በአምላክ ጽድቅ ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር
“እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ለአንተ ዛሬ እነሆ አስታወቅሁህ።”—ምሳሌ 22:19
1, 2. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በይሖዋ የሚታመኑት ለምንድን ነው? (ምሳሌ 22:19) (ለ) አንዳንድ ግለሰቦች በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠንከር እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ተባርከዋል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መንፈሳዊ “ምግባቸውን በጊዜው” ይሰጣቸዋል። (ማቴዎስ 24:45) ያገኙት እውቀት በአምላክ ላይ ለመታመን የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይሰጣቸዋል። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ደረጃ በይሖዋና በጽድቁ ላይ አስደናቂ የሆነ እምነት ያሳያሉ።
2 ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ አንዳንድ ምሥክሮች እንዲህ ያለውን በአምላክ ላይ የመታመን መንፈስ ማጎልበት የሚያስፈልጋቸው ይመስላል። አንዳንድ ጊዜ ማኅበሩ በጽሑፎቹ ላይ ያወጣቸውን ማብራሪያዎች የሚጠራጠሩ ሰዎች የሚጽፏቸው ደብዳቤዎች ይደርሱታል። እነዚህ ጥርጣሬዎች ምናልባት ቀደም ሲል በነበረን ማስተዋል ላይ ለተደረጉ ማስተካከያዎች የተሰማቸውን ስሜት ወይም ጠያቂው በተለይ ስሜታዊ በሆነ መንገድ የተነካባቸውን ጉዳዮች የሚያወሱ ሊሆኑ ይችላሉ።—ከዮሐንስ 6:60, 61 ጋር አወዳድር።
3. ይሖዋን በታማኝነት በሚያገለግሉት ላይ እንኳ ምን ሊደርስ ይችላል? ለምንስ?
3 እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ መክብብ 9:11 ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች እውነት መሆናቸውን ይገነዘባሉ:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል [“አጋጣሚ፣” NW] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” ሰፋ ባለ ወይም መንፈሳዊ በሆነ መንገድ ይህ እውነት መሆኑ የሚረጋገጠው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ፈጣኖች የነበሩ፣ ለእውነት ጥብቅና በመቆም በኩል ኃይለኞች የነበሩ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ጠቢባን የነበሩና ትክክለኛ እውቀትን በመከታተል በኩል ቀናተኞች የነበሩ ክርስቲያኖችን እናውቅ ይሆናል። ሆኖም “ጊዜና አጋጣሚ” በፈጠረው ምክንያት አንዳንዶች ባጋጠማቸው አደጋ ወይም በዕድሜ መግፋት አቅማቸው የተገደበ መሆኑን ይመለከቱ ይሆናል። ሞትን ሳይቀምሱ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም መግባት ስለመቻላቸው ያስቡ ይሆናል።
4, 5. ክርስቲያኖች በይሖዋ ጽድቅ ላይ ለመጠራጠር የሚያበቃ ምንም ምክንያት የሌላቸው ለምንድን ነው?
4 አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛውን በሞት ማጣቱ የሚያስከትልበት ሥቃይና የሃዘን ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነው። አንድ ላይ ሆነው ለዓመታት እንዲያውም ለአሥርተ ዓመታት ይሖዋን አገልግለው ሊሆን ይችላል። በሕይወት ያለው የትዳር ጓደኛ ሞት የጋብቻን ሰንሰለት እንደሚበጥስ ያውቃል።a (1 ቆሮንቶስ 7:39) ስለዚህ እምነቱ እየሟሸሸ እንዳይሄድ ለመከላከል ስሜቶቹን መቆጣጠር ይኖርበታል።—ከማርቆስ 16:8 ጋር አወዳድር።
5 የትዳር ጓደኛ፣ የወላጅ፣ የልጅ ወይም የቅርብ ክርስቲያን ወዳጅ ሞት በይሖዋ ጽድቅ ላይ ለመታመን የሚያስችል አጋጣሚ አድርገን መመልከቱ ምንኛ ጥበብ ነው! የምንወደውን ሰው በሞት ብናጣም እንኳ ይሖዋ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደማያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በሕይወት ተርፎም ሆነ በትንሣኤ አማካኝነት የዘላለምን ሕይወት የሚያገኝ ማንኛውም ሰው ደስተኛ እንደሚሆን ልንተማመን እንችላለን። መዝሙራዊው ስለ አምላክ እንዲህ ብሏል:- “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ። እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።”—መዝሙር 145:16-19
የደረሰብን መከራ ተገቢ እንዳልሆነ ሲሰማን
6, 7. (ሀ) ባለፉት ጊዜያት መከራ የተቀበሉ አንዳንድ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ የተለየ ማስተዋል ሊኖራቸው የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ባለፉት ጊዜያት እንዲህ የመሰለ መከራ እንዲደርስ መፍቀዱ ጽድቅ እንዳልሆነ አድርገን ልንመለከተው የማይገባን ለምንድን ነው?
