ጸሎታችሁ “እንደ ዕጣን” ነውን?
“ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ።”—መዝሙር 141:2
1, 2. የሚጤሰው ዕጣን ምንን የሚያመለክት ነበር?
ይሖዋ አምላክ ነቢዩን ሙሴን እስራኤላውያን የአምልኮ ሥርዓት ለሚያካሂዱበት የማደሪያ ድንኳን የሚያገለግል ቅዱስ ዕጣን እንዲያዘጋጅ አዝዞት ነበር። መለኮታዊው መመሪያ በሚያዝዘው መሠረት ዕጣኑ ጥሩ መዓዛ ያላቸውን አራት የተለያዩ ቅመሞች አንድ ላይ በማደባለቅ ይዘጋጃል። (ዘጸአት 30:34–38) በእርግጥም ጥሩ መዓዛ ያለው ነበር።
2 የእስራኤል ሕዝብ በገባው በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት በየዕለቱ ዕጣን ይጤስ ነበር። (ዘጸአት 30:7, 8) የዕጣኑ መጤስ ልዩ ትርጉም ነበረውን? አዎን፣ ነበረው፤ መዝሙራዊው እንዲህ ሲል የዘመረው በዚህ ምክንያት ነው:- “ጸሎቴን እንደ ዕጣን፣ የተዘረጉትን እጆቼን እንደ ማታ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበል።” (መዝሙር 141:2 የ1980 ትርጉም) ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በአምላክ ሰማያዊ ዙፋን ዙሪያ ያሉትን ዕጣን የሞላበት የወርቅ ዕቃ እንደያዙ አድርጎ ገልጿቸዋል። ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ዘገባ ‘ዕጣኑ’ “የቅዱሳን ጸሎት” እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 5:8) ስለዚህ ጥሩ መዓዛ ያለው የሚጤሰው ዕጣን የይሖዋ አገልጋዮች ቀንና ሌሊት የሚያቀርቧቸውን ተቀባይነት ያላቸው ጸሎቶች ያመለክታል።—1 ተሰሎንቄ 3:10፤ ዕብራውያን 5:7
3. ‘ጸሎቶቻችንን በይሖዋ ፊት እንደ ዕጣን ለማቅረብ’ የሚረዳን ነገር ምንድን ነው?
3 ጸሎቶቻችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከተፈለገ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጸለይ ይገባናል። (ዮሐንስ 16:23, 24) ይሁን እንጂ የጸሎቶቻችንን ጥራት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችን መመርመራችን ጸሎቶቻችንን በይሖዋ ፊት እንደ ዕጣን አድርገን ለማቅረብ ይረዳናል።—ምሳሌ 15:8
በእምነት ጸልዩ
4. እምነት ተቀባይነት ካለው ጸሎት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?
4 ጸሎቶቻችን ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ወደ አምላክ እንዲያርጉ ከተፈለገ በእምነት መጸለይ አለብን። (ዕብራውያን 11:6) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታ የሚቀበል በመንፈሳዊ የታመመ ሰው በሚያጋጥማቸው ጊዜ የሚያቀርቡት “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።” (ያዕቆብ 5:15) በእምነት የሚቀርቡ ጸሎቶች ሰማያዊ አባታችንን ደስ ያሰኙታል፤ የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናታችንም እንዲሁ ያስደስተዋል። መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሎ በዘመረ ጊዜ ጥሩ ዝንባሌ አሳይቷል:- “እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካምን ምክርና እውቀትን አስተምረኝ።” (መዝሙር 119:48, 66) ትሕትና በተሞላበት መንገድ በመጸለይ ‘እጆቻችንን እንዘርጋ፤’ የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅም እምነት እናሳይ።
5. ጥበብ ከጎደለን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 ለምሳሌ አንድን ፈተና ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ጎድሎናል እንበል። ምናልባትም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አሁን እየተፈጸመ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ገብቶን ይሆናል። ይህ መንፈሳዊነታችንን እንዲያዋዥቀው ከመፍቀድ ይልቅ ጥበብ ለማግኘት እንጸልይ። (ገላትያ 5:7, 8፤ ያዕቆብ 1:5–8) እርግጥ አምላክ ተአምራዊ በሆነ መንገድ መልስ እንዲሰጠን ልንጠብቅ አንችልም። አምላክ ከሕዝቦቹ የሚጠብቀውን ነገር አሟልተን በመገኘት ጸሎታችን ከልብ የመነጨ መሆኑን ማሳየት አለብን። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች በመታገዝ ቅዱሳን ጽሑፎችን እምነት በሚገነባ መንገድ ማጥናታችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 24:45–47፤ ኢያሱ 1:7, 8) በአምላክ ሕዝቦች ስብሰባዎች ላይ ዘወትር በመገኘት በእውቀት ማደግም ይኖርብናል።—ዕብራውያን 10:24, 25
6. (ሀ) ያለንበትን ዘመንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ በተመለከተ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ከመጸለያችንም በተጨማሪ ምን ማድረግ ይገባናል?
