ይሖዋ ከብሔራት ጋር ያለው ክርክር
“እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ክርክር አለውና ድምፅ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል።”—ኤርምያስ 25:31
1, 2. (ሀ) ከንጉሥ ኢዮስያስ ሞት በኋላ በይሁዳ ውስጥ ምን ተፈጸመ? (ለ) የመጨረሻው የይሁዳ ንጉሥ ማን ነበረ? ታማኝ ባለመሆኑ ምክንያት ምን ደረሰበት?
የይሁዳ ምድር አስጨናቂ በሆነ የመጨረሻ ዘመን ውስጥ ትገኝ ነበር። የሚነደው የይሖዋ ቁጣ ለጊዜው እንዳይወርድ ያደረገው ኢዮስያስ የተባለው ጥሩ ንጉሥ ነበር። ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በ629 ከዘአበ ከተገደለ በኋላ ምን ሆነ? ከእርሱ በኋላ የነገሡት ነገሥታት ይሖዋን አቃለሉት።
2 የይሁዳ የመጨረሻ ንጉሥ የሆነውና የኢዮስያስ አራተኛ ልጅ የነበረው ሴዴቅያስ ሁለተኛ ነገሥት 24:19 እንደሚለው “[ታላቅ ወንድሙ] ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ዘምቶ ሴዴቅያስን ከማረከና ወንዶች ልጆቹን ዓይኑ እያየ ከገደላቸው በኋላ ዓይኑን አጥፍቶ ወደ ባቢሎን ወሰደው። ከዚህም በላይ ባቢሎናውያን ለይሖዋ አምልኮ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ከመዘበሩ በኋላ ከተማይቱንና ቤተ መቅደሷን በእሳት አቃጠሉ። ከግድያ የተረፉት ነዋሪዎች ግዞተኞች ሆነው ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።
3. ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ስትጠፋ የትኛው ዘመን ጀመረ? ያ ዘመን ሲያበቃ ምን ይሆናል?
3 ይህ ዓመት ማለትም 607 ከዘአበ ኢየሩሳሌም ፈጽማ የወደመችበት ብቻ ሳይሆን በሉቃስ 21:24 ላይ የተጠቀሱት ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ የጀመሩበት ዓመት ሆነ። ይህ የ2,520 ዓመታት ጊዜ ያከተመው በእኛ መቶ ዘመን በ1914 ነው። በዚያ ዓመት ይሖዋ በነገሠውና ከናቡከደነፆር በሚበልጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በዚህ በተበላሸ ዓለም ላይ ፍርዱን የሚያወርድበት ዘመን ገባ። ፍርዱ የሚጀምረው የይሁዳ አምሳያ በሆነችውና የአምላክና የክርስቶስ ምድራዊ ወኪል ነኝ በምትለው በዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትና ላይ ነው።
4. አሁን ከኤርምያስ ትንቢት ጋር ግንኙነት ያላቸው ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
4 ይሁዳ በነገሥታት ትተዳደር በነበረችባቸው የመጨረሻ ዓመታት ባናወጣት ሁከትና ዛሬ አጎራባች ብሔራትን ጭምር በነካው ሕዝበ ክርስትናን እያመሳት ባለው ሁከት መካከል ተመሳሳይነት እንዳለ እንመለከታለንን? እንዴታ! ታዲያ የኤርምያስ ትንቢት ይሖዋ በዘመናችን ያለውን ሁኔታ ስለሚፈታበት መንገድ ምን ያመለክታል? እስቲ እያየነው እንሂድ።
5, 6. (ሀ) ከ1914 ጀምሮ ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ይሁዳ ከመጥፋቷ በፊት ከነበረችበት ሁኔታ ጋር የተመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ዘመናዊው ኤርምያስ ለሕዝበ ክርስትና ያስተላለፈው መልእክት ምንድን ነው?
