ምዕራፍ 133
የኢየሱስ አስከሬን ተዘጋጅቶ ተቀበረ
ማቴዎስ 27:57–28:2 ማርቆስ 15:42–16:4 ሉቃስ 23:50–24:3 ዮሐንስ 19:31–20:1
የኢየሱስን አስከሬን ከእንጨቱ ላይ አወረዱት
አስከሬኑ ለቀብር ተዘጋጀ
ሴቶቹ መቃብሩን ባዶ ሆኖ አገኙት
ዓርብ፣ ኒሳን 14 ምሽት እየተቃረበ ነው። ኒሳን 15 ላይ የሚውለው ሰንበት ፀሐይ ስትጠልቅ ይጀምራል። ኢየሱስ ሞቷል፤ ከጎኑ የተሰቀሉት ሁለቱ ዘራፊዎች ግን አሁንም በሕይወት አሉ። ሕጉ፣ በድን ‘በእንጨቱ ላይ ማደር’ እንደሌለበት ከዚህ ይልቅ “በዚያው ዕለት” መቀበር እንዳለበት ይናገራል።—ዘዳግም 21:22, 23
ዓርብ ከሰዓት በኋላ የዝግጅት ቀን ተብሎ ይጠራል፤ ምክንያቱም ሰዎች ምግብ የሚያዘጋጁትና ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ ሊቆዩ የማይችሉትን ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች የሚያጠናቅቁት በዚህ ቀን ነው። ፀሐይ ስትጠልቅ ድርብ ወይም “ታላቅ” ሰንበት ይጀምራል። (ዮሐንስ 19:31) ለሰባት ቀን የሚከበረው የቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ኒሳን 15 ነው፤ የዚህ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደግሞ ምንጊዜም ሰንበት ነው። (ዘሌዋውያን 23:5, 6) በዚህ ዓመት የበዓሉ የመጀመሪያ ቀን ከሳምንታዊው ሰንበት ይኸውም ከሰባተኛው ቀን ጋር ተገጣጥሟል።
አይሁዳውያን ጲላጦስ ፊት ቀርበው የኢየሱስና አጠገቡ ያሉት የሁለቱ ዘራፊዎች ሞት እንዲፋጠን ያደርግ ዘንድ ጠየቁት። ይህ የሚደረገው እንዴት ነው? እግሮቻቸውን በመስበር ነው። ይህም በእግሮቻቸው ተጠቅመው ሰውነታቸውን ወደ ላይ በመግፋት አየር መሳብ በጣም ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ስለዚህ ወታደሮቹ መጥተው የሁለቱን ዘራፊዎች እግር ሰበሩ። ኢየሱስ ግን መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም። ይህም “አጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤ አንዳቸውም ቢሆኑ አልተሰበሩም” የሚለው የመዝሙር 34:20 ጥቅስ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አደረገ።
ከወታደሮቹ አንዱ ኢየሱስ እንደሞተ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ለመሆን ጎኑን በጦር ወጋው፤ ጦሩም ልቡ አካባቢ በስቶ ስለገባ ወዲያው “ደምና ውኃ ፈሰሰ።” (ዮሐንስ 19:34) ይህ ደግሞ “እነሱም የወጉትን ያዩታል” የሚለው ሌላ ትንቢት እንዲፈጸም ያደርጋል።—ዘካርያስ 12:10
አርማትያስ ከተባለች ከተማ የመጣ ዮሴፍ የሚባል “ሀብታም” እና የተከበረ የሳንሄድሪን አባል ኢየሱስ ሲገደል በቦታው ተገኝቷል። (ማቴዎስ 27:57) ዮሴፍ “ጥሩና ጻድቅ ሰው” እንደሆነ እንዲሁም ‘የአምላክን መንግሥት እንደሚጠባበቅ’ ተገልጿል። “ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር” ቢሆንም ‘አይሁዳውያንን ስለፈራ ይህን ለማንም አልተናገረም።’ ያም ቢሆን ሸንጎው በኢየሱስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ አልደገፈም። (ሉቃስ 23:50፤ ማርቆስ 15:43፤ ዮሐንስ 19:38) ዮሴፍ ራሱን አደፋፍሮ ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። ጲላጦስም ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ ለማወቅ የመቶ አለቃውን ጠርቶ ጠየቀው። መሞቱን ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላም አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት።
ዮሴፍ ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ከገዛ በኋላ የኢየሱስን አስከሬን ከእንጨቱ ላይ አወረደው። ከዚያም አስከሬኑን ለቀብር ለማዘጋጀት በበፍታው ገነዘው። “ቀደም ሲል በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስም” አስከሬኑን በማዘጋጀቱ ሥራ አገዘ። (ዮሐንስ 19:39) ኒቆዲሞስ 30 ኪሎ ግራም ገደማ የሚሆን ውድ የሆነ የከርቤና የእሬት ድብልቅ ይዞ መጣ። ከዚያም ጥሩ መዓዛ ባላቸው በእነዚህ ቅመሞች ተጠቅመው የኢየሱስን አስከሬን በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ መሠረት ገነዙት።
ዮሴፍ ማንም ሰው ተቀብሮበት የማያውቅ ከዓለት ተፈልፍሎ የተሠራ አዲስ የመቃብር ስፍራ በአቅራቢያው አለው፤ የኢየሱስን አስከሬን እዚያ አሳረፉት። ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባለው መቃብሩን ዘጉት። አስከሬኑን ሰንበት ከመጀመሩ በፊት ለመቅበር ሲባል ዝግጅቱ የተከናወነው በጥድፊያ ነው። መግደላዊቷ ማርያምና የትንሹ ያዕቆብ እናት የሆነችው ማርያም የኢየሱስን አስከሬን ለቀብር በማዘጋጀቱ ሥራ አስተዋጽኦ አበርክተው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሴቶች ከሰንበት በኋላ የኢየሱስን አስከሬን ለመቀባት የሚጠቀሙባቸውን “ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችና ዘይቶች ለማዘጋጀት” በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሄዱ።—ሉቃስ 23:56
በማግስቱ ማለትም በሰንበት ቀን የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ “ያ አስመሳይ በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሳለሁ’ ብሎ የተናገረው ትዝ አለን። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡ ‘ከሞት ተነስቷል!’ እንዳይሉ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን። አለዚያ ይህ የኋለኛው ማታለያ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል።” ጲላጦስም “ጠባቂዎች መውሰድ ትችላላችሁ። ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው።—ማቴዎስ 27:63-65
እሁድ ጠዋት ማለዳ ላይ መግደላዊቷ ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሌሎች ሴቶች የኢየሱስን አስከሬን ለመቀባት ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞች ይዘው ወደ መቃብሩ ሄዱ። እርስ በርሳቸውም “በመቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል?” ተባባሉ። (ማርቆስ 16:3) ሆኖም ታላቅ የምድር መናወጥ ተከስቷል። ከዚህም ሌላ የአምላክ መልአክ ድንጋዩን አንከባሎታል፤ ጠባቂዎቹ ሄደዋል፣ መቃብሩም ባዶ ነው!