6 በቀደሙት ጊዜያት አንዳንድ ምሥክሮች ከሕሊናቸው የተነሳ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መከራ ደርሶባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን በእነዚያ ነገሮች ለመካፈል ሕሊናቸው ፈቅዶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከዓመታት በፊት በተወሰኑ የሲቪል አገልግሎቶች ውስጥ ለመካፈል ፈቃደኞች አልነበሩ ይሆናል። አሁን ግን አንድ ወንድም በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ያለውን ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ሳይጥስ በሕሊናው በመመራት እንደነዚህ ባሉ ተግባሮች መካፈል እንደሚችል ይሰማው ይሆናል።
7 አንድ ሰው ዛሬ ያለ ምንም ችግር ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ነገሮች በወቅቱ አላደርግም በማለቱ ምክንያት ይሖዋ መከራ እንዲደርስበት መፍቀዱ ጽድቅ እንዳልሆነ ይሰማዋልን? ይህን በመሰለ ሁኔታ ሥር ያለፉ በርካታ ሰዎች እንደዚያ አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ጥብቅ አቋም በመያዝ በአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ በተነሣው ክርክር ከማን ጎን እንደወገኑ ግልጽ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ለማሳየት አጋጣሚ በማግኘታቸው ይደሰታሉ። (ከኢዮብ 27:5 ጋር አወዳድር።) አንድ ሰው በሕሊናው ተመርቶ ከይሖዋ ጎን ለመቆም የጸና አቋም በመውሰዱ ቁጭት እንዲሰማው የሚያደርግ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? የተረዷቸውን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች በታማኝነት በመደገፋቸው ወይም ሕሊና ለሚሰጠው ጥቆማ ምላሽ በመስጠታቸው የይሖዋ ወዳጅ የመሆን ብቃት አስገኝቶላቸዋል። በእርግጥም አንድ ሰው ሕሊናን ከሚረብሽ ወይም ምናልባት ሌሎችን ከሚያደናቅፍ አካሄድ መራቁ ጥበብ ነው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የተወልንን ምሳሌ ልናስብ እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 8:12, 13፤ 10:31-33
8. ቀደም ሲል ሕጉን ይጠብቁ የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የይሖዋን ጽድቅ የሚጠራጠሩበት ምንም ምክንያት የሌላቸው ለምንድን ነው?
8 አይሁዳውያን ይሖዋን ለማስደሰት አሥሩን ትእዛዛትና የተለያዩ ሕግጋት ያቀፈውን ተጨማሪ 600 ሕጎችን መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊው ዝግጅት ውስጥ ይሖዋን ለማገልገል ለእነዚህ ሕጎች መታዘዙ አስፈላጊ መሆኑ አበቃ። በሥጋ አይሁዳውያን የሆኑትም እንኳ እነዚህን ሕጎች መታዘዝ አያስፈልጋቸውም። ከእነዚህም ውስጥ ስለ ግዝረት፣ ሰንበትን ስለ መጠበቅ፣ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ስለ ማቅረብና አንዳንድ የአመጋገብ ሥርዓተ ገደቦችን ስለ ማክበር የሚናገሩ ሕጎች ይገኙባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:19፤ 10:25፤ ቆላስይስ 2:16, 17፤ ዕብራውያን 10:1, 11-14) ሐዋርያቱን ጨምሮ ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዳውያን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ እንዲታዘዙ ይጠበቅባቸው ከነበሩት ሕጎች ነፃ ወጥተዋል። አምላክ ከጊዜ በኋላ አላስፈላጊ የሚሆኑ ነገሮችን እንዲጠብቁ ጠይቋቸው የነበረ መሆኑ ዝግጅቱ ጻድቅ አልነበረም ብለው እንዲያጉረመርሙ አድርጓቸዋልን? የለም፣ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ሰፊ ማስተዋል በማግኘታቸው ተደስተዋል።—ሥራ 16:4, 5
9. አንዳንድ ምሥክሮችን በተመለከተ እውነት የሆነው ነገር ምንድን ነው? ሆኖም የሚቆጩበት ምክንያት የሌላቸው ለምንድን ነው?
