የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ነሐሴ 2017
ከነሐሴ 7-13
it-2-E 1136 አን. 4
ጢሮስ
በከተማዋ ላይ የደረሰው ጥፋት። ናቡከደነጾር ጢሮስን ከቦ በቆየባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ሠራዊቱ ከባድ ሥራ አከናውነዋል። የራስ ቁራቸው ጸጉራቸውን ይፈገፍገው ስለነበር ‘ራሳቸው የተመለጠ’ ከመሆኑም ሌላ የከበባውን ግንብ ለመገንባት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ይሸከሙ ስለነበር ‘ትከሻቸው ተልጧል።’ ይሖዋ በጢሮስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ለማስፈጸም ናቡከደነጾርን እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፤ ሆኖም ናቡከደነጾር ለዚህ ምንም “ደሞዝ” ስላልተቀበለ ይሖዋ የግብፅን ሀብት እንደ ካሳ አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል። (ሕዝ 29:17-20) የታሪክ ምሁር የሆነው ጆሴፈስ እንደገለጸው ከበባው ለ13 ዓመታት የዘለቀ ሲሆን (አጌንስት አፒዮን፣ ጥራዝ 1፣ 156 [21]) ይህም ባቢሎናውያንን ከፍተኛ ወጪ አስወጥቷቸዋል። የዓለም የታሪክ መዛግብት የናቡከደነጾር ከበባ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበር የሚገልጹት ነገር የለም። ሆኖም በዚህ ከበባ የበርካታ ጢሮሳውያን ሕይወት እንዳለፈና ብዙ ንብረት እንደወደመ መገመት አያዳግትም።—ሕዝ 26:7-12
it-1-E 698 አን. 5
ግብፅ፣ ግብፃዊ
በናቡከደነጾር 37ተኛ የግዛት ዘመን (588 ዓ.ዓ.) እንደተጻፈ የሚታመን አንድ የባቢሎናውያን ጽሑፍ ተገኝቷል፤ ይህ ጽሑፍ ናቡከደነጾር በግብፅ ላይ ስላካሄደው ወረራ ይናገራል። ጽሑፉ የሚናገረው ስለ ናቡከደነጾር የመጀመሪያ ወረራ ይሁን ከዚያ በኋላ ስላካሄዳቸው ሌሎች ወታደራዊ ወረራዎች በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ያም ሆነ ይህ፣ ናቡከደነጾር የአምላክ ሕዝቦች ጠላት በሆነችው በጢሮስ ላይ ይሖዋ ያስተላለፈውን ፍርድ በማስፈጸም ላከናወነው ወታደራዊ አገልግሎት የግብፅን ሀብት እንደ ደሞዝ ተቀብሏል።—ሕዝ 29:18-20፤ 30:10-12
g86-E 11/8 27 አን. 4-5
ሁሉንም ዓይነት ግብር መክፈል ይኖርብናል?
የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ፈጣሪያችን ራሱ አንድ ዓለማዊ መንግሥት ላከናወነለት አገልግሎት ክፍያውን በመስጠት የተወውን ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ በጽድቅ ቁጣው ተነሳስቶ የጥንቷ የጢሮስ ከተማ እንድትጠፋ ፍርድ አስተላልፎ ነበር። አምላክ ይህን ፍርድ ለማስፈጸም በንጉሥ ናቡከደነጾር ሥር ያለውን የባቢሎንን ኃያል ወታደራዊ ሠራዊት ተጠቅሟል። ባቢሎን ጢሮስን ድል ያደረገች ቢሆንም ወረራው ብዙ ወጪ አስወጥቷታል። በመሆኑም ይሖዋ ባቢሎናውያን ላከናወኑት አገልግሎት ደሞዝ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተሰምቶታል። በሕዝቅኤል 29:18, 19 ላይ የሚገኘው ይሖዋ የተናገረው ቃል እንዲህ ይላል፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ሠራዊቱ በጢሮስ ላይ ታላቅ ግዳጅ እንዲፈጽም አደረገ። . . . ይሁን እንጂ እሱም ሆነ ሠራዊቱ በጢሮስ ላይ ላፈሰሱት ጉልበት ያገኙት ዋጋ የለም። ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ የግብፅን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር እሰጣለሁ፤ እሱም ሀብቷን ያግዛል፤ በእጅጉ ይበዘብዛል እንዲሁም ይመዘብራል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደሞዝ ይሆናል።’”
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናቡከደነጾር ትዕቢተኛና ራስ ወዳድ እንዲሁም አረማዊ የጣዖት አምላኪ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በተጨማሪም የባቢሎን መንግሥትም ሆነ ሠራዊቱ የማረኳቸውን ሰዎች በማሠቃየት ይታወቁ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንደማይቀበለው የታወቀ ነው፤ ሆኖም በእሱ ዘንድ ዕዳ ዕዳ ነው፤ በመሆኑም ዕዳውን ሙሉ በሙሉ ከፍሏል።
it-2-E 604 አን. 4-5
ፍጽምና
የመጀመሪያው ኃጢአተኛና የጢሮስ ንጉሥ። በዮሐንስ 8፡44 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ቃልና በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኘው ታሪክ እንደሚያመለክተው የሰው ልጅ ኃጢአት ከመሥራቱና ፍጽምናውን ከማጣቱ በፊት በመንፈሳዊው ዓለም ኃጢአት ተፈጽሞ ነበር። ሕዝቅኤል 28:12-19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሙሾ የወረደው ‘ለጢሮስ ንጉሥ’ ቢሆንም ይህ ሙሾ መጀመሪያ ኃጢአት የፈጸመው የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ከተከተለው አካሄድ ጋር በተያያዘም ይሠራል። ‘የጢሮስ ንጉሥ’ መታበይ፣ ራሱን እንደ ‘አምላክ’ መቁጠሩ፣ “ኪሩብ” ተብሎ መጠራቱ እንዲሁም ‘የአምላክ የአትክልት ስፍራ ኤደን’ መጠቀሱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን ዲያብሎስ ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ በትዕቢት እንደተነፋ፣ በኤደን ከታየው እባብ ጋር ተዛማጅነት እንዳለው እንዲሁም “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንደሆነ ይናገራል።—1ጢሞ 3:6፤ ዘፍ 3:1-5, 14, 15፤ ራእይ 12:9፤ 2ቆሮ 4:4
