የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መስከረም 2019
ከመስከረም 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 7-8
“እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ”
(ዕብራውያን 7:1, 2) አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ የሳሌም ንጉሥና የልዑሉ አምላክ ካህን የሆነው ይህ መልከጼዴቅ አግኝቶት ባረከው፤ 2 አብርሃም ደግሞ ከሁሉ ነገር አንድ አሥረኛ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ደግሞም የሳሌም ንጉሥ ማለትም “የሰላም ንጉሥ” ነው።
it-2 366
መልከጼዴቅ
የጥንቷ ሳሌም ንጉሥ እንዲሁም “የልዑሉ አምላክ [የይሖዋ] ካህን” ነበር። (ዘፍ 14:18, 22) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ካህን እሱ ነው፤ ካህን የሆነው ከ1933 ዓ.ዓ. በፊት ነው። ሳሌም ማለት “ሰላም” ማለት ስለሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ የሳሌም ንጉሥ የሆነውን መልከጼዴቅን “የሰላም ንጉሥ” በማለት ጠርቶታል፤ በስሙ ትርጉም መሠረት “የጽድቅ ንጉሥ” ተብሎም ተጠርቷል። (ዕብ 7:1, 2) የጥንቷ ሳሌም በኋላ ለተቋቋመችው የኢየሩሳሌም ከተማ መሠረት እንደሆነች ይታመናል፤ ስሟም ኢየሩሳሌም በሚለው ስም ውስጥ ተካቷል፤ ኢየሩሳሌምም “ሳሌም” ተብላ የተጠራችበት ጊዜ አለ።—መዝ 76:2
አብራም (አብርሃም) ኮሎዶጎምርንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ ወደ ሻዌ ሸለቆ ማለትም “ወደ ንጉሡ ሸለቆ” መጣ። በዚያም መልከጼዴቅ “ምግብና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ”፤ አብርሃምንም እንዲህ ሲል ባረከው፦ “ሰማይንና ምድርን የሠራው ልዑሉ አምላክ አብራምን ይባርክ፤ የሚጨቁኑህን በእጅህ አሳልፎ የሰጠህ፣ ልዑሉ አምላክ ይወደስ!” ከዚያም አብርሃም ንጉሥና ካህን ለሆነው ለዚህ ሰው “ከሁሉም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን” ማለትም በጦርነቱ ካገኘው “ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን” ሰጠው።—ዘፍ 14:17-20፤ ዕብ 7:4
(ዕብራውያን 7:3) አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።
it-2 367 አን. 4
መልከጼዴቅ
መልከጼዴቅ “ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም” የተባለው ከምን አንጻር ነው?
ጳውሎስ መልከጼዴቅን በተመለከተ አንድ አስደናቂ ነገር ተናግሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” (ዕብ 7:3) መልከጼዴቅ እንደ ማንኛውም ሰው ተወልዷል፤ እንዲሁም ሞቷል። ይሁንና የአባቱና የእናቱ ስም አልተገለጸም፤ ስለ አያት ቅድመ አያቶቹም ሆነ ስለ ዘሮቹ የተገለጸ ነገር የለም፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወቱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ምንም አይናገርም። በመሆኑም መልከጼዴቅ ለዘላለም ካህን ለሚሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ መሆኑ ተገቢ ነው። መልከጼዴቅ በክህነቱ ቀዳሚም ሆነ ተተኪ አልነበረውም፤ ከክርስቶስ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ከክርስቶስ በፊት እንደ እሱ ያለ ሊቀ ካህናት አልነበረም፤ ከእሱ በኋላም እንደማይነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ከዚህም ሌላ ክርስቶስ የተወለደው ከይሁዳ ነገድ፣ ከንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ ቢሆንም ክህነትን ያገኘው ከአባቶቹ አይደለም፤ እንዲሁም ክህነትንና ንግሥናን አጣምሮ ሊይዝ የቻለው በዘሩ ምክንያት አይደለም። ይህን ሹመት ያገኘው ይሖዋ ራሱ በገባለት ቃል መሠረት ነው።
(ዕብራውያን 7:17) “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመሥክሮለታልና።
it-2 366
መልከጼዴቅ
ለክርስቶስ ክህነት ጥላ ሆኗል። ስለ መሲሑ ከተነገሩ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ትንቢቶች በአንዱ ላይ ይሖዋ “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” በማለት ለዳዊት “ጌታ” ቃል ገብቶለታል። (መዝ 110:1, 4) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ መዝሙር፣ ዕብራውያን ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ካህንም ንጉሥም እንደሚሆን እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ” በማለት ይህ ትንቢት የሚናገረው ስለ ማን እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል።—ዕብ 6:20፤ 5:10፤ “ቃል ኪዳን” የሚለውን ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 8:3) እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው ስጦታና መሥዋዕት ለማቅረብ ነውና፤ በመሆኑም ይሄኛው ሊቀ ካህናትም የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል።
አምላክ የተደሰተባቸው መሥዋዕቶች
11 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 8:3) ጳውሎስ የጥንቱ እስራኤል ሊቀ ካህናት የሚሠዋቸውን ነገሮች “መባ” እና “መሥዋዕት” ወይም ‘ስለ ኃጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት’ በማለት ለሁለት ከፍሎ እንደተናገረ ልብ በል። (ዕብራውያን 5:1) በጥቅሉ ሰዎች ፍቅራቸውንና አድናቆታቸውን ለመግለጽም ሆነ ወዳጅነታቸውን ለማዳበር እንዲሁም በሌሎች ዘንድ ሞገስ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት ስጦታ ይሰጣሉ። (ዘፍጥረት 32:20፤ ምሳሌ 18:16) በተመሳሳይም ሕጉ በሚያዘው መሠረት የሚቀርቡት ብዙዎቹ መሥዋዕቶች በአምላክ ዘንድ ሞገስ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል የሚሰጡ ‘መባዎች’ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። አንድ ሰው ሕጉን ቢተላለፍ ካሳ እንዲከፈል ይጠበቅበት ነበር፤ ካሳውም “ስለ ኃጢአት” በሚቀርብ “መሥዋዕት” ይከፈል ነበር። ፔንታቱች (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) በተለይ ደግሞ የዘጸአት፣ የዘሌዋውያንና የዘኁልቁ መጻሕፍት መሥዋዕቶችንና መባዎችን በተመለከተ ብዙ ሐሳብ ይሰጣሉ። እነዚህን ሁሉ ዝርዝር ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ መረዳትና ማስታወሱ አስቸጋሪ ሊሆንብን ቢችልም ስለተለያዩ ዓይነት መሥዋዕቶች በሚናገሩ አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ላይ ትኩረት ብናደርግ ተገቢ ነው።
(ዕብራውያን 8:13) “አዲስ ቃል ኪዳን” ሲል የቀድሞውን ቃል ኪዳን ጊዜ ያለፈበት አድርጎታል። ስለዚህ ጊዜ ያለፈበትና እያረጀ ያለው ቃል ኪዳን ሊጠፋ ተቃርቧል።
it-1 523 አን. 5
ቃል ኪዳን
የሕጉ ቃል ኪዳን “ጊዜ ያለፈበት” የሆነው በምን መንገድ ነው?
