ምዕራፍ ሃያ አራት
ከዚህ ዓለም የሚገኝ እርዳታ የለም
1, 2. (ሀ) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተሸበሩት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሩሳሌምን ከገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳታችን ተገቢ ነው?
የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ተሸብረዋል! ደግሞም ቢሸበሩ አይገርምም! በዘመኑ እጅግ ኃያል የነበረው የአሦር ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ‘በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ላይ ጥቃት በመሰንዘር አንድ በአንድ ተቆጣጥሯቸዋል።’ አሁን ደግሞ የአሦር ወታደራዊ ኃይል የይሁዳን ዋና ከተማ ስጋት ላይ ጥሏል። (2 ነገሥት 18:13, 17) ንጉሥ ሕዝቅያስና ሌሎቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ምን ያደርጉ ይሆን?
2 ሕዝቅያስ ሌሎቹ የአገሩ ከተሞች በአሦር እጅ ስለ ወደቁ ኢየሩሳሌም ኃያል የሆነውን የአሦር ጦር የምትቋቋምበት አቅም እንደሌላት ያውቃል። ከዚህም በላይ አሦራውያን በጭካኔያቸውና በኃይለኝነታቸው የሚታወቁ ሰዎች ናቸው። ሠራዊቱ እጅግ አስፈሪ ከመሆኑ የተነሣ ጠላቶቻቸው ገና ሳይዋጉ የሚሸሹበት ጊዜ ነበር! ኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነዋሪዎቿ እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን መሄድ ይችላሉ? ከአሦራውያን ሠራዊት ማምለጥ የሚችሉበት መንገድ ይኖራልን? የአምላክ ሕዝብ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የገባው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወደ ኋላ መለስ ብለን ይሖዋ ቀደም ባሉት ዓመታት ከቃል ኪዳን ሕዝቡ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር መመርመር ይኖርብናል።
በእስራኤል ምድር የታየው ክህደት
3, 4. (ሀ) የእስራኤል መንግሥት ወደ ሁለት የተከፈለው መቼና እንዴት ነው? (ለ) ኢዮርብዓም የአሥሩን ነገዶች ሰሜናዊ መንግሥት አጀማመር ያበላሸው እንዴት ነው?
3 እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ባሉት ከ500 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች እንደ አንድ ብሔር ሆነው ኖረዋል። ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ግን ኢዮርብዓም አሥሩን ሰሜናዊ የእስራኤል ነገድ በዳዊት ቤት ላይ በማሳመፁ ብሔሩ ለሁለት ተከፈለ። ይህ የሆነው በ997 ከዘአበ ነበር።
4 ኢዮርብዓም የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ ሲሆን አሮናዊውን የክህነት አገልግሎትና ትክክለኛውን የይሖዋ አምልኮ ሕጋዊ መብት በሌለው የካህናት ወገንና በጥጃ አምልኮ ሥርዓት በመተካት ተገዢዎቹን በክህደት ጎዳና መርቷቸዋል። (1 ነገሥት 12:25-33) ይህ በይሖዋ ዘንድ እጅግ አስጸያፊ ተግባር ነበር። (ኤርምያስ 32:30, 35) ይሖዋ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች አሦር እስራኤልን በቁጥጥሯ ሥር እንድታስገባት ፈቅዷል። (2 ነገሥት 15:29) ንጉሥ ሆሴዕ ከግብጽ ጋር በማሴር የአሦራውያንን ቀንበር ለመስበር ቢሞክርም አልተሳካለትም።—2 ነገሥት 17:4
እስራኤል የተማመነችው በሐሰት መሸሸጊያ ነው
5. እስራኤል እርዳታ ለማግኘት ፊቷን የመለሰችው ወደ ማን ነው?
5 ይሖዋ እስራኤላውያን ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ይፈልጋል።a በመሆኑም ነቢዩ ኢሳይያስ የሚከተለውን የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲነግራቸው አድርጓል:- “ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፣ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፣ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፣ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው!” (ኢሳይያስ 31:1) እንዴት የሚያሳዝን ነው! እስራኤል ይበልጥ የታመነችው ሕያው በሆነው አምላክ በይሖዋ ሳይሆን በፈረሶችና በጦር ሰረገሎች ነው። በእስራኤላውያኑ ሰብዓዊ አመለካከት የግብጽ ፈረሶች በጣም ብዙና ብርቱ ሆነው ታይተዋቸዋል። እርግጥ ግብጽ የአሦራውያንን ሠራዊት ለመጋፈጥ ጠቃሚ አጋር ትሆናለች! ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከግብጽ ጋር የመሠረቱት ሰብዓዊ ጥምረት ከንቱ መሆኑን የሚገነዘቡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
6. እስራኤል ወደ ግብጽ ዘወር ማለቷ ጨርሶ በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌላት ያጋለጠው እንዴት ነው?
