የያዕቆብ ደብዳቤ
1 የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፣+ በየቦታው ለተበተኑት ለ12ቱ ነገዶች፦
ሰላምታ ይድረሳችሁ!
2 ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤+ 3 ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።+ 4 ይሁንና በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና* እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።+
5 እንግዲህ ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤+ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ* ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤+ ይህም ሰው ይሰጠዋል።+ 6 ሆኖም ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል፤+ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነውና። 7 እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከይሖዋ* አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ የለበትም፤ 8 ይህ ሰው በሁለት ሐሳብ የሚዋልልና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው።+
9 ይሁንና ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በመደረጉ ደስ ይበለው፤*+ 10 እንዲሁም ባለጸጋ የሆነው ዝቅ በመደረጉ+ ደስ ይበለው፤ ምክንያቱም ባለጸጋ ሰው እንደ ሜዳ አበባ ይረግፋል። 11 ፀሐይ ወጥታ በኃይለኛ ሙቀቷ ተክሉን ታጠወልጋለች፤ አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ ባለጸጋ ሰውም ልክ እንደዚሁ በዕለት ተዕለት ተግባሩ ሲዋትት ከስሞ ይጠፋል።+
12 ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤+ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ* እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል።+ 13 ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት “አምላክ እየፈተነኝ ነው” አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም። 14 ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል* ይፈተናል።+ 15 ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል።+
16 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አትታለሉ። 17 መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤+ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት+ ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።+ 18 ፈቃዱ ስለሆነም ከፍጥረታቱ መካከል እኛ እንደ በኩራት እንድንሆን+ በእውነት ቃል አማካኝነት ወለደን።+
19 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን እወቁ፦ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና+ ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት፤+ 20 የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግምና።+ 21 ስለዚህ ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና ክፋትን ሁሉ* አስወግዳችሁ+ እናንተን* ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ።
22 ሆኖም ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ+ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። 23 ማንም ሰው ቃሉን የሚሰማ እንጂ የማያደርገው ከሆነ+ የገዛ ፊቱን በመስተዋት እያየ ካለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 24 ይህ ሰው ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። 25 ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ+ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ነው፤ በሚያደርገውም ነገር ደስተኛ ይሆናል።+
26 አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ* ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ* ከሆነ+ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው። 27 በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ* ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና+ መበለቶችን+ በመከራቸው መርዳት+ እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።+