ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የሚገልጽ ትምህርት
ኢዮብን ያገጠሙት ዓይነት ችግሮች የደረሱባቸው ሰዎች የሉም ማለት ይቻላል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብቱንና መተዳደሪያውን አጣ፤ ልጆቹ በሙሉ በአሳዛኝ ሁኔታ ሞቱ፤ እንዲሁም መጨረሻ ላይ በጣም የሚያሠቃይ በሽታ ያዘው። ወዳጆቹና ዘመዶቹ ባይተዋር ስላደረጉት ሚስቱ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው።—ኢዮብ 2:9፤ 19:13, 14
ሆኖም ኢዮብ ተመሳሳይ ፈተናዎች ላጋጠመው ማንኛውም ሰው ልዩ የብርታት ምንጭ ነው። የደረሰበት ፈተና ያስገኘለት ጥሩ ውጤት ከግል ጥቅም ይልቅ በእውነተኛ ለአምላክ የማደር መንፈስ ተገፋፍተን መከራን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ብንጸና የይሖዋን ልብ እንደምናስደስት ይጠቁማል።—ኢዮብ ምዕራፍ 1, 2፤ 42:10–17፤ ምሳሌ 27:11
በተጨማሪም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደምንችል የሚገልጹ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይዟል። ችግሮች ላጋጠሙት ሰው እንዴት ምክር ሊሰጠው እንደሚገባና እንደማይገባ የሚጠቁሙ ማራኪ ምሳሌዎችን አቅፏል። ከዚህም በተጨማሪ የኢዮብ ተሞክሮ በከባድ ችግሮች ስንገላታ ሚዛናችን እንድንጠብቅ ሊረዳን ይችላል።
ከአፍራሽ የምክር አሰጣጥ የሚገኝ ትምህርት
“የኢዮብ አጽናኝ” የሚለው አባባል አንድ ሰው መከራ ሲደርስበት ከማጽናናት ይልቅ በቁስሉ ላይ እንጨት የሚሰድበትን ሰው ለመግለጽ ሲሠራበት ቆይቷል። ይሁን እንጂ የኢዮብ ጓደኞች ያተረፉት ስም የሚገባቸው ቢሆንም ዝንባሌያቸው ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነበር ብለን መደምደም አይገባንም። በተሳሳተ አመለካከታቸው ተመርተው ኢዮብን በተወሰነ መጠን ሊረዱት ፈልገው ነበር። ምክራቸው ጥሩ ውጤት ያላስገኘው ለምንድን ነው? የኢዮብን ንጹሕ አቋም ለማጉደፍ ቆርጦ ለነበረው ለሰይጣን መሣሪያ የሆኑት እንዴት ነው?
የሚሰጡት ምክር ሁሉ የተመረኮዘው መከራ የሚመጣው ኃጢአት በሠሩ ሰዎች ላይ ብቻ ነው በሚል በተዛባ ግምት ላይ ነበር። ኤልፋዝ በመጀመሪያ ንግግሩ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እባክህ አስብ፣ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማነው? እኔ እንዳየሁ፣ ኃጢአትን የሚያርሱ፣ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።” (ኢዮብ 4:7, 8) ኤልፋዝ ንጹሐን ከመከራ ነፃ ናቸው የሚል የተሳሳተ እምነት ነበረው። ኢዮብ ቁም ስቅሉን ያየው በአምላክ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራ መሆን አለበት ሲል አሰበ።a በተመሳሳይም በልዳዶስና ሶፋር ስለ ሠራው ኃጢአት ንስሐ እንዲገባ ኢዮብን ነዘነዙት።—ኢዮብ 8:5, 6፤ 11:13–15
ከዚህም ሌላ ሦስቱ ጓደኞች ከአምላክ ጥበብ ይልቅ የግል አመለካከታቸውን በመግለጽ ኢዮብን ተስፋ አስቆርጠውታል። ኤልፋዝ አምላክ ‘በአገልጋዮቹ ስለማይታመን’ ኢዮብ ጻድቅ ሆነ አልሆነ ለይሖዋ ለውጥ አያመጣም እስከ ማለት ደርሷል። (ኢዮብ 4:18፤ 22:2, 3) ከዚህ የበለጠ ተስፋ አስቆራጭ ወይም ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አስተያየት ይኖራል ብሎ መገመት ያዳግታል! ይሖዋ መጨረሻ ላይ ስለዚህ ስድብ ኤልፋዝንና ጓደኞቹን መውቀሱ አያስደንቅም። “እናንተ ስለ እኔ ትክክል የሆነውን ነገር አልተናገራችሁም” አላቸው። (ኢዮብ 42:7 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ ይበልጥ የሚጎዳው ከዚያ ቀጥሎ የተናገሩት ነው።
