መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ የሚጫወተው ሚና
“ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ . . . የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳ. 55:11
1. እቅድ በማውጣትና ዓላማ ይዞ በመነሳት መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ አስረዳ።
ሁለት ሰዎች በየፊናቸው በመኪና ለመጓዝ እየተዘጋጁ ነው እንበል። አንደኛው ግለሰብ ወደሚፈልግበት ቦታ ለመድረስ በየት በየት አድርጎ እንደሚሄድ አስቀድሞ በማሰብ አንድ የተወሰነ አቅጣጫ ለመከተል ይወስናል። ሌላኛው ግለሰብ የት መሄድ እንደሚፈልግ ጠንቅቆ ቢያውቅም አንድ የተወሰነ አቅጣጫ ከመከተል ይልቅ ወደሚፈልግበት ቦታ የሚያደርሱትን የተለያዩ አማራጮች በአእምሮው ይዟል። ይህ ሰው እንዳስፈላጊነቱ አቅጣጫውን ለመቀያየር ዝግጁ ነው። እነዚህ ሁለት ሰዎች ያደረጉት ውሳኔ በተወሰነ መንገድም ቢሆን በእቅድና በዓላማ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስረዳት እንደ ምሳሌ ሊያገለግል ይችላል። እቅድ ማውጣት፣ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ የምንከተለውን አቅጣጫ በዝርዝር ከመንደፍ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ዓላማ ይዞ መነሳት፣ ልንደርስበት የምንፈልገውን ግብ በአእምሯችን መያዝን የሚያመለክት ሲሆን እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ግን አንድ የተወሰነ አቅጣጫ መከተል ላያስፈልግ ይችላል።
2, 3. (ሀ) የይሖዋ ዓላማ ምን ያካትታል? አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ ይሖዋ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን እርምጃ ወሰደ? (ለ) የአምላክን ዓላማ አፈጻጸም በትኩረት መከታተልና ከዚያ ጋር ተስማምተን መኖር ያለብን ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ ፈቃዱን ከመፈጸም ጋር በተያያዘ አስቀድሞ የተነደፈ የማይለወጥ እቅድ አያወጣም፤ ከዚህ ይልቅ በጊዜ ሂደት ተግባራዊ የሚሆን ዓላማ ይኖረዋል። (ኤፌ. 3:11) ይህ ዓላማ ገና ከጅምሩ ለሰው ዘሮችና ለምድር የነበረውን ሐሳብ የሚያካትት ነው፤ ይኸውም ምድር ወደ ገነትነት እንድትለወጥና ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በሰላምና በደስታ ለዘላለም እንዲኖሩባት ማድረግ ነው። (ዘፍ. 1:28) አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ ይሖዋ ለሁኔታው ፈጣን ምላሽ በመስጠት ዓላማውን ዳር ለማድረስ የሚያስችሉ አንዳንድ ዝግጅቶች አደረገ። (ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።) የይሖዋን ድርጅት የምታመለክተው ምሳሌያዊት ሴት፣ ‘ዘር’ ወይም ልጅ እንድታስገኝ ለማድረግ ወሰነ፤ ከጊዜ በኋላ ይህ ዘር የችግሩ ጠንሳሽ የሆነውን ሰይጣንን የሚያጠፋው ሲሆን በእሱ ምክንያት የተከሰተውን ችግር በሙሉ ያስተካክላል።—ዕብ. 2:14፤ 1 ዮሐ. 3:8
3 አምላክ እንደሚፈጽመው የተናገረውን ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ ሊያግደው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል በሰማይም ሆነ በምድር የለም። (ኢሳ. 46:9-11 የ1954 ትርጉም) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም መንፈስ ቅዱስን ስለሚጠቀም ነው። ምንም ነገር የማያግደው ይህ ታላቅ ኃይል የአምላክ ዓላማ ‘እንደሚፈጸም’ ዋስትና ይሆናል። (ኢሳ. 55:10, 11) እኛም የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን መንገድ በትኩረት መከታተልና ከዚያ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መመላለስ ይኖርብናል። የወደፊት ሕይወታችን የተመካው በአምላክ ዓላማ መፈጸም ላይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዴት እንደሚጠቀምበት ማወቅ እምነታችንን የሚያጠናክር ነው። እንግዲያው መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ጥንት ምን ሚና እንደተጫወተ እንዲሁም አሁንና ወደፊት ምን ድርሻ እንደሚኖረው እንመርምር።
መንፈስ ቅዱስ ጥንት የተጫወተው ሚና
4. ይሖዋ ዓላማውን ደረጃ በደረጃ የገለጠው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ በጥንት ዘመን ዓላማውን ደረጃ በደረጃ ገልጦ ነበር። ተስፋ የተደረገበት ዘር ማንነት መጀመሪያ ላይ “ቅዱስ ሚስጥር” ሆኖ ነበር። (1 ቆሮ. 2:7) ይሖዋ ዘሩን በተመለከተ በድጋሚ የተናገረው 2,000 የሚሆኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 12:7ን እና 22:15-18ን አንብብ።) ይሖዋ ለአብርሃም ቃል የገባለት ሲሆን ይህ ቃል ኪዳን ስለ ዘሩ ማንነትም ሆነ ከዚህ ዝግጅት ጋር ተያይዘው ስለሚመጡት በረከቶች ተጨማሪ እውቀት ፈንጥቋል። “በዘርህ” የሚለው ቃል የሴቲቱ ዘር በአብርሃም የትውልድ መስመር በኩል ሰው ሆኖ እንደሚመጣ በግልጽ ይጠቁማል። ይሖዋ ዘሩን በተመለከተ ይህን ዝርዝር ጉዳይ ሲገልጥ ሰይጣን ሁኔታውን በትኩረት ይከታተል እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ የአምላክ ጠላት የአብርሃምን የዘር ሐረግ በማጥፋት ወይም ከእሱ የትውልድ ሐረግ የሚገኘው ሕዝብ የአምላክን ሞገስ እንዲያጣ በማድረግ የአምላክ ዓላማ ሲጨናገፍ ከማየት የበለጠ የሚፈልገው ነገር እንደሌለ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና የማይታየው የአምላክ መንፈስ ምንጊዜም በሥራ ላይ በመሆኑ የሰይጣን ፍላጎት ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም። ለመሆኑ የአምላክ መንፈስ የሚሠራው እንዴት ነው?
5, 6. ይሖዋ ዘሩ በሚመጣበት የትውልድ መስመር ላይ ያሉትን ግለሰቦች ለመጠበቅ በመንፈሱ የተጠቀመው እንዴት ነበር?
5 ይሖዋ ዘሩ በሚመጣበት የትውልድ መስመር ላይ ያሉትን ግለሰቦች ለመጠበቅ መንፈሱን ተጠቅሟል። ይሖዋ ለአብራም (ለአብርሃም) “እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 15:1) እነዚህ ቃላት እንዲሁ ከንቱ ሆነው አልቀሩም። ለምሳሌ ያህል፣ በ1919 ዓ.ዓ. ገደማ አብርሃምና ሣራ ለተወሰነ ጊዜ በጌራራ ይኖሩ በነበረበት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ፣ ሣራ የአብርሃም ሚስት መሆኗን ስላላወቀ ሚስቱ ሊያደርጋት ወሰዳት። ሣራ የአብርሃምን ልጅ እንዳትወልድ ለማድረግ ሰይጣን ከበስተ ጀርባ ሆኖ ነገሮችን እያቀናጀ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይልም። ሆኖም ይሖዋ በጉዳዩ ጣልቃ እንደገባ ይነግረናል። አቢሜሌክ ሣራን እንዳይነካት አምላክ በሕልም አማካኝነት አስጠነቀቀው።—ዘፍ. 20:1-18
6 ይሖዋ ጥበቃ ያደረገበት አጋጣሚ ይህ ብቻ አይደለም። ይሖዋ፣ አብርሃምንም ሆነ የቤተሰቡን አባላት በተለያዩ ጊዜያት ታድጓቸዋል። (ዘፍ. 12:14-20፤ 14:13-20፤ 26:26-29) በዚህም የተነሳ አብርሃምንና በእሱ የዘር ሐረግ የመጡ ሰዎችን አስመልክቶ መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “[ይሖዋ] ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤ ‘የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።’”—መዝ. 105:14, 15
7. ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር ጥበቃ ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
7 ይሖዋ ተስፋ የተደረገው ዘር የሚወለድበትን የጥንቱን የእስራኤል ብሔር በመንፈሱ አማካኝነት ጠብቋል። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ሕጉን ለእስራኤላውያን ሰጥቷል። ይህ ደግሞ እውነተኛው አምልኮ ሳይጠፋ እንዲቆይ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ አይሁዳውያን መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ንጽሕናቸው እንዳይበከል ጠብቋቸዋል። (ዘፀ. 31:18፤ 2 ቆሮ. 3:3) በመሳፍንት ዘመን እስራኤላውያንን ከጠላት እንዲታደጉ የይሖዋ መንፈስ ለአንዳንድ ሰዎች ኃይል ሰጥቷቸዋል። (መሳ. 3:9, 10) የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነው ኢየሱስ እስከተወለደበት ጊዜ ድረስ ባሉት በርካታ መቶ ዓመታት መንፈስ ቅዱስ ኢየሩሳሌምን፣ ቤተልሔምንና ቤተ መቅደሱን በመጠበቅ ረገድ ድርሻ አበርክቶ መሆን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም እነዚህ ቦታዎች ስለ ኢየሱስ በተነገሩት ትንቢቶች አፈጻጸም ረገድ የሚጫወቱት ሚና ነበር።
8. መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ልጅ ሕይወትና አገልግሎት ውስጥ ቀጥተኛ ድርሻ እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
