የጥናት ርዕስ 15
ሰላማችሁን ጠብቃችሁ በመኖር ኢየሱስን ምሰሉ
“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵ. 4:7
መዝሙር 113 ከአምላክ ያገኘነው ሰላም
የትምህርቱ ዓላማa
1-2. ኢየሱስ ተጨንቆ የነበረው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ላይ በጣም ተጨንቆ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በክፉ ሰዎች እጅ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሊገደል ነው። ሆኖም ኢየሱስን ያስጨነቀው ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ብቻ አልነበረም። አባቱን በጣም የሚወደው ከመሆኑም ሌላ እሱን ማስደሰት ይፈልጋል። ኢየሱስ ይህን ፈታኝ ወቅት በታማኝነት ከተወጣ የይሖዋ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያውቃል። ኢየሱስ ሰዎችንም ይወድ ነበር፤ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው ታማኝነቱን ጠብቆ በመሞቱ ላይ እንደሆነ ያውቃል።
2 ኢየሱስ በጣም ተጨንቆ የነበረ ቢሆንም ውስጣዊ ሰላሙን አላጣም። ሐዋርያቱን “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 14:27) ኢየሱስ “የአምላክ ሰላም” ማለትም አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ውድ ዝምድና በመመሥረቱ ምክንያት የሚያገኘው ውስጣዊ መረጋጋት ነበረው። ይህ ሰላም አእምሮውንና ልቡን አረጋግቶለታል።—ፊልጵ. 4:6, 7
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ማናችንም ብንሆን ኢየሱስ የደረሰበት ዓይነት ከባድ ፈተና እንደማይደርስብን የታወቀ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስን የሚከተል ማንኛውም ክርስቲያን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመዋል። (ማቴ. 16:24, 25፤ ዮሐ. 15:20) በዚህም የተነሳ ልክ እንደ ኢየሱስ የምንጨነቅበት ጊዜ ይኖራል። ታዲያ ጭንቀት እንዳይቆጣጠረንና የአእምሮ ሰላማችንን እንዳያሳጣን ምን ማድረግ እንችላለን? ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ያደረጋቸውን ሦስት ነገሮች እንዲሁም ፈተና ሲደርስብን እሱ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጸልዮአል
4. በ1 ተሰሎንቄ 5:17 ላይ ባለው ሐሳብ መሠረት ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ባጠናቀቀበት የመጨረሻ ቀን ላይ በተደጋጋሚ ይጸልይ እንደነበር የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
4 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:17ን አንብብ። ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ባጠናቀቀበት የመጨረሻ ቀን ላይ በተደጋጋሚ ጸልዮአል። የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ወቅት ለቂጣውና ለወይን ጠጁ ጸልዮአል። (1 ቆሮ. 11:23-25) የፋሲካን በዓል ካከበሩበት ቤት ከመውጣቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጸልዮአል። (ዮሐ. 17:1-26) ማታ ላይ እሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ከሄዱ በኋላ በተደጋጋሚ ጸልዮአል። (ማቴ. 26:36-39, 42, 44) ልክ ከመሞቱ በፊት የተናገረው ሐሳብ ራሱ ጸሎት ነበር። (ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ በዚያን ዕለት ከተከናወነው ከእያንዳንዱ ወሳኝ ክንውን ጋር በተያያዘ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል።
5. ሐዋርያቱ የደረሰባቸውን ፈተና በድፍረት መወጣት ያልቻሉት ለምን ነበር?
5 ኢየሱስ የደረሰበትን ፈተና በጽናት መወጣት የቻለበት አንዱ ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ አባቱ በመጸለይ የእሱን እርዳታ ይጠይቅ ስለነበር ነው። በሌላ በኩል ግን ሐዋርያቱ በዚያ ምሽት በጸሎት ሳይጸኑ ቀርተዋል። በመሆኑም የደረሰባቸውን ፈተና በድፍረት መወጣት አልቻሉም። (ማቴ. 26:40, 41, 43, 45, 56) እኛም ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ታማኝ ሆነን መቀጠል የምንችለው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ‘ሳናሰልስ ከጸለይን’ ብቻ ነው። ለመሆኑ ስለ ምን ነገር መጸለይ እንችላለን?
6. እምነት ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዳን እንዴት ነው?
