አምላክ ስለ አንተ ያስባል
ሜሪ የምትባል በአርባዎቹ ዕድሜ ማብቂያ ላይ የምትገኝ አንዲት ክርስቲያን ብዙ ችግር ደርሶባታል። ባሏ ምንዝር በመፈጸሙ ምክንያት ከአሥር ዓመት በፊት ተፋትተዋል። ሜሪ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አራት ልጆችዋን ያለ አባት የማሳደጉን ኃላፊነት ለመወጣት ስትታገል ቆይታለች። ቢሆንም እስካሁን ብቻዋን ነች፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነቱ ልትቋቋመው የማትችለው ነገር ሆኖ ይታያታል። ሜሪ ‘አምላክ ስለእኔም ሆነ አባት አልባ ስለሆኑት ልጆቼ አያስብም ማለት ነው?’ በማለት ራሷን ትጠይቃለች።
ይህን የመሰለ ችግር ቢደርስብህም ባይደርስብህም ሜሪ በተሰማት ስሜት ማዘንህ አይቀርም። ሁላችንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን ይሖዋ ችግሮቻችንን የሚፈታልን መቼና እንዴት እንደሆነ ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። አንዳንዶቹ ችግሮች የሚደርሱብን የአምላክን ሕግጋት በመጠበቃችን የተነሳ ነው። (ማቴዎስ 10:16-18፤ ሥራ 5:29) ሌሎቹ ደግሞ ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ የምንኖር ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን ምክንያት የሚመጡ ናቸው። (1 ዮሐንስ 5:19) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ይኖራል’ በማለት ጽፏል።—ሮሜ 8:22
ሆኖም ከፍተኛ መከራ ደረሰብህ ማለት ይሖዋ ትቶሃል ወይም ስለ ደህንነትህ አያስብም ማለት አይደለም። ለዚህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? አምላክ ስለ አንተ እንደሚያስብ የሚያሳየው ምንድን ነው?
አንድ የጥንት ምሳሌ
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች እንደሚያስብ ግልጽ ማስረጃ ያቀርባል። ዳዊትን ተመልከት። ይሖዋ ለዚህ ወጣት እረኛ በግለሰብ ደረጃ ያስብለት የነበረ ሲሆን “እንደ ልቡ የሆነ ሰው” ሆኖ አግኝቶታል። (1 ሳሙኤል 13:14) ዳዊት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ “በምትሄድበትም ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ይሖዋ ቃል ገብቶለታል።—2 ሳሙኤል 7:9 አዓት
ይህ ማለት ዳዊት ከማንኛውም ችግር ነፃ ሆኖ “ደልቶት” ይኖራል ማለት ነውን? አይደለም፣ ዳዊት ከመንገሡ በፊትና ከነገሠ በኋላ ከባድ ችግሮች አጋጥመውታል። ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ነፍሰ ገዳዩ ንጉሥ ሳኦል ለብዙ ዓመታት ያለማቋረጥ ያሳድደው ነበር። ዳዊት በስደት ላይ በነበረበት ጊዜ “ሰው እንደሚበሉ አንበሶች የሆኑ ጠላቶቼ ከብበውኛል፤ ጥርሳቸው እንደ ጦርና እንደ ፍላጻ ነው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 57:4 የ1980 ትርጉም
ዳዊት በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ሁሉ ይሖዋ በግል እንደሚያስብለት ጽኑ እምነት ነበረው። ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ምን ያህል እንደተቅበዘበዝኩ አንተ ራስህ ታውቃለህ” ብሏል። አዎን፣ ዳዊት የደረሰበትን ሥቃይ ሁሉ ይሖዋ መዝግቦ እንደያዘለት አድርጎ ይመለከት ነበር። በዚህ የተነሳ “እንባዬን በአቁማዳ ውስጥ አከማችልኝ። ሁሉም በመዝገብህ የሰፈሩ አይደሉምን?” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።a (መዝሙር 56:8 አዓት) ዳዊት በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ይሖዋ ችግሩን ብቻ ሳይሆን ችግሩ የሚያስከትለውን ስሜታዊ ተጽዕኖ ጭምር እንደሚያውቅ ያለውን ትምክህት አሳይቷል።
ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ሊሞት አቅራቢያ እንዲህ በማለት ለመጻፍ ችሏል፦ “ሰው ሊሄድበት የሚገባውን መንገድ እግዚአብሔር ያሳየዋል፣ ደስ የሚያሰኙትንም ሰዎች ይጠብቃቸዋል። እግዚአብሔር ስለሚደግፋቸው ቢወድቁ እንኳ ይነሣሉ።” (መዝሙር 37:23, 24 የ1980 ትርጉም) አንተም ብትሆን ያለ ማቋረጥ ለረጅም ጊዜ ችግሮች ቢደርሱብህም እንኳ ይሖዋ የምታሳየውን ጽናት በቁም ነገር እንደሚመለከተውና ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጠው እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ጳውሎስ “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 6:10