5 በርትራንድ ራስል የተባሉት እንግሊዛዊ የሒሳብና የፍልስፍና ሊቅ ወደ 40 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት እንዲህ ብለው ነበር፦ “የዓለምን አዝማሚያ የሚከታተል ማንኛውም ሰው ከ1914 ወዲህ ዓለም እየገሰገሰችበት ያለውን በቅድሚያ የተወሰነ የሚመስል ታይቶ የማያውቅ ጥፋት የሚያስከትል ጎዳና በመመልከት ይጨነቃል።” የጀርመን ርዕሰ ብሔር የነበሩት ኮንራት አደናወር ደግሞ “ከ1914 ወዲህ ፀጥታና እርጋታ ከሰዎች ሕይወት ጠፍቷል” ብለዋል።
6 ዛሬም እንደ ኤርምያስ ዘመን በዚህ መቶ ዘመን በተደረጉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች የሰዎች ደም እንደ ጎርፍ ፈስሷል። ይህም የሥርዓቱ ፍጻሜ መቅረቡን ያመለክታል። እነዚህ ጦርነቶች በአብዛኛው የተደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስን አምላክ እናመልካለን በሚሉ ክርስቲያን ነን ባይ አገሮች መካከል ነው። እንዴት ያለ ግብዝነት ነው! ይሖዋ በኤርምያስ 25:5, 6 ላይ የሚገኘውን እንዲህ የሚል መልእክት የሚናገሩ ምስክሮቹን ወደ እነርሱ መላኩ አያስደንቅም፦ “ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ . . . ታመልኩአቸውም ትሰግዱላቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፣ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቆጡኝ።”
7. ክርስቲያን ነን የሚሉ አገሮች የይሖዋን ማስጠንቀቂያዎች ችላ እንዳሉ የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?
7 ክርስቲያን ነን ባይ አገሮች ግን አንመለስም ብለዋል። እምቢተኝነታቸውንም በኮሪያና በቬትናም ለጦርነት አምላክ ተጨማሪ መሥዋዕት በማቅረብ አሳይተዋል። በተጨማሪም የሞት ነጋዴዎች ለሆኑት የጦር መሣሪያ አምራቾች የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣሉ። በ1980ዎቹ ውስጥ በየዓመቱ ለጦር መሣሪያ ማምረቻ ይውል ከነበረው አንድ ትሪልየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ አብዛኛውን ያዋጡት ክርስቲያን ነን የሚሉ አገሮች ናቸው። ከ1951 እስከ 1991 ባሉት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ለጦር መሣሪያ ያወጣችው ገንዘብ የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ካገኙት የተጣራ ትርፍ ጠቅላላ ድምር ይበልጣል። ብዙ የተባለለት ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ ወዲህ ዘመን ያለፈባቸው የኒኩሌር መሣሪያዎች እየተቀነሱ ቢሆንም የበለጠ የመግደል ኃይል ያላቸው ትላልቅ መሣሪያዎች ገና አልተወገዱም። አዳዲስ መሣሪያዎች መፈልሰፋቸውም አልቀረም። እነዚህ መሣሪያዎች ሥራ ላይ የሚውሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል።
ምግባረ ብልሹ በሆነው የሕዝበ ክርስትና ግዛት ላይ የተፈረደ ፍርድ
8. የኤርምያስ 25:8, 9 ቃላት በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚፈጸሙት እንዴት ነው?
8 ይሖዋ በኤርምያስ 25:8, 9 ላይ የተናገረው ተጨማሪ ቃል በተለይ የክርስትናን የጽድቅ ደረጃዎች ያልጠበቀችውን ሕዝበ ክርስትናን ይመለከታል፦ “ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፣ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፣ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፣ ለመደነቂያና ለማፍዋጨም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” ስለዚህ ታላቁ መከራ የአምላክ ሕዝብ ነኝ ከምትለው ሕዝበ ክርስትና ጀምሮ ‘በዙሪያዋ ወዳሉ አሕዛብ’ ማለትም በምድር በሙሉ ይዳረሳል።
9. ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ሁኔታ በዘመናችን ይበልጥ የተበላሸው በምን በምን መንገዶች ነው?
