በአምላክ ፊት ውድ ናችሁ!
“በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት [“በፍቅራዊ ደግነት” አዓት]ሳብሁሽ።”—ኤርምያስ 31:3
1. ኢየሱስ በእሱ ዘመን ለነበሩት ተራ ሰዎች የነበረው አመለካከት ፈሪሳውያን ለእነዚህ ሰዎች ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?
ይህን ከፊቱ ማንበብ ይችሉ ነበር። ይህ ሰው ማለትም ኢየሱስ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው ፈጽሞ የተለየ ነበር፤ በጣም ያስብላቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና” አዝኖላቸዋል። (ማቴዎስ 9:36) የሃይማኖት መሪዎቻቸው አፍቃሪና መሐሪ አምላክን የሚወክሉ አፍቃሪ እረኞች መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። ተራውን ሕዝብ እንደ አልባሌ አድርገው በመመልከት ይንቁት ነበር፤ እንዲሁም ርጉም አድርገው ይመለከቱት ነበር!a (ዮሐንስ 7:47–49፤ ከሕዝቅኤል 34:4 ጋር አወዳድር።) ይህ የተዛባና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው አመለካከት ይሖዋ ለሕዝቡ ካለው አመለካከት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነበር። ይሖዋ ሕዝቡን እስራኤልን “በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ” ብሏል።—ኤርምያስ 31:3
2. የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ኢዮብ በአምላክ ፊት ምንም ዋጋ እንደሌለው ለማሳመን የሞከሩት እንዴት ነበር?
2 ይሁን እንጂ የይሖዋ ውድ በጎች ምንም ዋጋ የለኝም የሚል እምነት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ሙከራ ያደረጉት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ፈሪሳውያን አልነበሩም። የኢዮብን ሁኔታ ተመልከት። ኢዮብ በይሖዋ ፊት ጻድቅና እንከን የለሽ ነበር፤ ሦስቱ “አጽናኞች” ግን ኢዮብ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን የሚጠቁም አሻራ እንኳ ሳይተው ደብዛው የሚጠፋ ሥነ ምግባር የጎደለው ክፉ ከሃዲ እንደሆነ አድርገው በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግረዋል። አምላክ ሌላው ቀርቶ የራሱን መላእክት እንኳ ስለማያምንና ሰማይን ራሱን ንጹሕ እንዳልሆነ አድርጎ ስለሚመለከት ኢዮብ የሠራውን ማንኛውንም ጽድቅ አምላክ ግምት ውስጥ እንደማያስገባው ተናግረዋል።—ኢዮብ 1:8፤ 4:18፤ 15:15, 16፤ 18:17–19፤ 22:3
3. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ሰዎች ምንም ዋጋ የለኝም፤ የሚወደኝም የለም የሚል እምነት እንዲያድርባቸው ለማድረግ የሚጠቀምበት ዘዴ ምንድን ነው?
3 በዛሬውም ጊዜ ሰይጣን ይህን ‘የተንኮል ዘዴ’ በመጠቀም ሰዎች የሚወዳቸው እንደሌለና ምንም ዋጋ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ በመሞከር ላይ ይገኛል። (ኤፌሶን 6:11 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) እውነት ነው፣ ሰይጣን ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ለክብራቸው የቆመ መስሎ በመቅረብ ያታልላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ይሁን እንጂ በቀላሉ ስሜታቸው ሊጎዳ የሚችል ሰዎች ለራሳቸው አቋም ያላቸውን ጥሩ ግምት እንዲያጡ በማድረግም ይደሰታል። ይህ ነገር በተለይ በእነዚህ አደገኛ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ እየተፈጸመ ያለ ነገር ነው። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ‘ፍቅር በሌላቸው’ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ናቸው፤ ብዙዎች በየዕለቱ ጨካኞች፣ ራስ ወዳዶችና እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉ ሰዎችን ባሕርይ መቋቋም አስፈልጓቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) እንዲህ ያሉ ሰዎች ለዓመታት የተፈጸመባቸው ጭካኔያዊ ተግባር፣ ዘረኝነት፣ ጥላቻ ወይም ግፍ ምንም ዋጋ የሌለኝ ሰው ነኝ፣ አንድም የሚወደኝ ሰው የለም የሚል እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለማንም ሰው ፍቅር የለኝም፤ የሚወደኝ አለ የሚል ስሜትም የለኝም። አምላክ ስለ እኔ ምንም ደንታ ያለው አይመስለኝም።”
4, 5. (ሀ) ምንም ዋጋ የለኝም የሚለው ሐሳብ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚጋጨው ለምንድን ነው? (ለ) የምናደርጋቸው ጥረቶች በሙሉ ምንም ዋጋ የላቸውም ብለን ማሰባችን የሚያስከትለው አንዱ አደገኛ መዘዝ ምንድን ነው?