ይሁን እንጂ አምላክ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚቋቋም በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ሲናገር የሕጉ ቃል ኪዳን “ጊዜ ያለፈበት” ሆኗል ሊባል ይችላል። (ኤር 31:31-34፤ ዕብ 8:13) በ33 ዓ.ም. ክርስቶስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞቱ የሕጉ ቃል ኪዳን ፈርሶ (ቆላ 2:14) በአዲሱ ቃል ኪዳን ተተክቷል።—ዕብ 7:12፤ 9:15፤ ሥራ 2:1-4
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
it-1 524 አን. 3-5
አዲሱ ቃል ኪዳን። ይሖዋ በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚያቋቁም የተነበየ ሲሆን ይህ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን ካፈረሱት የሕጉ ቃል ኪዳን የተለየ እንደሚሆን ገልጿል። (ኤር 31:31-34) ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ማለትም ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ላይ የጌታ ራት በዓልን ሲያቋቁም እሱ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት የሚጸድቅ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚቋቋም አስታውቋል። (ሉቃስ 22:20) ከሞት በተነሳ በ50ኛው ቀን ማለትም ወደ አባቱ ካረገ ከ10 ቀን በኋላ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ሰገነት ላይ ተሰብስበው በነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ላይ ከይሖዋ የተቀበለውን መንፈስ ቅዱስ አፈሰሰ።—ሥራ 2:1-4, 17, 33፤ 2ቆሮ 3:6, 8, 9፤ ዕብ 2:3, 4
ቃል ኪዳኑን የተጋቡት ይሖዋና ‘የአምላክ እስራኤል’ ማለትም የክርስቶስ ጉባኤ ወይም አካል የሆኑትና ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ናቸው። (ዕብ 8:10፤ 12:22-24፤ ገላ 6:15, 16፤ 3:26-28፤ ሮም 2:28, 29) አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም (መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው ሰብዓዊ ሕይወቱ) አማካኝነት ነው፤ የመሥዋዕቱ ዋጋ ለይሖዋ የቀረበው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ነው። (ማቴ 26:28) አምላክ አንድን ሰው ለሰማያዊ ጥሪ በሚመርጥበት ጊዜ (ዕብ 3:1) በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት በቃል ኪዳኑ እንዲታቀፍ ያደርገዋል። (መዝ 50:5፤ ዕብ 9:14, 15, 26) ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ (ዕብ 8:6፤ 9:15) ከመሆኑም ሌላ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል ነው። (ገላ 3:16) ኢየሱስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ በሚያከናውነው አገልግሎት አማካኝነት በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ በማግኘት በእርግጥም የአብርሃም ዘር ክፍል መሆን እንዲችሉ ይረዳቸዋል። (ዕብ 2:16፤ ገላ 3:29) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ጻድቃን ይላቸዋል።—ሮም 5:1, 2፤ 8:33፤ ዕብ 10:16, 17
እነዚህ በመንፈስ የተወለዱ የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሊቀ ካህናቱ ሥር ሆነው የሚያገለግሉ “ንጉሣዊ ካህናት” ይሆናሉ። (1ጴጥ 2:9፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) ቅቡዓኑ የክህነት ሥራ ይኸውም “ሕዝባዊ አገልግሎት” ያከናውናሉ (ፊልጵ 2:17 ግርጌ)፤ “የአዲስ ቃል ኪዳን አገልጋዮች” ተብለውም ተጠርተዋል። (2ቆሮ 3:6) ሰማያዊ ጥሪ ያገኙት እነዚህ ሰዎች እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታማኝ መሆንና የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ይኖርባቸዋል፤ ከዚህ በኋላ ይሖዋ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንዲሆኑ በማድረግ የመንግሥት ካህናት ያደርጋቸዋል፤ እንዲሁም የማይሞትና የማይበሰብስ ሕይወት ሽልማት አድርጎ በመስጠት በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ወራሾች ያደርጋቸዋል። (1ጴጥ 2:21፤ ሮም 6:3, 4፤ 1ቆሮ 15:53፤ 1ጴጥ 1:4፤ 2ጴጥ 1:4) የቃል ኪዳኑ ዓላማ ለይሖዋ ስም የሚሆኑ ሰዎችን መውሰድ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የአብርሃም “ዘር” ክፍል ናቸው። (ሥራ 15:14) ደግሞም የክርስቶስ “ሙሽራ” ይሆናሉ፤ ክርስቶስ አብረውት እንዲገዙ በቡድን ደረጃ ከእነሱ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን ገብቷል። (ዮሐ 3:29፤ 2ቆሮ 11:2፤ ራእይ 21:9፤ ሉቃስ 22:29፤ ራእይ 1:4-6፤ 5:9, 10፤ 20:6) ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት በሙሉ ከሞት ተነስተው በሰማይ የማይሞት ሕይወት እስኪያገኙ ድረስ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋሉን ይቀጥላል።
it-1 1113 አን. 4-5
ሊቀ ካህናት
የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ክህነት። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዕብራውያን መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ “እንደ መልከጼዴቅ . . . ለዘላለም ካህን” እንደሆነ ይናገራል። (ዕብ 6:20፤ 7:17, 21) የክርስቶስ ክህነት ከአሮን ክህነት የላቀ መሆኑን ለማሳየት ሲል ጸሐፊው፣ መልከጸዴቅ ንጉሥና ካህን የሆነው በውርስ ሳይሆን በሉዓላዊው አምላክ ተሹሞ እንደሆነ ገልጿል። ክርስቶስ ኢየሱስ የሌዊ ነገድ ሳይሆን ከይሁዳ ነገድ የሆነ የዳዊት ዘር ነው፤ በመሆኑም ክህነቱን ያገኘው የአሮን ዘር በመሆን ሳይሆን ልክ እንደ መልከጸዴቅ በአምላክ በቀጥታ በመሾም ነው። (ዕብ 5:10) መዝሙር 110:4 “ይሖዋ ‘እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ!’ ሲል ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም” ይላል፤ እዚህ ጥቅስ ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት ክርስቶስ ንጉሥና ካህን ሆኖ በሰማይ ያገለግላል፤ በተጨማሪም ክርስቶስ የዳዊት ዘር በመሆኑ ንጉሥ ሆኖ የመግዛት መብት አለው። የዳዊት ዘር መሆኑ ደግሞ በዳዊት ቃል ኪዳን መሠረት የንጉሣዊ ሥልጣን ወራሽ እንዲሆን ያደርገዋል። (2ሳሙ 7:11-16) በመሆኑም ልክ እንደ መልከጸዴቅ ንጉሥም ካህንም ሊሆን ችሏል።