6 የእስራኤልም ሆነ የይሁዳ ነዋሪዎች በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ለይሖዋ የተወሰነ ሕዝብ ሆነው ነበር። (ዘጸአት 24:3-8፤ 1 ዜና መዋዕል 16:15-17) እስራኤል እርዳታ ለማግኘት ወደ ግብጽ ዘወር ማለቷ በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌላት እንዲሁም የቅዱስ ቃል ኪዳኑ ክፍል የሆኑትን ሕግጋት ቸል እንዳለች የሚያሳይ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ በቃል ኪዳን ስምምነቱ ውስጥ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እስካላቀረቡ ድረስ ሕዝቡን እንደሚጠብቃቸው ቃል ገብቶ ነበር። (ዘሌዋውያን 26:3-8) በዚሁ የተስፋ ቃል መሠረትም ይሖዋ ‘በመከራ ጊዜ መጠጊያቸው’ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። (መዝሙር 37:39፤ 2 ዜና መዋዕል 14:2, 9-12፤ 17:3-5, 10) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ በሆነው በሙሴ አማካኝነት ወደፊት የሚነሡት የእስራኤል ነገሥታት ለራሳቸው ፈረስን እንዳያበዙ ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 17:16) ነገሥታቱ ይህን ሕግ መታዘዛቸው ‘የእስራኤል ቅዱስ’ ይጠብቀናል ብለው እንደሚተማመኑ የሚያሳይ ይሆን ነበር። የሚያሳዝነው የእስራኤል መሪዎች እንዲህ ዓይነት እምነት አልነበራቸውም።
7. እስራኤል ካሳየችው እምነት የለሽነት ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ያገኛሉ?
7 ይህ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች የሚያስተላልፈው ትምህርት አለ። እስራኤል ይበልጥ ኃያል ከሆነው ከይሖዋ ይልቅ ከግብጽ ሰብዓዊ ድጋፍ ማግኘትን መርጣለች። ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች በይሖዋ ላይ ሳይሆን የደህንነት ዋስትና ይሆናሉ በሚባሉት ሰብዓዊ ነገሮች ማለትም ባንክ ባስቀመጡት ገንዘብ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ሥልጣንና በዓለም ውስጥ በሚያውቋቸው ሰዎች ይታመኑ ይሆናል። ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶች ቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች የማሟላት ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር መወጣት እንዳለባቸው አይካድም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁን እንጂ በቁሳዊ ነገሮች አይታመኑም። እንዲሁም ‘ከመጎምጀትም ሁሉ ይጠበቃሉ።’ (ሉቃስ 12:13-21) ‘በመከራ ጊዜ ብቸኛው ረዳታቸው’ አምላክ ይሖዋ ነው።—መዝሙር 9:9፤ 54:7
8, 9. (ሀ) የእስራኤል እቅድ ጥሩ ወታደራዊ ስልት መስሎ ሊታይ ቢችልም ውጤቱ ምን ይሆናል? ለምንስ? (ለ) በይሖዋና በሰዎች የተስፋ ቃል መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
8 ኢሳይያስ ከግብጽ ጋር ስምምነት የመፍጠር ሐሳብ ባፈለቁት የእስራኤላውያን መሪዎች ላይ እንዲህ በማለት ያፌዝባቸዋል:- “እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፣ ክፉንም ነገር ያመጣል፣ ቃሉንም አይመልስም፣ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል።” (ኢሳይያስ 31:2) የእስራኤል መሪዎች ጠቢብ እንደሆኑ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ጥበብ አይበልጥምን? ላይ ላዩን ሲታይ እስራኤል ከግብጽ እርዳታ ለማግኘት የቀየሰችው ዘዴ ትክክለኛ የጦር ስልት መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለው ፖለቲካዊ ጥምረት በይሖዋ ዓይን መንፈሳዊ ምንዝር ነው። (ሕዝቅኤል 23:1-10) ከዚህ የተነሣ ይሖዋ ‘ክፉን ነገር እንደሚያመጣባቸው’ ኢሳይያስ ተናግሯል።
9 ሰዎች የሚሰጡት የተስፋ ቃል እምነት ሊጣልበት የሚችል እንዳልሆነ የማይታበል ሐቅ ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊ ከለላ ምንም ዋስትና የለውም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ‘ቃሉን መመለስ’ አያስፈልገውም። ቃል የገባውን ነገር አንድም ሳይቀር ይፈጽማል። የተናገረው ነገር በከንቱ ወደ እርሱ አይመለስም።—ኢሳይያስ 55:10, 11፤ 14:24
10. ግብጽም ሆነች እስራኤል ምን ይገጥማቸዋል?
