ደቀ መዛሙርት የማድረግ ዓላማ ይዛችሁ ስበኩ
“ጵርስቅላና አቂላም [አጵሎስን] በሰሙት ጊዜ፣ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።”—የሐዋርያት ሥራ 18:26
1. አጵሎስ ‘በመንፈስ ይቃጠል’ የነበረ ቢሆንም ምን ማወቅ ያስፈልገው ነበር?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አቂላና ጵርስቅላ የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት አጵሎስ በኤፌሶን ከተማ ውስጥ በሚገኝ ምኩራብ ንግግር ሲሰጥ አገኙት። የማሳመን ችሎታ ያለው አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ የነበረው አጵሎስ የአድማጮቹን ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። ‘በመንፈስ እየተቃጠለ ስለ ኢየሱስ በትክክል ያስተምር’ ነበር። ይሁን እንጂ አጵሎስ የሚያውቀው ‘የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር።’ ስለ ክርስቶስ ይሰብክ የነበረው እውነት ቢሆንም የተሟላ እውቀት ግን አልነበረውም። አጵሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ስለሚኖረው ሚና ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ያስፈልገው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 18:24-26
2. ጵርስቅላና አቂላ ለየትኛው ከባድ ሥራ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል?
2 ጵርስቅላና አቂላ ክርስቶስ ‘ያዘዘውን ሁሉ’ መጠበቅ እንዲችል አጵሎስን ለመርዳት ያለምንም ማመንታት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ታሪኩ እንደሚናገረው አጵሎስን “ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።” ይሁን እንጂ አጵሎስን ለማስተማር እንዲያመነቱ ሊያደርጓቸው የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ነበሩ። እነዚህ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? እንዲሁም ጵርስቅላና አቂላ ከአጵሎስ ጋር በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለመወያየት ካደረጉት ጥረት ምን እንማራለን? ይህን ታሪካዊ ዘገባ መመርመራችን አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር ትኩረት እንድንሰጥ የሚረዳን እንዴት ነው?
ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር ትኩረት ስጡ
3. የአጵሎስ ማንነት ጵርስቅላና አቂላ እርሱን ከማስተማር ወደኋላ እንዲሉ ያላደረጋቸው ለምንድን ነው?
3 በትውልድ አይሁዳዊ የነበረው አጵሎስ ያደገው በእስክንድርያ ከተማ ሳይሆን አይቀርም። በወቅቱ የግብፅ ዋና ከተማ የነበረችው እስክንድርያ የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ስትሆን በትልቅ ቤተ መጻሕፍቷም የታወቀች ነበረች። ከተማይቱ ምሑራንን ጨምሮ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩባት ነበር። ሴፕቱጀንት በመባል የሚታወቀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም በዚያ የተተረጎመው ለዚህ ነው። ከዚህ አኳያ አጵሎስ “በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ” መባሉ ምንም አያስደንቅም። አቂላና ጵርስቅላ ግን ድንኳን ሠፊዎች ነበሩ። ታዲያ አጵሎስ አንደበተ ርቱዕ መሆኑን ሲመለከቱ እርሱን ለመርዳት ብቃት እንደሚጎድላቸው ተሰምቷቸው ይሆን? በፍጹም። በዋነኝነት ትኩረት የሰጡት ማወቅ ለሚያስፈልጉት ነገሮችና እንዴት ሊረዱት እንደሚችሉ ነበር።
4. አጵሎስ የሚያስፈልገውን እርዳታ ያገኘው ከየትና እንዴት ነበር?
4 አጵሎስ ምንም ያህል አንደበተ ርቱዕ ቢሆን መማር የሚያስፈልገው ነገር ነበር። ይህ ትምህርት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉ የእምነት ባልንጀሮቹ እንጂ ከየትኛውም ዩኒቨርሲቲ የሚገኝ አልነበረም። አጵሎስ የሚያገኘው ትምህርት የአምላክን የመዳን ዝግጅት አስመልክቶ ትክክለኛውን ግንዛቤ ያስጨብጠዋል። ጵርስቅላና አቂላ “ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።”
5. ጵርስቅላና አቂላ የነበራቸው መንፈሳዊነት ምን ይመስላል?
