አንድ መንጋ አንድ እረኛ
“እኔን የተከተላችሁኝ እናንተም በአሥራ ሁለት ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።”—ማቴ. 19:28
1. ይሖዋ ከአብርሃም ዘሮች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረው? እንዲህ ሲባል ግን ስለ ሌሎች ብሔራት ግድ አይሰጠውም ነበር ማለት ነው?
ይሖዋ አብርሃምን ይወደው ስለነበር ለእሱ ዘሮች ጽኑ ፍቅር አሳይቷል። ይሖዋ ከ15 ለሚበልጡ መቶ ዓመታት የአብርሃም ዘር የነበሩትን እስራኤላውያንን የተመረጠ ሕዝብ ወይም “ርስት” አድርጎ ተመልክቷቸው ነበር። (ዘዳግም 7:6ን አንብብ።) እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ስለ ሌሎች ብሔራት ፈጽሞ ግድ አይሰጠውም ነበር ማለት ነው? በፍጹም። በዚያን ጊዜ እስራኤላዊ ያልሆነ ግለሰብ ይሖዋን ማምለክ ከፈለገ ልዩ ብሔር ከሆኑት ከእስራኤላውያን ጋር መቀላቀል ይችል ነበር። ወደ ይሁዲነት የተለወጡት እነዚህ ሰዎች እንደ ብሔሩ አባል ተደርገው ይታያሉ፤ እንዲሁም ከእስራኤል ብሔር ጋር በእኩል ዓይን ይታዩ ነበር። (ዘሌ. 19:33, 34) እነሱም የይሖዋን ሕጎች በሙሉ መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘሌ. 24:22
2. ኢየሱስ ምን አስገራሚ ሐሳብ ተናግሯል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?
2 ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት አይሁዳውያን “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” በማለት አንድ አስገራሚ ሐሳብ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 21:43) ይህ አዲስ ሕዝብ የሚያቅፈው እነማንን ነው? ይህ ለውጥ እኛን የሚነካው እንዴት ነው?
አዲሱ ሕዝብ
3, 4. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን አዲስ ሕዝብ ማንነት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ይህ አዲስ ሕዝብ ያቀፈው እነማንን ነው?
3 ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን አዲስ ሕዝብ ማንነት በግልጽ ተናግሯል። ለእምነት ባልደረቦቹ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:9) አስቀድሞ እንደተነገረው ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው የተቀበሉት ሥጋዊ አይሁዳውያን የዚህ አዲስ ሕዝብ የመጀመሪያ አባላት ሆነዋል። (ዳን. 9:27ሀ፤ ማቴ. 10:6) ጴጥሮስ ቀጥሎ “እናንተ በአንድ ወቅት አንድ ሕዝብ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ” ብሎ ስለተናገረ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ሰዎች የዚህ ሕዝብ አባላት ሆነዋል።—1 ጴጥ. 2:10
4 እዚህ ላይ ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ስለ እነማን ነበር? ጴጥሮስ በደብዳቤው መጀመሪያ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “[አምላክ] በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናል፤ እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል።” (1 ጴጥ. 1:3, 4) በመሆኑም ይህ አዲስ ሕዝብ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸውን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የአምላክ እስራኤል’ ናቸው። (ገላ. 6:16) ሐዋርያው ዮሐንስ የእነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ቁጥር 144,000 እንደሆነ በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ ሰዎች “ካህናት” ሆነው ለማገልገል እንዲሁም “[ከኢየሱስ] ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት” ለመግዛት ‘ለአምላክና ለበጉ በኩራት ሆነው ከሰዎች መካከል የተዋጁ’ ናቸው።—ራእይ 5:10፤ 7:4፤ 14:1, 4፤ 20:6፤ ያዕ. 1:18
ሌሎችስ ሊካተቱ ይችላሉ?
5. (ሀ) ‘የአምላክ እስራኤል’ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው ማንን ነው? (ለ) “እስራኤል” የሚለው ቃል ሰፋ ያለ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው?