10 ግብጻውያን ለእስራኤል አስተማማኝ መሸሸጊያ ይሆኑላት ይሆን? በፍጹም። ኢሳይያስ እስራኤላውያንን እንዲህ ይላቸዋል:- “ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፣ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፣ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፣ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።” (ኢሳይያስ 31:3) ይሖዋ በአሦር አማካኝነት የፍርድ እርምጃውን ሲያስፈጽም ረጂው (ግብጽ) እና ተረጂው (እስራኤል) ተሰናክለው ይወድቁና ይጠፋሉ።
የሰማርያ ውድቀት
11. እስራኤል የኃጢአትን ጎዳና በመከተል ምን ታሪክ አስመዝግባለች? የመጨረሻው ውጤትስ ምንድን ነው?
11 ይሖዋ እስራኤል ንስሐ እንድትገባና ወደ ንጹሕ አምልኮ እንድትመለስ ለማበረታታት በተደጋጋሚ ነቢያቱን በመላክ ምሕረት አሳይቷታል። (2 ነገሥት 17:13) ያም ሆኖ እስራኤል የጥጃ አምልኮ በማካሄድ የፈጸመችው ኃጢአት እንዳይበቃ በጥንቆላ፣ የሥነ ምግባር ብልግና ባለበት የበኣል አምልኮ በመጠላለፍና በማምለኪያ አጸዶች እንዲሁም በኮረብታ መስገጃዎች በመጠቀም ኃጢአቷን አብዝታለች። አልፎ ተርፎም እስራኤላውያን የአብራካቸው ክፋይ የሆኑትን ልጆች ለአጋንንት አማልክት በመሠዋት ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳልፈዋል።’ (2 ነገሥት 17:14-17፤ መዝሙር 106:36-39፤ አሞጽ 2:8) ይሖዋ የእስራኤልን ክፋት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት “ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች” ሲል ተናግሯል። (ሆሴዕ 10:1, 7) በ742 ከዘአበ የአሦር ሠራዊት የእስራኤል ዋና ከተማ በሆነችው ሰማርያ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ከሦስት ዓመታት ከበባ በኋላ ሰማርያ በ740 ከዘአበ ስትወድቅ የአሥሩ ነገድ መንግሥት ሕልውና አክትሟል።
12. ይሖዋ ዛሬ እንዲከናወን ያዘዘው ሥራ ምንድን ነው? ማስጠንቀቂያውን ቸል የሚሉ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
12 በዘመናችን ደግሞ ይሖዋ “በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ” ለማስጠንቀቅ ምድር አቀፍ የስብከት ሥራ እንዲከናወን አዝዟል። (ሥራ 17:30፤ ማቴዎስ 24:14) የአምላክን የመዳን መንገድ ለመቀበል አሻፈረን የሚሉ ሰዎች ‘በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ’ ሆነው ከሃዲ እንደነበረው የእስራኤል ብሔር ይጠፋሉ። በሌላ በኩል ግን ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች “ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) እንግዲያው የጥንቱ የእስራኤል መንግሥት የሠራቸውን ስህተቶች ላለመድገም መጠንቀቅ ምንኛ ጥበብ ይሆናል! መዳን ለማግኘት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንታመን።
የይሖዋ የማዳን ኃይል
13, 14. ይሖዋ ለጽዮን የሚናገረው የሚያጽናና ቃል ምንድን ነው?
13 ከእስራኤል ድንበር በስተ ደቡብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኘው የይሁዳ ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም ነች። የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሰማርያ ምን እንደደረሰባት አሳምረው ያውቃሉ። እነርሱም ቢሆኑ ሰሜናዊ ጎረቤታቸውን ባጠፋው አስፈሪ ጠላት ምክንያት ስጋት አጥልቶባቸዋል። ሰማርያ ከገጠማት ነገር ትምህርት ያገኙ ይሆን?
