የንግድ ሥራህ ምን መሥዋዕት እንድትከፍል ያስገድድሃል?
የአንድ የደቡብ አሜሪካ አገር ፕሬዘዳንት ባለቤት በራሷ ቤተሰብ አባላት ከተቋቋሙ የይስሙላ ኩባንያዎች ጋር በተደረጉ ውሎች በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር በስውር አሳልፋ በመስጠቷ ተወንጅላለች። በህንድ ውስጥ የሚኖር አንድ የ38 ዓመት የአክሲዮን ደላላ በባንክ ንግድና በአክሲዮን ገበያ 1.6 ቢልዮን ዶላር በማጭበርበር ከፍተኛ ቅሌት ፈጽመሃል ተብሎ ተይዟል፤ ምቾትና ውበት ያለው መኖሪያውንና 29 መኪናዎቹንም ተነጥቋል። በፊሊፒንስ በአንድ ደሴት ላይ የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት ሕገ–ወጥ በሆነ መንገድ ሽጉጥ በማምረት ነው። በዚህ ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኝ የንግድ ሥራ መቀጠል እንዲችሉ ዘወትር ለባለሥልጣናት ጉቦ እንደሚሰጡ ሪፖርት ተደርጓል።
አዎን፣ በንግድ ማታለልና ማጭበርበር በዓለም ዙሪያ የተንሰራፉ ነገሮች ናቸው። እንዲሁም ይህ ነገር ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ቦታቸውን፣ ስማቸውንና ገንዘባቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል።
አንተስ? በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተሃልን? ወይም ደግሞ አንድ የንግድ ሥራ ለመጀመር እያሰብክ ነው? ይህ ምን መሥዋዕት እንድትከፍል ያስገድድሃል? በንግድ ሥራ መሠማራት አንድ የሆነ መሥዋዕት እንድትከፍል እንደሚያደርግህ የተረጋገጠ ነው። ይህ ሁልጊዜ መጥፎ ይሆናል ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ አንድ የንግድ ሥራ ከመጀመር በፊት ወይም ቀደም ሲል የተቋቋመን የንግድ ሥራ በተመለከተ አንዳንድ ውሳኔዎችን ከመውሰድ በፊት ኪሳራውን ማስላት ጥበብ ነው። (ሉቃስ 14:28) በገጽ 31 ላይ የሚገኘው ሣጥን የንግድ ሥራ መሥዋዕት እንድታደርጋቸው የሚጠይቅብህን ግምት ውስጥ ልታስገባቸው የምትፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ያሳያል።
በንግድ ሥራ መሠማራት ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አንድ ክርስቲያን ሊያጤናቸው የሚገቡ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ግዴታዎች አሉ። የንግዱ ሥራ መሥዋዕት እንድታደርግ የሚጠይቅብህን ነገር ማሟላትና መንፈሳዊ ሚዛንህን ጠብቀህ መቀጠል ትችላለህን? የንግዱ ሥራ መሥዋዕት እንድታደርጋቸው የሚጠይቅብህ አንዳንድ ነገሮች በሥነ ምግባር ደረጃ ልትቀበለው ከምትችለው በላይ የሆኑ ናቸውን? የንግዱ ሥራ መሥዋዕት እንድታደርጋቸው ከሚጠይቅብህ ነገሮች መካከል የትኞቹ ተቀባይነት እንዳላቸው የትኞቹ ደግሞ እንደሌላቸው ለይተህ ለማወቅ እንድትችል የሚረዱህ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?
