የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 19—መዝሙር
ጸሐፊዎቹ:- ዳዊትና ሌሎች ሰዎች
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ.ል.በፊት በ460 ገደማ
መጽሐፈ መዝሙር በጥንት ጊዜ የነበሩ የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች እርሱን በዝማሬ ለማወደስ ይጠቀሙበት የነበረ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ፣ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሕዝቡ ለሚያቀርበው አምልኮ እንዲያገለግሉ የተዘጋጁና በሙዚቃ የሚታጀቡ 150 ቅዱስ መዝሙራት ስብስብ ነው። እነዚህ መዝሙራት ለይሖዋ የቀረቡ የውዳሴ ዜማዎች ከመሆናቸውም በላይ ምሕረትና እርዳታ ለማግኘት የቀረቡ የልመና ጸሎቶች እንዲሁም በአምላክ የመታመንና በእርሱ የመመካት ዝንባሌ የተንጸባረቀባቸውን ሐሳቦች ይዘዋል። ምስጋናንና ሐሴትን በሚገልጹ ቃላት እንዲሁም የላቀ ደስታ በተንጸባረቀባቸው መግለጫዎች የተሞሉ ናቸው። አንዳንዶቹ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና ታላላቅ ሥራዎቹን በማንሳት ያለፈውን ታሪክ የሚያወሱ ናቸው። እነዚህ መዝሙራት በርካታ ትንቢቶች የያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በአስገራሚ ሁኔታ ፍጻሜ አግኝተዋል። መጽሐፉ የአንባቢውን ስሜት በጥልቅ በሚነኩና ክንውኑ በዓይነ ሕሊናው እንዲታየው በሚያደርጉ ዕጹብ ድንቅ ቃላት የተገለጹ በጣም ብዙ ጠቃሚና የሚያንጹ ትምህርቶች ይዟል። መጽሐፈ መዝሙር ለዓይን ማራኪ ሆኖ የተዘጋጀና ለመመገብ በሚጋብዝ መንገድ ከፊታችን የቀረበ ታላቅ መንፈሳዊ ማዕድ ነው።
2 የመጽሐፉ ስም ምን ትርጉም አለው? የጻፈውስ ማን ነው? በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፉ ሴፌር ቴሂሊም የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን ትርጉሙም “የምስጋና መጽሐፍ” ማለት ነው፤ በአጭሩ ደግሞ ቴሂሊም ወይም “ምስጋና” ይባላል። ይህ ቃል ቴሂልላህ የሚለው ቃል ብዜት ሲሆን መዝሙር 145 አናት ላይ የሰፈረው መግለጫ እንደሚጠቁመው “ምስጋና” ወይም “የምስጋና መዝሙር” የሚል ትርጉም አለው። መጽሐፉ ለይሖዋ የሚቀርብ ውዳሴ የያዘ በመሆኑ “ምስጋና” የሚለው መጠሪያ በጣም ተስማሚ ነው። “ሳልምስ” የሚለው የመጽሐፉ የእንግሊዝኛ ስም ሳልሞይ የሚለውን ቃል ከተጠቀመው ከግሪኩ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተወሰደ ነው፤ ቃሉ በሙዚቃ መሣሪያ እየታጀቡ የተዘመሩ መዝሙሮችን ያመለክታል። ከዚህም ሌላ ቃሉ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በርካታ ቦታዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን ሉቃስ 20:42 እና የሐዋርያት ሥራ 1:20 ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። መዝሙር ለይሖዋ ውዳሴና አምልኮ ለማቅረብ የሚያገለግል ቅዱስ ዜማ ወይም ግጥም ነው።
3 በአብዛኞቹ መዝሙሮች አናት ላይ ርዕስ ወይም መግለጫ የሚገኝ ሲሆን እነዚህ መግለጫዎች ብዙውን ጊዜ የጸሐፊውን ስም ይናገራሉ። ሰባ ሦስት የሚያህሉ መግለጫዎች “የእስራኤል ተወዳጁ ዘማሪ” የሆነውን የዳዊትን ስም የያዙ ናቸው። (2 ሳሙ. 23:1) መዝሙር 2, 72 እና 95ንም የጻፈው ዳዊት እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። (የሐዋርያት ሥራ 4:25ን፣ መዝሙር 72:20ን እና ዕብራውያን 4:7ን ተመልከት።) በተጨማሪም መዝሙር 10 የመዝሙር 9፣ መዝሙር 71 ደግሞ የመዝሙር 70 ቀጣይ ክፍል ይመስላሉ፤ ስለዚህ እነዚህንም የጻፋቸው ዳዊት ሊሆን ይችላል። አሥራ ሁለት