6 በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ጥቅምና የሥራ ዕድገት የሚያሳድዱ መሆናቸው ወደ ‘ፍጻሜው ዘመን’ ጠልቀን እንደገባን እንዳልተገነዘቡ ያሳያል። (ዳንኤል 12:4) መሰል አማኞች እነዚህ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በ1914 ይሖዋ ሰማያዊ ንጉሥ አድርጎ በሾመው ጊዜ በሥልጣኑ ላይ መገኘት እንደጀመረና በጠላቶቹ መካከል እየገዛ እንደሆነ በሚያሳየው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ላይ ያላቸውን እምነት ዳግመኛ እንዲያቀጣጥሉና እንዲያጠነክሩ መጸለያቸው ተገቢ ነው። (መዝሙር 110:1, 2፤ ማቴዎስ 24:3) አስቀድመው የተነገሩት ክስተቶች ማለትም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የ“ታላቂቱ ባቢሎን” ጥፋት፣ የማጎጉ ጎግ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው ሰይጣናዊ ጥቃትና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በአርማጌዶን ጦርነት እነሱን ለማዳን የሚወስደው እርምጃ ፈጽሞ ባልተጠበቀ ሁኔታና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ሁሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ ይችላሉ። (ራእይ 16:14, 16፤ 18:1–5፤ ሕዝቅኤል 38:18–23) ስለዚህ አምላክ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር እንዲረዳን እንጸልይ። ሁላችንም የይሖዋ ስም እንዲቀደስ፣ መንግሥቱ እንዲመጣና በሰማይ የሆነው ፈቃዱ በምድርም እንዲሆን ከልባችን እንጸልይ። አዎን፣ እምነት ማሳየታችንንና ጸሎቶቻችን ከልብ የመነጩ መሆናቸውን ማስመስከራችንን እንቀጥል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ መንግሥቱንና ጽድቁን የሚያስቀድሙ እንዲሁም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በመስበክ ረገድ የሚችሉትን ያህል ጥሩ ተሳትፎ የሚያደርጉ ይሁኑ።—ማቴዎስ 6:33፤ 24:14
ይሖዋን አወድሱ፣ አመስግኑትም
7. በ1 ዜና መዋዕል 29:10–13 ላይ በከፊል ተመዝግቦ የሚገኘውን የዳዊት ጸሎት በተመለከተ አንተን የነካህ ነገር ምንድን ነው?
7 ‘ጸሎታችንን እንደ ዕጣን የምናቀርብበት’ አንዱ ትልቅ መንገድ አምላክን ከልብ በማወደስና በማመስገን ነው። ንጉሥ ዳዊት እሱና ሕዝቡ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ የሚውሉ ነገሮችን ባዋጡበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ጸሎት አቅርቦ ነበር። ዳዊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አቤቱ፣ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ። አቤቱ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፣ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፣ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው። አሁንም እንግዲህ፣ አምላካችን ሆይ፣ እንገዛልሃለን፣ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።”—1 ዜና መዋዕል 29:10–13
8. (ሀ) ከመዝሙር 148 እስከ 150 ላይ ከሚገኙት የውዳሴ ቃላት መካከል ልብህን ይበልጥ የነኩት የትኞቹ ናቸው? (ለ) በመዝሙር 27:4 ላይ የተገለጸው ዓይነት ስሜት ካለን ምን እናደርጋለን?
8 እንዴት ያለ ውብ የውዳሴና የምስጋና መግለጫ ነው! ጸሎቶቻችን ይህን ያህል ያማሩ ባይሆኑ እንኳ የዚህን ጸሎት ያህል ከልብ በመነጨ ስሜት ሊቀርቡ ይችላሉ። የመዝሙር መጽሐፍ በምስጋናና በውዳሴ ጸሎቶች የተሞላ ነው። ከመዝሙር 148 እስከ 150 ባሉት መዝሙራት ውስጥ የተመረጡ የውዳሴ ቃላት ይገኛሉ። በብዙዎቹ መዝሙራት ውስጥ ለአምላክ የቀረቡ የምስጋና ቃላት እናገኛለን። “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት” ሲል ዳዊት ዘምሯል። “እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።” (መዝሙር 27:4) በይሖዋ ሕዝብ ማኅበር ውስጥ በሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በቅንዓት በመሳተፍ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጸሎቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንመላለስ። (መዝሙር 26:12) ይህን ስናደርግና በአምላክ ቃል ላይ በየዕለቱ ስናሰላስል ከልብ በመነጨ ውዳሴና ምስጋና ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፉ ብዙ ምክንያቶች ይኖሩናል።
በትሕትና የይሖዋን እርዳታ ጠይቁ
9. ንጉሥ አሳ የጸለየው እንዴት ነው? ምንስ ውጤት አገኘ?
9 ምሥክሮቹ እንደ መሆናችን መጠን ይሖዋን በሙሉ ልባችን የምናመልከው ከሆነ እርዳታ ለማግኘት የምናቀርባቸውን ጸሎቶች እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 43:10–12) የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን አሳን ተመልከት። ለ41 ዓመታት (977–937 ከዘአበ) ከቆየው የግዛት ዘመኑ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ሰላም የሰፈነባቸው ነበሩ። ከዚያ በኋላ ይሁዳ ዝሪ በተባለው ኢትዮጵያዊ በሚመራው አንድ ሚልዮን ሰዎችን ባቀፈው ሠራዊት ተወረረች። አሳና ሠራዊቱ በቁጥር በእጅጉ ይበለጡ የነበረ ቢሆንም እንኳ ወራሪዎቹን ለመግጠም ወጡ። ይሁን እንጂ ከውጊያው በፊት አሳ ልባዊ ጸሎት አቀረበ። ይሖዋ ያለውን የማዳን ኃይል ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ እንዲረዳው በመማጸን ንጉሡ እንዲህ አለ:- “በአንተ ታምነናልና፣ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፣ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ።” ይሖዋ ለታላቅ ስሙ ሲል ይሁዳን ባዳነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ድል ተቀዳጁ። (2 ዜና መዋዕል 14:1–15) አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው ከፈተና በማዳንም ይሁን ፈተናውን እንድንቋቋም በማጠንከር፣ የእሱን እርዳታ ለማግኘት ያቀረብነውን ልመና እንደሚሰማ ምንም ጥርጥር የለውም።
10. አንድን ችግር እንዴት መወጣት እንደምንችል ግራ በምንጋባበት ጊዜ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ያቀረበው ጸሎት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
10 አንድን ችግር እንዴት መወጣት እንደምንችል ግራ ገብቶን ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳን የምናቀርበውን ልመና እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ሁኔታ ከ936 ከዘአበ ጀምሮ ለ25 ዓመት በገዛው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ዘመን ታይቷል። ይሁዳ በሞዓብ፣ በአሞንና በሴይር ተራራማ ክልል በሚኖሩ ሰዎች ጥምር ኃይሎች አደጋ አንዣቦባት በነበረ ጊዜ ኢዮሣፍጥ እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “አምላካችን ሆይ፣ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።” ይሖዋ ለዚህ ትሕትና የተሞላበት ጸሎት ምላሽ በመስጠት የጠላት ሠራዊት ቅጥ አንባሩ ጠፍቶበት እርስ በርሱ እንዲተላለቅ በማድረግ ለይሁዳ ተዋግቷል። በዚህም የተነሳ በአካባቢው የነበሩ ብሔራት በፍርሃት ከመዋጣቸውም በላይ በይሁዳ ሰላም ሊሰፍን ችሏል። (2 ዜና መዋዕል 20:1–30) አንድን ችግር ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ በሚጎድለን ጊዜ ልክ እንደ ኢዮሣፍጥ ‘ይሖዋ ሆይ ምን እንደምናደርግ አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው’ ብለን ልንጸልይ እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ ችግሩን ለመፍታት የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን እንድናስታውስ ሊያደርገን ይችላል፤ ወይም ደግሞ አምላክ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ሊረዳው በማይችለው መንገድ ሊረዳን ይችላል።—ሮሜ 8:26, 27
11. ነህምያ ከኢየሩሳሌም ግንቦች ጋር በተያያዘ ከወሰደው እርምጃ ጸሎትን በተመለከተ ምን ልንማር እንችላለን?
11 የአምላክን እርዳታ ለማግኘት በጸሎት መጽናት ሊያስፈልገን ይችላል። ነህምያ በፈረሱት የኢየሩሳሌም ግንቦችና በይሁዳ ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ በነበረው አሳዛኝ መከራ የተነሳ ለብዙ ቀናት ተክዟል፣ አልቅሷል፣ ጾሟል እንዲሁም ጸልዮአል። (ነህምያ 1:1–11) ውሎ አድሮ ግን ጸሎቶቹ ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ወደ አምላክ አርገዋል። አንድ ቀን የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ ከባድ ሐዘን ላይ ወድቆ የነበረውን ነህምያን “ምን ትለምነኛለህ?” ሲል ጠየቀው። “እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ” ሲል ነህምያ ዘግቧል። ነህምያ የፈራረሰውን ግንቧን መልሶ ለመገንባት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ልቡ የሻተውን እንዲፈጽም የተፈቀደለት በመሆኑ በልቡ ያቀረበው ይህ አጭር ጸሎት መልስ አግኝቷል።—ነህምያ 2:1–8
እንዴት እንደምትጸልዩ ከኢየሱስ ተማሩ
12. ኢየሱስ ባቀረበው የናሙና ጸሎት ላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ነጥቦች በራስህ አባባል ጠቅለል አድርገህ የምትገልጻቸው እንዴት ነው?
12 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሰፈሩት ጸሎቶች ሁሉ ይበልጥ ትምህርታዊ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን አድርጎ ያቀረበው የናሙና ጸሎት ነው። የሉቃስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- “ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ‘ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን?’ አለው። ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤ ‘. . . አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፤ የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን፤ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በልልን፣ ወደ ፈተናም አታግባን።’”” (ሉቃስ 11:1–4 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 6:9–13) እንደ ዳዊት ለመድገም ሳይሆን እንደ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግለን እስቲ ይህን ጸሎት እንመርምር።
13. “አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ” የሚሉት ቃላት ያዘሉትን ትርጉም የምትገልጸው እንዴት ነው?
13 “አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ።” ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮቹ ይሖዋን አባት ብለው መጥራታቸው ልዩ መብት ነው። ልጆች የሚያሳስባቸውን ነገር በሙሉ ሩኅሩኅ ለሆነ አባታቸው እንደሚነግሩ ሁሉ እኛም እርጋታና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ዘወትር በጸሎት ከአምላክ ጋር መነጋገር አለብን። (መዝሙር 103:13, 14) በይሖዋ ስም ላይ የተከመረው ነቀፋ ሁሉ የሚወገድበትን ጊዜ ለማየት የምንናፍቅ በመሆኑ ጸሎቶቻችን የስሙ ቅድስና የሚያሳስበን መሆኑን የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። አዎን፣ የይሖዋ ስም ተለይቶ እንዲታወቅና ቅዱስ ሆኖ እንዲታይ እንፈልጋለን።—መዝሙር 5:11፤ 63:3, 4፤ 148:12, 13፤ ሕዝቅኤል 38:23
14. “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን መጸለያችን ምን ትርጉም አለው?
14 “መንግሥትህ ትምጣ።” ይህ መንግሥት በልጁና ‘በቅዱሳኑ’ የኢየሱስ ተባባሪዎች እጅ ባለው መሲሐዊ ሰማያዊ መንግሥት የተገለጠው የይሖዋ አገዛዝ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14, 18, 27፤ ራእይ 20:6) በምድር ላይ ባሉት የአምላክን ሉዓላዊነት በሚቃወሙ ሁሉ ላይ በቅርቡ ‘ይመጣባቸዋል፤’ ጨርሶም ያጠፋቸዋል። (ዳንኤል 2:44) ከዚያ በኋላ የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ ይሆናል። (ማቴዎስ 6:10) የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ በታማኝነት የሚያገለግሉ ፍጥረታት ሁሉ ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!
15. ይሖዋ “የዕለት እንጀራችንን” እንዲሰጠን መጠየቃችን ምን ያመለክታል?
15 “የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን።” ይሖዋ ለ“ዕለት” የሚሆነንን ምግብ እንዲሰጠን መጠየቃችን በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ብቻ እንጂ እጅግ የተትረፈረፉ ነገሮችን የማንጠይቅ መሆኑን ያመለክታል። አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን የምናምን ቢሆንም እንኳ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት እንሠራለን እንዲሁም አግባብነት ያለውን መንገድ ሁሉ እንጠቀማለን። (2 ተሰሎንቄ 3:7–10) እርግጥ ነው፣ ከእነዚህ ዝግጅቶች በስተጀርባ የይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ኃይል ያለ በመሆኑ የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚሰጠንን ሰማያዊ አባታችንን ማመስገን አለብን።—ሥራ 14:15–17
16. የአምላክን ይቅርታ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
16 “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በልልን።” ፍጽምና የጎደለን ኃጢአተኛ ሰዎች በመሆናችን ፍጹም የሆኑትን የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ሙሉ በሙሉ ማሟላት አንችልም። በመሆኑም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር እንዲለን መጸለይ አለብን። ሆኖም ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ የዚህን መሥዋዕት ዋጋ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት እንዲጠቀምበት ከፈለግን ንስሐ መግባትና እሱ የሚሰጠንን ማንኛውም ዓይነት ተግሳጽ ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። (መዝሙር 65:2፤ ሮሜ 5:8፤ 6:23፤ ዕብራውያን 12:4–11) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ይቅር ይለናል ብለን ልንጠብቅ የምንችለው እኛ ‘የበደሉንን ይቅር የምንል’ ከሆነ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 6:12, 14, 15
17. “ወደ ፈተናም አታግባን” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?
17 “ወደ ፈተናም አታግባን።” መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አንዳንድ ነገሮች እንዲደርሱ በሚፈቅድበት ጊዜ እሱ እንዳደረገው አድርጎ የሚገልጽበት ጊዜ አለ። (ሩት 1:20, 21) አምላክ ኃጢአት እንድንፈጽም አይፈትነንም። (ያዕቆብ 1:13) መጥፎ ነገር እንድንሠራ የሚፈታተኑን ዲያብሎስ፣ ኃጢአተኛው ሥጋችንና ይህ ያለንበት ዓለም ናቸው። አታልሎ በአምላክ ላይ ኃጢአት እንድንሠራ ለማድረግ የሚሞክረው ፈታኝ ሰይጣን ነው። (ማቴዎስ 4:3፤ 1 ተሰሎንቄ 3:5) “ወደ ፈተናም አታግባን” ብለን ስንጠይቅ የእሱን ትእዛዝ እንድንጥስ በምንፈተንበት ጊዜ አምላክ እንድንወድቅ እንዳይፈቅድ መለመናችን ነው። ተሸንፈን ‘ለክፉው’ ለሰይጣን እጃችንን እንዳንሰጥ ሊመራን ይችላል።—ማቴዎስ 6:13፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13
ከጸሎታችሁ ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላለሱ
18. ደስታ የሰፈነበት ትዳርና የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን ካቀረብነው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ያቀረበው የናሙና ጸሎት ዋና ዋና ነጥቦችን ያካተተ ነው፤ ሆኖም ስለማንኛውም ጉዳይ መጸለይ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል አስደሳች ትዳር ለመመሥረት ስላለን ፍላጎት ልንጸልይ እንችላለን። እስከ ጋብቻ ጊዜ ድረስ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ራሳችንን መግዛት እንድንችል ልንጸልይ እንችላለን። ከዚያም ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ጽሑፎችም ሆነ መዝናኛዎች በማስወገድ ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ እንመላለስ። በተጨማሪም ‘በጌታ ብቻ ለማግባት’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ዘዳግም 7:3, 4) ካገባን በኋላ አምላክ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ትዳራችን ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ካቀረብነው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይኖርብናል። ልጆች ካሉን ደግሞ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መጸለያችን ብቻ አይበቃም። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነትና ዘወትር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዘናቸው በመሄድ የአምላክን እውነቶች በአእምሯቸው ውስጥ ለመቅረጽ የቻልነውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለብን።—ዘዳግም 6:5–9፤ 31:12፤ ምሳሌ 22:6
19. አገልግሎታችንን በተመለከተ ከጸለይን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 በአገልግሎታችን እንዲባርከን እየጸለይን ነውን? እንግዲያው በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ትርጉም ባለው መንገድ በመካፈል ከዚህ ጸሎታችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ እንመላለስ። ሌሎች ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እንድናገኝ ጸልየን ከሆነ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሚገባ መዝግበን መያዝና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የምንመራበትን ጊዜ በፕሮግራማችን ውስጥ ለማካተት ፈቃደኞች መሆን አለብን። አቅኚ ሆነን በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ መሳተፍ የምንፈልግ ከሆነስ? የስብከት እንቅስቃሴያችንን በመጨመርና ከአቅኚዎች ጋር በአገልግሎት በመሳተፍ ከጸሎታችን ጋር የሚስማሙ እርምጃዎች እንውሰድ። እንዲህ ዓይነቶቹን እርምጃዎች መውሰዳችን ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ እንደምንመላለስ ያሳያል።
20. የሚቀጥለው ርዕስ በየትኛው ነጥብ ላይ ያተኮረ ነው?
20 ይሖዋን በታማኝነት እያገለገልነው ከሆነ ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙትን ጸሎቶቻችንን እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ዮሐንስ 5:14, 15) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ጸሎቶች መካከል አንዳንዶቹን መመርመራችን ጠቃሚ ነጥቦች እንድንቀስም እንዳስቻለን አያጠራጥርም። የሚቀጥለው ርዕስ ‘ጸሎቶቻቸውን በይሖዋ ፊት እንደ ዕጣን አድርገው ማቅረብ’ ለሚፈልጉ ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ መምሪያዎች ይዟል።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ በእምነት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ውዳሴና ምስጋና በጸሎታችን ውስጥ ምን ሚና ሊኖራቸው ይገባል?
◻ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት በሙሉ ትምክህት መጸለይ የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ በናሙና ጸሎቱ ላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
◻ ከጸሎቶቻችን ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ‘ይሖዋ ሆይ ምን እንደምናደርግ አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው’ ብለን መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ካቀረበው የናሙና ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ ትጸልያለህን?