8 መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ውስጥ ቀጥተኛ ድርሻ ነበረው። መንፈስ ቅዱስ በድንግል ማርያም ላይ በማረፍ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ሆኖ የማያውቅ ነገር አከናውኗል፤ ይኸውም ፍጹም ያልሆነች ሴት በሞት እርግማን ሥር ያልሆነ ፍጹም ልጅ እንድትፀንስና እንድትወልድ አድርጓል። (ሉቃስ 1:26-31, 34, 35) ከዚያ በኋላም መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ተልእኮውን ከመፈጸሙ በፊት እንዳይሞት ጠብቆታል። (ማቴ. 2:7, 8, 12, 13) ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው አምላክ ልጁን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት የዳዊትን ዙፋን እንዲወርስ ሾመው እንዲሁም የስብከት ተልእኮ ሰጠው። (ሉቃስ 1:32, 33፤ 4:16-21) ኢየሱስ በሽተኞችን መፈወስን፣ ብዙ ሰዎችን መመገብንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ የተለያዩ ተአምራትን እንዲሠራ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቶታል። እነዚህ አስደናቂ ሥራዎች ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ወቅት እንደምናገኝ የምንጠብቃቸውን በረከቶች የሚያመላክቱ ነበሩ።
9, 10. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኖሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ዓላማውን ስለሚፈጽምበት መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምን አዲስ ነገር ተገልጧል?
9 በ33 ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ጀምሮ ይሖዋ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆኑትን ሰዎች ለመቀባት በመንፈሱ ተጠቅሟል፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ከአብርሃም የትውልድ ሐረግ የመጡ አልነበሩም። (ሮም 8:15-17፤ ገላ. 3:29) መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኖሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር እንደነበር በግልጽ ይታይ ነበር፤ ይህ መንፈስ ደቀ መዛሙርቱ በቅንዓት እንዲሰብኩና ተአምራትን እንዲሠሩ ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 1:8፤ 2:1-4፤ 1 ቆሮ. 12:7-11) መንፈስ ቅዱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንደነዚህ ያሉ ተአምራዊ ስጦታዎች እንዲኖሯቸው በማድረግ ይሖዋ ዓላማውን ስለሚፈጽምበት መንገድ አዲስ ነገር ገልጧል። ይሖዋ ለዘመናት ሲሠራበት የኖረውን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ማዕከል ያደረገውን የአምልኮ ዝግጅት ተወው። ከዚህ ይልቅ ትኩረቱን አዲስ በተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ አደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ በዚህ የቅቡዓን ጉባኤ ሲጠቀም ቆይቷል።
10 ይሖዋ፣ ዓላማው ወደ ፍጻሜው እንዲገሰግስ ለማድረግ በጥንት ዘመን በመንፈስ ቅዱስ ከተጠቀመባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ የዘሩ ክፍል ለሆኑት ጥበቃ ማድረግና ኃይል መስጠት እንዲሁም እነዚህን ሰዎች መቀባት ናቸው። ይሁንና ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ መንፈስ ቅዱሱን እየተጠቀመ ያለው እንዴት ነው? ከመንፈሱ ጋር ተስማምተን መኖር ስለምንፈልግ ስለዚህ ጉዳይ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። እንግዲያው ይሖዋ በዘመናችን መንፈሱን የሚጠቀምባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።
መንፈስ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ የሚጫወተው ሚና
11. መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? ከዚህ መንፈስ ጋር እንደምንተባበር ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?
