ሰው ሁሉ የይሖዋን ክብር ያውጅ
“ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ።”—መዝሙር 96:7, 8
1, 2. ይሖዋን እያወደሱ ያሉት እንዲሁም በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ ማበረታቻ የተሰጣቸው እነማን ናቸው?
የእሴይ ልጅ ዳዊት ያደገው በቤተ ልሔም አካባቢ እረኛ ሆኖ ነበር። ፀጥ እረጭ ባለ ምሽት የአባቱን መንጎች ሲጠብቅ በከዋክብት የተሞላውን የተንጣለለ ሰማይ በመመልከት ብዙ ጊዜ ሳይደመም አልቀረም! በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አነሳሽነት በ19ኛው መዝሙር ላይ የሚገኙትን ግሩም ቃላት ባቀናበረበትና በዘመረበት ወቅት ይህ አስደናቂ እይታ ወደ አእምሮው እንደመጣ አያጠራጥርም። እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።”—መዝሙር 19:1, 4
2 ይሖዋ ግርማ ሞገስ አላብሶ የፈጠራቸው ሰማያት ንግግርም ሆነ ቃል እንዲሁም ድምፅ ሳያሰሙ ቀንና ሌሊት የእርሱን ክብር ያውጃሉ። ፍጥረት ያለማቋረጥ የይሖዋን ክብር የሚያውጅ ሲሆን ሁሉም ሰው እንዲሰማው “ወደ ምድር ሁሉ” በወጣው በዚህ ምስክርነት ላይ ማሰላሰላችን ከቁጥር የማንገባ መሆናችንን እንድናስተውል ያደርጋል። ሆኖም ፍጥረት ያለ ድምፅ የሚሰጠው ምስክርነት በቂ አይደለም። ታማኝ የሰው ልጆችም ድምፃቸውን በማሰማት ተፈጥሮ ለሚሰጠው ምስክርነት ድጋፍ እንዲሰጡ ተበረታተዋል። ስሙ ያልተገለጸ አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ አነሳሽነት ታማኝ አምላኪዎችን “ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ” ብሏቸዋል። (መዝሙር 96:7, 8) ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ያላቸው ሰዎች ለዚህ ማበረታቻ በደስታ ምላሽ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ ለአምላክ ክብር ማምጣት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
3. የሰው ልጆች ለይሖዋ ክብር መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?
3 አምላክን ማክበር ከቃላት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አምላክን በከንፈራቸው ቢያከብሩትም አብዛኞቹ ይህንን የሚያደርጉት ከልባቸው አልነበረም። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፣ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፣ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና” ብሏል። (ኢሳይያስ 29:13) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያቀርቡት ውዳሴ ከንቱ ነበር። ለይሖዋ የምናቀርበው ውዳሴ ትርጉም ያለው እንዲሆን ለእርሱ ባለን ፍቅር መነሳሳትና ተወዳዳሪ የሌለውን ክብሩን መገንዘብ ይኖርብናል። ከይሖዋ ሌላ ፈጣሪ የለም። እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ በፍትሑ አቻ የሌለውና የፍቅር ተምሳሌት ነው። እርሱ የመዳን ምንጭና በሰማይም ሆነ በምድር ያለ ፍጡር ሁሉ ሊገዛለት የሚገባ ሉዓላዊ ገዢ ነው። (ራእይ 4:10, 11፤ 19:1) በዚህ በእርግጥ የምናምን ከሆነ ይሖዋን በሙሉ ልባችን እናክብረው።
4. ኢየሱስ አምላክን ማክበር የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ምን መመሪያ ሰጥቷል? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ክብር መስጠት የምንችልበትን መንገድ ነግሮናል። “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል” ብሏል። (ዮሐንስ 15:8) ብዙ ፍሬ ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበኩ ሥራ በሙሉ ልባችን በመካፈልና ግዑዝ ከሆኑት ፍጥረታት ጋር ተባብረን ‘ስለማይታዩት የአምላክ ባሕርያት’ “በመናገር” ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ ሮሜ 1:20) ከዚህም በላይ እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋ አምላክ ውዳሴ የሚያቀርቡ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በማፍራቱ ሥራ ሁላችንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድርሻ ይኖረናል። ሁለተኛ፣ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ የሚያፈራቸውን ፍሬዎች በመኮትኮት የይሖዋ አምላክን የላቁ ባሕርያት ለመኮረጅ ጥረት እናደርጋለን። (ገላትያ 5:22, 23፤ ኤፌሶን 5:1፤ ቆላስይስ 3:10) ከዚህም የተነሳ በዕለታዊ ኑሯችን የምናሳየው ባሕርይ አምላክን የሚያስከብር ይሆናል።
“በምድር ሁሉ ላይ”
5. ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለሌሎች በመናገር አምላክን የማክበር ኃላፊነት እንዳለባቸው አበክሮ የገለጸው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
5 ጳውሎስ በሮም ለነበሩ አማኞች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለሌሎች በማካፈል አምላክን የማክበር ኃላፊነት እንዳለባቸው አበክሮ ገልጿል። የሮሜ መጽሐፍ መዳን የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ብቻ መሆናቸውን ያጎላል። ጳውሎስ በመልእክቱ አሥረኛ ምዕራፍ ላይ “ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ” ሆኖ እያለ በዘመኑ የነበሩት ሥጋዊ እስራኤላውያን ግን የሙሴን ሕግ በመከተል የጽድቅ አቋም ለማግኘት ጥረት ያደርጉ እንደነበረ አመልክቷል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና” ብሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፣ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”—ሮሜ 10:4, 9-13
6. ጳውሎስ መዝሙር 19:4ን የተጠቀመበት እንዴት ነው?