መዝሙሮች ጸሐፊያቸው አሳፍ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከአሳፍ የሕይወት ዘመን በኋላ ስለተከናወኑ ክስተቶች የሚናገሩ በመሆናቸው አሳፍ የሚለው መግለጫ ቤተሰቡን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። (መዝ. 79፤ 80፤ 1 ዜና 16:4, 5, 7 የ1954 ትርጉም፤ ዕዝራ 2:41 የ1954 ትርጉም) አሥራ አንድ የሚሆኑ መዝሙሮችን ደግሞ የቆሬ ልጆች እንደጻፏቸው ተገልጿል። (1 ዜና 6:31-38) መዝሙር 43 የመዝሙር 42 ቀጣይ ክፍል ይመስላል፤ በመሆኑም ጸሐፊዎቹ የቆሬ ልጆች ሳይሆኑ አይቀሩም። ‘ከቆሬ ልጆች’ በተጨማሪ መዝሙር 88 ኤማንን የሚጠቅስ ሲሆን መዝሙር 89 ደግሞ ጸሐፊው ኤታን እንደሆነ ይገልጻል። የመዝሙር 90 ጸሐፊ ሙሴ ሲሆን 91ኛው መዝሙርም የእርሱ ሳይሆን አይቀርም። የመዝሙር 127 ጸሐፊ ሰሎሞን ነው። በመሆኑም ከሁለት ሦስተኛ የሚበልጡት መዝሙሮች የተጻፉት በተለያዩ ሰዎች ነው።
4 መጽሐፈ መዝሙር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መጻሕፍት ሁሉ በትልቅነቱ አንደኛ ነው። ከመዝሙር 90፣ 126 እና 137 ማየት እንደሚቻለው መጽሐፉ ተጽፎ ለማለቅ ረዥም ጊዜ ፈጅቷል፤ ቢያንስ ሙሴ መዝሙሩን ከጻፈበት ጊዜ (1513-1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አንስቶ አይሁዳውያን ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ እስካለውና ምናልባትም እስከ ዕዝራ ዘመን (537-460 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ) ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። በመሆኑም መጽሐፉ ተጽፎ ለማለቅ አንድ ሺህ ዓመታት ገደማ ፈጅቷል። ሆኖም በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ታሪክ የሚሸፍነው ጊዜ ከዚያ እጅግ ይበልጣል፤ ከፍጥረት ዘመን ጀምሮ የመጨረሻው መዝሙር ተቀናብሮ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት ጠቅለል ባለ መልኩ ይተርካል።
5 የመዝሙር መጽሐፍ የመደራጀትን አስፈላጊነት የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። ዳዊት ራሱ “አምላኬና ንጉሤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያደርገው የክብር አካሄድ ነው። መዘምራን ከፊት፣ መሣሪያ የሚጫወቱ ከኋላ ሆነው ሲሄዱ፣ ከበሮ የሚመቱ ቈነጃጅትም በመካከላቸው ነበሩ። እግዚአብሔርን በጉባኤ አመስግኑት” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 68:24-26) ይህም “ለመዘምራን አለቃ” የሚለው መግለጫ እንዲሁም በርከት ያሉ የግጥምና የሙዚቃ ስያሜዎች በመዝሙሮቹ አናት ላይ ተደጋግመው የተጠቀሱበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። በመዝሙሮቹ አናት ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ መግለጫዎች አንድ መዝሙር መቼ እንደሚዘመርና ዓላማው ምን እንደሆነ ያብራራሉ፤ ወይም ስለ ሙዚቃው መመሪያ ይሰጣሉ። (በመዝሙር 6፣ 30፣ 38፣ 60፣ 88፣ 102 እና 120 አናት ላይ የሰፈሩትን መግለጫዎች ተመልከት።) እንደ 18ኛውና 51ኛው መዝሙሮች ያሉት ቢያንስ 13 የሚሆኑ የዳዊት መዝሙሮች የተጻፉበት ምክንያት በአጭሩ ተገልጿል። ሠላሳ አራት የሚሆኑ መዝሙሮች በመግቢያቸው ላይ ምንም መግለጫ የላቸውም። በጽሑፉ መካከል 71 ጊዜ የሚገኘው “ሴላ” የሚለው አጭር ቃል ትክክለኛ ጠቀሜታው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም የሙዚቃውን ምት የሚጠቁም ወይም መዝሙሩን በቃል ለመያዝ የሚያገለግል እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። አንዳንዶች፣ በሚዘመርበት ወቅት ወይም በሚዘመርበትና ዜማው በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ በሚሰማበት ጊዜ መሃል ላይ ለማሰላሰል ሲባል ቆም የሚባልበትን ቦታ የሚያመለክት ነው ይላሉ። በመሆኑም በንባብ ወቅት ይህን ቃል መጥራቱ አስፈላጊ አይደለም።