ለገንዘብ ገደብ ያለው አመለካከት ይኑርህ
አንድ የንግድ ሥራ ለማካሄድ ገንዘብ አስፈላጊ ነው፤ ይህ ሥራ ደግሞ የአንድ ሰው ቤተሰብ ለኑሮ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት የሚያስችል በቂ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። ይሁን እንጂ ገንዘብን በተመለከተ የምናወጣቸው ግቦች በቀላሉ አቅጣጫቸውን ሊስቱ ይችላሉ። ስግብግብነት ትልቅ ቦታ ሊይዝ ይችላል። ለብዙ ሰዎች ገንዘብ ከማንኛውም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የምሳሌ መጽሐፍ ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው አጉር “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ” ባለ ጊዜ ሚዛናዊውን አመለካከት ገልጿል። (ምሳሌ 30:8) ለመኖር በሚያስፈልግ ነገር ብቻ የመርካትን ዋጋማነት ተገንዝቦ ነበር፤ በንግዱ ዓለም ውስጥ ያሉ አንዳንዶች እንደሚሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማጋበስ አልፈለገም።
ይሁን እንጂ ወርቅ የሆነ አጋጣሚ የሚባለው ነገር ሲከሰት ስግብግብነት አንድ ሰው ይህን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲዘነጋ ሊያደርገው ይችላል። በአንድ ታዳጊ አገር ውስጥ የሚያገለግል አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ አገልጋይ ይህን የመሰለ አንድ ሁኔታ ሪፖርት አድርጓል። የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚፈልግ አንድ ኩባንያ ኢንቨስተሮች ወዲያውኑ ምናልባትም በጥቂት ወራት ውስጥ ገንዘባቸውን በእጥፍ ማሳደግ የሚችሉበትን ሐሳብ አቀረበ። ይህ በቀላሉ ብዙ ገንዘብ ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ ብዙዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ አነሳሳቸው። ተጓዥ አገልጋዩ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች በዚህ ለመሳተፍ ከፍተኛ ጉጉት አድሮባቸው ነበር። ሁኔታውን በደንብ ለመመርመር በቂ ጥያቄዎች አላቀረቡም ነበር፤ እንዲሁም [ኢንቨስት የሚያደርጉት] ገንዘብ ተበደሩ።”
በአንጻሩ ሁለት ግለሰቦች ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት ሁኔታውን ለማጣራት ወደዚህ ኩባንያ ቢሮ ሄዱ። የማምረቻውን ተቋሞች ለመመልከት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም። ይህም ኩባንያውን እንዲጠራጠሩት አደረጋቸው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የተሸረበው የማታለያ ዘዴ ስለተጋለጠና ሰዎችም ስለተያዙ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማድረጋቸው ጥበቃ ሆኖላቸዋል። መጀመሪያ ሁኔታውን በደንብ ያልመረመሩ ሰዎች ምን ዓይነት ኪሳራ ላይ እንደወደቁ እስቲ አስበው። ያጡት ገንዘባቸውን ብቻ አይደለም፤ ውጥኑ የውኃ ሽታ ሆኖ ሲቀር የተበደሩትን ገንዘብ መልሰው መስጠት ባለመቻላቸው ካበደሯቸው ጓደኞቻቸውም ጋር ተቆራርጠው ሊሆን ይችላል። ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” የሚለውን የምሳሌ 22:3 መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ማዋል ምንኛ ጥበብ ነው!
የገባኸውን ቃል ጠብቅ
የንግዱ ሥራ ያሰብከውን ትርፍ ባያስገኝስ? መዝሙር 15:4 [ የ1980 ትርጉም] ጥቅም ባያገኝበትም እንኳ የገባውን ቃል ስለማያጥፍ ሰው ሲናገር “ምንም ያህል ከባድ ቢሆን የገባውን ቃል ኪዳን የሚፈጽም” በማለት ያወድሰዋል። ነገሮች ሲሰምሩ የገቡትን ቃል መጠበቅ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የገባው ቃል ገንዘብ ነክ በሆኑ ሁኔታዎች ረገድ የሚጎዳው ሆኖ ሲገኝ ቃሉን መጠበቅ ንጹሕ አቋምን የሚፈታተን ነገር ይሆናል።