9 በዚህ ዘመንም ማድረግ ስላለባቸውና ስለሌለባቸው ነገሮች ጥብቅ አቋም የነበራቸው አንዳንድ ምሥክሮች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ከሌሎች ይልቅ የበለጠ መከራ ተቀብለዋል። ከጊዜ በኋላ ያገኙት ተጨማሪ እውቀት ለነገሮች ያላቸውን አመለካከት እንዲያሰፉ ረድቷቸዋል። ቀደም ሲል ከሕሊናቸው ጋር ተስማምተው መኖራቸው ተጨማሪ መከራ ያስከተለባቸው ቢሆንም እንዲቆጩ የሚያደርጋቸው ምክንያት የላቸውም። ለይሖዋ ታማኞች በመሆን መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች መሆናቸውና ‘ለምሥራቹ ሲሉ ሁሉን ማድረጋቸው’ በእርግጥ የሚያስመሰግናቸው ነው። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ይባርካል። (1 ቆሮንቶስ 9:23፤ ዕብራውያን 6:10) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፣ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል” በማለት ማስተዋል የሞላበት ነገር ተናግሯል።—1 ጴጥሮስ 2:20
ከዮናስ መማር
10, 11. ዮናስ (ሀ) ወደ ነነዌ እንዲሄድ በታዘዘ ጊዜ (ለ) አምላክ የነነዌን ሰዎች ሳያጠፋ በቀረ ጊዜ በይሖዋ እንዳልታመነ ያሳየው እንዴት ነበር?
10 ዮናስ ወደ ነነዌ እንዲሄድ በታዘዘ ጊዜ ይሖዋ በእሱ ላይ ለነበረው እምነት አድናቆት እንደሌለው አሳይቷል። ዮናስ ለመታዘዝ እምቢተኛ በመሆኑ አስፈሪ መከራ ከደረሰበት በኋላ ወደ አእምሮው ተመለሰ፣ ስህተቱን ተገነዘበ፣ በባዕድ አገር እንዲሠራ የተሰጠውን የሥራ ምድብ ተቀበለ እንዲሁም የነነዌ ሰዎች ካንዣበበባቸው ጥፋት እንዲያመልጡ አስጠነቀቀ። ከዚያም ያልተጠበቀ ነገር ተፈጸመ:- የነነዌ ሰዎች ባሳዩት የንስሐ መንፈስ ምክንያት ይሖዋ እነርሱን ከማጥፋት ታቀበ።—ዮናስ 1:1–3:10
11 ዮናስ ምን ምላሽ ሰጠ? የተሰማውን ቅሬታ ለአምላክ በጸሎት ገለጸ። ቅሬታ እንዲሰማው ያደረገው ነገር ‘ሁኔታዎች መልካቸውን እንደሚቀይሩ ቀድሞም ቢሆን ገምቼ ነበር። ቀድሞውንም ቢሆን ወደ ነነዌ አልሄድም ያልኩት ለዚህ ነበር። አሁን ደግሞ በአንድ ትልቅ ዓሣ መዋጥ ያስከተለብኝን ፍርሃትና ውርደት ሁሉ ተሸክሜ እንዲሁም በነነዌ ሰዎች ላይ የማያዳግም ጥፋት እንደሚመጣ ለማስጠንቀቅ ጠንክሬ ከሠራሁ በኋላ መጨረሻው ይህ ሆነ! ልፋቴና መከራዬ ሁሉ መና ቀረ! ብሞት ይሻለኝ ነበር!’—ዮናስ 4:1-3
12. ከዮናስ ተሞክሮ ምን ልንማር እንችላለን?
12 ዮናስ ለማማረር የሚያበቃው በቂ ምክንያት ነበረውን? ይሖዋ ንስሐ ለገቡ ክፉ አድራጊዎች ምሕረቱን መዘርጋቱ ስህተት ነበርን? እንዲያውም ዮናስ መደሰት ይገባው ነበር፤ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከጥፋት ሊድኑ ነው! (ዮናስ 4:11) ይሁን እንጂ አክብሮት በጎደለው መንገድ ማማረሩ በይሖዋ ጽድቅ ላይ በተሟላ መንገድ እንደማይታመን አሳይቷል። ስለ ሌሎች ሳይሆን ስለ ራሱ ከሚገባው በላይ ያስብ ነበር። ራሳችንንና የግል ስሜቶቻችንን በሁለተኛ ደረጃ በማስቀመጥ ከዮናስ እንማር። ይሖዋን መታዘዝ፣ በድርጅቱ በኩል የሚሰጠውን መመሪያ መከተልና ውሳኔዎቹን ማክበር ልናደርገው የሚገባ ትክክለኛ ነገር መሆኑን ራሳችንን እናሳምን። “እግዚአብሔርን ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን” አሳማኝ ማስረጃ አግኝተናል።—መክብብ 8:12
እምነታችንን የምናጠነክርበት ጊዜ አሁን ነው!