11 አንደኛ፣ መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖርና ከዓላማው ፍጻሜ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ መሆን ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።) አንዳንዶች፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት እንደ ዝሙት፣ ምንዝርና ግብረ ሰዶም ያሉ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። እነዚህ ሰዎች ኃጢአት እንዲወለድ ምክንያት የሚሆኑ ሥር የሰደዱ መጥፎ ምኞቶች ነበሯቸው። (ያዕ. 1:14, 15) ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች ‘ታጥበው ነጽተዋል፤’ በሌላ አባባል በሕይወታቸው ውስጥ አምላክን ለማስደሰት የሚያስፈልጓቸውን ለውጦች አድርገዋል። አምላክን የሚወድ አንድ ሰው መጥፎ ምኞቱ የሚያሳድርበትን ተጽዕኖ በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም ምን ሊረዳው ይችላል? ‘የአምላካችን መንፈስ’ በማለት 1 ቆሮንቶስ 6:11 መልሱን ይሰጠናል። እኛም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ ይህ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዲኖረው እንደምንፈልግ እናሳያለን።
12. (ሀ) ሕዝቅኤል ባየው ራእይ መሠረት ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው? (ለ) ከመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር ተስማምተን እንደምንኖር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
12 ሁለተኛ፣ ይሖዋ ድርጅቱን በሚፈልገው መንገድ እንዲሄድ ለመምራት በመንፈሱ ይጠቀማል። ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል፣ ምንም ነገር ሳያግደው የይሖዋን ዓላማ ለማስፈጸም ወደፊት እየገሰገሰ ባለ ሠረገላ ተመስሏል። ይህ ሠረገላ አንድን አቅጣጫ ተከትሎ እንዲሄድ የሚያደርገው ምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ ነው። (ሕዝ. 1:20, 21) የይሖዋ ድርጅት አንደኛው በሰማይ ሌላው በምድር የሚገኙ ሁለት ክፍሎች እንዳሉት እናስታውስ። ሰማያዊውን ክፍል የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ከሆነ ምድራዊውንም ክፍል የሚመራው ይኸው መንፈስ መሆን አለበት። የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል የሚሰጠውን መመሪያ በታማኝነት በመታዘዝ ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል እንደምንጓዝና ከመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር ተስማምተን እንደምንኖር እናሳያለን።—ዕብ. 13:17
13, 14. (ሀ) ኢየሱስ የጠቀሰው “ይህ ትውልድ” የሚለው አባባል እነማንን ያመለክታል? (ለ) ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመግለጥ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚጠቀም የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር። (“እየጨመረ ከሚሄደው ብርሃን ጋር እኩል እየተጓዝክ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
13 ሦስተኛ፣ ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመግለጥ በመንፈስ ቅዱስ ይጠቀማል። (ምሳሌ 4:18) “ታማኝና ልባም ባሪያ” እየጨመረ የሚሄደውን ብርሃን ለሌሎች ለመግለጥ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በዋነኝነት ሲጠቀም ቆይቷል። (ማቴ. 24:45) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የጠቀሰውን “ይህ ትውልድ” የሚለውን አባባል በተመለከተ ያገኘነውን ማስተዋል እንመልከት። (ማቴዎስ 24:32-34ን አንብብ።) ኢየሱስ የጠቀሰው ስለ የትኛው ትውልድ ነው? “የክርስቶስ መገኘት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?” በሚል ጭብጥ በወጣው የጥናት ርዕስ ላይ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡ ደቀ መዛሙርቱን እንጂ ክፉዎችን ማመልከቱ እንዳልሆነ ተብራርቶ ነበር።a ምልክቱን ከማየት አልፈው ትርጉሙን የሚያስተውሉት ይኸውም ኢየሱስ “ደጃፍ ላይ እንደቀረበ” የሚረዱት በመጀመሪያው መቶ ዘመንና በዘመናችን ያሉት የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ናቸው።