5 በገላትያ 6:16 ላይ የሚገኘው ‘የአምላክ እስራኤል’ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር ከቅቡዓን ክርስቲያኖች በተጨማሪ ሌሎችን ለማመልከት እንደ ምሳሌ የተጠቀመባቸው ጊዜያት አሉ? የዚህን ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑት ሐዋርያት በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ ላይ ማግኘት እንችላለን፦ “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማዕዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ እንዲሁም በዙፋን ተቀምጣችሁ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እንድትፈርዱ ነው።” (ሉቃስ 22:28-30) ይህ ጥቅስ ፍጻሜውን የሚያገኘው “በዳግም ፍጥረት” ወይም ሁሉ ነገር በሚታደስበት በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ነው።—ማቴዎስ 19:28ን አንብብ።
6, 7. በማቴዎስ 19:28 እና በሉቃስ 22:30 ላይ የተጠቀሱት “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” የሚያመለክቱት እነማንን ነው?
6 በሺህ ዓመት ግዛት ወቅት 144,000ዎቹ በሰማይ ነገሥታት፣ ካህናትና ፈራጆች ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 20:4) የሚፈርዱትና የሚገዙት ማንን ነው? በማቴዎስ 19:28 እና በሉቃስ 22:30 ላይ እንደተገለጸው “በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” ላይ ይፈርዳሉ። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” የሚያመለክቱት እነማንን ነው? በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳድሩትን ሆኖም በንጉሣዊ ካህናት ክፍል ውስጥ የማይካተቱትን በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ያመለክታሉ። (የሌዊ ነገድ በ12ቱ ሥጋዊ እስራኤላውያን ነገዶች ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም።) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተወከሉት፣ 144,000ዎቹ በሚያከናውኑት የክህነት አገልግሎት መንፈሳዊ ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ የክህነት ቦታ የሌላቸውና ከክህነት አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችም የአምላክ ሕዝቦች ናቸው። አምላክ ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ይቀበላቸዋል። እነዚህ ሰዎች በጥንት ጊዜ በነበሩት የአምላክ ሕዝቦች መመሰላቸው የተገባ ነው።
7 ሐዋርያው ዮሐንስ 144,000 የሆኑ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከታላቁ መከራ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ማኅተም እንደተደረገባቸው ከተመለከተ በኋላ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ “ከሁሉም ብሔራት” የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መመልከቱም የተገባ ነው። (ራእይ 7:9) እነዚህ ሰዎች ከታላቁ መከራ ተርፈው ወደ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ይገባሉ። ከዚያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው ከእነሱ ጋር ይቀላቀላሉ። (ዮሐ. 5:28, 29፤ ራእይ 20:13) እነዚህ ሁሉ “በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን ኢየሱስና ከእሱ ጋር ተባብረው የሚገዙት 144,000ዎቹ የሚፈርዱት በእነዚህ ላይ ነው።—ሥራ 17:31፤ 24:15፤ ራእይ 20:12
8. በዓመታዊው የማስተሰረያ ቀን ይከናወኑ የነበሩ ነገሮች በ144,000ዎቹና በቀሪው የሰው ዘር መካከል ላለው ግንኙነት ጥላ የሚሆኑት እንዴት ነው?