9 ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት ይሰጥ የነበረበት፣ ጋብቻና የቤተሰብ ሕይወት የከፍተኛ ደስታ ምንጭ እንደሆነ የሚቆጠርበት፣ ሰዎች ማለዳ ተነሥተው በሠሩት ሥራ እርካታ ያገኙ የነበረበት ዘመን ነበር። ብዙዎች በየምሽቱ የአምላክን ቃል በመብራት እያነበቡ መንፈሳቸውን ያድሱ ነበር። ዛሬ ግን ኑሮ በወሲባዊ ሕገ ወጥነት፣ በፍቺ፣ በዕፅ ሱሰኝነት፣ በስካር፣ በወጣቶች ዓመፅ፣ በስግብግብነት፣ በስንፍና፣ በቴሌቪዥን ሱሰኝነትና በሌሎችም ብልግናዎች በአስደንጋጭ ሁኔታ ተበክሏል። ይህ ሁሉ ይሖዋ አምላክ ልል በሆነው የሕዝበ ክርስትና ግዛት ላይ ለሚያመጣው የቅጣት ፍርድ መቅድም ነው።
10. ይሖዋ ፍርዱን ካስፈጸመባት በኋላ ሕዝበ ክርስትና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደምትወድቅ ግለጽ።
10 ይሖዋ በኤርምያስ ምዕራፍ 25 ቁጥር 10 እና 11 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፣ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ፣ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ባድማ መደነቂያ ትሆናለች።” በእርግጥም ታላላቆቹ የሕዝበ ክርስትና ቤተ መቅደሶችና ቤተ መንግሥቶች ተንኮታኩተው መጥፋታቸው በጣም የሚያስደንቅ ይሆናል። ይህ ጥፋት የቱን ያህል ስፋት ይኖረዋል? በኤርምያስ ዘመን ይሁዳና አጎራባቿ የነበሩ ብሔራት ባድማ ሆነው የቆዩት ለ70 ዓመታት ነበር። ይህ ደግሞ በመዝሙር 90:10 ላይ እንደተገለጸው የአንድ ሰው ዕድሜ ነው። በዘመናችን የሚፈጸመው የይሖዋ ፍርድ ደግሞ ፍጹምና ዘላለማዊ ይሆናል።
በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የተፈረደ ፍርድ
11. ሕዝበ ክርስትናን ለማጥፋት እንደ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ማን ነው? ለምንስ?
11 ይሖዋ ራእይ 17:12–17 ላይ እንደተተነበየው “አሥሩ ቀንዶች” ማለትም ወታደራዊ ኃይል ያላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች የሐሰት ሃይማኖትን ግዛት በማጥፋት የአምላክን ዓላማ የመፈጸም ሐሳብ ወደ ልባቸው እንዲገባ የሚያደርግበት ጊዜ ይመጣል። ይሁን እንጂ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የራእይ ምዕራፍ 17 “አሥር ቀንዶች” ቁጥር 16 እንደሚናገረው ‘ጋለሞታይቱን ጠልተው . . . ሙሉ በሙሉ በእሳት የሚያቃጥሉበት’ ብዙ መንገድ አለ። የኒኩሌር መሣሪያዎች ጦርነት በሚያሰጋቸው የምድር አካባቢዎች ተሰራጭተዋል፤ በመሰራጨትም ላይ ናቸው። የፖለቲካ ገዥዎች የይሖዋን በቀል እንዲፈጽሙ እንዴት ወደ ልባቸው እንደሚያገባ ግን ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል።
12. (ሀ) ባቢሎን ኢየሩሳሌምን ካጠፋች በኋላ ምን ደረሰባት? (ለ) ብሔራት ሕዝበ ክርስትናን ካጠፉ በኋላ ምን ይደርስባቸዋል?