14 ይህ ማብራሪያ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? “ይህ ትውልድ” ምን ያህል የጊዜ ርዝመት እንዳለው በትክክል ማወቅ ባንችልም “ትውልድ” የሚለውን ቃል በተመለከተ ልብ ልንላቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ፦ “ትውልድ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሆኖም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በሕይወት የኖሩ ሰዎችን ነው፤ ለምሳሌ አባት በሕይወት እያለ ልጅ ከተወለደ ወይም አያት በሕይወት እያለ የልጅ ልጅ ከመጣ ሁሉም በአንድ ትውልድ ውስጥ ይጠቃለላሉ። የአንድ ትውልድ የጊዜ ርዝመት በጣም ረጅም አይደለም፤ መጨረሻም አለው። (ዘፀ. 1:6) ታዲያ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል በ1914 ምልክቱ መታየት ሲጀምር የተመለከቱት ቅቡዓን ሞተው ከማለቃቸው በፊት፣ እነዚህ ቅቡዓን ታላቁ መከራ ሲጀምር ከሚመለከቱት ቅቡዓን ጋር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተመሳሳይ ወቅት ላይ በሕይወት እንደሚኖሩ ማመልከቱ ነው። ያ ትውልድ መጀመሪያ እንደነበረው ሁሉ መጨረሻም እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም። የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች መፈጸማቸው ታላቁ መከራ ቅርብ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። የጥድፊያ ስሜታችንን ጠብቀን በመኖር እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን በመጠበቅ በየጊዜው እየጨመረ ከሚሄደው የእውነት ብርሃን ጋር እኩል እንደምንራመድና የአምላክ መንፈስ የሚሰጠውን አመራር እንደምንከተል እናሳያለን።—ማር. 13:37
15. ምሥራቹን እንድናውጅ ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
15 አራተኛ፣ መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን እንድናውጅ ኃይል ይሰጠናል። (ሥራ 1:8) ይህ ባይሆን ኖሮ ምሥራቹ በምድር ዙሪያ እንዴት ሊሰበክ ይችል ነበር? እስቲ አስበው፦ አንዳንዶች በጣም ስለሚፈሩ ወይም ዓይናፋር ስለሆኑ ‘በምንም ዓይነት ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ መስበክ አልችልም!’ ብለው ያሰቡበት ወቅት ነበር፤ አንተም እንደዚህ የተሰማህ ጊዜ ይኖር ይሆናል። ይሁንና አሁን በዚህ ሥራ በቅንዓት ትካፈላለህ።b ታማኝ የሆኑ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ተቃውሞ ወይም ስደት ሳይበግራቸው በስብከቱ ሥራ መካፈላቸውን ቀጥለዋል። የሚያጋጥሙንን ከባድ እንቅፋቶች እንድንወጣና በራሳችን ብርታት ፈጽሞ ልናደርጋቸው የማንችላቸውን ነገሮች እንድናከናውን ኃይል ሊሰጠን የሚችለው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ብቻ ነው። (ሚክ. 3:8፤ ማቴ. 17:20) በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ከዚህ መንፈስ ጋር እንደምንተባበር እናሳያለን።
መንፈስ ቅዱስ ወደፊት የሚጫወተው ሚና
16. በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ወደፊትም ይሖዋ ዓላማውን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ቅዱስ መንፈሱን አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ይጠቀምበታል። እስቲ መጀመሪያ ጥበቃ በማድረግ ረገድ እንዴት እንደሚጠቀምበት እንመልከት። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ በጥንት ዘመን ለአንዳንድ ግለሰቦችም ሆነ ለእስራኤል ብሔር ጥበቃ ለማድረግ በመንፈሱ ተጠቅሟል። በመሆኑም ይሖዋ እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ ወቅት ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ያንኑ ኃያል መንፈስ ይጠቀማል ብለን ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። በዚያ ወቅት ይሖዋ የሚንከባከበን እንዴት እንደሆነ መገመት አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ከእይታው ሊሰወሩ ወይም መንፈስ ቅዱስ የማይደርስበት ቦታ ሊሆኑ ፈጽሞ እንደማይችሉ ስለምናውቅ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን።—2 ዜና 16:9፤ መዝ. 139:7-12
