በጽናት ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ጨምሩ
“በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት] . . . ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:5, 6
1, 2. (ሀ) ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በናዚ ቁጥጥር ሥር ባሉ አገሮች በሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች ላይ ምን ደረሰ? ለምንስ? (ለ) ያደረሱባቸው ይህ ሁሉ ሥቃይ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምን ውጤት አመጣ?
ጊዜው በ20ኛው መቶ ዘመን ታሪክ ውስጥ ከነበሩት ጊዜያት ሁሉ የከፋ ጊዜ ነበር። ከ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ በናዚ ቁጥጥር ሥር በነበሩ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ይታሰሩና ወደ እስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ይጣሉ ነበር። ለምን? በቆራጥነት ገለልተኛ በመሆናቸውና ‘አዳኛችን ሂትለር ነው’ የሚል መፈክር ለማሰማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነበር። በእስር ቤት ውስጥስ ምን ደረሰባቸው? “የኤስ ኤስ ወታደሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን [የይሖዋ ምስክሮችን] ያህል . . . በጭካኔ ያሰቃዩት ሌላ የእስረኞች ቡድን አልነበረም። በዓለም ላይ ያለ የትኛውም ቋንቋ ሊገልጸው የማይችል የማያቋርጥ የአካልና የአእምሮ ሥቃይ ያደርሱባቸው ነበር።” — የቀድሞ የጀርመን መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበሩት ካርል ዊቲግ።
2 ታዲያ የይሖዋ ምስክሮች አቋም ምን ነበር? ዘ ናዚ ስቴት ኤንድ ዘ ኒው ሪሊጅንስ:- ፋይቭ ኬዝ ስተዲስ ኢን ነን ኮንፈርሚቲ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ዶክተር ክርቲን ኢ ኪንግ እንዲህ ብለዋል:- “[ከሌሎቹ የሃይማኖት ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር] የመንግሥት ጥረት ያልተሳካው በምስክሮቹ ላይ ብቻ ነበር።” አዎን፤ ምንም እንኳን የደረሰባቸው መከራ በመቶ ለሚቆጠሩት እስከ ሞት ድረስ መጽናትን የጠየቀባቸው ቢሆንም በቡድን ደረጃ ስንመለከታቸው የይሖዋ ምስክሮች ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ቆመዋል።
3. የይሖዋ ምስክሮች ከባድ መከራዎችን ችለው እንዲጸኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው?
3 የይሖዋ ምስክሮች በናዚ ጀርመን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሌሎች አገሮችም ጭምር እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ለአምላክ ያደሩ በመሆናቸው ምክንያት የሰማዩ አባታቸው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። ‘ይሖዋ ለእርሱ ያደሩትን ሰዎች ከፈተና እንዴት እንደሚያድን ያውቃል’ ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 2:9 አዓት) በዚያው ደብዳቤ ላይ ከፍ ብሎ ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት] . . . ጨምሩ” በማለት መክሯቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ስለዚህ ጽናት ለአምላክ ያደሩ ከመሆን ጋር በጣም የተያያዘ ነው። እንዲያውም እስከ መጨረሻው ለመጽናት ‘ለአምላክ ማደርን መከታተል’ እንዲሁም ማሳየት ይኖርብናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11 አዓት) ግን ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው?
ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው?
4, 5. ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ማለት ነው?