በተጨማሪም ይሖዋ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም እንቅፋት በጽናት ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት ሊረዳህ ይችላል። ዳዊት “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 34:19) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ” በማለት ይነግረናል።—2 ዜና መዋዕል 16:9
ይሖዋ ወደ እርሱ ስቦሃል
ኢየሱስ የተናገረው ነገር ይሖዋ በግል እንደሚያስብልን ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጠናል። “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44) አዎን፣ ይሖዋ ሰዎች የክርስቶስ መሥዋዕት ካስገኛቸው ጥቅሞች ተካፋይ እንዲሆኑ በግለሰብ ደረጃ ይረዳቸዋል። እንዴት? በአብዛኛው ይህንን የሚያደርገው በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ነው። ይህ ሥራ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር” ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም መልእክቱ ለሰዎች በነፍስ ወከፍ ይደርሳል። የምሥራቹን መልእክት ሰምተህ ምላሽ መስጠትህ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ ያሳያል።—ማቴዎስ 24:14
ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እያንዳንዱን ሰው ወደ ልጁና ወደ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ይስባል። ይህም በዘር የወረስነው ውስን የሆነ አቅምና አለፍጽምና ቢኖርም እያንዳንዱ ሰው መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተዋልና በተግባር ለማዋል ያስችለዋል። አንድ ሰው የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ካላገኘ በስተቀር የአምላክን ዓላማዎች ለመረዳት አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 2:11, 12) ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች እንደጻፈው ‘እምነት ለሁሉ አይደለም።’ (2 ተሰሎንቄ 3:2) ይሖዋ መንፈሱን የሚሰጠው ወደ እርሱ ለመሳብ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ነው።
ይሖዋ ሰዎችን የሚስበው በግለሰብ ደረጃ ስለሚወዳቸውና እንዲድኑ ስለሚፈልግ ነው። ይህ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን የሚያሳይ እንዴት ያለ ጠንካራ ማስረጃ ነው! ኢየሱስ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:14) አዎን፣ በአምላክ ዘንድ ሁሉም ሰው በግለሰብ ደረጃ ትልቅ ዋጋ አለው። ጳውሎስ “እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ሮሜ 2:6) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ [ግለሰብ] በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሏል።—ሥራ 10:34, 35
የኢየሱስ ተአምራት
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት አምላክ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው በሚገባ ያስገነዝባሉ። ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰው ከልብ በመነጨ ርኅራኄ ተነሳስቶ ነው። (ማርቆስ 1:40, 41) ኢየሱስ ‘አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ ከራሱ ምንም ሊያደርግ ስለማይችል’ ያሳየው ርኅራኄ ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳለው ያሳያል።—ዮሐንስ 5:19