17. ይሖዋ በአዲስ ዓለም ውስጥ መንፈስ ቅዱሱን የሚጠቀመው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ መንፈስ ቅዱሱን የሚጠቀመው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ የሚከፈቱት አዳዲስ ጥቅልሎች ሲዘጋጁ የአምላክ መንፈስ ድርሻ ይኖረዋል። (ራእይ 20:12) እነዚህ ጥቅልሎች በውስጣቸው የሚይዙት ምን ይሆን? ይሖዋ በሺው ዓመት ወቅት ከእኛ የሚጠብቅብንን ነገር በዝርዝር የሚይዙ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ጥቅልሎች ምን እንደያዙ ለመመርመር አትጓጓም? ይህንን አዲስ ዓለም በጉጉት እንጠባበቃለን። ይሖዋ ለምድርና በእሷ ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በሚፈጽምበት በዚያ አስደሳች ጊዜ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው።
18. ቁርጥ ውሳኔህ ምን መሆን አለበት?
18 ይሖዋ፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን ኃይል ይኸውም ቅዱስ መንፈሱን ስለሚጠቀም ዓላማው ወደ ፍጻሜ እንደሚደርስ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ይህ ዓላማ በሚፈጸምበት ጊዜ አንተም ጥቅም ታገኛለህ። እንግዲያው ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህ አጥብቀህ መለመን እንዲሁም ከመንፈሱ አመራር ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን። (ሉቃስ 11:13) እንዲህ ካደረግህ ይሖዋ ለሰው ልጆች በነበረው ዓላማ መሠረት ይኸውም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖርሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የየካቲት 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-25ን ተመልከት።
b ዓይናፋርነት በጣም የሚያጠቃው ሰው ይህንን ችግር አሸንፎ በአገልግሎቱ በቅንዓት መካፈል እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ለማግኘት የመስከረም 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19ን ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ይሖዋ ዓላማው ወደ ፍጻሜው እንዲገሰግስ ለማድረግ በጥንት ዘመን በቅዱስ መንፈሱ የተጠቀመው በየትኞቹ መንገዶች ነበር?
• ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በመንፈሱ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
• ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ወደፊት በመንፈሱ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥጥን]
እየጨመረ ከሚሄደው ብርሃን ጋር እኩል እየተጓዝክ ነው?
ይሖዋ ለሕዝቡ ብርሃኑን መፈንጠቁን ቀጥሏል። በመጠበቂያ ግንብ ላይ ከወጡት ማስተካከያዎች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
▪ ኢየሱስ ስለ እርሾ የተናገረው ምሳሌ ከመንፈሳዊ እድገት ጋር በተያያዘ በአዎንታዊ መልኩ የተብራራው እንዴት ነው? (ማቴ. 13:33)—ሐምሌ 15, 2008 ገጽ 19,20
▪ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች መጠራት የሚያበቃው መቼ ነው?—ግንቦት 1, 2007 ገጽ 30,31
▪ ይሖዋን “በመንፈስ” ማምለክ ማለት ምን ማለት ነው? (ዮሐ. 4:24)—ሐምሌ 15, 2002 ገጽ 15
▪ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡት በየትኛው አደባባይ ላይ ሆነው ነው? (ራእይ 7:15)—ግንቦት 1, 2002 ገጽ 30,31
▪ በጎቹን ከፍየሎቹ የመለየቱ ሥራ የሚከናወነው መቼ ነው? (ማቴ. 25:31-33)—ጥቅምት 15, 1995 ከገጽ 18-28