“በዋጋ ተገዝታችኋል”
“በዋጋ ተገዝታችኋልና . . . ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”—1 ቆሮንቶስ 6:20
1, 2. (ሀ) ከሞት የሚያስወጣውን መንገድ የከፈተው ምንድን ነው? (ለ) የክርስቶስን ሞት ሕጋዊ ለማድረግ ምን መደረግ ነበረበት? ለዚህስ ጥላ የሆነለት ነገር ምንድን ነው?
መዝሙራዊው “አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፣ ከሞት መውጣትም [ከይሖዋ (አዓት)] ነው” ብሎአል። (መዝሙር 68:20) የኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ይህንን መውጫ መንገድ ከፍቶታል። ይሁን እንጂ ይህንን መሥዋዕት ሕጋዊ ለማድረግ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ዘንድ መቅረብ ነበረበት።
2 ለዚህም ሊቀ ካህናቱ በሥርየት ቀን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባቱ ጥላ ሆኖአል። (ዘሌዋውያን 16:12-15) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎአል፣ “ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ . . . የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ክርስቶስ በእጅ ወደተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”—ዕብራውያን 9:11, 12, 24
የደም ኃይል
3. (ሀ) የይሖዋ አምላኪዎች ለደም ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? (ለ) ደም ኃጢአት ለማስተሰረይ የሚያስችል ሕጋዊ ኃይል እንዳለው የሚያመለክተን ምንድን ነው
3 በመዳናችን ረገድ የክርስቶስ ደም ምን ድርሻ ያበረክታል? እውነተኛ አምላኪዎች ከኖህ ዘመን ጀምሮ ደምን እንደ ቅዱስ ነገር ሲመለከቱ ኖረዋል። (ዘፍጥረት 9:4-6) መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሕይወቱ በደሙ ውስጥ ነው” ስለሚል ለሕይወት ተግባራት ሁሉ ደም በጣም አስፈላጊ ነው። (ዘሌዋውያን 17:11) በዚህም ምክንያት የሙሴ ሕግ ከብት በታረደ ጊዜ ደሙ በይሖዋ ፊት እንዲፈስ ያስገድድ ነበር። (ዘሌዋውያን 8:15፤ 9:9) “እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል። ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።”—ዕብራውያን 9:22
4. (ሀ) አምላክ የደምን አጠቃቀም የሚወስን ሕግ ማውጣቱ ለምን ዓላማ አገልግሎአል? (ለ) ኢየሱስ የሞተበት ሁኔታ ምን የተለየ ቁም ነገር ነበረው?
4 ስለዚህ በሙሴ ሕግ መሠረት በደም አለአግባብ መጠቀም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑ አያስደንቅም። (ዘሌዋውያን 17:10) ማንኛውም ነገር በቀላሉ የማይገኝ ሲሆን ወይም በአጠቃቀሙ ላይ ጥብቅ እገዳ ሲደረግበት ዋጋው ከፍተኛ እንደሚሆን ሁላችንም እናውቃለን። ይሖዋ በደም አጠቃቀም ላይ ገደብ ማበጀቱ ደም እንደተራ ነገር ሳይሆን በጣም ውድና ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ነገር እንዲታይ አድርጎታል። (ሥራ 15:29፤ ዕብራውያን 10:29) ይህም የክርስቶስ ደም ከሚያከናውነው ክቡር ኣላማ ጋር የሚስማማ ነው። ደሙ እንዲፈስ በሚያስችል ሁኔታ መገደሉም የተገባ ነበር። በዚህ መንገድ ክርስቶስ ሰብዓዊ ሥጋውን ከመሠዋቱም በተጨማሪ ነፍሱን እንዳፈሰሰ ይኸውም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን እንደሠዋ በግልጽ ታየ። (ኢሳይያስ 53:12) ኢየሱስ ለዚህ ሕይወቱ ያለውን ሕጋዊ መብት በአለፍጽምና ምክንያት አላጣም። ስለዚህም የፈሰሰው ደሙ ክቡር ዋጋ ያለው ስለሆነ ለሰው ልጅ የኃጢአት ሥርየት ለአምላክ ሊያቀርብ ይችላል።
5. (ሀ) ክርስቶስ ወደ ሰማይ ይዞ የሄደው ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) አምላክ የክርስቶስን መሥዋዕት መቀበሉ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
5 ክርስቶስ እውነተኛ ደሙን ወደ ሰማይ ሊወስድ አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ የወሰደው ደሙ የሚወክለውን ነገር ማለትም የተሠዋው ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱ ያስገኘውን ሕጋዊ ጥቅም ወይም ፋይዳ ነው። ኢየሱስ በአምላክ ፊት ቀርቦ ይህን ሕይወቱን ለኃጢአተኛው የሰው ልጆች ልዋጭ የሚሆን ቤዛ አድርጎ በይፋ ሊያቀርብ ይችል ነበር። ይሖዋ ይህን መሥዋዕት መቀበሉ በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ቀን በኢየሩሳሌም በነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ በመውረዱ ተረጋግጦአል። (ሥራ 2:1-4) አሁን ክርስቶስ የሰውን ልጆች በሙሉ በዋጋ ገዝቶ የራሱ ንብረት አደረጋቸው። (ገላትያ 3:13፤ 4:5፤ 2 ጴጥሮስ 2:1) ስለዚህ የቤዛው ጥቅሞች ለሰው ልጆች ሊፈስሱ ይችላሉ።
የመጀመሪያዎቹ የቤዛው ተጠቃሚዎች
6. አምላክ የክርስቶስ ቤዛ ያስገኛቸው ጥቅሞች በሥራ ላይ እንዲውሉ ምን ዝግጅቶች አድርጎአል?
6 ይሁን እንጂ ይህ ማለት የሰው ልጅ ወዲያውኑ አካላዊ ፍጽምና ይሰጠዋል ማለት አይደለም። የሰው ልጅ የኃጢአተኛነት ባሕርይ አስቀድሞ ካልተሸነፈ አካላዊ ፍጽምና ሊገኝ አይችልም። (ሮሜ 7:18-24) ኃጢአተኛነት የሚሸነፈው መቼና እንዴት ነው? አምላክ በመጀመሪያ 144,000 ሰዎች በሰማይ ‘የአምላካችን ካህናት እንዲሆኑና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ነገሥታት’ ሆነው ምድርን እንዲገዙ ዝግጅት አደረገ። (ራዕይ 5:9, 10፤ 7:4፤ 14:1-3) በእነርሱ አማካኝነት የቤዛው ጥቅሞች ለሰው ልጆች በሙሉ በሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይዳረሳሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ራዕይ 21:3, 4
7. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን ምንድን ነው? የቃሉ ኪዳኑስ ተዋዋዮች እነማን ናቸው? ቃል ኪዳኑስ ለምን ዓላማ አገልግሎአል? (ለ) አዲሱን ቃል ኪዳን ለማስገኘት ሞት አስፈላጊ የሆነው ለምን ነበር? የክርስቶስ ደም ምን ድርሻ አበርክቷል?
7 ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ እንዲቻል 144,000 ነገሥታትና ካህናት ‘ከሰው ዘር በሙሉ መዋጀት ይኖርባቸዋል።’ (ራዕይ 14:4) ይህ የሚከናወነው “በአዲሱ ቃል ኪዳን” አማካኝነት ነው። ይህ ቃል ኪዳን የመንፈሳዊ እሥራኤል አባሎች ነገሥታትና ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸው በይሖዋ አምላክና በመንፈሣዊው የአምላክ እስራኤል መካከል የተደረገ ቃል ኪዳን ነው። (ኤርምያስ 31:31-34፤ ገላትያ 6:16፤ ዕብራውያን 8:6-13፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ይሁን እንጂ አምላክ ፍጹም ካልሆኑት የሰው ልጆች ጋር እንዴት ቃል ኪዳን ሊገባ ይችላል? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል፤ “[በአምላክና ፍጹም ባልሆነው የሰው ልጅ መካከል] ቃል ኪዳን ሲኖር ቃል ኪዳን የገባው ሰው ሞት መረጋገጥ ይኖርበታል። ምክንያቱም ቃል ኪዳኑ ተፈጻሚነት የሚኖረው በሞቱ ሰዎች ላይ ነው። ቃል ኪዳኑን የሰጠው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ቃል ኪዳኑ ተፈጻሚነት አይኖረውም።”—ዕብራውያን 9:16, 17
8, 9. ቤዛው ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
8 ስለዚህ ኢየሱስ መካከለኛ የሆነለት አዲስ ቃል ኪዳን መሠረቱ የቤዛው መሥዋዕት ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ። እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ። ይህም በገዛ ዘመኑ ምሥክርነቱ ነበር።” (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) እነዚህ ቃላት በተለይ የሚሰሩት አዲሱ ቃል ለተገባላቸው የ144,000 ክፍሎች ነው።
9 አምላክ ከሥጋዊ እሥራኤል ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ የእንስሳ ደም ፈስሶ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ ቃል ኪዳኑ በሕግ አልጸደቀም ነበር። (ዕብራውያን 9:18-21) በተመሳሳይም አዲሱ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ እንዲውል ክርስቶስ የቃል ኪዳኑን ደም ማፍሰስ ነበረበት። (ማቴዎስ 26:28፤ ሉቃስ 22:20) ክርስቶስ ሊቀ ካህናትና “የአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ” ሆኖ ስላገለገለ አምላክ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ለሚገቡ ሁሉ የኢየሱስን ደም ጥቅም ሊሰጥና ሰብዓዊ ጽድቅ ሊያጎናጽፋቸው ችሎአል። (ዕብራውያን 9:15፤ ሮሜ 3:24፤ 8:1, 2) በዚህም ምክንያት አምላክ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ሊያስገባቸውና በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሊያደርጋቸው ችሎአል። ኢየሱስ መካከለኛቸውና ሊቀ ካህናቸው እንደመሆኑ መጠን በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ጠበቀው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል።—ዕብራውያን 2:16፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
በምድር ያሉትን መሰብሰብ
10, 11. (ሀ) ቤዛው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላልሆኑ ሰዎች የተዳረሰው እንዴት ነው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን ናቸው? በአምላክ ዘንድስ ምን አቋም አላቸው?
10 ቤዛው የሚያስገኘውን ነፃነት ይኸውም ለኃጢአታቸው ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸውን? አይደሉም። አምላክ በመከራው እንጨት ላይ በፈሰሰው ደም አማካኝነት ከሌሎች ሁሉ ጋር ሰላም በማድረግ ከራሱ ጋር ያስታርቃል። ይህም ቆላስይስ 1:14, 20 እንደሚያመለክተው ነው። ይህም በሰማይ ያሉትንና (144,000ዎቹን) በምድር ያሉትን የሚያጠቃልል ይሆናል። በምድር ያሉት የተባሉት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸው የሰው ልጆች ናቸው። በተለይ ከ1935 ወዲህ እነዚህን ሰዎች ለመሰብሰቡ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። እነዚህን ሰዎች ራዕይ 7:9-17 ማዳን የአምላክና የበጉ እንደሆነ የሚናገሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሆኑ ይገልጻቸዋል። ሙሉ በሙሉ ሕያው የሚሆኑትና ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የሚያገኙት የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲፈጸም እንደሆነ ራዕይ 20:5 ስለሚያመለክት ‘ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ’ መመራት ያስፈልጋቸዋል። በዚያ ጊዜ በፍጽምና አቋም እያሉ የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉ ሁሉ በምድር ላይ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ለማግኘት መብት ያላቸው ጻድቅን ይሆናሉ።—ራዕይ 20:7, 8
11 ቢሆንም “እጅግ ብዙ ሰዎች” “ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም በማንጻት የመጀመሪያ ደረጃ ንጽሕና አግኝተዋል።” (ራዕይ 7:14) ክርስቶስ ለእነርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ አይሆንላቸውም። ቢሆንም የአምላክ መንግሥት በሚሰራቸው ነገሮች አማካኝነት የዚህ ቃል ኪዳን ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን ያገለግላቸዋል። ይሖዋም በእርሱ አማካኝነት እንደ ጻድቅ ተቆጥረው የአምላክ ወዳጆች እስኪሆኑ ድረስ የቤዛውን ጥቅም ሊዘረጋላቸው ችሎአል። (ከያዕቆብ 2:23 ጋር አወዳድር።) በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ቀስ በቀስ ‘ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥተው ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት’ ይደርሳሉ።—ሮሜ 8:21
12. አምላክ ከክርስትና በፊት ከነበሩት ታማኝ ሰዎች ጋር እንደዚያ ያለ ግንኙነት ያደርግ የነበረው በምን መሠረት ነበር?
12 በአምላክ ፊት ባላቸው አቋም ረገድ ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ ከክርስትና በፊት ከነበሩት አምላኪዎች እምብዛም ልዩነት ያላቸው አይመስልም። ይሁን እንጂ አምላክ ለእነዚህ የጥንት አምላኪዎች የሚያደርገው ነገር ሁሉ ወደፊት የሚመጣውን የቤዛ ዝግጅት በማሰብ ነበር። (ሮሜ 3:25, 26) የኃጢአት ሥርየት ያገኙት በጊዜያዊነት ብቻ ነበር። (መዝሙር 32:1, 2) የእንስሳት መሥዋዕት ከኃጢአተኝነት ስሜት እነርሱን በማላቀቅ ፋንታ ኃጢአተኝነታቸውን ያሳስቧቸው ነበር።—ዕብራውያን 10:1-3
13. ከክርስትና በፊት ከነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በተሻለ ሁኔታ ላይ የምንገኘው እንዴት ነው?
13 ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁኔታ ግን እንደዚያ አይደለም። አምላክን የሚያመልኩት ቀደም ሲል የተከፈለውን ቤዛ መሠረት በማድረግ ነው። በሊቀ ካህናቸው አማካኝነት “ወደ ጸጋው ዙፋን” በድፍረት ይቀርባሉ። (ዕብራውያን 4:14-16) ከአምላክ ጋር መታረቁ በተስፋ ብቻ የሚጠበቅ ነገር ሳይሆን እውን የሆነ ነገር ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ሲሳሳቱ እውነተኛ ይቅርታ ሊያገኙ ይችላሉ። (ኤፌሶን 1:7) ንጹሕ የሆነ ሕሊና አላቸው። (ዕብራውያን 9:9፤ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) እነዚህ በረከቶች የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክ ልጆች በመሆን ወደፊት ለሚያገኙት ነፃነት እንደ አነስተኛ ቅምሻ የሚቆጠሩ ናቸው።
የአምላክ ፍቅርና ጥበብ ጥልቀት
14, 15. ቤዛው እጅግ ጥልቅ የሆነው የአምላክ ጥበብ እንዲሁም የጽድቁና የፍቅሩ መግለጫ የሆነው እንዴት ነው?
14 ቤዛ እንዴት ያለ አስደናቂ የሆነ የይሖዋ ሥጦታ ነው! ለመረዳት የሚያስቸግር ባይሆንም በጣም አዋቂ የሆነውን ሰው እንኳን በጣም ሊያስደንቅ የሚችል ጥልቀት ያለው ነው። ቀደም ሲል ስለ ቤዛው አሠራር የተመለከትነው ላይ ላዩን ብቻ ነው። ቢሆንም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በአድናቆት የሚከተለውን ለማለት እንገደዳለን፦ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው! ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።” (ሮሜ 11:33) ይሖዋ በአንድ ጊዜ የሰው ልጆችን ለማዳንና ልዕልናውን ለማረጋገጥ መቻሉ ጥበበኛ መሆኑን ያሳያል። በቤዛው አማካኝነት “የእግዚአብሔር ጽድቅ . . . ተገልጦአል። . . . እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሰሪያ አድርጎ አቆመው።”—ሮሜ 3:21-26
15 አምላክ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ አምላኪዎቹ የፈጸሙአቸውን ኃጢአቶች ይቅር በማለቱ ምንም ዓይነት ወቀሳ ሊደርስበት አይችልም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ጻድቅ ቅቡዓኖቹን ልጆቹ ስላደረጋቸው ወይም እጅግ ብዙ ሰዎችን ወዳጆቹ ስላደረጋቸው ወቀሳ ሊቀርብበት አይችልም። (ሮሜ 8:33) አምላክ ከፍተኛ ኪሣራ የሚያስከትልበት ቢሆንም በአድራጎቶቹ ሁሉ በሕግ የሚሠራ ወይም ትክክለኛ በመሆን ሰይጣን ይሖዋ አለፍትሕ የሚያስተዳድር ገዥ ነው በማለት ያቀረበበት ክስ ፈጽሞ ሐሰት መሆኑን አረጋግጦአል። አምላክ ለፍጡሮቹ ያለውም ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር በተመሳሳይ በማያጠያይቅ ሁኔታ ተረጋግጦአል።—ሮሜ 5:8-11
16. (ሀ) ቤዛው የአምላክ አገልጋዮች ንጹሕ አቋም ጠባቂ ስለመሆናቸው ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ያስገኘው በምን መንገድ ነው? (ለ) ቤዛው የጽድቅ አዲስ ዓለም ይመጣል የሚል እምነት እንዲኖረን መሠረት የሚሰጠን እንዴት ነው?
16 ቤዛው የተገኘበትም መንገድ የአምላክ አገልጋዮችን ንጹሕ አቋም ጠባቂነት በሚመለከት ለተነሣው ጥያቄ መልስ አስገኝቶአል። የኢየሱስ ታዛዥነት ብቻውን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ አስገኝቶአል። (ምሳሌ 27:11፤ ሮሜ 5:18, 19) በዚህ ላይ የሰይጣንን ተቃውሞ ሁሉ ተቋቁመው እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት የጸኑት 144,000 ክርስቲያኖች አኗኗር ተጨምሮበታል። (ራዕይ 2:10) ቤዛው እነዚህ የ144,000 ክፍል የሆኑ ክርስቲያኖች ያለመሞትን ባሕርይ ወይም ሊጠፋ የማይችል ሕይወት እንዲሸለሙ ያስችላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:53፤ ዕብራውያን 7:16) ይህም ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮች እምነት ሊጣልባቸው አይችልም ሲል ያቀረበውን ክስ ፈጽሞ ውድቅ ያደርገዋል። በተጨማሪም ቤዛው በአምላክ ተስፋዎች የጸና እምነት እንዲኖረን የሚያስችል ምክንያት አስገኝቶልናል። በቤዛው መሥዋዕት አማካኝነት በሕግ የተቋቋመውን የመዳን ዝግጅት መሠረታዊ መዋቅር ለማየት ችለናል። (ዕብራውያን 8:6) በዚህም ምክንያት ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚቋቋም በቂ ዋስትና አግኝተናል።—ዕብራውያን 6:16-19
ዓላማውን አትሳት
17. (ሀ) አንዳንዶች የቤዛውን ዓላማ እንደሳቱ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) በሥነ ምግባር ንጹሖች ሆነን እንድንኖር ምን ነገር ሊገፋፋን ይችላል?
17 አንድ ሰው ከቤዛው ጥቅም ለማግኘት ከፈለገ ዕውቀት ማግኘት፤ ማመንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት ጋር ተስማምቶ መኖር ያስፈልገዋል። (ዮሐንስ 3:16፤ 17:3) ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ የሚፈቅዱ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። (ማቴዎስ 7:13, 14) ሌላው ቀርቶ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል እንኳን አንዳንዶች ‘የአምላክን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ ዓላማውን ይስታሉ።’ (2 ቆሮንቶስ 6:1) ለምሳሌ ያህል ባለፉት ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የጾታ ብልግና ስለፈጸሙ ተወግደዋል። ይሖዋና ክርስቶስ ያደረጉልንን ነገሮች ስንመለከት ይህ እንዴት የሚያሳፍር ድርጊት ነው! አንድ ሰው ለቤዛው ያለው አድናቆት “የቀደመውን ኃጢአቱን መንጻት” እንዳይረሳ ሊገፋፋው አይገባምን? (2 ጴጥሮስ 1:9) ስለዚህ ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” በማለት ክርስቲያኖችን ማሳሰቡ ተገቢ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:20) ይህን ማስታወሳችን የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን እንድንኖር ኃይለኛ ግፊት ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 1:14-19
18. ከባድ ኃጢአት ላይ የወደቀ ክርስቲያን አሁንም ከቤዛው ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
18 አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ከሆነስ? በቤዛው አማካኝነት ከሚገኘው የኃጢአት ሥርየትና ከአፍቃሪ ሽማግሌዎች ከሚገኘው እርዳታ ለመጠቀም እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። (ያዕቆብ 5:14, 15) አንድ ንሥሐ የገባ ክርስቲያን ጠንካራ ተግሣጽ መቀበል የሚያስፈልገውን እንኳን ቢሆን ተማርሮ ከሚሰጠው እርማት መሸሽ አይኖርበትም። (ዕብራውያን 12:5) የሚከተለው አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና አለን፦ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።”—1 ዮሐንስ 1:9
19. አንድ ክርስቲያን እውነትን ከማወቁ በፊት ስለሠራው ኃጢአት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል?
19 አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም በሰሩት ሥራ ከመጠን በላይ ተስፋ ይቆርጣሉ። አንድ ቅስሙ የተሰበረ ክርስቲያን እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ወደ እውነት ከመምጣታችን በፊት እኔና ሚስቴ ኸርፐስ የተባለ የአባለ ዘር በሽታ ያዘን። አንዳንድ ጊዜ እርኩሶች እንደሆንና ንጹሕ በሆነው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ ልንኖር የማይገባን ሰዎች እንደሆንን ይሰማናል።” አንዳንዶች ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ እንኳን ቀድሞ የሰሩት በደል ያመጣባቸውን ፍሬ ለማጨድ ይገደዱ ይሆናል። (ገላትያ 6:7) ቢሆንም አንድ ሰው ከልቡ ንሥሐ ከገባ በይሖዋ ፊት ንጹሕ እንዳልሆነ እንዲሰማው የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም። “የክርስቶስ ደም . . . ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን” ሊያነጻ ይችላል።—ዕብራውያን 9:14
20. በቤዛው ማመን አንድን ክርስቲያን አስፈላጊ ካልሆነ የበደለኛነት ስሜት እንዴት ሊያሳርፈው ይችላል?
