የይሖዋን ሉዓላዊነት ትደግፋለህ?
“በሕዝቦች መካከል፣ ‘ይሖዋ ነገሠ፤’ በሉ።” —መዝሙር 96:10 NW
1, 2. (ሀ) ጥቅምት 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ምን ታላቅ ክንውን ተፈጸመ? (ለ) ይህ ክንውን ለኢየሱስ ምን ትርጉም ነበረው?
ጥቅምት 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ክንውን ተፈጸመ። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ እንዲህ ሲል ሁኔታውን ዘግቧል:- “ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ [በኢየሱስ ላይ] እንደ ርግብ ሲወርድበት [መጥምቁ ዮሐንስ] አየ። እነሆ፣ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።” ይህ ሁኔታ በአራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ከተዘገቡት ጥቂት ክንውኖች አንዱ ነው።—ማቴዎስ 3:16, 17፤ ማርቆስ 1:9-11፤ ሉቃስ 3:21, 22፤ ዮሐንስ 1:32-34
2 መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ መውረዱ የተቀባ ማለትም መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን የሚያመለክት ነበር። (ዮሐንስ 1:33) በመጨረሻ ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ ተገለጠ! በመጥምቁ ዮሐንስ አጠገብ የቆመው፣ ሰይጣን ተረከዙን የሚቀጠቅጠው ግለሰብ ሲሆን እሱም የይሖዋና የሉዓላዊነቱ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን የሰይጣንን ጭንቅላት ይቀጠቅጣል። (ዘፍጥረት 3:15) ኢየሱስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከይሖዋ ሉዓላዊነትና ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘውን ዓላማ ለማስፈጸም ጥረት ማድረግ እንዳለበት በሚገባ ተገንዝቦ ነበር።
3. ኢየሱስ፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ረገድ ለሚጫወተው ሚና ራሱን ያዘጋጀው እንዴት ነበር?
3 ኢየሱስ ለተሰጠው ሥራ ለመዘጋጀት “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው።” (ሉቃስ 4:1፤ ማርቆስ 1:12) ኢየሱስ በዚያ ለ40 ቀናት በቆየበት ወቅት፣ ሰይጣን ሉዓላዊነትን በተመለከተ ስላስነሳው ግድድር እንዲሁም የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ማከናወን ስለሚኖርበት ሥራ በጥልቀት ለማሰላሰል ጊዜ አግኝቶ ነበር። ይህ ግድድር በሰማይም ሆነ በምድር ላይ የሚኖሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን በሙሉ ይመለከታል። በመሆኑም እኛም የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ እንደምንፈልግ ለማሳየት ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ እንድንችል ኢየሱስ የተወውን የታማኝነት ምሳሌ መመርመር ይኖርብናል።—ኢዮብ 1:6-12፤ 2:2-6
ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት በግልጽ ተገዳደረ
4. ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት በግልጽ የተገዳደረው እንዴት ነበር?
4 እርግጥ ነው፣ ከላይ የተጠቀሱት ክንውኖች በሙሉ ከሰይጣን እይታ አላመለጡም። ሰይጣን ጊዜ ሳያጠፋ በአምላክ ‘ሴት’ ዋነኛ ‘ዘር’ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። (ዘፍጥረት 3:15) ኢየሱስ የአባቱን ፍላጎት ከመፈጸም ይልቅ የራሱን ጥቅም እንዲያስቀድም ሐሳብ በማቅረብ ሰይጣን ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ፈተነው። በተለይ ሦስተኛው ፈተና በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ በግልጽ የተሰነዘረ ግድድር ነበር። ሰይጣን “የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው” ለኢየሱስ ካሳየው በኋላ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” በማለት በግልጽ ጠየቀው። ኢየሱስ ‘የዓለም መንግሥታት’ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን በሚገባ ያውቅ ስለነበረ ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ግድድር ረገድ ምን አቋም እንዳለው ለማሳየት እንዲህ አለው:- “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና።”—ማቴዎስ 4:8-10
5. ኢየሱስ ምን ከባድ ተልእኮ መወጣት ነበረበት?