4 “ለአምላክ ያደሩ መሆን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም (ዩሴብያ) “ተገቢ የሆነ ከፍተኛ አክብሮት” ተብሎ ቃል በቃል ሊተረጎም ይችላል።a (2 ጴጥሮስ 1:6 ኪንግደም ኢንተርሊንየር) ቃሉ ለአምላክ የምናሳየውን ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ስሜት ያንጸባርቃል። በደብልዩ ኢ ቫይን አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም “ተገቢና አክብሮታዊ” የሚል ፍቺ ያለው ዩሴበስ የተባለው ቅጽል “አምላክን በቅድስና በማክበር የሚመራውንና በሙሉ ልብ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚገለጸውን ኃይል ያመለክታል።” — 2 ጴጥሮስ 2: 9
5 ስለዚህ “ለአምላክ ያደሩ መሆን” የሚለው ቃል ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር እንድናደርግ የሚያነሳሳን ከፍተኛ አክብሮት ወይም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ያመለክታል። አምላክን ከልባችን ስለምንወደው ይህን የምናደርገው ከባድ መከራዎች በሚደርሱብን ጊዜም ጭምር ነው። በአኗኗራችን የሚገለጽ ይሖዋን የሙጥኝ የማለትና በታማኝነት ከይሖዋ ጎን የመቆም ባሕርይ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ በማደር . . . ጸጥና ዝግ ብለው’ ለመኖር ይችሉ ዘንድ እንዲጸልዩ በጥብቅ ተመክረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2) የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ በሆኑት ጄ ፒ ሎ እና ኢ ኤ ኒዳ እንደገለጹት “በ1 ጢሞ 2.2 ላይ የተጠቀሰው [ዩሴብያ] በብዙ ቋንቋዎች ‘አምላክ የሚፈልገውን ዓይነት ኑሮ መኖር’ ወይም ‘አምላክ በነገረን መንገድ መኖር’ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።”
6. በጽናትና ለአምላክ ያደሩ በመሆን መካከል ምን ዝምድና አለ?
6 አሁን በመጽናትና ለአምላክ ያደሩ በመሆን መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ ለመገንዘብ እንችላለን። አምላክ በሚፈልገው መንገድ ማለትም ለአምላክ ያደርን ሆነን ስለምንኖር ዓለም ይጠላናል። ይህ ደግሞ የእምነት ፈተና ማስከተሉ አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ከሰማያዊ አባታችን ጋር ኃይለኛ ቅርርብ ባይኖረን ኖሮ እነዚህን የመሳሰሉትን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋማቸው አንገፋፋም ነበር። ከዚህም በላይ ይሖዋ እንዲህ ያለውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ዝም ብሎ አይመለከትም። ለይሖዋ በማደራቸው ምክንያት ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢመጣባቸው እርሱን ለማስደሰት ጥረት የሚያደርጉትን ሰዎች ሰማይ ሆኖ ሲመለከት ምን እንደሚሰማው አስብ። ‘ለአምላክ ያደሩትን ሰዎች ከፈተና ለማዳን’ እንደሚፈልግ አያጠራጥርም!
7. ለአምላክ የማደርን ባሕርይ መኮትኮት ያለብን ለምንድን ነው?
7 ይሁን እንጂ ለአምላክ ያደርን ሆነን አልተወለድንም፤ ወይም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ወላጆች ልንወርስ አንችልም። (ዘፍጥረት 8:21) ከዚህ ይልቅ መኮትኮትና ማደግ ያለበት ባሕሪይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:7, 10) በጽናታችንና በእምነታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ለመጨመር መጣር አለብን። ጴጥሮስ ይህን ማድረግ “ትጋት” እንደሚጠይቅ ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 1:5) ታዲያ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ እንዴት ልናገኝ እንችላለን?
8. ሐዋርያው ጴጥሮስ በተናገረው መሠረት ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው?
8 ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ልናገኝ የምንችልበትን ቁልፍ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “የመለኮቱ ኃይል፣ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፣ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል [ለአምላክ ያደሩ ለመሆን አዓት] የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፣ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።” (2 ጴጥሮስ 1:2, 3) ስለዚህ በእምነታችንና በጽናታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ለመጨመር ትክክለኛ እውቀት ማለትም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሟላ እውቀት ማግኘትና ማሳደግ ይገባናል።
9. ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት መያዝ ማንነታቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገርን እንደሚያጠቃልል በምሳሌ ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?
9 ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ማለት ምን ማለት ነው? ማንነታቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገር እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት:- ጎረቤትህ ማን እንደሆነ ታውቃለህ፤ እንዲያውም ስሙን እየጠራህ ሰላም ትለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ታበድረዋለህን? ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ በደንብ ካላወቅህ በስተቀር አታበድረውም። (ከምሳሌ 11:15 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ይሖዋንና ኢየሱስን በትክክል ወይም ሙሉ በሙሉ ማወቅ ሕልውናቸውን ከማመንና ስማቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ለእነርሱ ብለን እስከ ሞት ድረስ ለመጽናት ከፈለግን ከእነርሱ ጋር የቅርብ ትውውቅ ሊኖረን ይገባል። (ዮሐንስ 17:3) ይህ ምንን ይጨምራል?
10. ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት መያዝ ምን ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል? ለምንስ?
10 ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ወይም የተሟላ እውቀት ማግኘት ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል። እነርሱም:- (1) የይሖዋንና የኢየሱስን ስብዕና ማለትም ባሕርያቸውን፣ ስሜታቸውንና መንገዳቸውን ማወቅና (2) እነርሱን መምሰል ናቸው። ለአምላክ ያደሩ መሆን ይሖዋን በግል ከልባችን መውደድንና ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረትን ይጨምራል። ይህ ደግሞ የሚገለጸው በአኗኗራችን ነው። እንግዲያው ይህንን ባሕርይ ለማግኘት የሰው አቅም እስከሚችለው ድረስ ይሖዋን በግል ማወቅና ከፈቃዱና ከመንገዶቹ ጋር በደንብ መተዋወቅ አለብን። በእውነትም በአምሳሉ የፈጠረንን ይሖዋን ለማወቅ እንደዚህ ባለው እውቀት መጠቀምና እርሱን ለመምሰል መጣር አለብን። (ዘፍጥረት 1:26–28፤ ቆላስይስ 3:10) ኢየሱስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ስለመሰለው ኢየሱስን ማወቃችን ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ለማዳበር ጠቃሚ እገዛ ያደርግልናል። — ዕብራውያን 1:3
11. (ሀ) ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ታዲያ ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እንዲህ ያለውን እውቀት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት ነው።b ይሁን እንጂ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚያስገኝልን ጊዜ ወስደን ያነበብነውን ነገር ስናሰላስል ማለትም በነገሩ ላይ ስናስብበት ወይም ስናወጣና ስናወርደው ነው። (ከኢያሱ 1:8 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለአምላክ ያደሩ መሆን ለአምላክ ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ስሜት ማሳደር ማለት መሆኑን አስታውስ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ማሰላሰል ከምሳሌያዊው ልብ ማለትም ከውስጣዊው ሰውነት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ተገልጿል። (መዝሙር 19:14፤ 49:3፤ ምሳሌ 15:28) ያነበብነውን ነገር በአድናቆት ብናሰላስለው ውስጣዊ ሰውነታችን ውስጥ ጠልቆ ስለሚገባ አስተሳሰባችንን በመቆጣጠር ስሜታችንን ይቀሰቅሰዋል። ጥናታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን የግል ግንኙነት ሊያጠናክርልን የሚችለውና ፈታኝ ሁኔታዎች ወይም ከባድ መከራዎች ቢደርሱብንም እንኳን አምላክን በሚያስደስት መንገድ እንድንኖር የምንገፋፋው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።
በቤት ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማሳየት
12. (ሀ) ጳውሎስ በተናገረው መሠረት አንድ ክርስቲያን ለአምላክ ያደረ መሆኑን በቤት ውስጥ ለማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ያረጁ ወላጆቻቸውን መጦር ያለባቸው ለምንድን ነው?
12 ለአምላክ ያደሩ የመሆን ባሕርይ በመጀመሪያ ደረጃ መታየት የሚኖርበት በቤት ውስጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ የማደርን ባሕርይ አዓት] ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 5:4) ጳውሎስ እንዳስገነዘበው ያረጁ ወላጆችን መጦር ለአምላክ ያደርን ሰዎች መሆናችን ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ወላጆቻቸውን የሚጦሩት ግዴታቸው እንደሆነ ስለሚሰማቸው ብቻ ሳይሆን ለወላጆቻቸው ባላቸው ፍቅር የተነሳ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ ቤተሰብን መንከባከብን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ነገር አድርጎ እንደሚመለከተው ያውቃሉ። ወላጆች እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ጀርባቸውን መስጠት ‘ሃይማኖትን ከመካድ’ ጋር እንደሚመጣጠን በሚገባ ይገነዘባሉ። — 1 ጢሞቴዎስ 5:8
13. በቤት ውስጥ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማሳየት የሚያስቸግረው በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል? ይሁን እንጂ ወላጆችን በመጦር ምን እርካታ ይገኛል?
13 በቤት ውስጥ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። የቤተሰቡ አባሎች የሚኖሩት በጣም በተራራቁ ቦታዎች ሊሆን ይችላል። ራሳቸውን የቻሉት ልጆች የሚንከባከቡት የራሳቸው ቤተሰብ ሊኖራቸው ወይም የኢኮኖሚ ችግር ሊኖርባቸው ይችላል። ወላጆች የሚፈልጉት የእንክብካቤ ዓይነት ወይም መጠኑ የተንከባካቢውን የአካል፣ የአእምሮና የስሜት ጤንነት የሚያደክም ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን አንድ ሰው ወላጆቹን በመጦሩ ‘ብድሩን ከመመለሱም’ በላይ ‘በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ የሚሰየምበትን’ አምላክ ያስደስታል። — ኤፌሶን 3:14, 15 አዓት
14, 15. ልጆች ለወላጃቸው ያደረጉትን አምላካዊ ባሕርይ የሚታይበት እንክብካቤ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገር።
14 ቀጥሎ ያለውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተመልከት። ኤለስና አምስት ወንድሞቹና እህቶቹ አባታቸውን በቤት የማስታመም ከባድ ሥራ አለባቸው። “በ1986 አባቴ በደም ግፊት መብዛት ምክንያት ደሙ አንጎሉ ውስጥ በመፍሰሱ ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆነ” ይላል ኤለስ። ስድስቱም ልጆች አባታቸውን በማስታመሙ ሥራ ይካፈላሉ። ይህም ገላውን ከማጠብ አንስቶ የአልጋ ቁራኛ በመሆኑ ምክንያት ጎኑ እንዳይቆስል በየጊዜው ማገላበጥን ይጨምራል። “እናነብለታለን፣ እናወራለታለን ሙዚቃም እንጫወትለታለን። በአካባቢው እየተደረገ ያለውን ነገር ይወቅ አይወቅ እርግጠኞች አይደለንም፤ ቢሆንም ልክ ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ አድርገን እንይዘዋለን።”
15 ልጆቹ አባታቸውን ይህን ያህል የሚንከባከቡት ለምንድን ነው? ኤለስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በ1964 እናታችን ከሞተች በኋላ አባባ ያሳደገን ብቻውን ሆኖ ነበር። በጊዜው ዕድሜያችን ከ5 እስከ 14 ይደርስ ነበር። በዚያን ጊዜ የደረሰልን እርሱ ነበር፤ አሁን ደግሞ እኛ ደረስንለት።” እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ ማድረግ ቀላል እንዳልሆነና ልጆቹም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንደሚቆርጡ ግልጽ ነው። “ነገር ግን አባታችን በዚህ ሁኔታ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን” ይላል ኤለስ። “አባታችን ጤናው የሚመለስለትንና ከእናታችን ጋር እንደገና የምንገናኝበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።” (ኢሳይያስ 33:24፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ለወላጆች በሙሉ ልብ የሚደረግ እንዲህ ያለ እንክብካቤ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ያዘዘውን አምላክ ልብ ደስ እንደሚያሰኝ የተረጋገጠ ነው!c — ኤፌሶን 6:1, 2
ለአምላክ ያደሩ መሆንና አገልግሎት
16. የምናገለግልበት ዋነኛው ምክንያት ምን መሆን ይኖርበታል?
16 ኢየሱስ ‘ያለማቋረጥ እንድንከተለው’ ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ በሚያዝዝ መለኮታዊ ግዴታ ሥር ገብተናል ማለት ነው። (ማቴዎስ 16:24 አዓት፤ 24:14፤ 28:19, 20) በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ በአገልግሎት መካፈል ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ ለመስበክና ለማስተማር የምንነሳሳው ግዴታችን ስለሆነ ብቻ መሆን የለበትም። በአገልግሎቱ እንድንሳተፍና በዚያ መጠን ያህል እንድናገለግል የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር መሆን አለበት። ኢየሱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) አዎን፤ ልባችን ለይሖዋ ባለን ፍቅር የተትረፈረፈ ከሆነ ስለ እርሱ ለሌሎች ለመመስከር እንገፋፋለን። የሚገፋፋን ኃይል ለአምላክ ያለን ፍቅር ከሆነ አገልግሎታችን ለአምላክ ያደርን መሆናችን የሚገለጥበት ጥሩ መንገድ ይሆናል።
17. ለአገልግሎት የሚገፋፋንን ትክክለኛ ኃይል ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
17 ለአገልግሎት የሚገፋፋንን ትክክለኛ ዓላማ ልናዳብር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እርሱን እንድንወድደው የሰጠንን ሦስት ምክንያቶች በአድናቆት በማሰላሰል ነው። (1) እስካሁን ባደረገልን ነገሮች የተነሳ ይሖዋን እንወድደዋለን። ቤዛውን በመስጠት ካሳየን ፍቅር የሚበልጥ ፍቅር ሊያሳየን አይችልም። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 15:13) (2) በአሁኑ ጊዜ እያደረገልን ባሉት ነገሮች የተነሳ ይሖዋን እንወድደዋለን። ከይሖዋ ጋር በነፃነት ልንነጋገር እንችላለን። እርሱም ጸሎታችንን ይመልስልናል። (መዝሙር 65:2፤ ዕብራውያን 4:14–16) ለመንግሥቱ ጥቅሞች ቅድሚያ በሰጠን መጠን ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች እናገኛለን። (ማቴዎስ 6:25–33) የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም የሚረዳ የማያቋርጥ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:45) ከቀረው ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚለየን የዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አባላት በመሆናችን ተባርከናል። (1 ጴጥሮስ 2:17) (3) ገና ወደፊት በሚያደርግልን ነገሮች ምክንያትም ይሖዋን እንወድደዋለን። ከፍቅሩ የተነሳ ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን ይዘናል፤’ እርሱም ወደፊት የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ይሖዋ ያሳየንን ፍቅር ስንመለከት ስለ እርሱና ስለ ክቡር ዓላማው ለሌሎች በመንገሩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ልባችን እንደሚገፋፋ አያጠራጥርም! ማድረግ ስላለብን ነገር ወይም በአገልግሎቱ ምን ያህል መሥራት እንዳለብን ሌሎች እንዲነግሩን አያስፈልግም። የምንችለውን ያህል እንድናደርግ ልባችን ይገፋፋናል።
18, 19. አንዲት እህት በአገልግሎት ለመካፈል ስትል የተወጣችው ዕንቅፋት ምን ነበር?
18 ለአምላክ በማደር ባሕርይ የተገፋፋ ልብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙት እንኳን ለመናገር ይገፋፋል። (ከኤርምያስ 20:9 ጋር አወዳድር።) ይህም ስቴላ በተባለች እጅግ ዓይናፋር በሆነች ክርስቲያን እህት ተሞክሮ ታይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ገና እንደጀመረች ‘ከቤት ወደ ቤት መሄድ በጭራሽ አልችልም!’ ስትል አሰበች። “ሁልጊዜ ዝምተኛ ነበርኩ። ሰዎችን ቀርቤ አነጋግሬ ውይይት መጀመር ፈጽሞ አይሆንልኝም” ትላለች። ጥናቷን እየቀጠለች ስትሄድ ለይሖዋ ያላት ፍቅር እየጨመረ በመምጣቱ ስለ እርሱ ለሌሎች ለመናገር ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት። “የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዬን ‘ለመናገር በጣም እፈልጋለሁ፤ ግን መናገር አልችልም፤ አለመቻሌ ደግሞ ያናድደኛል’ ብዬ እንደነገርኳት አስታውሳለሁ። እሷም ‘ስቴላ፣ ለመናገር ፍላጎቱ ስላለሽ አመስጋኝ ሁኚ’ ብላ የነገረችን እስከመቼም አልረሳውም።”
19 ብዙም ሳትቆይ ስቴላ ለጎረቤቷ መመስከር ጀመረች። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በመካፈል ትልቅ እርምጃ ወሰደች። (ሥራ 20:20, 21) እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “የምናገረውን መልእክት ጽፌው ነበር፤ ግን በጣም ፈርቼና ተደናግጬ ስለነበር ማስታወሻዬ ከፊት ለፊቴ እያለ እንኳን ጎንበስ ብዬ ማንበብ አልቻልኩም!” አሁን ይህ ከሆነ 35 ዓመት ያለፈው ቢሆንም አሁንም ስቴላ በተፈጥሮዋ በጣም ዓይን አፋር ነች። ሆኖም የመስክ አገልግሎቱን ትወድደዋለች፤ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት በሚገባ ትካፈላለች።
20. ስደትም ሆነ እስራት ለይሖዋ ያደሩ ምስክሮችን አፍ ሊዘጋ እንደማይችል ምን ምሳሌ ያሳያል?
20 ስደትም ሆነ እስራት ለይሖዋ ያደሩ ምስክሮችን አፍ ሊዘጋ አይችልም። የጀርመናዊዎቹን የኧርንስትንና የሂልዴጋርት ዛሊገርን ምሳሌ ተመልከት። በእምነታቸው ምክንያት ሁለቱም በናዚ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፖችና በኮሚዩኒስት እስር ቤቶች ውስጥ በድምሩ ከ40 ዓመታት በላይ አሳልፈዋል። በእስር ቤት ውስጥ እያሉም እንኳን ለሌሎች እስረኞች መመስከራቸውን አላቋረጡም። ሂልዴጋርት የሆነውን ነገር በማስታወስ እንዲህ ብላ ነበር:- “የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣኖች እኔን በጣም አደገኛ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኝ ነበር። ምክንያቱም አንዲት ሴት ጠባቂ እንደተናገረችው ቀኑን ሙሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስናገር እውላለሁ። በዚህም ምክንያት በእስር ቤቱ ምድር ቤት የሚገኝ ክፍል ውስጥ ታሰርኩ።” በመጨረሻ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ወንድምና እህት ዛሊገር ሙሉ ጊዜያቸውን ለክርስቲያናዊው አገልግሎት አዋሉት። ወንድም ዛሊገር በ1985 ሚስቱ ደግሞ በ1992 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ሁለቱም በታማኝነት አገልግለዋል።
21. በጽናታችን ላይ ለአምላክ ማደርን ለመጨመር ምን ማድረግ አለብን?
21 የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና የተማርነውን ነገር ጊዜ ወስደን በአድናቆት በማሰላሰል ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እውቀት እያደግን እንሄዳለን። ይህም ውድ የሆነውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ሙሉ በሙሉ እንድናገኝ ያስችለናል። ለአምላክ የማደር ባሕርይ ካልኖረን ክርስቲያኖች በመሆናችን ምክንያት የሚመጡብንን መከራዎች በጽናት የምንቋቋምበት ምንም መንገድ አይኖርም። ስለዚህ የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር ተከትለን ‘በእምነታችን ላይ መጽናትን በመጽናትም ለአምላክ ያደሩ መሆንን መጨመራችንን’ እንቀጥል። — 2 ጴጥሮስ 1:5, 6 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዩሴብያን በተመለከተ ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ብለዋል:- “ከፍተኛ አክብሮት ወይም አምልኮ የሚል ትርጉም ያለው [የቃሉ ሥር የሆነው] ሴብ የሚለው ክፍል ነው። ዩ ደግሞ ተገቢ የሚል ትርጉም ያለው የግሪክኛ ቃል ነው፤ ስለዚህ ዩሴብያ ተገቢና ትክክለኛ በሆነ መንገድ የቀረበ ከፍተኛ አክብሮት ወይም አምልኮ ማለት ነው።” — ኒው ቴስታመንት ወርድስ
b ስለ አምላክ ቃል ያለንን እውቀት ጥልቅ ለማድረግ እንዴት ማጥናት እንደምንችል የሚገልጽ ማብራሪያ ለማግኘት የነሐሴ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 12–17ን ተመልከት።
c ላረጁ ወላጆች ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ እንዴት ማሳየት እንደሚቻል ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 11–108 ገጽ 15–21 ተመልከት።
መልስህ ምንድን ነው?
◻ ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ማለት ነው?
◻ በመጽናትና ለአምላክ ያደሩ በመሆን መካከል ምን ዝምድና አለ?
◻ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን በቤት ውስጥም ለአምላክ ያደረ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
◻ በአገልግሎት የምንሳተፍበት ዋናው ምክንያት ምን መሆን አለበት?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በራቨንስብሩክ በሚገኘው የናዚ እስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስረው የነበሩ የይሖዋ ምስክሮች ጽናትንና ለአምላክ የማደርን ባሕርይ አሳይተዋል