5 ጵርስቅላና አቂላ በመንፈሳዊ የጎለመሱና ጠንካራ እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች ነበሩ። የሚያነጋግሩት ሰው ሀብታምም ይሁን ድሃ፣ ምሑርም ይሁን ባሪያ ‘ስለተስፋቸው ለሚጠይቃቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ’ እንደነበሩ አያጠራጥርም። (1 ጴጥሮስ 3:15) አቂላና ሚስቱ ‘የእውነትን ቃል በትክክል የመጠቀም’ ችሎታ ነበራቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW ) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። አጵሎስ ‘ሕያውና የሚሠራ ከሆነው የአምላክ ቃል’ በተሰጠው ትምህርት ልቡ በጥልቅ ተነክቶ ነበር።—ዕብራውያን 4:12
6. አጵሎስ ለተደረገለት እርዳታ አድናቆት እንዳሳየ እንዴት እናውቃለን?
6 አጵሎስ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታውን ይበልጥ በማዳበር ለአስተማሪዎቹ መልካም አርዓያነት ያለውን አድናቆት አሳይቷል። ያገኘውን እውቀት ምሥራቹን በተለይ ለአይሁድ ማኅበረሰብ በመስበኩ ሥራ በሚገባ ተጠቅሞበታል። አጵሎስ አይሁዳውያንን በክርስቶስ እንዲያምኑ በማድረግ ረገድ የተዋጣለት ነበር። “በመጻሕፍት እውቀት የበረታ” ስለነበር ሁሉም የጥንት ነቢያት የክርስቶስን መምጣት ይጠባበቁ እንደነበር በማስረጃ ሊያሳያቸው ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 18:24) አጵሎስ ወደ አካይያ የሄደ ሲሆን እዚያም ዘገባው አክሎ እንደሚናገረው “አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው” ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 18:27, 28
ከሌሎች አስተማሪዎች ምሳሌ ተማር
7. አቂላና ጵርስቅላ የተዋጣላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?
7 አቂላና ጵርስቅላ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነበር? በትጋት ማጥናታቸውና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው መገኘታቸው እንዲሁም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረታቸው በእጅጉ ሳይጠቅማቸው አልቀረም። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳለ በጵርስቅላና በአቂላ ቤት ለ18 ወራት የኖረ ሲሆን አብረው ድንኳን ይሠሩና ይጠግኑ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:2, 3) ጥልቀት ያላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶችን ያደርጉ እንደነበረ መገመት አያዳግትም። ከጳውሎስ ጋር መቀራረባቸው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ምን ያህል ረድቷቸው ይሆን! ምሳሌ 13:20 “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል። የመሠረቱት መልካም ወዳጅነት ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:33
8. ጵርስቅላና አቂላ ከጳውሎስ አገልግሎት ምን ትምህርት አግኝተዋል?
8 ጵርስቅላና አቂላ ጳውሎስ ስለ መንግሥቱ ሲመሰክር ሲመለከቱ በማስተማር ችሎታው ግሩም ምሳሌ እንደሚሆናቸው ተገንዝበዋል። በሐዋርያት ሥራ ላይ የሚገኘው ዘገባ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳለ “በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፣ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር” ይላል። ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ ከመጡም በኋላ ጳውሎስ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር።” ጵርስቅላና አቂላ ጳውሎስ በምኩራብ ውስጥ እምብዛም በጎ ምላሽ ባላገኘ ጊዜ የስብከት እንቅስቃሴውን ይበልጥ አመቺ ሆኖ ወዳገኘው ከምኩራቡ አጠገብ ወደሚገኝ ቤት እንዳዞረ ተመልክተዋል። እዚያም ጳውሎስ “የምኵራብ አለቃ” የነበረውን ቀርስጶስን ደቀ መዝሙር እንዲሆን ረዳው። የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር መሆን የአካባቢው ሰዎች ለምሥራቹ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ያመጣውን ጉልህ ለውጥ ጵርስቅላና አቂላ ሳይመለከቱ አልቀረም። ዘገባው “ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፣ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 18:4-8
9. ጵርስቅላና አቂላ የጳውሎስን አርዓያ የተከተሉት እንዴት ነው?