5 ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛ ዓላማው የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ እንደሆነ በአኗኗሩ በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ አምላክ የመግዛት መብት እንዳለው ለማረጋገጥ ሲል በትንቢት በተነገረው መሠረት ሰይጣን የሴቲቱን ‘ዘር’ ተረከዝ እስከሚቀጠቅጥበት ጊዜ ማለትም እስከሚያስገድለው ድረስ ታማኝ መሆን እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 16:21፤ 17:12) ከዚህም በተጨማሪ ዓመጸኛውን ሰይጣንን ለማጥፋት እንዲሁም ፍጥረት በሙሉ ሰላምና ሥርዓት በሰፈነበት ሁኔታ መኖር እንዲችል ለማድረግ ይሖዋ የሚጠቀምበት መሣሪያ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ መመሥከር ነበረበት። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ ይህን ከባድ ተልእኮ ለመወጣት ምን አድርጎ ይሆን?
‘የአምላክ መንግሥት ቀርባለች’
6. ይሖዋ ‘የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ’ የሚጠቀመው በአምላክ መንግሥት እንደሆነ ኢየሱስ ያሳወቀው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር “የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣ ‘ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች’” ይል ነበር። (ማርቆስ 1:14, 15) እንዲያውም “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:18-21, 43) ኢየሱስ በይሁዳ ምድር በመዘዋወር “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች” ሰብኳል። (ሉቃስ 8:1) ከዚህም በላይ ሕዝቡን በመመገብ፣ አስቸጋሪ የአየር ጠባይን በመቆጣጠር፣ የታመሙትን በመፈወስ እንዲሁም የሞቱትን በማስነሳት በርካታ ተአምራትን ፈጽሟል። ኢየሱስ እነዚህን ተአምራት መፈጸሙ አምላክ፣ በኤደን የተነሳው ዓመጽ ያስከተለውን ጉዳትና ሥቃይ በማስወገድ ‘የዲያብሎስን ሥራ እንደሚያፈርስ’ አረጋግጧል።—1 ዮሐንስ 3:8
7. ኢየሱስ ተከታዮቹን ምን እንዲያደርጉ አዘዛቸው? ምንስ ውጤት አገኙ?
7 ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ወንጌል በተቻለ መጠን በሁሉም ቦታ እንዲሰበክ ለማድረግ ሲል ታማኝ ተከታዮቹን ሰብስቦ ለዚህ ሥራ አሰለጠናቸው። መጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ . . . ላካቸው።” (ሉቃስ 9:1, 2) ከዚያም ሌሎች 70 ተከታዮቹን “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች” እያሉ ለሰዎች እንዲሰብኩ ላካቸው። (ሉቃስ 10:1, 8, 9) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክ ያገኙትን አስደሳች ውጤት ሲነግሩት ኢየሱስ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” አላቸው።—ሉቃስ 10:17, 18
8. የኢየሱስ ሕይወት ምን አሳይቷል?
8 ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ራሱን ያስጠመደ ከመሆኑም በላይ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። በሕይወቱ ውስጥ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ጭምር መሥዋዕት በማድረግ ቀን ከሌት ይሠራ ነበር። ኢየሱስ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” ብሎ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 9:58፤ ማርቆስ 6:31፤ ዮሐንስ 4:31-34) ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው” በማለት ለጳንጢዮስ ጲላጦስ በድፍረት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ታላቅ አስተማሪ ወይም ተአምር ፈጻሚ አሊያም ደግሞ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ አዳኝ ለመሆን ሳይሆን የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ እንዲሁም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ፈቃዱን የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ለመመሥከር እንደነበር በአኗኗሩ አሳይቷል።—ዮሐንስ 14:6
“ተፈጸመ”
9. ሰይጣን የአምላክን ሴት ‘ዘር’ ተረከዝ በመቀጥቀጥ ረገድ የተሳካለት እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ያከናወናቸው ነገሮች ሁሉ የአምላክ ጠላት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን አላስደሰቱትም። ሰይጣን በምድር ባለው የእሱ ‘ዘር’ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ክፍል በመጠቀም የአምላክን ሴት ‘ዘር’ ለመግደል በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥረት አድርጓል። ኢየሱስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ የሰይጣንና የግብረ አበሮቹ የጥቃት ዒላማ ሆኖ ነበር። በመጨረሻም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጸደይ ወራት የሰው ልጅ በጠላቱ እጅ አልፎ የሚሰጥበትና ተረከዙ የሚቀጠቀጥበት ጊዜ ደረሰ። (ማቴዎስ 20:18, 19፤ ሉቃስ 18:31-33) አስቆሮቱ ይሁዳ፣ የካህናት አለቆች፣ ጻፎች፣ ፈሪሳውያንና ሮማውያን በኢየሱስ ላይ እንዲፈረድበትና በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃይቶ እንዲሞት እንዲያደርጉ ሰይጣን እንዴት እንደተጠቀመባቸው የወንጌል ዘገባዎች በግልጽ ያሳያሉ።—የሐዋርያት ሥራ 2:22, 23
10. ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በመሞቱ በዋነኝነት ያከናወነው ነገር ምንድን ነው?
10 ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ረዘም ላለ ሰዓት ተሠቃይቶ እንደሞተ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ኢየሱስ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ሲል ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ያቀረበውን ቤዛዊ መሥዋዕት ታስታውስ ይሆናል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 15:13) አሊያም ይሖዋ ይህን መሥዋዕት በማዘጋጀት ያሳየውን ታላቅ ፍቅር ታደንቅ ይሆናል። (ዮሐንስ 3:16) ምናልባትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” እንዳለው የሮም ሠራዊት አዛዥ ይሰማህ ይሆናል። (ማቴዎስ 27:54) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ትክክል ናቸው። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ከመሞቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ቃል “ተፈጸመ” የሚል እንደሆነ አስታውስ። (ዮሐንስ 19:30) ተፈጸመ የተባለው ምንድን ነው? ኢየሱስ በሕይወት እያለም ሆነ በመሞቱ ብዙ ነገሮች ቢያከናውንም ወደ ምድር የመጣበት ዋናው ዓላማ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ለተነሳው ግድድር መልስ ለመስጠት ነው። ደግሞም ‘ዘሩ’ የይሖዋን ስም ከተሰነዘረበት ነቀፋ ሁሉ ለማንጻት በሰይጣን እጅ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚደርስበት አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 53:3-7) እነዚህ ከባድ ኃላፊነቶች ቢሆኑም ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ተወጥቷቸዋል። በእርግጥም የተሰጠውን ኃላፊነት ፈጽሟል!
11. በኤደን የተነገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ኢየሱስ ምን ያደርጋል?
11 ኢየሱስ ታማኝ በመሆኑ ሰብዓዊ አካል ለብሶ ሳይሆን “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ” በመሆን ከሞት ተነስቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:45፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ይሖዋ ክብር ለተላበሰው ልጁ “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” በማለት ቃል ገብቶለት ነበር። (መዝሙር 110:1) እዚህ ላይ ‘ጠላቶች’ የተባሉት ዋነኛ ዓመጸኛ የሆነው ሰይጣንና አጠቃላይ ‘የዘሩ’ ክፍሎች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የይሖዋ መሲሐዊ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ዓመጸኞች በሙሉ በማጥፋት ረገድ ቅድሚያውን የሚወስደው እሱ ይሆናል። (ራእይ 12:7-9፤ 19:11-16፤ 20:1-3, 10) በዚህ ጊዜ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢትም ሆነ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ያስተማራቸው ጸሎት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።—ማቴዎስ 6:10፤ ፊልጵስዩስ 2:8-11
ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ
12, 13. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ምን ምላሽ እየሰጡ ነው? (ለ) የክርስቶስን ፈለግ ለመከተል ከፈለግን ራሳችንን ምን እያልን መጠየቅ ይገባናል?