12 በጥንት ዘመን ባቢሎንም የይሖዋን የቁጣ ትኩሳት የምትቀምስበት ተራ ደርሷት ነበር። በዚህም መሠረት ትንቢቱ ከኤርምያስ ምዕራፍ 25 ቁጥር 12 ጀምሮ የሚፈጸሙትን ነገሮች የሚገልጸው ከጊዜ በኋላ ከሚኖረው የተለወጠ ሁኔታ አንፃር ነው። ናቡከደነፆርና ባቢሎን የይሖዋ ቅጣት አስፈጻሚዎች መሆናቸው ስለቀረ ከዓለማዊ ብሔራት መካከል ተቆጥረዋል። ይህም በዘመናችን ከሚሆነው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተገለጹት “አሥር ቀንዶች” የሐሰት ሃይማኖትን ያጠፋሉ። በኋላ ግን እነርሱ ራሳቸው በራእይ ምዕራፍ 19 ላይ እንደተገለጸው ከሌሎቹ የምድር “ነገሥታት” ጋር ጥፋት ይደርስባቸዋል። ኤርምያስ 25:13, 14 ባቢሎን የአምላክን ሕዝቦች ከጨቆኑት ‘ከአሕዛብ ሁሉ’ ጋር እንዴት ፍርዷን እንደምትቀበል ይገልጻል። ይሖዋ ይሁዳን ለመቅጣት ናቡከደነፆርን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል። ሆኖም እርሱም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሱት የባቢሎን ነገሥታት ታብየው ራሳቸውን በይሖዋ ላይ ከፍ ከፍ አደረጉ። የይሖዋን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ማርከሳቸው ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። (ዳንኤል 5:22, 23) ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉ ጊዜ የይሁዳ ጎረቤቶች የነበሩት ብሔራት ማለትም ሞአብ፣ አሞን፣ ጢሮስ፣ ኤዶምና ሌሎቹ ብሔራት ደስ ከመሰኘታቸውም በላይ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተዘባብተዋል። እነርሱም ከይሖዋ የሚገባቸውን ብድራት ማግኘት ይገባቸዋል።
“በአሕዛብ ሁሉ” ላይ የተፈረደ ፍርድ
13. ‘ይህ የቁጣ ወይን ጠጅ ጽዋ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ከጽዋው የሚጠጡስ ምን ይሆናሉ?
13 በዚህም ምክንያት ኤርምያስ በምዕራፍ 25 ቁጥር 15 እና 16 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ የዚህን ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ፣ አንተንም የምሰድድባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። ከምሰድድባቸውም ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዱማል ያብዳሉም።” ‘የይሖዋ ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ’ የተባለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ማቴዎስ 26:39, 42 እና ዮሐንስ 18:11 ላይ “ጽዋ” አምላክ ለእርሱ ያለውን ፈቃድ የሚያመለክት ምሳሌ እንደሆነ ጠቁሟል። እዚህም ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ጽዋ ብሔራት መለኮታዊ በቀሉን እንዲጠጡ የይሖዋ ፈቃድ መሆኑን የሚያመለክት ምሳሌ ነው። ኤርምያስ 25:17–26 እነዚህን ለዘመናችን ብሔራት ጥላ የሚሆኑትን ብሔራት ይዘረዝራል።
14. በኤርምያስ ትንቢት መሠረት ከይሖዋ የቁጣ ወይን ጠጅ ጽዋ እንዲጠጡ የተደረጉት እነማን ናቸው? ይህስ ለዘመናችን የምን ምሳሌ ነው?