ኤልፋዝ በመጨረሻ ከመጠን ያለፉ ቀጥተኛ የሆኑ ወቀሳዎችን እስከ መሰንዘር ደረሰ። ኢዮብ ጥፋተኛ መሆኑን እንዲያምን ሊያደርገው ስላልቻለ ኢዮብ ፈጽሟቸው መሆን አለበት ብሎ የሚያስባቸውን ኃጢአቶች መፍጠር ጀመረ። “ክፋትህ የበዛ አይደለምን? ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም። የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፣ የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል። ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፣ ለራብተኛም እንጀራን ከልክልሃል” ሲል ኤልፋዝ ተናገረ። (ኢዮብ 22:5–7) እነዚህ ጨርሶ መሠረት ቢስ የሆኑ ክሶች ነበሩ። ይሖዋ ራሱ ኢዮብ “ፍጹምና ቅን” እንደነበር ገልጿል።—ኢዮብ 1:8
ኢዮብ በንጹሕ አቋሙ ላይ ለተሰነዘሩት ለእነዚህ የቃላት ጥቃቶች ምን ምላሽ ሰጠ? እነዚህ ቃላት በመጠኑም ቢሆን እንዲማረርና እንዲጨነቅ ቢያድርጉትም ክሶቹ ሐሰት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆረጠ። እንዲያውም የራሱን ንጹሕነት ለማስመስከር በጣም ከመጣሩ የተነሣ ለደረሰበት ችግር ይሖዋን ማማረር ጀመረ። (ኢዮብ 6:4፤ 9:16–18፤ 16:11, 12) ዋነኛው አከራካሪ ጉዳይ ችላ ተባለና እሰጥ አገባው ኢዮብ ጻድቅ ነው ወይስ አይደለም ወደሚል ከንቱ ክርክር ተለወጠ። ክርስቲያኖች ከዚህ ጎጂ የምክር አስጣጥ ምን ትምህርቶችን ሊያገኙ ይችላሉ?
1. አንድ አፍቃሪ ክርስቲያን አንድ ወንድም ችግር የደረሰበት ከራሱ ጥፋት ነው ብሎ ገና ከመጀመሪያው አይደመድምም። ስሕተቱ እውነትም ይሁን በምናብ የተፈጠረ ያለፈውን ስሕተት በማንሣት መተቸት በርትቶ መታገል የፈለገን ሰው ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። የተጨነቀ ነፍስ ከመወገዝ ይልቅ ‘መጽናናት’ ይፈልጋል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) ይሖዋ የበላይ ተመልካቾች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” እንዲሆኑ እንጂ እንደ ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ያሉ ‘የሚያደክሙ አጽናኞች’ እንዲሆኑ አይፈልግም።—ኢሳይያስ 32:2፤ ኢዮብ 16:2
2. ግልጽ መረጃ ሳይኖረን በፍጹም ሰውን መውቀስ የለብንም። ኤልፋዝ የነበሩት ዓይነት አሉባልታዎችና ግምቶች ለመውቀስ የሚያስችሉ ትክክለኛ ምክንያቶች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ በስሕተት አንድን ሰው ቢወቅስ ተአማኒነቱን ሊያጣ እንዲሁም በሌሎች ላይ ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል። ኢዮብ እንዲህ ዓይነቱን የተዛባ ምክር ሲሰማ ምን ተሰማው? ከደረሰበት ከባድ ጭንቀት ማምለጫ መንገድ ሲፈልግ “ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው!” ሲል በምፀት ተናገረ። (ኢዮብ 26:2) አሳቢ የበላይ ተመልካች ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ ‘የላሉትን እጆች ያቀናል።’—ዕብራውያን 12:12