13. ሁላችንም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ልናጠነክር የምንችለው እንዴት ነው?
13 በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠንከራችን የጥበብ መንገድ ነው። (ምሳሌ 3:5-8) እርግጥ ነው እምነታችን የበለጠ እንዲጎለብት እንዲረዳን ወደ ይሖዋ ከመጸለይ የበለጠ ነገር ማድረግ አለብን። እምነት የሚያድገው በትክክለኛ እውቀት ላይ ሲመሠረት ነው፤ ስለዚህ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግን ማለትም መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን ማንበብን የዘወትር ልማዳችን ልናደርግ ይገባል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት እንዲሁም የቻልነውን ያክል ጥሩ ዝግጅትና ተሳትፎ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በተጨማሪም ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ማካፈልን ልማድ ማድረግና ተቃውሞዎችን በዘዴ ማሸነፍ በይሖዋና በቃሉ ላይ ያለንን እምነት ያጎለብትልናል። በዚህ መንገድ ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና በየቀኑ እያደገ ይሄዳል።
14. የአምላክ ሕዝቦች በቅርቡ በይሖዋ ላይ ያላቸውን ትምክህት ከምንጊዜውም በበለጠ እንዲያሳዩ የሚጠበቅባቸው ለምንድን ነው?
14 በቅርቡ በሰው ልጆች ላይ እስካሁን ከወረደው መከራ ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ታላቅ መከራ በድንገት ይፈነዳል። (ማቴዎስ 24:21) ይህ በሚሆንበት ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ከምንጊዜውም በበለጠ በይሖዋ ጽድቅና በድርጅቱ በኩል በሚሰጠው አመራር እንደሚታመኑ ሊያሳዩ ይገባል። በምሳሌያዊ አነጋገር “ሕዝቤ ሆይ፣ ና ወደ ቤትህም ግባ፣ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ” የሚለውን የአምላክ መመሪያ በእምነት ይታዘዛሉ። (ኢሳይያስ 26:20) አሁንም እንኳ ጥበቃ በሚያገኙባቸው በ232 አገሮች ውስጥ በሚገኙ ከ85,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ተጠልለዋል። “ወደ ቤትህም ግባ” የሚለው መመሪያ የሚያጠቃልለው ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሌላ ነገር ይኑር ተግባራዊ ለማድረግ እንድንችል ይሖዋ እንደሚረዳን ልንተማመን እንችላለን።
15. በ1998 እምነት የማሳየት አስፈላጊነት ትኩረት የተሰጠው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጉ ትክክል የሆነውስ ለምንድን ነው?
15 አሁኑኑ እምነታችንን ማጠንከራችን የግድ አስፈላጊ ነው። በክርስቲያን ወንድሞቻችን፣ በይሖዋ ድርጅትና ከሁሉም በላይ ደግሞ በራሱ በይሖዋ ላይ እምነት ከሌለን በሕይወት መትረፉ የማይቻል ነገር ነው። ስለዚህ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በሚለው የ1998 የዓመት ጥቅሳቸው አማካኝነት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ማግኘታቸው ምንኛ የተገባ ነው! (ሮሜ 10:13) በዚህ ተስፋ እንደምናምን ማሳየታችንን መቀጠል አለብን። በዚህ እምነት ላይ ቅንጣት ታክል እንኳ የጥርጣሬ መንፈስ እንዳለን ከተሰማን አሁኑኑ አዎን፣ ዛሬውኑ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
የይሖዋ ፍርድ ጽድቅ ይሆናል
16. እምነት እያደገ ካልሄደ ምን ሊደርስበት ይችላል? እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይደርስብን እንዴት መከላከል እንችላለን?
16 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዕብራውያን 3:14 ላይ የሚከተለው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል:- “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፣ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና።” በመሠረቱ እነዚህ ቃላት ምድራዊ ተስፋ ባላቸው ክርስቲያኖችም ላይ ይሠራሉ። መጀመሪያ ላይ የነበረ እምነት እያደገ ካልሄደ ተሸርሽሮ ሊጠፋ ይችላል። ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችንን በመቀጠል እምነታችን የተዋቀረበትን መሠረት ማጠንከራችን ምንኛ የተገባ ነው!
