የአንባብያን ጥያቄዎች
አንዲት የታመነች ክርስቲያን ሚስት የትዳር ጓደኛዋ የሚያቀርብላትን የፍቺ ጥያቄ መቃወም የሚኖርባት እስከ ምን ድረስ ነው?
የመጀመሪያው ሰብዓዊ ጋብቻ ሲመሠረት አምላክ ባልና ሚስት አንድ ላይ ‘መጣበቅ’ እንዳለባቸው ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18-24) ከጊዜ በኋላ ሰዎች ፍጽምናቸውን ማጣታቸው በብዙ ትዳሮች ውስጥ ችግር አስከትሏል። ይሁን እንጂ የአምላክ ፍላጎት ዛሬም ቢሆን የትዳር ጓደኛሞች አንድ ላይ ተጣብቀው መኖር እንደሚገባቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፣ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፣ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፣ እኔ ግን አላዝም፣ ጌታ እንጂ።”—1 ቆሮንቶስ 7:10, 11
ከእነዚህ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች መካከል አንደኛው የትዳር ጓደኛ ለመለያየት ሊወስን የሚችልበት ጊዜ ይኖራል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ አንዱ የትዳር ጓደኛ ቢለይ ሁለቱም ‘ሳያገቡ መኖር እንዳለባቸው’ ተናግሯል። ለምን? አንደኛው የትዳር ጓደኛ ተለየ እንጂ በአምላክ ፊት ሁለቱም አንድ ናቸው። ጳውሎስ ይህንን ሊል የቻለው ኢየሱስ ትዳርን በማስመልከት ለክርስቲያኖች ካወጣው የአቋም ደረጃ በመነሳት ነው። “ያለ ዝሙት [በግሪክኛ ፖርኒያ ] ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፣ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል።” (ማቴዎስ 19:9) አንድን ትዳር ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ለማፍረስ መሠረት የሚሆነው ብቸኛ ምክንያት “ዝሙት” ማለትም የፆታ ብልግና ነው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በጳውሎስ አገላለጽ መሠረት ሁለቱም ባለ ትዳሮች ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት አልፈጸሙም። በመሆኑም ባልየው ወይም ሚስትየው በመለየታቸው ብቻ ጋብቻው በአምላክ ዓይን አይፈርስም።
ከዚያም ጳውሎስ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የማያምን የትዳር ጓደኛ ቢኖረው ሊፈጠር ስለሚችል ሁኔታ ጠቅሷል። ጳውሎስ የሰጠውን መመሪያ ልብ በል:- “የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።” (1 ቆሮንቶስ 7:12-16) አንዲት የታመነች ሚስት የማያምን ባሏ ትቷት ቢሄድ አልፎ ተርፎም በሕጋዊ መንገድ ፍቺ እንዲፈጽሙ ቢጠይቃት ምን ማድረግ ትችላለች?
እንዲለያት አትፈልግ ይሆናል። አሁንም ትወደውና የጋራ ስሜታዊና ፆታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንዲሁም እርሷም ሆነች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቿ (ካሉ) የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ድጋፍ ትገነዘብ ይሆናል። በተጨማሪም አንድ ቀን ባሏ አማኝ ሆኖ ሊድን እንደሚችል ተስፋ ታደርግ ይሆናል። ይሁንና ትዳሩ እንዲፈርስ (ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ምክንያት) አንዳንድ እርምጃዎችን ከወሰደ ጳውሎስ እንደጻፈው ሚስትየው ‘እንዲለይ’ ልትተወው ትችላለች። አንድ የሚያምን ባልም አምላክ ለትዳር ያለውን አመለካከት ችላ በማለት ለመለየት ቆርጦ ከተነሣ ሁኔታው ተመሳሳይ ይሆናል።
ይሁንና እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር የራሷንም ሆነ የልጆቿን ደህንነት ማስጠበቁ አስፈላጊ ሆኖ ይታያት ይሆናል። እንዴት? ለምትወዳቸው ልጆቿ የእናትነት ፍቅሯን መለገሷን ለመቀጠል፣ ሥነ ምግባራዊ ሥልጠና ለመስጠትና ግሩም በሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተውን እምነት በውስጣቸው ለመትከል የሚያስችል አጋጣሚ ለማግኘት ስትል ልጆቿን የማሳደግ መብት እንዲኖራት ትፈልግ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ፍቺው መብቶቿን የሚያሳጣት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ከልጆቿ ጋር የመገናኘት መብቷን ለማስጠበቅ እንዲሁም ባሏ ትቶት የሄደውን ቤተሰቡን የመደገፍ ግዴታ እንዳለበት ለማረጋገጥ ስትል ጉዳዩን በባለ ሥልጣናት ፊት በአግባቡ ለማቅረብ አንዳንድ እርምጃዎችን ትወስድ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች የፍቺ ጥያቄን የምትቃወም ሴት ባሏ ባቀረበው የፍቺ ጥያቄ ሳትስማማም ልጆችን ማሳደግንና የገንዘብ ድጋፍ ማግኘትን በተመለከተ አንዳንድ ዝግጅቶችን በሚዘረዝር ሕጋዊ ሰነድ ላይ መፈረም ትችላለች። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የሰነዱ ስምምነት የተቀመጠበት መንገድ በፍቺው እንደተስማማች የሚጠቁም ነው። በመሆኑም ባሏ ምንዝር በመፈጸም በደለኛ ሆኖ ከነበረ ሚስትየው በዚህ ሰነድ ላይ መፈረሟ ባሏን እንደማትፈልገው እንዳረጋገጠች ይቆጠራል።