6 ከጥንት ጀምሮ የመዝሙር መጽሐፍ በአምስት የተለያዩ መጻሕፍት ወይም ጥራዞች ተከፋፍሏል፤ እነርሱም:- (1) መዝሙር 1-41፤ (2) መዝሙር 42-72፤ (3) መዝሙር 73-89፤ (4) መዝሙር 90-106፤ (5) መዝሙር 107-150። ከእነዚህ መዝሙሮች መካከል የመጀመሪያዎቹን ስብስቦች ያዘጋጀው ዳዊት እንደሆነ ይታሰባል። ይሖዋ፣ የመዝሙር መጽሐፍ አሁን ያለውን መልክ እንዲይዝ የተጠቀመው ካህንና “በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ” የነበረውን ዕዝራን ሳይሆን አይቀርም።—ዕዝራ 7:6 የ1954 ትርጉም
7 በመዝሙር 14 እና 53፤ 40:13-17 እና 70፤ 57:7-11 እና 108:1-5 መካከል ካለው ድግግሞሽ መመልከት እንደሚቻለው አንዳንዶቹ መዝሙሮች በተለያዩ ቦታዎች የተደገሙት መጽሐፉ በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ ስለተሰባሰበ ሊሆን ይችላል። አምስቱም ክፍሎች ይሖዋን በማመስገን ወይም በመባረክ ይደመደማሉ፤ የመጀመሪያዎቹ አራት ክፍሎች ሲያበቁ ሕዝቡ ለምስጋናው ምላሽ የሚሰጡ ሲሆን በመጨረሻው ክፍል ላይ ግን መደምደሚያው 150ኛውን መዝሙር በሙሉ ያካትታል።—መዝሙር 41:13 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
8 በዘጠኝ መዝሙሮች ላይ ልዩ የአጻጻፍ ስልት ተንጸባርቋል፤ እነዚህ መዝሙሮች የተጻፉት በዕብራይስጥ ፊደል ቅደም ተከተል ነው። (መዝሙር 9, 10, 25, 34, 37, 111, 112, 119 እና 145) በዚህ የአጻጻፍ ስልት መሠረት የአንድ መዝሙር የመጀመሪያ ስንኝ ወይም የመጀመሪያው አርኬ ስንኞች የሚጀምሩት አሌፍ (א) በሚለው የዕብራይስጥ ሆሄያት የመጀመሪያ ፊደል ነው፤ ቀጣዩ ቁጥር ደግሞ ቤት (ב) በሚለው ሁለተኛ ፊደል የሚጀምር ሲሆን እንዲህ እያለ ሁሉንም የዕብራይስጥ ፊደላት ወይም አብዛኛዎቹን ተከትሎ ይሄዳል። ይህ ለማስታወስ እንዲቀል ተብሎ የተደረገ ሊሆን ይችላል፤ የቤተ መቅደሱ ዘማሪዎች እንደ 119ኛው መዝሙር ያሉ ረዣዥም መዝሙሮችን በቃላቸው ማስታወስ ነበረባቸው! በመዝሙር 96:11 ላይ የይሖዋ ስም የሚጻፍባቸው ፊደላት በቅደም ተከተል የሚገኙ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። በዕብራይስጥ የዚህ ጥቅስ የመጀመሪያ ስንኝ አራት ቃላት የያዘ ሲሆን የእነዚህ ቃላት የመጀመሪያ ፊደላት ከቀኝ ወደ ግራ ሲነበቡ የሐወሐ (יהוה) የሚሉትን የይሖዋ ስም የሚጻፍባቸውን አራቱን የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ማለትም ቴትራግራማተን ይሰጣሉ።
9 እነዚህ ቅዱስ ግጥሞች በዕብራይስጥ ቤት ባይመቱም ውብ የሆነና የሐሳብ ወጥነት ያለው የአጻጻፍ ስልት ተንጸባርቆባቸዋል። አእምሮንና ልብን ይነካሉ። አንባቢው ግልጽ የሆነ ምናባዊ ሥዕል እንዲታየው ያደርጋሉ። ለየት ያለው የዳዊት የሕይወት ተሞክሮ መዝሙሮቹ የሚያወሱት ርዕሰ ጉዳይም ሆነ በውስጣቸው የተንጸባረቁት ጠንካራ ስሜቶች ስፋትና ጥልቀት እንዲኖራቸው በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ለብዙዎቹ መዝሙሮች መሠረት ሆኗል። ዳዊት በልጅነቱ እረኛ የነበረ፣ ከጎልያድ ጋር ብቻውን የተፋለመ፣ የቤተ መንግሥት ሙዚቀኛ ሆኖ ያገለገለ፣ ከወዳጅም ሆነ ከጠላት ስደት የገጠመው፣ ንጉሥና ድል አድራጊ፣ አፍቃሪ አባት ቢሆንም በቤተሰቡ ውስጥ መከፋፈል የገጠመው፣ ከባድ ኃጢአት የሚያስከትለውን መራራ ፍሬ ከአንዴም ሁለቴ የቀመሰ ቢሆንም ይሖዋን ከልቡ የሚያመልክና ሕጉን የሚወድ ሰው ነበር። እንደ እርሱ በሕይወቱ የተለያዩ ሁኔታዎች ያጋጠሙት ሰው እምብዛም አይገኝም። ከዚህ ዓይነት ሁኔታ በመነሳት የተጻፈው የመዝሙር መጽሐፍ የሰው ልጆችን ስሜት በአጠቃላይ የሚዳስስ መሆኑ ምንም አያስገርምም! መጽሐፉ የዕብራይስጥ ጥቅሶች መለያ በሆነው የማወዳደርና የማነጻጸር የአጻጻፍ ዘይቤ የተዘጋጀ መሆኑ ኃይልና ውበት ጨምሮለታል።—መዝ. 1:6፤ 22:20፤ 42:1፤ 121:3, 4