3. ምክር መሰጠት ያለበት በአምላክ ቃል ላይ ተመርኩዞ እንጂ በግል አስተሳሰብ መሆን የለበትም። የኢዮብ ጓደኞች ማሳመኛ ነጥቦች ትክክል ያልሆኑና የሚጎዱ ነበሩ። ኢዮብ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ ከማድረግ ይልቅ ከሰማያዊ አባቱ የሚለየው ነገር እንዳለ እንዲሰማው አድርገውታል። (ኢዮብ 19:2, 6, 8) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በጥበብ መጠቀም ነገሮችን ሊያስተካክል፣ ሌሎችን ሊያበረታቸውና እውነተኛ መጽናናት ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ሉቃስ 24:32፤ ሮሜ 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 4:2
የኢዮብ መጽሐፍ ክርስቲያኖች አንዳንድ እንቅፋቶችን ለይተው እንዲያውቁ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ ውጤታማ ምክር እንዴት መለገስ እንደሚችሉ የሚጠቁም ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል።
የምክር አሰጣጥ
የኤሊሁ ምክር በይዘቱም ሆነ ምክሩን ለኢዮብ ባቀረበበት መንገድ ከኢዮብ ሦስት ጓደኞች ጨርሶ የተለየ ነበር። የኢዮብን ስም የተጠቀመ ሲሆን እንደ ጓደኛው እንጂ እንደ ፈራጅ ሆኖ አላነጋገረውም። “ነገር ግን፣ ኢዮብ ሆይ፣ ንግግሬን እንድትስማ፣ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ። እነሆ፣ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ።” (ኢዮብ 33:1, 6) ኤሊሁ ኢዮብን ስለ ትክክለኛ አካሄዱ ለማመስገንም ፈጣን ነበር። “በጽድቅህ ተደስቻለሁ” ሲል ለኢዮብ አረጋገጠለት። (ኢዮብ 33:32 አዓት) ኤሊሁ ከዚህ በደግነት ከቀረበ የምክር አሰጣጥ በተጨማሪ በሌሎች ምክንያቶችም ተሳክቶለታል።
ኤሊሁ ሌሎች ንግግራቸውን እስኪጨርሱ ድረስ በመጠበቁ ምክር ከመስጠቱ በፊት አከራካሪ የሆኑትን ጉዳዮች በደንብ ለማጤን ችሎ ነበር። ኢዮብ ጻድቅ ሰው ከሆነ ይሖዋ ይቀጣዋልን? ኤሊሁ “ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር፣ በደልን ይሠራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።” “ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም” ሲል ተናገረ።—ኢዮብ 34:10፤ 36:7
ዋናው አከራካሪ ጉዳይ የኢዮብ ጻድቅነት ነበርን? ኤሊሁ ኢዮብ ትኩረቱን ወደ አንድ የተዛባ አመለካከት እንዲያዞር አደረገ። “አንተ ‘ጽድቄ ከአምላክ ጽድቅ ይበልጣል’ ብለሃል። ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ እይ፤ ከአንተም ከፍ ከፍ ያሉትን ደመናት ተመልከት” ሲል ተናገረ። (ኢዮብ 35:2 አዓት, 5) ደመናዎች ከእኛ በጣም ከፍ እንደሚሉ ሁሉ የይሖዋ መንገዶች ከእኛ መንገዶች በጣም ከፍ ያሉ ናቸው። እኛ እሱ ነገሮችን በሚሠራበት መንገድ ላይ መፍረድ አንችልም። “ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤ በልባቸው ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም” ሲል ኤሊሁ ሐሳቡን ቋጨ።—ኢዮብ 37:24፤ ኢሳይያስ 55:9
የኤሊሁ ጤናማ ምክር ኢዮብ ከራሱ ከይሖዋ ተጨማሪ ትምህርት እንዲያገኝ አእምሮውን አዘጋጀለት። እንዲያውም ኤሊሁ በምዕራፍ 37 ላይ ‘የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች’ የገለጸበትና ከምዕራፍ 38 እስከ 41 ያሉት ይሖዋ ራሱ ለኢዮብ የተናገራቸው ቃላት በጣም ይመሳሰላሉ። ኤሊሁ ነገሮቹን ከይሖዋ አመለካከት አንፃር እንደተመለከታቸው ግልጽ ነው። (ኢዮብ 37:14) ክርስቲያኖች የኤሊሁን ጥሩ ምሳሌ ሊኮርጁ የሚችሉት እንዴት ነው?