6 “እምነት ጨምርልን” በማለት ወደ ይሖዋ ልንጸልይ እንችላለን። (ሉቃስ 17:5፤ ዮሐ. 14:1) ሰይጣን የኢየሱስን ተከታዮች በሙሉ ስለሚፈትን እምነት ያስፈልገናል። (ሉቃስ 22:31) ይሁንና ተደራራቢ የሆኑ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እምነት ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው? እምነት፣ አንድን ፈታኝ ሁኔታ ለመወጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን በኋላ የቀረውን ለይሖዋ እንድንተው ያነሳሳናል። ይሖዋ ጉዳዩን ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ሊይዘው እንደሚችል ስለምንተማመን ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን።—1 ጴጥ. 5:6, 7
7. ከወንድም ሮበርት ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
7 ጸሎት ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ሮበርት የተባሉ አንድ ታማኝ የጉባኤ ሽማግሌ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብለዋል፦ “በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘው ምክር በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝን ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድወጣ ረድቶኛል። የኢኮኖሚ ችግር ያጋጠመኝ ወቅት ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደግሞ በሽምግልና የማገልገል መብቴን አጥቼ ነበር።” ታዲያ ወንድም ሮበርት ውስጣዊ ሰላማቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት ነው? “ጭንቀት ሲሰማኝ ወዲያውኑ እጸልያለሁ። በተደጋጋሚ አጥብቄ በጸለይኩ ቁጥር ይበልጥ ውስጣዊ ሰላም አገኛለሁ” በማለት ተናግረዋል።
ኢየሱስ በቅንዓት ሰብኳል
8. በዮሐንስ 8:29 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ውስጣዊ ሰላሙን ይዞ እንዲቀጥል የረዳው ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?
8 ዮሐንስ 8:29ን አንብብ። ኢየሱስ ስደት በደረሰበት ጊዜም እንኳ ውስጣዊ ሰላሙን ይዞ መቀጠል የቻለው አባቱን እያስደሰተ እንዳለ ስላወቀ ነው። የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር ከመታዘዝ ወደኋላ አላለም። አባቱን ይወድ ስለነበር መላ ሕይወቱ ያተኮረው እሱን በማገልገል ላይ ነበር። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ አምላክን አገልግሏል። (ምሳሌ 8:30) ወደ ምድር ከመጣ በኋላ ደግሞ ሌሎችን ስለ አባቱ በቅንዓት አስተምሯል። (ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 5:17) ይህ ሥራ ለኢየሱስ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል።—ዮሐ. 4:34-36
9. በስብከቱ ሥራ መጠመዳችን ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዳን እንዴት ነው?
9 ይሖዋን በመታዘዝና ‘ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛልን በመሆን’ ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። (1 ቆሮ. 15:58) በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ስንጠመድ’ ለችግሮቻችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ቀላል ይሆንልናል። (ሥራ 18:5) ለምሳሌ ያህል፣ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከእኛ የባሱ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ሆኖም ለይሖዋ ፍቅር እያዳበሩ ሲሄዱና ምክሮቹን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሕይወታቸው ስለሚሻሻል ደስተኞች ይሆናሉ። ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ለውጥ ስንመለከት ይሖዋ እኛንም እንደሚንከባከበን ያለን እምነት ይጠናከራል። ይህ እምነት ደግሞ ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። ሥር ከሰደደ የመንፈስ ጭንቀትና የዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር ዕድሜ ልኳን ስትታገል የኖረች አንዲት እህት የዚህን እውነተኝነት ተመልክታለች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በአገልግሎት ስጠመድ ስሜቴ ይረጋጋል እንዲሁም ደስተኛ እሆናለሁ። ምክንያቱም አገልግሎት ላይ ስሆን ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።”
10. ከብሬንዳ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
10 ብሬንዳ የተባለችን እህት ተሞክሮም መመልከት እንችላለን። እሷም ሆነች ሴት ልጇ የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ሽባ በሚያደርግ በሽታ (መልቲፕል ስክለሮሲስ) ይሠቃያሉ። ብሬንዳ ያለተሽከርካሪ ወንበር እርዳታ መንቀሳቀስ አትችልም፤ እንዲሁም በሽታው አቅም ያሳጣታል። ሁኔታዋ ሲፈቅድላት ከቤት ወደ ቤት ታገለግላለች፤ በዋነኝነት የምትመሠክረው ግን በደብዳቤ አማካኝነት ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ያለብኝ የጤና እክል በዚህ ሥርዓት መፍትሔ እንደሌለው አምኜ መቀበሌ ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቴ ላይ እንዳተኩር አስችሎኛል። በአገልግሎት መካፈሌ፣ የሚያስጨንቁኝን ነገሮች እንድረሳ ይረዳኛል። ምክንያቱም ትኩረቴ ያረፈው በጉባኤያችን ክልል ውስጥ የማገኛቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ ነው። በተጨማሪም የወደፊቱ ተስፋዬ ምንጊዜም ከአእምሮዬ እንዳይጠፋ ያስችለኛል።”
ኢየሱስ ወዳጆቹ የሰጡትን እርዳታ ተቀብሏል
11-13. (ሀ) ሐዋርያቱ እንዲሁም ሌሎች ወንዶችና ሴቶች የኢየሱስ እውነተኛ ወዳጆች መሆናቸውን ያስመሠከሩት እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ ወዳጆች ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድረውበታል?
11 በፈተና በተሞላው የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ታማኝ ሐዋርያቱ የኢየሱስ እውነተኛ ወዳጆች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። ሐዋርያቱ “ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ” የሚለውን ጥቅስ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። (ምሳሌ 18:24) ኢየሱስ እንዲህ ላሉት ወዳጆቹ ከፍ ያለ ግምት ነበረው። አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ከሥጋ ወንድሞቹ መካከል አንዳቸውም አላመኑበትም ነበር። (ዮሐ. 7:3-5) እንዲያውም በአንድ ወቅት ዘመዶቹ አእምሮውን እንደሳተ ሰው ቆጥረውታል። (ማር. 3:21) ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ታማኝ ሐዋርያቱን አስመልክቶ ሲናገር “እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል” ብሏል።—ሉቃስ 22:28
12 እርግጥ ነው፣ ሐዋርያቱ ኢየሱስን የሚያሳዝን ድርጊት የፈጸሙባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ኢየሱስ ግን በሠሯቸው ስህተቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ተመልክቷል። (ማቴ. 26:40፤ ማር. 10:13, 14፤ ዮሐ. 6:66-69) ከመገደሉ በፊት ከእነሱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 15:15) የኢየሱስ ወዳጆች ከፍተኛ የብርታት ምንጭ እንደሆኑለት ምንም ጥርጥር የለውም። በአገልግሎት ያደረጉለት ድጋፍ ልቡ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል።—ሉቃስ 10:17, 21
13 ኢየሱስ ከሐዋርያቱ በተጨማሪ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ወዳጆች ነበሩት፤ እነዚህ ሰዎች በስብከቱ ሥራም ሆነ በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች ድጋፍ አድርገውለታል። አንዳንዶቹ ቤታቸውን ምንጊዜም ክፍት በማድረግ አብሯቸው እንዲመገብ ይጋብዙት ነበር። (ሉቃስ 10:38-42፤ ዮሐ. 12:1, 2) ሌሎቹ ደግሞ አብረውት በመጓዝ በንብረታቸው የሚያስፈልገውን ነገር ያሟሉለት ነበር። (ሉቃስ 8:3) ኢየሱስ ጥሩ ወዳጆች ሊኖሩት የቻሉት እሱ ራሱ ጥሩ ወዳጅ ስለነበር ነው። ለወዳጆቹ መልካም ነገር ያደርግ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከእነሱ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነበር። ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም ፍጽምና የጎደላቸው ወዳጆቹ ለሚያደርጉለት ድጋፍ አድናቆት ነበረው። ደግሞም ወዳጆቹ ውስጣዊ ሰላሙን ጠብቆ እንዲኖር እንደረዱት ምንም ጥርጥር የለውም።
14-15. ጥሩ ወዳጆችን ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያሉ ወዳጆች የሚረዱንስ እንዴት ነው?