14 ሕዝበ ክርስትና ልክ እንደ ይሁዳ “ባድማና መደነቂያ ማፍዋጫም እርግማንም” ከሆነች በኋላ መላው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ይጠፋል። ከዚያ ቀጥሎ በግብጽ የተመሰለው መላው ዓለም የይሖዋን ቁጣ ወይን ይጠጣል! አዎን፣ ‘የቀረቡና የራቁ፣ አንዱም ከሌላው ጋር ያሉ የሰሜን ነገሥታት ሁሉ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትም ሁሉ’ መጠጣት አለባቸው። በመጨረሻ “የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል።” ይህ “የሼሻክ ንጉሥ” ማነው? ሼሻክ ምሳሌያዊ ስም ሲሆን ባቢሎንን የሚያመለክት የምሥጢር ስም ነው። ሰይጣን የባቢሎን ስውር ንጉሥ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስ እንዳመለከተው እስከ ዛሬ ድረስ “የዚህ ዓለም ገዥ” ነው። (ዮሐንስ 14:30) ስለዚህ ኤርምያስ 25:17–26 ከራእይ ምዕራፍ 18 እስከ 20 ጋር በሚመሳሰል መንገድ የይሖዋ የቁጣ ጽዋ በሚሰጥበት ጊዜ የሚሆኑትን ነገሮች አፈጻጸም ቅደም ተከተል ግልጽ ያደርጋል። መጀመሪያ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት፣ ቀጥሎ የፖለቲካ ኃይላት ከጠፉ በኋላ ሰይጣን ራሱ በጥልቅ ውስጥ ይታሰራል።—ራእይ 18:8፤ 19:19–21፤ 20:1–3
15. “ሰላምና ደኅንነት” ሆኗል የሚለው ጩኸት ሲሰማ ምን ይሆናል?
15 ቀዝቃዛው ጦርነት አብቅቷል ከተባለና አንድ ልዕለ ኃያል መንግሥት ብቻ ከቀረ ወዲህ ስለ ሰላምና ደኅንነት ብዙ ይወራል። ይህ ልዕለ ኃያል መንግሥት፣ ማለትም የአውሬው ሰባተኛ ራስ ራእይ 17:10 ላይ እንደተገለጸው “ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” ይህ “ጥቂት ጊዜ” ሊያከትም ተቃርቧል። በቅርቡ የሚሰማው “ሰላምና ደኅንነት” ሆኗል የሚለው ጩኸት ‘ድንገት ለሚመጣው ጥፋት’ መንገድ ይከፍታል። ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ይህንን ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3
16, 17. (ሀ) ማንም ሰው ከይሖዋ ቅጣት ለማምለጥ ቢሞክር ምን ይደርስበታል? (ለ) የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ የሚፈጸመው በምን ዓይነት አጥፊ መንገድ ነው?
16 መላው የሰይጣን ዓለም ሥርዓት፣ ከሕዝበ ክርስትና ጀምሮ የይሖዋን የበቀል ጽዋ መጠጣት ይኖርበታል። በምዕራፍ 25 ቁጥር 27 እስከ 29 ላይ ያለው ይሖዋ ለኤርምያስ የሰጠው ተጨማሪ ትዕዛዝ ይህን ግልጽ ያደርጋል፦ “አንተም፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፣ ስከሩም፣ አስታውኩም ውደቁም፣ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። ይጠጡም ዘንድ ጽዋውን ከእጅህ ለመቀበል እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ በላቸው። እነሆ፣ ስሜ የተጠራባትን ከተማ አስጨንቃት ዘንድ እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
17 እነዚህን ቃላት የተናገረው የጽንፈ ዓለሙ ልዑል ጌታ ይሖዋ አምላክ በመሆኑ በእውነትም ጠንካራና የሚያስፈሩ ቃላት ናቸው። ይሖዋ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በቅዱስ ስሙ ላይ ሲከመር የቆየውን ስድብ፣ ነቀፋና ጥላቻ ታግሦ ኖሯል። አሁን ግን ውድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ላስተማረው ጸሎት ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ ደርሷል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ እንደ ሰይፉ በመሆን በቀሉን እንዲፈጽም የይሖዋ ፈቃድ ነው።
18, 19. (ሀ) በይሖዋ ስም ድል ለመንሣት እየጋለበ የሚወጣው ማን ነው? ድል አድራጊነቱን ከማጠናቀቁ በፊትስ ምን እስኪሆን ይጠብቃል? (ለ) መላእክቱ የይሖዋን ቁጣ ዐውሎ ነፋስ ሲለቅቁት በምድር ላይ ምን ዓይነት አስፈሪ ነገሮች ይከሰታሉ?