10 ይሖዋን ለማመስገን የሚዘመሩት እነዚህ ጥንታዊ መዝሙሮች ከተቀሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ መሆናቸው ትክክለኛነታቸውን በሚገባ ያረጋግጣል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ከመዝሙር መጽሐፍ ብዙ ጊዜ ጠቅሰዋል። (መዝ. 5:9 [ሮሜ 3:13]፤ መዝ. 10:7 [ሮሜ 3:14]፤ መዝ. 24:1 [1 ቆሮ. 10:26]፤ መዝ. 50:14 [ማቴ. 5:33]፤ መዝ. 78:24 [ዮሐ. 6:31]፤ መዝ. 102:25-27 [ዕብ. 1:10-12]፤ መዝ. 112:9 [2 ቆሮ. 9:9]) ዳዊት ራሱ በመጨረሻው መዝሙሩ ላይ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ” ብሏል። ሳሙኤል ከቀባው ዕለት ጀምሮ በእርሱ ላይ ይሠራ የነበረው ይኸው መንፈስ ነው። (2 ሳሙ. 23:2፤ 1 ሳሙ. 16:13) ሐዋርያትም ከመዝሙሮች ላይ ጠቅሰዋል። ጴጥሮስ “መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፉ ቃል” በማለት ተናግሯል፤ የዕብራውያን ደብዳቤ ጸሐፊም ከመዝሙር የወሰዳቸውን በርካታ ጥቅሶች አምላክ እንደተናገራቸው በመግለጽ አሊያም “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” በማለት አስፍሯቸዋል።—ሥራ 1:16፤ 4:25፤ ዕብ. 1:5-14፤ 3:7፤ 5:5, 6
11 የመጽሐፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከሁሉ የላቀው ጠንካራ ማስረጃ ከሞት የተነሳው ጌታ ኢየሱስ ሲሆን እርሱም ለደቀ መዛሙርቱ “‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” ብሏቸዋል። እዚህ ላይ ኢየሱስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ፣ አይሁዳውያን በሚጠቀሙበትና ደቀ መዛሙርቱ ጠንቅቀው በሚያውቁት መንገድ ከፋፍሎ መጥቀሱ ነበር። የመዝሙር መጻሕፍት ሲል በሦስተኛው የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ውስጥ የተካተቱትን መጻሕፍት በሙሉ ማመልከቱ ነበር፤ እነዚህ መጻሕፍት ሃጊዎግራፋ (ወይም ቅዱሳን ጽሑፎች) ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ከዚህ ክፍል ውስጥ የመጀመሪያው መጽሐፍ መዝሙር ነው። ኢየሱስ ከላይ ያለውን ከመናገሩ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ለነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት ‘በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን [“ሁሉ፣” የ1954 ትርጉም] ባስረዳቸው’ ወቅት የተናገረው ሐሳብ ይህን ያረጋግጣል።—ሉቃስ 24:27, 44
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