በጢሮስ ከተማ ይኖር የነበረውና “ፍጹም ውብ ነኝ” ይል የነበረው ስሙ ያልተጠቀሰ ንጉሥ፣ ‘ጥበብ የተሞላና ፍጹም [የዕብራይስጡ ቅጽል፣ ካላል] ውበት የተላበሰ’ ከመሆኑም ሌላ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በደል እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ ‘በመንገዱ ሁሉ ምንም እንከን አልነበረበትም [ዕብራይስጥ፣ ታሚም]።’ (ሕዝ 27:3፤ 28:12, 15) በሕዝቅኤል ላይ የሚገኘው ሙሾ በዋነኛነት ወይም በቀጥታ የተነገረው ለአንድ የተወሰነ ንጉሥ ሳይሆን በጢሮስ ለሚነሱ ነገሥታት በሙሉ ሊሆን ይችላል። (ስሙ ስላልተገለጸ ‘የባቢሎን ንጉሥ’ ከሚናገረው በኢሳ 14:4-20 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር አወዳድር።) እንዲህ ከሆነ፣ የጢሮስን ንጉሥ በተመለከተ “ምንም እንከን አልነበረብህም” የተባለው በንጉሥ ዳዊትና በንጉሥ ሰለሞን የግዛት ዘመን የነበሩት የጢሮስ ነገሥታት ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ወዳጅነትና ትብብር ስለነበራቸው ሊሆን ይችላል፤ በዚያን ወቅት ጢሮስ በሞሪያ ተራራ ላይ ለሚከናወነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ የግንባታ ሥራም እንኳ ድጋፍ አድርጋ ነበር። ከዚህ አንጻር ጢሮስ የይሖዋ ሕዝቦች ለነበሩት ለእስራኤላውያን መጀመሪያ ላይ በነበራት አመለካከት ረገድ ምንም እንከን አልነበረባትም ማለት ይቻላል። (1ነገ 5:1-18፤ 9:10, 11, 14፤ 2ዜና 2:3-16) ከጊዜ በኋላ የተነሱት ነገሥታት ግን እንዲህ ያለውን ‘እንከን የሌለበት’ አካሄድ አልተከተሉም፤ በመሆኑም አምላክ በነቢዩ ኢዩኤል፣ አሞጽና ሕዝቅኤል አማካኝነት በጢሮስ ላይ የፍርድ መልእክት አስተላልፏል። (ኢዩ 3:4-8፤ አሞጽ 1:9, 10) ትንቢቱ ‘የጢሮስ ንጉሥ’ የተከተለው አካሄድ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ከተከተለው አካሄድ ጋር ያለውን ተመሳሳይነት የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ “ፍጽምና” እና “እንከን የለሽነት” የሚሉት ቃላት አንጻራዊ በሆነ መንገድ ሊሠራባቸው እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ይሆናል።
ከነሐሴ 14-20
it-2-E 1172 አን. 2
ጠባቂ
ምሳሌያዊ ፍቺ። ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ ጠባቂ ሆነው የሚያገለግሉ ነቢያትን አስነስቶላቸው ነበር፤ (ኤር 6:17) እነዚህ ነቢያት ደግሞ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ ጠባቂ ሆነው ስለሚያገለግሉ ሰዎች የተናገሩበት ጊዜ አለ። (ኢሳ 21:6, 8፤ 52:8፤ 62:6፤ ሆሴዕ 9:8) በጠባቂ የተመሰሉት ነቢያት ክፉዎችን ስለሚመጣባቸው ጥፋት የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ነበረባቸው፤ እንዲህ ሳያደርጉ ከቀሩ በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናሉ። እርግጥ ነው፣ ሰዎቹ ማስጠንቀቂያውን ሰምተው ምላሽ ካልሰጡ ደሙ በራሳቸው ላይ ይሆናል። (ሕዝ 3:17-21፤ 33:1-9) ታማኝ ያልሆነ ነቢይ ከዕውር ጠባቂ ወይም መጮኽ ከማይችል ውሻ ጋር ተመሳስሏል።—ኢሳ 56:10
w88-E 1/1 28 አን. 13
ከደም ተጠያቂነት መራቅ
13 ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ስለ መጪው የአምላክ ፍርድ ሰዎችን እንዲያስጠነቅቁ የተሰጣቸው ኃላፊነት ሕዝቅኤል ከተሰጠው ኃላፊነት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሕዝቅኤል ለእስራኤል ቤት ጠባቂ ተደርጎ ተሹሞ ነበር። እስራኤላውያን ከመጥፎ መንገዳቸው ካልተመለሱ የቅጣት ፍርድ እየመጣባቸው እንዳለ የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ነበረበት። ሕዝቅኤል የጠባቂነት ኃላፊነቱን ሳይወጣ ቢቀር ፍርዱ በክፉዎች ላይ መምጣቱ አይቀርም፤ ሆኖም የእነዚህ ሰዎች ደም ቸልተኛ በሆነው ጠባቂ ራስ ላይ ይሆናል። ይህም ይሖዋ፣ ያስተላለፈውን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ ያለውን አቋም ያሳያል፤ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በክፉው ሰው ሞት ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እፈልጋለሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለምን ትሞታላችሁ?”—ሕዝ 33:1-11
w91-E 3/15 17 አን. 16-17
ሰዎቹ ግድየለሽ መሆናቸው ተስፋ አላስቆረጠውም
16 በተጨማሪም ሕዝቅኤል የሰዎችን ግድየለሽነት ወይም ፌዘኝነት ተቋቁሞ የይሖዋን ትእዛዝ በመፈጸም እንዲሁም ተስፋ ባለመቁረጥ መልካም ምሳሌ ትቶልናል። እኛም በንጹሑ ቋንቋ ላይ ከሚደረገው ለውጥ ጋር እኩል ለመራመድ ጥረት በማድረግ ሠረገላውን የሚነዳውን ንጉሥ ተከትለን መጓዝ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን እሱ የሚሰጠንን ትእዛዛት ተግባራዊ ለማድረግ ያስታጥቀናል፤ እንዲሁም የይሖዋን የፍርድ መልእክት በምንነግራቸው ሰዎች ግድየለሽነት ወይም ፌዝ ተስፋ እንዳንቆርጥ ጥንካሬ ይሰጠናል። አምላክ ሕዝቅኤልን እንዳስጠነቀቀው ሁሉ እኛንም አንዳንዶች መልእክታችንን እንደሚቃወሙ እንዲሁም ግትርና ልበ ደንዳና እንደሚሆኑ አስጠንቅቆናል። ሌሎች ደግሞ ይሖዋን መስማት ስለማይፈልጉ ለምንሰብከው መልእክት ጆሮ አይሰጡም። (ሕዝቅኤል 3:7-9) ይሖዋ ግብዞች የሚሆኑ ሰዎችም እንደሚኖሩ ተናግሯል፤ ሕዝቅኤል 33:31, 32 እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እንደ ሕዝቤ በፊትህ ለመቀመጥ ተሰብስበው ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም በተግባር አያውሉትም። በአፋቸው ይሸነግሉሃልና፤ ልባቸው ግን አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይስገበገባል። እነሆ፣ አንተ ለእነሱ ባማረ ድምፅ እንደሚዘፈንና በባለ አውታር መሣሪያ አሳምረው እንደሚጫወቱት የፍቅር ዘፈን ሆነህላቸዋል። ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም አንዳቸውም አያደርጉትም።”
17 ሕዝቅኤል ይህን መልእክት ማወጁ ምን ውጤት ያስገኛል? ቁጥር 33 እንዲህ ይላል፦ “ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ፣ ደግሞም ይፈጸማል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ ያውቃሉ።” እነዚህ ቃላት ሕዝቅኤል ሕዝቡ አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ ተስፋ እንዳልቆረጠ ያሳያሉ። የሌሎች ግድየለሽነት እሱም ግድየለሽ እንዲሆን አላደረገውም። ሰዎቹ መልእክቱን ቢሰሙም ባይሰሙም፣ እሱ ግን አምላክን በመታዘዝ ተልእኮውን ፈጽሟል።
ከነሐሴ 21-27
w88-E 9/15 24 አን. 11
“እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”
11 ቀሪዎቹ ወደ ይሁዳ ከተመለሱ በኋላ፣ ባድማ ሆኖ የነበረው ምድር ተለውጦ ፍሬያማ እንደሆነው “እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ” ሆኗል። (ሕዝቅኤል 36:33-36ን አንብብ።) በተመሳሳይም ይሖዋ በአንድ ወቅት ባድማ የነበረውን የቅቡዓን ቀሪዎች ግዛት ከ1919 ጀምሮ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ ተካፋይ ወደሆኑበት ፍሬያማ መንፈሳዊ ገነት ለውጦታል። ይህ መንፈሳዊ ገነት ቅዱስ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩበት እንደመሆኑ መጠን ራሱን የወሰነ እያንዳንዱ ክርስቲያን የዚህ ገነት ንጽሕና ተጠብቆ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለበት።—ሕዝቅኤል 36:37, 38
ከነሐሴ 28–መስከረም 3
w89-E 8/15 14 አን. 20
ወደ ገነት የሚመልሰውን መንገድ መክፈት
20 ነገር ግን ብሔራት ትተዉት የሚሄዱት የጦር መሣሪያ በሙሉ ምን ይሆናል? በእሳት መቃጠል የሚችሉትን የመሣሪያዎቹን ክፍሎች ለማስወገድ ስለሚፈጀው ጊዜ የተሰጠው ምሳሌያዊ መግለጫ የጦር መሣሪያዎቹ ብዛት ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠቁማል። (ሕዝቅኤል 39:8-10) ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች ብሔራት የተዉአቸውን የጦር መሣሪያዎች ጠቃሚ ነገሮችን ለመሥራት ያውሏቸው ይሆናል።—ኢሳይያስ 2:2-4