9 እንደ ጵርስቅላና አቂላ ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጳውሎስ የመስክ አገልግሎትን በሚመለከት የተወውን ምሳሌ ኮርጀዋል። ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ጵርስቅላና አቂላ የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል አጵሎስ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ይበልጥ በትክክል እንዲገነዘብ ረድተውታል። እርሱም በበኩሉ ሌሎችን ረድቷል። ጵርስቅላና አቂላ በሮም፣ በቆሮንቶስና በኤፌሶን በነበሩበት ወቅት ሌሎች ሰዎችም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እንደረዱ አያጠራጥርም።—የሐዋርያት ሥራ 18:1, 2, 18, 19፤ ሮሜ 16:3-5
10. ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 18 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሊረዳህ የሚችል ምን ትምህርት አግኝተሃል?
10 የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 18ን በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል? አቂላና ጵርስቅላ ከጳውሎስ ተምረው ሊሆን እንደሚችል ሁሉ እኛም የአምላክን ቃል በማስተማር ረገድ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ክርስቲያኖች ምሳሌ በመከተል ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታችንን ማዳበር እንችላለን። ‘ለቃሉ ከሚተጉትና ከሚመሰክሩት’ ጋር መቀራረብ እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 18:5) በማሳመን ችሎታቸው ተጠቅመው የሰዎችን ልብ እንዴት እንደሚነኩ ልንመለከት እንችላለን። እንዲህ ያሉ ችሎታዎች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይረዱናል። አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ሌሎች የቤተሰቡን አባላት ወይም ጎረቤቶቹን በጥናቱ ላይ እንዲገኙ እንዲጋብዛቸው ሐሳብ ልናቀርብለት እንችል ይሆናል። ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ እንዲነግረን ልንጠይቀው እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 18:6-8
ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፍጠሩ
11. አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ለማግኘት ምሥራቹን የት የት መስበክ ይኖርብናል?
11 ጳውሎስና የእምነት ባልንጀሮቹ በሁሉም ሥፍራ ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ በገበያ ቦታ እንዲሁም በጉዞ ላይ ምሥራቹን በመስበክ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ይጥሩ ነበር። አንተስ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግብ ያለህ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪ እንደመሆንህ መጠን የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴህን ማስፋት ትችላለህ? የሚገባቸውን ሰዎች አግኝተህ ለእነርሱ ለመመሥከር የምታገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በሚገባ ትጠቀምበታለህ? አንዳንድ የምሥራቹ አስፋፊዎች ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ውጤታማ ሆነው ያገኟቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እስቲ በመጀመሪያ በስልክ የሚሰጥ ምሥክርነት ምን ውጤት እንዳስገኘ እንመልከት።
12-14. በስልክ ምሥክርነት መስጠት የሚያስገኘውን ውጤት ለማሳየት በአንቀጾቹ ውስጥ የቀረቡትን ወይም በግል ያገኘሃቸውን ተሞክሮዎች ተናገር።
12 በብራዚል የምትኖር አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ከአፓርታማ ስትወጣ ላገኘቻት አንዲት ወጣት ሴት ትራክት ሰጠቻት። ከዚያም የትራክቱን ርዕስ እንደ መግቢያ በመጠቀም ‘ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጊያለሽ?’ በማለት ጠየቀቻት። ወጣቷም “እፈልጋለሁ። ሆኖም መምህር ስለሆንኩ የማስተማር ሥራዬ ጊዜዬን ሁሉ ይወስድብኛል” አለቻት። እህት በስልክ እየተገናኙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ እንደሚችሉ ገለጸችላት። ወጣቷ ስልክ ቁጥሯን ለእህት ሰጠቻትና የዚያኑ ዕለት ማታ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር በስልክ ማጥናት ጀመረች።a