23 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መዝሙራት ውብና ግሩም የአጻጻፍ ስልት የተከተሉ በመሆናቸው በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን ከታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል የሚካተቱ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ መዝሙራት የሥነ ጽሑፍ ሥራ ብቻ እንደሆኑ ተደርገው መታየት የለባቸውም። የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ራሱ ያስጻፋቸው ሕያው መልእክቶች ናቸው። እነዚህ መዝሙራት በዋነኝነት የሚናገሩት የመልእክቱ ባለቤት ስለሆነው ስለ ይሖዋ በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች በተመለከተ ጥልቅ ማስተዋል ይሰጣሉ። አጽናፈ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው እርሱ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል። (8:3-9፤ 90:1, 2፤ 100:3፤ 104:1-5, 24፤ 139:14) ይሖዋ የሚለው ስም በጥንታዊው ጽሑፍ ላይ 700 ጊዜ ያህል የሚገኝ በመሆኑ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ “ያህ” የሚለው አኅጽሮተ ስያሜ 43 ጊዜ ስለሚገኝ መለኮታዊው ስም በአጠቃላይ በእያንዳንዱ መዝሙር ውስጥ በአማካይ 5 ጊዜ ያህል ይገኛል። ከዚህም በላይ ይሖዋ 350 ጊዜ ያህል ኤሎሂም ወይም አምላክ ተብሎ ተጠርቷል። በብዙ መዝሙሮች ውስጥ የሚገኘው ሉዓላዊ ጌታ የሚለው አጠራር ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን የመግዛት ሥልጣን እንዳለው ይገልጻል።
24 ዘላለማዊ ከሆነው አምላክ ጋር ሲነጻጸር የሰው ልጅ በኃጢአት እንደተወለደና ቤዛ እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ሟች እንደሆነና ወደ “ዐፈር” ማለትም የሰው ልጆች መቃብር ወደሆነው ወደ ሲኦል እንደሚመለስ ተገልጿል። (6:4, 5፤ 49:7-20፤ 51:5, 7፤ 89:48፤ 90:1-5፤ 115:17፤ 146:4) የመዝሙር መጽሐፍ የአምላክን ሕግ የመከተልንና በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። (1:1, 2፤ 62:8፤ 65:5፤ 77:12፤ 115:11፤ 118:8፤ 119:97, 105, 165) ከትዕቢተኝነትና “ከተሰወረ በደል” እንድንርቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (19:12-14፤ 131:1) እንዲሁም በሐቀኝነት ላይ የተመሠረተ ጤናማ ወዳጅነትን ያበረታታል። (15:1-5፤ 26:5፤ 101:5) ትክክለኛ ምግባር የይሖዋን ሞገስ እንደሚያስገኝ ይጠቁማል። (34:13-15፤ 97:10) “ማዳን የእግዚአብሔር ነው” በማለት ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ለሚፈሩት ‘ነፍሳቸውን ከሞት እንደሚያድን’ ይገልጻል። (3:8፤ 33:19) ይህ ደግሞ ትንቢታዊ ወደሆነው ገጽታው ይወስደናል።
25 የመዝሙር መጽሐፍ “የዳዊት ልጅ” ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚጠቁሙና ክርስቶስ ይሖዋ የቀባው ንጉሥ ሆኖ በሚጫወተው ሚና ላይ በሚያተኩሩ ትንቢቶች የተሞላ ነው።a (ማቴ. 1:1) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም፣ መንፈስ ቅዱስ የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ በተመለከተ ለሐዋርያት መንፈሳዊ ማስተዋል መፈንጠቅ ጀመረ። ጴጥሮስ በዚያን ዕለት ባቀረበው የታወቀ ንግግሩ ላይ ከመዝሙር መጽሐፍ በተደጋጋሚ ጠቅሷል። የንግግሩ ጭብጥ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ’ የተባለው ግለሰብ ነበር። ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ታላቁ ዳዊት እንደሆነና ይሖዋ ነፍሱን በሔዲስ እንደማይተወው ከዚያ ይልቅ ከሞት እንደሚያስነሳው ለማሳየት ያቀረበው ማስረጃ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል በመዝሙር ጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነው። “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም”፤ ከዚያ ይልቅ መዝሙር 110:1 ላይ እንደተተነበየው ወደ ሰማይ የወጣው የእርሱ ጌታ ነው። የዳዊት ጌታ ማን ነው? ጴጥሮስ ወደ ንግግሩ ዋና ነጥብ በመምጣት ‘እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስ ነው’ በማለት አስረግጦ ተናግሯል።—ሥራ 2:14-36፤ መዝ. 16:8-11፤ 132:11