14 ቀጥሎ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሚያጽናኑ ናቸው። ይሖዋ አሁንም ቢሆን የቃል ኪዳን ሕዝቡን እንደሚወድ ሲያረጋግጥላቸው እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔርም እንዲህ ይለኛልና:- አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሣ፣ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፣ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል።” (ኢሳይያስ 31:4) ባደነው እንስሳ ላይ እንደቆመ ደቦል አንበሳ ይሖዋ ቅዱስ ከተማውን ጽዮንን በቅንዓት ይጠብቃል። የአሦራውያን ሠራዊት የሚነዛው ምንም ዓይነት ጉራ፣ የሚሰነዝረው ምንም ዓይነት የማስፈራሪያ ቃል ወይም ሌላ እንቅስቃሴ ይሖዋን ከዓላማው ዝንፍ አያደርገውም።
15. ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች በርኅራኄና በእንክብካቤ የሚይዛቸው እንዴት ነው?
15 አሁን ደግሞ ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች እንዴት በእንክብካቤና በርኅራኄ እንደሚይዛቸው ተመልከት:- “እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፣ ይታደጋታል፣ አልፎም ያድናታል።” (ኢሳይያስ 31:5) አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ለመከላከል ምን ጊዜም ትጉ ነች። ክንፎቿን ዘርግታ ከጫጩቶቿ በላይ እያንዣበበች አደጋ እንዳለ የሚጠቁም ነገር መኖር አለመኖሩን ትከታተላለች። ጫጩቶቿን የሚጎዳ አውሬ ከመጣ ወደታች ተወንጭፋ በመውረድ ትከላከልላቸዋለች። በተመሳሳይም ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከወራሪው የአሦር ኃይል ለማስጣል ይጠብቃቸዋል።
‘እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ ተመለሱ’
16. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቡ ምን ፍቅራዊ ጥሪ አቅርቦላቸዋል? (ለ) የይሁዳ ሰዎች ዓመፅ ይበልጥ ግልጽ የሆነው መቼ ነው? አብራራ።
16 አሁን ይሖዋ ሕዝቡ የሠሩትን ኃጢአት ካስታወሳቸው በኋላ የተሳሳተ ጎዳናቸውን እንዲተዉ ያበረታታቸዋል:- “እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፣ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ።” (ኢሳይያስ 31:6) ያመፀው የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ብቻ አልነበረም። “የእስራኤል ልጆች” የሆኑት የይሁዳ ነዋሪዎችም ‘በእጅጉ ዓምፀው’ ነበር። ኢሳይያስ ትንቢታዊ መልእክቱን ካጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሥልጣን በያዘው በሕዝቅያስ ልጅ በምናሴ የንግሥና ዘመን ይህ ነገር ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታያል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንደሚለው ‘ምናሴ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አስቷል።’ (2 ዜና መዋዕል 33:9) እስቲ አስበው! ይሖዋ አረማዊ ብሔራትን ያጠፋው በጣም የሚዘገንን ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ስለነበር ነው። ይሁንና ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና የመሠረቱት የይሁዳ ነዋሪዎች ከእነዚያ ብሔራት የከፋ ነገር ፈጽመዋል።
17. ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች በምናሴ ዘመን በይሁዳ ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉት በምን መንገድ ነው?
17 በ21ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ያለው ሁኔታም በምናሴ ዘመን በይሁዳ ከነበረው ሁኔታ ጋር በብዙ መልኩ የሚመሳሰል ነው። ዓለም ይበልጥ በሃይማኖት፣ በዘርና በጎሳ ጥላቻ እየተከፋፈለ ሄዷል። አሰቃቂ ግድያዎች፣ የጭካኔ ተግባራት፣ የግዳጅ ወሲብ እና የዘር ማጽዳት እየተባለ የሚጠራው እንቅስቃሴ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ሕዝቦችና ብሔራት በተለይም ደግሞ የሕዝበ ክርስትና ብሔራት ‘አጥብቀው ዓምፀዋል።’ ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህ ዓመፅ እንዲሁ እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም በኢሳይያስ ዘመን ምን እንደተከናወነ እናውቃለን።
ኢየሩሳሌም ነፃ ወጣች
18. ራፋስቂስ ለሕዝቅያስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?