ልክ እንደ ኤሊሁ በተለይ የበላይ ተመልካቾች እነሱም ፍጹም እንዳልሆኑ በማስታወስ የሰውን ችግር የሚረዱና ደግ መሆን አለባቸው። ምክር ከመስጠታቸው በፊት አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎች በሙሉ እንዲያውቁና ጉዳዩን እንዲረዱ በጥንቃቄ ማዳመጥ ይፈለግባቸዋል። (ምሳሌ 18:13) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመጠቀም የይሖዋን አመለካከት ማንጸባረቅ ይችላሉ።—ሮሜ 3:4
የኢዮብ መጽሐፍ ይህን ተግባራዊ ምክር ለሽማግሌዎች የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ችግሮችን እንዴት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ልንቋቋም እንደምንችል ያስተምረናል።
መጥፎ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ማድረግ የሌለብን ነገር
ኢዮብ ባጋጠመው መከራ ተደቁሶና በሐሰተኛ አጽናኞቹ አዝኖ ስለነበር በጣም ተማረረ፤ ተጨነቀ። “ያ የተወለድኩበት ቀን ይጥፋ፣ . . . ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት” ሲል በምሬት ተናገረ። (ኢዮብ 3:3፤ 10:1) ጥፋተኛው ሰይጣን እንደሆነ ስላላወቀ የደረሱበትን መከራዎች ያመጣበት አምላክ መስሎት ነበር። ጻድቅ ሆኖ መሠቃየቱ አልዋጥለት አለው። (ኢዮብ 23:10, 11፤ 27:2፤ 30:20, 21) ይህ አመለካከት ኢዮብ ሌሎች ነገሮችን ግምት ውስጥ እንዳያስገባ አደረገውና አምላክ ከሰው ልጆች ጋር የሚያደርጋቸውን ግንኙነቶች ወደ መንቀፍ መራው። ይሖዋ “በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?” ሲል ጠየቀው።—ኢዮብ 40:8
ምናልባትም ችግር ሲያጋጥመን እንደ ኢዮብ እንደተጠቃን ሊሰማን ይችላል። የተለመደው ምላሽ ‘ለምን በኔ ላይ ብቻ ችግር ይደርሳል? ከእኔ የከፉት ሌሎች ከእኔ ጋር ሲነፃፀር ከችግሮች ነፃ የሆነ ሕይወት የሚመሩት ለምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቅ ነው። እነዚህ የአምላክን ቃል በማሰላሰል ልንዋጋቸው የምንችላቸው አፍራሽ አስተሳሰቦች ናቸው።
ከኢዮብ በተሻለ ሁኔታ ከነገሩ ጋር የሚያያዘውን አከራካሪ ጉዳይ ማስተዋል እንችላለን። ሰይጣን ‘የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ እየዞረ’ እንዳለ እናውቃለን። (1 ጴጥሮስ 5:8) የኢዮብ መጽሐፍ እንደሚጠቁመው ሰይጣን በእኛ ላይ ችግሮችን በማምጣት ንጹሕ አቋማችን ቢያጎድፍ ይደሰታል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚሆኑት ሲያመቻቸው ብቻ ነው የሚለውን አባባሉን ለማረጋገጥ ቆርጧል። (ኢዮብ 1:9–11፤ 2:3–5) የይሖዋን ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ አድርጎ ሰይጣን ሐሰተኛ እንደሆነ ለማረጋገጥ የሚያስችል ድፍረት ይኖረናልን?