8 በዓመታዊው የማስተሰረያ ቀን ይከናወኑ የነበሩ ነገሮች በ144,000ዎቹና በቀሪው የሰው ዘር መካከል ላለው ግንኙነት ጥላ ይሆናሉ። (ዘሌ. 16:6-10) ሊቀ ካህናቱ በመጀመሪያ “ለራሱና ለቤተ ሰቡ” አንድ ወይፈን የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ነበረበት። በመሆኑም የኢየሱስ መሥዋዕት በመጀመሪያ ከእሱ ጋር በሰማይ የበታች ካህናት ሆነው ለሚያገለግሉት ኃጢአት ማስተሰረያ ሆኖ ያገለግላል። በተጨማሪም በጥንት ዘመን በማስተሰረያ ቀን ለተቀሩት እስራኤላውያን ኃጢአት ማስተሰረያ ሁለት አውራ ፍየሎች መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ ነበር። ካህን ሆኖ የሚያገለግለው ነገድ 144,000ዎቹን የሚያመለክት ሲሆን የተቀሩት እስራኤላውያን ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ያመለክታሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በማቴዎስ 19:28 ላይ “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በመንፈስ የተወለዱትንና ከኢየሱስ ጋር የበታች ካህናት ሆነው የሚያገለግሉትን ሳይሆን በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሰዎችን በሙሉ ነው።a
9. ሕዝቅኤል ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ ባየው ራእይ ውስጥ ካህናቱ እና ካህናት ያልሆኑት እስራኤላውያን የሚያመለክቱት እነማንን ነው?
9 ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ ራእይ ተመልክቶ ነበር። (ሕዝ. ከምዕ. 40 እስከ 48) በዚህ ራእይ ላይ በቤተ መቅደሱ የሚያገለግሉ ካህናት ከይሖዋ ምክርና እርማት ተቀብለው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር። (ሕዝ. 44:23-31) እንዲሁም የተለያዩ ነገዶች አባላት ለአምልኮና መሥዋዕት ለማቅረብ ይመጡ ነበር። (ሕዝ. 45:16, 17) በዚህ ራእይ ላይ ካህናቱ ቅቡዓኑን፣ ካህናት ያልነበሩት እስራኤላውያን ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። ራእዩ የካህናቱ ክፍል በንጹሕ አምልኮ ውስጥ አመራር እየሰጡ ሁለቱም ቡድኖች ተባብረው እንደሚሠሩ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
10, 11. (ሀ) እምነት በሚያጠናክር መንገድ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ የተመለከትነው የትኞቹ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ናቸው? (ለ) ስለ ሌሎች በጎች ምን ጥያቄ ይነሳል?
10 ኢየሱስ “ትንሽ መንጋ” የሆኑት ቅቡዓን ተከታዮቹ በሚገኙበት “ጉረኖ” ውስጥ ስለማይካተቱት “ሌሎች በጎች” ተናግሯል። (ዮሐ. 10:16፤ ሉቃስ 12:32) ኢየሱስ “እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ” በማለት ተናግሯል። የእነዚህን ቃላት ፍጻሜ መመልከት እንዴት እምነት የሚያጠናክር ነው! ሁለት የሰዎች ቡድን ይኸውም አነስተኛ የሆኑት የቅቡዓን ቡድንና የሌሎች በጎች ቡድን የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሳስረዋል። (ዘካርያስ 8:23ን አንብብ።) ሌሎች በጎች በመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ላይ የማገልገል መብት ባይኖራቸውም በቤተ መቅደሱ ውጨኛ አደባባይ ላይ ያገለግላሉ።
11 ይሁንና ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ካህናት ያልነበሩ የጥንት እስራኤላውያንን ሌሎች በጎችን ለማመልከት ይጠቀም ከነበረ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን መካፈል ይገባቸዋል? አሁን የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።
አዲሱ ቃል ኪዳን
12. ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው አዲስ ዝግጅት ምንድን ነው?