6 ቀጥሎም ጳውሎስ “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” በማለት ምክንያታዊ ጥያቄዎች አቅርቧል። (ሮሜ 10:14) ጳውሎስ እስራኤላውያንን በተመለከተ “ነገር ግን ሁሉ ምሥራቹን አልታዘዙም” ብሏል። እስራኤላውያን ያልታዘዙት ለምን ነበር? ያልታዘዙት እምነት ስላልነበራቸው እንጂ አጋጣሚውን ስላላገኙ አይደለም። ጳውሎስ መዝሙር 19:4ን በመጥቀስና ጥቅሱን ፍጥረት ያለ ድምፅ ለሚሰጠው ምሥክርነት ሳይሆን ለክርስቲያናዊው የስብከት ሥራ በመጠቀም ይህንን አሳይቷል። “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ” ብሏል። (ሮሜ 10:16, 18) አዎን፣ ግዑዙ ፍጥረት ይሖዋን እንደሚያከብረው ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም የመዳንን ምሥራች በሁሉም ቦታ በመስበክ አምላክን “በምድር ሁሉ ላይ” አወድሰውታል። ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይም ምሥራቹ ምን ያህል በስፋት እንደተሰራጨ ገልጿል። ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” እንደተሰበከ ተናግሯል።—ቆላስይስ 1:23
ቀናተኛ ምሥክሮች
7. ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ክርስቲያኖች ምን ኃላፊነት አለባቸው?
7 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ ከ27 ዓመታት በኋላ እንደሆነ ይገመታል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የስብከቱ ሥራ እስከ ቆላስይስ ድረስ ሊሰራጭ የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ቀናተኞች በመሆናቸውና ይሖዋም በቅንዓት ያከናወኑትን ሥራ ስለባረከላቸው ነው። ኢየሱስ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” ብሎ ትንቢት በተናገረ ጊዜ ተከታዮቹ ቀናተኛ ሰባኪዎች እንደሚሆኑ አመልክቷል። (ማርቆስ 13:10) ከዚህ ትንቢት በተጨማሪ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል የመጨረሻ ቁጥሮች ላይ የሚገኘውን ትእዛዝም ሰጥቷል:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹ ይህንን ትእዛዝ መፈጸም ጀመሩ።
8, 9. በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ የፈጸሙት እንዴት ነው?
8 ታማኝ የኢየሱስ ተከታዮች በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንደወረደባቸው ያደረጉት የመጀመሪያው ነገር “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” በኢየሩሳሌም ለተሰበሰበው ሕዝብ መስበክ ነበር። የስብከት ሥራቸው ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ “ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ” ሊጠመቅ ችሏል። ደቀ መዛሙርቱ አምላክን በሕዝብ ፊት በቅንዓት ማወደሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:4, 11, 41, 46, 47
9 የእነዚህ ክርስቲያኖች እንቅስቃሴ ወዲያው የሃይማኖት መሪዎቹን ትኩረት ሳበ። ጴጥሮስና ዮሐንስ በግልጽ መናገራቸው ስላስቆጣቸው መስበካቸውን እንዲያቆሙ ሁለቱን ሐዋርያት አዘዟቸው። ሐዋርያቱም “እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” በማለት መለሱላቸው። አስፈራርተው ከለቀቋቸው በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ወንድሞቻቸው ተመለሱና ሁሉም ወደ ይሖዋ ጸለዩ። “ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው” በማለት ያቀረቡት ጸሎት በሁኔታው አለመደናገጣቸውን ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 4:13, 20, 29
10. እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ስደት አጋጠማቸው? እነርሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?
10 ያቀረቡት ጸሎት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንደነበር ብዙም ሳይቆይ በግልጽ ታይቷል። ሐዋርያት ቢታሰሩም አንድ መልአክ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ነፃ አወጣቸው። መልአኩ “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 5:18-20) ሐዋርያት ስለታዘዙ ይሖዋ እነርሱን መባረኩን ቀጠለ። በዚህም የተነሳ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 5:42) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የኢየሱስ ተከታዮች ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ይህ በሕዝብ ፊት ለይሖዋ ክብር እንዳያመጡ አላገዳቸውም።
11. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለስብከቱ ሥራ ምን አመለካከት ነበራቸው?
11 ከጥቂት ጊዜ በኋላ እስጢፋኖስ ተያዘና በድንጋይ ተወግሮ ተገደለ። የእርሱን መገደል ተከትሎ በኢየሩሳሌም ከባድ ስደት የተነሳ ሲሆን ከሐዋርያት በቀር ደቀ መዛሙርት በሙሉ ከኢየሩሳሌም ለመሸሽ ተገደዱ። ስደቱ ተስፋ አስቆርጧቸው ይሆን? በምንም ዓይነት። ዘገባው “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 8:1, 4) የአምላክን ክብር የማወጅ ቅንዓት እንዳላቸው በተደጋጋሚ አሳይተዋል። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9 ላይ ፈሪሳዊ የነበረው የጠርሴሱ ሳውል በደማስቆ ባሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ስደት ለማስነሳት ወደዚያ ሲጓዝ ኢየሱስን በራእይ እንደተመለከተውና ዓይነ ስውር እንደሆነ እናነባለን። በደማስቆ ሐናንያ በተዓምራዊ መንገድ ጳውሎስን ከዓይነ ስውርነቱ አዳነው። በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳውል ያደረገው የመጀመሪያው ነገር ምን ነበር? ዘገባው “ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 9:20
ሁሉም በስብከቱ ሥራ ተካፍለዋል
12, 13. (ሀ) አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደተናገሩት የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ ተለይቶ የሚታወቀው በምን ነበር? (ለ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍና ጳውሎስ የተናገረው ነገር ታሪክ ጸሐፊዎች የሰጡትን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት ነው?
12 የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ እንደነበር በሰፊው የሚታወቅ ነው። ፊሊፕ ሻፍ በዚያን ጊዜ ስለነበሩት ክርስቲያኖች “እያንዳንዱ ጉባኤ የሚስዮናውያን ማኅበር የነበረ ሲሆን እያንዳንዱ አማኝ ክርስቲያን ደግሞ ሚስዮናዊ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ) ዊልያም ሳሙኤል ዊልያምስ ደግሞ “በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን የነበሩት ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም ተዓምራዊ ስጦታ [የመንፈስ ስጦታዎች] የነበራቸው ወንጌሉን ይሰብኩ እንደነበረ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ” በማለት ተናግረዋል። (ምዕመናኑ ያከናወኑት ታላቅ አገልግሎት) አክለውም “ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከቱ ሥራ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚያገኙት መብት እንዲሆን ዓላማው አልነበረም” በማለት ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። የክርስትና ጠላት የነበረው ሴልሰስ እንኳ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሸማኔዎች፣ ጫማ ሠሪዎች፣ ቆዳ ፋቂዎች፣ ያልተማሩና ተራ የተባሉ ሰዎች ቀናተኛ የወንጌሉ ሰባኪዎች ነበሩ።”
13 በሐዋርያት ሥራ ላይ የተመዘገበው ታሪክ የእነዚህን አባባሎች እውነተኝነት ያረጋግጣል። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ሁሉም ደቀ መዛሙርት የአምላክን ታላቅ ሥራ በሕዝብ ፊት አውጀዋል። የእስጢፋኖስን መገደል ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ስደት በኋላ የተበተኑት ክርስቲያኖች በሙሉ ምሥራቹን በሰፊው አሰራጭተዋል። ጳውሎስ ከ28 ዓመታት ገደማ በኋላ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት” በማለት የተናገረው ጥቂት አባላትን ላቀፈ የቀሳውስት ቡድን አልነበረም። (ዕብራውያን 13:15) ጳውሎስ እርሱ ራሱ ለስብከቱ ሥራ ያለውን አመለካከት ሲገልጽ “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንደነበራቸው ግልጽ ነው።
14. እምነትና የስብከቱ ሥራ ምን ዝምድና አላቸው?
14 በእርግጥም፣ የስብከቱ ሥራ ከእምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በዚህ ሥራ መካፈል አለበት። ጳውሎስ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ብሏል። (ሮሜ 10:10) እምነት ያላቸውና በዚህም ምክንያት የመስበክ ኃላፊነት የተጣለባቸው በቀሳውስት ቡድን መልክ ያሉ ጥቂት የጉባኤው አባላት ብቻ ናቸው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው! እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጠንካራ እምነት የሚገነቡ ከመሆኑም ሌላ ይህን እምነታቸውን ለሌሎች ለማሳወቅ ይነሳሳሉ። እንደዚህ የማያደርጉ ከሆነ እምነታቸው የሞተ ነው። (ያዕቆብ 2:26) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ መንገድ እምነታቸውን በመግለጻቸው ለይሖዋ ስም ከፍተኛ ውዳሴ ቀርቧል።
15, 16. ችግሮች ቢኖሩም የስብከቱ ሥራ እድገት ማሳየቱን እንደቀጠለ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤው ከውስጥም ሆነ ከውጭ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ይሖዋ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ ሕዝቦቹን ባርኳቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 6 ላይ በዕብራይስጥና በግሪክኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረ ተዘግቧል። ሐዋርያት ለችግሩ መፍትሔ ያስገኙ ሲሆን “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፣ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቊጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።”—የሐዋርያት ሥራ 6:7
16 ቆየት ብሎ፣ በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ አግሪጳ እንዲሁም በጢሮስና በሲዶና ነዋሪዎች መካከል የፖለቲካ ውጥረት ተከስቶ ነበር። በእነዚህ ከተማዎች የሚኖሩ ሰዎች ለዕርቅ ባቀረቡት ልመና ሄሮድስ ተታልሎ ለሕዝቡ ንግግር ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆነ። ንግግሩን ለማዳመጥ የተሰበሰበው ሕዝብ “የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም” ብሎ ጮኸ። ሄሮድስ አግሪጳ “ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ” ወዲያው የይሖዋ መልአክ ቀስፎ ገደለው። (የሐዋርያት ሥራ 12:20-23) ተስፋቸውን በሰብዓዊ መሪዎች ላይ ጥለው ለነበሩ ሰዎች ይህ ምንኛ አሳፋሪ ነው! (መዝሙር 146:3, 4) ያም ሆኖ ክርስቲያኖች ይሖዋን ማክበራቸውን ቀጥለዋል። በመሆኑም የፖለቲካ አለመረጋጋት እያለም “የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 12:24
ጥንትና ዛሬ
17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ሰዎች በየትኛው ሥራ ተካፍለዋል?
17 በእርግጥም፣ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓለም አቀፍ የክርስቲያን ጉባኤ ቀናተኛና ትጉ የሆኑ የይሖዋ አምላክ አወዳሾችን ያቀፈ ነበር። ሁሉም ታማኝ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በማሰራጨቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር። አንዳንዶች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ያጋጠሟቸው ሲሆን ኢየሱስ እንደተናገረው ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምረዋቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በውጤቱም ጉባኤው ያደገ ከመሆኑም በላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ግለሰቦች ለይሖዋ ምስጋና በማምጣት ረገድ በጥንት ዘመን የኖረውን የንጉሥ ዳዊትን አርዓያ ተከትለዋል። “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤ ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና” የሚሉትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት ሁሉም አስተጋብተዋል።—መዝሙር 86:12, 13
18. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤና ዛሬ ባለችው ሕዝበ ክርስትና መካከል ምን ልዩነት አለ? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?
18 ከዚህ አንጻር ሲታይ የቲኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አሊሰን ትራይትስ የሰጡት ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው። በዘመናችን ያለችውን ሕዝበ ክርስትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የክርስትና እምነት ጋር በማወዳደር እንዲህ ብለዋል:- “በዛሬው ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው ቁጥራቸው የሚጨምረው ልጆች በመወለዳቸው (የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ቤተሰብ ልጆች የዚያ እምነት ተከታይ ሲሆኑ) ወይም በዝውውር (ከሌላ ቦታ የመጣ ሰው የቤተ ክርስቲያኑ አባል ሲሆን) ነው። ሆኖም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚያሳየው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጭማሪ የተገኘው ሰዎች ወደ ክርስትና እምነት በመለወጣቸው ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑ ገና አዲስ የተመሰረተ በመሆኑ ነበር።” ይህ ሲባል እውነተኛ ክርስትና ኢየሱስ በተናገረው መንገድ እድገት ማድረጉን አቁሟል ማለት ነው? እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሕዝብ ፊት ለአምላክ ውዳሴ በማምጣት ረገድ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ቀናተኞች ናቸው። በሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንመለከታለን።
ልታብራራ ትችላለህ?
• አምላክን የምናከብረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
• ጳውሎስ መዝሙር 19:4ን የተጠቀመበት እንዴት ነው?
• እምነትና የስብከቱ ሥራ ምን ዝምድና አላቸው?
• የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ተለይቶ የሚታወቀው በምን ነበር?
[በገጽ 8,9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰማያት ምንጊዜም የይሖዋን ክብር ያውጃሉ
[ምንጭ]
Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብከቱ ሥራና ጸሎት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው