የሥጋ መውጊያቸውን ተቋቁመው ኖረዋል
“የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም [“አለማቋረጥ፣” NW ] የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ”—2 ቆሮንቶስ 12:7
1. በዛሬው ጊዜ ሰዎች የገጠሟቸው አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ከአንድ ዓይነት ፈተና ጋር እየታገልህ ነውን? ከሆነ ፈተና የሚደርስብህ አንተ ብቻ አይደለህም። በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ የሚኖሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ከባድ ተቃውሞ፣ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ሕመም፣ የገንዘብ እጦት፣ የስሜት መቃወስ፣ የሚወድዱትን ሰው በሞት ማጣትና ሌሎች ችግሮች ከሚያስከትሏቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ጋር ይታገላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በአንዳንድ አገሮች የምግብ እጥረትና ጦርነት የብዙ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል።
2, 3. እንደ መውጊያ ያሉ ችግሮች ምን ዓይነት አፍራሽ ስሜት ሊያሳድሩብን ይችላሉ? ይህስ አደገኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
2 እንደነዚህ ያሉት ችግሮች በተለይ ደግሞ ተደራርበው በሚመጡበት ጊዜ የአንድን ሰው ስሜት በጣም ሊጎዱት ይችላሉ። “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” የሚሉትን በምሳሌ 24:10 ላይ የሚገኙትን ቃላት ልብ በል። አዎን፣ ፈተና የሚያስከትለው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ጉልበታችንን ሊያሟጥጥብንና እስከ መጨረሻው ለመጽናት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያዳክምብን ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
3 ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አስተሳሰባችንን ሊያዛባብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የደረሰብንን መከራ አጋንነን እንድንመለከት ሊያደርገንና ከፍተኛ ትካዜ ውስጥ ሊከተን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች “ይህ ሁሉ እንዲደርስብኝ ለምን ትፈቅዳለህ?” በማለት ወደ አምላክ እንዲጮኹ ሊያደርጋቸው ይችላል። እንዲህ ያለው አፍራሽ አስተሳሰብ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሥር ከሰደደ ደስታውንና የመተማመን ስሜቱን ሊሸረሽርበት ይችላል። አንድ የአምላክ አገልጋይ በጣም ተስፋ ሊቆርጥና “መልካሙን የእምነት ገድል” መጋደሉን እስከማቆም ሊደርስ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:12
4, 5. በአንዳንድ ችግሮቻችን ረገድ ሰይጣን እጁን የሚያስገባው እንዴት ነው? ሆኖም ምን ትምክህት ሊያድርብን ይችላል?
4 ይሖዋ አምላክ ፈተና እንደማያመጣብን የታወቀ ነው። (ያዕቆብ 1:13) ለአምላክ ታማኝ ለመሆን የምናደርገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ ፈተና ሊያስከትልብን ይችላል። እንዲያውም ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ የቀንደኛ ጠላቱ የሰይጣን ዲያብሎስ ዒላማ ይሆናሉ። ክፉው “የዚህ ዓለም አምላክ” በቀረው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይሖዋን የሚወድድ ማንኛውም ሰው የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ወደኋላ እንዲል ጥረት በማድረግ ላይ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ላይ የቻለውን ያህል መከራ ለማምጣት ይጥራል። (1 ጴጥሮስ 5:9) እርግጥ ነው የሚደርሱብንን ችግሮች በሙሉ የሚያመጣው ሰይጣን ነው ማለት አይደለም። ሆኖም እኛን ለማዳከም እነዚህን ችግሮች እንደ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይችላል።
5 ሰይጣንም ሆነ የሚጠቀምበት መሣሪያ ምንም ያህል የሚያስፈራ ቢሆን ልናሸንፈው እንችላለን! በዚህ ረገድ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ምክንያቱም ስለ እኛ ሆኖ የሚዋጋው ይሖዋ አምላክ ነው። ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች በሚመለከት አምላክ ለአገልጋዮቹ በቂ እውቀት ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) እንዲያውም የአምላክ ቃል በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን መከራዎች በዝርዝር ይነግረናል። በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ የደረሰውን መከራ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሥጋ መውጊያ’ በማለት ይጠራዋል። ለምን? የአምላክ ቃል ይህን ሐረግ እንዴት እንደሚፈታው እንመልከት። ከዚያም ፈተናዎችን ለማሸነፍ የይሖዋ እርዳታ የሚያስፈልገን እኛ ብቻ እንዳልሆንን እንመለከታለን።
ፈተናዎች እንደ መውጊያ የተቆጠሩት ለምንድን ነው?
6. ጳውሎስ ‘የሥጋ መውጊያ’ ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? መውጊያው ምን ሊሆን ይችላል?
6 ከባድ ፈተና የደረሰበት ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ የሚከተለውን ጽፏል:- “የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።” (2 ቆሮንቶስ 12:7) ጳውሎስ በሥጋው ላይ የነበረው መውጊያ ምንድን ነው? እንደ እሾህ ያለ አንድ ሹል ነገር ቆዳን አልፎ ሰውነት ውስጥ ሲገባ እንደሚያም የታወቀ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ የሰፈረው ምሳሌያዊ አነጋገር በጳውሎስ ላይ አካላዊም ይሁን ስሜታዊ ወይም ሁለቱንም ዓይነት ሕመም ያስከተለ ነገር እንዳለ ያመለክታል። ምናልባት ጳውሎስ የማየት ወይም ሌላ ዓይነት አካላዊ እክል ኖሮበት ሊሆን ይችላል። ወይም መውጊያው የጳውሎስን ሐዋርያነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉትንና የስብከቱንና የማስተማር ሥራውን ጥያቄ ላይ የጣሉትን ግለሰቦች የሚጨምር ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 10:10-12፤ 11:5, 6, 13) መውጊያው ምንም ይሁን ምን አብሮት የኖረ ከመሆኑም በላይ ሊወገድ የሚችል አልነበረም።
7, 8. (ሀ) ‘አለማቋረጥ መጎሰም’ የሚለው መግለጫ ምን ያመለክታል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ የሚያሠቃየንን መውጊያ ተቋቁመን መኖራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 መውጊያው ጳውሎስን አለማቋረጥ ይጎስመው እንደነበር ልብ በል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛው ግስ “የጣት መጋጠሚያ አንጓ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ ቃል በማቴዎስ 26:67 ላይ ቃል በቃል እንዲሁም 1 ቆሮንቶስ 4:11 ላይ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ቃሉ በቡጢ የመመታትን ሐሳብ ያስተላልፋል። ሰይጣን ለይሖዋና ለአገልጋዮቹ ካለው የከረረ ጥላቻ አንጻር ጳውሎስ በመውጊያው አለማቋረጥ መጎሰሙ ዲያብሎስን እንዲደሰት እንዳደረገው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ዛሬም በተመሳሳይ ሰይጣን በሥጋ መውጊያ እየተሠቃየን ስንኖር ደስ ይለዋል።
8 ስለዚህ እኛም እንደ ጳውሎስ እነዚህን መውጊያዎች እንዴት መቋቋም እንደምንችል ማወቅ ይኖርብናል። ሕልውናችን የተመካው እንዲህ በማድረጋችን ላይ ነው! ይሖዋ እንደ መውጊያ ያሉ ችግሮች ፈጽሞ በማይኖሩበት በእርሱ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ሊያኖረን ይፈልጋል። ይህን ድንቅ ሽልማት እንድናገኝ ለመርዳት ሲል ይሖዋ የሥጋቸውን መውጊያ ሙሉ በሙሉ ተቋቁመው ያሸነፉ የብዙ ታማኝ አገልጋዮቹን ምሳሌ በቅዱስ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። እነዚህ ሰዎች ልክ እንደ እኛ ፍጹማን ያልሆኑ ተራ ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ ‘እንደ ደመና ያሉ’ ብዙ “ምስክሮች” መካከል የአንዳንዶቹን ታሪክ መመርመራችን ‘በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንድንሮጥ’ ሊረዳን ይችላል። (ዕብራውያን 12:1) በጽናት በተቋቋሟቸው ችግሮች ላይ ማሰላሰላችን ሰይጣን በእኛ ላይ የሚያመጣውን ማንኛውንም ዓይነት መውጊያ መቋቋም እንደምንችል ያለንን እምነት ሊያጠናክርልን ይችላል።
ሜምፊቦስቴን ያሠቃየው መውጊያ
9, 10. (ሀ) ሜምፊቦስቴ በሥጋው ላይ መውጊያ የደረሰበት እንዴት ነው? (ለ) ንጉሥ ዳዊት ለሜምፊቦስቴ ምን ደግነት አደረገለት? እኛስ ዳዊትን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
9 የዳዊት ወዳጅ የዮናታን ልጅ የሆነውን ሜምፊቦስቴን ተመልከት። ሜምፊቦስቴ ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ ዮናታንና አያቱ ሳኦል እንደተገደሉ የሚገልጽ ወሬ መጣ። የልጁ ሞግዚት በጣም ተደናገጠች። “አዝላው . . . ፈጥናም ስትሸሽ ወድቆ ሽባ ሆነ።” (2 ሳሙኤል 4:4) ሜምፊቦስቴ በዚህ ጊዜ የደረሰበት ጉዳት በቀሪው የሕይወት ዘመኑ በጽናት ሊቋቋመው የሚገባ መውጊያ ሆኖበት እንደነበር አያጠራጥርም።
10 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ዳዊት ለዮናታን ከነበረው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ለሜምፊቦስቴ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቶታል። ዳዊት የሳኦልን ንብረት በጠቅላላ መለሰለትና ሲባ የተባለ የሳኦል አገልጋይ መሬቱን እንዲያርስለት ዝግጅት አደረገ። በተጨማሪም ዳዊት ለሜምፊቦስቴ “ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው።” (2 ሳሙኤል 9:6-10) ዳዊት ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ሜምፊቦስቴን እንዳጽናናውና የደረሰበት ጉዳት ያስከተለበትን ሥቃይ በተወሰነ ደረጃ እንዳቀለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! እኛም ከሥጋ መውጊያ ጋር እየታገሉ ላሉት ደግነት ማሳየት ይገባናል።
11. ሲባ ሜምፊቦስቴን በማስመልከት ምን ተናገረ? ሆኖም የተናገረው ውሸት መሆኑን እንዴት እናውቃለን? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
11 ከጊዜ በኋላ ሜምፊቦስቴ ከሌላ የሥጋ መውጊያ ጋር መታገል አስፈልጎት ነበር። ንጉሥ ዳዊት ልጁ አቤሴሎም በእርሱ ላይ በማመፁ ምክንያት ከኢየሩሳሌም ሸሽቶ ሳለ አገልጋዩ ሲባ በንጉሡ ፊት የሜምፊቦስቴን ስም አጠፋ። ሜምፊቦስቴ ታማኝነቱን እንዳጎደለና ንግሥና አገኛለሁ በሚል በኢየሩሳሌም እንደቀረ ሲባ ተናገረ።a ዳዊት የሲባን የሐሰት ወሬ በማመን የሜምፊቦስቴን ንብረት በሙሉ በመውሰድ ለዚህ ውሸታም ሰው ሰጠው።—2 ሳሙኤል 16:1-4
12. ሜምፊቦስቴ ለደረሰበት ሁኔታ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለእኛ ግሩም ምሳሌ የሚሆነውስ እንዴት ነው?
12 ይሁን እንጂ በመጨረሻ ሜምፊቦስቴ ከዳዊት ጋር በተገናኘ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነገረው። ዳዊትን ለመገናኘት ይዘጋጅ በነበረበት ጊዜ ሲባ እርሱን ወክሎ እንደሚሄድ በመናገር እንዳታለለው ገለጸ። ታዲያ ዳዊት የተፈጸመውን ስህተት አስተካከለ? በከፊል አስተካክሏል። ንብረቱን ሁለቱም እንዲካፈሉት አደረገ። በዚህ ወቅት ሜምፊቦስቴ የገጠመው ሁኔታ በሥጋው ላይ ሌላ ተጨማሪ መውጊያ ሊሆን የሚችል ነበር። ታዲያ በገጠመው ሁኔታ እጅግ ቅር ተሰኘ? ትክክለኛ ፍርድ እንዳልተሰጠው በመግለጽ የዳዊትን ውሳኔ ተቃወመ? በጭራሽ፣ የንጉሡን ውሳኔ በትሕትና ተቀብሏል። የእስራኤል ሕጋዊ ንጉሥ በሰላም መመለሱ ያስደሰተው መሆኑን በመግለጽ መልካም በሆነው ገጽታ ላይ ትኩረት አድርጓል። በእርግጥም ሜምፊቦስቴ የነበረበትን አካላዊ እክል፣ የተነገረበትን ሐሜትና የደረሰበትን ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ ተቋቁሞ በመኖር ግሩም ምሳሌ ትቷል።—2 ሳሙኤል 19:24-30
ነህምያ የደረሰበትን ፈተና ተቋቋመ
13, 14. ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ዳግመኛ ለመሥራት በተመለሰ ጊዜ የትኞቹን መውጊያዎች በጽናት መቋቋም አስፈልጎት ነበር?
13 ነህምያ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ቅጥር አልባ ወደሆነችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ የተቋቋመውን ምሳሌያዊ መውጊያ አስብ። ከተማዋ ለጥቃት ተጋልጣ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደ ከተማዋ ተመልሰው የሰፈሩት አይሁዳውያንም ባልተደራጀ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ተስፋ ቆርጠውና በይሖዋ ፊትም ረክሰው አገኛቸው። ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመገንባት የሚያስችል ፈቃድ ከንጉሥ አርጤክስስ ያገኘ ቢሆንም እንኳ ተልዕኮው በከተማዋ አቅራቢያ በነበሩት ገዥዎች ዘንድ የተጠላ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። “ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።”—ነህምያ 2:10
14 እነዚህ ባዕዳን ተቃዋሚዎች የነህምያን ሥራ ለማስተጓጎል ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። እርሱን ተስፋ ለማስቆረጥ ሰላዮች መላክን ጨምሮ ይሰነዝሩ የነበረው ዛቻ፣ ይናገሩ የነበረው ውሸትና ሐሜት እንዲሁም ማስፈራሪያ ሥጋውን አለማቋረጥ እንደሚያሳምም መውጊያ ሆኖበት መሆን አለበት። ጠላቶቹ በሸረቡት የተንኮል ዘዴ ተሸንፎ ይሆን? በጭራሽ! ሙሉ በሙሉ የታመነው በአምላክ ላይ ስለነበር እጁን አላላላም። በዚህም የተነሳ የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ዳግመኛ ተገንብተው ባለቁ ጊዜ ይሖዋ ለነህምያ ፍቅራዊ ድጋፍ እንዳደረገለት የሚያረጋግጡ ቋሚ ምሥክሮች ሆነው አገልግለዋል።—ነህምያ 4:1-12፤ 6:1-19
15. ነህምያን በእጅጉ እንዲረበሽ ያደረጉት በአይሁድ መካከል ተፈጥረው የነበሩት ችግሮች ምንድን ናቸው?
15 ነህምያ አለቃ እንደመሆኑ መጠን በአምላክ ሕዝቦች መካከል የተፈጠሩትን በርካታ ችግሮች ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ነበረበት። እነዚህ ችግሮች ሕዝቡ ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ዝምድና ነክተውባቸው ስለነበር ልክ እንደ መውጊያ አሠቃይተውት ነበር። ባለጠጎች ሕዝቡን አራጣ ያስከፍሉ ነበር። ድሃ ወንድሞቻቸውም ዕዳቸውንና የፋርስ መንግሥት የጣለባቸውን ግብር ለመክፈል ሲሉ መሬታቸውን ማስያዝና ልጆቻቸውን ለባርነት መሸጥ ነበረባቸው። (ነህምያ 5:1-10) ብዙ አይሁዶች የሰንበትን ሕግ ይተላለፉ የነበረ ሲሆን ለሌዋውያኑና ለቤተ መቅደሱ ድጋፍ መስጠታቸውን አቁመው ነበር። እንዲሁም አንዳንዶቹ “የአዛጦንንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች” አግብተው ይኖሩ ነበር። ይህ ሁሉ ነህምያን ምን ያህል አሠቃይቶት ይሆን! ይሁን እንጂ እነዚህ መውጊያዎች ሥራውን እርግፍ አድርጎ እንዲተው አላደረጉትም። የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት በቅንዓት የሚደግፍ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። እኛም እንደ ነህምያ ሌሎች የሚያሳዩት ታማኝነት የጎደለው አኗኗር ለይሖዋ ከምናቀርበው የታማኝነት አገልግሎት ዘወር እንዲያደርገን አንፍቀድ።—ነህምያ 13:10-13, 23-27
ታማኝ ሆነው የተገኙ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተቋቁመው ኖረዋል
16-18. በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ችግር ይስሐቅንና ርብቃን፣ ሐናን እንዲሁም ዳዊትንና ሆሴዕን የነካቸው እንዴት ነው?
16 መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መውጊያ ያሉ ሥቃይ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የኖሩ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችንም ይዞልናል። እንደዚህ ካሉት መውጊያዎች መካከል አንደኛው በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ችግር ነው። ሁለቱ የዔሳው ሚስቶች የወላጆቹን “የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።” እንዲያውም ርብቃ በእነዚህ ሚስቶች ምክንያት ሕይወቷን እንደጠላች ተናግራለች። (ዘፍጥረት 26:34, 35፤ 27:46) እንዲሁም ሐናንና በመካንነቷ ምክንያት ጣውንቷ ፍናና እንዴት ‘ታስቆጣትና ታበሳጫት’ እንደነበር አስብ። ምናልባት ሐና ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ እንዲህ ያለው ፌዝ በተደጋጋሚ ተሰንዝሮባት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ፍናና በሌሎች ፊት ማለትም ቤተሰቡ በዓል ለማክበር ወደ ሴሎ በሚወጣበት ጊዜ በወዳጅ ዘመድ ፊት ታበሳጫት ነበር። ይህ ደግሞ መውጊያው በሐና ሥጋ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ወደ ውስጥ የመግፋት ያህል ነው።—1 ሳሙኤል 1:4-7
17 ዳዊት አማቱ ንጉሥ ሳኦል ከፍተኛ ቅናት ይሰማው በነበረበት ጊዜ ያሳለፈውን መከራ አስብ። ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ሲል ዓይንጋዲ በሚባለው ምድረ በዳ በዓለት የተሞሉና አደገኛ የሆኑ ገደላማ ቦታዎችን እየወጣና እየወረደ በዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገድዶ ነበር። ዳዊት በሳኦል ላይ የፈጸመው ምንም መጥፎ ነገር ስላልነበር ይህ ሁኔታ አበሳጭቶት መሆን አለበት። ያም ሆኖ ዳዊት በሳኦል ቅናት ምክንያት ለዓመታት ከቦታ ቦታ እየተንከራተተ ለመኖር ተገድዶ ነበር።—1 ሳሙኤል 24:14, 15፤ ምሳሌ 27:4
18 በነቢዩ ሆሴዕ ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ሚስቱ አመንዝራ ሆነች። ብልሹ ምግባሯ ልቡ ላይ እንደተሰካ መውጊያ እንደሆነበት መገመት አያዳግትም። በዝሙት ሁለት ልጆች በወለደች ጊዜ ሥቃዩ ምንኛ ተባብሶበት ይሆን!—ሆሴዕ 1:2-9
19. ነቢዩ ሚክያስ ምን ስደት ደረሰበት?
19 ሌላው የሥጋ መውጊያ ደግሞ ስደት ነው። ነቢዩ ሚክያስ የደረሰበትን ሁኔታ ተመልከት። ሚክያስ ክፉው ንጉሥ አክዓብ በሐሰት ነቢያት ተከብቦ ሲመለከትና የሚናገሩትን ዓይን ያወጣ ውሸት እንደተቀበለ ሲያይ ጻድቅ ነፍሱ ተጨንቃ መሆን አለበት። ከዚያም ሚክያስ እነዚያ ሁሉ ነቢያት የሚናገሩት ‘በሐሰተኛ መንፈስ’ ተነድተው እንደሆነ ለአክዓብ ሲናገር የእነዚህ አታላዮች መሪ ምን አደረገ? “ሚክያስንም ጉንጩን በጥፊ መታው”! ሬማት ዘገለዓድን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ሁሉ መና ሆኖ እንደሚቀር ይሖዋ ለሰጠው ማስጠንቀቂያ አክዓብ ያሳየው ምላሽ ደግሞ ከዚያ የከፋ ነበር። ሚክያስ እስር ቤት እንዲከተትና የሚሰጠውም ቀለብ እንዲቀነስ አክዓብ አዘዘ። (1 ነገሥት 22:6, 9, 15-17, 23-28) በተጨማሪም ኤርምያስንና ነፍሰ ገዳይ የሆኑት አሳዳጆቹ ያደረሱበትን ሁኔታ አስታውስ።—ኤርምያስ 20:1-9
20. ኑኃሚን ምን መውጊያዎችን በጽናት መቋቋም ነበረባት? የተካሰችውስ እንዴት ነው?
20 የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትም ከፍተኛ ሐዘን የሚያስከትል እንደ ሥጋ መውጊያ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ክስተት ነው። ኑኃሚን ባሏንና ሁለት ልጆቿን በሞት ማጣቷ ያስከተለባትን ከባድ ሐዘን መቋቋም ነበረባት። በሐዘን እንደተደቆሰች ወደ ቤተ ልሔም ተመለሰች። ወዳጆቿ ኑኃሚን ብለው ሳይሆን የደረሰባትን መሪር ሐዘን በሚያንጸባርቅ ስም ማራ ብለው እንዲጠሯት ነገረቻቸው። በመጨረሻ ግን ይሖዋ ከመሲሑ የዘር ሐረግ ጋር የሚያገናኝ የልጅ ልጅ በመስጠት ላሳየችው ጽናት ክሷታል።—ሩት 1:3-5, 19-21፤ 4:13-17፤ ማቴዎስ 1:1, 5
21, 22. ኢዮብ የነበረውን ሁሉ ያጣው እንዴት ነው? ምንስ ምላሽ ሰጠ?