18 በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ ኢየሱስ በነጭ ፈረስ እንደጋለበና ‘ድል እየነሣ፣ ድል ለመንሣት እንደወጣ’ እናነባለን። (ቁጥር 2) ይህ ግልቢያ የተጀመረው ኢየሱስ በ1914 ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ሲጭን ነው። ከእርሱ በኋላ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ምድርን እየቀሰፉ ያሉት የአጠቃላይ ጦርነት፣ የረሃብና የቸነፈር ምሳሌ የሆኑ ሌሎች ፈረሶችና ፈረሰኞች ተከትለዋል። ይህ ሁሉ እልቂት የሚያበቃው መቼ ይሆን? ራእይ ምዕራፍ 7 መንፈሳዊ እስራኤልና ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡት እጅግ ብዙ ሕዝቦች ለደኅንነት እስኪሰበሰቡ ድረስ አራት መላእክት “አራቱን የምድር ነፋሳት” አግደው እንደያዙ ይነግረናል። (ቁጥር 1) ከዚያ በኋላስ?
19 ኤርምያስ ምዕራፍ 25 ቁጥር 30 እና 31 እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “እግዚአብሔር በላይ ሆኖ ይጮኻል፣ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፣ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ክርክር አለውና፣ ድምፅ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፣ ኃጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፣ ይላል እግዚአብሔር።” የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ከመጠጣት የሚያመልጥ ብሔር አይኖርም። ስለዚህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሙሉ አራቱ መላእክት የይሖዋን የቁጣ አውሎ ነፋስ ከመልቀቃቸው በፊት በአስቸኳይ ራሳቸውን ከብሔራቱ ክፋት መለየት ይኖርባቸዋል። በእርግጥም ይህ ዐውሎ ነፋስ በጣም ኃይለኛ ነው። ምክንያቱም የኤርምያስ ትንቢት በቁጥር 32 እና 33 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦
20. የይሖዋን ፍርድ ኃይለኛነት በግልጽ የሚያሳየው የትኛው መግለጫ ነው? ይህ እርምጃ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
20 “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፣ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፣ ጽኑም ዐውሎ ነፋስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይከማቹም አይቀበሩምም።” በእርግጥም በጣም የሚያሰቅቅ ትርዒት ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ቃል የገባው ገነት ከመምጣቱ በፊት ምድርን ለማጽዳት ይህን የመሰለ እርምጃ መወሰዱ የግድ አስፈላጊ ነው።
የሚያለቅሱና የሚጮኹ እረኞች
21, 22. (ሀ) በኤርምያስ 25:34–36 ላይ የተገለጹት የእስራኤል “እረኞች” እነማን ናቸው? እንዲያለቅሱ የሚገደዱትስ ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ቁጣ ሊቀበሉ የሚገባቸው ዘመናዊዎቹ እረኞች እነማን ናቸው? ይህስ ቁጣ በእነርሱ ላይ መውረዱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
21 ቁጥር 34 እስከ 36 እንዲህ በማለት ስለ ይሖዋ ፍርድ ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል፦ “ትታረዱና ትበተኑ ዘንድ ቀናችሁ ደርሶአልና፣ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች አልቅሱ ጩኹም፤ እናንተ የመንጋ አውራዎች፣ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። ሽሽትም ከእረኞች ማምለጥም ከመንጋ አውራዎች ይጠፋል። እግዚአብሔር ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል።”
