ራስን የመግዛት ባሕርይ ይኑራችሁ፤ ይብዛላችሁም
“በእምነታችሁ . . . ራስን መግዛት ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:5, 6
1. አንድ ክርስቲያን በየትኛው ያልተለመደ ሁኔታ ምስክርነት ሊሰጥ ይችላል?
ኢየሱስ “ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 10:18) በአንድ ገዥ፣ ዳኛ ወይም ፕሬዚደንት ፊት እንድትቀርብ ብትጠራ ምን ብለህ ትናገር ነበር? ምናልባት በመጀመሪያ የምትናገረው እዚያ ስለመጣህበት ጉዳይ ማለትም ስለ ተከሰስክበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። የአምላክም መንፈስ እንደዚሁ እንድታደርግ ይረዳሃል። (ሉቃስ 12:11, 12) ነገር ግን ራስን ስለ መግዛት እናገራለሁ ብለህ ታስባለህን? ይህንን ነጥብ የክርስቲያን መልእክታችን አንዱ ከፍተኛ ክፍል አድርገህ ትቆጥረዋለህን?
2, 3. (ሀ) ጳውሎስ ለፊልክስና ለድሩሲላ ሊመሰክርላቸው የቻለው እንዴት ነበር? (ለ) በዚያ ሁኔታ ጳውሎስ ራስን ስለመግዛት መናገሩ ተስማሚ የነበረው ለምንድን ነው?
2 የሚቀጥለውን በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የደረሰውን ምሳሌ ተመልከት። ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ የሆነው ይህ ሰው ታሰረና ተከስሶ ለፍርድ ቀረበ። እንዲናገር ዕድል ሲሰጠው እንደ አንድ ክርስቲያን ማለትም እንደ አንድ ምስክር ስለሚያምነው ነገር ለማስረዳት ፈለገ። የተጻፈውን መዝገብ ልትመረምርና “ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ” አሳማኝ በሆኑ የመከራከሪያ ነጥቦች ተጠቅሞ የሰጠውን ምስክርነት ማንበብ ትችላለህ። እዚህ ላይ እየጠቀስን ያለነው ሐዋርያው ጳውሎስ በቂሣሪያ ያጋጠመውን ሁኔታ ነው። ቀደም ሲል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። “ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፣ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለማመን የሚናገረውን ሰማው።” (ሥራ 24:24) ፊልክስ “በንግሥና ግዛቱ ሥር በሚገኙት ባሮቹ ሁሉ ላይ ያልፈጸመው የጭካኔና የብልግና ድርጊት የለም” በማለት ታሪክ ይዘግባል። ድሩሲላ (የአምላክን ሕግ በመተላለፍ) ባሏን ፈትታ እሱን እንድታገባ አባብሎ ሦስተኛ ሚስቱ እንድትሆን ከማድረጉ በፊት ሁለት ጊዜ አግብቶ ነበር። ምናልባትም ስለ አዲሱ ሃይማኖት ማለትም ስለ ክርስትና መስማት የፈለገችው እሷ ልትሆን ትችላለች።
3 ጳውሎስ “ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ” መናገሩን ቀጠለ። (ሥራ 24:25) ይህ ንግግሩ ትክክለኛዎቹን የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ፊልክስና ድሩሲላ ከፈጸሙት ጭካኔና የፍትሕ መጓደል ጋር እንዳነጻጸረ ግልጽ ነው። ምናልባትም ጳውሎስ ፊልክስ በፊቱ ለቀረበለት ጉዳይ ፍትሕ ለማሳየት ይገፋፋ ይሆናል ብሎ ተስፋ አድርጎ ይሆናል። ታዲያ “ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ” ማንሣት ለምን አስፈለገው? እነዚህ ስነ ምግባር የጎደላቸው ባልና ሚስት “በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን” ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ይጠይቁት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን መከተል ራስን መግዛት ማለትም አስተሳሰብን፣ ንግግርንና ድርጊትን መግታት እንደሚጨምር ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ሰዎች ሁሉ ስለሚያስቡት፣ ስለሚናገሩትና ስለሚያደርጉት ነገር ለአምላክ መልስ ይሰጣሉ። ስለዚህም በጳውሎስ ጉዳይ ላይ ፊልክስ ከሚሰጠው ፍርድ ይልቅ ገዥውና ሚስቱ በአምላክ ፊት የሚጠብቃቸው ፍርድ ይበልጥ ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ ነበር። (ሥራ 17:30, 31፤ ሮሜ 14:10–12) ‘ፊልክስ ፈራ፤’ ለምን እንደፈራም ይገባናል።
በጣም አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ቀላል አይደለም
4. ራስን መግዛት በክርስትና እምነት ውስጥ የግድ አስፈላጊ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ ራስን መግዛት በክርስትና እምነት ውስጥ የግድ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ተገንዝቧል። ከኢየሱስ የቅርብ ተባባሪዎች አንዱ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስም የራስን መግዛት አስፈላጊነት አረጋግጧል። በሰማይ “ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች” ለሚሆኑት ክርስቲያኖች በጻፈበት ጊዜ ጴጥሮስ እንደ እምነት፣ ፍቅርና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ባሕርዮች የማሳየቱን አስፈላጊነት አጥብቆ አሳስቧል። “እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና” ተብሎ ለተሰጠው ዋስትና ራስን መግዛትም ድርሻ አለው። — 2 ጴጥሮስ 1:1, 4–8
5. ራስን የመግዛት ባሕርይ በተለይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
5 ራስ መግዛትን ማሳየት አለብን ብሎ መናገር በየዕለቱ ራስን የመግዛት ባሕርይ በተግባር ከማሳየት እንደሚቀልል አንተ ራስህ ሳታውቀው አትቀርም። አንዱ ምክንያት ራስን የመግዛት ባሕርይ ብዙ ሰዎች የማያሳዩ መሆናቸው ነው። በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ ጳውሎስ በዘመናችን ማለትም “በመጨረሻው ቀን” ጎልተው የሚታዩትን ጠባዮች ዘርዝሯል። ዘመናችንን ተለይቶ እንዲታወቅ ከሚያደርጉት ጠባዮች አንዱ ብዙዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” መሆናቸው ነው። ይህ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ነገሮች በዙሪያችን ሲፈጸሙ እናይ የለምን?
6. በዛሬው ጊዜ ራስን የመግዛት ጉድለት ጎልቶ የሚታየው እንዴት ነው?
6 በመሠረቱ ብዙ ሰዎች “ሲወጣልህ” ወይም “ስትተነፍሰው” ጥሩ ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች እንደ ምሳሌ በሚጠቀሱ በሕዝብ ዘንድ ታዋቂና ዝነኛ በሆኑ ራስን ስለ መግዛት ምንም ደንታ በሌላቸውና የመጣላቸውን በመናገርና በማድረግ ስሜታቸውን በሚገልጹ ሰዎች አመለካከታቸው ተጠናክሯል። ለምሳሌ ያህል ታዋቂ የስፖርት ዓይነቶችን የሚወዱ ሰዎች ስሜታቸውን በጣም በሚያስቀይም መንገድ መግለጻቸውና እንዲያውም ዓመፅ ማነሣሳታቸው የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። በስፖርት ዝግጅቶች ወቅት አሠቃቂ ጠብ ወይም በአድማ የተቀሰቀሰ ረብሻ ያጋጠመበትን ጊዜ ቢያንስ ከዜና ማሰራጫዎች የሰማህበትን ጊዜ አታስታውስምን? የተነሣንበት ዓላማ ራስ መግዛት የታጣባቸውን ምሳሌዎች በመከለስ ብዙ ጊዜ እንድናጠፋ አይጠይቅብንም። ራስን የመግዛት ባሕርይ ልናሳይባቸው የሚገቡባቸውን ብዙ አቅጣጫዎች መዘርዘር ትችላለህ። ከእነርሱም መካከል የምግብና የመጠጥ አወሳሰዳችን፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ጠባይ እንዲሁም በጊዜ ማሳለፊያዎቻችን ላይ የምናጠፋው ጊዜና ገንዘብ ይገኙባቸዋል። እነዚህን ሁሉ አገላብጠን ለመመርመር ከመሞከር ይልቅ ራስ መግዛትን ማሳየት የሚኖርብንን አንዱን ዋና አቅጣጫ እንመርምር።
ስሜታችንን በተመለከተ ራስን መግዛት
7. የትኛው ራስን የመግዛት ባሕርይ ገጽታ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል?
7 ብዙዎቻችን ድርጊቶቻችንን በሚመለከት በመጠኑ ራሳችንን መቆጣጠር ወይም መግታት ችለናል። አንሰርቅም፣ በብልግና ድርጊት አንወድቅም ወይም አንገድልም። ስለ እነዚህ ነገሮች የአምላክ ሕግ ምን እንደሚል እናውቃለን። ታዲያ ስሜቶቻችንን በመቆጣጠር ረገድ ምን ያህል ተሳክቶልናል? ስሜታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸው ሰዎች ውለው አድረው ድርጊቶቻቸውንም መቆጣጠር እንደሚያቅታቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለዚህ ስሜቶቻችንን በመቆጣጠሩ ላይ እናተኩር።
8. ስሜቶቻችንን በተመለከተ ይሖዋ ከእኛ ምን ይጠብ ቅብናል?
8 ይሖዋ አምላክ እንደ አውቶማቲክ መኪናዎች ምንም ስሜት የሌላቸው ወይም ስሜት እንዳላቸው የማያሳዩ ሰዎች እንድንሆን አይጠብቅብንም። በአልዓዛር የመቃብር ቦታ ኢየሱስ “በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ።” ከዚያም “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።” (ዮሐንስ 11:32–38) ከቤተ መቅደሱ ገንዘብ ለዋጮችን ባባረራቸው ጊዜ ድርጊቶቹን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ለየት ያለ ስሜት አሳይቷል። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:14–17) ታማኝ ደጋፊ ሆነው የቆሙት ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ጥልቅ ስሜቶችን አሳይተው ነበር። (ሉቃስ 10:17፤ 24:41፤ ዮሐንስ 16:20–22፤ ሥራ 11:23፤ 12:12–14፤ 20:36–38፤ 3 ዮሐንስ 4) ይሁን እንጂ ስሜቶቻቸው ወደ ኃጢአት እንዳይመሩአቸው ራስ የመግዛትን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። ኤፌሶን 4:26 ይህን ግልጽ ሲያደርግ “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቍጣችሁም ላይ ፀሐይ አይግባ” ይላል።
9. ስሜቶቻችንን መቆጣጠራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 አንድ ክርስቲያን ስሜቶቹ ከቁጥጥር ውጪ ሆነው እያሉ ራሱን የገዛ መስሎ ቢታይ አደገኛ ነው። አምላክ የአቤልን መሥዋዕት በተቀበለ ጊዜ የተፈጠረውን ሁኔታ አስታውስ:- “ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። እግዚአብሔርም ቃየንን አለው:- ‘ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው።’” (ዘፍጥረት 4:5–7) ቃየን አቤልን ወደ መግደል የመራውን ስሜቱን መቆጣጠር ተሣነው። ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ስሜት ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ ድርጊት መራ።
10. ከሐማ ምሳሌ ምን ትማራለህ?
10 በመርዶክዮስና በአስቴር ዘመን የተፈጸመ ሌላ ምሳሌ ተመልከት። ባለ ሥልጣን የነበረው ሐማ መርዶክዮስ ስላልሰገደለት በጣም ተናደደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሐማ በስሕተት እርሱ ከፍ ከፍ እንደሚደረግ አድርጎ አሰበ። “በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቆጣ። ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ።” (አስቴር 5:9, 10) የደስታ ስሜት በቶሎ የተሰማው ሰው ነበረ። ነገር ግን ቂም በያዘበት ሰው ላይ ደግሞ በቁጣ ለመሞላት ጊዜ አልፈጀበትም። መጽሐፍ ቅዱስ ሐማ ግን “ታግሦ” ሲል ራስን በመግዛት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው ማለት ነውን? እንደዚያ ማለቱ አልነበረም። ለጊዜው ሐማ ድርጊቶቹንና የሚያሳየውን ስሜት ብቻ ተቆጣጠረ እንጂ የምቀኝነት ቁጣውን መቆጣጠር ተስኖት ነበር። ስሜቱ የግድያ ዕቅድ እንዲያውጠነጥን አደረገው።
11. በፊልጵስዩስ ጉባኤ ምን ችግር ተፈጥሮ ነበር? ለችግሩ ምክንያት የነበረው ምን ሊሆን ይችላል?
11 በተመሳሳይም ዛሬ ስሜትን ለመቆጣጠር አለመቻል ክርስቲያኖችን በጣም ሊጎዳቸው ይችላል። አንዳንዶች ‘አይ፣ እንዲህ ዓይነቱ ችግር በጉባኤው ውስጥ አይኖርም’ የሚል ስሜት ይኖራቸው ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከዚህ በፊት ነበረ። በፊልጵስዩስ ጉባኤ የነበሩ ሁለት ቅቡዓን ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ያላሰፈረው አንድ ዓይነት ከባድ አለመግባባት ነበረባቸው። እስቲ ችግራቸው የሚከተለው ነው ብለን እናስብ:- ኤዎድያ አንዳንድ ወንድሞችንና እኅቶችን ለእራት ግብዣ ወይም አብረው ደስ የሚል ጊዜ ለማሳለፍ ጠራቻቸው። ሲንጤኪ ግን ስላልተጠራች ተቀይማለች። በሌላ ጊዜ ኤዎድያንን ባለመጥራት ብድሯን መልሳ ይሆናል። ከዚህ በኋላ አንዳቸው የሌላውን ስሕተት አጉልተው ማየት ጀመሩና እንዲያውም ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ መነጋገር አቆሙ። እንዲህ ባለው ሁኔታ የችግሩ መሠረታዊ መነሻ እራት አለመጋበዝ ብቻ ሊሆን ይችላልን? ሊሆን አይችልም። ይህ የክብሪት ጭረት ያህል ብቻ ነው። እነዚህ ሁለት ቅቡዓን እኅቶች ስሜቶቻቸውን መቆጣጠር ሲሣናቸው የተጫረው ክብሪት ወደ ሰደድ እሳትነት ተለወጠ። ችግሩ ከርሮና አድጎ አንድ ሐዋርያ ጣልቃ እስኪገባበት ድረስ ደረሰ። — ፊልጵስዩስ 4:2, 3
ስሜትህና ወንድሞችህ
12. አምላክ በመክብብ 7:9 ላይ ያለውን ምክር የሰጠን ለምንድን ነው?
12 አንድ ሰው ቸል እንደተባለ፣ እንደተጎዳ ወይም አላግባብ እንደተያዘ ሲሰማው ስሜቱን መቆጣጠር ቀላል አለመሆኑ የታመነ ነው። ይሖዋ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት በመመልከቱ ስለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ በቂ እውቀት አለው። አምላክ “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፣ ቁጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና” በማለት ይመክረናል። (መክብብ 7:9) እዚህ ላይ አምላክ በቅድሚያ ትኩረት የሰጠው ለድርጊት ሳይሆን ለስሜት መሆኑን ልብ በል። (ምሳሌ 14:17፤ 16:32፤ ያዕቆብ 1:19) ራስህን ‘ስሜቴን ለመቆጣጠሩ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ልሰጠው ይገባኛልን?’ ብለህ ጠይቅ።
13, 14. (ሀ) በዓለም ውስጥ ስሜትን ለመቆጣጠር ባለመቻል ብዙ ጊዜ ምን ይፈጠራል? (ለ) ክርስቲያኖችን ቂም ወደ መያዝ ሊያመሯቸው የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
13 ስሜታቸውን መቆጣጠር የተሣናቸው በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ ወይም በዘመዳቸው ላይ ስለተፈጸመ ወይም ተፈጽሟል ብለው ስለሚገምቱት አንድ ዓይነት በደል መራር በሆነና ዓመፅ በተሞላበት መንገድ እንዴት እንደሚበቀሉ ማሰብ ይጀምራሉ። ስሜት አንዴ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ጎጂ ተጽእኖው ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። (ከዘፍጥረት 34:1–7, 25–27፤ 49:5–7፤ 2 ሳሙኤል 2:17–23፤ 3:23–30 እና ከምሳሌ 26:24–26 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያኖች ከየትኛውም አገር ወይም ባሕል የመጡ ቢሆኑም እንደዚህ ያለውን መራራ ጥላቻና ቂም እንደ ስሕተት፣ መጥፎና ሊሸሹት እንደሚገባ ነገር መቁጠር እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘሌዋውያን 19:17) ቂመኛነትን መሸሽ ስሜቶችህን በተመለከተ ራስህን ከምትቆጣጠርባቸው ክፍሎች አንዱ አድርገህ ትመለከተዋለህን?
14 በኤዎድያና በሲንጤኪ ሁኔታ ላይ እንደታየው ስሜትን ለመቆጣጠር አለመቻል አሁንም ቢሆን ወደ ችግር ሊመራ ይችላል። አንዲት እኅት ወደ አንድ ሠርግ ባለመጠራቷ ቸል እንደተባለች ሊሰማት ይችል ይሆናል። ወይም ልጅዋ ወይም ዘመዷ አልተጠሩ ይሆናል። ወይም አንድ ወንድም ያገለገለ መኪና ከሌላ ክርስቲያን ወንድሙ ገዝቶ ብዙም ሳይቆይ መኪናው ተበላሽቶበት ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይህ ሁኔታ የመጎዳት ስሜት አመጣና ስሜት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ብስጭትን አስከተለ። ከዚያስ ምን ሊከተል ይችላል?
15. (ሀ) በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረ መቀያየም ምን አሳዛኝ ውጤቶች አስከትሏል? (ለ) ቂም የመያዝን ዝንባሌ እንድናስወግድ የሚረዳን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ነው?
15 የተበሳጨው ግለሰብ ስሜቱን ቶሎ ተቆጣጥሮ ከወንድሙ ጋር ሰላምን ለመፍጠር ካልጣረ ቂም መያዝ ሊመጣ ይችላል። አንድ ምስክር በዚያ የሚሰበሰቡ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ወይም አንዱን ቤተሰብ “ስለማይወዳቸው” ሌላ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ላይ እንዲመደብ የጠየቀበት ጊዜ አጋጥሞናል። እንዴት ያሳዝናል! መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ቢወስዷቸው ሽንፈት ነው ይላል። ታዲያ በእኛ ላይ ወይም በዘመዳችን ላይ ደርሶ በነበረ አንድ ዓይነት ቅሬታ ላይ ተመርኩዘን አንድን ወንድም መሸሹስ ሽንፈት አይሆንምን? ስሜታችን ከወንድሞቻችንና ከእኅቶቻችን ጋር ሰላም ከመፍጠር ይልቅ የሥጋ ዝምድናን የምናስበልጥ መሆናችንን አያጋልጥብንምን? ስሜታችን አሁን ከእርሷ ጋር እንዳንነጋገር የሚገፋፋን ከሆነ ለእኅታችን ለመሞት እንኳ ፈቃደኞች ነን ልንል እንችላለንን? (ከዮሐንስ 15:13 ጋር አወዳድር።) አምላክ በማያሻማ አነጋገር “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ” በማለት ይነግረናል። — ሮሜ 12:17–19፤ 1 ቆሮንቶስ 6:7
16. ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ አብርሃም ምን ምሳሌ ትቶልናል?
16 ስሜታችንን ለመቆጣጠር የሚረዳን እርምጃ ጥላቻ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ሰላም ለመፍጠር ወይም ለቅሬታ ምክንያት የሆነውን ነገር ለመፍታት መጣር ነው። የአብርሃምንና የሎጥን እጅግ ብዙ መንጋ ለመያዝ ምድሪቱ አልበቃ ባለች ጊዜና መንጎቻቸውን በሚጠብቁላቸውም ሠራተኞቻቸው መካከል ጠብ በተነሣ ጊዜ የሆነውን ነገር አስታውስ። አብርሃም ስሜቱ እንዲያሸንፈው ፈቀደለትን? ወይስ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳየ? የሚያስመሰግነውን ሰላማዊ መፍትሔ በማቅረብ እያንዳንዳቸው በተለያየ አካባቢ እንዲኖሩና ችግራቸው በዚህ እንዲቃለል ሐሳብ አቀረበ። በመጀመሪያ ሎጥ የመረጠውን እንዲወስድ ፈቀደለት። አብርሃም ምንም ዓይነት ቅሬታ ወይም ቂም እንዳልያዘበት የሚያሳየው ጥቂት ቆይቶ ሎጥን ለመርዳት መዋጋቱ ነው። — ዘፍጥረት 13:5–12፤ 14:13–16
17. ጳውሎስና በርናባስ በአንድ ወቅት ጉድለት ያሳዩት እንዴት ነበር? ከዚያ በኋላ ግን ምን ሆነ?
17 ጳውሎስና በርናባስን ካጋጠማቸው ሁኔታም ራስን ስለ መግዛት ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ለብዙ ዓመታት የአገልግሎት ጓደኛሞች ሆነው ካገለገሉ በኋላ ማርቆስን በጉዞአቸው በመውሰድና ባለመውሰዱ ጉዳይ ላይ ሊግባቡ አልቻሉም። “ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፣ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።” (ሥራ 15:39) እነዚህ ጎልማሳ ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር ባቃታቸው በዚህ ወቅት የደረሰው ሁኔታ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። በእነርሱ ላይ ሊደርስ ከቻለ በእኛም ላይ ሊደርስ ይችላል። ይሁን እንጂ የነበራቸው ወዳጅነት ተቋርጦ እንዲቀር ወይም ቂም በቀል በውስጣቸው እንዲያድግ አልፈቀዱም። መዝገቡ እንደሚያረጋግጠው እነዚህ ወንድሞች ስሜታቸውን መልሰው ተቆጣጥረውታል እንዲሁም በሰላም አብረው ሠርተዋል። — ቆላስይስ 4:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:11
18. አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ወንድሙ እንደጎዳው ቢሰማው ምን ሊያደርግ ይችላል?
18 በአምላክ ሕዝቦች መካከል የመጎዳት ስሜት እንዲያውም መቀያየም እንኳ ሊኖር እንደሚችል መገመት እንችላለን። በዕብራውያንና በሐዋርያት ዘመን እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ነበሩ። ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን በእኛ ዘመን ባሉት የይሖዋ አገልጋዮች ላይም ደርሷል። (ያዕቆብ 3:2) ኢየሱስ በወንድሞች መካከል የሚፈጠሩትን እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች ወዲያውኑ እንዲያስወግዷቸው ተከታዮቹን አሳስቧል። (ማቴዎስ 5:23–25) ነገር ግን ስሜቶቻችንን የምንቆጣጠርበትን መንገድ በማሻሻል ቀድሞውኑ እንዳይነሡ መከላከሉ ይሻላል። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት ባደረጉት ወይም በተናገሩት ትንሽ ነገር ችላ እንደተባልክ ከተሰማህ ወይም ከተከፋህ ስሜትህን ተቆጣጥረህ ለምን አትተወውም? ያስከፋህ ሰው ስሕተት መሥራቴን አምኛለሁ ካላለኝ አልረካም ብለህ ከዚያ ሰው ጋር ፊት ለፊት መነጋገርህ የግድ አስፈላጊ ነውን? አንተ ራስህ የራስህን ስሜት በመቆጣጠር ረገድ ምን ያህል ጠንካራ ነህ?
