቀላሉ መፍትሔ ልናገኝለት እንደምንችል ይሰማን ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት ያጋጠመውን ሁኔታ መመርመራችን በዚህ ረገድ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። አማሌቃውያን በጺቅላግ ከተማ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር የዳዊትን ጨምሮ አብረውት ያሉትን ሰዎች ሚስቶችና ልጆች ማርከው ይዘው ሄዱ። ዳዊት “ይህን ወራሪ ሰራዊት ልከተለውን?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም “በእርግጥ ትደርስባቸዋለህ፤ ምርኮውንም ትመልሳለህ፤ ተከተል” ሲል መለሰለት። ዳዊት ይሖዋን በመታዘዝ “አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ።”—1 ሳሙ. 30:7-9, 18-20
13 አማሌቃውያን ወረራ ካካሄዱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን እስራኤልን ሊወጉ መጡ። በዚህ ጊዜም ዳዊት ይሖዋን በመጠየቅ ግልጽ የሆነ መልስ አገኘ። ይሖዋ “ሂድ፤ በእርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። (2 ሳሙ. 5:18, 19) ብዙም ሳይቆይ ፍልስጤማውያን እንደገና ዳዊትን ሊወጉ መጡ። በዚህ ጊዜ ዳዊት ምን ያደርግ ይሆን? ‘ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኛል፤ ከዚህ ቀደም እንዳደረግኩት እነዚህን የአምላክ ጠላቶች ሄጄ ልውጋቸው’ ብሎ ያስብ ይሆን? ወይስ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠው ይጠይቃል? ዳዊት ከዚህ በፊት ባጋጠመው ሁኔታ ላይ ብቻ ተመርኩዞ እርምጃ ለመውሰድ አልሞከረም። በዚህ ጊዜም ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። መቼም ዳዊት ይህን በማድረጉ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! ምክንያቱም በዚህ ወቅት አምላክ የሰጠው መመሪያ ከቀድሞ የተለየ ነበር። (2 ሳሙ. 5:22, 23) እኛም ከዚህ በፊት የደረሰብን ዓይነት ሁኔታ ወይም ችግር ሲያጋጥመን ባለን የሕይወት ተሞክሮ ላይ ብቻ እንዳንታመን መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ኤርምያስ 10:23ን አንብብ።
14. ኢያሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች ከገባዖናውያን ጋር በተያያዘ ካደረጉት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
14 ልምድ ያካበቱ ሽማግሌዎችም እንኳ ሳይቀሩ ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን በመሆኑ ውሳኔ ስናደርግ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት እንዳለብን መርሳት አይኖርብንም። ብልሃተኞቹ ገባዖናውያን ራሳቸውን በመለወጥ ከሩቅ ቦታ እንደመጡ ለማስመሰል በሞከሩ ጊዜ የሙሴ ተተኪ የሆነው ኢያሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች ምን እንዳደረጉ ተመልከት። ኢያሱም ሆነ ሽማግሌዎቹ ይሖዋን ሳይጠይቁ ከገባዖናውያን ጋር በሰላም ለመኖር ቃል ኪዳን አደረጉ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የተደረገውን ስምምነት ደግፎታል፤ ያም ቢሆን መመሪያ አለመጠየቃቸው ትክክል ባለመሆኑ ዘገባው ለእኛ ትምህርት እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል።—ኢያሱ 9:3-6, 14, 15
ፈተናዎችን ለመቋቋም ስንታገል
15. ፈተናን ለመቋቋም ጸሎት አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ አብራራ።
15 ‘የኃጢአት ሕግ’ በአካል ክፍሎቻችን ውስጥ ስለሚገኝ የኃጢአት ዝንባሌን ለመዋጋት ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይኖርብናል። (ሮም 7:21-25) ሆኖም በትግሉ አሸናፊዎች መሆን እንችላለን። እንዴት? ኢየሱስ ፈተናዎችን ለመቋቋም ጸሎት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 22:40ን አንብብ።) ወደ አምላክ ከጸለይን በኋላም መጥፎ ምኞቶችና ሐሳቦች ወደ አእምሯችን እየመጡ የምንቸገር ከሆነ እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ‘አምላክን ያለማሰለስ መለመን’ ይኖርብናል። ይሖዋም “ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና” እንደሚሰጥ ቃል ገብቶልናል። (ያዕ. 1:5) በተጨማሪም ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል [በመንፈሳዊ] የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል።”—ያዕ. 5:14, 15
16, 17. ፈተናዎችን ለመቋቋም እርዳታ በምንጠይቅበት ጊዜ የተሻለ የሚሆነው መቼ ብንጸልይ ነው?
