ምዕራፍ 9
አምላክ ‘ከወዳጁ’ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጠቃሚ ሆኖአል
1, 2. (ሀ) በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጥቅም ምን የወዳጅነት ዝምድና ጀምሯል? (ለ) አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ሊሆን የቻለው ለምን ነበር?
ከ1950 ዓመታት በፊት የሁሉም የሰው ዘሮች እውነተኛ ወዳጅ የነበረው:- “ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 15:13) ይህንን የተናገረው በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው ማለትም የይሖዋ አምላክ ወዳጅ የተባለው ሰው ዘር የሆነው ኢየሱስ ነው። ይህ የወዳጅነት ዝምድና ያልተመጣጠነ ቢመስልም እንኳ ባሁኑ ጊዜ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጥቅም ማምጣቱን ጀምሯል።
2 ከአምላክ ጋር በነበረው ወዳጅነት ምክንያት ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘው ይህ በጥንት ዘመን የነበረው ሰው ማን ነው? በኖኅ ዘመን ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ ተራፊዎች የአንዱ ማለትም የሴም ዝርያ የሆነው አብርሃም ነው። አብርሃም የእውነተኛ ወዳጅን ጠባዮች በማሳየት ከአምላክ ጋር ወዳጅነትን መሠረተ። አብርሃም በፍቅርና በእምነት በመገፋፋት ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ርምጃ ወስዷል። በዚህም ምክንያት አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “መጽሐፍም:- አብርሃም [ይሖዋን (አዓት)] አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ [የይሖዋም] ወዳጅ ተባለ።”— ያዕቆብ 2:23
3, 4. (ሀ) አብርሃም በእርሱ ላይ የነበረውን እምነትና ትምክህት ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በኢሳይያስ 41:8 ላይ ያለውን ቃሉን ወደ ከፍተኛው ፍጻሜ ያደረሰው እንዴት ባለ አነጋገር ነው?
3 ይህ የእምነትና የተግባር ሰው ከከለዳውያን ከተማ ከዑር የመጣና ዕብራዊ ተብሎ በመጠራት የመጀመሪያው የሆነ ሰው ነው። (ዘፍጥረት 14:13) ይህ ስያሜ የእስራኤል ሕዝብ ለሆኑት ዘሮቹም የሚሠራ ሆኗል። (ፊልጵስዩስ 3:5) ይሖዋ አምላክ አብርሃምን ወዳጁ በማድረጉ ምስጢራዊ ወደሆኑ ጉዳዮቹም ጭምር አስገብቶት ነበር። በዘፍጥረት 18:17–19 ላይ የሰፈረው ሐሳብ ይህንን ያመለክታል።
4 አብርሃም በይሖዋ ላይ የጣለውን እምነትና ትምክህት ይሖዋ አምላክ የቱን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደ ሰጠው ይህ ማስረጃ ይሆናል። የአብርሃም እምነትና ትምክህት አለምንም ጥያቄ የሚታዘዝ አድርጎታል። ስለዚህ ያለ ምንም እፍረት ወይም ፀፀት “ባሪያዬ እስራኤል፣ የመረጥሁህ ያዕቆብ፣ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ” በማለት ይሖዋ ለእስራኤላውያን የተናገረውን ንግግር ወደ መጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር።— ኢሳይያስ 41:8
ከአብርሃም ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን
5, 6. (ሀ) ይሖዋ ከወዳጁ ከአብርሃም ጋር ምን ቃል ኪዳን አደረገ? (ለ) ‘ዘርን’ በሚመለከት አምላክ ለወዳጁ ቃል የገባው ተቃራኒ የሚመስሉ ምን ሁኔታዎች እያሉ ነው?
5 አንድ ሰው ከሚያፈቅረው ወዳጁ ጋር የሚኖረው መተሳሰር ወደ ምን ሊመራው እንደሚችል የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ይሖዋ ኢምንት ፍጡር ከሆነው ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ምሳሌ ሊሆን ይችላል። በዘፍጥረት 15:18 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በዚያ ቀን (ይሖዋ) ለአብራም (ለአብርሃም) እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ:- ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቻለሁ።”
6 ኤፍራጥስ አብርሃምና ቤተሰቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተሻግረው ያለፉት ወንዝ ነው። ወንዙን በተሻገሩበት ጊዜ እርሱ 75 ዓመት ቢሆነውና ሚስቱም ልጅ የመውለጃዋ ጊዜ ቢያልፍም እንኳ አብርሃም ልጅ አልነበረውም። (ዘፍጥረት 12:1–5) ሆኖም እንደነዚህ ባሉ ተቃራኒ ሁኔታዎች ውስጥ እያለ አምላክ ለታዛዡ ለአብርሃም:- “ወደ ሰማይ ተመልከት፣ ከዋክብትንም ልትቆጥራቸው ትችል እንደሆነ ቁጠር . . . ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው።”— ዘፍጥረት 15:2–5
7. (ሀ) ቃል ኪዳኑ ምን ተብሎ ይጠራል? (ለ) የጸናው በየትኛው ዓመት ላይ ነው? በአብርሃም ሕይወት ምን በሆነበት ወቅት ላይ ነበር? (ሐ) ይህ የሆነው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የሕግ ቃል ኪዳን ከመደረጉ ከስንት ዓመታት በፊት ነው?
7 ይሖዋ ‘ከወዳጁ’ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን የአብርሃም ቃል ኪዳን ብለን እንጠራዋለን። ይህ ቃል ኪዳን የጸናው አብርሃም የአምላክን የቃል ኪዳን ብቃቶች በማሟላት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዝ የኤፍራጥስን ወንዝ ከተሻገረበት ጊዜ ይኸውም ከ1943 ከዘአበ ጀምሮ ነው። በዚያ ዓመት ይሖዋ አምላክ ልጅ የሌለውን አብርሃምን “ዘር” ሰጥቶ ለመባረክ ግዴታ ውስጥ ገባ። በሲና ተራራ ላይ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን ክፍል የሆነው ሕግ የተሰጠው ከዚያ 430 ዓመት ቆይቶ በ1513 ከዘአበ ነው።— ዘፍጥረት 12:1–7፤ ዘፀአት 24:3–8
በአብርሃም ቃል ኪዳን ላይ የተጨመረው የሕግ ቃል ኪዳን
8. (ሀ) የሕጉ ቃል ኪዳን ዓላማ ምን ነበር? (ለ) የሕጉ ቃል ኪዳን የአብርሃምን ቃል ኪዳን ሽሮት ነበርን?
8 በዚያን ጊዜ በልጁ በይስሐቅ በኩል የተገኙት የአብርሃም ዘሮች ነፃ ሕዝብ ሆነው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ነፃ ወጥተው በአረብ ምድር ወደሚገኘው ወደ ሲና ተራራ እየተመሩ ተወስደው ነበር። መካከለኛ በነበረው በሙሴ በኩል ከይሖዋ አምላክ ጋር በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ገብተው ነበር። እነዚህ እስራኤላውያን የይሖዋ “ወዳጅ” የአብርሃም ዘሮች ከነበሩ የዚህ የሕግ ቃል ኪዳን ዓላማ በእርግጥ ምን ነበር? ይህ ቃል ኪዳን ምርጥ ለሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች እንደ ጥበቃ ሆኖ የሚያገለግል ነበር። የሕጉ ቃል ኪዳን የእስራኤል ሕዝብ ከአምላክ ፍጹም ሕግ አንጻር ሲታዩ የኃጢአት መተላለፍን በመፈጸም ረገድ ጥፋተኞች መሆናቸውን ቢያሳይም እንኳ የአብርሃምን ቃል ኪዳን አልሻረውም።— ገላትያ 3:19–23
9, 10. (ሀ) የአብርሃም ዝርያዎች ሁሉም አሕዛብ ስለሚባረኩበት “ዘር” በአጠቃላይ የሚሰማቸው እንዴት ነበር? (ለ) አስተሳሰባቸውስ ትክክል ሆኖ ተገኝቷልን?
9 በምሳሌያዊ አባባል እስራኤላውያን የዚህ የሕግ ቃል ኪዳን “ልጆች” ሆኑ። ሥጋዊ የአብርሃም ዘሮች በመሆናቸው ወዲያውኑ አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩበት “ዘር” እንደሚሆኑ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ነገሩ እንደዚያ ሆኗልን? አልሆነም! ዛሬ ከ3, 500 ዓመታት ገደማ በኋላ ጥላቻ ባላቸው ብዙ ብሔራት መካከል ለኅልውናዋ የምትዋጋውንና በራስዋ የምትመራዋን ዓለማዊት የእስራኤል ሪፖብሊክ እንመለከታለን።
10 ስለዚህ በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው የቀረውን የሰው ዘር የመባረክን ሐሳብ በአእምሮው በመያዝ የአብርሃም “ዘር” ክፍል ለመሆን ሃይማኖቱን ለውጦ የተገረዘ አይሁዳዊ መሆኑ ይሖዋ አምላክ የፈቀደው መንገድ አይደለም። እንግዲያው የሆነው ነገር ምንድን ነው?
11. ሐዋርያው ጳውሎስ የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያዎች ምን እንደደረሰባቸው ያብራራው እንዴት ነው?