ፍቺው የተፈጸመው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ኖሮ መሆን አለመሆኑን የመሳሰሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የአካባቢው ሰዎችም ሆኑ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች አያውቁም። በመሆኑም ነገሮቹ ያን ያህል ገፍተው ከመሄዳቸው በፊት ሚስትየው ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹና በጉባኤ ውስጥ ላለ ሌላ አንድ ሽማግሌ ስለጉዳዩ ማሳወቋ (በጽሑፍ ቢሆን ይመረጣል) ጥሩ ይሆናል። ይህን ማድረጓ ያን ጊዜም ይሁን ቆይቶ ጥያቄ ቢነሳ እንኳ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር ይኖራቸዋል።
አሁን ኢየሱስ ወደ ተናገረው ሐሳብ እንመለስ:- “ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” አንድ ባል የፆታ ብልግና በመፈጸሙ በደለኛ ሆኖ ሳለ ከሚስቱ ጋር በትዳሩ መቀጠል ቢፈልግ ሚስቱ (በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ንጹሕ ወገን) በደሉን ይቅር ብላው ሳይከላከሉ አንድ ላይ ለመኖር ወይም አልፈልግም ለማለት መምረጥ ይኖርባታል። ይቅርታ አድርጋለት ከሕጋዊ ባሏ ጋር ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኗ የሥነ ምግባር እድፈት አይሆንባትም።—ሆሴዕ 1:1-3፤ 3:1-3
የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመው ባል ፍቺ ለመፈጸም በሚፈልግበት ጊዜ እንኳ ሚስቱ አብሮኝ ይኖራል በሚል ተስፋ ይቅርታ ልታደርግለት ፈቃደኛ ትሆን ይሆናል። ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በሕሊናዋ ተጠቅማ የፍቺ ጥያቄውን መቃወም አለመቃወም የራሷ ውሳኔ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች የፍቺ ጥያቄውን የምትቃወም ሚስት በፍቺ ጥያቄው መስማማቷን ሳትጠቅስ ልጆቹን የማሳደግ መብትና የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ የሚያስችል ሰነድ መፈረም የምትችልበት ሁኔታ ይኖራል። እንዲህ ባለው ሰነድ ላይ መፈረሟ ብቻ እርሱን አልፈልግም እንዳለች አያስቆጥራትም። ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች ደግሞ አንዲት ሚስት የፍቺ ጥያቄውን ተቃውማ በምትቀርብበት ጊዜ በፍቺው እንደምትስማማ የሚጠቁም ሰነድ እንድትፈርም ልትጠየቅ ትችላለች። እንዲህ ያለውን ሰነድ መፈረሟ በደለኛውን ባሏን አልፈልገውም እንዳለች በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጥ ይሆናል።
በዚህም ጊዜ ቢሆን ሚስትየው ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ለማስቀረት ምን እርምጃዎች እየተወሰዱ እንዳሉና ይህ የሚደረገው ምን በማሰብ እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ጉባኤውን ለሚወክሉት ወንዶች መስጠቷ ጥሩ ይሆናል። ይቅር ልትለውና በሚስትነት አብራው ልትኖር ፈቃደኛ መሆኗን ለባሏ እንደነገረችው ልትጠቅስ ትችላለች። ይህም ፍቺው የሚፈጸመው ያለ ፈቃዷ እንደሆነ እንዲሁም ባሏን እንደማትፈልገው አለመግለጿን ይልቁንም ይቅር ልትለው ፈቃደኛ እንደነበረች የሚያሳይ ይሆናል። ይቅር ልትለውና ከእርሱ ጋር በትዳር ለመቀጠል ፈቃደኛ እንደነበረች በዚህ መንገድ ግልጽ ካደረገች በኋላ ገንዘብ ነክ እና/ወይም ልጆችን የማሳደጉ ጉዳይ እንዴት እልባት እንደሚያገኝ ብቻ በሚጠቁም ሰነድ ላይ መፈረሟ ባሏን እንደማትፈልገው የሚያረጋግጥ አይሆንም።a
ፍቺው ከተፈጸመም በኋላ ይቅር ልትለው ፈቃደኛ መሆኗን ስላረጋገጠች እርሷም ሆነች ባሏ ሌላ ለማግባት ነፃ አይሆኑም። ታማኝ የሆነችው ሚስቱ የዘረጋችው የይቅርታ እጅ ምላሽ በማጣቱ ምክንያት ከጊዜ በኋላ በፈጸመው ብልግና ምክንያት አልፈልገውም የሚል ውሳኔ ላይ ከደረሰች ሁለቱም ነፃ ይሆናሉ። ኢየሱስ ነፃ የሆነው ወገን እንዲህ ያለ ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው ጠቅሷል።—ማቴዎስ 5:32፤ 19:9፤ ሉቃስ 16:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሕጋዊ አሠራሮችና ሰነዶች ከቦታ ወደ ቦታ ይለያያሉ። ከፊርማው በፊት በሕጋዊ ሰነዱ ላይ የሰፈረው የፍቺ ስምምነት በጥንቃቄ ሊመረመር ይገባል። አንድ ታማኝ የሆነች ሚስት (ወይም ባል) የትዳር ጓደኛዋ ያቀረበውን የፍቺ ጥያቄ እንደማትቃወም በሚጠቁም ሰነድ ላይ ከፈረመች የትዳር ጓደኛዋን እንደማትፈልገው ያረጋገጠች ያህል ይሆናል።—ማቴዎስ 5:37