ኢየሱስ ስለ ፈጸመው አንድ ተአምር የሚናገረውን በማርቆስ 7:31-37 ላይ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። እዚህ ላይ ኢየሱስ መስማት የተሳነውና ኮልታፋ የነበረ ሰው እንደፈወሰ ይናገራል። “ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከዚያም “ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና፦ ኤፍታህ አለው፣ እርሱም ተከፈት ማለት ነው።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ኢየሱስ ይህንን ሰው ከሕዝቡ ለይቶ ብቻውን የወሰደው ለምንድን ነው? መናገር በጣም የሚቸግረውና መስማት የተሳነው አንድ ሰው በሰዎች ፊት መናገር ስለሚያሳፍረው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ሰውዬው የሚሰማውን የሐፍረት ስሜት አስተውሎ ሊሆን ይችላል፤ ከሰው ገለል አድርጎ ሊፈውሰው የመረጠውም ለዚህ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ኢየሱስ ሰውዬውን እንደ አንድ በሽተኛ ብቻ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት እንዳሳየው ጠቅላላ ታሪኩ በግልጽ ያሳየናል። ሰውዬው የራሱ የሆነ አንድ ልዩ ችግር ነበረበት። ኢየሱስ ከልብ በመነጨ አሳቢነት ተነሳስቶ ስሜቱን በማይጎዳና ችግሩን እንደተረዳለት በሚያሳይ መንገድ ረድቶታል።”
ይህ ታሪክ ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች እንደሚያስብ ያሳያል። ለአንተም እንደሚያስብልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። መሥዋዕታዊ ሞቱ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ከኃጢአት ሊዋጁ ለሚችሉ ሰዎች ያለው ፍቅር መግለጫ ነው። ቢሆንም ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ወዶኛል እንዲሁም ስለ እኔ ራሱን ሰጥቷል’ ብሎ በገለጸው መሠረት ይህ ለአንተም በግልህ እንደተደረገልህ አድርገህ ልትቆጥረው ትችላለህ። (ገላትያ 2:20) በተጨማሪም ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት ስለተናገረ ይሖዋም ለእያንዳንዱ አገልጋዩ እንደሚያስብ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐንስ 14:9
ይሖዋ መልሶ ይክሳል
ስለ አምላክ ማወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ባሕርያቱ ያላቸውን የተለያዩ ገጽታዎች በጠቅላላ ማወቅን ያጠቃልላል። “ይሆናል” የሚል ትርጉም ያለው ይሖዋ የሚለው ስም ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም መሆን የሚፈልገውን ሁሉ መሆን እንደሚችል ያሳያል። ይሖዋ ባለፉት የታሪክ ዘመናት የተለያዩ ሚናዎችን ተጫውቷል። ለምሳሌ ፈጣሪ፣ አባት፣ ሉዓላዊ ጌታ፣ እረኛ፣ የሠራዊት ጌታ፣ ጸሎት ሰሚ፣ ፈራጅ፣ ታላቅ አስተማሪና የሚቤዥ ሆኗል።b
የአምላክ ስም ያለውን ትርጉም ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ይሖዋ መልሶ በመካስ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ማወቅ አለብን። ጳውሎስ “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 11:6
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እርሱን በሙሉ ልባቸው የሚያገለግሉትን ሰዎች በገነቲቱ ምድር ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። ይህ ታላቅ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ራስ ወዳድነት አይደለም። ወይም በዚያ እንዳለን አድርገን ማሰባችን ራስን ማመጻደቅ አይደለም። ሙሴ “ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአል።” (ዕብራውያን 11:26) ጳውሎስም በተመሳሳይ አምላክ ታማኝ ለሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሰጠውን ተስፋ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። “ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሰጠኝ ሕይወት ነው” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 3:14 የ1980 ትርጉም
አንተም ብትሆን ይሖዋ ለሚጸኑ ሰዎች እሰጣቸዋለሁ ብሎ ቃል የገባውን ሽልማት በጉጉት ልትጠባበቅ ትችላለህ። ስለ አምላክ ያገኘኸው እውቀት ይህን ሽልማት በጉጉት እንድትጠባበቅ ይገፋፋሃል፤ አምላክን በጽናት ማገልገል የምትችለውም ይህን ሽልማት በጉጉት ስትጠባበቅ ነው። ይሖዋ ወደፊት ስለሚሰጥህ በረከቶች በየቀኑ አሰላስል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሜሪ ይህን ለማድረግ ልዩ ጥረት አድርጋለች። እንዲህ አለች፦ “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እኔም ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በግለሰብ ደረጃ መጠቀም እንደምችል አመንኩ። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልኝ ይሰማኝ ጀመር። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ክርስቲያን የነበርኩ ቢሆንም ይህንን ያመንኩት በቅርቡ ነው።”
ሜሪም ሆነ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ባጠኑት ነገር ላይ ከልብ በማሰላሰል ይሖዋ በጥቅሉ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ለሕዝቦቹ እንደሚያስብ እየተገነዘቡ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ነገር ላይ እምነት ስለነበረው “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:7) አዎን፣ አምላክ ስለ አንተ ያስባል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አቁማዳ እንደ ውኃ፣ ዘይት፣ ወተት፣ ወይን ጠጅ፣ ቅቤና አይብ የመሳሰሉ ነገሮችን ለመያዝ የሚያገለግል ከእንስሳት ቆዳ የተሠራ ዕቃ ነው። የጥንቶቹ አቁማዳዎች በመጠንም ሆነ በቅርጽ ይለያያሉ። አንዳንዶቹ የቆዳ ከረጢት ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ቀጭን አንገትና ውታፍ አላቸው።
b መሳፍንት 11:27፤ መዝሙር 23:1፤ 65:2፤ 73:28፤ 89:26፤ ኢሳይያስ 8:13፤ 30:20፤ 40:28፤ 41:14ን እንዲሁም በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አፔንዴክስ 1J ገጽ 1568 ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የትንሣኤ ተስፋ አምላክ እንደሚያስብልን ያረጋግጣል
አምላክ ለእያንዳንዱ ግለሰብ እንደሚያስብ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ይገኛል። ጥቅሱ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” አዓት] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” በማለት ይናገራል።
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛው ቃል ታፎስ (መቃብር) ሳይሆን ምኔሚዮን (መታሰቢያ መቃብር) የሚለው ነው። ታፎስ መቃብር ማለት ነው። ምኔሚዮን የሚለው ቃል ግን አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ታሪኩ እንደሚታሰብ ያሳያል።
በዚህ ረገድ ይሖዋ አምላክ አንድን ሰው ከሞት ለማስነሳት ምን እንደሚጠይቅበት እስቲ አስብ። አምላክ አንድን ሰው ወደ ሕይወት ለማምጣት ስለዚያ ሰው ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት። ይህም የእርሱን ወይም የእርሷን የተፈጥሮ ጠባይና በአእምሯቸው ውስጥ ያለውን ነገር በጠቅላላ ማወቅን ያጠቃልላል። የሞተው ሰው ቀደም ሲል የነበረውን ማንነት ይዞ መነሳት የሚችለው እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው።
እንዲህ ማድረጉ ከሰው ችሎታ በላይ ቢሆንም “በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል።” (ማርቆስ 10:27) ይሖዋ ሌላው ቀርቶ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ምን ነገር እንዳለ ለማወቅ እንኳ ይችላል። ግለሰቡ የሞተው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ቢሆንም እንኳ አምላክ አይረሳውም፤ ከአእምሮው አይጠፋም። (ኢዮብ 14:13-15) በዚህ የተነሳ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከሞቱ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ስለ እነርሱ ሲናገር “ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም” ለማለት ችሏል።—ሉቃስ 20:38 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ስለዚህ ይሖዋ ሞተው ስላሉት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ በአንድ ያውቃል። አምላክ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማረጋገጫ ነው!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለፈወሳቸው ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት አሳይቷቸዋል