18 የአሦር ነገሥታት በጦር ሜዳ ላገኙት ድል ያመሰገኑት አማልክቶቻቸውን ነው። ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ቴክስትስ የተባለው መጽሐፍ የአሦር ንጉሠ ነገሥት የነበረውንና “ታላላቆቹ አማልክት፣ ጌቶ[ቹ]፣ ማለትም በታላላቅ አውደ ግንባሮች የውጊያ (ልምድ ያላቸውን) ወታደሮች . . . ድል [ሲያደርግ] ከጎ[ኑ] ተለይተው የማያውቁት፣ አሸር፣ ቤልና ነቦ” እንደሚመሩት የተናገረውን የአሸርባኒፓልን ጽሑፍ ያካተተ ነው። በኢሳይያስ ዘመን የንጉሥ ሰናክሬም ወኪል የነበረው ራፋስቂስ ለንጉሥ ሕዝቅያስ በላከው መልእክቱ ውስጥ ሰዎች በሚያደርጉት ውጊያ አማልክት እጃቸውን ጣልቃ ያስገባሉ የሚል ተመሳሳይ እምነት እንደነበረው አንጸባርቋል። የአይሁዳውያኑ ንጉሥ ለመዳን በይሖዋ እንዳይታመን ለማስጠንቀቅ ሲል የሌሎች ብሔራት አማልክት ከኃያሉ የአሦር ጦር ሕዝቦቻቸውን መታደግ እንደተሳናቸው ተናግሯል።—2 ነገሥት 18:33-35
19. ለራፋስቂስ መሳለቅ ሕዝቅያስ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?
19 ንጉሥ ሕዝቅያስ የሚሰጠው ምላሽ ምን ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፣ ማቅም ለበሰ፣ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ።” (2 ነገሥት 19:1) ሕዝቅያስ ከዚህ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወጣ ሊረዳው የሚችለው አንድ አካል ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ራሱን በማዋረድ ከይሖዋ መመሪያ ጠይቋል።
20. ይሖዋ የይሁዳን ሕዝብ ለመከላከል እርምጃ የሚወስደው እንዴት ነው? ከዚህስ ምን ሊማሩ ይገባል?
20 ይሖዋም የጠየቀውን መመሪያ ሰጥቶታል። በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ አለው:- “በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን [“ከንቱ፣” NW ] ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ።” (ኢሳይያስ 31:7) ይሖዋ ለሕዝቡ በሚዋጋላቸው ቀን የሰናክሬም አማልክት ከንቱ መሆናቸው ገሃድ ይወጣል። ይህ የይሁዳ ነዋሪዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ትልቅ ትምህርት ነው። ሕዝቅያስ የታመነ ንጉሥ ቢሆንም የይሁዳ ምድር ግን እንደ እስራኤል ሁሉ በጣዖታት የተሞላች ነበረች። (ኢሳይያስ 2:5-8) የይሁዳ ነዋሪዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለመጠገን ከፈለጉ ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባትና ‘ከንቱ ጣዖቶቻቸውን መጣል’ ነበረባቸው።—ዘጸአት 34:14ን ተመልከት።
21. ይሖዋ በአሦር ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ ኢሳይያስ በትንቢታዊ መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
21 አሁን ደግሞ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ አስፈሪ በሆነው የይሁዳ ጠላት ላይ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ ትንቢታዊ መግለጫ ይሰጣል:- “አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፣ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻል ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ።” (ኢሳይያስ 31:8) ያ የቁርጥ ቀን ሲደርስ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሰይፋቸውን ከአፎቱ ማውጣት እንኳ አያስፈልጋቸውም። ምርጥ የሚባለው የአሦር ሠራዊት በሰው ሳይሆን በይሖዋ ሰይፍ ይበላል። የአሦራውያኑ ንጉሥ ሰናክሬምም ‘ከሰይፍ ይሸሻል።’ አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ተዋጊዎቹ በይሖዋ መልአክ ከተገደሉ በኋላ ወደ አገሩ ተመለሰ። ከጊዜ በኋላም በአምላኩ በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ሳለ የገዛ ልጆቹ ገድለውታል።—2 ነገሥት 19:35-37
22. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በሕዝቅያስና በአሦራውያን ሠራዊት መካከል ከነበረው ሁኔታ ምን ትምህርት ያገኛሉ?