13 በኢትዮጵያ የምትኖር አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በስልክ ምሥክርነት ለመስጠት ወደ አንድ ቤት ደወለች። ስልኩ ሲነሳ ሰዎች ሲጨቃጨቁ በመስማቷ ትንሽ ደንገጥ አለች። ስልኩን ያነሳው ሰው ቆየት ብላ እንድትደውል ጠየቃት። እንደተባለችው ትንሽ ቆይታ ስትደውል ሰውዬው ይቅርታ ጠየቃትና ቀደም ሲል ሊያነጋግራት ያልቻለው እርሱና ባለቤቱ ይጨቃጨቁ ስለነበር እንደሆነ ነገራት። እህት ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ግሩም መመሪያ እንደያዘ ጠቀሰችለት። በርካታ ቤተሰቦች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በማንበብ እንደተጠቀሙ ነገረችው። ሰውዬው መጽሐፉ ከደረሰው ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደገና ደወለችለት። እርሱም “መጽሐፉ ትዳሬን ከመፍረስ አድኖልኛል!” በማለት በደስታ ነገራት። እንዲያውም ከመጽሐፉ ያገኛቸውን ጥሩ ጥሩ ነጥቦች ለማካፈል የቤተሰብ ስብሰባም አድርጎ ነበር። ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ።
14 በስልክ በመመሥከር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያገኘች አንዲት በዴንማርክ የምትኖር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንዲህ ትላለች:- “የጉባኤያችን የአገልግሎት የበላይ ተመልካች በስልክ በመመሥከሩ ሥራ እንድካፈል አበረታቶኝ ነበር። በመጀመሪያ ‘ይህ እንኳን ለእኔ የሚሆን አይደለም’ ብዬ አመንትቼ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን እንደምንም ራሴን አደፋፈርኩና ወደ አንድ ቤት ደወልኩ። ሶንያ የምትባል ሴት ስልኩን አነሳችና ትንሽ ከተወያየን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ለመውሰድ ተስማማች። አንድ ቀን ምሽት ፍጥረትን በሚመለከት ስንነጋገር ሕይወት እንዴት ተገኘ—በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ለማንበብ እንደምትፈልግ ነገረችኝ።b በግንባር ተገናኝተን በዚህ ርዕስ ላይ ውይይት ብናደርግ እንደሚሻል ሐሳብ ሳቀርብላት ተስማማች። በቀጠሯችን ስንገናኝ ሶንያ ለማጥናት ተዘጋጅታ እየጠበቀችኝ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየሳምንቱ እየተገናኘን እናጠናለን።” እህት ስትደመድም እንዲህ ትላለች:- “ለረጅም ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማግኘት እጸልይ ነበር። በስልክ በመመሥከር ጥናት አገኛለሁ ብዬ አስቤ ግን አላውቅም።”
15, 16. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት መከታተል ያለውን ጥቅም የሚያሳዩ ተሞክሮዎች ተናገር።
15 በርካታ ክርስቲያኖች ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ እንድንመሠክር የተሰጠንን ማበረታቻ ተግባራዊ በማድረጋቸው ስኬታማ ሆነዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት መኪናዋን በአንድ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ከአንድ የዕቃ ማጓጓዣ መኪና ጎን አቆመች። በመኪና ውስጥ የነበረችው ሴት ስታያት እህት መጽሐፍ ቅዱስን ስለማስተማር ሥራችን አንዳንድ ነገሮችን ነገረቻት። ሴትየዋ ካዳመጠቻት በኋላ ከመኪናዋ ወርዳ ወደ እህት መኪና ተጠጋችና እንዲህ አለቻት:- “ስላነጋገርሽኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ጽሑፎቻችሁን ለረጅም ጊዜ አላገኘሁም ነበር። እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እፈልጋለሁ። ልታስጠኚኝ ፈቃደኛ ነሽ?” ይህች እህት ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችላትን አጋጣሚ ፈጥራለች።