11 ሐዋርያው ጳውሎስ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ያብራራልናል:- “አንዱ ከባሪያይቱ (ከአጋር) አንዱም [ከነፃዋ (አዓት)] (ከሣራ) የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፎልናል። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዷል፣ [የነፃዋ ልጅ (አዓት)] ግን በተስፋው ቃል ተወልዷል። ይህም ነገር (ምሳሌያዊ ድራማ) ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸው። ከደብረ ሲና (ከሲና ተራራ) የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፣ እርሷም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፣ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት እርሷም እናታችን ናት።”— ገላትያ 4:22–26
12. የቤት አገልጋይዋ አጋር የምታመለክተው ማንን ነው?
12 የቤት አገልጋይ በነበረችው ልጃገረድ በአጋር የተመሰለችው ኢየሩሳሌም ሥጋዊ አይሁዶች የሚኖሩባት ምድራዊት ኢየሩሳሌም ናት። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን ኢየሩሳሌም የእስራኤል ሕዝብ ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ነበረች። (ማቴዎስ 23:37, 38) በሙሴ መካከለኛነት የጸናው ቃል ኪዳን ገና በሥራ ላይ ስለነበረ ሥጋዊት እስራኤል የሚታየው የይሖዋ ድርጅት ነበረች። በዚህም ምክንያት በአንዲት ሴት ማለትም የሣራ የቤት አገልጋይ በነበረችው በአጋር ልትመሰል ትችል ነበር።
የአብርሃም ቃል ኪዳን እውነተኛ ልጆች
13. (ሀ) በአብርሃም ሚስት በሣራ የተመሰለችው ምንድን ናት? (ለ) “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” “ነፃ” ናት ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው?
13 በሌላው በኩል ግን “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” የይሖዋ የማይታይ ሰማያዊት ድርጅት ነበረች። በተመሳሳይ መንገድ በአንዲት ሴት ማለትም የአብርሃም እውነተኛ ሚስት በነበረችው በሣራ ልትመሰል ችላለች። የሕጉ ቃል ኪዳን የተደረገው ከዚህች ድርጅት ጋር አልነበረም፤ በዚህም ምክንያት “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” እንደ ጥንትዋ ሣራ ነፃ ነበረች። የተስፋውን “ዘር” የምታስገኝ ድርጅት ይህች ነበረች። ሐዋርያው ጳውሎስ “እናታችን” ብሎ ሊጠራት የቻለውም ለዚህ ነው።
14. የአብርሃም ቃል ኪዳን “ለላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ይሠራልን? ስለዚህ በመንፈስ የተዋጁት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ምን ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ?
14 እንግዲያው በእርግጥም እርስዋ የታላቁ አብርሃም ምሳሌያዊት ሚስት እንደመሆንዋ የአብርሃም ቃል ኪዳን በእርስዋ ላይ ይሠራል። አዎ፤ በሰማያት ለምትገኘው የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊት ድርጅት ይሠራል። ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉት በመንፈስ የተመረጡት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የአብርሃም ቃል ኪዳን ወንዶች ልጆች ወይም ልጆች ናቸው። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጉዳዩን በዚህ መንገድ ማብራራቱን ይቀጥላል:-
15. የአብርሃምን የቃል ኪዳን “ልጆች” በሚመለከት ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 4:27–31 ላይ ምን አለ?
15 “አንቺ የማትወልጂ መካን፣ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ እልል በይና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። እኛም፣ ወንድሞች ሆይ፣ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? [የቤት አገልጋይዋ ልጅ ከነፃዋ ሴት (አዓት)] ልጅ ጋር አይወርስምና [የቤት አገልጋይዋን (አዓት)] ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ [የነፃዋ (አዓት)] ልጆች ነን እንጂ [የቤት አገልጋይዋ ልጆች (አዓት)] አይደለንም።”— ገላትያ 4:27–31፤ ኢሳይያስ 54:1
16. የጥንቱ ምሳሌያዊ ድራማ የሕጉን ቃል ኪዳን በሚመለከት ወደፊት ምን እንደሚሆን አመልክቶ ነበር? ይህስ ምን እንዲቀር ያደርጋል?
16 ስለዚህ ያ ጥንታዊ የሆነ ምሳሌያዊ ድራማ ታላቁ አብርሃም ይሖዋ አምላክ በሲና ተራራ ላይ ከእስራኤል ጋር የተደረገውን የሕግ ቃል ኪዳን እንደሚያስወግደው ተንብዮአል። በዚህም መንገድ በአብርሃም ቃል ኪዳን ላይ ተደርጎ የነበረው ጭማሪ (የሕጉ ቃል ኪዳን) ተቀነሰና ወይም ተወገደና የምድር ወገኖች በሙሉ ራሳቸውን የሚባርኩበት “ዘር” ይመጣል የሚል ተስፋ የያዘው የአብርሃም ቃል ኪዳን ብቻ ቀረ።
17. (ሀ) የሕጉ ቃል ኪዳን የሚቀጥለው እስከምን ያህል ጊዜ ድረስ ነበር? (ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ ዋነኛው የአብርሃም ዝርያ የሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) ኢየሱስ ሁሉንም የምድር ቤተሰቦች ለመባረክ የአምላክ ዋነኛ ወኪል መሆኑ የተመካው በምን ላይ ነበር?
17 ስለዚህ የተጨመረው የሕግ ቃል ኪዳን ተስፋ የተደረገበት “ዘር” እስከሚመጣ ድረስ የሚቀጥል ነበር፣ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተገኝቷል። እርሱም አምላክ በፈጸመው ተዓምር የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያ ሆነ። የዚያ የጥንት የቤተሰብ ራስ ዋነኛ ዝርያም ሆነ። እርሱ የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያ ብቻ ሳይሆን የአምላክ ልጅም በመሆኑ ፍጹም ሰው ነበር። “(ታማኝ)፣ ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ” ሆኖ የቀጠለ ፍጹም ሰው ነበር። (ዕብራውያን 7:26) ይሁን እንጂ የምድርን ቤተሰቦች ሁሉ ለመባረክ የአምላክ ዋነኛ ወኪል ሆኖ ማገልገሉ የተመካው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረጉና የዚህንም ዋጋ ለሁሉም የሰው ዘር ጥቅም በማዋሉ ላይ ነበር። እንደዚህ ባለ መንገድ የራስን ጥቅም በመሠዋት ሁሉንም መለኮታዊ ብቃቶች የሚያሟላ መሥዋዕት የሚያቀርብ የይሖዋ ታላቅ ሊቀ ካህን ሆኖ ያገለግላል።
የሕጉ ቃል ኪዳን በኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ ተጠርቋል
18. የቤዛው መሥዋዕት ጥቅሞች በመጀመሪያ መቅረብ የነበረባቸው ለማን ነበር? ለምንስ? (ለ) ኢየሱስ ምን ሆኗል?
18 የዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች በመጀመሪያ ኢየሱስ በድንግል ማርያም አማካኝነት በተዓምራታዊ መንገድ በመወለድ አባል ለሆነበት ለአይሁድ ሕዝብ መቅረብ ነበረባቸው። ይህም በተለይ በድርብ የሞት ኩነኔ ስር ለነበሩት አይሁዶች የግድ አስፈላጊ ነገር ነበር። እንዴት? በመጀመሪያ የኃጢአተኛው የአዳም ዘሮች ናቸው፤ ሁለተኛ ደግሞ ባለፍጽምናቸው ምክንያት ከአምላክ ጋር በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት ለመኖር ባለመቻላቸው የተረገሙ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለእነርሱ ርግማን ተቀባይ ሆነላቸው። እስከ ሞት ድረስ በመከራ እንጨት ላይ በመሰቀል ‘ከእስራኤል ቤት ከጠፉት በጎች’ ላይ ርግማኑን ለማንሳት ችሏል። በ33 እዘአ የሕጉ ቃል ኪዳን በኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ ተጠርቆ ስለነበር በዚያ ጊዜያዊ የሕግ ቃል ኪዳን ሥር የነበረው የአይሁዳውያን የበጎች በረት ተዘጋ፣ ፈረሰ።— ማቴዎስ 15:24፤ ገላትያ 3:10–13፤ ቆላስይስ 2:14
19. (ሀ) ምን አዲስ የበጎች በረት መከፈት ነበረበት? ምንንስ መያዝ ነበረበት? (ለ) ታዲያ ወደ አዲሱ የበጎች በረት የገቡት ምን ይሆናሉ?
19 ስለዚህ ከሞት የተነሣው የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሳዊ በጎች የሚገቡበት አዲስ የበጎች በረት መከፈት ነበረበት። በተጨማሪም ራሱን መሥዋዕት ያደረገው መልካሙ እረኛ ራሱ ለዚህ አዲስ የበጎች በረት ምሳሌያዊ በር ነው። (ዮሐንስ 10:7) በመልካሙ እረኛ ስር ወደዚህ አዲስ በረት የሚመጡት ሁሉ በመንፈስ የተዋጁ የታላቁ አብርሃም ልጆችና የእርሱ “ዘር” ክፍል ይሆናሉ። (ሮሜ 2:28, 29) ከዚህ ሐቅ ጋር በመስማማት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የዚህ መንፈሳዊ “ዘር” ቀሪዎች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ለሚገኙት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረከት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
[በገጽ 80, 81 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሲና ተራራ ላይ የተደረገው የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ከኢየሱስ ጋር በመሰቃያው እንጨት ላይ በተቸነከረ ጊዜ ወደ ፍጻሜው መጥቷል