በኢያሱ ዘመን የተፈጸመ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ አስታውስ። ገባዖናውያን የእስራኤል አለቆች ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡና እንዳያጠፏቸው ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ቀየሱ። እርግጥ እነርሱ በእስራኤል ላይ ሥጋት የሚፈጥሩ ተደርገው ይታዩ ከነበሩት ሕዝቦች መካከል የሚገኙ ነበሩ። የማታለያ ዘዴያቸው ሲደረስበት “የሕዝቡም አለቆች . . . በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም።” (ኢያሱ 9:18) እነዚህ ሰዎች ከጠላት ክልል የመጡ ቢሆንም እንኳ አለቆቹ ቃላቸውን መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ከዚያ በኋላ የተከናወኑት ነገሮችም ይሖዋ በነገሩ ደስ እንደተሰኘ ያሳያሉ።—ኢያሱ 10:6–11
ሁኔታዎች አንተ እንዳሰብከው ሳይሆኑ ቢቀሩም እንኳ የንግድ ስምምነቶችህንና ውሎችህን ትጠብቃለህን?a እንዲህ ማድረግህ ምንጊዜም ቃሉን የማያጥፈውን ይሖዋን ይበልጥ እንድትመስለው ያደርግሃል።—ኢሳይያስ 55:11
ሐቀኛ ሁን
በዛሬው የንግድ ዓለም ውስጥ ሐቀኝነት ከናካቴው ሊጠፋ ምንም ያህል አልቀረውም ማለት ይቻላል። አንተ በተሰማራህበት የንግድ ዓይነት የተሰማሩ ሌሎች ገቢያቸውን ለማሳደግ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ይሆናል። የሚያወጧቸው የንግድ ማስታወቂያዎች ሐቀኝነት የጎደላቸው ይሆናሉ። የሌላውን ኩባንያ ስም ወስደው በራሳቸው ምርት ላይ ይለጥፉ ይሆናል። ወይም አንድን ተራ የምርት ውጤት ምርጥ ዕቃ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ የማታለያ መንገዶች ናቸው። ይህን የሚያደርጉ ሁሉ አሳፍ እንዳለው ‘ባለጠግነታቸውን እንደሚያበዙ ክፉዎች’ ናቸው፤ ይህንንም የሚያደርጉት በማጭበርበር ነው።—መዝሙር 73:12
ክርስቲያን እንደ መሆንህ መጠን ሕገ–ወጥ የሆኑ ዘዴዎችን ትጠቀማለህ? ወይስ “ማንንም አልበደልንም፣ ማንንም አላጠፋንም፣ ማንንም አላታለልንም”፤ “የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም”፤ “ሁለት ዓይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፣ ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም” በሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ትመራለህ? (2 ቆሮንቶስ 4:2፤ 7:2፤ ምሳሌ 20:23) የአታላይነት ምንጭ “የሐሰት አባት” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንጂ ሌላ ማንም እንዳልሆነ አስታውስ።—ዮሐንስ 8:44
አንዳንዶች ‘አንድ ሰው ሌሎች እንደሚያደርጉት የማታለያ መንገዶችን ካልተጠቀመ በንግድ ዓለም ውስጥ መሰንበት አይችልም’ በማለት የተቃውሞ ሐሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ክርስቲያኑ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ሊያሳይ የሚችለው በዚህ ጊዜ ነው። አንድ የሆነ ነገር መሥዋዕት እንድናደርግ የሚጠይቅብን በሚሆንበት ጊዜ ሐቀኝነት ፈተና ላይ ይወድቃል። አንድ ሰው ሳያታልል ኑሮውን መምራት አይችልም ማለት አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ደንታ የለውም እንደ ማለት ነው። በይሖዋ ላይ እውነተኛ እምነት ያለው ሰው አምላክ በማንኛውም አገርና በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ላይ ለሚገኙት አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሊሰጣቸው እንደሚችል ያውቃል። (ዕብራውያን 13:5) እውነት ነው፣ አንድ ሰው በማታለል የሚሠሩ ሰዎች ከሚያገኙት ባነሰ ገቢ መርካት ሊያስፈልገው ይችላል፤ ይሁን እንጂ የአምላክን በረከት ለማግኘት ይህን ዋጋ መክፈሉ የሚበዛ ነገር ነውን?