16 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት ወደ አንድ የአረጋውያን መንከባከቢያ ቤት በሄደችበት ወቅት የሚከተለውን ተሞክሮ አግኝታለች:- በተቋሙ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያለውን አንድ ሰው ቀርባ በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ራሷን በፈቃደኝነት ማቅረብ እንደምትፈልግ ገለጸችለት። አክላም ፍላጎት ላላቸው ሁሉ በየሳምንቱ ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ፈቃደኛ መሆኗን ነገረችው። ሰውዬው በየመኖሪያ ክፍሎቹ እየሄደች እንድታነጋግር ፈቀደላት። ብዙም ሳይቆይ በሳምንት ሦስት ጊዜ እየሄደች 26 የሚያህሉ የተቋሙን ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች። ከመካከላቸው አንዱ አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል።
17. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመር ረገድ ብዙውን ጊዜ ውጤታማ የሆነው የትኛው አቀራረብ ነው?
17 አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን አብረዋቸው እንዲያጠኑ ሰዎችን በቀጥታ መጋበዙን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። አንድ ቀን 105 የሚያህሉ አስፋፊዎች ያሉት የአንድ ጉባኤ አባላት ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ የሚያገኙትን እያንዳንዱን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና የመጋበዝ ግብ ይዘው ወደ አገልግሎት ወጡ። በዕለቱ በመስክ አገልግሎት የተካፈሉት አስፋፊዎች 86 ሲሆኑ ሁለት ሰዓት ያህል ካገለገሉ በኋላ በድምሩ 15 የሚያህሉ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ችለዋል።
የሚገባቸውን ሰዎች መፈለጋችሁን አታቋርጡ
18, 19. ኢየሱስ የሰጠንን የትኛውን አስፈላጊ መመሪያ መዘንጋት የለብንም? ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
18 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ከሆንክ በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ትፈልግ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ምሥክርነት የምንሰጥባቸውን መንገዶች ስንመርጥ የአካባቢውን ልማድ ግምት ውስጥ ማስገባታችን ተገቢ ይሆናል። በተጨማሪም ኢየሱስ የሚገባቸውን ሰዎች እንድንፈልግና ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እንድንረዳቸው የሰጠንን መመሪያ ምንጊዜም አንዘንጋ።—ማቴዎስ 10:11፤ 28:19
19 ይህን ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ‘የእውነትን ቃል በትክክል እንጠቀም።’ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ አሳማኝ ማስረጃዎችን በማቅረብ ይህን ማድረግ እንችላለን። ይህ ደግሞ ለምሥራቹ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ልብ ለመንካትና ለተግባር ለማነሳሳት ያስችለናል። ይሖዋ እንዲረዳን በጸሎት በመጠየቅ ሌሎች ሰዎችም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳቱ ሥራ መካፈል እንችላለን። ይህ ሥራ ትልቅ በረከት የሚያስገኝ ነው! ስለዚህ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ዓላማ ይዘን የምንሰብክ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን ‘የተፈተነውን ራሳችንን ለአምላክ ለማቅረብ በመትጋት’ ምንጊዜም ይሖዋን እናክብር።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ታስታውሳለህ?
• አጵሎስ የአምላክ መንገድ በተሟላ ሁኔታ እንዲብራራለት ያስፈለገው ለምን ነበር?
• ጵርስቅላና አቂላ ከጳውሎስ ምን ተምረዋል?
• ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 18 ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በሚመለከት ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጵርስቅላና አቂላ ለአጵሎስ “የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት”
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጵሎስ ደቀ መዝሙር የማድረግ ችሎታውን አዳብሯል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ሰብኳል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፍጠሩ