ምዕራፍ 19
“በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠው . . . የአምላክ ጥበብ”
1, 2. ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባው የትኛው “ቅዱስ ሚስጥር” ነው? ለምንስ?
ሚስጥር የሆነ ነገር ስለሚያጓጓና ትኩረት ስለሚስብ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሚስጥር መያዝ ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “አንድን ጉዳይ መሰወር ለአምላክ ክብሩ ነው” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 25:2) አዎን፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢና ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እሱ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ አንዳንድ ነገሮችን ከሰዎች ሚስጥር አድርጎ የመሰወር መብት አለው።
2 ሆኖም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የገለጸው አንድ አስገራሚና ትኩረት የሚስብ ሚስጥር አለ። ይህም “[የአምላክ ፈቃድ] ቅዱስ ሚስጥር” በመባል ይታወቃል። (ኤፌሶን 1:9) ይህ ቅዱስ ሚስጥር ምን እንደሆነ መረዳትህ የማወቅ ጉጉትህን ከማርካት የበለጠ ጥቅም አለው። ለመዳን የሚያስችል አጋጣሚ የሚከፍትልህ ከመሆኑም በላይ ይህ ነው የማይባለውን የይሖዋ ጥበብ በተወሰነ ደረጃ እንድታስተውል ይረዳሃል።
ደረጃ በደረጃ ተገለጠ
3, 4. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ተስፋ የሚፈነጥቀው እንዴት ነው? “ሚስጥር” የሆነው ነገርስ ምንድን ነው?
3 አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ ይሖዋ ምድር ገነት እንድትሆንና ፍጹም በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ለማድረግ የነበረው ዓላማ የከሸፈ መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ችግሩ እልባት የሚያገኝበትን አቅጣጫ ያስቀመጠው ወዲያውኑ ነው። “በአንተና [በእባቡና] በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ” በማለት ተናግሯል።—ዘፍጥረት 3:15
4 ይህ መግለጫ ግራ የሚያጋባና እንቆቅልሽ ነበር። ሴቲቱ ማን ነች? እባቡ ማን ነው? የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው “ዘር” ማን ነው? አዳምና ሔዋን የራሳቸውን ግምት ከመስጠት በቀር በትክክል የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ሆኖም አምላክ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ ታማኝ ለሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ተስፋ የሚፈነጥቁ ነበሩ። ጽድቅ ድል ማድረጉና የይሖዋ ዓላማ ዳር መድረሱ የማይቀር ነው። ግን እንዴት? ይህ ሚስጥር ነበር! መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሚስጥር ‘በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠ የአምላክ ጥበብ፣ የተሰወረ ጥበብ’ በማለት ይገልጸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:7
5. ይሖዋ ሚስጥሩን ደረጃ በደረጃ የገለጠው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
5 ይሖዋ “ሚስጥርን የሚገልጥ” አምላክ ስለሆነ ከዚህ ሚስጥር ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን መግለጹ አይቀርም። (ዳንኤል 2:28) ሆኖም ይህን የሚያደርገው ደረጃ በደረጃ ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን “እንዴት ነው የተወለድኩት?” ብሎ ቢጠይቀው አባትየው በምን መንገድ እንደሚመልስለት ማሰብ እንችላለን። አስተዋይ የሆነ አባት የሚሰጠው መልስ ከልጁ የመረዳት ችሎታ ጋር የሚመጣጠን ነው። ልጁ እያደገ ሲሄድ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠዋል። በተመሳሳይም ይሖዋ ፈቃዱንና ዓላማውን ለሕዝቦቹ መቼ መግለጽ እንዳለበት ያውቃል።—ምሳሌ 4:18፤ ዳንኤል 12:4
6. (ሀ) ቃል ኪዳን ወይም ውል ለምን ዓላማ ያገለግላል? (ለ) ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ቃል ኪዳን መግባቱ አስገራሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ ይህን ሚስጥር የገለጠው እንዴት ነው? የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን በመግባት ወይም ውሎችን በመዋዋል ነው። ቤት ለመግዛት ወይም ገንዘብ ለማበደር አሊያም ለመበደር ውል የተዋዋልክባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ውል ለስምምነቱ መፈጸም ሕጋዊ ዋስትና ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከሰዎች ጋር እንዲህ ዓይነት ቃል ኪዳን መግባት ወይም ውል መዋዋል ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይሖዋ አንድን ነገር እንደሚፈጽም መናገሩ ብቻ በቂ ዋስትና ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ያም ሆኖ አምላክ በተለያየ ጊዜ፣ የገባው ቃል ሕጋዊ በሆነ ውል የተደገፈ እንዲሆን አድርጓል። እነዚህ ሕጋዊ የሆኑ ውሎች፣ ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።—ዕብራውያን 6:16-18
ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን
7, 8. (ሀ) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ምን ቃል ኪዳን ገባ? ይህስ ቅዱሱ ሚስጥር በተወሰነ ደረጃ እንዲገለጥ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ዘሩ የሚመጣበት የዘር ሐረግ ደረጃ በደረጃ ግልጽ እየሆነ እንዲመጣ ያደረገው እንዴት ነው?
7 የሰው ልጅ ከገነት ከተባረረ ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ ይሖዋ ታማኝ ለሆነው አገልጋዩ ለአብርሃም “[ዘርህን] በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት . . . በእርግጥ አበዛዋለሁ፤ . . . ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ” ሲል ነግሮታል። (ዘፍጥረት 22:17, 18) እዚህ ላይ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ሕጋዊ በሆነ ቃል ኪዳንና በመሐላ አጽንቶታል። (ዘፍጥረት 17:1, 2፤ ዕብራውያን 6:13-15) የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ የሰው ልጆችን ለመባረክ በውል ራሱን ሕጋዊ ግዴታ ውስጥ ማስገባቱ እጅግ የሚያስገርም ነው!
“ዘርህንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት . . . አበዛዋለሁ”
8 ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን፣ ተስፋ የተደረገበት ዘር ሰው ሆኖ እንደሚመጣ ጠቁሟል፤ ምክንያቱም ይህ ዘር የሚመጣው በአብርሃም በኩል ነው። ይሁን እንጂ ዘሩ ማን ነው? ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ዘሩ ከአብርሃም ልጆች መካከል በይስሐቅ በኩል እንደሚመጣ አስታወቀ። ከይስሐቅ ሁለት ልጆች መካከል ደግሞ ያዕቆብ ተመረጠ። (ዘፍጥረት 21:12፤ 28:13, 14) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ያዕቆብ ከአሥራ ሁለት ወንዶች ልጆቹ መካከል አንዱን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢታዊ ቃል ተናገረ፦ “ሴሎ [ወይም “ባለቤት የሆነው፣” የግርጌ ማስታወሻ] እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት ከይሁዳ፣ የአዛዥም በትር ከእግሮቹ መካከል አይወጣም፤ ለእሱም ሕዝቦች ይታዘዙለታል።” (ዘፍጥረት 49:10) ይህ ትንቢት ዘሩ በይሁዳ በኩል እንደሚመጣና ንጉሥ እንደሚሆን የሚጠቁም ነበር።
ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ምን ቃል ኪዳን ገብቷል? ይህ ቃል ኪዳንስ ለሕዝቡ ምን ጥበቃ አድርጓል? (ለ) ሕጉ የሰው ልጆች ቤዛ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳየው እንዴት ነው?
9 በ1513 ዓ.ዓ. ይሖዋ ቅዱሱ ሚስጥር ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን የሚረዳ አንድ ዝግጅት አደረገ። ከአብርሃም ዘሮች ማለትም ከእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገባ። እርግጥ ነው፣ ይህ የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚነቱ አብቅቷል፤ ያም ቢሆን ተስፋ የተደረገበት ዘር እንዲመጣ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። እንዴት? ሦስት መንገዶችን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ ሕጉ ጥበቃ የሚያደርግ ግድግዳ ሆኖ አገልግሏል። (ኤፌሶን 2:14) በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት የጽድቅ ደንቦች፣ እንደ አጥር በመሆን እስራኤላውያን አምላክን ከማያገለግሉት አሕዛብ የተለዩ እንዲሆኑ አድርገዋል። በመሆኑም ይህ ሕግ ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሚመጣበት የዘር ሐረግ እንዳይበረዝ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። መሲሑ ከይሁዳ ነገድ የሚወለድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የእስራኤል ብሔር ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።
10 በሁለተኛ ደረጃ ሕጉ የሰው ዘር ቤዛ እንደሚያስፈልገው በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጹም የሆነውን ይህን ሕግ በተሟላ ሁኔታ ሊጠብቁ እንደማይችሉ በተግባር ታይቷል። በመሆኑም ሕጉ “ቃል የተገባለት ዘር እስኪመጣ ድረስ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ለማድረግ” መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። (ገላትያ 3:19) በሕጉ መሠረት የእንስሳት መሥዋዕት በማቅረብ ጊዜያዊ የሆነ የኃጢአት ስርየት ማግኘት ይቻል ነበር። ይሁንና ጳውሎስ እንደገለጸው “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ [ስለማይችል]” እነዚህ መሥዋዕቶች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥላ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ። (ዕብራውያን 10:1-4) በመሆኑም ይህ ቃል ኪዳን ታማኝ አይሁዳውያንን “ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ [ሞግዚት]” ሆኗል።—ገላትያ 3:24
11. የሕጉ ቃል ኪዳን ለእስራኤል ሕዝብ ምን ልዩ አጋጣሚ ከፍቶ ነበር? ሆኖም ሕዝቡ በብሔር ደረጃ ይህ አጋጣሚ ያመለጠው ለምንድን ነው?
11 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቃል ኪዳኑ የእስራኤል ሕዝብ ታላቅ መብት ሊያገኝ የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍቷል። ይሖዋ ቃል ኪዳኑን እስከጠበቁ ድረስ “የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር” እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል። (ዘፀአት 19:5, 6) በኋላም የሰማያዊው የካህናት መንግሥት የመጀመሪያዎቹ አባላት እንዲሆኑ የተመረጡት ሰዎች በሥጋ እስራኤላውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ የእስራኤል ሕዝብ በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ በማመፁና መሲሐዊውን ዘር አልቀበልም በማለቱ ይህን መብት አጥቷል። ታዲያ የካህናት መንግሥቱን አባላት ቁጥር የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ይህ የተባረከ ሕዝብ ተስፋ ከተደረገበት ዘር ጋር ዝምድና የሚኖረውስ እንዴት ነው? እነዚህ የቅዱሱ ሚስጥር ገጽታዎች አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ግልጽ ይሆናሉ።
ከዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን
12. ይሖዋ ከዳዊት ጋር ምን ቃል ኪዳን ገብቷል? ይህስ የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር በተወሰነ ደረጃ ግልጽ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ሌላ ቃል ኪዳን በገባበት ወቅት ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል። ታማኝ ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት “ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። . . . የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ መዝሙር 89:3) በዚህም ተስፋ የተደረገበት ዘር በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ግልጽ ሆነ። ይሁን እንጂ አንድ ተራ ሰው ለዘላለም ሊገዛ ይችላል? (መዝሙር 89:20, 29, 34-36) ደግሞስ አንድ ሰብዓዊ ንጉሥ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ሊታደግ ይችላል?
13, 14. (ሀ) በመዝሙር 110 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ለተቀባው ንጉሥ ምን ቃል ገብቷል? (ለ) የይሖዋ ነቢያት ዘሩን በተመለከተ ምን ተጨማሪ መግለጫዎች ሰጥተዋል?
13 ዳዊት በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ጌታዬን ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው። ይሖዋ ‘እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ!’ ሲል ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም።” (መዝሙር 110:1, 4) ዳዊት የተናገራቸው ቃላት በቀጥታ የሚያመለክቱት ተስፋ የተደረገበትን ዘር ወይም መሲሕ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:35, 36) ይህ ንጉሥ የሚገዛው በኢየሩሳሌም ሆኖ ሳይሆን በሰማይ በይሖዋ ‘ቀኝ’ ተቀምጦ ነው። ይህም በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ላይ እንደሚገዛ የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 2:6-8) እዚህ ላይ አምላክ ግልጽ ያደረገው አንድ ሌላም ነገር አለ። ይሖዋ፣ መሲሑ ‘እንደ መልከጼዴቅ ካህን’ እንደሚሆን በመግለጽ ምሏል። በአብርሃም ዘመን ካህንም፣ ንጉሥም ሆኖ እንዳገለገለው እንደ መልከጼዴቅ ሁሉ አስቀድሞ የተነገረለት ዘርም ንጉሥ እና ካህን ሆኖ እንዲያገለግል በቀጥታ በአምላክ ይሾማል።—ዘፍጥረት 14:17-20
14 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ ቅዱስ ሚስጥሩን በነቢያቱ አማካኝነት ደረጃ በደረጃ አሳውቋል። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ ዘሩ መሥዋዕት ሆኖ እንደሚሞት ገልጿል። (ኢሳይያስ 53:3-12) ሚክያስ መሲሑ የሚወለድበትን ቦታ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሚክያስ 5:2) ዳንኤል ደግሞ ዘሩ የሚገለጥበትንና የሚሞትበትን ጊዜ ሳይቀር ተንብዮአል።—ዳንኤል 9:24-27
ቅዱሱ ሚስጥር ተገለጠ!
15, 16. (ሀ) የይሖዋ ልጅ ‘ከሴት ሊወለድ’ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሰብዓዊ ወላጆቹ የወረሰው ነገር ምንድን ነው? በትንቢት የተነገረለት ዘር ሆኖ የተገለጠውስ መቼ ነው?
15 ዘሩ በምድር ላይ እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ትንቢቶች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም። ገላትያ 4:4 “ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውን . . . ልጁን ላከ” በማለት ይገልጻል። በ2 ዓ.ዓ. አንድ መልአክ ማርያም ለምትባል አንዲት አይሁዳዊት ድንግል እንዲህ አላት፦ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤ ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።”—ሉቃስ 1:31, 32, 35
16 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር ከሴት እንዲወለድ አደረገ። ማርያም ፍጽምና የጎደላት ሴት ነበረች። ሆኖም ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” በመሆኑ ከማርያም ኃጢአትን አልወረሰም። በሌላ በኩል ደግሞ የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆች የዳዊት ዘሮች ስለነበሩ የዳዊት ዙፋን ሕጋዊ ወራሽ የመሆን መብት እንዲያገኝ አስችለውታል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22, 23) በ29 ዓ.ም. ኢየሱስ ሲጠመቅ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ የቀባው ሲሆን “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:16, 17) በዚህ መንገድ ዘሩ ተገለጠ። (ገላትያ 3:16) ይህ ወቅት ቅዱሱ ሚስጥር ይበልጥ ግልጽ የሚሆንበት ጊዜ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 1:10
17. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ የመጣው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው እባብ ሰይጣን እንደሆነና የእባቡ ዘር ደግሞ የሰይጣን ተከታዮች እንደሆኑ ገልጿል። (ማቴዎስ 23:33፤ ዮሐንስ 8:44) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰይጣንም ሆነ ዘሮቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጨፈለቁት እንዴት እንደሆነ ተገለጸ። (ራእይ 20:1-3, 10, 15) ሴቲቱ ደግሞ “ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም” ወይም የአምላክ ሚስት እንደሆነች በሌላ አባባል መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል እንደምታመለክት ግልጽ ሆነ።a—ገላትያ 4:26፤ ራእይ 12:1-6
አዲሱ ቃል ኪዳን
18. ‘የአዲሱ ቃል ኪዳን’ ዓላማ ምንድን ነው?
18 ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ከሁሉ አስገራሚው እውነታ ግልጽ የሆነው ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ‘አዲሱ ቃል ኪዳን’ በነገራቸው ጊዜ ነው። (ሉቃስ 22:20) ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ከእሱ በፊት እንደነበረው የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን “የካህናት መንግሥት” የሚያስገኝ ነው። (ዘፀአት 19:6፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ሆኖም በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት የሚቋቋመው ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ብሔር ነው፤ ይህ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ሲሆን ታማኝ የሆኑትን ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች ብቻ ያቀፈ ነው። (ገላትያ 6:16) በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር በመሆን ለሰው ልጆች በረከት ያስገኛሉ!
19. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን ለሰው ዘር በረከት የሚያመጣ “የካህናት መንግሥት” ሊያስገኝ የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አዲስ ፍጥረት” የተባሉት ለምንድን ነው? በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚያገለግሉትስ ስንት ናቸው?
19 ሆኖም አዲሱ ቃል ኪዳን ለሰው ዘር በረከት የሚያመጣ “የካህናት መንግሥት” ሊያስገኝ የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አዲሱ ቃል ኪዳን የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በኃጢአታቸው የሚኮንን ሳይሆን ኢየሱስ በከፈለው መሥዋዕት አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። (ኤርምያስ 31:31-34) ይህም በይሖዋ ፊት ጻድቃን ተደርገው እንዲቆጠሩ ያደርጋል፤ በመሆኑም በሰማይ ያለው ቤተሰቡ አባል አድርጎ የሚቀበላቸው ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ይቀባቸዋል። (ሮም 8:15-17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21) በመሆኑም ‘በሰማይ ተጠብቆ ለሚቆያቸው ሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ይወለዳሉ።’ (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ እንዲኖሩ ከመሆኑ አንጻር ይህ ተስፋ የተሰጣቸው በመንፈስ የተወለዱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አዲስ ፍጥረት” ተብለው ተጠርተዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሆነው ከኃጢአት የተቤዠውን የሰው ዘር የሚገዙት ሰዎች ቁጥር 144,000 እንደሚሆን ይገልጻል።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4
20. (ሀ) በ36 ዓ.ም. ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ምን ነገር ተገለጠ? (ለ) ለአብርሃም ቃል የተገባውን በረከት የሚያገኙት እነማን ናቸው?
20 እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር “የአብርሃም ዘር” ክፍል ሆነዋል።b (ገላትያ 3:29) የዚህ ዘር የመጀመሪያዎቹ አባላት ሥጋዊ አይሁዳውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በ36 ዓ.ም. የቅዱሱ ሚስጥር አንድ ሌላ ገጽታ ተገለጠ፤ አሕዛብ ወይም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችም የሰማያዊው ተስፋ ተካፋይ እንደሚሆኑ ታወቀ። (ሮም 9:6-8፤ 11:25, 26፤ ኤፌሶን 3:5, 6) ለአብርሃም ቃል የተገባውን በረከት የሚያገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው? የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተከፈለው ለመላው ዓለም ስለሆነ የዚህ በረከት ተካፋዮች የሚሆኑት ቅቡዓን ብቻ አይደሉም። (1 ዮሐንስ 2:2) ይሖዋ ቁጥራቸው ያልተወሰነ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በሰይጣን ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጥፋት እንደሚተርፉ በኋላ ላይ ገለጸ። (ራእይ 7:9, 14) ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከሞት ተነስተው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ!—ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11-15፤ 21:3, 4
የአምላክ ጥበብና ቅዱሱ ሚስጥር
21, 22. ቅዱሱ ሚስጥር የይሖዋን ጥበብ የሚገልጠው በምን መንገዶች ነው?
21 ቅዱሱ ሚስጥር “በርካታ ገጽታዎች ያሉት የአምላክ ጥበብ” አስደናቂ መገለጫ ነው። (ኤፌሶን 3:8-10) ይህን ሚስጥር በማዘጋጀትም ሆነ ደረጃ በደረጃ በመግለጥ ይሖዋ ታላቅ ጥበቡን አሳይቷል! ጥበበኛ የሆነው አምላክ የሰዎችን የመረዳት ችሎታ ግምት ውስጥ አስገብቷል፤ ሚስጥሩ የተገለጠው ደረጃ በደረጃ መሆኑ የሰዎች ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲገለጥም አድርጓል።—መዝሙር 103:14
22 ይሖዋ ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ መምረጡም ወደር የለሽ ጥበቡን የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ልጅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካለ ከማንኛውም ፍጥረት ይበልጥ እምነት የሚጣልበት ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በኖረበት ዘመን ብዙ ዓይነት መከራዎች ደርሰውበታል። የሰው ልጆች ያሉባቸውን ችግሮች በሚገባ ይረዳል። (ዕብራውያን 5:7-9) ከኢየሱስ ጋር አብረው ስለሚገዙትስ ምን ማለት ይቻላል? ባለፉት መቶ ዘመናት ከተለያዩ ዘሮች፣ ቋንቋዎችና የኑሮ ደረጃዎች የተመረጡ ወንዶችና ሴቶች በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ያልደረሰባቸውና ያልተወጡት መከራ የለም ማለት ይቻላል። (ኤፌሶን 4:22-24) በእነዚህ ሩኅሩኅ ነገሥታትና ካህናት አገዛዝ ሥር መኖር ምንኛ አስደሳች ነው!
23. ከይሖዋ ቅዱስ ሚስጥር ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች ምን መብት አላቸው?
23 ሐዋርያው ጳውሎስ “ካለፉት ሥርዓቶችና ካለፉት ትውልዶች አንስቶ ተሰውሮ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር . . . [አሁን] ለቅዱሳኑ ተገልጧል” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 1:26) አዎን፣ በመንፈስ የተቀቡት የይሖዋ ቅዱሳን አገልጋዮች ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ብዙ ግንዛቤ ያገኙ ሲሆን ይህንንም እውቀት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች አካፍለዋል። ይሖዋ “የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ [በማሳወቁ]” ሁላችንም ታላቅ መብት አግኝተናል። (ኤፌሶን 1:9) ሌሎችም ወደር የለሽ የሆነውን የይሖዋ አምላክ ጥበብ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ይህን አስደናቂ ሚስጥር እናካፍላቸው!
a በተጨማሪም “ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር” በኢየሱስ በኩል ተገልጧል። (1 ጢሞቴዎስ 3:16) ያላንዳች እንከን በታማኝነት ከአምላክ ጎን የሚቆም ሊኖር ይችላል? የሚለው ጥያቄ ለረጅም ጊዜ መልስ ሳያገኝ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ አስገኝቷል። የሰይጣንን ፈተናዎች ሁሉ በመቋቋም በታማኝነት ጸንቷል።—ማቴዎስ 4:1-11፤ 27:26-50
b በተጨማሪም ኢየሱስ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ ገብቷል። (ሉቃስ 22:29, 30) ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ሆነው በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲገዙ ከዚህ “ትንሽ መንጋ” ጋር ውል የተዋዋለ ያህል ነው።—ሉቃስ 12:32