20 አዎ፤ በቤዛው ማመናችን አስፈላጊ ያልሆነ የበደለኛነት ስሜት እንዳይጫነን ሊረዳን ይችላል። አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከ11 አመት ለሚበልጥ ጊዜ የጾታ እርካታ ለማግኘት ብልቴን የማሻሸት ልማዴን ለማሸነፍ ስታገል ቆይቼአለሁ። በአንድ ወቅት ይሖዋ እንደ እኔ ያለው እርኩስ ሰው ድርጅቱን እንዲያረክስበት አይፈልግም ብዬ በማሰብ ጉባኤውን ትቼ እስከመሄድ ደርሼ ነበር።” ይሁን እንጂ የአመጻን ድርጊት ጠንክረን እስከተዋጋንና ለመሸነፍ ፈቃደኞች እስካልሆንን ድረስ ይሖዋ “መሐሪና ይቅር ባይ ነው።”—መዝሙር 86:5
21. ቤዛው ለበደሉን ሰዎች ያለንን አመለካከት እንዴት ሊነካ ይገባል?
21 በተጨማሪም ቤዛው ከሌሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ለውጥ ማምጣት ይገባዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን ወንድምህ ሲያስቀይምህ ምን ታደርጋለህ? ክርስቶስ እንዳደረገው ይቅር ትለዋለህን? (ሉቃስ 17:3, 4) ‘ለሌሎች የምትራራና የምታዝን እንዲሁም አምላክ በክርስቶስ በኩል ይቅር እንዳለህ አንተም ሌሎችን ይቅር የምትል ነህን?’ (ኤፌሶን 4:32) ወይስ መቀየምና ማኩረፍ የሚቀናህ ነህ? እንዲህ ብታደርግ የቤዛውን ዓላማ ስተሃል ማለት ነው።—ማቴዎስ 6:15
22, 23. (ሀ) ቤዛው በሚኖሩን ግቦችና በአኗኗራችን ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል? (ለ) ሁሉም ክርስቲያኖች በቤዛው ረገድ ምን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል?
22 በመጨረሻም ለቤዛው ያለን አድናቆት አኗኗራችንንና የሕይወት ግባችንን በጥልቅ ሊነካው ይገባል። ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና የሰው ባሪያዎች አትሁኑ” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 7:23) አሁንም ሕይወትህ ያተኮረው ቤት፣ ሥራ፣ ምግብ፣ ልብስ በማግኘት ላይ፤ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ነውን? ወይስ አምላክ የሚያስፈልግህን በሙሉ እንደሚሰጥህ በሰጠው ቃል በመታመን መንግሥቱን ታስቀድማለህ? (ማቴዎስ 6:25-33) ለአሰሪህ እንደ ባሪያ እየተገዛህ ለአምላካዊ ሥራዎች በቂ ጊዜ ታጣለህን? ክርስቶስ “መልካሙን ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ ስለ እኛ ነፍሱን” እንደሰጠ አስታውስ።—ቲቶ 2:14፤ 2 ቆሮንቶስ 5:15
23 ይህን ታላቅ የቤዛ ሥጦታ ለሰጠን “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን።” (ሮሜ 7:25) ቤዛው ሕይወታችንን የሚመራልን ታላቅ ኃይል እንዲሆን እንፍቀድ እንጂ የቤዛውን ዓላማ አንሳት። በዋጋ የተገዛን መሆናችንን በአመስጋኝነት እያሰብን ሁልጊዜ በአስተሳሰባችን፤ በቃላችንና በድርጊታችን አምላክን እናክብር።
የክለሣ ጥያቄዎች
◻ ደም እንደ ቅዱስ ነገር ተደርጎ የሚታየው ለምንድን ነው? የክርስቶስ ደም በሰማይ ለይሖዋ የቀረበው እንዴት ነው?
◻ የክርስቶስ ደም አዲሱን ቃል ኪዳን በማቋቋም ረገድ ምን ድርሻ ነበረው?
◻ ቤዛው ቅቡዓንንም ሆነ እጅግ ብዙ ሰዎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?
◻ የቤዛውን ዓላማ አለመሳታችንን እንዴት ለማሳየት እንችላለን?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ መሥዋዕት ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይሉ ያለው ሕይወት አድን በሆነው ደሙ ላይ ነው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ይቅር ባይነት የሚያደንቅ ሰው ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ይሆናል