17. በሕይወት መትረፍን በተመለከተ ኢየሱስ በትክክል እንደሚፈርድ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
17 በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክርስቶስ በሁሉም ብሔራት የሚገኙትን ሰዎች በመመርመር “እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።” (ማቴዎስ 25:31-33) ክርስቶስ በሕይወት መትረፍ ለሚገባው ሁሉ በጽድቅ እንደሚፈርድ ልንተማመን እንችላለን። ‘በዓለም ላይ በጽድቅ ለመፍረድ’ የሚያስችለውን ጥበብ፣ ማስተዋልና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን ይሖዋ ሰጥቶታል። (ሥራ 17:30, 31) እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረው እንደ አብርሃም የጸና እምነት ይኑረን:- “ይህ ከአንተ [ከይሖዋ] ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፣ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፣ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?”—ዘፍጥረት 18:25
18. አሁን ስለማናውቃቸው ነገሮች ከመጠን በላይ መጨነቅ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
18 በይሖዋ ጽድቅ ላይ ሙሉ እምነት ካሳደርን እንደሚከተሉት ያሉት ጥያቄዎች አእምሯችንን አያስጨንቁትም:- ‘ሕፃናትና ትንንሽ ልጆች ፍርድ የሚያገኙት እንዴት ይሆናል? አርማጌዶን በሚመጣበት ጊዜ ምሥራቹ ያልደረሳቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆን? የአእምሮ እክል ያለባቸው ሰዎችስ? . . .?’ ይሖዋ እነዚህን ጉዳዮች እንዴት እንደሚፈታቸው አሁን አናውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርገው በጽድቅና በርኅራኄ ይሆናል። ይህን በፍጹም ልንጠራጠር አይገባም። እንዲያውም እነዚህን ነገሮች ባልጠበቅነውና ባላሰብነው መንገድ ሲፈታቸው መመልከቱ ሳያስገርመንና ሳያስደስተን አይቀርም።—ከኢዮብ 42:3፤ መዝሙር 78:11-16፤ 136:4-9፤ ማቴዎስ 15:31፤ ሉቃስ 2:47 ጋር አወዳድር።
19, 20. (ሀ) ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቁ ስህተት የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ አስፈላጊዎቹን መልሶች የሚሰጠው መቼ ነው?
19 አንዳንድ ተቃዋሚዎች በሐሰት እንደሚናገሩት የይሖዋ ድርጅት ከቅን ልቦና በመነሳሳት ወቅታዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ ስህተት ነው አይልም። (1 ጴጥሮስ 1:10-12) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ግምታዊና እርባና የሌላቸው ጥያቄዎችን ከመጠየቅ እንድንርቅ ይመክረናል። (ቲቶ 3:9) ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅና በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረቱ መልሶች ለማግኘት የአምላክን ቃልና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን መመርመር ያለንን ትክክለኛ እውቀት ይጨምርልናል እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ሊያጠነክርልን ይችላል። ድርጅቱ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል። ኢየሱስ መልስ የሚያገኙበት ጊዜ ላልደረሱ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል። “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 16:12) በተጨማሪም በወቅቱ አንዳንድ የማያውቃቸው ነገሮች መኖራቸውን አምኖ ተቀብሏል።—ማቴዎስ 24:36
20 ይሖዋ ወደ ብርሃን የሚያመጣው ገና ብዙ ነገር አለ። አምላክ ጊዜውን ጠብቆ ዓላማዎቹን እንደሚያስፈጽም በመተማመን እርሱን መጠባበቁ ምንኛ ጥበብ ነው። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ስለ መንገዶቹ ተጨማሪ ማስተዋል በማግኘት እንደምንደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አዎን፣ በይሖዋና እርሱ በሚጠቀምበት ድርጅት ላይ ፍጹም እምነት እንዳለን ማሳየታችንን ከቀጠልን እንካሳለን። ምሳሌ 14:26 “እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፣ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሚከተሉትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች (የእንግሊዝኛ) ተመልከት:- ጥቅምት 15, 1967 ገጽ 638፤ ሰኔ 1, 1987 ገጽ 30
[ምን ይመስልሃል?]
◻ ስሜቶቻችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዲያመነምኑት መፍቀድ ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
◻ ዮናስ ከገጠመው ተሞክሮ ምን ልንማር እንችላለን?
◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምንወደውን ሰው በሞት ብናጣም እንኳ ይሖዋ ጻድቅ መሆኑን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መታመኛህ ይሖዋ መሆኑን እርግጠኛ ነህን?