4 ምንም ዋጋ የለኝም የሚለው ሐሳብ የአምላክ ቃል እውነት የሆነውን የቤዛውን ትምህርት በቀጥታ የሚነካ ነው። (ዮሐንስ 3:16) አምላክ ለዘላለም መኖር የምንችልበትን አጋጣሚ ለመስጠት ሲል የገዛ ራሱን ልጅ ውድ ሕይወት አሳልፎ በመስጠት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው በእርግጥም ቢወደን መሆን አለበት፤ በእርግጥም በእርሱ ፊት ዋጋ አለን ማለት ነው!
5 ከዚህም በላይ አምላክን እያሳዘንኩት ነው፣ የማደርገው ማንኛውም ጥረት ምንም ዋጋ የለውም ብሎ ማሰብ ምንኛ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው! (ከምሳሌ 24:10 ጋር አወዳድር።) ይህ አፍራሽ አመለካከት ካለ ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት ባለን አጋጣሚ ሁሉ እንድናሰፋው ታስቦ የሚሰጠን ጠቃሚ ማበረታቻ ለአንዳንዶች እንደ ነቀፋ ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። የማደርገው ነገር ሁሉ በቂ አይደለም የሚለውን የራሳችንን ውስጣዊ ስሜት መልሶ ማስተጋባት ሊመስል ይችላል።
6. ስለ ራሳችን እጅግ አፍራሽ የሆኑ ሐሳቦችን እንዳንይዝ መከላከል የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው ነገር ምንድን ነው?
6 እንዲህ ዓይነት አፍራሽ ስሜቶች የሚሰሙህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ብዙዎቻችን አንዳንድ ጊዜ አለምክንያት ራሳችንን እንኮንናለን። የአምላክ ቃል ‘ልብን ለማቅናት’ እና “ምሽግን ለመስበር” እንደሚያገለግል አስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፣ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፣ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።” (1 ዮሐንስ 3:19, 20) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ፊት ውድ መሆናችንን የሚያስተምርባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣችኋል
7. ኢየሱስ ሁሉንም ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ስላላቸው ከፍ ያለ ዋጋ ያስተማረው እንዴት ነው?
7 በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዳችን በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለን በቀጥታ ያስተምራል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።” (ሉቃስ 12:6, 7) በዚያ ዘመን ለምግብነት ከሚሸጡት ወፎች ሁሉ በርካሽ ዋጋ ይሸጡ የነበሩት ድንቢጦች ነበሩ፤ ሆኖም አንዷም ብትሆን በፈጣሪዋ ዘንድ እንደ አልባሌ አትታይም ነበር። በዚህ መንገድ በጥሩ ሁኔታ ለማነጻጸር የሚያስችል መሠረት ተጥሏል። ከድንቢጦች እጅግ በጣም የላቀ ዋጋ ያላቸውን ሰዎች በተመለከተ አምላክ እያንዳንዷን ነገር በዝርዝር ያውቃል። የራሳችን ፀጉር አንድ በአንድ የተቆጠረ ያህል ነው ማለት ይቻላል!
8. ይሖዋ የራሳችንን ፀጉር መቁጠር ይችላል ብሎ ማሰቡ ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?