12 ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ለሕዝቡ አዲስ ዝግጅት እንዳደረገ ገልጿል፦ “ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው . . . ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (ኤር. 31:31-33) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት ለዘለቄታው ክብራማ ፍጻሜውን ያገኛል።—ዘፍጥረት 22:18ን አንብብ።
13, 14. (ሀ) የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች እነማን ናቸው? (ለ) የቃል ኪዳኑ ተጠቃሚዎችስ እነማን ናቸው? አዲሱን ቃል ኪዳን ‘የሚጠብቁት’ እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን አዲስ ቃል ኪዳን ጠቅሷል፦ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው።” (ሉቃስ 22:20፤ 1 ቆሮ. 11:25) ሁሉም ክርስቲያኖች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ይታቀፋሉ? በፍጹም። በዚያ ምሽት ከጽዋው እንደጠጡት ሐዋርያት ሁሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ናቸው።b ኢየሱስም በመንግሥቱ ከእሱ ጋር እንዲገዙ ከቃል ኪዳኑ ተካፋዮች ጋር ሌላ ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። (ሉቃስ 22:28-30) እነዚህ ክርስቲያኖች በመንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ።—ሉቃስ 22:15, 16
14 በኢየሱስ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ስለሚኖሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚዎች ናቸው። (ገላ. 3:8, 9) እነዚህ ክርስቲያኖች የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ባይሆኑም እንኳ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው የሚፈለግባቸውን በማሟላት ቃል ኪዳኑን ‘ይጠብቃሉ’፤ ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፦ “እርሱን ለማገልገል፣ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ጋር ያቈራኙ መጻተኞች፣ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም በመውደድ፣ እርሱንም በማምለክ፣ ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣ ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።” በመቀጠልም ይሖዋ “ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል” በማለት ተናግሯል።—ኢሳ. 56:6, 7
መካፈል ያለባቸው እነማን ናቸው?
15, 16. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮችን ከምን ነገር ጋር አያይዞ ገልጿቸዋል? (ለ) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን መካፈል የማይገባቸው ለምንድን ነው?
15 የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች “ወደ ቅዱሱ ስፍራ መግባት የሚያስችል ድፍረት” አላቸው። (ዕብራውያን 10:15-20ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ሊናወጥ የማይችለውን መንግሥት ይቀበላሉ።’ (ዕብ. 12:28) በመሆኑም አዲሱን ቃል ኪዳን ከሚወክለው “ጽዋ” መካፈል የሚገባቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የዚህ አዲስ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ከበጉ ጋር በጋብቻ እንደሚጣመሩ ቃል የተገባላቸው ክርስቲያኖች ናቸው። (2 ቆሮ. 11:2፤ ራእይ 21:2, 9) በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ የሚገኙት ሌሎች ተሰብሳቢዎች ሥነ ሥርዓቱን በአክብሮት ይከታተላሉ እንጂ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን አይካፈሉም።
16 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን የማይካፈሉበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ይህን ቂጣ በበላችሁና ከዚህ ጽዋ በጠጣችሁ ቁጥር ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ማወጃችሁን ትቀጥላላችሁ።” (1 ቆሮ. 11:26) ጌታ ‘የሚመጣው’ መቼ ነው? የሙሽራው ክፍል የሆኑትንና በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን በሰማይ ወደሚገኘው ቤታቸው ለመውሰድ በሚመጣበት ጊዜ ነው። (ዮሐ. 14:2, 3) በየዓመቱ የሚከበረው የጌታ እራት ሁልጊዜ የሚቀጥል ነገር እንዳልሆነ ከዚህ በግልጽ መመልከት ይቻላል። በምድር ላይ ‘የቀሩት’ የሴቲቱ ዘር አባላት በሙሉ በሰማይ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት እስኪያገኙ ድረስ ከዚህ ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን መካፈላቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 12:17) በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች ከዚህ ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን የሚካፈሉ ቢሆኑ ኖሮ ይህ በዓል ለዘላለም መከበሩን ይቀጥል ነበር።