16 ፈተናዎችን ለመቋቋም ጸሎት ወሳኝ ቢሆንም በትክክለኛው ጊዜ የመጸለይን አስፈላጊነት መገንዘብ ይኖርብናል። በምሳሌ 7:6-23 ላይ የተገለጸውን ወጣት እንመልከት። ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ የሥነ ምግባር ብልግና የምትፈጽም ሴት እንደምትኖርበት ወደሚያውቀው አካባቢ መጓዝ ጀመረ። ይህችን ሴት ካገኛት በኋላ በሚያግባባ አነጋገሯና በለሰለሰ አንደበቷ ስለተታለለ ለእርድ እንደሚነዳ በሬ ሳያንገራግር ተከተላት። ለመሆኑ ይህ ወጣት ወደዚያ አካባቢ የሄደው ለምንድን ነው? ወጣቱ “ማስተዋል የጐደለው” በሌላ አባባል ብስለት የሌለው በመሆኑ ከመጥፎ ምኞቶቹ ጋር እየታገለ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 7:7) ይህ ወጣት ይበልጥ የሚጠቀመው መቼ ቢጸልይ ነበር? ፈተናው ውስጥ ባለበት በማንኛውም ጊዜ ቢሆን መጸለዩ ጥቅም እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እሷ በምትገኝበት መንገድ የመሄድ ሐሳብ ወደ አእምሮው በመጣ ጊዜ ቢጸልይ የተሻለ ነበር።
17 በዛሬው ጊዜም፣ አንድ ሰው የብልግና ምስሎችን ላለመመልከት ከፍተኛ ትግል እያደረገ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ሰው የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ፎቶዎችና ፊልሞች እንደሚገኙበት የሚያውቀውን አንድ የኢንተርኔት ድረ ገጽ እየቃኘ ነው እንበል። ታዲያ የዚህ ሰው ሁኔታ በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ ከተጠቀሰው ወጣት ጋር የሚመሳሰል አይደለም? እንዲህ ባለ መንገድ ላይ ጉዞ መጀመር በጣም አደገኛ ነው! አንድ ሰው የብልግና ምስሎችን እንዲመለከት የሚገፋፋውን ስሜት መቋቋም ከፈለገ እንዲህ ያሉ ምስሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች የመቃኘት ሐሳብ ገና ወደ አእምሮው ሲመጣበት ምኞቱን ማሸነፍ እንዲችል በጸሎት የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ አለበት።
18, 19. (ሀ) መጥፎ ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋንን ስሜት መቋቋም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም ይህን ፈተና በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው? (ለ) ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
18 መጥፎ ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋን ስሜት መቋቋምም ሆነ መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋ ፍላጎት ከመንፈስ ፍላጎት ጋር፣ የመንፈስ ፍላጎት ደግሞ ከሥጋ ፍላጎት ጋር አይጣጣምም” በማለት ጽፏል። ስለሆነም ‘ማድረግ የምንፈልገውን አናደርግም።’ (ገላ. 5:17) ይህን ፈተና ለመወጣት ከፈለግን መጥፎ ሐሳቦች ገና ወደ አእምሯችን ሲመጡ ወይም መጥፎ ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋን ስሜት ብቅ ሲል መጸለይና ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። የሚደርስብን ፈተና “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ” ስላልሆነ በይሖዋ እርዳታ ለእሱ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንችላለን።—1 ቆሮ. 10:13
19 ምናልባት አንድ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞን ወይም ውሳኔ የሚያሻው ከባድ ጉዳይ ተጋርጦብን አሊያም አንድን ፈተና ለመቋቋም እየታገልን ይሆናል፤ ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ሊረዳን የሚችል ድንቅ ስጦታ ይኸውም ውድ የሆነውን የጸሎት መብት ሰጥቶናል። መጸለያችን በይሖዋ እንደምንታመን ያሳያል። በተጨማሪም አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ሁልጊዜ መጠየቅ ይኖርብናል፤ ይህ መንፈስ ደግሞ ይመራናል እንዲሁም ያበረታናል። (ሉቃስ 11:9-13) እንግዲያው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በይሖዋ እንታመን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
ታስታውሳለህ?
• በይሖዋ በመታመን ረገድ ከሕዝቅያስ፣ ከሐና እና ከዮናስ ምን እንማራለን?
• ዳዊትና ኢያሱ የተዉት ምሳሌ ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ሲያጋጥሙን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላው እንዴት ነው?
• ፈተናዎችን ለመቋቋም ይበልጥ ጥሩ የሚሆነው መቼ ብንጸልይ ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈተናዎችን በመቋቋም ረገድ ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ብንጸልይ ነው?