12 ኢየሱስ እንደተነበየው በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንግሥት ወንጌል በበርካታ የምድር ክፍሎች እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በዚህም የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለአምላክ ወስነዋል። እነዚህ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች በማወቃቸው ተደስተዋል። ገነት በምትሆነው ምድር በሰላምና ያለ ምንም ስጋት ለዘላለም ለመኖር የሚናፍቁ ከመሆኑም በላይ ይህን ተስፋቸውን ለሌሎች በደስታ ይናገራሉ። (መዝሙር 37:11፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አንተስ ከእነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አንዱ ነህ? ከሆነ ልትመሰገን ይገባሃል። ይሁን እንጂ እያንዳንዳችን ልናስብበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ።
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እዚህ ላይ ጴጥሮስ የጠቀሰው ኢየሱስ በስብከቱ ሥራ ያሳየውን ቅንዓት ወይም የማስተማር ችሎታውን ሳይሆን መከራ መቀበሉን እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ኢየሱስ፣ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ለመገዛት እንዲሁም ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል እስከ ምን ድረስ መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ እንደነበር ጴጥሮስ ተመልክቷል። ታዲያ የኢየሱስን ፈለግ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍና ለማክበር ስል እስከ ምን ድረስ ለመሠቃየት ፈቃደኛ ነኝ? የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ በሕይወቴ ውስጥ ዋናውን ቦታ እንደሚይዝ በአኗኗሬም ሆነ በአገልግሎት ላይ ባለኝ ቅንዓት አሳያለሁ?’—ቈላስይስ 3:17
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ የተሳሳተ ምክርና ግብዣ ሲቀርብለት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? እንዲህ ያደረገውስ ለምን ነበር? (ለ) ሁልጊዜ ልናስታውሰው የሚገባን የትኛውን ጉዳይ ነው? (“ከይሖዋ ጎን መቆም” ከሚለው ሣጥን ውስጥ ተጨማሪ ሐሳብ ስጥ።)
14 በየዕለቱ ጥቃቅንና ከባድ ፈተናዎች እንዲሁም ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በዚህ ጊዜ የምንወስደው እርምጃ በምን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል? ለአብነት ያህል፣ ክርስቲያናዊ አቋማችንን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንድንፈጽም ስንፈተን ምን እናደርጋለን? ጴጥሮስ ‘እንዲህ ያለ ነገር አይድረስብህ’ ሲለው የኢየሱስ ምላሽ ምን ነበር? “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው። (ማቴዎስ 16:21-23) የተሻለ ገቢ ወይም ሥራ የማግኘት አጋጣሚ ብናገኝና ይህ ሁኔታ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንንና ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆን ኢየሱስ የወሰደው ዓይነት እርምጃ እንወስዳለን? ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት የተመለከቱ ሰዎች “መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ” ሲያውቅ በፍጥነት ከእነሱ ዘወር አለ።—ዮሐንስ 6:15
15 ኢየሱስ በዚህ ጊዜም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ጠንከር ያለ አቋም የወሰደው ለምን ነበር? ምክንያቱም ከራሱ ደኅንነት ወይም ጥቅም ይበልጥ አስፈላጊ ነገር እንዳለ ስለተገነዘበ ነው። የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸምና የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ሲል ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ አላለም። (ማቴዎስ 26:50-54) በመሆኑም በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳውን ግድድር እንደ ኢየሱስ ሁልጊዜ ካላስታወስን አቋማችንን ልናላላ ወይም ትክክለኛ የሆነውን ነገር ሳናደርግ ልንቀር እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ስህተት የሆነውን ነገር ጥሩ አስመስሎ በማቅረብ ረገድ የተካነው ሰይጣን፣ ሔዋንን እንዳታለላት ሁሉ እኛንም በመሠሪ ዘዴዎቹ ተጠቅሞ በቀላሉ ሊያጠምደን ስለሚችል ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14
16. ሰዎችን ስንረዳ ዋነኛው ዓላማችን ምን መሆን አለበት?