የክርስቶስን ሊቀ ክህነት የላቀ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። የአይሁድ ካህናት አባት የሆነው ሌዊ ለመልከጸዴቅ አሥራት ሰጥቷል ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም አብርሃም ለሳሌም ካህንና ንጉሥ አሥራት በሰጠበት ጊዜ ሌዊ በአብርሃም አብራክ ውስጥ ነበር። ከዚህ አንጻር መልከጸዴቅ ሌዊን ባርኮታል ሊባል ይችላል፤ አነስተኛ የሆነውን የሚባርከው ከእሱ የሚበልጠው እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዕብ 7:4-10) ሐዋርያው፣ መልከጸዴቅ “አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ” እንደሌለው ገልጿል፤ ይህም ከሞት ተነስቶ “የማይጠፋ ሕይወት” ያገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክህነት ይወክላል።—ዕብ 7:3, 15-17
ከመስከረም 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 9-10
“ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ”
(ዕብራውያን 9:12-14) ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን። 13 የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ ሥጋን በማንጻት የሚቀድስ ከሆነ 14 በዘላለማዊ መንፈስ አማካኝነት ራሱን ያላንዳች እንከን ለአምላክ ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው ለሆነው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ ሕሊናችንን ከሞቱ ሥራዎች እንዴት አብልጦ አያነጻም?
it-1 862 አን. 1
ይቅርታ
አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ እንደሚያዘው በአምላክ ወይም በባልንጀራው ላይ ኃጢአት የሠራ ሰው ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት ከፈለገ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ለበደሉ ካሳ መክፈል፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ለይሖዋ የደም መባ ማቅረብ ነበረበት። (ዘሌ 5:5–6:7) ጳውሎስ “አዎ፣ በሕጉ መሠረት ሁሉም ነገር ማለት ይቻላል በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ ማግኘት አይቻልም” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው። (ዕብ 9:22) ይሁንና መሥዋዕት ሆነው የቀረቡ እንስሳት ደም የግለሰቡን ኃጢአት በማስወገድ ሙሉ በሙሉ ንጹሕ የሆነ ሕሊና ሊሰጠው አይችልም። (ዕብ 10:1-4፤ 9:9, 13, 14) በተቃራኒው ግን በትንቢት የተነገረው አዲስ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እውነተኛ ይቅርታ ማስገኘት ችሏል። (ኤር 31:33, 34፤ ማቴ 26:28፤ 1ቆሮ 11:25፤ ኤፌ 1:7) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜም እንኳ አንድን ሽባ ሰው በመፈወስ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል።—ማቴ 9:2-7
(ዕብራውያን 9:24-26) ክርስቶስ የገባው በሰው እጅ ወደተሠራውና የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ ወደሆነው ስፍራ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ አሁን ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ ወደ ሰማይ ገብቷል። 25 የገባው ግን ሊቀ ካህናቱ የራሱን ሳይሆን የእንስሳ ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገባ እንደነበረው ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አይደለም። 26 አለዚያማ ዓለም ከተመሠረተ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ኃጢአትን ለማስወገድ በሥርዓቶቹ መደምደሚያ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን ገልጧል።
“እኔን መከተልህን ቀጥል”
4 ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ ወደ ሰማይ በተመለሰበት ጊዜ ምን ዓይነት አቀባበል እንደተደረገለትና ከአባቱ ጋር ሲገናኝ ስለነበረው አስደሳች ሁኔታ የሚገልጹት ነገር የለም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ምን እንደሚከናወን አስቀድሞ ተናግሯል። መቼም አይሁዳውያን ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት አንድ ቅዱስ ሥርዓት በቋሚነት ሲከናወን ይመለከቱ እንደነበር ሳታውቅ አትቀርም። ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡትን እንስሳት ደም በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለመርጨት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር። በዚያ ቀን ይህን የሚያከናውነው ሊቀ ካህናት ለመሲሑ ጥላ ሆኖ ያገለግል ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ትንቢታዊ ትርጉም ያለው ይህ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል። ኢየሱስ በሰማይ ይሖዋ ወደሚገኝበት ክብራማ ቦታ ይኸውም በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ እጅግ ቅዱስ ወደሆነው ስፍራ በመግባት የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ ለአባቱ አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:11, 12, 24) ታዲያ ይሖዋ ተቀብሎት ይሆን?
(ዕብራውያን 10:1-4) ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ የእነዚህ ነገሮች እውነተኛ አካል አይደለም፤ ስለዚህ ሕጉ ከዓመት ዓመት እነዚያኑ መሥዋዕቶች በማቅረብ አምላክን የሚያመልኩትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው አይችልም። 2 ቢችልማ ኖሮ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረም? ምክንያቱም ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ሰዎች አንዴ ከነጹ በኋላ ሕሊናቸው በጥፋተኝነት ስሜት አይወቅሳቸውም ነበር። 3 ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች ከዓመት ዓመት ኃጢአት እንዲታወስ ያደርጋሉ፤ 4 የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልምና።
it-2 602-603
ፍጽምና
የሙሴ ሕግ ፍጽምና። በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ የክህነት ሥርዓትን እንዲሁም የተለያዩ እንስሳት መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡበትን ዝግጅት ያካተተ ነበር። ሕጉ ከአምላክ የመጣ በመሆኑ ፍጹም ቢሆንም ሐዋርያው በመንፈስ መሪነት እንደተናገረው ሕጉ፣ ካህናቱም ሆኑ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች በሕጉ ሥር ለነበሩት ሰዎች ፍጽምና አላስገኙም። (ዕብ 7:11, 19፤ 10:1) ሕጉ ሕዝቡን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ከማውጣት ይልቅ የኃጢአትን ምንነት አሳውቋል። (ሮም 3:20፤ 7:7-13) ሆኖም እነዚህ መለኮታዊ ዝግጅቶች አምላክ ያሰበላቸውን ዓላማ አሳክተዋል፤ ሕጉ “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” በመሆን እንደ ‘ሞግዚት’ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መርቷል። (ገላ 3:19-25፤ ዕብ 10:1) ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕጉ ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ደካማ” (ሮም 8:3) እንደሆነ ሲናገር ዕብራውያን 7:11, 18-28 እንደሚያብራራው (በሕጉ መሠረት መሥዋዕት የማቅረብና በስርየት ቀን የመሥዋዕቱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የመግባት ኃላፊነት ያለበት) የአይሁድ ሊቀ ካህናት፣ የሚያገለግላቸውን ሰዎች ሙሉ በሙሉ “ሊያድናቸው” እንደማይችል እየገለጸ መሆን አለበት። በአሮን የክህነት ሥርዓት ሥር የሚቀርበው የእንስሳ መሥዋዕት ሕዝቡ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም እንዲኖራቸው ቢያደርግም ከኃጢአተኝነት ስሜት ሙሉ በሙሉ ወይም ፍጹም በሆነ መንገድ ነፃ እንዲሆኑ አላደረጋቸውም። ሐዋርያው በስርየት ቀን የሚቀርበው መሥዋዕት “አምላክን የሚያመልኩትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው” ማለትም ፍጹም በሆነ መንገድ ንጹሕ ሕሊና ሊሰጣቸው እንደማይችል የገለጸው ለዚህ ነው። (ዕብ 10:1-4፤ ከዕብ 9:9 ጋር አወዳድር።) ሊቀ ካህናቱ ከኃጢአት እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት የሚያስችለውን ቤዛ መክፈል አይችልም ነበር። ይህን ሊያደርግ የሚችለው የክርስቶስ ዘላለማዊ የክህነት አገልግሎትና እሱ ያቀረበው የተሟላ መሥዋዕት ብቻ ነው።—ዕብ 9:14፤ 10:12-22
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 9:16, 17) ቃል ኪዳን ሲኖር ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው መሞቱ መረጋገጥ አለበት፤ 17 ምክንያቱም ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ቃል ኪዳኑ መቼም ተፈጻሚ ሊሆን ስለማይችል ቃል ኪዳን የሚጸናው ሞትን መሠረት በማድረግ ነው።
የአንባብያን ጥያቄዎች
በአምላክና በሰዎች መሃል የሚገባ ቃል ኪዳን ለማጽናት ሞት አስፈላጊ እንደሚሆን ጳውሎስ ጠቅሶአል። ለዚህም የሕጉ ቃል ኪዳን ምሳሌ ይሆነናል። በአምላክና በሥጋዊ እሥራኤል መሃል የተደረገውን ውል ያዋዋለው ሙሴ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ ነበር። ስለዚህ ሙሴ እሥራኤላውያንን ወደ ቃል ኪዳኑ ለማምጣት ያገለገለና ወሳኝ ሚና የተጫወተ ሰው ነበር። በመሆኑም ሙሴ ከይሖዋ አምላክ ለመነጨው የሕግ ቃል ኪዳን እንደሰብአዊ ቃልኪዳን አድራጊ ሊቆጠር ይችላል። ታዲያ የሕጉ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ እንዲውል ሙሴ ደመ ሕይወቱን ማፍሰስ አስፈልጎታልን? አላስፈለገውም። ለሙሴ ደም ምትክ ሆኖ የቀረበው የእንስሳት ደም ነበር።—ዕብራውያን 9:18-22
በይሖዋና በመንፈሳዊ እሥራኤል መሃል ስለተደረገው አዲስ ቃል ኪዳንስ ምን ሊባል ይችላል? በይሖዋና በመንፈሳዊ እሥራኤል መሃል አስታራቂና መካከለኛ የመሆን ታላቅ ሥራ የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ ቃል ኪዳን የመነጨው ከይሖዋ ቢሆንም የቃልኪዳኑ መጽደቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመካ ነበር። ኢየሱስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ከመሆኑም ሌላ ወደዚህ ቃል ኪዳን ከሚገቡት የመጀመሪያ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ ሥጋዊ ግንኙነት ነበረው። (ሉቃስ 22:20,28,29) ከዚህም በላይ አዲሱን ቃል ኪዳን ለማጽደቅ የሚያስፈልገውን መሥዋዕት ለማቅረብ ብቃት ነበረው። ይህም መሥዋዕት የእንስሳት ሥጋ ሳይሆን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ክርስቶስን የአዲሱ ቃል ኪዳን ሰብዓዊ ቃልኪዳን አድራጊ ሊለው ችሏል። “ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሷ ወደሰማይ” ከገባ በኋላ አዲሱ ቃል ኪዳን ፀደቀ።—ዕብራውያን 9:12-14,24
ጳውሎስ ሙሴና ኢየሱስ ሰብዓዊ ቃልኪዳን አድራጊዎች መሆናቸው ሲናገር ማንኛቸውም መካከለኛ የሆኑላቸውን ቃል ኪዳኖች ራሳቸው እንዳመነጩአቸው ማመልከቱ አልነበረም። ምክንያቱም እነዚህ ቃል ኪዳኖች የተደረጉት በአምላክ ነበር።እነዚህ ሰዎች ግን መካከለኛ የሆኑላቸውን ቃል ኪዳኖች ለማቋቋም እንደመካከለኛ በመሆን ቀጥተኛ ድርሻ አበርክተዋል። በሁለቱም ቃልኪዳኖች ሞት አስፈልጊ ሆኖ ነበር። በአሮጌው ቃል ኪዳን ረገድ እንስሳት የሙሴ ምትክ ሆነው ሲገደሉ ኢየሱስ ደግሞ በአዲሱ ቃል ኪዳን ወስጥ ለገቡት ሰዎች ሲል የራሱን ደመ ሕይወት ሰጥቷል።
(ዕብራውያን 10:5-7) ስለዚህ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “‘መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ። 6 ሙሉ በሙሉ በሚቃጠል መባና ለኃጢአት በሚቀርብ መባ ደስ አልተሰኘህም።’ 7 በዚህ ጊዜ ‘እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ (ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል እንደተጻፈ) ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ’ አልኩ።”
it-1 249-250
ጥምቀት
ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ይጸልይ እንደነበር ሉቃስ ተናግሯል። (ሉቃስ 3:21) ለዕብራውያን የተላከውን ደብዳቤ ጸሐፊም ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ” (ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ኢየሱስ ለመጠመቅ ራሱን ያቀረበበትንና አገልግሎቱን የጀመረበትን ጊዜ ነው፤ ምክንያቱም በተወለደበት ጊዜ ማንበብም ሆነ እነዚህን ቃላት መናገር አይችልም ነበር) በመዝሙር 40:6-8 (ግርጌ) ላይ በተገለጸው መሠረት “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ። . . . እነሆ፣ መጥቻለሁ። ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል ተጽፏል። አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ብሎ ነበር። (ዕብ 10:5-9) ኢየሱስ የተወለደው በአይሁድ ብሔር ውስጥ ነው፤ አይሁዳውያን ደግሞ በብሔር ደረጃ ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን (የሕጉ ቃል ኪዳን) ያላቸው ሕዝብ ነበሩ። (ዘፀ 19:5-8፤ ገላ 4:4) በመሆኑም ኢየሱስ ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ ከመሄዱ በፊትም ከይሖዋ አምላክ ጋር ቃል ኪዳን ነበረው። ኢየሱስ የተጠመቀው በሕጉ ውስጥ የሚጠበቅበትን ነገር ለማድረግ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የአባቱን “ፈቃድ” ለማድረግ ለአባቱ ለይሖዋ ራሱን አቅርቧል፤ ይህም ‘የተዘጋጀለትን’ አካል መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብንና በሕጉ መሠረት የሚቀርበውን የእንስሳት መሥዋዕት ማስቀረትን ይጨምራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ‘ፈቃድ’ መሠረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።” (ዕብ 10:10) አብ ለኢየሱስ ያለው ፈቃድ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚያከናውነውን ሥራም ያካትታል፤ ኢየሱስ ራሱን ያቀረበው ለዚህ አገልግሎትም ጭምር ነው። (ሉቃስ 4:43፤ 17:20, 21) ይሖዋ ልጁን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባትና “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ በመናገር ልጁ ራሱን ሲያቀርብ እንደተቀበለው ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ማር 1:9-11፤ ሉቃስ 3:21-23፤ ማቴ 3:13-17
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከመስከረም 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 11
“እምነት አስፈላጊ ነው”
(ዕብራውያን 11:1) እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው፤ በተጨማሪም የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።
ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላችሁ በተግባር አሳዩ
6 መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምን እንደሆነ በዕብራውያን 11:1 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ ያብራራል። እምነት፣ ልናያቸው በማንችላቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፦ (1) ‘ተስፋ የተደረጉት ነገሮች።’ ይህም ወደፊት እንደሚፈጸሙ ተስፋ የተሰጠባቸው ሆኖም ገና ያልተፈጸሙ ነገሮችን፣ ለምሳሌ ክፋት ሁሉ እንደሚወገድና አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠንን ተስፋ ይጨምራል። (2) ‘በዓይን ባይታዩም እውን የሆኑ ነገሮች።’ እዚህ ጥቅስ ላይ “ተጨባጭ ማስረጃ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ነገር በዓይን ባይታይም እውን መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫን ያመለክታል፤ ለምሳሌ ይሖዋ አምላክን፣ ኢየሱስ ክርስቶስንና መላእክትን በዓይን ማየት ባንችልም እውን መሆናቸውን እናውቃለን፤ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ዕብ. 11:3) ታዲያ ተስፋችን እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንደሆንን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ በተሰጠባቸው የማይታዩ ነገሮች እንደምናምን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በንግግራችንና በድርጊታችን ነው፤ አለዚያ እምነታችን የተሟላ አይሆንም።
(ዕብራውያን 11:6) በተጨማሪም ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።
‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ’
ይሖዋን ለማስደሰት ምን ማድረግ አለብን? ጳውሎስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ጽፏል። ጳውሎስ፣ ‘ያለ እምነት አምላክን ማስደሰት አስቸጋሪ ነው’ እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው የተናገረው ያለ እምነት አምላክን ማስደሰት እንደማይቻል ነው። በሌላ አነጋገር፣ አምላክን ለማስደሰት እምነት በጣም ወሳኝ ነገር ነው።
ይሖዋን የሚያስደስተው ምን ዓይነት እምነት ነው? በአምላክ ላይ ያለን እምነት ሁለት ነገሮችን ያካተተ መሆን አለበት። አንደኛ፣ ‘እሱ መኖሩን ማመን አለብን።’ አምላክ መኖሩን የምንጠራጠር ከሆነ እሱን እንዴት ልናስደስተው እንችላለን? ይሁን እንጂ አጋንንትም እንኳ ይሖዋ መኖሩን ያምናሉ፤ በመሆኑም ትክክለኛ እምነት ካለን ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠበቅብናል። (ያዕቆብ 2:19) አምላክ እውን እንደሆነ ያለን እምነት ለተግባር ሊያንቀሳቅሰን ይኸውም አኗኗራችን እሱን የሚያስደስት እንዲሆን በማድረግ እምነታችንን በተግባር እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይገባል።—ያዕቆብ 2:20, 26
ሁለተኛ፣ አምላክ “ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን [ይኖርብናል]።” እውነተኛ እምነት ያለው ሰው፣ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር የሚያደርገው ጥረት ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር ፈጽሞ አይጠራጠርም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይሖዋ ለእኛ ወሮታ ለመክፈል ችሎታው ወይም ፍላጎቱ ያለው መሆኑን የምንጠራጠር ከሆነ እሱን እንዴት ልናስደስተው እንችላለን? (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ ስለ እኛ እንደማያስብ፣ የምናደርገውን ጥረት እንደማያደንቅ እንዲሁም ለጋስ እንዳልሆነ የሚያስብ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አምላክ አያውቀውም።
ይሖዋ ወሮታ የሚከፍለው ለእነማን ነው? “ከልብ ለሚፈልጉት” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “ከልብ ለሚፈልጉት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ስለ አምላክ ለማወቅ ጥረት ማድረግን ብቻ ሳይሆን እሱን ለማምለክ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድንም ያመለክታል። አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ደግሞ ይህ የግሪክኛ ግስ የገባበት መንገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን እንደሚያመለክት ይገልጻል። አዎን፣ ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ለሚያሳድሩና በዚህም የተነሳ ከልብ በመነጨ ፍቅር እና ቅንዓት ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሰዎች ወሮታ ይከፍላል።—ማቴዎስ 22:37
(ዕብራውያን 11:33-38) እነዚህ ሰዎች በእምነት መንግሥታትን ድል አድርገዋል፤ ጽድቅን አስፍነዋል፤ የተስፋን ቃል ተቀብለዋል፤ የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል፤ 34 የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል፤ ከሰይፍ ስለት አምልጠዋል፤ ደካማ የነበሩት ብርታት አግኝተዋል፤ በጦርነት ኃያላን ሆነዋል፤ ወራሪ ሠራዊትን አባረዋል። 35 ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀብለዋል፤ ሌሎች ወንዶች ግን ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን ስላልፈለጉ ከባድ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፤ ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው። 36 አዎ፣ ሌሎች ደግሞ መዘባበቻ በመሆንና በመገረፍ ይባስ ብሎም በመታሰርና ወህኒ ቤት በመጣል ፈተና ደርሶባቸዋል። 37 በድንጋይ ተወግረዋል፤ ተፈትነዋል፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀዋል፤ በሰይፍ ተቀልተዋል፤ እየተቸገሩ፣ መከራ እየተቀበሉና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ተንከራተዋል፤ 38 ዓለም እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሚገቡት ሆኖ አልተገኘም። በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።
በተስፋችሁ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ
10 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በስም ያልተጠቀሱ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በጽናት የተወጧቸውን መከራዎች ዘርዝሯል። ለአብነት ያህል፣ ሐዋርያው ልጆቻቸውን በሞት ስላጡና በኋላም በትንሣኤ ስለተቀበሉ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶች ጠቅሷል። በተጨማሪም “ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን ስላልፈለጉ” ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ገልጿል፤ እነዚህ ሰዎች “ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው።” (ዕብ. 11:35) ጳውሎስ ይህን የተናገረው እነማንን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባንችልም አምላክን በመታዘዛቸውና የእሱን ፈቃድ በመፈጸማቸው በድንጋይ ተወግረው ስለሞቱት ስለ ናቡቴ እና ስለ ዘካርያስ መናገሩ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 21:3, 15፤ 2 ዜና 24:20, 21) ዳንኤልና ጓደኞቹም ንጹሕ አቋማቸውን ቢያላሉ “ነፃ መሆን” የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው። እነዚህ ወጣቶች በአምላክ ኃይል ላይ እምነት ስለነበራቸው “የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል” እንዲሁም “የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል” ሊባልላቸው ችሏል።—ዕብ. 11:33, 34፤ ዳን. 3:16-18, 20, 28፤ 6:13, 16, 21-23
11 እንደ ሚካያህ እና ኤርምያስ ያሉት ነቢያት ‘መዘባበቻ በመሆንና ወህኒ ቤት በመጣል ፈተና ቢደርስባቸውም’ እምነት ስለነበራቸው ተቋቁመውታል። እንደ ኤልያስ ያሉ ሌሎች ደግሞ “በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።” ሁሉም መጽናት የቻሉት “ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት [ይጠብቁ]” ስለነበር ነው።—ዕብ. 11:1, 36-38፤ 1 ነገ. 18:13፤ 22:24-27፤ ኤር. 20:1, 2፤ 28:10, 11፤ 32:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 11:4) አቤል፣ ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ለአምላክ በእምነት አቀረበ፤ አምላክ ስጦታውን ስለተቀበለ በዚህ እምነቱ የተነሳ ጻድቅ እንደሆነ ተመሥክሮለታል፤ ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካኝነት አሁንም ይናገራል።
it-1 804 አን. 5
እምነት
በጥንት ዘመን የኖሩ የእምነት ምሳሌዎች። ጳውሎስ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” በማለት የጠቀሳቸው ሰዎች በሙሉ (ዕብ 12:1) እምነታቸው ጠንካራ መሠረት ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ አቤል ‘የእባቡን’ ራስ ስለሚቀጠቅጠው “ዘር” አምላክ የሰጠውን ተስፋ ያውቅ እንደነበር ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ይሖዋ በኤደን ውስጥ በወላጆቹ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ መፈጸሙን የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎችን ተመልክቷል። ምድር ስለተረገመች እሾህና አሜኬላ ታበቅል ነበር፤ በመሆኑም ከኤደን ውጭ ይኖሩ የነበሩት አዳምና ቤተሰቡ ምግብ የሚያገኙት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ነበር። አቤል የሔዋን ምኞት ሁሉ ባሏ እንደነበረና አዳምም ይገዛት እንደነበር ሳያስተውል አልቀረም። እንዲሁም እናቱ በእርግዝናዋ ወቅት ስለተሰማት ሕመም ተናግራ መሆን አለበት። በተጨማሪም የኤደን የአትክልት ስፍራ መግቢያ በኪሩቤልና ያለማቋረጥ በሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ ይጠበቅ ነበር። (ዘፍ 3:14-19, 24) ይህ ሁሉ ነገር አቤል ‘ተስፋ በተገባለት ዘር’ አማካኝነት መዳን እንደሚመጣ እርግጠኛ እንዲሆን የሚያደርግ “ተጨባጭ ማስረጃ” ሆኖለታል። በዚህም ምክንያት ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው “መሥዋዕት ለአምላክ” በእምነት አቅርቧል።—ዕብ 11:1, 4
(ዕብራውያን 11:5) ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ፤ አምላክ ወደ ሌላ ቦታ ስለወሰደውም የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም፤ ከመወሰዱ በፊት አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበርና።
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
ታዲያ ሄኖክ “ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” የተባለው ከምን አንጻር ነው? ሄኖክ በጠላቶቹ እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳይገደል ይሖዋ ታድጎት መሆን አለበት፤ በዚህ መንገድ ሳይሠቃይ በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ ወስዶታል ሊባል ይችላል። ከመወሰዱ በፊት ግን “አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበር።” እንዴት? ልክ ከመሞቱ በፊት፣ አምላክ ገነት የሆነችውን ምድር በራእይ አሳይቶት ሊሆን ይችላል። ሄኖክ በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዳገኘ የሚያሳየውን ይህን ግልጽ ምልክት ካየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሄኖክን ጨምሮ ስለ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሲናገር “እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ” ብሏል። (ዕብራውያን 11:13) ከዚያ በኋላ ጠላቶቹ አስከሬኑን ለመፈለግ ሞክረው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የሄኖክ አስከሬን “የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም”፤ ይህ የሆነው ይሖዋ እነዚህ ሰዎች አስከሬኑን እንዳያረክሱት ወይም የሐሰት አምልኮን ለማራመድ እንዳይጠቀሙበት ለማገድ ሲል ስለሰወረው ሊሆን ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከመስከረም 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 12-13
“ተግሣጽ—የይሖዋ ፍቅር መግለጫ”
(ዕብራውያን 12:5) ደግሞም ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን የተሰጣችሁን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት፤ በሚያርምህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤
‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ
18 ሥቃይ ያስከተለብን ምክር። ከዚህ በፊት የተሰጡንን አንዳንድ ምክሮች እያስታወስን የምንበሳጭ ቢሆንስ? እንዲህ ማድረጋችን ሥቃይ የሚያስከትልብን ከመሆኑም በላይ ቀስ በቀስ ኃይላችንን በማዳከም ‘እንድንታክት’ ሊያደርገን ይችላል። (ዕብ. 12:5) ምክሩን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን ‘ብናቃልለው’ አሊያም መጀመሪያ ላይ ተቀብለን በኋላ ችላ በማለት ‘ብንታክት’ ዞሮ ዞሮ ለውጥ የለውም፤ ሁለቱም ቢሆኑ ከምክሩ ጥቅም ለማግኘትም ሆነ ለመሻሻል ፈቃደኞች እንዳልሆንን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው። ሰለሞን “ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ መከተል ምንኛ የተሻለ ነው። (ምሳሌ 4:13) የመንገድ ምልክቶችን በማክበር እንደሚጓዝ አሽከርካሪ አንተም ምክርን ተቀብለህ ተግባራዊ በማድረግ ወደፊት መጓዝህን ቀጥል።—ምሳሌ 4:26, 27፤ ዕብራውያን 12:12, 13ን አንብብ።
(ዕብራውያን 12:6, 7) ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል።” 7 ተግሣጽ የምትቀበሉበት አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ መከራ ሲደርስባችሁ መጽናት ያስፈልጋችኋል። አምላክ የያዛችሁ እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው። ለመሆኑ አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?
“በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ’”
አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ ሲያድጉ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚሆኑ ስለሚያሳስበው ተግሣጽ ይሰጣቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) እንዲህ ዓይነቱ አባት ጥብቅ ሊሆን ቢችልም ልጆቹን በጭካኔ አይቀጣም። በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባታችን አንዳንድ ጊዜ እኛን መገሠጽ አስፈላጊ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ምንጊዜም ተግሣጽ የሚሰጠው በፍቅር ተነሳስቶ ሲሆን ተግሣጹም ቢሆን በፍጹም የሚያስመርር አይደለም። ኢየሱስም በዚህ ረገድ የአባቱን ዓይነት ባሕርይ አሳይቷል፤ ደቀ መዛሙርቱ ለሰጣቸው እርማት ፈጣን ምላሽ ባልሰጡበት ወቅትም ቢሆን ተግሣጽ የሰጣቸው በደግነት ነው።—ማቴዎስ 20:20-28፤ ሉቃስ 22:24-30
(ዕብራውያን 12:11) እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያስደስት አይመስልም፤ ይልቁንም ያስከፋል፤ በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል።
“ተግሣጽን ስሙ፤ ጥበበኞችም ሁኑ”
18 ተግሣጽ ሕመም ሊያስከትል ቢችልም ከዚያ የከፋ ሕመም ሊያስከትልብን የሚችለው ተግሣጹን አለመቀበላችን ነው። (ዕብ. 12:11) የቃየንንና የንጉሥ ሴዴቅያስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ቃየን አቤልን ወደ መግደል ሊያመራ የሚችል ጥላቻ በውስጡ እያቆጠቆጠ በነበረበት ወቅት አምላክ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶት ነበር፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ? መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?” (ዘፍ. 4:6, 7) ቃየን ግን አልሰማም። በመሆኑም ኃጢአት ተቆጣጠረው። በዚህም የተነሳ ቃየን አላስፈላጊ ሕመምና ሥቃይ በራሱ ላይ አመጣ! (ዘፍ. 4:11, 12) ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ የሚያስከትልበት ሕመም ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ምንኛ የተሻለ ነበር!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 12:1) እንግዲያው እንዲህ ያለ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ፤
ሩጫውን በጽናት ሩጡ
11 “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” የተባሉት ውድድሩን ለማየት አሊያም የሚወዱት ሯጭ ወይም ቡድን ሲያሸንፍ ለመመልከት ብቻ የተሰበሰቡ ተመልካቾች ወይም ደጋፊዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ራሳቸው በውድድሩ የሚሳተፉ ሯጮች ናቸው። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ሩጫውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀዋል። አሁን በሕይወት ባይኖሩም አዲስ ተወዳዳሪዎችን ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ልምድ ያላቸው ሯጮች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። አንድ አዲስ ሯጭ ታዋቂ የሆኑ ሯጮች በዙሪያው እንዳሉ ወይም እየተመለከቱት እንደሆነ ቢያውቅ ምን ሊሰማው እንደሚችል ገምት። አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ እንዲያውም ከሌላው ጊዜ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አይነሳሳም? እነዚህ የጥንት ምሥክሮች እንዲህ ያለው ምሳሌያዊ ውድድር ምንም ያህል አድካሚ ቢሆን ማሸነፍ እንደሚቻል ማስረጃ ናቸው። በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የዕብራውያን ክርስቲያኖች፣ “የምሥክሮች ደመና” የተባሉት የጥንት የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን ምሳሌ በአእምሯቸው መያዛቸው ደፋሮች እንዲሆኑና ‘ሩጫውን በጽናት እንዲሮጡ’ ይረዳቸዋል፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።
(ዕብራውያን 13:9) በልዩ ልዩና እንግዳ በሆኑ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን በምግብ ሳይሆን በአምላክ ጸጋ ቢጠናከር መልካም ነውና፤ በዚህ የተጠመዱ ምንም አልተጠቀሙም።
w89 12/15 22 አን. 10
ይሖዋን የሚያስደስቱ መሥዋዕቶች አቅርቡ
10 ስለዚህ ዕብራውያን የይሁዲነት እምነት ጠበቆች በሚያስፋፉት የተለያየ እንግዳ ትምህርት ከመወሰድ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 5:1-6) ልባቸው ጠንክሮና በእውነት ጸንቶ ሊቆም የሚችለው እንደዚህ ባሉት ትምህርቶች ሳይሆን በአምላክ የጸጋ ቸርነት ነው። ጳውሎስ ‘ልብ ጸንቶ የሚቆመው በመብል አይደለም’ ስላለ ስለመብልና ስለመሥዋዕት የሚከራከሩ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው። ‘በእነዚህ ነገሮች የተጠመዱት ግን አልተጠቀሙበትም።’ መንፈሳዊ ጥቅም የሚገኘው ለአምላክ በማደርና የቤዛውን ጥቅም ተረድቶ በመኖር ነው እንጂ አንዳንድ ምግቦችን ስለመብላትና ስላለመብላት ወይም አንዳንድ ቀኖችን ስለማክበር ከሚገባው በላይ በመጨነቅ አይደለም። (ሮሜ 14:5-9) ከዚህም በላይ የክርስቶስ መሥዋዕት ሌዋዊውን መሥዋዕት ዋጋ ቢስ አድርጎታል።—ዕብራውያን 9:9-14፤ 10:5-10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
it-1 629