21 ኢዮብ ከብቶቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ የሚወድዳቸው አሥር ልጆቹ በድንገት አሰቃቂ በሆነ መንገድ መሞታቸውን ሲሰማ ምን ያህል በድንጋጤ ተውጦ ሊሆን እንደሚችል አስብ። በድንገት ሰማይ የተከደነበት ያህል ነበር! ኢዮብ ከዚህ ሁሉ መከራ ገና ሳያገግም ሰይጣን በበሽታ መታው። ኢዮብ ከዚህ አደገኛ በሽታ በሕይወት እተርፋለሁ ብሎ አስቦ ላይሆን ይችላል። ሕመሙ ፈጽሞ ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ሆኖበት ስለነበር እረፍት እንዲያገኝ ሞትን ተመኝቶ ነበር።—ኢዮብ 1:13-20፤ 2:7, 8
22 ይህ ሁሉ ሳያንስ ሚስቱ በሐዘንና በጭንቀት ወደ እርሱ ቀርባ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው።” ይህ በሚያሠቃየው ሥጋው ላይ ያረፈ ምንኛ የሚያሳምም መውጊያ ነው! ከዚያም የኢዮብ ሦስት ጓደኞች እርሱን ከማጽናናት ይልቅ በድብቅ ኃጢአት እንደፈጸመና ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት በዚህ ምክንያት እንደሆነ በሐሰት በመናገር ጥቃት ሰነዘሩበት። እንዲህ ያለው የተሳሳተ አስተሳሰባቸው መውጊያው በሥጋው ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ወደ ውስጥ የገፉት ያህል ነው። ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ለምን እንደሚደርስበትም ሆነ ሕይወቱ ከሞት እንደሚተርፍ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም “በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፣ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።” (ኢዮብ 1:22፤ 2:9, 10፤ 3:3፤ 14:13፤ 30:17) ኢዮብ ብዙ መውጊያዎች በአንድ ጊዜ የወጉት ቢሆንም እንኳ ከጽኑ አቋሙ ፍንክች አላለም። ምንኛ የሚያበረታታ ነው!
23. እስከ አሁን የተመለከትናቸው ታማኝ ሰዎች በሥጋቸው ላይ የደረሱባቸውን መውጊያዎች በጽናት ያሸነፉት እንዴት ነው?
23 ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው ምሳሌዎች ለናሙና ያህል የቀረቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችንም ይዟል። እነዚህ ሁሉ ታማኝ አገልጋዮች ከራሳቸው ምሳሌያዊ መውጊያዎች ጋር መታገል አስፈልጓቸው ነበር። የገጠሟቸው ችግሮች የተለያዩ ናቸው! ሆኖም አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። አንዳቸውም ቢሆኑ ለይሖዋ ያቀርቡት የነበረውን አገልግሎት አላቆሙም። ከባድ ሥቃይ የሚያስከትሉ ፈተናዎች እያሉባቸው ይሖዋ በሚሰጣቸው ጥንካሬ ሰይጣንን አሸንፈውታል። እንዴት? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ እኛም በሥጋችን ላይ እንደ መውጊያ ሊሆንብን የሚችለውን ማንኛውንም ነገር እንዴት መቋቋም እንደምንችል ያሳየናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሜምፊቦስቴ አድናቂና ትሑት ሰው ስለነበር ሥልጣን ለማግኘት ሲል እንዲህ ያለ እርምጃ ይወስዳል ብሎ ማመን ያስቸግራል። የአባቱን የዮናታንን የታማኝነት ታሪክ እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ዮናታን የንጉሥ ሳኦል ልጅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ በትህትና አምኖ ተቀብሏል። (1 ሳሙኤል 20:12-17) ዮናታን ፈሪሃ አምላክ የነበረው የሜምፊቦስቴ ወላጅና የዳዊት ታማኝ ወዳጅ እንደመሆኑ መጠን ልጁ ንጉሣዊ ሥልጣን እንዲመኝ አያስተምረውም።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የሚገጥሙን ችግሮች እንደ ሥጋ መውጊያ ሊቆጠሩ የሚችሉት ለምንድን ነው?
• ሜምፊቦስቴ እና ነህምያ መቋቋም የነበረባቸው አንዳንድ የሥጋ መውጊያዎች ምንድን ናቸው?
• የተለያዩ የሥጋ መውጊያዎችን በጽናት ከተቋቋሙት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንተን በተለይ የነካህ የትኛው ነው? ለምንስ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሜምፊቦስቴ የደረሰበትን አካላዊ እክል፣ ሐሜትና ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ መቋቋም ነበረበት
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነህምያ ተቃውሞ ቢደርስበትም ጸንቷል