16 በአገልግሎታችን ላይ ሰዎችን ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች ለማወያየትና መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማሳየት እንጥራለን። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ውጤታማ መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ዋናው ዓላማችን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ወይም የአምላክ መንግሥት ምን በረከቶችን እንደሚያመጣ እንዲያውቁ መርዳት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ የተነሳውን ግድድር እንዲያውቁ ልንረዳቸው ይገባል። እነዚህ ሰዎች፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆን የራሳቸውን “የመከራ እንጨት” ለመሸከምና ለአምላክ መንግሥት ሲሉ መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው? (ማርቆስ 8:34 NW) የይሖዋን ሉዓላዊነት ከሚደግፉት ጎን በመቆም ሰይጣን ውሸታምና ስም አጥፊ መሆኑን ለማረጋገጥ ዝግጁ ናቸው? (ምሳሌ 27:11) የይሖዋን ሉዓላዊነት የመደገፍም ሆነ ሌሎች ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የመርዳት መብት አግኝተናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
አምላክ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ሲሆን
17, 18. የይሖዋን ሉዓላዊነት የምንደግፍ ከሆነ ምን ዓይነት አስደናቂ ጊዜ እንደሚመጣ መጠበቅ እንችላለን?
17 በአኗኗራችንም ሆነ በአገልግሎታችን የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ [የሚያስረክብበትን]” ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። ይህን የሚያደርገው መቼ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ የሚሆነው “ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ” እንደሆነ ገልጿል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። . . . እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ [“ለሁሉም ሁሉንም ነገር፣” NW] እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።”—1 ቆሮንቶስ 15:24, 25, 28
18 አምላክ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ሲሆን እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይሆናል! በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት የተቋቋመበትን ዓላማ ዳር ያደርሳል። የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙ ሁሉ ይጠፋሉ። በመላው አጽናፈ ዓለም ሰላም የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ ሥርዓት ይኖራል። መዝሙራዊው እንዳለው ፍጥረት ሁሉ እንዲህ በማለት ይዘምራል:- “ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ . . . በሕዝቦች መካከል፣ ‘እግዚአብሔር ነገሠ፤’ በሉ።”—መዝሙር 96:8, 10
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ ሉዓላዊነት ዋነኛ ቦታ ይሰጥ የነበረው እንዴት ነው?
• ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት እንዲሁም ሲሞት በዋነኝነት የፈጸመው ምንድን ነው?
• የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከይሖዋ ጎን መቆም
በኮሪያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚኖሩ በርካታ ወንድሞች እንዳደረጉት ክርስቲያኖች ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው እንደነዚህ ዓይነት ፈተናዎች የሚደርስባቸው ለምን እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው።
በቀድሞው የሶቪየት አገዛዝ ወቅት ታስሮ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ለመጽናት የረዳን በኤደን ገነት የተነሳውን ጥያቄ ማለትም በአምላክ የመግዛት መብት ላይ የተነሳውን ግድድር በግልጽ መረዳታችን ነው። . . . የይሖዋን አገዛዝ ለመደገፍ የሚያስችል አጋጣሚ እንዳገኘን እናውቅ ነበር። . . . ይህን ማወቃችን ያጠናከረን ከመሆኑም በላይ በታማኝነት እንድንጸና ረድቶናል።”
አንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ እሱንም ሆነ የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ የነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹን ምን እንደረዳቸው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋ ደግፎናል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በመንፈሳዊ ንቁዎች ነበርን። በአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ በተነሳው ግድድር ረገድ ከይሖዋ ጎን እንደቆምን አንዳችን ሌላውን በማስታወስ እንበረታታ ነበር።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሰይጣን በተፈተነበት ወቅት የይሖዋን ሉዓላዊነት የደገፈው እንዴት ነበር?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሲሞት ምን ተፈጽሟል?