14 ጥሩ ወዳጆች ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ይረዱናል። እንዲህ ያሉ ወዳጆችን ማፍራት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ እኛ ራሳችን ጥሩ ወዳጆች ሆነን መገኘት ነው። (ማቴ. 7:12) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ሳንቆጥብ ሌሎችን በተለይም ‘የተቸገሩትን’ እንድንረዳ ያበረታታናል። (ኤፌ. 4:28) ከጉባኤህ አባላት መካከል ልትረዳው የምትችለው ሰው ይኖር ይሆን? በዕድሜ መግፋት ወይም በሕመም ምክንያት ከቤት መውጣት ለማይችል አስፋፊ ገበያ ወጥተህ አንዳንድ ነገሮችን ልትገዛለት ትችላለህ? የኢኮኖሚ ችግር ላለበት አንድ ቤተሰብ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ነገር መስጠት ትችል ይሆን? jw.org® የተባለውን ድረ ገጽና JW Library® የተባለውን አፕሊኬሽን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የምታውቅ ከሆነ ደግሞ ሌሎች የጉባኤህ አባላትም ከእነዚህ ዝግጅቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት ትችላለህ? ሌሎችን በመርዳት ላይ ትኩረት ስናደርግ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን።—ሥራ 20:35
15 በዚህ መልኩ የምናፈራቸው ወዳጆች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይደግፉናል፤ እንዲሁም ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል። ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ ሲናገር ኤሊሁ እንዳዳመጠው ሁሉ ወዳጆቻችንም ያስጨነቀንን ነገር ስንናገር በትዕግሥት ያዳምጡናል። (ኢዮብ 32:4) ወዳጆቻችን ውሳኔዎችን እንዲያደርጉልን መጠበቅ የለብንም፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጡን ማዳመጣችን ጥበብ ነው። (ምሳሌ 15:22) ንጉሥ ዳዊት ወዳጆቹ ያደረጉለትን እርዳታ በትሕትና ተቀብሏል፤ እኛም በኩራት ተሸንፈን ወዳጆቻችን የሚሰጡንን እርዳታ ከመቀበል ወደኋላ ማለት የለብንም። (2 ሳሙ. 17:27-29) በእርግጥም እንዲህ ያሉ ወዳጆች የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው።—ያዕ. 1:17
ሰላማችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
16. በፊልጵስዩስ 4:6, 7 መሠረት ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው? አብራራ።
16 ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ። ይሖዋ እሱ የሚሰጠውን ሰላም ማግኘት የምንችለው “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት” እንደሆነ የነገረን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ዘላቂ የሆነ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምንችለው ኢየሱስ የሚጫወተውን ሚና ከተረዳንና በዚያ ላይ እምነት ካሳደርን ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኃጢአታችን ሁሉ ይቅር የሚባልልን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (1 ዮሐ. 2:12) ይህን ማሰባችን ከፍተኛ እፎይታ ያስገኝልናል! ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሰይጣንና እሱ የሚቆጣጠረው ሥርዓት በእኛ ላይ ያደረሱትን ማንኛውንም ጉዳት ያስወግድልናል። (ኢሳ. 65:17፤ 1 ዮሐ. 3:8፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ተስፋ ነው! በተጨማሪም ኢየሱስ ከባድ ኃላፊነት የሰጠን ቢሆንም እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ ከእኛ ጋር በመሆን ይደግፈናል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህም ደፋሮች እንድንሆን ያደርገናል! እፎይታ፣ ተስፋና ድፍረት ደግሞ የአእምሮ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዱ በጣም ወሳኝ ነገሮች ናቸው።
17. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ውስጣዊ ሰላሙን ጠብቆ መኖር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በዮሐንስ 16:33 ላይ ቃል በገባው መሠረት ምን ማድረግ እንችላለን?
17 ታዲያ ከባድ ፈተናዎች ሲደርሱብህ የአእምሮ ሰላምህን ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች በማድረግ ነው። አንደኛ፣ ጸልይ እንዲሁም በጸሎት ጽና። ሁለተኛ፣ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይሖዋን በመታዘዝ ምሥራቹን በቅንዓት ስበክ። ሦስተኛ፣ ወዳጆችህ የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ የአምላክ ሰላም አእምሮህንና ልብህን ይጠብቅልሃል። በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ ማንኛውንም ፈተና ማሸነፍ ትችላለህ።—ዮሐንስ 16:33ን አንብብ።
መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ
a ሁላችንም ሰላማችንን ሊያሳጡን ከሚችሉ ችግሮች ጋር እንታገላለን። ይህ ርዕስ ኢየሱስ ሰላሙን ጠብቆ እንዲኖር የረዱትን ሦስት ነገሮች ያብራራል፤ እኛም እነዚህን ነገሮች በማድረግ ከባድ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ሰላማችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።