‘የእኔ ሕዝብ ይሆናሉ’
17, 18. በሕዝቅኤል 37:26, 27 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚኖራቸውን አንድነት በተመለከተ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል፦ “ከእነርሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ቃል ኪዳኑም የዘላለም ይሆናል። አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ፤ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ። ማደሪያዬ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”—ሕዝ. 37:26, 27
18 ይህ አስደናቂ ትንቢት ይኸውም በክርስቲያኖች መካከል ሰላም እንደሚሰፍን የሚጠቁመው የሰላም ቃል ኪዳን ፍጻሜውን ማግኘቱ ለሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ጥቅም ያስገኛል። አዎን፣ ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ አገልጋዮቹ በሙሉ ሰላም እንደሚኖራቸው ዋስትና ሰጥቷል። ሁሉም የመንፈሱን ፍሬ እንዳፈሩ በግልጽ ይታያል። እዚህ ጥቅስ ላይ ንጹሕ ክርስቲያናዊ አምልኮን የሚያመለክተው የአምላክ መቅደስ በመካከላቸው ይገኛል። ማንኛውንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ስላስወገዱና ይሖዋን ብቻ አምላካቸው አድርገው ስለሚያመልኩ በእርግጥም ሕዝቦቹ ሆነዋል።
19, 20. ይሖዋ “የእኔ” ብሎ ከጠራው “ሕዝብ” መካከል የሚካተቱት እነማን ናቸው? አዲሱ ቃል ኪዳን ምን ነገር ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስችሏል።
19 በዘመናችን እነዚህ ሁለት ቡድኖች አንድ ሲሆኑ ማየት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው እጅግ ብዙ ሕዝቦች ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ባይኖራቸውም ከቅቡዓኑ ጋር ተባብረው በመሥራታቸው ኩራት ይሰማቸዋል። ራሳቸውን ከአምላክ እስራኤል ጋር አቆራኝተዋል። ይህን እርምጃ መውሰዳቸው ይሖዋ “የእኔ” ብሎ ከሚጠራው “ሕዝብ” ጋር እንዲካተቱ አስችሏቸዋል። የሚከተለው ትንቢት በእነሱ ላይ ፍጻሜውን ሲያገኝ እንመለከታለን፦ “በዚያ ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፤ የእኔም ሕዝብ ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ።”—ዘካ. 2:11፤ 8:21፤ ኢሳይያስ 65:22ን እና ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።
20 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት ይህ ሁሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስችሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ መጻተኞች ሞገሱን ያገኘው የይሖዋ ሕዝብ አባላት መሆን ችለዋል። (ሚክ. 4:1-5) በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተካተቱ ዝግጅቶችን በመቀበልና የኪዳኑን ሕጎች በመታዘዝ ይህን ቃል ኪዳን እየጠበቁ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (ኢሳ. 56:6, 7) ከአምላክ እስራኤል ጋር በመሆን ይህን በማድረጋቸው ቀጣይነት ያለው የተትረፈረፈ ሰላም በማግኘት ይባረካሉ። አንተም አሁንም ሆነ ለዘላለም ይህን በረከት እንድታገኝ ምኞታችን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በተመሳሳይም “ጉባኤ” የሚለው ቃል በዋነኝነት ቅቡዓኑን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዕብ. 12:23) ይሁንና “ጉባኤ” የሚለው ቃል ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ክርስቲያኖች ሊያመለክት ስለሚችል ሌላም ትርጉም ሊኖረው ይችላል።—የሚያዝያ 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-23 ተመልከት።
b ኢየሱስ የዚህ ቃል ኪዳን አስታራቂ ወይም መካከለኛ እንጂ ተካፋይ አይደለም። አስታራቂ እንደመሆኑ መጠን ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን እንዳልተካፈለ ግልጽ ነው።
ታስታውሳለህ?
• “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” እነማን ናቸው?
• ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ ያላቸው ሚና ምንድን ነው?
• ሁሉም ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን መካፈል ይገባቸዋል?
• በዘመናችን ምን ዓይነት አንድነት እንደሚኖር ትንቢት ተነግሯል?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ብዙ ሰዎች ከአምላክ እስራኤል ጋር በአንድነት እያገለገሉ ነው
1950 | 373,430
1970 | 1,483,430
1990 | 4,017,213
2009 | 7,313,173