ይቻላል!
19. ውይይታችን ስሜታችንን በመቆጣጠሩ ላይ ማተኮሩ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ራስን የመግዛት ገጽታ አንዱ ክፍል ስለሆነው ስሜታችንን ስለ መቆጣጠር በሰፊው ተመልክተናል። ይህ ደግሞ ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ስሜታችንን መቆጣጠር ከተሣነን አንደበታችንን ስድ የተለቀቀ ወደ ማድረግ ሊያመራ፣ የጾታ ግፊቶቻችንን፣ የአመጋገብ ልማዳችንንና ራስን መግዛት ልናሳይባቸው የሚገቡንን ሌሎች ብዙ የኑሮአችንን ዘርፎች ሊነካብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:8, 9፤ ያዕቆብ 3:5–10) ነገር ግን አይዞህ፣ ራስን በመግዛት ረገድ ማሻሻል ትችላለህ!
20. ራስ መግዛትን በተመለከተ ማሻሻል እንደሚቻል እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
20 ይሖዋ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ነው። ስለዚህ ጉዳይ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ራስን መግዛት ከመንፈሱ ፍሬዎች አንዱ ክፍል ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ከዚህም የተነሣ ከይሖዋ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ብቁ በሆንንና ፍሬዎቹን ለማሳየት በጣርን መጠን በዚያው ልክ ራሳችንን የምንገዛ ልንሆን እንችላለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ኢየሱስ ‘በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል’ በማለት የሰጠውን ዋስትና አትርሳ። — ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15
21. ራስን መግዛትና ስሜቶችህን መቆጣጠርን በተመለከት ወደፊት ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
21 ነገሩ ቀላል ይሆናል ብለህ አታስብ። ለስሜታቸው ገደብ የለሽ ነፃነት የሚሰጡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በትንሹ የሚቆጡ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ላደጉ ወይም ራስ መግዛት የሚባለውን ነገር ፈጽሞ ሳያሳዩ ለኖሩ ሰዎች ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። እንደዚህ ያለው ክርስቲያን ራስን መግዛት እንዲኖረውና እንዲበዛለት ማድረጉ ትልቅ ፈተና ይሆንበታል። ቢሆንም፣ ይቻላል! (1 ቆሮንቶስ 9:24–27) ወደ አሁኑ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እየተቃረብን በሄድን መጠን ውጥረቶቹና ግፊቶቹ እየጨመሩ ይሄዳሉ። ወደፊት ከአሁኑ ያነሰ ሳይሆን ከአሁኑ የበለጠ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት ያስፈልገናል። ራስህን እየገዛህ ስለመሆኑ ራስህን መርምር። ማሻሻል የሚያስፈልግህ አቅጣጫ ካለ ያንን ለማሻሻል ጣር። (መዝሙር 139:23, 24) አምላክ ጨምሮ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው። ልመናህን ይሰማል እንዲሁም ራስን የመግዛት ባሕርይ እንዲኖርህ ብቻ ሳይሆን እንዲበዛልህም ይረዳሃል። — 2 ጴጥሮስ 1:5–8
የምታስብባቸው ነጥቦች
◻ ስሜቶችህን መቆጣጠር ያን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ከሐማ እንዲሁም ከኤዎድያና ከሲንጤኪ ምን ተምረሃል?
◻ የተከፋህበት ሁኔታ ካጋጠመህ በሐቀኝነት ምን ለማድረግ ጥረት ታደርጋለህ?
◻ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማንኛውንም ዓይነት ቂም ከመያዝ እንድትርቅ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፊልክስና በድሩሲላ ፊት በቀረበ ጊዜ ጳውሎስ ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ተናግሯል