አታላይነት ሲወረወር ወርዋሪውን መልሶ እንደሚመታ ቀስት እንደሆነ አስታውስ። አንድ የንግድ ሥራ የሚያካሄድ ሰው አታላይ ሆኖ ቢገኝ ብዙውን ጊዜ ደንበኞቹም ሆኑ የሚነግደውን ዕቃ የሚያቀርቡለት ሰዎች ይርቁታል። አንዴ ሊያታልላቸው ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ ላያታልላቸው ይችላል። በሌላ በኩል የንግድ ሥራ የሚያካሄድ ሐቀኛ ሰው ብዙውን ጊዜ በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያገኛል። ‘ማንም የሚያደርገው ነገር ስለሆነ እኔም ባደርገው ችግር የለውም’ በሚል ተልካሻ ምክንያት እንዳትታለል ተጠንቀቅ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት “ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል” ይላል።—ዘጸአት 23:2
በንግድ ሥራህ ለረጅም ጊዜ ሸሪክ ሆኖ የሚሠራው ሰው መሰል ክርስቲያን ያልሆነና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እምብዛም የማይጠብቅ ሰው ነው እንበል። አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ነገር ሲፈጸም ኃላፊነቱን ከራስህ ላይ ለማውረድ ይህን እንደ ሰበብ አድርገህ መጠቀም ተገቢ ነውን? እንደ አዳምና እንደ ሳኦል ያሉትን ምሳሌዎች አስታውስ። ኃጢአት ከመሥራት መቆጠብ ሲገባቸው ለሌሎች ተጽእኖ ተንበርክከዋል፤ ከዚያም አብረዋቸው በነበሩት ሰዎች አሳብበዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም ክፉኛ ተቀጥተዋል!—ዘፍጥረት 3:12, 17–19፤ 1 ሳሙኤል 15:20–26
ከመሰል አማኞች ጋር የሚኖርህ የንግድ ግንኙነት አግባብ ያለው ይሁን
ከመሰል የይሖዋ አምላኪዎች ጋር የንግድ ግንኙነት በምንመሠርትበት ጊዜ ልናሰላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉን? ነቢዩ ኤርምያስ በትውልድ ከተማው በዓናቶት ከአጎቱ ልጅ እርሻ ሲገዛ እንዲሁ ገንዘቡን በመክፈል የቃል ስምምነት አላደረገም። ከዚህ ይልቅ “በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፣ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት” ብሏል። (ኤርምያስ 32:10) እንዲህ ዓይነት የጽሑፍ ውል መፈራረም ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች ቢለወጡ ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ለማስወገድ ያስችላል።
ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ወንድም በንግድ ሥራ ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢፈጽምባችሁስ? ፍርድ ቤት ታቆሙታላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ግልጽ ሐሳብ ይሰጣል። “ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን?” ሲል ጳውሎስ ጠይቋል። አንድ ችግር በበቂ ሁኔታ ወዲያውኑ ሊፈታ ካልቻለስ? ጳውሎስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” ከድርጅቱ ውጭ ያሉ ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ፍርድ ቤት ቀርበው እየተሟገቱ እንዳሉ ቢሰሙ በክርስቲያናዊው ድርጅት ላይ የሚያርፈውን ጥቁር ነጥብ እስቲ አስበው! በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች አንድ ሰው ለገንዘብ ያለው ፍቅር ለወንድሙ ካለው ፍቅር በልጦ ይሆን? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ስሙ በመጥፋቱ ከፍተኛ የበቀል ስሜት በአእምሮ ውስጥ ተጠንስሶ ይሆን? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ መጎዳት እንደሚሻል የጳውሎስ ምክር ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 6:1, 7፤ ሮሜ 12:17–21
እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ሙግቶችን በጉባኤው ውስጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ መያዝ የሚቻልበት መንገድ አለ። (ማቴዎስ 5:37፤ 18:15–17) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የተሰጡትን ሐሳቦች ደረጃ በደረጃ እንዲከተሉ ወንድሞችን በመርዳት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ጠቃሚ ምክር ሊለግሷቸው ይችላሉ። በእንዲህ ዓይነት ውይይቶች ወቅት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር መስማማት ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የተሰጠውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ምክሩን እንደተቀበልክ ታሳያለህን? ለአምላክና ለመሰል ክርስቲያኖች ያለን ፍቅር እንዲህ እንድናደርግ ያስገድደናል።
የንግድ ሥራ አንድ የሆነ ነገር መሥዋዕት እንድታደርግ እንደሚጠይቅብህ ምንም አያጠራጥርም። መሥዋዕት የምታደርገው ተገቢ የሆኑትን ነገሮች ብቻ ነው ተብሎ ይታመናል። ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች ወይም ማንኛውም ዓይነት አጠያያቂ ሁኔታ ሲያጋጥምህ በሕይወት ውስጥ ከገንዘብ እጅግ የላቀ ዋጋ ያላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አስታውስ። ለገንዘብ ገደብ ያለው አመለካከት በመያዝ፣ ቃልን በመጠበቅ፣ ሐቀኛ በመሆንና ከንግድ ሸሪኮች ጋር ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ግንኙነት በማድረግ አንድ ንግድ ከሚገባው በላይ ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ እንዳይሆን ማድረግ እንችላለን፤ እግረ መንገዳችንንም ጓደኞቻችንን ሳናጣ እንዲሁም ንጹሕ ሕሊናና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንደያዝን መቀጠል እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ሰው በንግድ ሥራ የገባውን ቃል መጠበቅ እንዳለበት የሚያሳይ ዘመናዊ ምሳሌ ለማግኘት በግንቦት 8, 1988 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ላይ ከገጽ 11–13 ላይ የሚገኘውን “ከቃሌ ውልፍት አልልም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የንግድ ሥራህ መሥዋዕት እንድታደርጋቸው ሊጠይቅብህ የሚችላቸው ነገሮች
ጊዜ፦ የራስን የንግድ ሥራ ማካሄድ ምንጊዜም በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ከመሥራት የበለጠ ጊዜን ይወስዳል ማለት ይቻላል። የንግድ ሥራህ አስፈላጊ ለሆኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምታውለው ጊዜ በጣም እንዲጣበብ በማድረግ ፕሮግራምህን ያቃውሰዋልን? በበጎው ጎኑ ደግሞ፣ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ጉዳዮችህን ማስተካከል ትችላለህን? እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ነው። ነገር ግን ተጠንቀቅ! ይህን ማድረጉ እንደ መናገሩ ቀላል አይሆንም።
ገንዘብ፦ ገንዘብ ለማትረፍ ገንዘብ ያስፈልጋል። ለንግድ ሥራህ ምን ዓይነት መዋዕለ ንዋይ ያስፈልግሃል? ገንዘቡ አለህ? ወይስ መበደር ያስፈልግሃል? የተወሰነ ገንዘብ ብታጣ ሁኔታውን መቋቋም ትችላለህ? ወይስ ነገሮች እንደጠበቅከው ሳይሆኑ ቢቀሩ ኪሳራው ልትቋቋመው ከምትችለው በላይ ይሆን ብሃል?
ጓደኞች፦ የንግድ ሥራ የሚያካሄዱ ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴዎች በሚነሱ ችግሮች የተነሣ ከጓደኞቻቸው ጋር ተቆራርጠዋል። ጓደኞችን የማፍራቱ አቅም ቢኖርም የጠበቀ ዝምድና የመመሥረቱ ጉዳይ በጣም አጠራጣሪ ነው። እነዚህ ጓደኞቻችን ክርስቲያን ወንድሞቻችን ቢሆኑስ?
ጥሩ ሕሊና፦ በዛሬው ጊዜ ሰዎች በንግድ ዓለም የሚሠማሩት “እኔ ልብላ አንተ ጦም እደር” የሚል ፈሊጥ በመያዝ ወይም “ጥቅም ላገኝበት የምችለው እንዴት ነው?” የሚል አመለካከት በመያዝ ነው። በአውሮፓ ውስጥ በተካሄደ አንድ ጥናት 70 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች በንግድ ዓለም ውስጥ የሥነ ምግባር ደንቦች ምንም ቦታ የላቸውም ብለዋል። አጭበርባሪነት፣ አታላይነትና አጠያያቂ የሆኑ የንግድ ድርጊቶች የተለመዱ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። አንተም እንደ ሌሎች እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ትፈተናለህን?
ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና፦ በንግድ ሥራ ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጻራሪ የሆነ ማንኛውም ድርጊት በንግድ ጉዳዮች የተለመደ ነገር ቢሆንም እንኳ አንድ ሰው ከፈጣሪው ጋር ያለውን ዝምድና ያበላሽበታል። የዘላለም ሕይወት ተስፋውን እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል። አንድ ታማኝ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ቁሳዊ ጥቅም ቢያገኝ ይህን ማጣቱ ከፍተኛ ኪሳራ መሆኑ ግልጽ አይደለምን?
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኋላ አለመግባባት እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚረዳው የትኛው ነው? በቃል የሚደረግ ስምምነት ወይስ በጽሑፍ ላይ የሚሰፍር ውል?