8 ፀጉራችን ደግሞ ይቆጠራል እንዴ? ይህ የኢየሱስ ምሳሌ ትክክለኛነቱ ካጠራጠረህ የሚከተለውን ነገር አስታውስ፦ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ወደ ቀጣይ ዘሮች የሚተላለፉትን ሁለንተናዊ ባሕርያት የሚወስነውን ውስብስብ ንድፍና በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ያሳለፏቸውን ተሞክሮዎችና ያሏቸውን ትዝታዎች ጨምሮ ቀድሞ የነበራቸውን እያንዳንዱን ነገር መልሶ በመስጠት እንደገና ወደ ሕይወት ለማምጣት እስኪችል ድረስ በደንብ ያስታውሳቸዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ፀጉራችንን (በአማካይ ወደ 100,000 የሚጠጉትን የራስ ፀጉሮች) መቁጠር ቀላል ነገር ነው!—ሉቃስ 20:37, 38
ይሖዋ እንዴት አድርጎ ይመለከተናል?
9. (ሀ) ይሖዋ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ ባሕርያት ምንድን ናቸው? (ለ) እነዚህን የመሰሉ ባሕርያት በእርሱ ዘንድ ውድ ናቸው ብለህ እንድታስብ ያደረገህ ምንድን ነው?
9 በሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ እንዴት አድርጎ እንደሚመለከተን ያስተምረናል። በአጭሩ ባሉን በጎ ባሕርያትና በምናደርጋቸው ጥረቶች ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃል” ብሎታል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) አምላክ በዚህ ዓመፀኛና ጥላቻ በሞላበት ዓለም ውስጥ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ በሚመረምርበት ጊዜ ሰላምን፣ እውነትንና ጽድቅን የሚወድ ልብ ሲያገኝ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ከዮሐንስ 1:47ና ከ1 ጴጥሮስ 3:4 ጋር አወዳድር።) አምላክ እሱን የሚወድ እንዲሁም ስለ እርሱ ለመማርና እንዲህ ዓይነቱን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል የሚፈልግ ልብ ሲያገኝ ምን ያደርጋል? በሚልክያስ 3:16 ላይ ይሖዋ ስለ እርሱ ከሌሎች ጋር የሚነጋገሩትን ሰዎች እንደሚሰማና አልፎ ተርፎም “እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ” ሁሉ ያዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” እንዳለ ይነግረናል። እነዚህን የመሰሉ ባሕርያት በእርሱ ፊት ውድ ናቸው!
10, 11. (ሀ) አንዳንዶች ለሚያሳዩአቸው ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ይሖዋ ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ የሚያሳየውን ማስረጃ ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርጉት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ መጠኑ ይብዛም ይነስ ለሁሉም ጥሩ ባሕርያት ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ የአብያ ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው?
10 ራሱን የሚኮንን ልብ ግን በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለን የሚያሳየውን እንዲህ ያለውን ማስረጃ ላይቀበል ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ልብ በዚህ ጊዜም እንኳ ‘ግን እኮ በእነዚህ ባሕርያት ረገድ ከእኔ የበለጠ ምሳሌ የሚሆኑ ሌሎች ብዙ ሰዎች አሉ። ይሖዋ ከእነርሱ ጋር ሲያነጻጽረኝ ምንኛ ያዝንብኝ ይሆን!’ በማለት አሁንም አሁንም በውስጡ ሊናገር ይችላል። ይሖዋ አንዱን ከሌላው አያነጻጽርም፤ እንዲሁም ግትርና አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ካልተሠራ ከናካቴው ቢቀር ይሻላል የሚል አመለካከት ያለው አይደለም። (ገላትያ 6:4) ልብን በጥልቀት ይመረምራል፤ መጠኑ ምንም ይሁን ምን ለየትኛውም ጥሩ ባሕርይ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣል።
11 ለምሳሌ ያህል ይሖዋ የንጉሥ ኢዮርብዓም ከሀዲ ሥርወ መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንዲያከትምለትና ልክ እንደ “ፋንድያ” ተጠራርጎ እንዲጠፋ በወሰነ ጊዜ ከንጉሡ ልጆች መካከል አንዱ አብያ ብቻ በወግ በማዕረግ እንዲቀበር አዝዞ ነበር። ለምን? “በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ . . . በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታል።” (1 ነገሥት 14:10, 13) ይህ ማለት አብያ ታማኝ የይሖዋ አምላኪ ነበር ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም እንደ ሌሎቹ ክፉ የቤተሰቡ አባላት እርሱም ሞቷል። (ዘዳግም 24:16) ያም ሆኖ ግን ይሖዋ በአብያ ልብ ውስጥ የተመለከተውን “መልካም ነገር” ከፍ ያለ ግምት ሰጥቶታል፤ ከዚህም ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። ማቲው ሄንሪስ ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሆል ባይብል እንዲህ ይላል፦ “አንድ ጥሩ ባሕርይ መጠኑ የተወሰነ ቢሆንም እንኳ መገኘቱ አይቀርም፤ በእኛ ውስጥ ጥሩ ባሕርያትን ለማግኘት የሚፈልገው አምላክ ይመለከተዋል፤ መጠኑ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ይደሰትበታል።” አምላክ ሌላው ቀርቶ አንድ አነስተኛ መጠን ያለው ጥሩ ባሕርይ እንኳ ካገኘብህ እሱን በታማኝነት ለማገልገል ጥረት እስካደረግህ ድረስ ባሕርይውን ሊያሳድገው እንደሚችል አትርሳ።
12, 13. (ሀ) ይሖዋ ለምናደርጋቸው ጥረቶች ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ መዝሙር 139:3 የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የምንሠራቸውን ነገሮች ያበጥራል ማለት የሚቻለው ከምን አንጻር ነው?
12 ይሖዋ ጥረቶቻችንንም እንደዚሁ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣቸዋል። በመዝሙር 139:1–3 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “አቤቱ፣ መረመርኸኝ፣ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ።” ስለዚህ ይሖዋ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር ያውቃል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከማወቅም በላይ አልፎ ይሄዳል። በዕብራይስጥ “መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ” የሚለው ሀረግ “መንገዶቼን ሁሉ እንደ ውድ ሀብት አድርገህ ተመለከትካቸው” ወይም “መንገዶቼን ሁሉ ከፍ አድርገህ ተመለከትካቸው” የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል። (ከማቴዎስ 6:19, 20 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እኛ ፍጽምና የሌለን ኃጢአተኞች ሆነን ሳለን ይሖዋ መንገዶቻችንን እንደ ውድ ነገር ሊመለከታቸው የሚችለው እንዴት ነው?
13 የሚገርመው ነገር በአንዳንድ ምሁራን አባባል መሠረት ዳዊት ይሖዋ ፍለጋውንና ዕረፍቱን ‘እንደመረመረው’ ሲጽፍ የተጠቀመበት የዕብራይስጡ ቃል ቃል በቃል ሲተረጎም “መንፋት” ወይም “ማዝራት” ማለት ነው። አንድ የምርምር ሥነ ጽሑፍ የሚከተለውን አመልክቷል፦ “ገለባውን በሙሉ ማዝራትና እህሉን በሙሉ ማስቀረት ማለትም ዋጋ ያለውን ሁሉ ማስቀመጥ . . . ማለት ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ በምሳሌያዊ አነጋገር አምላክ ዳዊትን አበጥሮታል ማለት ነው። . . . ገለባ የሆነውን ወይም ዋጋ የሌለውን ሁሉ በተነው፤ እንዲሁም የቀረውን እውነተኛውንና ተጨባጩን ነገር ተመለከተ።” ራሱን የሚኮንን ልብ ሥራችንን በተቃራኒው መንገድ ሊያበጥረው ይችላል፤ ቀደም ሲል በሠራናቸው ኃጢአቶች ምክንያት ክፉኛ ሊኮንነንና የሠራናቸውን መልካም ነገሮች ሊያጣጥልብን ይችላል። ይሁን እንጂ ከልባችን ንስሐ ከገባንና ስህተቶቻችንን ላለመድገም ትጋት የተሞላበት ጥረት ካደረግን ይሖዋ ኃጢአቶቻችንን ይቅር ይለናል። (መዝሙር 103:10–14፤ ሥራ 3:19) ይሖዋ የሠራናቸውን ጥሩ ሥራዎች በደንብ መርምሮ ይለያል እንዲሁም ያስታውሳቸዋል። እንዲያውም ለእርሱ ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ እነዚህን መልካም ሥራዎች ለዘላለም ያስታውሳቸዋል። እነዚህን ነገሮች መርሳት እንደ ዓመፅ አድርጎ ይቆጥረዋል፤ እሱ ደግሞ ዓመፀኛ አይደለም!—ዕብራውያን 6:10
14. ይሖዋ በክርስቲያናዊ አገልግሎት የምናደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳየው ምንድን ነው?
14 አምላክ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጣቸው ጥሩ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል የምናደርገውን ነገር ሁሉ ያጠቃልላል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እንግዲያው አንዱ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሥራ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የማዳረሱ ሥራ ነው። በሮሜ 10:15 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው”! ምንም እንኳ እኛ እግሮቻችን “ያማሩ” ናቸው ብለን ባናስብም ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመው ቃል በግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም ላይ ርብቃን፣ ራሔልንና ዮሴፍን ለመግለጽ ከገባው ቃል ጋር አንድ ነው፤ ሦስቱም በውበታቸው የታወቁ ነበሩ። (ዘፍጥረት 26:7፤ 29:17፤ 39:6) ስለዚህ በአምላካችን በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ በእርሱ ፊት በጣም ያማረና ውድ ነገር ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
15, 16. ይሖዋ ለጽናታችን ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ለምንድን ነው? በመዝሙር 56:8 ( አዓት) ላይ ያሉት የዳዊት ቃላት ይህን ሐቅ ጠበቅ አድርገው የሚገልጹትስ እን ዴት ነው?
15 አምላክ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ሌላው ባሕርይ ጽናታችን ነው። (ማቴዎስ 24:13) ሰይጣን ለይሖዋ ጀርባህን እንድትሰጥ እንደሚፈልግ አስታውስ። ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ የምትውልበት እያንዳንዱ ቀን ሰይጣን ለሰነዘረው ነቀፋ መልስ ለመስጠት የሚያስችል አስተዋጽኦ የምታበረክትበት ተጨማሪ ቀን ነው። (ምሳሌ 27:11) አንዳንድ ጊዜ ጽናት ቀላል አይሆንም። የጤና እክሎች፣ ገንዘብ ነክ ችግሮች፣ የአእምሮ ጭንቀትና ሌሎች እንቅፋቶች እንያንዳንዱን ቀን ፈታኝ ሊያደርጉት ይችላሉ። በተለይ እነዚህን በመሰሉ ፈተናዎች ሥር መጽናት ለይሖዋ ውድ ነገር ነው። ንጉሥ ዳዊት “በመዝገብህ የሰፈሩ አይደሉምን?” ብሎ ሙሉ በሙሉ ተማምኖ በመጠየቅ እንባውን ይሖዋ በምሳሌያዊ “አቁማዳ” ውስጥ እንዲያከማችለት ጠይቋል። (መዝሙር 56:8 አዓት) አዎን፣ ይሖዋ ከእሱ ጎን ቆመን ታማኝነታችንን በመጠበቅ የምናፈሰውን እንባና ችለን የምናሳልፈውን መከራ ሁሉ እንደ ውድ ነገር ይቆጥረዋል፤ ያስታውሰዋልም። እነዚህም ነገሮች በእርሱ ፊት ውድ ናቸው።
16 ካሉን የተሻሉ መልካም ባሕርያትና ከምናደርጋቸው ጥረቶች አንጻር ስንመለከተው ይሖዋ ከፍ ያለ ግምት ሊሰጠው የሚችለው ብዙ ነገር በእያንዳንዳችን ላይ ሊያገኝ እንደሚችል ግልጽ ነው! የሰይጣን ዓለም በፈለገው መንገድ ቢመለከተን የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ ይሖዋ እንደ ውድ ነገርና ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠው ዕቃ’ ክፍል እንደሆንን አድርጎ ያየናል።—ሐጌ 2:7
ይሖዋ ፍቅሩን ለመግለጽ ያደረገው ነገር
17. የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ይሖዋና ኢየሱስ እኛን በግለሰብ ደረጃ ይወዱናል ብለን እንድናምን ሊያደርገን የሚገባው ለምንድን ነው?
17 በሦስተኛ ደረጃ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ይህ ነው የማይባል ነገር አድርጓል። የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሰይጣን እኛ ዋጋ እንደሌለን ወይም የሚወደን እንደሌለ አድርጎ ለተናገረው ቅጥፈት ከሁሉ የላቀ አፍ የሚያሲዝ መልስ ነው። ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት የደረሰበት ከፍተኛ ሥቃይና ከዚያ በበለጠ ደግሞ ይሖዋ የውድ ልጁን ሞት በመመልከት እንደ ምንም ችሎ ያሳለፈው ሥቃይ ለእኛ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይገባንም። ከዚህም በላይ ይህ ፍቅር ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ይሠራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የአምላክ ልጅ ወደደኝ፤ ስለ እኔም ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ’ ብሎ ስለጻፈ ነገሩን የተመለከተው በዚህ መንገድ ነበር።—ገላትያ 2:20
18. ይሖዋ ወደ ክርስቶስ ይስበናል የምንለው ከምን አን ጻር ነው?
18 ይሖዋ የክርስቶስ መሥዋዕት ካስገኛቸው ጥቅሞች ተቋዳሾች እንድንሆን እኛን በግለሰብ ደረጃ በመርዳት ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ኢየሱስ በዮሐንስ 6:44 ላይ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በሚደርሰን በስብከቱ ሥራና ውስን የሆነ አቅምና አለፍጽምና ቢኖርብንም እንኳ መንፈሳዊ እውነቶችን እንድንረዳና በሥራ ላይ እንድናውላቸው እኛን ለመርዳት በሚጠቀምበት ቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በግለሰብ ደረጃ ወደ ልጁና ወደ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ይስበናል። ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ በማለት ለእስራኤል የተናገረውን ለእኛም መናገር ይችላል፦ “በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት [“በፍቅራዊ ደግነት” አዓት] ሳብሁሽ።”—ኤርምያስ 31:3
19. የጸሎት መብት ይሖዋ ለእኛ ፍቅር እንዳለው ሊያሳምነን የሚገባው ለምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ በሚያቀራርብ ሁኔታ የይሖዋን ፍቅር የምንቀምሰው በጸሎት መብት መሆን አለበት። እያንዳንዳችን ‘ሳናቋርጥ ወደ እርሱ እንድንጸልይ’ ይጋብዘናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ጸሎታችንን ያዳምጣል! እንዲያውም ‘ጸሎት ሰሚ’ ተብሏል። (መዝሙር 65:2) ይህን ማዕረግ ለሌላ ለማንም ፍጡር ሌላው ቀርቶ ለራሱ ልጅ እንኳ አልሰጠም። እስቲ አስቡት፦ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የመናገር ነጻነት በመስጠት በጸሎት ወደ እርሱ እንድንቀርብ አጥብቆ ይመክረናል። ሌላው ቀርቶ የምታቀርባቸው ልመናዎች ይሖዋ እነዚህን ልመናዎች ባታቀርብ የማይፈጽመውን ነገር እንዲፈጽም ሊገፋፉት ይችላሉ።—ዕብራውያን 4:16፤ ያዕቆብ 5:16፤ ኢሳይያስ 38:1–16ን ተመልከት።
20. ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ወይም ራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን ለመመልከት ሰበብ ሊሆነን የማይችለው ለምንድን ነው?
20 ማንኛውም ሚዛናዊ የሆነ ክርስቲያን ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅርና አድናቆት የሚያሳየውን እንዲህ ያለ ማስረጃ ራሱን ከሚገባው በላይ ከፍ ከፍ አድርጎ ለመመልከት ሰበብ አድርጎ አይጠቀምበትም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።” (ሮሜ 12:3) ስለዚህ ምንም እንኳ በሰማያዊ አባታችን ፍቅር ብንደሰትም ጤናማ አእምሮ ይኑረን፤ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ደግሞ ይገባናል የማንለው እንደሆነ እናስታውስ።—ከሉቃስ 17:10 ጋር አወዳድር።
21. ያለማቋረጥ ልንከላከለው የሚገባን የትኛውን ሰይጣናዊ ውሸት ነው? ዘወትር ልናሰላስለው የሚገባንስ የትኛውን መለኮታዊ እውነት ነው?
21 ሰይጣን ወደ ጥፋት በተቃረበው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ እያስፋፋቸው ያሉትን ሐሳቦች በሙሉ ለመቋቋም እያንዳንዳችን የምንችለውን ሁሉ ጥረት እናድርግ። ይህም ዋጋ የለኝም ወይም የሚወደኝ የለም የሚለውን ሐሳብ ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግን ይጨምራል። የዚህ ሥርዓት ኑሮ የአምላክ የጠለቀ ፍቅር እንኳ ችግሮችህን እንድትቋቋም ሊረዳህ እንደማይችል እስኪሰማህ ድረስ ምን ጊዜም እንቅፋት እንደማያጣህ አድርገህ በማሰብ በጣም ተስፋ እንድትቆርጥ ወይም ሁሉንም ነገር ማየት የሚችሉት የአምላክ ዓይኖች እንኳ ልብ ሊሏቸው እንደማይችሉ እስኪሰማህ ድረስ የሠራሃቸው ጥሩ ሥራዎች ከቁብ የማይቆጠሩ እንደሆኑ አድርገህ እንድትመለከታቸው አለዚያም ደግሞ ኃጢአቶችህ የአምላክ ውድ ልጅ ሞት ሊሸፍናቸው እንደማይችል እስኪሰማህ ድረስ በጣም ብዙ እንደሆኑ አድርገህ እንድትመለከታቸው አድርጎህ ከሆነ ተሳስተሃል። እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ አመለካከቶች አንቅረህ ትፋቸው! ምንጊዜም በሮሜ 8:38, 39 ላይ የሚገኙትን ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸውን ቃላት በአእምሯችን ማኅደር ውስጥ እናኑራቸው፦ “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንዲያውም “አምሃሬትስ” ወይም “የምድር ሰዎች” በሚል የንቀት መጠሪያ በመጠቀም ድሀዎቹን ሰዎች አጣጥለዋቸው ነበር። አንድ ምሁር እንዳሉት ከሆነ ፈሪሳውያን አንድ ሰው ለእነዚህ ሰዎች ውድ የሆኑ ነገሮችን አምኖ ሊሰጣቸው፣ የምሥክርነት ቃላቸውን ሊያምን፣ በእንግድነት ሊያስተናግዳቸው፣ የእነርሱ እንግዳ ሆኖ ሊስተናገድ ወይም ሌላው ቀርቶ ከእነርሱ ሊገዛ አይገባውም ሲሉ አስተምረዋል። ሃይማኖታዊ መሪዎቹ አንድ ሰው ሴት ልጁን ከእነዚህ ሰዎች ለአንዱ መዳር ማለት ሁለት እጆቿን ጠፍሮ ለአውሬ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው ብለው ይናገሩ ነበር።
ምን ይመስልሃል?
◻ ሰይጣን ምንም ዋጋ የለኝም የሚወደኝም የለም የሚል እምነት እንዲያድርብን ለማድረግ የሚሞክረው ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጠን ኢየሱስ ያስተማረው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ጥሩ ጥሩ ባሕሪዎቻችንን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እንዴት እናውቃለን?
◻ ይሖዋ ጥረቶቻችንን እንደ ውድ ነገር እንደሚቆጥራቸው እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ስሙን የሚያስቡትን ሰዎች ይመለከታል፤ እንዲሁም ያስታውሳቸዋል