22 እነዚህ እረኞች እነማን ናቸው? ቀደም ሲል የይሖዋን ቁጣ የጠጡት ሃይማኖታዊ መሪዎች አይደሉም። በኤርምያስ 6:3 ላይ የተገለጹትና ይሖዋን በመቃወም ሠራዊታቸውን አግተልትለው ያሰለፉት ወታደራዊ እረኞች ናቸው። ተገዥዎቻቸውን በመበዝበዝ ራሳቸውን ያበለጸጉት የፖለቲካ ገዥዎች ናቸው። አብዛኞቹ አጭበርባሪዎችና በሥልጣን የሚባልጉ ናቸው። በድኅነት ሥር በሚማቅቁ አገሮች የሚኖሩትን ብዙ ሕዝቦች የጨረሰውን ረሀብ ለማቃለል አልፈጠኑም። በአነስተኛ ወጪ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከሞት ሊያድን የሚችለውን የሕክምና እርዳታና አልሚ ምግብ ሳይሰጡ “የመንጋ አውራዎች” የሆኑትን በጦር መሣሪያ የሚነግዱትን ቱጃሮችና አካባቢያችንን የሚያበላሹትን ስግብግቦች አበልጽገዋል።
23. ይሖዋ የጥፋት እርምጃውን ከወሰደ በኋላ የሰይጣን ግዛት ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚወድቅ ግለጽ።
23 ኤርምያስ ምዕራፍ 25 ቁጥር 37 እና 38 በራስ ወዳድነት ለራሳቸው ብቻ ሰላም ለማግኘት ስለፈለጉት ስለ እነዚህ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት መደምደሙ አያስደንቅም፦ “ከእግዚአብሔር ጽኑ ቁጣ የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። እንደ አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቁጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።” በእርግጥም ባድማ ትሆናለች! የይሖዋ የቁጣ ትኩሳት ራእይ 19:15, 16 ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” በተባለው እንዲሁም አሕዛብን በብረት በትር በሚጠብቀው የይሖዋ “ሰይፍ” በኩል ይገለጣል። ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል?
24. የሐሰት ሃይማኖትና የቀረው የሰይጣን ዓለም መጥፋት ጻድቅ ለሆኑት የሰው ልጆች ምን በረከቶች ያመጣላቸዋል?
24 ማዕበል ወይም ከባድ አውሎ ነፋስ በተነሳበት አካባቢ ኖራችሁ ታውቃላችሁ? በጣም የሚያስፈራ ነው። በማግስቱ ጠዋት ግን አካባቢው ሁሉ በፍርስራሽ የተሞላ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የአየሩ ሁኔታ በጣም ጸጥ ያለና የሚያስደስት ስለሚሆን ይሖዋ ይህን የመሰለ ጥሩ ቀን ስላመጣ እንድታመሰግኑት ትገፋፋላችሁ። በተመሳሳይ ሁኔታ የታላቁ መከራ አውሎ ነፋስና ማዕበል ጋብ ሲል ይሖዋ ጠብቆ ከጥፋቱ ስላተረፋችሁና የጸዳችውን ምድር ወደ ገነትነት ለመለወጥ በሚያከናውነው ሥራ ለመካፈል ዝግጁ ስለሆናችሁ ምድርን እያያችሁ በአመስጋኝነት ትሞላላችሁ። ይሖዋ ከአሕዛብ ጋር ያደረገው ክርክር ወደ ታላቁ መደምደሚያው ይደርሳል። ስሙ ይቀደሳል፤ ፈቃዱም በመሲሐዊው መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ሥር በምድር ላይ የሚፈጸምበት መንገድ ይጠረጋል። ይህች መንግሥት ቶሎ ትምጣልን!
የዚህን ርዕስ አንቀጽ 5–24 መከለስ
◻ አምላክ የፈረደው በየትኛው የሕዝበ ክርስትና የግብዝነት መንገድ ላይ ነው?
◻ ይህን ፍርድ በሚመለከት በኤርምያስ 25:12–38 ላይ ምን ሰፋ ያለ መግለጫ ተሰጥቷል?
◻ ሁሉም ብሔራት እንዲጠጡት የሚቀርብላቸው የበቀል ጽዋ ምንድን ነው?
◻ የሚያለቅሱትና የሚጮኹት እረኞች እነማን ናቸው? የተጨነቁበትስ ምክንያት ምንድን ነው?
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል18]
ይሖዋ ሕዝበ ክርስትናን የሚያጠፋበትን መሣሪያ መርጧል
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል23]
ከታላቁ መከራ አውሎ ነፋስ በኋላ የጸዳች ምድር ትታያለች