ኢየሱስና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ያጋጠማቸው ሁኔታ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በእኛ ላይ አንድ ዓይነት መከራ መድረሱ እንደማይቀር ያሳያሉ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እሱን ለመከተል ከፈለጉ ‘የየራሳቸውን የመከራ እንጨት ለመሸከም’ ፈቃደኛ መሆን እንዳለባቸው ተናግሯል። (ሉቃስ 9:23 አዓት) የእኛ “የመከራ እንጨት” ኢዮብ ከደረሱበት ችግሮች አንዱ ወይም ብዙዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ማለትም ሕመም፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፣ ጭንቀት፣ የኢኮኖሚ ችግር ወይም ከማያምኑ ሰዎች የሚመጣ ተቃውሞ ሊደርስብን ይችላል። የቱንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ሁኔታው መልካም ጎን ይኖረዋል። የደረሰብንን ችግር ጽናትንና ለይሖዋ ያለንን የማያወላውል ታማኝነት የምናሳይበት አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን።—ያዕቆብ 1:2, 3
የኢየሱስ ሐዋርያት ያደረጉት እንደዚህ ነበር። ከጰንጠቆስጤ በኋላ ስለ ኢየሱስ በመስበካቸው ተገርፈው ነበር። ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ “ደስ እያላቸው” ወጡ። የተደሰቱት መከራ ስለተቀበሉ ሳይሆን “ስለ ስሙ [የክርስቶስ ስም] ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ” ነበር።—ሥራ 5:40, 41
እርግጥ የሚደርሱብን ችግሮች ሁሉ ይሖዋን ከማገልገላችን የሚመጡ አይደሉም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ችግሮቻችን ቢያንስ እስከ ተወሰነ መጠን ራሳችን የፈጠርናቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ምናልባት በራሳችን ጥፋት ባይሆንም ችግሩ መንፈሳዊ ሚዛናችንን አዛብቶት ይሆናል። ችግሩ ምንም ይሁን ምን እንደ ኢዮብ ያለ የትሕትና መንፈስ ምን ላይ እንደተሳሳትን እንድንገነዘብ ያስችለናል። ኢዮብ ለይሖዋ “እኔ የማላስተውለውን፣ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ” ሲል በመናገር ስሕተቱን አምኗል። (ኢዮብ 42:3) በዚህ መንገድ ስሕተቶቹን የሚገነዘብ ሰው ወደፊት ከሚያጋጥሙት ተመሳሳይ ችግሮች ሊድን ይችላል። ምሳሌው እንደሚለው “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል።”—ምሳሌ 22:3
ከዚህ ይበልጥ ደግሞ የኢዮብ መጽሐፍ የሚደርሱብን ችግሮች ጊዜያዊ እንደሆኑ ያስታውሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ “በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና” ይላል። (ያዕቆብ 5:11) በተመሳሳይም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉት አገልጋዮቹ ላሳዩት ታማኝነት ወሮታ እንደሚከፍል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
በተጨማሪም ከፊታችን ሁሉም ዓይነት ችግሮች ያሉበት ማለትም “የቀደመው ሥርዓት” የሚያልፍበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ራእይ 21:4) ያ ቀን እስኪጠባ ድረስ የኢዮብ መጽሐፍ ችግሮችን በጥበብና በቆራጥነት እንድንጋፈጥ የሚረዳ ዋጋው የማይተመን መመሪያ ይሆንልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ቢልም አንድ ሰው መከራ የሚደርስበት የግድ በመለኮታዊ ብቀላ ነው ማለት አይደለም። (ገላትያ 6:7) በዚህ በሰይጣን በሚገዛ ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ ጻድቃን ከክፉዎች የባሰ ችግር ይገጥማቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:19) “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ነገሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:22) ሕመምም ሆነ ሌላ ዓይነት መከራ በማንኛውም ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ላይ ሊደርስ ይችላል።—መዝሙር 41:3፤ 73:3–5፤ ፊልጵስዩስ 2:25–27
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ እይ፤ ከአንተም ከፍ ከፍ ያሉትን ደመናት ተመልከት።” ኤሊሁ በዚህ መንገድ የአምላክ መንገዶች ከሰው መንገዶች በጣም ከፍ እንደሚሉ እንዲያስተውል ኢዮብን ረዳው