22 ሕዝቅያስን ጨምሮ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከአሦር ሠራዊት እጅ የሚታደጋት እንዴት እንደሆነ አስቀድሞ ሊያውቅ የሚችል አንድም ሰው አልነበረም። ያም ሆነ ይህ ሕዝቅያስ ችግሩን ለመወጣት የመረጠው ጎዳና ዛሬም ችግር ለሚገጥማቸው ሁሉ እጅግ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18) ኢየሩሳሌምን ስጋት ላይ ጥለዋት የነበሩት አሦራውያን ካተረፉት አስፈሪ ስም አንጻር ሕዝቅያስ ፍርሃት አድሮበት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ነገሥት 19:3) ያም ሆኖ ግን በይሖዋ ላይ እምነት ስለነበረው መመሪያ ለማግኘት የጣረው ከሰው ሳይሆን ከይሖዋ ነው። እንዲህ ማድረጉ ለኢየሩሳሌም ምንኛ ታላቅ በረከት ነበር! ዛሬ ያሉ አምላክን የሚፈሩ ክርስቲያኖችም በጣም የሚያስጨንቅ ነገር ሲገጥማቸው ከፍተኛ የስሜት ውጥረት ውስጥ ይገቡ ይሆናል። አብዛኞቹ ሁኔታዎች የሚያስፈሩ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ‘ጭንቀታችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ ከጣልን’ እርሱ አይተወንም። (1 ጴጥሮስ 5:7) ፍርሃታችንን እንድንወጣና ያስጨነቀንን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንድናገኝ ይረዳናል።
23. መጨረሻ ፍርሃት ላይ የወደቀው ሕዝቅያስ ሳይሆን ሰናክሬም ነው የምንለው ለምንድን ነው?
23 በመጨረሻ ፍርሃት ላይ የወደቀው ሕዝቅያስ ሳይሆን ሰናክሬም ነበር። እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ዞር ሊል ይችላል? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፣ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 31:9) ሰናክሬም እንደ ‘አምባ’ ታምኖባቸው የነበሩት አማልክት ሊያስጥሉት አልቻሉም። ‘ከፍርሃት የተነሣ እንዳለፉ’ ያህል ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሰናክሬም መሳፍንት ጭምር ምንም ሳይፈይዱ ቀርተዋል። እነርሱም በድንጋጤ ደርቀው ቀርተዋል።
24. አሦራውያን ከደረሰባቸው ነገር ምን የማያሻማ ትምህርት ማግኘት ይቻላል?
24 ይህ የኢሳይያስ ትንቢት አምላክን ለመቃወም ለሚሞክሩ ሁሉ የሚያስተላልፈው መልእክት የማያሻማ ነው። የይሖዋን ዓላማ የሚያጨናግፍ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ፣ ምንም ዓይነት ኃይል ወይም ሴራ የለም። (ኢሳይያስ 41:11, 12) በተመሳሳይም አምላክን እናመልካለን እያሉ ለደህንነታቸው ዋስትና ለማግኘት በሰብዓዊ ነገሮች የሚታመኑ ሁሉ መጨረሻቸው አሳዛኝ ይሆናል። ‘ወደ እስራኤል ቅዱስ የማይመለከቱትን ሁሉ’ ይሖዋ ‘ክፉ ነገር ያመጣባቸዋል።’ (ኢሳይያስ 31:1, 2) በእርግጥም ብቸኛው እውነተኛና ዘላቂ መሸሸጊያ ይሖዋ አምላክ ነው።—መዝሙር 37:5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኢሳይያስ ምዕራፍ 31 ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቁጥሮች በዋነኛነት የሚናገሩት ስለ እስራኤል መሆን አለበት። የመጨረሻዎቹ ስድስት ቁጥሮች ግን የሚያመለክቱት ይሁዳን ይመስላል።
[በገጽ 319 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቁሳዊ ነገሮች የሚታመኑ ሰዎች መጨረሻቸው አሳዛኝ ነው
[በገጽ 322 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያደነውን እንስሳ እንደሚጠብቅ አንበሳ ይሖዋ ቅዱስ ከተማውን ይጠብቃታል
[በገጽ 324 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓለም በሃይማኖት፣ በዘርና በጎሳ ጥላቻ ተከፋፍላለች
[በገጽ 326 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕዝቅያስ እርዳታ ለማግኘት የሄደው ወደ ይሖዋ ቤት ነው