26 ጴጥሮስ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ተመሥርቶ የሰጠው ንግግር ጠቃሚ ነበር? በዚያኑ ዕለት 3,000 ያህል ሰዎች ተጠምቀው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት መሆናቸው በራሱ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆናል።—ሥራ 2:41
27 ከዚያም ብዙም ሳይቆይ፣ ደቀ መዛሙርቱ ባደረጉት ለየት ያለ ስብሰባ ላይ መዝሙር 2:1, 2ን በመጥቀስ ለይሖዋ ልመና አቀረቡ። ገዥዎች በአንድ ላይ በማሤር አምላክ ‘በቀባው በቅዱሱ ብላቴናው በኢየሱስ ላይ’ በመነሳታቸው ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ተናግረዋል። ዘገባው በመቀጠል “ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ይላል።—ሥራ 4:23-31
28 አሁን ደግሞ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተላከውን ደብዳቤ እንመልከት። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ፣ በሰማይ በዙፋን ላይ በመቀመጡ ከመላእክት በላይ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ታላቅነት የሚናገሩ ከመዝሙር መጽሐፍ የተወሰዱ በርካታ ጥቅሶች እናገኛለን። ጳውሎስ መዝሙር 22:22ንና ሌሎች ጥቅሶችን በመጠቀም ኢየሱስ የአብርሃም ዘርና “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” የሆኑ “ወንድሞች” እንዳሉት ተናግሯል። (ዕብ. 2:10-13, 16፤ 3:1) ከዚያም ከዕብራውያን 6:20 አንስቶ እስከ ምዕራፍ 7 ድረስ ኢየሱስ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት” በመሆን ያገኘውን ተጨማሪ ሥልጣን ሰፋ አድርጎ ገልጿል። ይህም በመዝሙር 110:4 ላይ የሚገኘውን አምላክ በመሐላ ያጸናውን ቃል የሚያመለክት ሲሆን ጳውሎስ የኢየሱስ የክህነት አገልግሎት ከአሮን የሚበልጥ መሆኑን ለማረጋገጥ ይህን ጥቅስ በተደጋጋሚ ተጠቅሞበታል። ጳውሎስ እንዳብራራው ይሖዋ በገባው መሐላ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳይሆን በሰማይ “ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ይህም የክህነት አገልግሎቱ የሚያስገኘው ጥቅም ዘላለማዊ ይሆናል ማለት ነው።—ዕብ. 7:3, 15-17, 23-28
29 በተጨማሪም በዕብራውያን 10:5-10 ላይ ኢየሱስ፣ የመሥዋዕትነት ሕይወት እንዲኖር ለሚጠይቅበት ለአባቱ ፈቃድ ስለነበረው አድናቆትና ይህንን ፈቃድ ለመፈጸም ስለወሰደው ቆራጥ አቋም ተገልጿል። ይህ ጥቅስ መዝሙር 40:6-8 ላይ በሚገኙት ዳዊት በተናገራቸው ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው። ሁላችንም የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንድንችል ይህንን ምሳሌ የሚሆን ለአምላክ የማደር መንፈስ መመርመራችንና ለመኮረጅ ጥረት ማድረጋችን በጣም ይጠቅመናል።—በተጨማሪም መዝሙር 116:14-19ን ተመልከት።