ይሖዋ በአገልጋዮቹ ላይ ስደት እንዲደርስ ሲፈቅድ ሁኔታው ተግሣጽ ወይም ሥልጠና ሊሆን ይችላል፤ እንዲህ ያለው ሥልጠና መጨረሻ ላይ፣ ተፈላጊ የሆነውን የጽድቅ ሰላማዊ ፍሬ ለማፍራት ያስችላል። (ዕብ 12:4-11) የአምላክ ልጅም እንኳ ሩኅሩኅና የሰው ስሜት የሚገባው ሊቀ ካህናት ሊሆን የቻለው አባቱ መከራ እንዲደርስበት ስለፈቀደ ነው።—ዕብ 4:15
ከመስከረም 30–ጥቅምት 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ያዕቆብ 1-2
“ወደ ኃጢአትና ወደ ሞት የሚመራው መንገድ”
(ያዕቆብ 1:14) ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።
ፈተና
ማንኛውም ሰው አንድን ነገር በተለይ ደግሞ ስህተት የሆነን ነገር ለማድረግ ከጓጓ መፈተኑ አይቀርም። ለምሳሌ በአንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ስትዘዋወር አንድ የምትፈልገው ነገር አየህ እንበል። ማንም ሳያይህ ዕቃውን ሰርቀህ ልትወስደው እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ሕሊናህ ይህን ማድረግ እንደሌለብህ ይነግርሃል። በመሆኑም ሐሳብህን ቀይረህ መንገድህን ትቀጥላለህ። እንዲህ ማድረግህ ፈተናውን እንዳሸነፍክ ያሳያል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አንድ ነገር ለማድረግ መፈተንህ በራሱ መጥፎ ሰው እንደሆንክ የሚያሳይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ፈተና እንደሚያጋጥመን ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ዋናው ነገር በምንፈተንበት ጊዜ የምንወስደው እርምጃ ነው። አንዳንዶች በውስጣቸው ያደረውን መጥፎ ምኞት ለማስወገድ ጥረት ስለማያደርጉ ውሎ አድሮ በፈተና ይሸነፋሉ። ሌሎች ግን እንዲህ ያለውን ምኞት ወዲያውኑ ከአእምሮአቸው ያወጡታል።
“እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።”—ያዕቆብ 1:14
(ያዕቆብ 1:15) ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል።
ፈተና
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ መጥፎ ድርጊት የሚመሩትን እርምጃዎች ይናገራል። ያዕቆብ 1:15 “[መጥፎ] ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች” ይላል። በሌላ አባባል አንዲት የፀነሰች ሴት መውለዷ እንደማይቀር ሁሉ በልባችን ውስጥ ያደረውን መጥፎ ምኞት ለማስወገድ ጥረት የማናደርግ ከሆነ ኃጢአት መሥራታችን አይቀርም። ይሁን እንጂ መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠር እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ለእነዚህ ምኞቶች ባሪያ አንሆንም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ያዕቆብ 1:17) መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።
it-2 253-254
ብርሃን
ይሖዋ ‘የሰማይ ብርሃናት አባት’ ነው። (ያዕ 1:17) “በቀን እንድታበራ ፀሐይን የሰጠው፣ በሌሊትም እንዲያበሩ የጨረቃንና የከዋክብትን ሕጎች ያወጣው” እሱ ነው (ኤር 31:35)፤ በተጨማሪም የመንፈሳዊ እውቀት ብርሃን ሁሉ ምንጭ ነው። (2ቆሮ 4:6) ሕጉ፣ የፍትሕ እርምጃውና ቃሉ ለሚመሩባቸው ሰዎች ብርሃን ናቸው። (መዝ 43:3፤ 119:105፤ ምሳሌ 6:23፤ ኢሳ 51:4) መዝሙራዊው “በብርሃንህ፣ ብርሃን ማየት እንችላለን” በማለት ተናግሯል። (መዝ 36:9፤ ከመዝ 27:1 እና 43:3 ጋር አወዳድር) የፀሐይ ብርሃን ከማለዳ ተነስቶ “እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራ” ድረስ እየደመቀ እንደሚሄድ ሁሉ የጻድቃን መንገድም የአምላክ ጥበብ በሚሰጠው ብርሃን እየደመቀ ይሄዳል። (ምሳሌ 4:18) የይሖዋን መንገድ ከተከተልን በብርሃኑ እንሄዳለን። (ኢሳ 2:3-5) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ነገሮችን የሚያየው ንጹሕ ባልሆነ መንገድ ወይም በክፋት ከሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው። ኢየሱስ ይህን ጉዳይ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ዓይንህ ምቀኛ ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን!”—ማቴ 6:23፤ ከዘዳ 15:9 እና 28:54-57 ጋር አወዳድር፤ ምሳሌ 28:22፤ 2ጴጥ 2:14
(ያዕቆብ 2:8) እንግዲያው በቅዱስ መጽሐፉ መሠረት “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ መልካም እያደረጋችሁ ነው።
it-2 222 አን. 4
ሕግ
“ንጉሣዊ ሕግ።” አንድ ንጉሥ ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ሁሉ ‘ንጉሣዊው ሕግም’ በሰው ልጆች መካከል ሊኖር ከሚገባው ግንኙነት ጋር በተያያዘ ከተሰጡ ሌሎች ሕጎች ይበልጥ አስፈላጊና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። (ያዕ 2:8) የሕጉ ቃል ኪዳን ዋነኛ ጭብጥ ፍቅር ነበር፤ እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” (ንጉሣዊው ሕግ) የሚለው ትእዛዝ መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል ከተመሠረቱባቸው ትእዛዛት መካከል ሁለተኛው ነው። (ማቴ 22:37-40) ክርስቲያኖች በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ባይሆኑም በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት በንጉሡ በይሖዋ እና ንጉሥ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕግ ሥር ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