30 በመከራ እንጨት ላይ በደረሰበት አስከፊ መከራ የተጠናቀቀው የኢየሱስ የሕይወት ጎዳና በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በሚያስደንቅ መንገድ በዝርዝር ተተንብዮአል። ይህም ሆምጣጤ እንዲጠጣ የሚሰጠው መሆኑን፣ በቀሚሱ ላይ ዕጣ እንደሚጣጣሉ፣ እጆቹና እግሮቹ እንደሚቸነከሩ፣ መዘባበቻ እንደሚሆንና በከባድ ጭንቀት ተውጦ “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” በማለት በሲቃ የሚጮኽ መሆኑን ይጨምራል። (ማቴ. 27:34, 35, 43, 46፤ መዝ. 22:1, 7, 8, 14-18፤ 69:20, 21) ዮሐንስ 19:23-30 እንደሚጠቁመው ኢየሱስ እነዚህ ጥቅሶች በሙሉ አንድም ነገር ሳይቀር መፈጸም እንዳለባቸው ያውቅ ስለነበር በዚያ ሰዓት እንኳ ከመዝሙር መጽሐፍ ብዙ ማጽናኛና መመሪያ አግኝቶ መሆን አለበት። ኢየሱስ የመዝሙር መጽሐፍ ስለ ትንሣኤውና ከዚያ በኋላ ስለሚያገኘው ክብር ጭምር እንደሚናገር ያውቅ ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆነው ‘መዝሙር ሲዘምሩ’ እነዚህ ነገሮች በአእምሮው እንደሚመላለሱ ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 26:30
31 በመሆኑም የመዝሙር መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ባለችው ጽዮን ንጉሥና ካህን ሆኖ የተሾመው “የዳዊት ልጅ” እና የመንግሥቱ ዘር፣ ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል። በዚህ የይሖዋ ቅቡዕ ላይ እንደተፈጸሙ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጹትን ሁሉንም የመዝሙር ጥቅሶች ለመዘርዘር ቦታ ባይበቃም ጥቂት ተጨማሪ ምሳሌዎችን እንመልከት:- መዝ. 78:2—ማቴ. 13:31-35፤ መዝ. 69:4—ዮሐ. 15:25፤ መዝ. 118:22, 23—ማር. 12:10, 11 እና ሥራ 4:11፤ መዝ. 34:20—ዮሐ. 19:33, 36፤ መዝ. 45:6, 7—ዕብ. 1:8, 9። እንዲሁም ለይሖዋ ስም ክብር በሚያመጣ ሥራ እንዲካፈሉ ከአሕዛብ ሁሉ ተሰባስበው የአምላክን ሞገስ ያገኙትን የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ጉባኤ በተመለከተ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በግለሰብ ሳይሆን በቡድን ደረጃ ትንቢት ተነግሯል።—መዝ. 117:1—ሮሜ 15:11፤ መዝ. 68:18—ኤፌ. 4:8-11፤ መዝ. 95:7-11—ዕብ. 3:7, 8፤ 4:7
32 ስለ መዝሙር መጽሐፍ ማጥናታችን ይሖዋ አምላክ፣ ተስፋ በተሰጠበት ዘርና በመንግሥቱ ወራሽ አማካኝነት ሉዓላዊነቱን ለማስከበር እንዲሁም ስሙን ለማስቀደስ የሚጠቀምበትን የንግሥና ሥልጣኑን በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ በእጅጉ ያሳድግልናል። ‘በይሖዋ ግርማ ውበትና ክብር’ ደስ ከሚላቸውና “የዳዊት የምስጋና መዝሙር” በሆነው በመዝሙር 145 ላይ “ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤ በዚህም ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ። መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል” ከተባለላቸው ታማኝ ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃን። (መዝ. 145:5, 11-13) በትንቢታዊው መዝሙር ላይ እንደተገለጸው በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ግርማ አሁንም እንኳ በመላው ብሔር ለሚገኙ የሰው ልጆች በመነገር ላይ ነው። ለዚህ መንግሥትና ለንጉሡ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል! “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ያመስግን። ሃሌ ሉያ” የሚሉት የመዝሙር መጽሐፍ የመደምደሚያ ቃላት ምንኛ ተስማሚ ናቸው!—150:6
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 710-711